‹‹የዓረና ፓርቲ አመራሮች ራሳቸው ድብደባ ፈጽመዋል›› – የአዲግራት ባለስልጣን

የአረና ፓርቲ አመራሮች በአዲግራት ከተማ ድብደባና ጥቃት ደረሰብን በማለት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በፌስቡክና በሌሎች ሚዲያዎች ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

‹‹ጉዳቱ የደረሠብን ህወሓት ባሠማራቸው ከአዲግራት ውጭ የመጡ ወጣቶች ነው››፣ ‹‹ለስብሰባው ጥበቃ እንደማያደርግልንም አስተዳደሩ ነግሮናል››፣ ‹‹በዚህም የተነሳ እሁድ ጥር 18/2006 በአዲግራት ከተማ ልናደርገው የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ ለመሰረዝ ተገደናል>> የሚሉ ክሶችንም አሰምተዋል፡፡

በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው እና ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩትን የዞኑን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ተፈሪን በስልክ አነጋግሬያቸው የሚከተለውን ማብራሪያ ሠጥተውኛል።

አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት አረና ፓርቲን በተመለከተ ያለው ወቅታዊ ጉዳይ በአዲግራት ከተማ ብቻ ሳይሆን የአጎራባች የእዳጋ ሀሙስና ፋፂ ከተሞችንም የሚመለከት ነው። የፓርቲው አመራሮች አርብ ጥር 16 ቀን ጀምረው በከተማይቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች በእግራቸው በመዘዋወር ቅስቀሳ ያካሂዱ ነበር። ቅስቀሳንውም በትንኮሳ የተሞላና ግለሠቦችን በመዝለፍ ላይ የተመሠረተ ነበር ይላሉ።

አመራሮች ለቅስቀሳ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በእግራቸው በሚዞሩበት ወቅት ህፃናትና ወጣቶች ይከተሏቸው ነበር። ከሚከተሏቸው ውስጥም አንዳንዶቹ <<እኛ የምንመርጠው ኢህአዴግን ነው፤ እናንተን አንፈልግም>> በሚሏቸው ወቅት ግርግር መፈጠሩን ሃላፊው ገልፀዋል። ሰፋ ያለ ችግርና ግርግር የተፈጠረው ጥር 16 ቀን ቢሆንም በማግስቱ ቅዳሜም የአረና አመራሮች ተመሳሳይ ችግር መፍጠራቸውን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ገልፀውልኛል፡፡

የአረና አመራሮች በወቅቱ በህወሓትም ሆነ እነሱ እንደሚሉት በ‹‹›ቅጥረኞች› ምንም ጥቃት ያልደረሰባቸው ሲሆን በአንፃሩ እነሱ ግን ህፃናትን ጭምር ደብድበዋል ነው ያሉት። <<ለምን ልጆቻችንን ደበደባቹሁ?>> በማለት ወላጆች ሲጠይቋቸውም ከነሱ ጋር ግጭት አድርገዋል የፓርቲው አመራሮች፡፡ በዚህ ወቅት ጉዳቱን ያደረሱት የፓርቲው አመራሮችና ተበድለናል የሚሉ የአካባቢው ነዋሪወች ወደ አስተዳደሩ መጥተዋል ብለዋል አቶ ደሳለኝ።

የአረና አመራር አባላት በተጨባጭ ሠው መደብደባቸውን ብናውቅምና ወላጆችም በህግ ይጠየቁልን እያሉን ቢሆንም ግለሠቦቹ ሠበብ ፍለጋ ላይ መጠመዳቸውን ስለተረዳን ምንም የተወሠደባቸው እርምጃ አልነበረም ሲሉ ሁኔታውን ገልፀውታል።

ለተበዳዮች ሁኔታውን በማስረዳት ቢቻል ነገሩን በሆደ ሰፊነት ተመልክተው እንዲያልፉት ካልሆነም ፖሊስ ጣቢያ ሄደው እንዲከሱ ነግረን አሰናብተናቸዋል ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ <<እኛን ተው ብላችሁ እነሱን ከህግ እንዲሸሹ አደረጋችሁ>> ተብለን በህብረተሰቡ ተወቅሰናል ነው የሚሉት፡፡

ፓርቲው ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት አዳራሽ እንደተፈቀደለትና ለህዝባዊ ስብሰባው በቂ ጥበቃ እንደተመደበ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በእለቱ የፓርቲው አመራሮች ወደ አዳራሹ አልመጡም ነው ያሉት፡፡ ይህንንም ያደረጉት አላማቸውን ደግፎ ለስብሰባ የሚወጣላቸው ሰው እንደማይኖር ስላወቁ መሆኑን ሃላፊው ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ሃላፊው እንዳረጋገጡልኝ በፓርቲው ሃላፊዎች ላይ ምንም አይነት እርምጃ አልተወሰደባቸውም፡፡ ጉዳዩ በህግ የሚያስጠይቃቸው ሆኖ ሳለ የአካባቢው አስተዳደር ለእነሱ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ቀዳዳ ላለመክፈትና ሰበብ ላለመፍጠር ሲል በህግ ቁጥጥር ስር ከማዋል እንኳን መቆጠቡን ተናግረዋል፡፡ <<ተደብድበን፤ ሆስፒታል ገብተናል>> የሚለውም ክስ ሀሰት እንደሆነና ይህንንም ከየትኛውም የጤና ተቋም ጠይቆ ማጣራት እንደሚቻል ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የአረና አመራሮች ጥር 18 ቀን ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ የመጠየቂያ ደብዳቤ ቢያስገቡም እዳጋ ሐሙስንና ፋፂን ጨምሮ በከተማ እየዞሩ ቅስቀሳ ለማድረግ የሚያስችላቸው ምንም አይነት ማስታወቂያ ወይም ጥያቄ አለማስገባታቸውን አቶ ደሳለኝ ተፈራ ተናግረዋል፡፡

*******

Kebede Kassa

more recommended stories