Leaked| ዕንቁ መፅሔት ቆርጦ ያስቀረው የቴዲ አፍሮ አስተያየት

(Daniel Berhane)

ዕንቁ የተሰኘው መፅሔት ለአፄ ምኒሊክ ሰፊ ሽፋን የሰጠበትን ያለፈውን ወር ዕትም ሽፋን ገጽ ላይ ‹‹ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የገቡበት ጦርነት ለእኔ ቅዱስ ጦርነት ነው›› የሚል የቴዲ አፍሮ(ቴድሮስ ካሳሁን) አስተያየት በማስፈር ለኢሜይል ደንበኞቹ ማሰራጨቱ – ዘግይቶ ግን የተለየ ጥቅስ የያዘ ሽፋን ገፅ ማሠራጨቱ ይታወሳል፡፡

የመጽሔቱ አዘጋጆች ክስተቱ ‹‹የቴክኒክ ስህተት›› ነበር የሚል መልዕክት ለኢሜይል ደንበኞቻቸው ከመላካቸው በስተቀር ዝምታን ሲመርጡ ከቴዲ አፍሮ ሆነ ከማናጀሩ እስከአሁን የተሰማ ነገር የለም፡፡

ከሚታመን ምንጭ ያገኘነውንና መጽሔቱ ቆርጦ ያስቀረውን የቴዲ አፍሮ ቃለ-ምልልስ ያካተተ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡
————-

ዕንቁ፡- ዳግማዊ ምኒልክ ስለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መፈጠር ሲሉ የገቡበትን ጦርነት እንዴት ነው የምትመለከተው?

ቴዎድሮስ፡- ምኒልክ በዚያን ጊዜ ያካሄዷቸው ፖለቲካዊ ተግባራት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች በመዘዋወር ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የገቡበት ጦርነት ለእኔ ቅዱስ ጦርነት ነው። ይህም የራሴ ዕምነት ነው። ምንጊዜም ሰዎች የሚበጃቸውን ነገር እስኪገነዘቡት ድረስ ያለመግባባቱ መጠን ይሰፋል። ያም ግጭት ሊፈጥር ይችላል። ወይም ደግሞ በእኛ ሀገር ሁኔታ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሆነም ነው። እንዲህም ሆኖ ግን ምኒልክ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዘምተው ንጉሥ ጦናን ማርኩ። ከማረኳቸውም በኋላ እግራቸውን እያጠቡ ‹‹የእኛ አንድ አለመሆን፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አለመመሥረታችን፤ የጋራ ለሚሆነው ጠላታችን ጥቃት አሳልፎ የሚሰጠን አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በዚህ ምክንያት ነው ወደ አንተ ጦር ያዘመትኩት እንጂ ሥልጣንህን ለመቀማትና በአንተ ላይ ለመግነን… ፈልጌ አይደለም። ማእከላዊ መንግሥታችንን ማጠናከሩ ግን ሁላችንንም የሚጠቅመን ነው። አገራችንን፣ በሕላችንን፣ ታሪካችንን፣ ቋንቋችንን ጠብቀንና ድንበራችንን አስከብረን ለመኖር ይረዳናል›› ነበር ያሏቸው።Enqu magazine's cover quoting Teddy Afro as saying 'For me, Menilik's unification campaign was a Holy War' - (Ethiopia)

እንግዲህ ምኒልክ ንጉሥ ጦናን አሏቸው እንደሚባለውም ይሁን በሌሎችም ብሔራዊ ክብርንና ማንነትን አስጠብቆ ለመኖር በሚያስችለው ፖለቲካዊ መመዘኛ ሲታይ፤ ቋንቋንም ጠብቆ ለመኖር እንኳ ቢያስፈልግ… ከጠላት ማንኛውም ጥቃት ራስን መከላከል ወይም ማስከበር በሚቻልበት አቅም መጠን መኖርን የግድ ይላል። ምናልባትም በዚያን ጊዜ እንደ ምኒልክ ያለው ባለውለታ ተፈጥሮልን… ከጠላት ተጠብቀን መኖር ባንችል ኖሮ፤ ዛሬ የምንጠራበት ስማችን ኢትዮጵያዊ ቀለም ሊኖረው አይችልም ነበር። እኔም ቴዎድሮስ፣ ሌላውም ምኒልክ፣ ጥላሁን፣ ፀሐይ… አንባልም ነበር። የነበረው ቋንቋችን ሁሉ ይጠፋ ነበር። ግን ቋንቋንም፣ ባሕልንም ሰብስቦ ለመያዝ፤ ከዛም በላይ ደግሞ ሕዝብን አስተባብሮ በአንድነት ለመሥራት፤ የአንድነትን ታላቅ ዋጋ ቀድሞ መገንዘብ ያስፈልጋል። ያንን ቅዱስ ያልኩትን ጦርነት ሊያስነሳው የቻለውም ይኸው ግንዛቤ ይመስለኛል።

ለማንኛውም ነገሮችን በቀና ማየትና የጎደለውን ሞልቶ፣ ያለውን ጥሩ ነገር እንዳለ ይዞ መሄዱ፤ ለተሻለ ሀገራዊ ርምጃ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን የመሰለው አካሄድ ደግሞ በሌሎች አገሮች አልተሠራበትም የሚል ቅንጣት ዕምነትም የለኝም። በሚገርም ሁኔታ አንድ ስማቸውን ለጊዜው የማላስታውሳቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ግዛት ንጉሥ ነበሩ… እንደውም ሥረ መሠረታቸው ከሰሎሞን ዝርያ የመጣ ነው ተብሎ ይታመናል። የእኚህን ንጉሥ ልዩ የሆነ የጨዋነት ባሕርይ መናገር እፈልጋሁ። ምኒልክ እኚህን ንጉሥ ሊዘምቱባቸው በተነሱ ጊዜ፤ አሁንም በቅጡ የማላስተውሰው የጀርመን መንግሥት ይሁን ሌላ የመሣሪያ ዕርዳታ ሊያደርግላቸው ይሞክራል። በዚህን ጊዜ ንጉሡ ‹‹የምዋጋው ከምኒልክ ጋር ነው። እሱ ወግቶ ከሻነፈኝ መላው ኢትዮጵያን ገዝቶ ይኖራል። ምኒልክን ተዋግቼ የማሸንፈው ከሆነም እኔ የመላው ኢትዮጵያ አስተደዳሪ እሆናለሁ። አሁን የምንጣላው ወንድማማቾች ስለሆንን ምንም ዓይነት መሣሪያ አልፈልግም። ነገር ግን የጋራ አገራችንን የሚጎዳና የሚያጠቃ ወራሪ የመጣ ጊዜ ዛሬ እንስጥህ የምትሉኝን እንዳትነፍጉኝ…›› በማለት መልስ ሰጥተዋል። እኚህ ንጉሥ ከምኒልክ ጋር ወጊያ ገጥመው ሽንፈታቸውን ሲቀበሉም፤ የነበራቸውን የንጉሥነት ታሪክና ክብራቸውን ለመጠበቅ አሣሪዎቻቸው በሚቀርቧቸው ጊዜ ‹‹እኔ የምታሠረው በብር ሰንሰለት እንጂ በብረት አይደለም›› ብለው በመቃወማቸው፤ እንዳሉት በብር ሰንሰለት ታስረዋል።

ይሄንና ሌሎችም ገጽታ በነበራቸው ሂደቶች የኢትዮጵያ የሀገርነትና የመንግሥትነት መሠረት ተጥሎ፤ ዛሬ ያለንበትን የአገራዊ አንድነት መልክና ቅርፅ ልናገኘው በቅተናል። ለዚህም ጸንቶ የቆየን አገራዊ መሠረት የበኩላቸውን ሚና የተጫወቱት፣ ስለዚህም ትልቅ ዋጋ ሊሰጣቸው የሚገባቸው መሪ ቢኖሩ፤ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ናቸው። ወቅቱ በረዳቸውም መሠረት የነበረውን የሥልጣን ክፍተትና ደረጃ ሞልተውና አመጣጥነው ማእከላዊ መንግሥቱን ከነበረው የግንዛቤ ማነስ ሁሉ… ቀድመው፤ በተቻለ መጠን የክርስቶስን አስተምህሮ ተግባራዊ የማድረጉንም ጥበብ በመጠቀምና፤ ዝቅ ብለው እግር በማጠብ ጭምር የነበረውን መጥፎ ሁኔታ መልክ ለማስያዝ ደክመዋል። ዛሬ ያለው ኢትዮጰያዊም ከተለያየ የኢትዮጵያ ብሔሮች ምንጭ ፈልቆ ወይም ተገኝቶ.. ይኸው በአንድነት ስለአንዲት ኢትዮጵያ ያለ ልዩነት ለመወያየትም ይሁን ‹‹ኢትዮጵያዊያን ነን›› ለማለት ችሏል። ስለዚህ የምኒልክ ስም ብሔራዊ አክብሮት ማግኘት የሚገባው፣ በሕልውናችንም ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና ያለው፣ የተባበታተነውን ሰብስበው ያቆዩ በመሆናቸው ነው።

ዕንቁ፡- “በዐፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመሩት ሥልጣኔን የመከተል ጉዞዎች እንደጅምራቸው ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ያደጉትን ሀገራት ጎራ ለመቀላቀል በቻለች ነበር” በማለት የሚቆጩ ወገኖች አሉ። አንተስ ምን ትላለህ?

ቴዎድሮስ፡- ያንን የሥልጣኔ ጅምር ከነበረው የኋላቀርነት ሁኔታ ጋር ሲመለከቱት ለመቀበል በጣም ከባድ ነበር። ለምሣሌ ‹‹ ስልክ ማነጋገር የሰይጣን ተግባር ነው…›› በማለት የተቃውሞ ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩ ሰዎች ነበሩ። በዚህ በኩል ከየመሳፍንቱ ቤት ገብተው የስልኩን መስመር በጣጥሰው እስከመጣል ደረጃ የደረሱ ቀሳውስትም ተይተዋል። እንደዚህ ያለውን አሮጌ አስተሳሰብ አሸንፎ ለመሄድ ምኒልክ ብዙ ደክመዋል። ሌላው ይቅርና ጫማ ማድረግ እንደ ሥጋ ደዌ በሽተኛ ያስቆጥር ነበር። ይሄንንና ሌላውንም ከቃል ባለፈ ደረጃ ተግባራዊነቱን በራሳቸው ላይ እየተገበሩ ተከታዮቻቸው እንዲለምዱት ለማድረግ ጥረዋል። ከዚህ ተነስተን ሂደቶቹን በሙሉ ብንመለከትና የምኒልክ ጅምር ቢቀጥል የት ነበር ዛሬ የምንደርሰው? የሚለውን ስናየው፤ ፈሩን ተከትሎ የመሄዱ ጉዳይ በእሳቸው ተነሳሽነትና አስተማሪነት መጠን ቢቀጥል ውጤታማነቱ የሰመረ ይሆነ ነበር እላለሁ።

ዕንቁ፡- ኢትዮጵያውያን ባለታሪክ የሆኑ አርዓያዎቻቸውን ያለማክበራቸው ችግር ከምን የመነጨ ነው?

ቴዎድሮስ፡- የችግሩን ምንጭ አጠር አድርጎ ለመግለጽ ያስቸግራል። ነገር ግን ምንግዜም ቢሆን ለጥሩም ይሁን ለመጥፎው ድርጊት፤ መንግሥትም በመንግሥትነቱ፣ ሕዝቡም በሕዝብነቱ የየራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዲያም ሆኖ ለሀገርና ለወገን የሠራን ሰው ማክበር ጠቃሚ ባሕል ነው። ምንግዜም ቢሆን ጥሩ ተምሳሌት በማይኖረው ማኅበረሰብ ውስጥ የሆነ ነገር መፍጠር አይቻልም። እስካሁን በተሄደባቸው ሀገራዊ መንገዶች፤ ጥሩ ያልነሆችውን ችግር ከነሰንኮፏ አንስቶ እሷኑ ብቻ በኃይል በማጉላትና ጠቃሚ የሆኑትን ጠቅላላ ነገሮች በማጥፋት ውስጥ ነው፤ እንደ ውሃ ስንረጫጭ ዘመናችንን ያሳለፍነው። ይህ ደግሞ ብዙ ዋጋ የከፈልንበት ብቻም ሳይሆን ወደፊትም ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን ነው። ከየትኛውም አመራር ውስጥ የበዛ አደጋ ኖሮ በመሀሉ መልካም ነገር ካለ፤ መልካሙን ነገር ማጉላት፣ የበዛውን አደገኛ ነገር ደግሞ እንዳይነሳ ማድረግ፤ የበዛውን መልካም ነገርም ባሉት ዕክሎች ብቻ ዐይናችን ታውሮ ‹‹ይሄንን ሰውዬ አልየው…›› የምንልበት የትግል መንገድ ስንሄድ፤ አሁንም እንደገና የምናከናውነው ተግባር ነገም ለምስጋና የማይበቃ ይሆናል። ስለዚህ በማንኛውም ሁኔታ ጥሩ የሠራን ሰው ማመስገን፣ ማክበር ጠቃሚ ባህል መሆኑን ተረድተን፤ በዚህ በኩል እስከዛሬ ያለውን ስሕተት ማረም አለብን። ጥሩን ነገር ማየት፣ ማክበርም ይሁን ማመስገን መቻል፤ ያ ጥሩ ነገር በራስም ውስጥ እንዲሰርጽ መፈለግ ወይም መፍቀድ ማለት ስለሆነ፤ ከሞቱት ሰዎች ሕይወት ያለው ሥራ ጋር መራመድ የሚገባን ይመስለኛል።

*********************

Daniel Berhane

more recommended stories