የአፄ ምኒሊክ ውዝግብ እና የፌስቡክ ጎራዎች

(አሉላ ሰለሙን)

ሠሞኑን በአጼ ምንሊክ የሙት ዓመት መከበር እና እሱን ተከትሎ አንድ አርቲስት በሠጠው ያልተገባ አስተያየት የተነሳ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ እና ንትርኮች ሲካረሩ ተስተውሏል። ይህንን በመንተራስ ኢትዮጵያዊያን የኦሮሞ ክልል ተወላጆች በተለይ በአርቲስቱ የ”ቅዱስ ጦርነት” አስተያየት የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞቻችን በአጼ ምንሊክ እና የበደል አሞካሻቸው አርቲስት ላይ በተከፈተው የአጸፋ መልስ ተከፍተዋል። እነዚህ በዚህ ጸረ ምንሊክ እና የበደል አቀንቃኛቸው በተካኼደ ዘመቻ የተከፉትን በሁለት ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል። እነሱም 1) በተነሳው ተጨባጭ ኹነትን የማጋለጥ ኺደት የተከፉ “አትንኩብን” ባዮች እና 2) ከስጋት በመነጨ የራሳቸው ስሌት የወሰዱ ድንጉጦች ናቸው።

 “አትንኩብን” ባዮች

እነዚህ በተጨባጭ የዘውድ አምላኪነት የተጠናወታቸው ኃይሎች፣ ሠማያዊ ፓርቲ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፣ በአንድ በኩል የምንሊክ ጉድ ለምን ተነሳ የሚል ኩርፍያ ያደረባቸው ሲኾኑ፤ ጉዳዩም አጼ ምንሊክ ከፈጸሟቸው ውጫዊ እና ውስጣዊ ስሕተቶች በቀጥታ የሚገናኙ ናቸው። በሌላ በኩል አሁን ካለው የሀገራችን ነባራዊ የፖለቲካ ኹኔታ ጋር ተያይዞ፣ የምንሊክን ስሕተት መደበቁ አኹን ያለውን ገዢ ፓርቲ ብቻ በብሄራዊ ጥቅሞች ዙሪያ ተጠያቄ የማድረግ ስሌት በመያዙ ነው። በዚህ ጎራ የተሰለፉ በብሔር የተለያዩ ናቸው። ከሰሜኑም ደቡብም አሉበት። ለምሳሌ የትግራይ ተወላጅ ኾነው አኹን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት የሚቃወሙ አንዳንድ ግለሰቦች በዚህ ጎራ ተሰልፈዋል። ለዚህም ቀደም ብሎ የተገለጸው የብሄራዊ ጥቅም እና ገዢውን መቃወም እንደ ግብ የመቆጠር አካሄድን መሠረት ያደረገ ነው። ይህ አካሄድ በተለይ አቶ መለስ ዜናዊን ብሄራዊ ጥቅማችን አሳልፎ እንደሰጠ እና ለኤርትራ መገንጠል ኹነኛ ሚና እንደተጫወተ መሪ አድርጎ ከመውሰድ ይመነጫል። በዚህም ምክንያት፣ አንድም አጼ ምንልክን ማጋለጥ የህወሓት አጀንዳ ተደርጎ ስለሚወሰድ፣ “አጼ ምንሊክን ከነኩ ህወሓትን እንደ መደገፍ ተደርጎ ይቆጠርብናል” ከሚል ስጋት እና ህወሓትን ለማበሳጨት ምንሊክን መከላከል እንደ ጊዚያዊ ስትራቴጂ፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ አጼ ምንሊክ በብሄራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ተወቃሽ ከሆኑ እና ከተጋለጡ፣ መለስ ዜናዊን ባህር በር ያሳጣን፣ ኤርትራን ያስገነጠለ በሚል ለመክሰስ እና ለማጠልሸት የሚጠቀሙበት ሴራ ዋጋ ቢስ ያደርግባቸዋል። ስለዚህ በደምሳሳው ለጊዚያዊ ፖለቲካዊ ትርፍ ሲባል ምንሊክን ባይነኩ ይመርጣሉ። በተለይ የዓረና ፓርቲ ካድሬዎች ለአንድነት ፓርቲ ያቀረቡት የውህደት ጥያቄ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ከምንሊክ አሞካሺዎች ጎን መቆምን እንደ እጅ መንሺያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ግን በአጠቃላይ፣ በቀኝ ዘመም ጎራ የተሠለፉ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች በውል ለታወቁ እና ላልታወቁ ምክንያቶች በዚህ “ምንሊክን አትንኩብን” በሚል ጅምላዊ አስተሳሰብ (bandwagon) ተሳፍረዋል።

ስጋት

ይህ ሁለተኛው ጎራ ደግሞ የአጼ ምንሊክ ስሕተቶች በአንዳንድ ቅጥ ባጡ አስተያየቶች እና ጉዳዩ ከህዝብ ጋር በማያያዝ ስሕተቱን ለማካስ የሚወሰድ የበቀል እርምጃ ለኛም ይተርፋል በሚል ስጋት የተሰባሰበ ነው። አጼ ምንሊክ የፈጸሟቸው በደሎች የብሔር ባለቤትነት ታርጋ ተለጥፎባቸው ጉዳዩ ወደ ብሔር ግጭት እንዳያመራ የሚሠጉ አሉ። በዚህ ጎራ ፖለቲካውም ታሪኩም በቅጡ ያልገባቸው፣ በጉዳዩ ጠለቅ ያለ ዕውቀት የሌላቸው አብዛኛዎችም ይጨነቃሉ። ነገር ግን ፖለቲካዊም ታሪካዊም ሂደቱን ተረድተውም የሚፈሩ አሉ። እነዚህ የኋላዎቹ፣ ከዚህ አሁን ከተፈጠረው የሙት አመት ዝክር እና የ”ቅዱስ ጦርነት” ጉዳይ የአጼ ምንሊክ እውነተኛ ታሪክ መጋለጥ ሲጀምር እና በፊት ነገሮች ሲብላሉ ጀምሮ፣ የብሔር ጭቆና እና የምንሊክ በደሎች እመኑ በሚል በተደጋጋሚ በቀረበላቸው ሐሳብ ተደናግጠው ጉዳዩ ወደ ብሔር ግጭት ሊያመራ ይችላል በሚል፣ አንዳንድ ትንታግ የማህበራዊ ድረ ገጽ ጸሀፊዎቻቸው ሳይቅር ወላፈኑን መቋቋም ተስኗቸው ኮብልለዋል። በፌስቡካዊ አነጋገር አካውንታቸው ዲአክቲቨት አድርገዋል። ገሚሶቹ ደግሞ ዝምታን መርጠዋል። አንዳንዶቹ፣ በተሳትፎ ቢቆዩም እንኳ፣ በማህበራዊ ደረ ገጽ “በቃ!” በሚል መፈክር አመጽ አነሳስተው መንግስት ይቀይርልናል ብለው የጠበቁት ሳይኾን ቀርቶ በዚህ ጉዳይ መጠመዱ በእንብርክክ ሄደብን ወይም አስኬደን ብለው ሲጽፉ ተመልክተናል።

ከዚህ አጼ ምንሊክ የፈጸሙትን በደል ከህዝብ ማቆራኘት የወለደውን ፍርሃት እና በተዛባ አስተሳሰብ ምክንያት ይህ ጎራ የተለያዩ ብሔሮች አላቀፈም። አጼ ምንሊክን የአማራ ወኪል አድርጎ በማስቀመጥ፣ እሳቸው የፈጸሙት በደል ሒሳብ ለማወራረድ የሚደረግ ማናቸውም፣ እውነተኛ ታሪኩንም የመፃፍ ጨምሮ፣ ለኛም ይተርፋል የሚል የስጋት አስተሳሰብ ያነገበ ነው። እዚህ ላይ ግን፣ አጼ ምንሊክን ማነው የአማራ ወኪልም አማራም ያደረጋቸው? ይህንን ለማጥቃትም እና ለመከላከልም የሚደረገው ትንቅንቅ ነገሩን አባብሶታል። ይህ ግን ፈጽሞ የተሳሳተ አረዳድ ነው። ሰውዬው አማራም አይደሉም አማራንም አይወክሉም። እንድያ ቢሆን ኖሮ ቁጥር አንድ ላይ የተገለጹ “ምንሊክ አትንኩብን” ባዮች የተለያዩ ብሔር ተወላጆች አይኾኑም ነበር። የምንሊክ ስም በክፉ ሲነሳ የሚከፋቸው ጉራጌ፣ ትግራዋይ ጓደኞች አሉኝ።

የአጼ ምንሊክ አማራነት አማርኛ ቋንቋን ባስቀጠለ፣ በተናገረ እና ባስፋፋ ከኾነ፣ አጼ ዮውሃንስም አቶ መለስም አማራ ናቸው ማለት ነው። ከዚህ በዘለለ አጼ ምንሊክን አማራ እና የአማራ ወኪል የማድረግ አካሄደ ስሕተት ነው። በነገራችን ላይ፣ እንደ አቶ መለስ ዜናዊ መንግስት አማርኛ ያስፋፋ ስርዓት በኢትዮጵያ አልታየም። ይኽ የአሃዝ ጉዳይ ነው። ነገር ግን አቶ መለስ አማርኛን ያስቀጠሉት እና ያስፋፉት ጡት በመቁረጥ፣ እጅ በመበጠስ አይደለም። አስገድዶ በመጫን ሳይኾን፣ በፍላጎት እንዲስፋፋ አድርገዋል። ከሀገሪቱ አጠቃላይ የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት፣ ትምህርትና የሥራ ዕድል ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ አማርኛውም የሚነገርበት ሽፋኑ ሰፍቷል።

ከታሪክ በስተጀርባ ያለ የፖለቲካ “ትብብር”?

መግቢያ ላይ ከተገለጸው ሐሳብ ጋር ተያይዞ፣ በፖለቲካ አቋም የማይመሳሰሉ በፊት በሁለት ጫፍ የነበሩ አሁን የፖለቲካ ዝሙት በሚመስል ግንባር ፈጠሩ በሚል የተከሰሱ የፖለቲካ ጎራዎችም አሉ። እነዚህም፡ ጃዋር የሚመራው ኢትዮጵያዊያን የኦሮሞ ክልል ተወላጆች በከፈቱት ዘመቻ በቀጥታ የሚሳተፉ እና ተባብራችኋል ተብለው የተከሰሱ ይገኙበታል። በፊት ሲቃወሙት ከነበሩት የጃዋር ቡድን ጋር አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ እንዴት ሊተባበሩ ቻሉ? ይህ የፖለቲካ ዝሙትነት አይደለም ወይ? ነው ክሱ። በፖለቲካ አቋም ከጃዋርም ኾነ ከኦነግ የተስማማ የለም። በአጼ ምንሊክ እና አሞካሺዎቻቸው የተያዘው አቋምም፣ ከእነ ጃዋር ዘመቻ በፊት የነበረ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው እላይ ቁጥር አንድ ላይ ከተገለጹ “አትንኩብን” ባዮች መግባባት ያልነበረው። አኹን ላይ ደርሶ በዚች ነጥብ ከጃዋር እና ቡድኑ የተወዳጀ የለም። በዚህ ረገድ ጊዚያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ተብሎ አዲስ የተፈጠረ ግንባርም የለም። ለምን ሐሳቡ ተመሳሰለ ከኾነ፣ ሐሳቡ አስቀድሞም ነበር፤ ለዛውም ከአጼ ምንሊክ መቶኛ ሙት አመት መከበር እና “ቅዱስ ጦርነት” በፊት። ጃዋር በፊት በሜንጫው ተውግዟል። አሁን ላይ ደርሶ ይኼ ውግዘት አይነሳም፤ ይቅርታ እስካልጠየቀ ድረስ። ጃዋር ከኢሳት እና የአንድነት ቀኝ ዘመም ፖለቲካ ፍቅር ከመመስረቱ በፊት ባለው ጊዜም ይህ የምንሊክ እውነተኛ ታሪክ፣ የፈፀሙት በደል እና ሀገራዊ ክህደት የማጋለጥ ሂደት ነበረ። አኹንም ይቀጥላል። ይህ ሂደት አሁን እነ ጃዋር ስለተቀላቀሉትም አይቆምም። ለምን ተቀላቀሉ ተብሎ የባለቤትነት መብት ጥየቃም የለም። እንዲሁም የአቋም ለውጥም አይኖርም። እነ ጃዋር ተገቢ እና ተቀባይነት የሚያገኙበት መስሎ ሲሰማቸው ኢሳትን እና የአንድነት ኃይሎች ተሰናብተው መጥተዋል። እንኳን ወደ እውነታው በሰላም መጣችሁ ሊባሉ ብቻ ነው የሚገባው፤ የፖለቲካ አቋም ልዩነቱ እንደተጠበቀ ኾኖ።

************

*The author Alula Solomon is a lecturer in Mekelle University, he is a guest writer on this blog and can be reached at [email protected]

Alula Solomon

more recommended stories