ሀሰን ታጁ፡ ጥያቄው ፖለቲካ ገብቶበታል – የገቢ ምንጭ ሆኗል

Highlights:
* በመጀመሪያ ሃያ አባላት ያሉት ኮሚቴ ሲመረጥ አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡
* የእንቅስቃሴው ሌላ አደጋ በሚስጥር እየተመራ ያለ መሆኑ ነው፡፡
* ኢትዮጵያ ውስጥ “እስላማዊ መንግስት ይመስረት” ብሎ የጠየቀ የለም፡፡ መንግስትም ይህን የሃይማኖታችሁን አንቀፅ አሻሽሉ ወይም በዚህ ተመሩ አላለም፡፡
* ኢትዮጵያ ለ700 አመታት በክርስቲያን መንግስት ነው ስትተዳደር የነበረው፡፡ ስለሆነም ካሰጋትም የክርስቲያን አክራሪነት ነው፡፡
* የቀረቡት ጥያቄዎች በመርህ ደረጃ መመለሳቸውን የታሰሩ የኮሚቴ አባላትም አምነዋል፡፡
* አጀንዳውን የገቢ ምንጭ አድርገው የያዙ ወገኖችም አሉ፡፡
* መነሻ ጥያቄው ሃይማኖታዊ ቢሆንም እያደር ፖለቲካ ገብቶበታል ብዬ አስባለሁ፡፡
* የመንግስትን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ልትቃወም ትችላለህ እንጅ “ጭራሽም ወደኔ አትዙር” ልትለው አትችልም፡፡ ከመንግስት ጋር መስማማት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እስልምና አሁን ባለው ተጨባጭ አለም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡
* ከውጭ ተምረው የሚመጡት ደግሞ የውጭ አስተሳሰብን ነው ይዘው የሚመጡት፡፡ የሳዑዲው የሳውዲን፤ የግብፁ የግብፅን አስተሳሰብ ይዘው ይመጣሉ፡፡

————

ታዋቂው የእስልምና ምሁር እና ለ1 ዓመት ተኩል ሲካሄድ የቆየውን የአወልያ ንቅናቄ ሂደት በቅርበት ሲከታተል የነበረው ኡስታዝ ሀሰን ታጁ ከ‹ፋክት› መጽሔት ጋር ከሁለት ሳምንት በፊት ረዥም ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ የሀሰን ታጁ አስተያየቶች የዚህን ብሎግ አንባቢዎች እንደሚስብ በማመን ሙሉ ቃለ-ምልልሱን በኮምፒውተር አስተይበን ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡

*************

ኡስታዝ ሀሰን ታጁ የእስልምና ሃይማኖት ካፈራቸው የሃይማኖት ልሂቃን አንዱ ነው፡፡ ከሚያውቁት ብቻም ሳይሆን ያወቁትን ወደ ህዝባቸው ከሚያደርሱ የተግባር ሰዎች መሀል ይመደባሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከ10 ባልራቁ አመታት ዉስጥ የተረጎመውና ያዘጋጃቸው ከ120 በላይ እስላማዊ መፃህፍት (ከእነዚህ ዉስጥ ወደ 90 የሚጠጉት ታትመውለታል)፤ በተጨማሪም በተሟላ እስላማዊ አስተምህሮ ለአንባብያን እንዲደርሱ የአርትዖት ስራ የሰራባቸው ከ45 በላይ እስላማዊ መፃህፍት ህያው ምስክሮቹ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው የእስልምና ሃይማኖት ከባህላዊ አስተሳሰብ ወጥቶ በዘመናዊ እውቀት እንዲራመድ ካስቻሉ ጥቂት ሙስሊም ምሁራን አንዱ ነው፡፡ አሁን ግን በኡስታዝ ሀሰን ታጁና ጥቂት በማይባሉ የሃየማኖቱ ተከታዮች መካከል ክብሪት ተለኩሷል፡፡ ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግ በአጠቃላይ አካሄዱ ዙሪያ ከፋክት መፅሔት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- መጋቢት 2005 “በመንታ መንገድ ላይ ነን፤ የቱን አቅጣጫ እንከተል?” የሚለውን 89 ገፅ ያለውን በወቅቱ የመንግስትና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች (ብዙና ጥቂት የሚለውን ገመድ ጉተታ እንተወውና) ዘንድሮ የተጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ ያቀረረብከውን መፅሀፍ መነሻ አድርገን ወደ ተጓዳኝ ሀሳቦች እንዘልቃለን፡፡ ይህንኑ ቀደም ሲል በወረቀት የተበተነውን፤ በማህበራዊ ድረ ገፆች የተለቀቀውን በመጨረሻም በመፅሀፍ ታትሞ የወጣውንና የውዝግብ አጀንዳ የከፈተውን መፅሀፍ ለማዘጋጀት ሰበብህ ምንድን ነው?

ሀሰን ታጁ– አንብበኽው ከሆነ ዋንኛ ምክንያቱ በመፅሀፉ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- አዎን ግን ለዚህ ቃለመጠይቅ አንባቢያን ደግመን እናንሳው፡፡

ሀሰን ታጁ– መልካም፡፡ ዋንኛ ምክንያቶቹን በሶስት ዋና መደቦች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ካሁን ቀደምም ካንተ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተናል፡፡ የሙስሊሙ ህብረተሰብ የመብት ንቅናቄ ትግል በጣም በተራዘመ መለኩ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ትግሉ ለምን ሊራዘም ቻለ? ያልተገባ ጥያቄ በመነሳቱ? መንግስት ባለመስማማቱ? ወይስ በምን?

ሀሰን ታጁ– ጥያቄው ተገቢ፤ አነሳሱም ሰላማዊ ነው፡፡ ነገር ግን ሂደቱ ላይ የተፈጡUstaz Hasen Taju - Ethiopian author and Islamic scholar ሁኔታዎች ወደ አደገኛ አዝማሚያ ይሄዳሉ የሚል ስጋት አሳድሯል፡፡ ጥያቄዎቹ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሲንዛዙና ሲጓተቱ ወደ መጥፎ ሁኔታ ተገባ፡፡ ከዚያ በኋላ እስር መጣ፡፡ ቀጥሎ የመጣው ሂደት ለሙስሊሙ ህብረተሰብም ሆነ ለመንግስት ጥሩ አይደለም፡፡ ከስድስት ወር በፊት አለመግባባቱ ወደ ደም መፋሰስ ሊሄድ ይችላል የሚለው ሁኔታ ስላሳሰበን ነው ፅኁፉን ያወጣነው፡፡ እስካሁንም እንደሚፈራው አልሆነም፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በመንግስት በኩል ትዕግስት ታያለህ፡፡ ምንአልባት ሃይማኖት ስለሆነ ይሆናል ነገሮችን በጥንቃቄ የመያዝ ሁኔታን ታያለህ፡፡ ሁኔታው በአለመግባባቱ ገፍቶ የሀገር ደህንነት ችግርና ስጋት ከመሆኑ በፊት በጊዜ መቋጨት አለበት በሚል መነሳሳት ነው ፅሁፎቹ የወጡት፡ መፅሃፉም የተዘጋጀው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- እስቲ ላለመግባባቱ ዋንኛ ምክንያት ናቸው ያልካቸውን ሶስት ጉዳዮች አንሳልን?

ሀሰን ታጁ– የመጀመሪያው የተጠናከረና በስርዓት የሚመራ መሪ (አመራር) ያለመኖሩ ነው፡፡ ሁለተኛው ወጥ አመለካከት የሚያሲዙ ሃይማኖታዊ ተቋሞች ያለመኖራቸው ነው፡፡ ባህላዊወቹ እየተዳከሙ ነው፤ በዘመናዊው አልተተኩም፡፡ ይህ ያለመሆኑ በማይታወቅ ስርዓተ ትምህርት የሚሰለጥኑ ሰዎችን ይፈጥራል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ምን ማለት ነው በማይታወቅ ስርዓተ ትምህርት መሰልጠን?

ሀሰን ታጁ– በፊት የነበረው ባህላዊ ስርዓተ ትምህርት ጥሩ ነበር፡፡ ዘመናዊ ስርዓተ ትምህርት በሀገር ውስጥ ስለሌለ አንዳንዶች ውጭ ተምረው ይመጣሉ፡፡ ከውጭ ተምረው የሚመጡት ደግሞ የውጭ አስተሳሰብን ነው ይዘው የሚመጡት፡፡ የሳዑዲው የሳውዲን፤ የግብፁ የግብፅን አስተሳሰብ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ብዙውን ግዜ የውጭዉ የአስተሳሰብ ዘር ለዚህ ሀገር አፈር አይስማማውም፡፡ ስለዚህ ጥሩ ምርት አያፈራም፡፡ እስልምና አለም አቀፍ ነው፡፡ በሁሉም ሀገራት ተመሳሳይ ነው፡፡ እስላማዊ እንቅስቃሴዎች ግን ከሀገር ሀገር ይለያያሉ፡፡ ሀገራቱ በራሳቸው ውስጣዊ አጀንዳ ነው እንቅስቃሴውን የሚመሩት፡፡ እኛ ሀገር ደሞ ሌላ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ግብፅ ከ90 በመቶ በላይ፤ ሳውዲ መቶ በመቶ ሙስሊም ናቸው፡፡ እነሱ ሌላ አጀንዳ ነው ያላቸው፡፡ የእኛ ሀገር ሌላ ነው፡፡ ከ60 በመቶ ያላነሰ ክርስቲያን ያለበት ሀገር ነው፡፡ ታሪካችንና ተጨባጭ ሁኔታችን ስለሚለያይ አጀንዳችንም ይለያያል፡፡ በሀገራችን ወጥ ስርዓተ ትምህርት ያላቸው እስላማዊ የትምህገርት ተቋማት አለመኖራችው ችግሩን እንዳባባሰው ተጠቅሷል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- በቀዳሚነት ወደተጠቀሰው የጠንካራ መሪ አለመኖር ጉዳይ እንመለስ፡፡ በደካማው መጅሊስ እግር የተተካውን መጅሊስ ሙስሊሙ (አሁንም ቁጥር ሳንጠቅስ) አልተቀበለውም፡፡ የጠንካራ መጅሊስ መኖር ለሙስሊሙ ምን ማለት ነው?

ሀሰን ታጁ– ለሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ጥቅምና ጉዳቱ ለክርስቲያኑም፤ በአጠቃላይ ለሀገርም ነው፡፡ ጠንካራ አመራር በሌለ ቁጥር በየቦታው ትንንሽ መሪዎች ይፈጠራሉ፡፡ እነዚያ መሪዎች ደግሞ ገዢ ያልሆነ ጥሬ አስተሳሰብ ከውጭ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ጎጃም ውስጥ ያለ ሙስሊምና ወሎ ዉስጥ ያለው ሙስሊም ምን ምን እንደሚያስቡ አታውቅም፡፡ ምክንያቱም አጠቃላይ አመራር የሚሰጥ አካል ስለሌለ፡፡ ኦርቶዶክስ ጋር ብትሄድ ቤተክርስቲያኗን በማየት የአማኙን አቅጣጫ ማወቅ ትችላለህ፡፡ በሙስሊሙ ግን መጅሊሱን በማየት ሙስሊሙ ምን እንደሚያስብ ማወቅ አትችልም፡፡ መጅሊሱ መሪ አይደለም፡፡ በእሱ አይደለም እየተሰራ ያለው፡፡ የመጅሊሱ መዳከም አማኙን ለጥሬ አስተሳሰብ ዳርጎታል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- በመፅኃፍህ ላይ “መጅሊስ የተባለው ተቋም የአላዋቂዎች መጫወቻ ሆኗል” ይላል፡፡ይህ የሆነው በማን ፍላጎት ነው? መንግስት ሃይማኖቱ በእውቀት እንዲመራ ስላልፈለገ? ፍትሃዊ ምርጫ ባለመደረጉ? መሪነት በአላዋቂዎች እጅ ገብቶ? ወይስ በምን?

ሀሰን ታጁ– ይህ ሰፊ ታሪክ ነው ያለው፡፡ ከአፄ ኃይለስላሴ እስከ ደርግ ስርዓት ድረስ ሃይማኖቱ በታላላቅና ስማቸው በሚጠቀስ የሃይማኖት ሰዎች ተመራ፡፡ ደርግ ሃይማኖት ላይ ያለው አቋም እንዳለ ሆኖ ለእነርሱና በአካባቢያቸው ላሉት የሃይማኖቱ መሪዎች ክብር ነበረው፡፡ መሪዎቹም የሚታመኑና ግርማ ሞገስ ያላቸው ነበሩ፡፡ ከዚያ በኃላ ደርግ ሊወድቅ አካባቢ መሪያችን ሞቱ፡፡ ከዚያ በኃላ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በሃይማኖቱ ውስጥ ነበረ፡፡ ኢሕአዴግ ሲመጣ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የተቋም ጥያቄ አነሳ፡፡ ይህ ክርክር ቀጥሎ 1987 ላይ ፈነዳ፡፡ በወቅቱ ብዙ ሰዎች ሞቱ፤ ደም ፈሰሰ፡፡ በ1988 ዓ.ም አዲስ መጅሊስ የማቋቋም ስራ ተሰራ፡፡ በሆነ መልኩ መጅሊሱ ተቋቋመ፡፡ በዚያን ግዜ መጅሊሱን እንዲመሩ የተመረጡት ሰዎች በትምህርት ከ6ኛ ክፍል ያላለፉ፤ በሃይማኖቱም እውቀት የሌላቸው ይበዙበት ነበር፡፡ መጅሊሱ ዘመናዊ አሰራር እንዲኖረው የተወሰነ ጥረት ቢኖርም ሃይማኖቱ ላይ ደካሞች ነበሩ፡፡ በህገ ደንቡ መሰረት 1992 ምርጫ ሲደረግ የቀደመው ካቢኔ እንዳለ ራሱ ቀጠለ፡፡ ህዝቡ በመጅሊሱ ላይ እምነት ስላጣ “ተቋሙን እንደፈለጋችሁ አድርጉት” ብሎ ትቷቸዋል፡፡ እስልምና ያለመጅሊስም መኖር ይችላል፡፡ ካቢኔው በሙስናና በእርስ በርስ ሽኩቻ ሲታመስ ካቢኔው እንዲወርድ ተደርጎ በሌላ ተተካ፡፡ በ1997 እና በ2002 ምርጫ መደረግ ሲገባው በካቢኔዊ እንቢተኝነት ተዘለለ፡፡ ሙስሊሙ ሁሉን ትቶት በሃይማኖተ ፀንቶ ሳለ መጅሊሱ “አህባሽ” የሚል አዲስ አስተሳሰብ ከውጭ እናመጣለን ብሎ ሲንቀሳቀስ ሙስሊሙ “በጭራሽ” አለ፡፡ “እስከዛሬም ዝምያልናችሁ ተቋሙን እንደፈለጋችሁት አድርጉት ብለን ነው፤ ሃይማኖቱን ስትነኩት ግን አንቀበላችሁም” አላቸው፡፡ ከዚያም “እንደውም እናንተ ማን ናችሁ?” ብሎ መጠየቅ ጀመረ፡፡

አሁን በስራ ላይ ያለው መጅሊስ ከመመረጡ በፊት በቦርድ ይመራና ጊዜ ተወስዶ ሁሉም የሚያምነው መጅሊስ ይቋቋም የሚል ሃሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ኮሚቴዎች ታሰሩ፡፡ ምርጫው ተካሄደ፡፡ አሁን ያለው ጥያቄ “ልጆቻችንን ፍቱ፤ ምርጫው ደግሞ ፍትሃዊ አይደለም” የሚል አዙሪት ውስጥ ነው የተገባው፡፡ ዞሮ ዞሩ ህዝቡ የማይወደውና ሃይማኖቱን የማይወክል መጅሊስ ነው የተቋቋመው፡፡ የሚል አመለካከት ነው ያለው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- የቀድሞው መጅሊስ ደካማነትን ሁሉም ቢስማማበትም አዲሱ መጅሊስም ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ የተመረጠ ስለሆነ ይፍረስና እንደገና ይገንባ የሚል ተቃውሞ አለ፡፡ ያንተ አቋም ምንድን ነው?

ሀሰን ታጁ– ምርጫው ተደርጓል፤ ባይደረግ ጥሩ ነበር፡፡ “ምርጫው ዘግይቶና በስርዓት ታስቦበት ይደረግ” ብለው ከሚያምኑትና ከተናገሩት አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ያለውን መጅሊስ በማፍረስና እንደገና እንምረጥ በሚለው አላምንበትም፡፡ ግዜና ጉልበት ነው የሚባክነው፡፡ መጅሊሱን አሁን ባለበት ሁኔታ ማስተካከል ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መጂሊስ ያለስምምነት ሊቋቋም አይችልም፡፡ የመንግስትን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ልትቃወም ትችላለህ እንጅ “ጭራሽም ወደኔ አትዙር” ልትለው አትችልም፡፡ ከመንግስት ጋር መስማማት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እስልምና አሁን ባለው ተጨባጭ አለም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ከሙስሊሙ ውጭ ያለው ወገን “ተቋሙን ያልሆኑ ሰዎች ተቆጣጠረውት ወደ መጥፎ አቅጣጫ ሊመሩት ስለሚችሉ ስጋት አለኝ” ካለ ስጋት አለው ማለት ነው፡፡ መንግስት “አክራሪ ሃይሎች እጃቸውን አስገብተው ህዝብ ሊያተራምሱ ይችላሉ” ካለ ሌላው ቀርቶ ኦርቶዶክስም “ሙስሊሞች ጎረቤቶቼ ስለሆኑና የሀገሬ ጉዳይ ስለሆነ ያሰጋኛል” ካለ ያሰጋቸዋል ማለት ነው፡፡ መሆን ያለበት “የናንተን ስጋት እንጋራለን፤ የእናንተ ስጋት የእኛም ነው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታችንን ሙሉ በሙሉ ሊወክል የሚችል፤ የእናንተን ስጋት ደግሞ ሊቀርፍ የሚችል ተቋም አንመስርት” ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በጭራሽ ለመንግስት የሚመች መጂሊስ መመስረት ማለት አይደለም፡፡ ተቋሙ የእኛ ነው፤ የሚያመጣው ጣጣ ግን ሁሉንም ነው የሚጎዳው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- “እስረኞቹ” ይፈቱ ከሚለው ጥያቄ ውጭ (እስካሁን አልተፈቱምና) ያሉትን ጥያቄ መንግስት ባለመመለሱ ነው ግጭቱ የተነሳውና ያልበረደው?

ሀሰን ታጁ– መንግስት በመርህ ደረጃ ጥያቄዎቹን መመለሱን ታሳሪዎቹ እራሳቸው አምነውበታል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- የቶቹን ጥያቄዎች?

ሀሰን ታጁ– መንግስት ሶስት ጥያቄ ቀረበለት፡፡ “መጂሊስ ይመረጥ” ተባለ፡፡ “መምረጥ ትችላላችሁ” አለ፡፡ “አወሊያ በቦርድ ይተዳደር” አለ ሙስሊሙ፤ “አህባሽ የሚባል አስተሳሰብ እየተጫነብን ነው”፤ “ሃይማኖት በሃይል መጫን አይቻልም” አለ ይህንንም ተቀብሎታል፡፡ መጅሊስ ሲመረጥ እንዴትና ማን ይሁን? የሚለው ላይ በቂ ውይይት ያስፈልግ ነበር፤ ይህ አልተደረገም፡፡

ፋክት መፅሔት፡- መንግስት የሙስሊሙን ጉዳይ ለምን በስጋት ያየዋል?

ሀሰን ታጁ– በጎረቤትና በአለም ሀገራት ላይ ያለው ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ትርምስ እኛ ሀገር እንዳይመጣ ሊሰጋ ይችላል፡፡ መንግስት ሃይማኖቱ ዉስጥ አያገባውም፤ አስተሳሰብ መጫን ላይ አያገባውም፡፡ ተቋሙን በተመለከተ ሀገር ውስጥ መጥፎ ቡቃያ እንዳይበቅል በቅርበት የመከታተል መብት ግን አለው፡፡ እዚህ ጋ ነውም ውይይቱ የሚያስፈልገው፡፡ በኦርቶዶክስ ውስጥም ቢሆን መንግስት አንዳንች ስጋት ሲሰማው ሲኖዶሱን ሰብስቦ “ይህ ነገር አስግቶኛልና አንድ ነገር አድርጉ” ማለት ይችላል፡፡ መንግስት “ካቶሊክ ሁኑ፡፡” “ሙስሊም ሁኑ፡፡” “ኦርቶዶክስ ሁኑ፡፡” ወይም ከሃይማኖቱ “ይህ አንቀፅ ወጥቶ ያኛው ይግባ” ለማለት መብት የለውም፡፡ ስጋት የሆኑ ነገሮችን ግን የማየትና የማረም መብት አለው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- አንዳንድ ሙስሊም ወዳጆቼ መንግስት የእስልምና ሃይማኖት አቅም እንዲገነባ እንደማይፈልግ ይነግሩኛል፡፡ እንደውም አንደኛው “በሌላ ሃይማኖት ያሉትን መሪዎች ስታያቸው በትምህርት የገፉ ናቸው፡፡ እኛ ጋ ግን አንደኛ ደረጃ እንኳን ያልጨረሱ ሰዎች ናቸው መሪ እንዲሆኑ የተደረገው፡፡ ይህ ደግሞ ሆን ተብሉ ነው የተደረገው” ብሎኛል፡፡ ያንተኑ አገላለፅ ልዋስና መጅሊሱ “የአላዋቂዎች መጫወቻ” ቢሆን ወይስ አዋቂዎች ቢመሩት ነው መንግስት የሚጠቀመው? (ስውር አላማ አለው ብንል እንኳን)

ሀሰን ታጁ– እኔ ግን መጅሊሱ እንዲዳከም የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ መጅሊስ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ በግለሰብ ግርማ ሞገስ ምስጋናና ታማኝነት ነው ሲመራ የነበረው፡ ፡ ግለሰቡ ሲሞቱ መጅሊሱም አብሮ ሞተ፡፡ እስልምና በኢትዮጵያ 1400 አመት ቢያስቆጥርም መጅሊሱ ከኖረው ግን ገና 50 አመቱ ነው፡፡ በግለሰብ የመንፈስ አባቶች ነው ሲመራ የነበረው፡፡ ተቋሙ ጠንካራ መሆኑ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ሃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ያስኬደዋል፡፡ ደካማ ከሆነ የሚቀበለው ስለማይኖር ህዝቡ በጎበዝ አለቆች መመራት ይጀምራል፡፡ ይህ ደግሞ ለተበታተነ ሁኔታ ያጋልጣል፡፡ የተበታተነው ሁኔታ ደግሞ እኛን ብቻ አይደለም የሚያስቸግረው፡፡ መንግስትንም ያስቸግራል፡፡ ጠንካራ መጅሊስ ከሌለ ለማስተባበር አትችልም፡፡ ኦርቶዶክስን ማስተባበር ብትፈልግ በየቤተክርስቲያኑ ትናገራለህ፡፡ በሙስሊሙ ግን ይህ የለም፡፡ ታማኝ ተቋም አለመኖሩ ለሀገርም ነው ጉዳቱ፡፡ የአወሊያ ት/ቤት ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ አይደለም፡፡ በየትምህርት ተቋማቱ የሃይማኖት አተገባበርን በተመለከተ ያለው ጉዳይም ጠንካራ መጅሊስ አለመኖሩ የፈጠረው ነው፡፡ ግለሰቦች ጠያቂና ተጋፊ ሳይሆኑ መጅሊሱ ትምህርት ሚኒስቴርን በር አንኳኩቶ፤ መንግስትን አንኳኩቶ፤ ጥናት አቅርቦ ተፈፃሚ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ግጭቶቹ አይፈጠሩም፡፡ መንግስትም ይህን ላይፈልገው አይችልም፡፡

ፋክት መፅሔት፡- “ግልፅነትና ወጥነት የሌለው የመንግስት አሰራር ያስከተለው በደል” ብለህ ያስቀመጥከውን ፈታ አድርገው እስኪ፡፡

ሀሰን ታጁ– በተለይ በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚታየው ወጥ በሆነው የዩንቨርስቲውUstaz Hasen Taju - Ethiopian author and Islamic scholar ደንብና በሃይማቱ መካከል ያለውን ድንበር ያለማስመር ችግር ነው፡፡ እንድ ሙስሊም ወደ ዩንቨርስቲ ሲገባ ሙስሊም እንደሆነ ነው፡፡ አምስት አመት ሙሉ አትስገድ ልትለው አትችልም፡፡ ኦርቶዶክሱ በሳምንት አንድ ቀን፤ ፕሮቴስታንቱም በፈለገው ቀን ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው ሊያመልኩ ይችላሉሉ፡፡ አንድ ሙስሊም ግን በቀን አምስት ግዜ መስገድ አለበት፡፡ ይህ ስርዓት ከሃይማኖቱ ጋር የተፈጠረ ነው፡፡ “አንዋር መስጊድ ሄደህ ስገድ” ልትለው አትችልም፡፡ አፍሪካ አዳራሽ ብትሄድ አዳራሹ ጥግ የመስገጃ ስፍራ አለ፡፡ ይህ ለሙስሊሙ የተዘጋጀ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም በስብሰባ ላይ ሙሉ ቀን ከዋለ አምስት ግዜ ይመላለሳል፡፡ ክርስቲያኑ ግን እሁድን ጠብቆ ቤተክርስቲያን መሄድ ይችላል፡፡ ሙስሊሞች ተማሪዎች አካባቢ ጥፋት የለም እያልኩ አይደለም፡፡ ሊኖር ይችላል፡፡ የ17 እና 18 አመት ተማሪዎች ናቸው ዩንቨርስቲ የሚገቡት፡፡ እነሱን ማረም ይቻላል፡፡ ወጥና የሚያስማማ አሰራር ቢዘረጋ ሙስሊሙ ተማሪ በዚያ እንዲተዳደር ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን ግን በየዩንቨርስቶዎቹ መሪዎች መልካም ፈቃድ ነው የሚሰራው፡፡ የየሃይማኖቱን ባህሪ ያገናዘበ ወጥ አሰራር ሊኖር ይገባል፡፡ ወጥ አሰራር ካልተዘረጋ የዛሬ 10 አመትም ችግሩ ሊያገረሽ ይችላል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መኖር አስፈላጊነትን ደጋግመህ ታነሳዋለህ፡፡ አንዳንዶች እስልምና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃ ቢሰጥ አደጋ እንደሚኖረው ይጠረጥራሉ፡፡ አለማወቅ ለየትኛቸው ወገን መፍትሄ ሊሆን ይችላል?

ሀሰን ታጁ– ይህ ብጥብጡንና ትርምሱን ለሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች ካልሆነ ለማንም አማራጭ ሊሆን አይችልም፡፡ የሃይማኖት አስተማሪዎችን ቀርፀው የሚያወጡ ዩንቨርስቲዎች ሲኖሩ ከውጭ ተምሮ የሚመጣውን ሃይል ይተኩታል፡፡ ውጭ የተማረው የውጭውን አስተሳሰብ ይዞ ይመጣል፡፡ እኔ የውጭ የሰበካ ተቋማት ለዚች ሀገር ሙሉ በሙሉ መርዝ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ የሀገራችንን እስልምናና የእስልምናውን ስርዓተ ትምህርት ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አገናዝበን መቅረፅ ያለብን ራሳችንን ነን፡፡ አለም አቀፍ ሃይማኖት ነው ያለን፤ ነገር ግን ከሀገራችን ታሪክ፤ ባህል፤ ተጨባጭ ሁኔታና የህዝብ መስተጋብር አደርጎ ነው ትምህርቱ መሰጠት ያለበት፡፡ ዩንቨርስቲው በዚህ መልኩ የሚሰራ ሆኖ በየገጠሩ ደግሞ ባህላዊ የሆኑ የእስልምና ሊቃውንትን ማጎልበትና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እነሱ ከሀገራቸው ባህል አንፃር ነው እስልምናን የሚያስተምሩት፡፡ ኢትዮጵያዊ እስልምና እንዲጎለብት ለማድረግ በዋነኝነት እኛው ሙስሊሞች፤ ቀጥሎ መንግስት ተቋሙን እስከመገንባት መድረስ አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ ሌሎች ሃይማኖቾችም ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ አለማወቅ፤ አለመማር ሲመጣ ለማንም ወገን ስጋትና አደጋ እንጅ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን ባናደርግ ሰዎችን አትማሩ ማለት ስለማይቻል ዉጭ ሄደው እየተማሩ አደጋ ይዘውብን ይመጣሉ፡፡

ፋክት መፅሔት፡- መፅሃፍህ ላይ “ሃይማኖታዊ መሰረት ያለውን ጥያቄ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ጥቅም ለማሳካት የሚጠቀሙበት ሃይላት መኖራቸው ችግሩን አወሳስቦታል” የሚል አረፍተ ነገር አለ፡፡ አሁን ካለው ተቃውሞና የተቃውሞ ተቃውሞ አለመግባባት ጀርባ ፖለቲካ አለ ልንል እንችላለን? ካለስ የማን ፖለቲካ? የመንግስት ወይስ የሃይማኖት ፖለቲካ?

ሀሰን ታጁ– መነሻ ጥያቄው ሃይማኖታዊ ቢሆንም እያደር ፖለቲካ ገብቶበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፅሁፉ ሲፃፍ ሁለት ወገኖች ተጠንተዋል፡፡ “ይቁም” ብሎ የሚያምን የምሁራንና የሊቃውንት ወገን አለ፡፡ 13 ነጥቦችን በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡ “መቀጠል አለበት” የሚሉት ደግሞ 7 ምክንያቶችን አስቀምጠዋል፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ በዚህ ሃይማኖታዊ መሰረት ያለው ትግል ውስጥ ፖለቲካ ገብቶበታል፡፡ በተለይም ዲያስፖራው አካባቢ ይህች ምክንያት ተገኝታ በዚህ ንቅናቄ መንግስትን የመጣል ፍላጎት አለ፡፡ ኢሕአዴግ ይውደቅ አይውደቅ የኔ አጀንዳ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ወደ 6 ሚሊዮን አባላት አሉት፡፡ እነሱ ያስቡለት፡፡ ግን የፈራሁት ሃይማኖቱ ውስጥ በተለይም መንግስትን የመጣል አላማ ያለው የዲያስፖራው ፖለቲካ ጣልቃ መግባቱን ነው፡፡ አንዳንድ ክርስቲያን ዲያስፖራ ፖለቲከኞች ከሙስሊሞች ጋር ተባብረው “አላህ ዋክበር” እያሉ ትግሉን ለግል መጠቀሚያቸው ሲያደርጉት ለሙስሊሙ አስበው ነው ማለት አልችልም፡፡

ፋክት መፅሔት፡- በዚህ የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ ገባ ወይስ ቀድሞውንም መነሻው ፖለቲካዊ ይዘት ነበረው ማለት ይቻላል?

ሀሰን ታጁ– ግጭትና አለመግባባቱ እንዲቆም የማይፈልጉ ሃይሎች አሉ፡፡ ጥያቄዎቹ ሁሉ በተፈለገ መጠን ቢመለሱ አለመግባባቱ እንዲቋረጥ የማይፈልጉ አሉ፡፡ ሀገር ውስጥ ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ማለት ይቻላል /ከሰማያዊ ፓርቲ እስከ አንድነት/ የሙስሊሞችን አጀንዳ የመጀመሪያ አጀንዳ አድርገው ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲን ሰላማዊ ሰልፍ ካየህ እጅግ የሚበዙት ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ የሀገሪቱ ፓርቲዎች ህጋዊ ስለሆኑ ላይቸግር ይችላል፡፡ የውጭዎቹን ግን ነገሩን የመግፋትና የማቀጣጠል እንዳይበርድ የማድረግ ፍላጎት ታይቶባቸዋል፡፡ እስረኞች እንዳይፈቱ የሚፈልጉ ወገኖችም አሉ፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ለምን?

ሀሰን ታጁ– እነሱ ከተፈቱ ሰው ቤቱ ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የማይፈልጉ አሉ፡፡ አጀንዳውን የገቢ ምንጭ አድርገው የያዙ ወገኖችም አሉ፡፡ ውጭ “ለእስረኛ ቤተሰብ”፤ “ለትግሉ” እየተባለ ከፍተኛ ገንዘብ ይዋጣል፡፡ ከኳታር፤ ከኩዌት፤ ከሳውዲ፤ ከአውሮፓም አካባቢ ገንዘብ ይዋጣል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- የተዋጣው ገንዘብ ለእስረኞች ቤተሰብ ይደርሳል?

ሀሰን ታጁ– አይመስለኝም፡፡ የእስረኞቹን ቤተሰቦችና ህይወታቸውን በቅርበት እናውቃለን፡፡ ይደርሳቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ ለአንድ ቤተሰብ 4ሺና 5ሺ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የሚዋጣውን ያህል ይደርሳቸዋል ብዬ ግን አላምንም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ወገኖች በፍፁም ግጭቱ እንዲቆም ይፈልጋሉ ብዬ አላምንም፡፡

ፋክት መፅሔት፡- መንግስት የእስላማዊ እንቅስቃሴውን ተሳታፊዎች “ጥቂት” ቢላቸውም /ደርግም ወደ 16/17 ጄነራሎችን ገድሎ ‘ጥቂት’ ነው ሲላቸው የነበረው/ በአደባባይ ተቃውሞ የሚሳተፉን በአደባባይ ያልወጡት የሂደቱ ደጋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ የፖለቲካም ሆነ ሃይማኖታዊ አጀንዳ ይዞ ኖሮ ትግሉ ግን ሁለት አመት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ በአንተ አገላለፅ ህዝበ ሙስሊሙ መንታ መንገድ ላይ ሊሆን የቻለውና ሰላም ያልሰፈነው /ቀደም ሲል የተገለፀው ምክንያት እንዳለ ሆኖ/ ጥያቄዎቹ አግባብነት ስላልነበራቸው ነው? ወይስ ከመንግስትና ከተቃዋሚ ሃይማኖተኞች አንዱ ወይም ሁለቱም የገረረ አቋም በመያዛቸው ነው?

ሀሰን ታጁ– መደማመጡ ስለሌለ ነው የሚመስለኝ፡፡ ጥያቄዎቹ ትክክል ናቸው ግን ቀላል ናቸው፡፡ ይህን ያህል መስዋዕትነት የሚያስከፍሉ አይደሉም፡፡ እንደውም ለመንግስት የሚከብዱ ትልልቅ የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚያነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ግን ቀላል ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አወሊያ አንድ ትምህርት ቤት ነው፡ በቦርድ ይተዳደር፤ አይተዳደር መንግስትን የሚያሳስበው ሊሆን አይችልም፡፡ ቀላል ነገሮችን በቀላሉ የመፍታት ችግር ነው የገጠመን፡፡ የቀረቡት ጥያቄዎች በመርህ ደረጃ መመለሳቸውን የታሰሩ የኮሚቴ አባላትም አምነዋል፡፡ መንግስት በመርህ ደረጃ የተቀበለውን ወደ ተግባር እንዲለውጠው ማድረግ ደግሞ ከውይይት አልፎ ይህን ያህል ዋጋ ሊያስከፍል የሚገባው ሊሆን አይገባም፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ጥያቄዎቹ በቀዳሚነት ወደ መንግስት መሄድ ለምን አስፈለጋቸው? ደካማም ቢሆን መጅሊሱ እያለ እንዴት መንግስትና ሙስሊሙ ፍጥጫ ዉስጥ ሊገቡ ቻሉ?

ሀሰን ታጁ– መንግስት አቤቱታ ተቀባይ ነው የነበረው እንጂ በቀጥታ እሱን የሚመለከት አይደለም፡፡ “መጅሊስ የሚባለው ተቋም በድሎናልና እንደ አዲስ ማደራጀት እንፈልጋለን” የሚል ጥያቄ ነው የቀረበው፡፡ መንግስት ተከሳሽ አልነበረም፡፡ ለጥያቄው በሰጠው መልስ አለመግባባት ተፈጥሮ ነው “እንደውም መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል” የተባለው፡፡ ከዚያ ፀቡ በመጅሊስና በኮሚቴው መሃል መሆኑ ቀርቶ መጅሊሱ ራሱን አግልሎ የመንግስትና የኮሚቴው ፀብ ሆነ፡፡

ፋክት መፅሔት፡- በመፅሃፍህ የመፍትሄ ጥቆማ ላይ “የታሳሪዎቹን ጉዳይ በፖለቲካዊ አግባብ ማየት” የሚል ሀሳብ ተነስቷል፡፡ ለምን በህግ አግባብ አላልክም? ፖለቲካው እንዴት ከህጉ የቀለለ መፍትሄ ሆነ?

ሀሰን ታጁ– ታሳሪዎቹ በሽብርተኝነት ተከሰዋል፡፡ ሁለት እድል ነው ያላቸው፡፡ አንዱ ነፃ ናችሁ መባል ነው፤ ይህ ከሆነ ተገላገልን፡፡ በ1987 የታሰሩ የሙስሊም መሪዎች ከሶስት አመት በኋላ “ነፃ ናችሁ” ብሎ ፍርድ ቤቱ አሰናብቷቸዋል፡፡ እንደያኔው ሁሉ የአሁኑም ፍርድ ቤት በነፃ ካሰናበታቸው እሰየው፡፡ ካቀረበው ክስ ክብደትና በየሚዲያው ከሚተላለፈው ዘገባ ድምፅ የምትረዳው ግን ፍርድ ቤቱ በነፃ ካላሰናበታቸው ከባድ ክስ ነው፡፡ የሚቀረው የእርቅና የይቅርታ አማራጭ ነው፡፡ የይቅርታና እርቅ አማራጭ መውሰድን ነው ፖለቲካዊ አማራጭ ያደረኩት፡፡

ፋክት መፅሔት፡- እኮ “በህግና በፖለቲካ አግባብ” ማለቱ አይሻልም? ነው ወይስ በህጉ ላይ ተስፋ ስለሌለህ ነው አንደኛውን ፖለቲካውን አማራጭ ያደረከው?

ሀሰን ታጁ– ህግ ምንም ይበል ምን ከህግ በላይ በአባታዊው /በፖለቲካው/ መንገድ እንዲታይ ነው፡፡ በመንግስት የታሰሩት ልጆች ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት 4 ወራት ነበሩ፡፡ የማግባባት መስመሩ ቢኖር መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ግን መንግስት ህግ የሚሰጠውን መብት ተጠቅሞ በፖለቲካ አይን ጉዳዩን እንዲያይ ማድረግ የሚገባ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የያዘውን ጉዳይ በአመፅ ለማስጨረስ ማሰብ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ዳኞች ነፃነት ኖሯቸው ሲፈርዱ እንጂ “ሙስሊሞቹ ላይ ብፈርድ አመፅ ይነሳብኛል” ወይም “ለእነሱ ብፈርድባቸው መንግስት ይጎዳኛል፡፡” ብለው ማሰብ የለባቸውም፡፡ ነፃነቱ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ይገባል ላይ የማይስማማ ያለ አይመስለኝም፡፡ ጥያቄው ግን ነፃ ናቸው ወይ? ነው፡፡ ባለፉት 22 አመታት ፍርድ ቤቶች መንግስት ወደ ህግ ከወሰዳው ትላልቅ የፖለቲካ ጉዳዮች በተቃራኒው ፈርደው መንግስት ተሸንፎና ግለሰቦች አሸንፈው የተዘጋ ፋይል አለ ወይ? ጥያቄው ይህ ነው፡፡

ሀሰን ታጁ– ፍርድ ቤት ላይ የሚኖርህ እምነት አንፃራዊ ነው፡፡ እንደ ህዝብ የሚያዋጣን የፍትህ አካሉን ማመን ነው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- እየተሳሳተና ለመንግስት አድሎ እየፈፀመም ቢሆን?

ሀሰን ታጁ– መጠገንና ታማኝ እንዲሆን ማድረግ ነው የሚሻለን፡፡ ሰዎችን በማሰልጠን፤ የአስፈፃሚው አካል ፖለቲካዊ ጫና እንዲገደብና የፍትህ አካሉ ነፃ እንዲሆን ማድረግ ነው የሚሻለው እንጅ አለማመን ጉዳት ነው ያለው፡፡ ስለዚህ በልባችን ትናንሽ ጥርጣሬዎች ቢኖሩም መቀበሉ ነው የሚሻለን፡፡ የሚፈርደውን ባይቀበሉት እስከ ሰበር ድረስ ይሄዳሉ፡፡ በመጨረሻ ግን ወደ ድርደር ነው የሚሄደው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- መቼም አንድ ቀን ፍርድ መስጠቱ አይቀርም፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ በእርቅና ይቅርታ ያልቃል የሚል ተስፋ አለህ?

ሀሰን ታጁ– ይመስለኛል፡፡ መንግስት ከአንድ ኮሚቴ ጋር የመበቃቀል ስራ ውስጥ መግባት አይጠበቅበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገሮች ከሰከኑ በኋላ መንግስት ሆደ ሰፊነት ያጣል ብዬ አላምንም፡፡ በተጀመረው ግብግብ ብንቀጥል ግን ጥያቄዎቻችንን እናጣለን፤ ኮሚቴዎቻችንን እናጣለን፤ ህይወት እናጣለን፤ ክርስቲያን-ሙስሊም ግንኙነት ጋር አደጋ ይፈጠራል፡፡ እኔን የሚያሰጋኝ እሱ ነው፡፡ ይሄ “አክራሪነት”ና “የመቻቻልና የሃይማኖት ጉባዔ” የሚባል ነገር ባይመጣ በጣም ነበር የምመኘው፡፡ ክርስቲያኑ ወገን “ሙስሊሞቹ አክራሪ የመሆን አቅም አላቸው” ብሎ ሊጠረጥርህ አይገባም፡፡ ነገሩ ተደጋግሞ ሲነገር ክርስቲያኑ ይሰጋል፡፡ ወደ መንግስት የሚወረወሩትና መንግስትም የሚሰጠው ምላሽ ግንኙነቱን እንዳያጠለሹት እሰጋለሁ፡፡ ሰው በሃይማኖት ባይቧደን ይበጀናል፡፡ በብሄር መቧደን በራሱ ብዙ ጣጣ አምጥቶብናል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- አሁን ያለው ያለመግባባት የሙስሊሙና መንግስት ይሁን እንጅ ስጋቱ ውስጥ ክርስቲያኑም አለበት፡፡ አንዳንድ ለክርስቲያኑ እናስባለን የሚሉ ወገኖች ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረ ገፆች በቃላት ትንኮሳ የግጭት ክብሪት እየለኮሱ ይገኛሉ፡፡ የሙስሊሙ ወገን እንዳለ ሆኖ ክርስቲያኖቹ ይህን ግዜ በሰላም ለማለፍና ቀጣዩን ግዜ የተሸለ ለማድረግ ምን ይጠበቅባቸዋል?

ሀሰን ታጁ– ነገሩ በቀላል እንዲፈታ የክርስቲያኑም ወገን እገዛ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የራሳችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንዲኖረን የክርስቲያኑ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ክርስቲያን ስንል መንግስትና አስፈፃሚው አካል ላይ ያሉትንም ማለታችን ነው፡፡ የሙስሊሞችን ችግር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሙስሊሞች ዩንቨርስቲ ውስጥ “እንሰግዳለን” ሲሉ ለመበጥበጥ ፈልገው አይደለም፡፡ አንዲት ሴት “ሂጃብ አለብሳለሁ” ስትል አክራሪ ስለሆነች ወይም መበጥበጥ ስለፈለገች አይደለም፡፡ የሚያጠፉ ልጆች የሉም እያልኩ አይደለም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ስለመቻቻል ተሸነጋግለው ነው የሚሄዱት፡፡ ኦርቶዶክሱ፤ ሙስሊሙ፤ ፕሮቴስታንቱ በጋራ የሚያሳትሙት መፅኃፍ፤ የጋራ ፕሮግራም ቢኖራቸው እመርጣለሁ፡፡ እምነቶቹን ማቀላቀል ማለት አይደለም፡፡ በሀገር ፍቅር፤ በልማት ዙሪያ የጋራ አጀንዳ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- የክርስቲያን ሙስሊም ግንኙነት ላይ ሁለት ፅንፎች ይታዩኛል፡፡ በአንድ በኩል በሰላምና በፍቅር ያለኮሽታ ኖረው አሁን ግንኙነቱ እንደፈረሰ አድርጎ ማቅረብ አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለአመታት ሳይነገሩ የቆዩ ነገር ግን በታሪክም የተመዘገቡ አለመግባባቶች ኖረው አሁን ከግዜው አንፃር በግልፅ መነገራቸው ነው አዲስ ያስመሰለው የሚሉ አሉ፡፡ ከእድሜህ እጥፍ በላይ የሃይማኖት መፅሃፍትን እንደፃፈና የሃይማኖት ታሪክ ድርሳናትን እንዳገላበጠ ሆነህ ስታስበው አንተ ከየቱ ወገን ትቆማለህ? /የሃይማኖት መንገዳችን ነፃና ወለል ያለ ነበር?/

ሀሰን ታጁ– የመቻቻል ታሪክ ብዙ ግዜ ከእውነቱ ይልቅ ተረቱ ይበዛል፡፡ በታሪካችን ውስጥ ጥሩም መጥፎም ታሪኮች ነበሩ፡፡ ዋናው ነገር ምን መሰለህ? በታሪክ ውሥጥ እኔ የአህመድ ግራኝ ታሪክ ወራሽ፤ አንተም የዘረያዕቆብ ታሪክ ወራሽ አይደለንም፡፡ የሚበጀው ነገር ጥሩውን ጎን አድንቀን መጥፎውን ማመን ነው፡፡ ሙስሊሙ ላይ በታሪክ ውስጥ የሚያሙ ድርጊቶች ተፈፅመዋል፡፡ አልተጨቆንክም ብትለው ህመሙ አይድንም፡፡ እኔ ጎንደር ነው የተወለድኩት፡፡ ጎንደር አዲስ አለም የሚባል ቦታ አለ፡፡ ሙስሊሞች ከከተማው እንዲወጡ የተደረገበት ወቅት ነበር፡፡ እዛ የነበረውን ችግር አያቴ ትነግረኛለች፡፡ “ለሊት መስገድ አንችልም፤ መብራት አብርተን መብላት፤ መፆም አንችልም፡፡ መብራት አጥፉ እንባላለን፡፡ መቁጠሪያ ስንስብ ቀጭ ቀጭ የሚለውን ድምፅ በጆሯቸው እየሰሙ ይቀጡን ነበር፡፡” ትለኛለች፡፡ በታሪክ ውስጥ የተዛቡ ግንኙነት ነበሩ፡፡ ጥፋቱን ግን እኔም አንተም አንወርሰውም፡፡ አባቶቻችን ዘመናቸውን መሰረት አድርገው የሰሩት ጥፋት ነው፡፡ ይህ ላለመደገሙ ሁላችንም መተማመንና ቃል መግባት አለብን፡፡ አለበለዚያ “ያለፈው ዘመን ጥሩና ወርቃማ ነው” ካልክ “እድሉን ካገኘሁ እደግመዋለሁ” እንዳልከኝ ነው የምቆጥረው፡፡ ያለፈውን ማመንና በግልፅ ማውገዝ ነው የሚበጀን፡፡ ይህ ትውልድ የራሱን ህይወትና ኑሮ መኖር ያለበት፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ሃይማኖት ሙሉ መሰረቱ እምነት ብቻ ስላልሆነ መሰለኝ ወገንተኝነት፤ አድሏዊነትና ፅንፈኝነት ይታይበታል፡፡ ብዙ ክርስቲያን ወገኖቼ “አሊ አብዶ ለሙስሊሞች መሬት ሰጥተው ብዙ መስጊድ እንዲሰራ አድርገዋል” ብለው ይኮንኗቸዋል፡፡ እነዚሁ ወገኖች የማይወዷቸው ጳጳስ አቡነ ጳውሎስ ሙስሊሞችን የሚጎዳና የቤተክርስቲያኒቱን ተከታይ “የሚጠቅም” ተግባር ቢፈፅሙ ግን አያወግዟቸውም፡፡ ከሙስሊም ወገኖቼም የአህመድ ግራኝን ድርጊት በግልፅ የሚያወግዙ አልገጠመኝም፡፡ /ከሁለቱም ወገን ጭራሽ የሉም ማለት ግን አይደለም/ ይህ ፅንፈኝነት የት ያደርሰናል? ምኑስ ላይ ነው በተሸፋፈነ የታሪክ መደብ ላይ ተቀምጠን መቻቻላችን?

ሀሰን ታጁ– መቻቻል ካለ ግን ይህን አመነንና ቆሻሻችንን አራግፈን መሆን አለበት፡፡ መቻቻልና ማስመሰል ተደበላልቆብናል፡፡ መቻቻል ማለት እኔም እንደ እምነቴ፤ አንተም እንደ እምነትህ እየኖርን በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በጋራ መስራት ማለት ነው፡፡ ስለመቻቻል ሲነሳ “ሙስሊሙ ታቦት ይሸኝ ነበር” ይባላል፡፡ ታቦት መሸኘት እኮ በእስልምና ጥፋት ነው፡፡ ወንጀል ነው፡፡ “አብረን ማህበር እንጠጣ ነበር” ይሉሃል፡፡ ጠጁን፤ ጠላውን አብረህ መጠጣት እኮ ለሙስሊሙ መመሳሰል እንጅ መቻቻል አይደለም፡፡ ታቦት መሸኘቱ፤ ጠላና ጠጅ አብሮ መጠጣቱ አሁን ቀረ ሲባል “ስላከረሩ” ይባላል፡፡ መቻቻል ደፈረሰ ማለት ነው፡፡ ሳትሸነጋገር የምር ተነጋግረህ፤ በታሪክ ውስጥ ያሉ ስህተቶች ታርመው፤ የእኛ ጥፋት እንዳልሆነ አምነን መጣልና አዲስ ታሪክ መመስረት ነው የሚሻለን፡፡

ፋክት መፅሔት፡- በመንግስት ወገን በተለይም ከተወሰኑ ግዜያት ወዲህ “አክራሪዎች” ሲባል ተደጋግሞ ይደመጣል፡፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሃይማኖት አክራሪነት አለ ብለህ ታምናለህ?

ሀሰን ታጁ– ምን ማለት ነው አክራሪነት? እሱን ቅድሚያ መፍታት ያስፈልጋል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- እንፍታዋ?

ሀሰን ታጁ– በመንግስት ፍቺ መሰረት ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው፡፡ የተለያዩ መሆናቸውን የማይቀበል፤ ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገር መሆን የማይቀበል፤ በሀገሪቱ መንግስታዊ ሃይማኖት ያለመኖሩንና ሊኖርም የማይችል መሆኑን የማይቀበል ነው አክራሪ የሚባለው፡፡ በዚህ ትርጉም መሰረት ከሄድን ኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ኢትዮጵያን እስላማዊ አክራሪነት አያሰጋትም፡፡ ከሚሊዮን አንድ የሚቃዥ ሊኖር ይችላል፡፡ አንድ ሀገርና አንደ ሃይማኖት እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለ700 አመታት በክርስቲያን መንግስት ነው ስትተዳደር የነበረው፡፡ ስለሆነም ካሰጋትም የክርስቲያን አክራሪነት ነው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- “አክራሪነት” የምንለው በኢትዮጵያ ቀርቶ በአለለምስ ላይ አለ? /የሙስሊሙ አለም ምዕራባዊያን በሙስሊሙ ላይ የጫኑት ስያሜ ነው ብለው ነው የሚረዱትና/

ሀሰን ታጁ– የምዕራቡና የሙስሊሙ አለም ኢኮኖሚ በለው፤ ባህልም በለው፤ ስልጣኔም በለው ጠብ አለ፡፡ ምዕራቡ አለም አጀንዳውን በአለም ላይ መጫን ይችላል፡፡ ምዕራቡና ሙስሊሙ አለም በነዳጅም ይሁን በሌላ ጭቅጭቅ አላቸው፡፡ የራሳቸውን አጀንዳ ወደሌላው መጫን ይመስለኛል “አክራሪነት” የሚለውን ቃል የፈጠረው፡፡ በነገራችን ላይ “አክራሪነትን መዋጋት” አትራፊ ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡ ልክ እንደ ኤች አይ ቪ፤ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ብር በጣም ያስገኛል፡፡ አንዳንድ ግዜ ለትርፍ ተብሎ የሚሰራ ስራም አለ፡፡ “አክራሪነት”ና “ሽብርተኝነት” የሚሉት ቃላት ወጥ በሆነ መልኩ ትርጉም የላቸውም፡፡ ሁሉም ወገን ለፈለገው አላማ ያውለዋል፡፡ እኔ ቃሉን ራሱ መጠቀም አግባብ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ በአለም ላይ ምዕራቡ አለም “አክራሪነት ማለት እስልምና ነው” ብሎ ስላሳመነ አክራሪ ስትል ሰው ትዝ የሚለው እስልምና ራሱ ነው፡፡ ቃሉ ራሱ ባይጠቀስ እመርጣለሁ፡፡ የተወሰኑ ሰዎችም ተሰብስበው “ሃይማኖታዊ መንግስት እንመሰርታለን” ካሉ ክርስቲያንም ይሁን ሙስሊም በህገ መንግስት ጥሰት ነው መከሰስ ያለባቸው፡፡ ከውጭ መንግስት ጋር ከተባበሩ ደግሞ በሀገር ክህደት ነው አንቀፅ ሊጠቀስባቸው የሚገባው እንጂ ሃይማኖታዊ አንደምታ ያለውን ቃል መጠቀም ተገቢነት የለውም፡፡

ፋክት መፅሔት፡- የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 11 የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት በሚለው ርዕስ ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ይላል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ደግሞ አንዱ በሌላው ዉስጥ ጣልቃ እንደገባ አድርገው እየተካሰሱ ነው፡፡ ባንተ አረዳድ ማነው በማን ውስጥ ጣልቃ የገባው?

ሀሰን ታጁ– ሁለቱም ገብተዋል ብዬ አላምንም፡፡ አለመግባባት ነው የተፈጠረው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ “እስላማዊ መንግስት ይመስረት” ብሎ የጠየቀ የለም፡፡ መንግስትም ይህን የሃይማኖታችሁን አንቀፅ አሻሽሉ ወይም በዚህ ተመሩ አላለም፡፡ የተሰበረ የግንኙነት ድልድይ አለ፡፡ አለመግባባቱ በውይይት ሊፈታ የሚችል ነው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ከመፅሃፉ ወጣ ብለን ጥቂት መዝጊያ ጥያቄዎችን እናንሳ፡፡ አንተ ለውይይት የቀረበ ብለህ በወረቀትና በፌስቡክ የለቀቅከው ፅኁፍ ሃሳብ የተመለከቱ ሰዎች በርካታ ተቃውሞ አሰምተውብሃል፡፡ ለዚህ ቃለ መጠይቅ ያነጋገርኳቸው ስድስት ሙስሊሞች ሁሉንም መንገድህን ተቃውመውታል፡፡ “ሀሰን ለኢሕአዴግ አድሮ ትግሉን ሊያሰናክል እየሞከረ ነው” ያሉኝ አሉ፡፡ አንድ ሙስሊም ወዳጄ ደግሞ “ሀሰን ብዙ እስላማዊ መፅሃፍትን ስለሚያሳትም ከመንግስት ተቀያይሞ ገቢው እንዳይጎድል ነው” ብሎኛል፡፡ ሌሎችም ሌላ ብለውኛል፡፡ ኡስታዝ ሀሰን ታጁ የቱ ጋር ነህ?

ሀሰን ታጁ– ጥያቄዎቹን በስርዓት ላያቸው መንግስትን የሚወቅሱ ናቸው፡፡ ከህዝቡ የበለጠ መንግስትን ነው የሚጫነው፡፡ “ተአማኒነት ያለው ተቋም የለንም”፤ “ወጥ አሰራር የለም”፤ “የሃይማኖት አስተዳደር አያያዙ ጉድለት አለው” ማለት መንግስትን ነው የሚጫነው፡፡ ተቃውሞው አለ፡፡ በፍርሃት እውነትን የመደበቅ ልማድ የለኝም፡፡ ከአሁን ቀደም ትክክል ያልመሰለኝና ሙስሊሙን ህብረተሰብ ግን ለግዜው ሊያስቆጣ የሚችል ሶስት አራት ፅሁፎችን ፅፌያለሁ፡፡ ይህን መፅሃፍ በተመለከትም ገና ሳያነቡት የተቃወሙት ብዙ ሰዎች ካነበቡ በኋላ እየደወሉ ይቅርታ ይጠይቁኛል፡፡ እኛ ሀገር ችግሩ እውነቱን ራስህ አንብበህና ሰምተህ ከማረጋገጥ ይልቅ በሰሚ ሰሚ ማመን አለ፡፡ ብዙዎች ሙሉውን ሀሳብ ሳይረዱት ነው የሚቃወሙኝ፡፡ አይቃወሙኝ እያልኩ ግን አይደለም፡፡ አንዳንዶች “እንቅስቃሴው ሙሉ በሙሉ ይቁም ብሏል” ብለው አምርረው ከጠሉኝ በኋላ ፅሁፉን አንብበው ግን እንደውም ወደ እንቅስቃሴው ወግኗል ነው የሚሉት፡፡ ፅኁፉ እንቅስቃሴው ይቁም ሳይሆን የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ራሱን ወደ ጥሩ አቅጣጫ እንዲያመራ ነው የጋራ አማራጭ ያቀረበው፡፡ በጋራ አማራጭነት ያቀረብናቸው ሶስት ሀሳቦች “ለግጭትና ደም መፋሰስ የሚያበቁ ጉዳዮች ስለማይበጀን አቁሙ፤ የህዝባችንን ሙቀትና ስሜት ጠብቁ፡፡ ያለውን የህዝብ ጉልበት ወደሚጠቅም አቅጣጫ /ወደ ልማቱ፤ ወደ ትምህርቱ/ አስፋፉት፡፡ በግብ ግብ ህዝቡን አታድክሙት” የሚል ነው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ይህ ሃሳብ ተቀባይነት ያጣውስ በምን ምክንያት ይመስልሃል?

ሀሰን ታጁ– በስሜት ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም ሀሳቡን ካቀረብን ከ6 ወር በኋላ እኛ ያልነውን ነው እየፈፀሙ ያሉት፡፡ እኛ በሰላሙ ግዜ ያልነውን ደም ከፈሰሰ በኋላ “ላልተወሰነ ግዜ አቁመንዋል” ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳ እኔ ወዳልኩት ሀሳቤ መጥተዋል፡፡ ግን ብዙ ነገሮች ከተበላሹ በኋላ ነው፡፡

ፋክት መፅሔት፡- አንድ ወዳጄ እንደውም “ሀሰን በርካታ መፃህፍትን እንደተረጎመዉ ህዝቡን መተርጎም አልቻለም” ብሎኛል፡፡ አባባሉ ምን ትርጉም ይሰጥሃል?

ሀሰን ታጁ– ምንም፡፡ እኔ ህዝባችንን በጣም ነው የማውቀው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወጣቱን፤ የታሰሩትን የኮሚቴ አባላት ወንድሞቼንና እንቅስቃሴውንም አውቀዋለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በቅርበት ስለምከታተለው ማለት ነው፡፡ ሰው ስሜታዊ ነው፡፡ ብዙው ሰው ነገሩን መርምሮና ጥቅምና ጉዳቱን ለይቶ ሳይሆን በስሜት ነው የሚነዳው፡፡ ስሜት ጥሩ ሆኖ ግራ ቀኙን ማየት ግን ያስፈልጋል፡፡ ስሜት፤ ቁጭት፤ እልህ የሚባሉት ነገሮች አስተሳሰብህን ከሸፈኑት እንደ አደንዛዥ እፅ ናቸው ያሰክሩሃል፡፡ የእንቅስቃሴው ሌላ አደጋ በሚስጥር እየተመራ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ሚስጥራዊ እንቅስቃሴው መሃል ላይ ተጠልፎ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፡፡ በውጭው አለም የአልቃይዳም ሆነ ሌላ እንቅስቃሴ በሚስጢር ስለሚሰሩ የተጠለፉና የደህንነት መጫወቻ የሆኑ ናቸው፡፡ ሌላ አላማ ያለው ወገን ወደፈለገው አቅጣጫ ሊወስደውና ሊያሾረው ይችላል፡፡ የቴክኖሎጂ ነገር ስለሆነ አንድ ወገን /መንግስት ማለቴ አይደለም/ ጠልፎት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሊነዳው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ አደገኛ ነው፡

ፋክት መፅሔት፡- ሀሰን አሁን ከታሰሩት ኮሚቴዎች ጋር ተመርጦ አብሯቸው ጥቂት ከተጓዘ በኋላ ራሱን አግልሏል የሚሉና ይህን ማግለልህን በጥርጣሬ ያዩት አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ከሰነዘርካቸው የተለያዩ አስተያየቶች ጋር በመደመር ደግሞ ይበልጥ ጥርጣሬያቸው ፋፍቶ ሀሰን ከሙስሊሙ የተለየ አጀንዳ አለው የሚሉህም አሉ፡፡ ምን ምላሽ አለህ?

ሀሰን ታጁ– በመጀመሪያ ሃያ አባላት ያሉት ኮሚቴ ሲመረጥ አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ሃያዎቻችንም ወጣቶችን ስለነበርን “ይህ ትክክል አይደለም፤ ሽማግሌዎችም ይግቡበት” የሚል ጥያቄ አቀረብን፡፡ ሀሳባችን ተቀባይነት አግኝቶ 12 ሽማግሌዎችና 5 ወጣቶች ሲመረጡ ከቀሩት መሃል እኔ ነበርኩ፡፡ ከዚያም ከኮሚቴ አባልነት ብንወጣም ኮሚቴዎቹ እስከታሰሩ ድረስ አብረን ነበርን፡፡ መገለል ሳይሆን ከኮሚቴው ሳንርቅ ብዙ ውይይቶች እናደርግ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹ ተገቢ ቢሆኑም በአፈፃፀም ላይ ልዩነት ስላመጣን ልንለያይ ችለናል፡፡

ፋክት መፅሔት፡- አንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን አንተን ጠርተው “እናንተ ናችሁ በርካታ መፅኃፍትን እያሳተማችሁ ወጣቱን ወደዚህ እንቅስቃሴ እንዲገባ ያደረጋችሁት” ብለው አነጋግረውሃል እንዴ? /በዚህ ነው እነ ሀሰን ወደ ኋላ የተመለሱት የሚሉ አሉ፡፡/

ሀሰን ታጁ– በፍፁም! ኮሚቴዎቹ ከመታሰራቸው በፊት ዶ/ር ኢድሪስ ያለበት የሽምግልና ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ከዚያ በኋላ ዶ/ር ኢድሪስ “ኮሚቴዎቹ የስነ ስርዓትና የአፈፃፀም ጉድለት አለባቸው እንጅ አላማቸውና ጥያቄያቸው ተገቢ ነው” ብሎ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ካሁን ቀደም ካንተ ጋር ያደረግነው ቃለ መጠይቅ እኮ ኮሚቴዎቹ የታሰሩ ቀን ነው የወጣው፡፡ ከባድ ኢንተርቪው ነበረ፡፡ ማንም አናግሮኝ ሳይሆን የሚታየው እውነት መርቶኝ ነው ሁሉንም ያደረኩት፡፡

ፋክት መፅሔት፡- ይህ የዛሬው ቃለ መጠይቃችንም እንዳለፈው ሁሉ ብዙዎችን ላያስደስት ይችላል፡፡ በዚሀ ምን ይሰማሃል?

ሀሰን ታጁ– የእስልምና ሃይማኖት “ሰውን ለማስደሰት ብለህ ምንም ነገር አትስራ” ነው የሚለው፡፡ ቢደሰት ጥሩ ነው፡፡ ግን የሰው መደሰትና አለመደሰት ሀሳብህ ላይ ጫና ባያሳድርብህ የበለጠ ጥሩ ነው፡፡ ረጋ ብለው ያነበቡ ሰዎች ይደሰቱበታል ብዬ አምናለሁ፡፡

***********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories