የ‹አንድነት› ፓርቲ አመራሮች በፖሊስ ጣቢያ ለሰዐታት ቆዩ

(Daniel Berhane)

ዛሬ ማምሻውን ቢያንስ ሰባት የ‹‹አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ›› ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በፖሊስ ጣቢያ ነበሩ – ከመንግስት ተቃዋሚዎች በፌስቡክ/ትዊተር እንዲሁም በስልክ በደረሱኝ ጥቆማዎች መሠረት፡፡

ይሁን እንጂ መንግሰት ጉዳዩን አጣጥሎታል፡፡

የመንግስትንና የ‹‹አንድነት›› ፓርቲ አመራሮችን ለማግኘት ባለፉት ሰዓታት በርካታ ጥረት ካደረግሁ በኋላ ከተቃዋሚው የፓርላማ አባል የተከበሩ ግርማ ሰይፉ እና ከክቡር ሚኒስተር ሬድዋን ሁሴን አስተያየት በስልክ ላገኝ ችያለሁ፡፡

የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ (ከምሽቱ 3፡30 ገደማ) እንደገለፁልኝ ከሆነ እሳቸውን ጨምሮ ቁጥራቸውን ያልገለጹልኝ የፓርቲው አባላት በፖሊስ ተይዘው የነበር ሲሆን እሳቸውና የተወሰኑ አባላት እኔ ስልክ ከመደወሌ ጥቂት ቀደም ብሎ ተለቀዋል፡፡ ሌሎችን ለማስለቀቅ የፓርቲው ሰዎች ጥረት እያደረጉ እንደሆነ እና የተቀሩት ሰዎች ፖሊስ ጣቢያ እንደማያድሩ በእርግጠኝነት ነግረውኛል፡፡

‹‹የፖሊስ ምክንያት/ሰበብ ምንድነው›› ብዬ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ፤ ፖሊስ ‹‹ህጋዊ ያልሆነ ቅስቀሳ አድርጋችኋል›› የሚል ስሞታ እንዳቀረበ፤ ሆኖም የመንገድ ላይ ቅስቀሳን የሚከለክል ሕግ እንደሌለ ገልፀውልኛል፡፡

ፓርቲው ለቀጣዩ እሁድ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ስምምነት እንዳገኘ ይሁን እንጂ እስከአሁን የሰልፉ ቦታ በውል እንዳልተለየ የተገንዘብኩ ሲሆን፤ ዛሬ ፓርቲውን ከፖሊስ ያወዛገበው ለሰልፉ የሚደረገው የመንገድ ላይ ቅስቀሳ ነው፡፡

እንደአቶ ግርማ አመለካከት መንግስት ሰልፉን ለማደናቀፍ እየሞከረ ነው፡፡

የመንግስት ምላሽ፡-

የመንግስት ሀላፊዎችን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ካደረግሁ በኋላ ከአዲሱ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስተር ሬድዋን ሁሴን (በቅርቡ በበረከት ስምዖን ቦታ የተተካው) ምላሽ ላገኝ ችያለሁ፡፡ ከኔ የስልክ ቀፎ ወይም ከኔትወርክ ደካማነት በመነጨ ችግር ዝርዝር ሀሳቡን ለመስማት/ለመጠየቅ ስላልቻልኩ በጽሑፍ (SMS) ምላሽ እንዲሰጡኝ ጠይቄያቸው (ከምሽቱ 4:15  ሰዐት ገደማ) የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውኛል::

‹‹የታሠረ ሰው የለም፡፡ በመንግሰት ዕውቅና ለተሰጠው ስብሰባ ወይም ሰልፍ ወይም መሰል ተግባራት ለሚደረግ ቅስቀሳ ፈቃድ አያስፈልግም – ሁከት ሊፈጥር የሚችል ቅስቀሳ ካልተደረገ በቀር፡፡ መመሪያ/ማብራሪያ ለመስጠት የሆነ ሰው ተጠራ ማለት ታሠረ ማለት አይደለም፡፡››

(ምላሹን ያገኘሁት በእንግሊዘኛ ሲሆን፡ በአተረጓጎሜ ላይ ጥርጣሬ ስላለኝ ስላለኝ እንደወረደ እንብቡት “No one is detained. No permission is needed if it is related to an already recognized meeting or demonstration or any sorts, so long as one is not stirring public disturbances. If someone is summoned just for a briefing, that is not tantamount to detention.”)

የኢትዮጲያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነገሮች የማስጮህ ባህል እንዳላቸው የምገነዘብ ቢሆንም፣ ‹አንድነት› ፓርቲ በቅስቀሳ ላይ እንቅፋት ገጠመኝ ሲል ይህ የመጀመሪያ ባለመሆኑ – የመንገድ ላይ ቅስቀሳን በተመለከት ያለውን ሕግና አሠራር በተቻለ ፍጥነት ቃኝቼ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

**********

* በጣም ከመሸ በኋላ መረጃ ለመስጠት ስለተባበሩ ለክቡር ሚኒስተር ሬድዋን ሁሴን እና ለተከበሩ ግርማ ሰይፉ በራሴና በአንባቢዎች ስም ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ሌሎችም ከነሱ እንደሚማሩ ተስፋ አለኝ፡፡

Daniel Berhane

more recommended stories