ኢትዮጵያዊነት፣ ዜግነት፣ ማንነት – በየማነ ናጊሽና በፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

የሪፖርተሩ ጋዜጠኛ የማነ ናጊሽ በራሱ የፌስቡክ ገጽ ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን›› የሚል ጽሑፍ በትግርኛ ቋንቋ ያተመው ልክ የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ ነበር፡፡ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የማነ ጽሑፉን ወደአማርኛ ተርጉሞ እዚያው ፌስቡክ ገጹ ላይ ያተመው ቢሆንም፤ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ለየማነ የከረረ ምላሽ የሰጡት ገና በትግርኛ ካተመው ከቀናት በኋላ ነበር፡፡

መስፍን ለየማነ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ሙሉ ጽሑፉን አስተርመው ስለማንበባቸው ማወቅ ባልችልም፤ የቆየ ፀብ ወይም አለመግባባት ያላቸው እንደሆነ ለየማነ ጠይቄው ‹‹የለንም›› ብሎኛል፡፡ በአንጻሩ አንዳንድ ሰዎች መስፍንና የማነ በስብሰባዎች ላይ ተገናኝተው የተወራረፉባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ ጠቁመውኛል፡፡

የሁለቱንም ጽሑፎች ሙሉ ቃል ከዚህ በታች አትመናቸዋል፡፡

የማነ ናጊሽ በራሱ የፌስቡክ ገጽ ላይ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን›› የሚል ጽሑፍ በትግርኛ ቋንቋ ጥር 15 ያተመው ጽሑፍ የአማርኛ ትርጉም እንሚከተለው ይነበባል፡-

እንዲህ ብሎ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም፣

እንዲህ ብሎ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም፣ ሊኖርም አይችልም፤ኢትዮጵዊነት ዜግነት ነው፡፡ አለ ከተባለም የውሸት ነው፤ሽፋን ብቻ ነው፡፡‹ከመይ ይብል ለባም›[የትግርኛ አባባል ሲሆን ‹ልባም ሁሌም እንዴት ብሎ ይጠይቃል› እንደ ማለት ነው]፡፡

ልቀጥል፡፡ ሲጀምር እኛው ራሳችን ነን፡፡ ምንጫችንም ቤተሰብ ነው፤ መሰረታዊ የሰው ልጅ ተቋም፡፡ ከዝያም ቀጥሎ ንጹኅ ትግራዋይነት** ማንነት አለን፡፡እሱም ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ በስምምነትና በውል የታሰረ አይደለም፡፡ አብሮን የተወለደና በውስጣችን ተዋህዶ የሚኖር፤ ያለእእሱ ሌላ መገለጫ የለንም፡፡ ለዘመናት በደም፣ በቋንቋ ፣ በስነ-ልቦና፣ በባህልና በታሪክ የተገነባ እንጂ ትናንት የተፈበረከ አይደለም፡፡ቀድሞም ይመጣል፡፡

በአንጻሩ፣ ኢትዮጵያዊነት እንደእኛው አይነት የተለያዩ ማንነቶች ያሏቸው ወገኖች ወደውና ተስማምተው የሚያስሩት ቃልኪዳን ነው፡፡ ቃልኪዳን ደግሞ ውል ነው፤ ሲፈለግ ይታሰራል ሳይፈልግ ሲቀር ይፈርሳል፡፡ ሌላም ውል ሊታሰር ይችላል፡፡ እየሰፋም ከሄደ በአገሮች መካከል ህብረት ይፈጠራል፤ አንድ አህጉር፣ አንድ አለም እያለ ይቀጥላል፡፡

ይኼው ኅብረት ግን እኛ ጋር ተጣብቆ የሚኖርበት ግዴታ የለም፡፡አዲስ ሀገር፣ አዲስ ዜግነት ይፈጠራል፤ አዲስ ማንነት ግን አይፈጠርም፡፡ በአሁኑ ግዜ በኤርትራ የሚገኙት ተጋሩ(ትግራውያን) በቃ ተጋሩ ናቸው፡፡ አትዮጵያውያን ነበሩ፤ ዛሬ ግን አይደሉም፤ አንድ ውል አፍርሰው ሌላ ውል መስርተው ይኖራሉ፡፡ በአገራችን ያሉት ዓፋሮችም ሆኑ ሶማልያውያንም አንዲሁ፤አሁን የገቡት ውል ካልመሰላቸው አፍርሰው አዲስ ውል ሊያስሩ ይችላሉ፡፡ ሌላ ሀገር፣ ሌላ ዜግነት እንጂ ሌላ ማንነት ግን አይኖራቸውም፡፡ ዜግነታቸው ከአገር አገር የሚቀያይሩ ሰዎችም ተመሳሳይ ነው፤ማንነታቸው ማንም አይነካውም፡፡

አንዳንድ ግብዞች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ‹አንድነት› በሚል ባእድ የማንነት ድሪቶ ጠቅልለው ሊያለብሱን ይፈልጋሉ፡፡እርቃናችን አይተውን አይደለም፤ የማንነት ችግርም የለብን፡፡ የራሳችን አውልቀን፤ በምትኩ የእነሱ ማንነት ለብሰን፣ እኛነታችንን ጠልተን እነሱ እንድንመስል ስለሚፈልጉ ብቻ ነው፡፡

በየቤታችን ተከባብረን በሙሉ ፍላጎት የሚፈጠር አንድነት ፈጽሞ የሚጠላ አይደለም፡፡ አቅምም ይፈጥራል፡፡ የራስን ማንነት ሸጦ የማይሆኑትን መስሎ የሚመጣው አንድነት ግን ገደል ይግባ፡፡ ‹እናንተን መምሰል አንፈልግም› የምንላቸቸውን፣ ዘረኞች የሚል ቅጽል ይለጥፍቡናል፤ እውነተኛ ዘረኞች ግን እነሱ ራሰቸው ናቸው፡፡ ‹አኛን ካልመሰላችሁ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም› በሚል ፈሊጥ አንደኛና ሁለተኛ የዜግነት ደረጃ አውጥተው የሚያድሉ፡፡ወጊድ እንበላቸዋ!!

ለሚወረወረላቸው ትርፍራፊ ጥቅማጥቅም ሲሉ፤ይህንን ድሪቶ ባህል ወደው የሚለብሱ አንዳንድ አነፍናፊ ግን አይጠፉም፡፡ በታሪክም ያልታየ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ትግራዋይነታችን ለማጥፋት ላይ ታች ሲዋትቱ የኖሩ ፊትለፊታቸው እነማንን አሰልፈው ሆነና! ዛሬም ቢሆን ይህንን ድሪቶ ለመልበስ የሚዳዳቸው ሰዎች ወደው አይምሰላችሁ፤ በማንነት ቀውስ የተጠቁ ናቸው፡፡ አልያም ቅሪቶች ይሆናሉ፡፡ እግዚሄር ከዚሁ ደዌ ይማራቸው ወደ ነብሳቸውም ይመለሱ ዘንድ የእኛ ፀሎት አይለያቸው እላለሁ፡፡ ይሄው በሽታ ግን እንደ ተስቦ ተዛማች ነው፤ እኛንም እንዳንለከፍ በየግዜው ክትባት መውሰደም፤ መስጠትም ያስፈልገናል፡፡
(ዘግየት ብሎ የማነ ጽሑፉን በአማርኛ ተርጉሞ እዚያው ፌስቡክ ገጹ ላይ አትሞታል)

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ለዚህ ጽሑፍ በቁጣ ስድብ አከል ምላሽ የሰጡት ገና የማነ ጽሑፉን በትግርኛ ባተመ ከቀናት በኋላ ነበር፡፡ መስፍን ለየማነ ምላሽ ሲሰጡ ሙሉ ጽሑፉን አስተርመው ስለማንበባቸው ማወቅ ባልችልም፤ የግል ፀብ ወይም አለመግባባት ያላቸው እንደሆነ ለየማነ ጠይቄው የለንም ብሎኛል፡፡

መስፍን ከሁለት ሳምንት በፊት በጥር 21/2006 ያተሙት (በስህተት ‹‹ኅዳር 21/2006›› የሚል ቀን ሰጥተውታል) በፌስቡክ ገጻቸው ላያ ያተሙት ምላሽ እንደሚከተለው ነበር፡-

ማንነት መስፍን
ወልደ ማርያም

በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ጽሑፌ ውስጥ ‹‹ማንነት ምንድን ነው፤ በሚል ንዑስ ርእስ ስር ከገጽ 98 ጀምሮ በተቻለኝ መጠን አፈታትቻለሁ፤ የሪፖርተር ጋዜጠኛ ይህንን ለማንበብ ጊዜ አላገኘም፤ ወይም የተገለጠለት ዱሽ ቅንጫቢ በቅቶት ይሆናል፤ የምጠቅሰውም ለሱ ሳይሆን ለሌሎች ነው፡፡ በቅርቡ በፌስቡክ ላይ አንድ አውቀቱ ይሁን ጤንነቱ፣ ወይም ኪሱ የተቃወሰበት ሰው በትግርኛ ስለማንነት ጽፎ ነበር፤ ከዚህ በፊትም ጽፎ አስተሳሰቡ ሁሌም የተወላገደ በመሆኑ አልፌው ነበር፤ አሁን ደግሞ ሲጽፍና በአንዳንድ የሱ ቢጤዎች አበጀህ! አበጀህ! ሲባል ሳይ አደገኛነቱን ተገነዘብሁ፤ አንዱን ጎባጣ ሀሳብ ቶሎ ካላስተካከሉት ብዙ ጎባጦችን ያፈራል፤ የተጣራና ቀና የሆነ ሀሳብን ለመግለጽ በጣም ያስቸግራል፤ ማሰብ መጨነቅን፣ ማበጠርን፣ ማጣራትን ይጠይቃል፤ አፍ እንዳመጣ መልቀቅ ቀላል ነው፤ በተለይ የሚዳኝ ከሌለ! በመጀመሪያ ሀሳብን ለመግለጽ የተመረጠው ቋንቋ ጠበብ ያለና የተፈለጉ አድናቂዎች ዘንድ ለመድረስ ብቻ ከተፈለገ ሀሳቡም እንደቋንቋው ለተወሰኑ ሰዎች የተመጠነ ይሆናል፤ በዚህ ዓይነት የቀረበው ቅንጣቢ ሀሳብ በሌላ ቋንቋ ሊተረጎም አይቻልም፤ ደንቆሮነትን ማጋለጥ ይሆናል፤ ለምሳሌ በትግርኛ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› የሚለውን ‹‹ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤›› በማለት፣ በእንግሊዝኛ ደግሞ ‹‹There is no identity called Ethiopian.›› ተብሎ ሊተረጎም ነው፤ እንግዲህ ይህ አወቀች፤ አወቀች ሲሏት መጽሐፉን አጠበች እንደተባለችው ሴትዮ፣ ወይም ደግሞ አላዋቂ ሳሚ እንትን ይለቀልቃል! የሚባል ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ብሎ በትግርኛ የጻፈው ሰው የአለማወቁ አዘቅት ዓለምን በሙሉ የሚያናጋ መሆኑን አልተገነዘበም፤ (አሜሪካን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣልያን … የሚባል ማንነት የለም ሊለን ነው፤) የመንደር ማንነትን በሁለት እጆቹ ይዞ፣ አእምሮውን በመንደር ማንነት ጨቅጭቆ በየፓስፖርቱ ላይ የማንነት መግለጫ ተብሎ የተሰየመውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀውን ማንነት ካደው፡፡ በፍጹም ያልገባውን የፈረንሳዩን ፈላስፋ፣ የሩሶን ሀሳብ አበለሻሽቶ ከቆሻሻ መጣያ ውስጥ ያገኘው ቡትቶ ሊያደርገው ይከጅላል! ከጥራዝ-ነጠቅም አጉል ጥራዝ-ነጠቅ! ትግራይን የመገንጠል ዓላማ ያለው ሰው በእውነትና በግልጽ ዓላማውን ቢያራምድ በበኩሌ አልደግፈውም እንጂ አልቃወምም፤ መብቱ ነው፤ ነገር ግን በሰንካላ አስተሳሰብና በተንኮል ወጣቶችን ለመመረዝ የሚፈልገውን ሰው አጥብቄ እቃወማለሁ፤ ትግራይን እንደኤርትራ ካስገነጠለ በኋላ እንደኤርትራ ለትግራይም የኢትዮጵያዊነት ማንነትንን ማገድ ይቻላል፤ ከዚያ በፊት ግን ተንኮል ይቅር፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የሚደረገው ሙከራ አዲስ ኤደለም፤ ኢጣልያኖች በሰፊው ዘርተውት የሄዱት ጉዳይ ስለሆነ የአባቶቻቸውን ውርስ የሚከተሉ ዛሬም ይኖራሉ፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ብዙ ገንዘብና ሌላም የሚከፍሉ ብዙ የተለያዩ ድርጅቶች መኖራቸው የታወቀ ነው፤ ዱሮ የኢጣልያ ወኪሎች ተጠቅመውበታል፤ ዛሬ ደግሞ ሌሎችም ተጨምረው ያንኑ ተልእኮ የሚያራምዱ አሉ፤ በየዋህነት እንደበፊቱ እንዳናስተናግዳቸው እንጠንቀቅ!

**********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories