በትግራይ የጥቁር ሰው ምስል ያለበት የ6ኛ ዘመን ቅርስ ተገኘ

በትግራይ ክልል ሃውዜን አካባቢ በ6ኛው ወይም በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለነገስታቶች ከአውሮፓ በስጦታነት የመጣ ሳይሆን እንደማይቀር የተገመተ የጥቁር ሰው ምስል ያለበት የሽቶ ማስቀመጫ ጠርሙስ በቅርቡ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በኤጀንሲው ጽ/ቤት የሚገኘው የሽቶ ማስቀመጫ አነስተኛ ጠርሙስ፣ ጠፍጣፋ የብርሌ ቅርጽ ያለው ሲሆን፤ በላዩ ላይ የጥቁር አፍሪካዊ ወንድ ምስል ተቀርፆበታል፡፡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ አማረ እንደገለፁት፤ ይህ ታሪካዊ ቅርስ ሃውዜን አካባቢ በእርሻ ስራ ላይ የነበረ ገበሬ ያገኘው ሲሆን አንዲት እንግሊዛዊት አርኪዎሎጂስት ከገበሬው ላይ ገዝታ ለኤጀንሲው ማስረከቧን ገልፀዋል፡፡ አርኪዎሎጂስቷ የሽቶ ጠርሙሱን ትክክለኛ እድሜ ለማወቅና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለመመርመር ጥናት እያደረገች መሆኑን አቶ ከበደ ተናግረዋል፡፡

የሽቶ ጠርሙሱን የጥንት ሮማውያን ይሠሩት እንደነበረ የታወቀ ሲሆን ሮማውያኑ በሽቶ ጠርሙሶች ላይ የአፍሪካውያንን ምስል ይጠቀሙ እንደነበርም አመላካች እንደሆነ በጥናት ተደርሶበታል ተብሏል፡፡ በሃውዜን ገበሬ የተገኘው እድሜ ጠገብ የሽቶ ጠርሙስ፤ በአሁን ሰአት ብቸኛ ተመሳሳዩ በእንግሊዝ ሃገር ሙዚየም እንደሚገኝ አቶ ከበደ ገልፀዋል፡፡ የተገኘው ቅርስ ጥናት ከተደረገበትና በሚገባ ከተፀዳ በኋላ በሙዚየም ተቀምጦ ቱሪስቶች እንዲመለከቱት ይደረጋል ብለዋል – ሃላፊው፡፡

በትግራይ ክልል ከውቅሮ ከተማ በ8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአዲ አካውህ በተመሳሳይ በ1999 ዓ.ም በተደረገ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ የአምልኮ መስዋዕት ማቅረቢያ እና የሴት ምስል ሃውልት መገኘቱ እንዲሁም ስርአቱ ይፈፀምበት የነበረ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ መገኘቱ የሚታወስ ነው፡፡

በክልሉ በርካታ የአርኪዮሎጂ ቦታዎች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ከበደ በርካታ ቦታዎች ተለይተው ጥናት እየተደረገባቸው ሲሆን ሌሎችም ቀደም ሲል የት እንዳሉ የማይታወቁትን ለማፈላለግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የአክሱም ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ ዲፓርትመንት ተከፍቶ ባለሙያዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ የአካባቢውን የቤት አሠራር ጥበብ ጠብቆ ለማቆየትና ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ህድሞ የሚባሉት ከድንጋይ ብቻ የሚሰሩ ቤቶች የሚገነቡበት የመቀሌ ከተማ ክፍል እንዲኖር ለማድረግ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡

**********

Source: Addis Admas – Sept. 7, 2013

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories