የአንድነት ጉባኤና ፖለቲካዊ አንደምታው

(በዘሪሁን ሙሉጌታ)

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሦስተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ከመጀመሪያው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ከሰሞኑም የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በቀጣይ ሁለት አመታት ፓርቲውን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ሦስት እጩዎችን ይፋ አድርጓል።

አንድነት ፓርቲውን ለመምራት ብቃቱ አለን በማለት በፍላጎታቸው በእጩነት ቀርበው የነበሩት የቀድሞው የፓርቲው ምክትል ተቀዳሚ ሊቀመንበር የነበሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ ብቸኛው የፓርላማው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ የፓርቲው የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ ሽመልስ ሀብቴ፣ አቶ ትግስቱ አወሉ ነበሩ።

ከአምስቱ እጩዎች ሦስቱን በመለየት በቀጣይ ጥቅምት ወር ላይ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሦስቱ እጩዎች የሚወዳደሩ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ለሊቀመንበርነት ከታጩት መካከል ሰፊ የፖለቲካ ልምድ ያላቸውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚዲያ የራቁት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አንዱ ናቸው። ኢንጂነር ግዛቸው ቀደም ሲል የፓርቲ አመራርነት ቦታውን ለወጣቶች ማስረከብ ይገባል የሚል አቋም በማራመድ ከፓርቲ አመራርነት ቢርቁም በአሁኑ ወቅት እንደገና ተመልሰዋል። የኢንጂነር ግዛቸው እንደገና መመለስ በ8ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ የብአዴን አመራሮች መካከል በመተካካት ሂደት ከቦታቸው ተነስተው የነበሩትን የእነ አቶ አዲሱ ለገሰን ስልት ያስታወሰ ይመስላል።

ሆኖም ኢንጂነር ግዛቸው በምርጫ 97 ወቅት ከፍተኛ ተሰሚነትን ካገኙ አመራሮች አንዱ የነበሩ ከመኢአድ እስከ ቅንጅት በኋላም መድረክን በመጠንሰስና በማሳካት ሂደት ጉልህ ድርሻ የነበራቸው፤ በሙያቸው በኬሚካል ምህንድስናው ዘርፍ ሀገራቸውን ያገለገሉ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ያገለገሉ ተወዳጅ ፖለቲከኛ ናቸው።

ሌላኛው እጩ አቶ ተክሌ በቀለ ናቸው። አቶ ተክሌ በህብረት ስራ ግብይት የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው፣ በኢዴፓ ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ አድርገው ከቀድሞ ቅንጅት መፍረስ በኋላ በ2001 ዓ.ም ከአንድነት ጋር የተቀላቀሉ፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩ እንዲሁም በመቀሌ በሚገኘው ኒውሚሊኒየም የተባለ የግል ኮሌጅ በዲንነት ያገለገሉ ሰው ናቸው። አቶ ተክሌ ጎልማሳ ጥሩ እውቀት የታጠቁ እንደመሆናቸው በምርጫው ሂደት ዋነኛ ተፎካካፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገመቱ አመራር ናቸው።

በሦስተኝነት ለፕሬዝዳንትነት የታጩት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ናቸው። አቶ ግርማ በኢኮኖሚክስ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሊግ (ኢድሊ) ጀምሮ በቅንጅትና በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የፖለቲካ ልምድ ያዳበሩ አመራር ናቸው።

ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚሉት ለፓርቲው ፕሬዝዳንትነት የቀረቡት አመራሮች አሁን ፓርቲው ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አጥጋቢ ቢሆኑም፤ ለፓርቲው መጠናከር ጠንካራ ጥረት እያደረጉ ያሉት አቶ በላይ ፈቃዱ፣ በቅርቡ ወደ ፓርቲው የተቀላቀሉት ወጣቱ ሐብታሙ አያሌው እና በውጪ አገር የሚገኙት አቶ ስዬ አብርሃ በፕሬዝዳንታዊው እጩ መካተት ነበረባቸው የሚል ኀሳብ የሚያቀርቡ አሉ።

የሦስቱ አመራር መታጨት ከመድረክ አንድነት ግንኙነት አንፃር

በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ እልባት ከሚሰጣቸው አብይ አጀንዳዎች የአንድነትና የመድረክ ግንኙነት ላይ ሊሆን ይችላል። እስካሁን ባለው ሁኔታ የመድረክና የአንድነት ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ጤናማ አይመስልም። ጤናማ ላለመምሰሉ አንዱና ዋነኛው ማሳያ አንድነት ‘‘የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት’’ በሚል መሪ ቃል የጀመረውን ሕዝባዊ ንቅናቄን መድረክ አለመደገፉ ወይም በሂደቱ ተሳታፊ አለመሆኑ ሊጠቀስ ይችላል። 33ቱ ፓርቲዎችና መኢአድ አንድነት በዋናነት ባስተባበረው ሕዝባዊ ንቅናቄ ላይ በይፋ አጋርነታቸውን ሲያሳዩ መድረክ እንደ መድረክ ‘‘እኔ በእቅዱ ባልተሳተፍኩበት ፕሮግራም ውስጥ አልገባም’’ የሚል አቋም በመያዝ በንቅናቄው ሂደት ውስጥ ሲሳተፍ አይታይም። መግለጫ በማውጣትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድጋፎችን ሲያደርግ አይታይም።

እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተደራርበው የአንድነትና የመድረክን ግንኙነት በሚፈለገው መጠን እንዲሞቅ አላደረገውም። ለፕሬዝዳንትነት እጩነት ካቀረቡት ሦስት አመራሮች ከኢንጂነር ግዛቸው በስተቀር ሁለቱ እጩዎች በመድረክ አንድነት ላይ ግልፅ ጥያቄ የሚያነሱ እንደመሆናቸው መጠን በአንድነት መድረክ ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል።

ከኢንጂነር ግዛቸው በስተቀር ሌሎቹ እጩዎች የመድረክና የአንድነት ግንኙነት እንዲጠናከር ካልሆነ አንድነት የመድረክ ሞግዚት ሆኖ የሚቀጥልበት ሂደት መልክ እንዲይዝ የሚፈልጉና በብሔራዊ ምክር ቤቱ አባላት ላይም ተፅእኖ መፍጠር የሚችሉ ናቸው። ይህም ኀሳባቸው ወደ ጠቅላላ ጉባኤው እንዲሰርፅ ከተደረገ ብዙም ያላማረው የመድረክና የአንድነት ግንኙነት ላይ እልባት ሊሰጡት ይችላሉ ተብሎ ይጠብቃል።

የአቶ ስዬና የወጣት ሐብታሙ ለፕሬዝዳንትነት ያለመታጨት ጉዳይ

አቶ ስዬ አብርሃ የፓርቲው የብሔራዊ ም/ቤት አባል ናቸው። ምንም እንኳ ለአንድ አመት ትምህርት አሜሪካን ሀገር ሄደው ቢቀሩም ከአባልነታቸው እስካሁን አልተሰረዙም። በውጪ ሀገርም ፓርቲውን የሚረዳ ተግባር እያደረጉ መሆኑንም የፓርቲው አመራር አባላት ሲገልፁ ይሰማል።

አቶ ስዬ አዲስ አበባ በነበሩት ወቅት የፓርቲውን የአምስት አመት የስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ሂደት ንቁ ተሳትፎ የነበራቸውና ሻዶ ፓርላማ እስከማቋቋም ውጥን የሰነቁ አመራር ናቸው። የፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄድበትን ጊዜና ቅርፅ ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ጭምር በአንድነት መዋቅር ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መልካም ተሳትፎ የነበራቸው አመራር ነበሩ። በ2007ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ጎልተው በመውጣት በፖለቲካው አየር ውስጥ ቢጠበቁም በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በእጩነት እራሳቸውን አላቀረቡም።

የመድረክ ጠንሳሽና ቴክኒሻን ከነበሩት አንዱ አቶ ስዬ የብሔርና ሕብረብሔር የሚገናኙበትን ‘‘አማካይ ስፍራ’’ን በአንድነት ውስጥ ለመፍጠር የሄዱበት ርቀት ከፍተኛ ቢሆንም አሁን ካለው የመድረክ አንድነት ግንኙነት አንፃር ግባቸውን መቷል ለማለት አያስደፍርም። አቶ ስዬ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር አለመቅረባቸው ብዙዎችን የፓርቲ አባላት ማነጋገሩ አልቀረም።

በአሁኑ ወቅት አቶ ስዬ የተባበሩት መንግስታት ቅጥር ሠራተኛ ሆነዋል። ከተመቻቸ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በተጨማሪ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ሂደት ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል። በአለም አቀፍ ሚሊተሪ እንቅስቃሴ ውስጥ ተካተዋል። ሰውዬው በአንድ ሆነ በሌላ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ሚሊተሪ ውስጥ በተለይ ከሰላም ማስከበር ጋር በተያያዘ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል።

በሌላ በኩል አንድነት ፓርቲ ‘‘በአንድ ግለሰብ ገፅታው የማይሳል’’ በቡድን አመራር መርህ የሚመራ በመሆኑ የእነ ስዬ አለመኖር ተፅዕኖው የከፋ አለመሆኑን የሚገልፁ የፓርቲው አባላት አሉ።

ከአቶ ስዬ በተጨማሪ ለፓርቲው አመራርነት ሲጠበቁ የነበሩት በቅርቡ ፓርቲውን የተቀላቀለው ወጣት ሐብታሙ አያሌው ነው። ወጣት ሐብታሙ የትምህርት ደረጃ አላሟላም የሚል አሉባልታ ተነስቶበት እንደነበር ገልጿል። በጉዳዩ ላይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት ገና ከጅምሩ ለፓርቲ ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ጥያቄ አለማቅረቡን አስረድቷል።

በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በሂዩማን ሪሶርስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዳለውና በቲዮሎጂ ትምህርት የሦስተኛ አመት ተማሪ እንደሆነ አመልክቷል። በመሆኑም የትምህርት ዝግጅት አላሟላም የሚለው ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሷል። ምሁርነት በሰርተፊኬት የማይለካ መሆኑን፣ አቶ መለስ ዜናዊ የሜዲካል ሁለተኛ አመት ተማሪ ሆነው በተልዕኮ ዲግሪ እስኪያገኙ ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ኢትዮጵያን የመሩት የትምህርት ማስረጃ ይዘው አልነበረም ያለው ወጣት ሐብታሙ መለሰ በሰርተፊኬት ባገኙት እውቀት በላይ አንብበው ያገኙት እውቀት ኢትዮጵያን መምራት እንደቻሉ በማስታወስ ለፖለቲካ መሪነት ሰርተፊኬት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጿል።

ለፕሬዝዳንትነት ያልተወዳደረባቸው ምክንያቶች ወጣት ሐብታሙ ሲገልፅ ለፓርቲው ፕሬዝዳንት አሁን በእጩነት የቀረቡት ከእርሱ የተሻለ የፖለቲካ እውቀት ያላቸው በመሆኑ፣ ሁለተኛው ምክንያት በተቃውሞ ጎራ አንድ አመት ብቻ ያሳለፈ በመሆኑ፤ አንድ አመቱ ደግሞ የለውጥ ፍላጎት መኖሩን የሚያሳይ ቢሆንም በተቃውሞ ጎራ ያለውን ፖለቲካ በበቂ ሁኔታ መረዳት ስላለብኝ ነው ብለዋል።

‘‘አጠቃላይ የተቃውሞ ጎራውን ቤተሰብ የበለጠ መተዋወቅ ይኖርብኛል። አቅሜን ማየትና መገምገም አለብኝ። በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አንድን ትልቅ የተቃዋሚ ፓርቲ እመራለሁ ብዬ እራሴን አላስቀመጥኩትም’’ ያለው ወጣት ሐብታሙ ከፓርቲው አባላት በኩል እንዲወዳደር ፍላጎት ቢኖርም ቀደም ብዬ ከሦስትና አራት ወራት በፊት ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ኀሳብ እንደሌለኝ አሳውቄአለሁ ብሏል። ‘‘ገና ሰከን ብዬ ልምድና እውቀት ማግኘት አለብኝ። የተሻለ ብቃት ካለኝ ተጎትቼም ቢሆን ወደመሪነት ልመጣ እችላለሁ’’ ያለው ወጣት ሐብታሙ አሁን እየተማረ መሆኑን በቅርቡም ለንባብ የሚበቃ መፅሐፍ በማዘጋጀት ላይ መሆኑንም አመልክቷል።

የቀድሞ ሥራ አስፈፃሚ ምንሰራ?

የፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት እየተሰናበተ ያለውን የሥራ አስፈፃሚ መገምገሙ ተገልጿል። በግምገማውም ውጤት ባለፉት ሁለት አመታት አንድነት እንደ ፓርቲ ምን ሰራ የሚለውን ተመልክቷል።

በግምገማው ሂደት የሥራ አስፈፃሚውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተፈትሿል። በግምገማው ሥራ አስፈፃሚው የድርጅታዊ ስራ የተሻለ አፈፃፀም እንዳለው መግባባት ቢኖርም የፖለቲካ ስራ ላይ ግን ድክመት እንደነበረበትም ተገልጿል።

የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ በቢሮና በአደረጃጀት ስራዎች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ትግሉን በመግፋት በኩል ግን ደካማ መሆኑ ተመልክቷል። ለረጅም ጊዜ ድርጅት በመፍጠሩ ሂደት ላይ በመቆየቱ ገፍቶ ሄዶ ኢህአዴግ ታግሎ ሕዝቡ ሊሸከማቸው ያልቻሉ ችግሮችን ተንትኖ ወደ አደባባይ በማቅረብ ረገድ ደካማ ነበር የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

ምንም እንኳ ፓርቲው የተለያዩ ምሁራንን በጽ/ቤቱ በመጋበዝና በፓርቲው ልሳን አማካኝነት ወደ ሕዝቡ ለመቅረብ የተደረገው ጥረት እንደተጠበቀም ቢሆን ትግሉን ወደ ሕዝቡ በማውረድ በኩል ግን ፓርቲው ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር አጥጋቢ አለመሆኑ በፓርቲው አመራር አባላት ዘንድ የታመነበት ጉዳይ ሆኗል። አዲሱ የስራ አስፈፃሚ በቀጣይ ፖለቲካውን ወደ ሕዝቡ በማውረድ በኩል በቅርቡ የተጀመረውን ንቅናቄ አጠናክሮ በማስቀጠል ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚወድቅበት ይሆናል።

የአንድነት ጉባኤ በሌሎች ፓርቲዎች ላይ ያለው ተፅዕኖ

የአራት ፓርቲዎች ‘‘ግንባር’’ የነበረው መድረክ አባል ፓርቲዎቹ እርስ በርስ እየተዋሃዱ ነው። ቀደም ሲል ስድስት የነበሩት ወደ አራት ዝቅ ብለዋል። የመድረክ አባል የነበሩትና በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተቋቋሙት ኦህኮ እና ኦፌዴን ‘‘ኦፌኮ’’ የሚል አዲስ ውህድ ፓርቲ ፈጥረዋል። በተመሳሳይ የደቡብ ህብረት እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ‘‘ኢማዴደህአፓ’’ የሚል አዲስ ውህድ ፓርቲ ፈጥረዋል።

የቀሩት አንድነትና አረና ናቸው። አረና ደግሞ በሦስተኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ፓርቲውን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለማዋሐድ መወሰኑ በቅርቡ ሌላ ውህደት እንዲፈጠር ማስገደዱ አልቀረም። አንድነት ከአረና ጋር የመዋሃዱ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከናውኖ ከመድረክ ማህፀን እንደገና ሦስት አዳዲስ ውህድ ፓርቲ ለመፍጠር ሁኔታዎች የተመቻቹ ይመስላል።

ከፖለቲካ መድረኩ በሂደት እየራቀ ያለው መድረክ በቀጣይ ጊዜያት ወይ ወደ ታሪክነት ሊቀየር ይችላል፤ አሊያ የኦፌኮ እና የኢማዴህአፓ ‘‘ግንባር’’ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል። በአረና በኩል መድረክን የማዋሐድ ፍላጎት ቢኖርም ከፓርቲዎቹ የአፈጣጠር ልዩነትና ከመሪዎቹ ፍላጎት በተጨማሪ ከፕሮግራም አለመጣጣም ጋር በተያያዘ ውህደቱ ይሳካል ተብሎ አይገመትም። ይልቁኑ በአንድነት እና በሰማያዊ መካከል የተፈጠረው የፉክክር ፖለቲካ መድረክን ከፖለቲካው ጨዋታ እያስወጣው መሆኑን የሚጠቀሙ ሁኔታዎች እየታዩ ነው።

አረና በመድረክ ውስጥ ጠላትም ወዳጅም ያለመሆን አቋም እንደማያዋጣው የተገነዘበ ይመስላል። በቅርቡም ነባር አመራሮቹን በማንሳት የውህደት አቀንቃኝ የሆኑ ወጣቶች የመሪነቱን ሚና ይዘዋል። ይህንንም ተከትሎ አረና በአንድነትም በሰማያዊ የሚፈለግ ፓርቲ ሆኗል። አረና ከቅርበት አንፃር ወደ አንድነት ይመጣል ተብሎ የቅድሚያ ግምት ቢሰጠውም አሁን ካለው እንቅስቃሴና የወጣቶች ስብስብ አንፃር ወደ ሰማያዊ ተጠቃሎ የሚገባበት ዕድልም ሙሉ በሙሉ ዝግ አለመሆኑን መገመት ይቻላል።

ምንም እንኳ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ፓርቲው በመርህ ደረጃ ‘‘ውህደት አንፈልግም’’ የሚል ኀሳብ ቢያንፀባርቁም ሌሎች የፓርቲው አመራሮች ግን ለአጠቃይ ትግሉ መጠናከር ሲባል ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተዋህዶ መቀጠሉን እየፈለጉት ነው። ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት ሰማያዊ ፓርቲ አመራር ውስጥ ውህደትን በተመለከተ ‘‘እንዋሃድ ወይም አንዋሃድ’’ የሚለው አቋም ውስጥ ውስጡን እየተብላላ ስለመሆኑ ይነገራል።

አረና የሀገር አቀፋዊ አጀንዳን በመያዝ፣ ክልላዊ የፖለቲካ አስተሳሰብን ከተወ ሰማያዊ ፓርቲ አልዋሐድም የሚልበት አሳማኝ ምክንያት እንደማይኖረው ከወዲሁ እየተገለፀ ነው። በአዲስ አበባ የታጠረውን ትግሉን ወደ ትግራይና ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ይሄንን አማራጭ ችላ ብሎ ያልፈዋል ተብሎ አይገመትም። ‘‘እንዋሐድ’’ የሚሉት የሰማያዊ አመራሮች ፓርቲው ከአረና ጋር እንዲሰራ ውስጥ ውስጡን ፍላጎት እንዳላቸውም ለማወቅ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት ከአረና የተጫረው የውህደት ክብሪት በሦስቱ ማለትም በአንድነት፣ በሰማያዊና በመድረክ ውስጥ ሊያቀጣጥለው የሚችል ነገር እንዳለ ይገመታል። ከአረና የተነሳው የውህደት ጥያቄ መድረክን ይበላዋል ወይም ያጠናክረዋል የሚል ግምት እንዳለ ሁሉ በአንድነትና በሰማያዊ መካከልም የአስታራቂነት ሚና ይዞ የመምጣት ዕድል ሊፈጥር ይችላል።

አረና፣ ሰማያዊና አንድነት ወደ ውህደት ከመጡ የትግራይ ክልልን የሳተፈ ‘‘አዲስ ቅንጅት’’ በመፍጠር ‘‘ወደመጡበት እንመልሳቸዋለን’’ የሚለውን የትግራይ ሊህቃንን የፖለቲካ ፍርሃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማስወገድ አቅም ይፈጥራል።

አቅጣጫው ያልጠራው ‘‘የ33ቱ ፓርቲዎች’’ አካሄድ በራሳቸው የሚፈጥሩት የፖለቲካ ተፅዕኖ ባለመኖሩ በትላልቆቹ አሳዎች መዋጣቸው የሚጠበቅ ይሆናል። ለጊዜው የሁሉንም ፓርቲዎች ቀልብ መግዛት ያልቻለው መኢአድ ከቻለ በሦስትዮሹ ውህደት (አረና ሰማያዊና አንድነት) የመቀላቀል ካልሆነ ደግሞ በራሱ የሚሄድበት ዕድል አለው። በዚህ ወቅት መኢአድና አንድነት የመሠረቱት በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መኢአድን ወደ ሦስትዮሹ መንፈስ (አዲሱ ቅንጅት) ሊያመጣው ይችላል። በዚህም ተባለ በዚያ ከአንድነት ጉባኤ በኋላ የውህደት አቅጣጫዎች ተፅዕኖአቸው መመንዘር የሚጀምርበት ይሆናል።

***********

Source: Sendek – Sept. 26, 2013 – <የአንድነት ጉባኤና ፖለቲካዊ አንደምታው>.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories