ስለስደት ‹ብልህም ሞኝም› መሆን አቅቶናል

( አርአያ ጌታቸው)

እውነት እልዎታለሁ አሁን አሁንስ እኛ ኢትዮጵያውያን በብዙ ነገሮች ብልህም ሞኝም መሆን እያቃተን መጥተናል፡፡ አንድ ሰው ብልህ ካልተባለ ሞኝ መባሉ የጁ ነው፡፡ ሞኝ ካልሆነ ግን ምን እንደሚባል ለጊዜው ስያሜ የሚሆን ቃል የለኝም፡፡ ምናልባት እርስዎ ሞኝም ብልህም ላልሆነ ሰው ስያሜ እስከሚያስቡ እኔ ነገሬን ልቀጥል፡፡

መቼም እልዎታለሁ ብዙ አስተማሪም፣ ገሳጭም፣ አዝናኝም፣ ሌላም ሌላም የሆኑ ተረትና ምሳሌዎች ወይንም ምሳሌያዊ አነጋገሮች ብሎም ፈሊጦች አሊያም አባባሎች በብዛት ያለባት አገር ከተባለ የእኛይቱን ኢትዮጵያ የሚስተካከል አገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እኔም ለዛሬ ከእነዚህ የብሂል እሴቶች መካከል አንዱን መዘዝኩ፤ «ብልህ ሰው ከሰው ይማራል፤ ሞኝ ደግሞ ከራሱ ይማራል» የሚለውን፡፡

ከላይ ከርዕሱ እንደተመለከቱት በኢትዮጵያችን ላይ በስደት ዙሪያ ብልህም ሞኝም ጠፋ ብዬ መከራከሪያ ነጥቤን ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡ ለመሆኑ እርስዎ ብልህ ወይንስ ሞኝ ነኝ ብለው ያስባሉ? እኔ ግን እልዎታለሁ ነጮቹ «ናይዘር ኦፍ ቱ» እንዲሉ ብልህም ሞኝም አለመሆንዎን ዝቅ ብዬ እነግርዎታለሁ መፅናኛ ከሆንዎትም ብልህም ሞኝም ያልሆኑት እርስዎ ብቻ እንዳልሆኑ ሌሎችንም እያነሳሁ አሳይዎታለሁ፡፡

እርስዎ ምናልባት «ለራስ ሲቆርሱ… » ነውና ነገሩ « እኔማ ብልህ ነኝ» ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ ይሄ የሰው ባህሪ ስለሆነ ትክክል ባይሆኑም እንኳን ይሁን ብዬ አልፌዎታለሁ፡፡ ምክንያቱም ስህተት መሆንዎን ከዚህ አንቀጽ ትንሽ ወረድ እንዳሉ ራስዎት ይናገራሉና ነው፡፡

ነገሬ ያለው ወዲህ ነው፡፡ እንዳልኩዎት የሀገሬ ሰው «ብልህ ሰው ከሰው ይማራል፤ ሞኝ ደግሞ ከራሱ ይማራል» የሚል እድሜ ጠገብ አባባል አለው፡፡ ይሄንን አባባል ይዘን የስደትን ነገር እስኪ እንመልከት፡፡

ምን መሰልዎት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ከገጠር እስከ ከተማ ሁሉንም እያነጋረ ያለው ጉዳይ እንደ እኔ ቁጥር አንድም የሆነው ማህበራዊ ቀውስ የስደት ችግር ነው፡፡ ስለ ስደት መቼም «አይኔን ግንባር ያድርገው» ካላሉ በስተቀር ከአንድ ጊዜም በላይ ሲነገር ሳይሰሙ አይቀርም፡፡ ታዲያ ስለ ስደት መልካምነት እንዳልሰሙ እምነቴ ነው፡፡ ለመሆኑ ስደት ወጥቶ በክብር የተመለሰን ወይንስ መርዶውን የሰሙት ሰው ነው አካባቢዎን የሞላው?

እውነት እንነጋገር ከተባለ ስደት የመጨረሻ አማራጭ እንጂ የመጀመሪያ ሊሆን አይገባም ነበር፡፡ በእኔና በእርስዎ አካባቢ ግን ለነገሩማ በቤተሰባችንም ውስጥ ሊሆን ይችላል፣ ስደትን እንደ መጀመሪያ አማራጭ የሚቆጥሩ ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ እርስዎም ያውቁታል፡፡ ታዲያ ይሄንን ስደት ለማስቆም እርስዎ ምን እያደረጉ ነው? በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራና ሰቆቃስ ለማስቆም ምን እየሰሩ ነው? ምንም፡፡ ብልህ ቢሆኑ ኖሮ ግን በሌሎች ከደረሰው መከራና ሰቆቃ ተነስተው ልጅዎትን ወይንም ዘመድዎን ብሎም ጎረቤትዎን ለማስቀረት አንዳች እርምጃ ይወስዱ ነበር፡፡ ሞኝም ቢሆኑ ኖሮ ከራስዎት የትናንት ጥፋት ተምረው ዛሬ ስደትን የመከላከል ስራዎትን ይጀምሩ ነበር፡፡ ይህ ግን አልሆነም ለምን? ሞኝ አይደሉማ፡፡

ከዚህ ተነስቼ ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ብልህም ሞኝም ጠፍቷል ማለቴ፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ እስኪ አንዳፍታ ይሄንን መረጃ ይመልከቱና በእርግጥም ኢትዮጵያ ውስጥ ብልህም ሞኝም እንደሌለ ይረዱ፡፡

በ2002 ዓ.ም 14 ሺ 946 ኢትዮጵያውያን፤ በ2003 ዓ.ም 42 ሺ 233 እንዲሁም በ2004 ዓ.ም ደግሞ 198 ሺ 667 ዜጎች ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌትና ዱባይ በታወቀ መንገድ መሰደዳቸው ተረጋግጧል፡፡ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ደግሞ ወደ ሳዑዲ አረቢያና ኩዌት አገራት ብቻ 134 ሺ 897 ዜጎች ተልከዋል።

በድምሩ በሶስት አመት ከሰባት ወር ውስጥ ብቻ 391 ሺ 743 ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ጥለው ተሰድደዋል፡፡ ይሄ ቁጥር በቦሌ የሄዱትን ወይንም በቃሉ ብዙም ባልስማማበትም «በህጋዊ» መንገድ የሄዱትን ብቻ እንደሚያካትት ልብ ይበሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በህገወጥ አዛዋዋሪዎች ስደት የወጡት ኢትዮጵያውያን ከዚህም በላይ እንደሚሆን አይጠራጠሩ፤ መረጃውንም ዝቅ ብለው ያገኙታል፡፡

ታዲያ እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ላይ አማራጭ አጥተው ይሆን? ወይንስ ኢትዮጵያ ጠባቸው? ሁለቱም አይደሉም፡፡ የሚያሳዝነው ከእነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ምናልባት ተሳክቶላቸው ለራሳቸውም ለቤተሰባቸውም የተረፉት ሩቡ እንኳን አይሆኑም፡፡ የተቀረው አገሩን ጥሎ የወጣበትን ቀን እየረገመና አገሩንና ቤተሰቡን እየናፈቀ «እያነቡ እስክስታ» በሚሉት አይነት ፈሊጥ ኑሮውን እየገፋ ይገኛል፡፡ በህይወት የተረፈው ማለቴ ነው፡፡ ታዲያ የእነዚህ ሰዎች ብልህ አለመሆንን አስቤ ዛሬም ድረስ ኢሜግሬሽን የተሰለፈውን የወዶ ተሰዳጅ ብዛት ስመለከት «አገሬ ሆይ ወየው አለመታደልሽ ብልሁ ቀርቶብሽ ሞኝ እንኳን ጠፋብሽ » ስል አዘንኩ፡፡

በእኔ ድምዳሜ ብልህም ሞኝም መሆን ያልቻልነው ብዙ ነን፡፡ የመጀመሪያው አካል ራሱ ስደት የሚወጣው ወጣቱ መከረኛ ነው፡፡ ብልህ ቢሆን ኖሮማ በሌሎች ስደተኞች ላይ ከሚደርሰው ሰቆቃ ተምሮ እግሩን ሰበስቦ በአገሩ ላይ ሰርቶ ለመለወጥ አርፎ ይቀመጥ ነበር፡፡ ስንቶች በበረሃ እንደቀሩ፤ ስንቶችስ አካላቸው እንደ እንስሳ ብልት እየተበለተ ሲቸበቸብ አልሰማሁም አላየሁም የሚል ስደተኛ አለ? ስንቶችስ በባሀር ሰምጠው እንደቀሩ ስንቶችስ በረሃ በውሃ ጥምና በረሃብ የአውሬ እራት ሆነው እንደቀሩ አልሰማሁም ሊባል ነው? ሰምቷልም አይቷልም፡፡ ነገር ግን ከሰው የሚማር ብልህ ስለሆነ ብቻ ካላየሁ አላምንም በሚል የተሳሳተ ቀመር ዛሬም ድረስ ስንቶች በቦሌም በሌላም (ሣሬስ መተማ ሱማሌና ጅቡቲ የመፍለሻ መንገድ ሆነዋል) እየወጡ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ብልህ አይደሉማ፡፡

ይሄም ይሁን ብልህ እንኳን መሆን ባይችሉ ለምን ሞኝ መሆን ተሳናቸው? ስል እራሴን ጠየኩ፡፡ ሞኝ ከራሱ የሚማር ነው ካልን እነዚህ ተስፈኛ ስደተኞች የመጀመሪያው ስደት አልሆን ብሏቸው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ሳይውሉ ሳያድሩ ሁለተኛውን ሶስተኛውንም የስደት ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ታዲያ እንዴት ብለን ነው እነዚህን እንደ ቀትር እባብ እየተክለፈለፉ ወደ ሞት የሚነዱ ወጣቶችን ሞኝስ የምንላቸው?

ብልህ ነን ካሉ ከሌሎች መከራ ተምረው አርፈው ይቀመጡ ነበር፡፡ ሞኝ ነን ካሉም ከራሳቸው መከራ ተምረው አሁንም አርፈው ይቀመጡ ነበር፡፡ ሰው የሚማረው እኮ አንድም ከፊደል ሌላም ከመከራ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ግን ብልህም ሞኝም አይደሉምና ፊደሉም መከራውም ሳያስተምራቸው ዛሬም ድረስ የዘፈናቸው ቅኝት «ስደት ስደት» ብቻ የሚል ሆኗል፡፡

በነገራችን ላይ የዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን እና ከኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ በ2011 ያካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በስደት ከሚጓዙት ሴት ስደተኞች ብቻ ከ53 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ19 እስከ 25 ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው። ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከ25 እስከ 30 ዓመት እድሜ አላቸው። እንግዲህ እነዚህ የነገ ሰዎቻችንን ነው በስደት እየተነጠቅን ብልህም ሞኝም መሆን አቅቶን ዝም ብለን የምናየው፡፡

ሌላው ስለስደት ብልህም ሞኝም መሆን ያልቻሉት ወላጆች ናቸው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ፣ በደቡብም ያሉቱ በምስራቅም ይሁን በምዕራብ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወላጆች እንደ አለመታደል ሆኖ ብልህም ሞኝም መሆን አቅቷቸው ይታያሉ፡፡ ብልህ ቢሆኑ ኖሮማ ዛሬ ሁሉም የስደትን አስከፊነት ሲናገር፤ ቴሌቪዥኑም ሆነ ሬዲዮኑ ሁሉ ስደት ስደት እያሉ ስለ ቀሳፊነቱ ሲናገሩ እየሰሙና እያዩ ልጆቻቸውን ለአውሬ አሳልፈው ባልሰጡ ነበር ይቅርታ ባልሸጡ ነበር፡፡

ቴሌቪዥኑንም አላየንም ሬዲዮኑንም አልሰማንም ይበሉ፡፡ ልጆቻቸው አረብ አገራት እንደወጡ በቀሩባቸው ጎረቤቶቻቸው ለቅሶ ላይ ተገኝተው አላስተዛዘኑምስ ይሆን? እሺ ይሄም ይቅር አንድ ወይንም ከዚያ በላይ ልጃቸውን በአስከፊው ስደት ተነጥቀው ሲያበቁ ዳግም ሁለተኛ ልጃቸውን ለአውሬ የሚያቀበሉስ የሉም ይሆን? እንዴታ አሉ እንጂ፡፡ ታዲያ እንዴት ብለን ነው እነዚህን ወላጆች ብልህ ይቅርና ሞኝስ የምንላቸው? ሞኝ እኮ ከራሱ ስህተት የሚማር ነው፡፡ እነዚህ ወላጆች ግን ከራሳቸውም የሚማሩ አልሆኑም፡፡ ብልህም ካልሆኑ ሞኝም መሆን ካልቻሉ ምን እንደምላቸው እንዳልኩዎት ለጊዜው ቃል የለኝም፡፡

ብልህም ሞኝም መሆን ያልቻሉ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ደላሎች ናቸው፡፡ እንዴት ያለ ኢትዮጵያውነት እንዴትስ ያለ ኢ-ሰብአዊነት ይሆን ወገንን አሳልፎ ለአውሬ መስጠትን ስራ ብለው የሚሰሩት? እውነት ነው ስራ ክቡር ነው፡፡ ዜጎችን በአጉል ተስፋ እያማለሉ ለቀንም ለማታም አውሬ አሳልፎ መስጠት ግን ስራ ሊባል አይችልም፡፡ ይሄንን እኩይ ተግባር «ስራ» ነው የሚል ካለ እንደ እኔ ይህ ሰው ኢትዮጵያዊነቱንም ብቻ ሳይሆን ሰው መሆኑንም እጠራጠራለሁ፡፡

ለማንኛውም ግን ደላሎች ዛሬም ድረስ ይሄንን አረመኔነት የተሞላበትን ድርጊታቸውን «ስራ» የሚል ታርጋ ሰጥተውት ዜጎቻችንን ከገጠርም ከከተማም እየመለመሉ እያስፈጁብን ናቸው፡፡ ምክንያቱም ብልህም ሞኝም አይደሉማ፡፡ ብልህ ቢሆኑ ኖሮ ሰንሰለታቸውን ዘርግተው አብረው ከሚሰሯቸው የሌሎች አገራት ደላሎችና ዜጎች ስህተት ተምረው ዜጎቻችንን በረሃ ላይ ከትመው ወዳሉ የሰው መበለቻ ቄራዎች መላክ ባቆሙ ነበር፡፡ ሞኝም ቢሆኑ ኖሩ ከራሳቸው የትናንት ስህተትና ጥፋት ተምረው ዛሬ የሰው ንግዳቸውን እርግፍ አድርገው በተውት ነበር፡፡ ይሄ ሲሆን ግን አላየንም፤ ምክንያቱም ብልህም ሞኝም አይደሉምና ነው፡፡

እኔና እርስዎም ብንሆን ምክንያቱ ባልገባን ዝምታ ተሸብበን ደላሎችን በጉያችን አቅፈንና ደግፈን ይዘን ዛሬ ድረስ አለን፡፡ አይዝዎት አይፈረድብንም ብልህም ሞኝም ስላይደለን ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ሞኝ እንኳን ሆነን ቢሆን ኖሮ ደላሎችን ለህግ አሳልፈን እንሰጥ ነበር፡፡ ይሄንን እንዳናደርግ ግን ስያሜ ያጣሁለት ነገር አነውልሎን ይሄውና ወደ አዲሱ አመት ከነችግራችን ልንሻገር ነን፡፡

እስኪ ይሄንን መረጃ ይመልከቱት፡፡ እንዳልኩዎት በቃሉ ባልስማማበትም «በህጋዊ መንገድ» ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመጓዝ ጥያቄ የሚያቀርቡ ዜጎች ቀጥር እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም በአራት እጥፍ ጨምሯል ከ20 ሺ ወደ 80 ሺ አሻቅቧል ይላል እዚሁ ጋዜጣ ላይ ያገኘሁት መረጃ። ይህ ቁጥር ግን ወደ ዓረብ አገራት ከሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ከ30 እስከ 40 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን እንደሆነ ነው በጽሁፉ ላይ የተመለከተው፡፡ የተቀረው ማለትም ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞቹ ግን በህገ ወጥ ደላሎች ተመልምለው በጓሮ በር የሚጓዙ ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ብልህም ሞኝም መሆን ያቃታቸው ደላሎች አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በጓሮ እያስወጡ እያስፈጁት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ኤጀንሲ የሚባል የወል ስም ያላቸውና ህጋዊ የሆኑ ህገወጥ የሰው ነጋዴዎችም ብልህም ሞኝም መሆን አልቻሉም፡፡ «መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ» እንዲሉ ስማቸውንና ተክለሰውነታቸውን በህጋዊነት ስም ሸፋፍነውና አሳምረው ህገ ወጥ የሰው ንግድ እያካሄዱ ዛሬም ድረስ አሉ፡፡ እነዚህ ኤጀንሲ ተብዬዎች ወገናቸውን አሳልፈው ለሰው አገር አውሬ ሸጠው የሚበሉት እንጀራ ከጉሮሯቸው ይወርድ ይሆን? እነሱስ ልጅ፣ ወንድም፣ እህትስ የላቸው ይሆን? መቼም ሰው ያለ ሰው አይፈጠርምና አንዳች ቤተሰብ ወይንም ዘመድ ይኖራቸዋል፡፡ ታዲያ ሌሎችን አሳልፈው በሚሰጡበት መንገድ የገዛ ቤተሰባቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ? አይመ ስለኝም፡፡

ብዙዎቹ ስደተኛ ወጣቶች በቦሌ ወይንም በአውሮፕላን ከአገር ስለወጡ ብቻ በህጋዊ መንገድ የሄዱ ይመስላቸዋል፡፡ በሌላ በኩልም ቢያንስ ለራሳቸው «ህጋዊ» ነን ብለው በሚያምኑ ኤጀንሲዎች በኩል ስለሄዱ ነገሩ ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆኖ የሚጠብቃቸው የሚመስላቸው ብዙ ናቸው፡፡ እውነታው ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ከአገር ካስወጧቸው በኋላ ምን ላይ እንደወደቁ እንኳን ዘወር ብለው የማያዩ፤ ሲደወልላቸው ወይንም ሲጠየቁ ምንም መፍትሄ የሌላቸው ኤጀንሲዎች እልፍ ናቸው፡፡ እነዚህ «ህጋዊ» ነን ባይ ኤጀንሲዎች ከትናንቱ ስህተታቸው ሳይማሩ፣ የእናቶችም እንባ ሆዳቸውን ሳያባባቸው የንጹሃን ዜጎቻችን ደምም ሳያራራቸው ዛሬም ድረስ ሺዎችን ወደ አረብ እና ሌሎች አገራት እየላኩ እያስፈጁ ናቸው፤ ለምን ቢሉ ብልህም ሞኝም አይደሉማ መልሴ ነው፡፡

ሌላው ብልህም ሞኝም መሆን ያቃታቸው በየሀገሩ ባሉ ኤንባሲዎቻችን ወይንም ቆንስላዎቻችን ውስጥ እየሰሩ ያሉ የመንግስት ቢሮዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቢሮዎች ስላሉበት አገር ሁኔታ እውነታውን አገር ቤት ላሉ ምልምል ስደተኞች ሲናገሩ ሰምታችሁ ታውቃላቸሁ? በጭራሽ፡፡ ምናልባት ከጎጃም ተነስቶ ጋምቤላ ለሚሄድ ኢትዮጵያዊ ምንም አይነት ገለጻ አያስፈልገውም ተብሎ ይታሰብ ይሆን ይሆናል፡፡ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ኩዌት ወይንም ወደ ሌላ አገር ለሚሄድ ስደተኛ ግን ኑ ወይንም አትምጡ ብሎ መናገር ባይቻል እንኳን «ስትመጡ ይሄ ይሄ ያጋጥማቸኋል» የሚል መረጃ ማቀበል ማንን ገደለ?

እንደ አለመታደል ሆኖ ግን የቆንስላዎቻችን ሰዎች ቢያንስ ለእነሱ ከዜጎች ደህንነት በላይ በሆነ «ስራ» ተጠምደዋል፡፡ እውነታው ግን ይሄ አይመስለኝም፡፡ የእስከዛሬው ይበቃልና እባካችሁ በየበሮቻችሁ እየመጡ ለሚጮኹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችሁ በሮቻችሁን ክፈቱላቸው፤ አለንላችሁም በሏቸው፡፡ ስለናንተ ደስ የማይል ነገር እየሰማን ነውና እስከዛሬ ብልህ ለመሆን ባትታደሉም እንኳን ሞኝ ለመሆን ሞክሩ፡፡ እስኪ የፍሊፒንስ አቻዎቻችሁ ምን እንደሚሰሩ ጠይቁና እናንተም እንደዚያው አድርጉ፡፡

እንደዚህ እንደዚህ እያልኩ ብቀጥል ብዙ በጣም ብዙ ብልህም ሞኝም መሆን ያልቻሉ ኢትዮጵያውያንን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ የጸጥታ አካላት፣ በየክልሉ በተለያዩ ቢሮዎች ያሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሚዲያዎች ወዘተ ወዘተ እነዚህ ሁሉ በእኔ ድምዳሜ ብልህም ሞኝም መሆን ያልቻሉ ናቸው፡፡ «ነገር ቢረዝም በአቋማዳ አይጫንም» ነውና ነገሩ ነገሬን ላብቃ፡፡

ለማንኛውም ግን ሁላችንም በአንድነት ስደትን በቃ ልንለውና አንዳች ነገር ልንሰራ ጊዜው ዛሬ አሁንም መሆኑን ልብ እንበልና አንዳች መልካም ነገር እንስራ፡፡ ይሄንን ማድረግ ካልቻልን ግን ብልህም ሞኝም ሳንሆን ሁላችንም ተያይዘን ማለቃችን ነው፡፡

እኔ ግን እልዎታለሁ «ምን ቸገረኝ» ብለው ተቀምጠው ከሆነ ሩቅ ነው አይደርስብኝም ያሉት የስደት ማቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርዎን ባልጠበቁት መንገድ ማንኳኳቱ አይቀርም፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ግድየልዎትም ቢያንስ ሞኝ ይሁኑ፡፡ «ለጠቢብ ሰው አንድ ቃል ይበቃዋል» ማለቴ ነው፡፡ አበቃሁ ደህና ይሁኑ፡፡

********

Source: Addis Zemen, Sept. 3,2013 titled “ስለስደት «ብልህም ሞኝም» አለመሆናችንን ልብ ብላችኋልን?”, authored by Araya Getachew.

Written by አርአያ ጌታቸው

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories