Brief: የርዕዮት ዓለሙ የ‹ረሀብ ዐድማ›

(Daniel Berhane)

ከትላንት በስቲያ – የዘመን መለወጫ ዕለት – ጀምሮ በፌስቡክና ትዊተር <<ርዕዮት ዓለሙ የረሀብ ዐድማ ጀመረች>> የሚል ዜና ሲሰማ ቆይቷል፡፡

ስለሁኔታው የማረሚያ ቤት አስተዳደርን ዛሬ በስልክ ጠይቄ ‹‹ከውጭ የሚመጣላትን ምግብ እየተቀበለች ነው›› ብለውኛል፡፡ በራሴ ላረጋግጥ የምችልበት መንገድ የለም፡፡

ለረሀብ አድማው መነሻ የተባለው፡- ማረሚያ ቤቱ ሰሞኑን በርዕዮት ላይ የጣለው ዕግድ ነው፡፡ ከአባቷ፣ እናቷ እና የንስሀ አባቷ ውጭ ጠያቂ እንዳታገኝ መከልከሏ፡፡

ያነጋገረኝን የማረሚያ ቤት አስተዳደር ሀላፊ፡- ‹‹ለምን ጎብኝዎች ላይ ገደብ አደረጋችሁ›› ብዬ ጠይቄያቸው ነበር፡፡

ጉዳዩን ሳያምንም ሳይክድም (ያመነ ይመስላል)፡- ‹‹ማረሚያ ቤቱ ሕግን አልጣሰም፣ በታራሚዎች ላይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ የመውሰድ የሕግ ስልጣን አለው›› አሉኝ፡፡

የወንጀል ሕጉን፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጅንና ደንብን ይዘትና መንፈስ ስለማውቀው (ከሥር ተመልከቱ) በዚያ ላይ ሳልከራከር፣ በድፍኑ፡- ‹‹ሕጎቹ ጥቅል ናቸው- ማስፈፀሚያ ደንብ ወይንም መመሪያ አላችሁ ወይ›› ብዬ ጠየቅሁ፡፡

በሕጉ በግልጽ ያልተቀመጡ መብቶችን በተመለከተም ቢሆን እንኳን ‹አንድን ታራሚ ከሌላ ታራሚ በተለየ ለማስተናገድ ግልጽ አሠራር ያስፈልጋል› በሚል ዕሳቤ ያነሳሁት ጥያቄ ነበር፡፡

‹‹አዎ ማረሚያ ቤቱ የውስጥ መመሪያ አለው – ያን ተከትለን ነው የምንሠራው›› አለኝ፡፡

በስልክ ከዚህ በላይ መረጃ መጠየቅ አዳጋች ስለሆነ አመስግኜ ተሰናበትኩ፡፡ (እንደአስፈላጊነቱና ከተባበሩኝ ዝርዝር መረጃዎችን – ለሌላም ግዜ እንዲሆን – ሰኞ በአካል እጠይቃለሁ)

ሌላው ተያይዞ የሚወራው ወሬ፡- በቅርቡ በሙስና ተጠርጥረው የታሠሩት ወ/ሮ ሀይማኖት እየዛቱባት በፍርሀት ውስጥ ትገኛለች የሚል ነው፡፡ አንድ ዕድሜያቸው በ40ዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኙ፣ ባለትዳርና የልጆች እናት – እንዴት ለአንዲት ወጣት ስጋት እንደሚሆኑ ስላልተዋጠልኝ፤ ጥያቄውን አንስቼ ራሴን ማስገመት ስላልፈለግሁ አልፌዋለሁ፡፡

በነገራችን ላይ፡- አንዳንድ ሰዎች ትንሽ የተምታታባቸው ይመስላል፡፡ የረሀብ አቆም አድማ ማለትኮ አድመኛው ‹‹ምግብ አልበላም›› አለ/ች ማለት እንጂ ‹‹ምግብ ተከለከለ›› ማለት አይደለም፡፡

እንደሚባለው ርዕዮት ዓለሙ የረሀብ አድማ መትታ ከሆነ፤ ተቃዋሚዎች ለመንግስት ማለት ያለባቸው ‹‹እረ እቺ ልጅ እንዳትሞትባችሁ ጥያቄዎቿን ፈጽሙላት›› እንጂ ‹‹መንግስት በረሀብ ሊገላት ነው›› አይደለም፡፡

ለማንኛውም አዲስ መረጃ ሲገኝ እንአግባቡ አቀርብላችኋለሁ፡፡

********

Daniel Berhane

more recommended stories