ሰማያዊ ፓርቲ 250 ገደማ ሰዎች የተገኙበት ሰልፍ አካሄደ

(በታደሰ ብዙ አለም)

ፓርቲው በጃን ሜዳ ሰለማዊ ሰልፉን እንዲያካሂድ ቢፈቀድለትም ስፍራውን በመተው የፖርቲው ፅህፈት ቤት አድራሻ ባለበት የግንፍሌ አካባቢ ነው ያካሄደው።

በሰልፉ ላይ በግምት ከ220 እስከ 250 የሚደርሱ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ፥ የታሰሩ እስረኞች ይፈቱ ፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይግባ የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል።

የፓርቲው ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንደሚሉት ፥ ፓርቲያቸው መጀመሪያ ለከተማ አስተዳደሩ በፃፈው የማሳወቂያ ደብዳቤ ሰልፉን በመስቀል አደባባይ እንደሚያደርግ ነው።

ሆኖም አስተዳደሩ ፓርቲያቸው ሳያውቀው ሰልፉን ወደ ጃን ሜዳ እንደቀየረባቸው ነው የሚናገሩት።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ግን ፓርቲው ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የማሳወቂያ ደብዳቤ ባስገባበት ዕለት የሰልፉ ቦታ በጃን ሜዳ እንደሚሆን ምክንያቱ ተጠቅሶ ተነግሮታል ብለዋል።

መስቀል አደባባይ አሁን እየተካሄደበት ካለው የባቡር መስመር ዝርጋታና ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር በተያያዘ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያካሄድበት መፍቀድ ተገቢ ነው ተብሎ በአስተዳደሩ እንዳልታመነበት አቶ አባተ የገለጹት።

ሰማያዊ ፓርቲም ሰልፉን በመስቀል አደባባይ ለማድረግ ጥያቄ ሲያቀርብ መልሱ ከነበቂ ምከንያቱ ቢገለጸለትም ፓርቲው ሆን ብሎ ተጨባጨ ያልሆነ የተዛባ መረጃ እያሰራጨ እንደሆነም ነው የተናገሩት

አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ እየታየ ፓርቲው መንገድ በመዝጋትና ትራፊክ በማጨናነቅ አጃቢ ለማግኘት ከማለም የተነሳ መስቀል አደባባይ አልተፈቀደለኝም የሚል ክስ እያስተጋባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

**********

Source: Fana – Sept. 22. 2013

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories