አቶ መሐመድ ሀሰን የ1966ቱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቃውሞ ሠላማዊ ሠልፍ አደራጅ የነበሩ ሲሆን፤ እንዲሁም በ1999(2007 እ.ኤ.አ) በሐጅ ነጂብ መሐመድ የተመራው የልዑካን ቡድን አባል እና ቡድኑ ለጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ያቀረበው ዶክመንት ዝግጅት ተሳታፊ ነበሩ፡፡

የበድር ፋውንዴሽን መጽሔት በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ በ2000 ዓመተ-ምህረት ከመሐመድ ሐሰን ጋር ያደረገውን ሙሉ ቃለ-ምልልስ ከታሪካዊ ፋይዳው አንጻር እዚህ አቅርበነዋል፡፡

Highlights:-
* “የአሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር [መለስ ዜናዊ] ከዩንቨርስቲው ማህበረሰብ ጋር መፈክር ከማዘጋጀት ጀምሮ የተባበሩ ናቸው፡፡”
* “በሃገራችን ሴኩላር መንግስት አለ ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችል አይመስለኝም ፡፡”
* “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሁኔታዎች በሰላም አልስተካከል እያለ ካስቸገራቸውና የሕዝቦች ሙሉ ነጻነት ፍትህና ዲሞክራሲ ለሁሉም እስካልሆነ ድረስ የትግል አቅጣጫቸዉን አይቀይሩም ማለት ዘበት ይመስለኛል፡፡”

*********

በድር መጽሔት፡- – አቶ መሐመድ ሀሰን አሰላሙአለይኩም ወረህመቱላሂ ወበረካትሁ የዛሬ 34 አመት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ አንግቦ ያነሳዉና በመድረክነትና በአዘጋጅነት ሰፊ አስተዋጽዎ ያደረገው የወጣቶቹ ክበብ መሪ እንደነበሩ ይታወቃል ስለዚህ ታሪካዊ ክስተት ለአንባቢዎቻችን ሰፋ አድርገው ቢገልጹልን፡፡

አቶ መሐመድ— ወአለይኩምሰላም ወረህመቱላሂ ወበረካትሁ፤ ቢስሚላሂ ረህማን ረሂም በመጀመርያ ይህንን ታሪካዊ ክስተት ህዝቡ እንዲያውቀው መጽሄቱ እድል በመስጠቱ አዘጋጁን ክፍል አመሰግናለሁ፡፡ አላህ ይመንዳችሁ! የወጣቶቹ ክበብ የተቋቋመው በ1964 ትእይንተ-ህዝቡን ከማዘጋጀታችን 2ዓመት ቀደም ብሎ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ዘመኑ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት በሃገሪቱ መዲና እነ ጥላሁን ግዛው በአደባባይ የተገደሉበት እነ ዋለልኝ የተሰዉበት ተማሪው ከአስተዳደሩ ጋር በ14ቱም ጠቅላይ ግዛቶች ሰፊ ትንቅንቅ ላይ የነበረበት ነበር፡፡ ሙስሊሙ ደግሞ ድርብ ተጨቋኝ ያደረገው በእምነቱ ላይ ያነጣጠረ ለዘመናት የቆየ በደል ስለነበረበት እኔም የዚያው ጊዜ ትውልድ በመሆኔ በአጠቃላይ ተማሪዎች ይዘን ከምንታገልባቸው ጉዳዮች ጎን ለጎን የሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ዎች አጉልቶ ሊያሳይ የሚችል አካል ከጓደኞቼ ከመድኃንያለም ት/ቤት እኔና አቶ አብዱ መስUድ፤ ከልUል መኮንን አቶ መሐመድ ዩሱፍ ከተግባረእድ አቶ አበጋዝ እንዲሁም አቶ አብዶ በሽር በመሆን የመጀመርያዉን የሙስሊም ወጣቶች ክበብ መሰረትን፡፡Ethiopian Muslims - the 1974 (1966) demonstration

ይህን ክበብ በሂደት በአዲስ አበባ ከተለያዩ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተዉጣጡ ጠንካራ ወንድሞችና እህቶች የክበቡን አላማ በመከተል ተደባልቀው በአመራርም ላይ ተቀምጠው አስተዋጽዎ አድርገዋል፡፡ ሆኖም በጊዜው የሙስሊሙን ጥያቄ ለማስተናገድ የሚረዳ መድረክ አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየአመቱ የረመዳን ወር ላይ የጋራ የጀመዓ ሰላት ለማድረግ የምንቸገርበት ወቅት ነበር፡፡ ጣልያን ሰርቶት በሄደው አንዋር መስጂድ አስተዳዳሪ የነበሩት ሐጅ አብዱረህማን ሸሪፍን ለወጣቶች መገናኛ የሚሆን ቦታ እንዲሰጡን ጠየቅን እሳቸዉም አላህ ጀዛቸዉን ከፍ ያድርግላቸዉና አንድ መጠነኛ ስፋት ያለው ቦታ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ እንዲዉል ብለው ፈቀዱልን በኋዋላም ለስብሰባዎችና ለቤተ-መጽሃፍትነት የተጠቀምንበትን ማለት ነው፡፡ ሁኔታዎች ቀስ በቀስ እየተቀያየሩ ድሮ ወጣቶችን በሰላት ወቅት ማየት የማንችልበት መስጂድ በወጣቶች መሞላት ጀመረ፡፡ የስፖርት፣ የስነጽሁፍ፣ የሴቶች፣ የዳእዋ ወዘተ የተለያዩ ኮሞቴዎችም በወጣቶች ተቋቋሙ፡፡ ፈጣንም እንቅስቃሴዎች መታየት ጀመሩ፡፡ ሙስሊም ወጣቶች ዲናቸዉን ተግባራዊ የሚያደርጉበት፣ ጥያቄዎቻቸዉን ጠይቀው ምላሽን የሚያገኙበት፣ የእረፍት ጊዜያቸዉን የሚያሳልፉበት ብቻም ሳይሆን በመብት ዙርያ ዉይይት የሚደረግበት፣ የተለያዩ ሙስሊም ምሁራንን እየጋበዝን የምናወያይበት ቦታ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት የወጣቱ የህሊና ንቃት እየዳበረ መጣ፡፡ በጊዜው ከዉጭ ሃገር ትምህርታቸዉን ጨርሰው የተመለሱና በእምነታቸው ምክንያት በመንግስት መደበኛ ስራ የተነፈጉ ሙስሊም ምሁራኖች በተለያዩ የእዉቀት መስኮች ያነቁን ነበር፡፡ የተለያዩ የህይወት ልምዳቸዉንም ያካፍሉን ነበር፡፡ በዲኑ በኩል አላህ ይርኸማቸዉና ሼህ ሃሚድ ዩሱፍ ለወጣቱ ብቻ ሳይሆን ለመላው ምእመናን አገልግሎት በመስጠት ዉሏቸው እዚያው መስጂዱ ዉስጥ ነበር፣ በመብት ጥያቄ ዙርያ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መብት ታጋይ የነበሩት ሼህ ሰኢድ ሙሃመድ ሳዲቅ የነበሩ ሲሆን፣ ተወዳጁ አባታችን ሐጂ መሃመድ ሳኒ ሃቢብ ደግሞ የወጣቱ የጀርባ አጥንት በመሆን ሳምንታዊ ትምህርት መስጠት ጀመሩ፤ ሁሉም ተረባረቡ ህግን በተመለከተ እነ አባቢያ አባጆቢር፣ ከሚድያ ሰዎች እነ ሐጅ በሽር ዳዉድና ጋዜጠኛ መሐመድ ኢድሪስ ፣ ሐጅ አብዱል ከሪም ኑር ሁሴን በሌላ በኩል ደግሞ እነ ሐጂ Uመር ሁሴን ነበሩ፡፡ ከዩንቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች የኢድ ፓርቲ አዘጋጅ ኮሚቴም ጋር አብሮ በመስራት ትያትር፣ ስነ-ጽሁፎችን ማቅረብ ተጀመረ ቀጥሎም ተመሳሳይ ክበቦች በየቦታው ተቋቋሙ፡፡

በአጠቃላይ አንዋር መስጂድን ወጣቱ ህይወት ዘራበት ማለት እችላለሁ፡፡ ይህ ከተለያዩ የህብረተሰብና የሙያ ዘርፍ የሚመጣው ሙስሊም ወጣት በተለይ ጁምዓ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ቅዳሜና እሁድ ድረስ በቡድን በቡድን ሆነው ስለዲናቸው፣ ስለ መብታቸው፣ ስለ ማህበራዊ ኑሮዋቸው የሚወያዩበት ብቸኛ ቦታ ሆነ፡፡ ታድያ ይህ ሁሉ ሲሆን የአባቶች ስጋት ነበር፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ለነሱ አዲስ አልነበረም፤ ከዚህ ቀደም ”ሰላማዊ ማህበር” በሚል የመሰረቱት ማህበራቸው ከፍተኛ እድገት ማሳየት በጀመረ ጊዜ አንድ አይነት የሃሰት ተንኮል ተሸርቦ በመንግስቱ የጸጥታ ክፍል እንደተዘጋባቸው ገና ከህሊናቸው አልወጣም ነበርና እኛም የነሱ እድል እንዳይደርሰብን ለዘብተኛ የሆነ አካሄድ እንዲኖረን ይፈልጉ ነበር፡፡

በድር መጽሔት፡- የ1966ቱ ትእይንተ-ሕዝብና ለወቅቱ ጠ/ሚኒስትር የቀረቡት ጥያቄዎች አጠቃላይ እንቅስቃሴ እንዴት ተጀመረ ?

አቶ መሐመድ ሐሰን:- ወቅቱ ሙስሊሞች ትልቅ ፈተና ዉስጥ የነበርንበት ነበር፤ ድርጅት አልባ ነበርን (ለነገሩ አሁንም ያው ነን) ተምረን ጨርሰን በያዝነው የሙስሊም ስም ምክንያት ብቻ ስራ የማንቀጠርበት የዜግነትና የእምነት መብቶቻችንን የተገፈፍንበት በአጠቃላይ በብዙ መልኩ እንደሁለተኛ ዜጋ የምንታይበት ወቅት ስለነበር የማንነት ጥያቄ በሙስሊሙ አይምሮ ዉስጥ መንጠልጠሉ አይቀሬ ነበር፡፡ በዛ ላይ የሙስሊሙን መደራጀት የሚያወግዙ የተለያዩ መመርያዎች በየጊዜው የሚወጡበት፣ የመብት ንቅናቄዎች በተገንጣይነት የሚፈረጁበት፤ የሙስሊም ድርጅቶችን ከኤርትራው ንቅናቄ ጋር ግንኙነት አላችሁ እየተባሉ መሪዎች የሚታሰሩበት፣ ድርጅቶች የሚዘጉበትና የሚወረሱበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ችግር እንግዲህ ተማሪው በአገር አቀፍ ደረጃ “ሆ” ብሎ ከተነሳባቸው ጥያቄዎች ጎን የሚታይ ነው፡፡ አገዛዙ እንደ ሁኔታው እያየ በግልጽና በሚስጥር ሲሰራበት የቆየ ጸረ-ኢስላም ፖሊሲ ነበረው፡፡

እዚህ ላይ ማስገንዘብ የምፈልገው የወጣቶቹን ማህበር ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅ ነበር ከማለት ይልቅ መድረክ ሆኖ ያገለገለ ነበር ማለቱ ይመረጣል፤ ምክንያቱም በጊዜው ሃሳቡ የመጣው ከተለያየ የህብረተሰቡ ክፍል ፤ ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩንቨርስቲ ተመሪዎች፤ ከመድሃንያለም፣ ከተግባረእድ፣ ከኮሜርስ፣ ከወጣቶች ክበብ በተዉጣጡ ሙስሊም ተማሪዎች ይህንን ሃሳብ ይዘው ስብሰባዎችን በተለያዩ ቦታዎች፣ ለምሳሌ በኮልፌ እንዲሁም ሃደሬ ሰፈር በሚገኘው አባድር ት/ቤት የጋራ ስብሰባዎች ይካሄዱ ነበር፡፡Ethiopian Muslims - the 1974 (1966) demonstration

ይሁን እንጂ ይህ ሃሳብ ለህብረተሰቡ የተገለጸው በመስጂዱ ቅጥር ግቢ ዉስጥ ይደረግ በነበረው ኢስላማዊ በዓል ላይ የወጣቱ ክበብ አባላት እንደተለመደው ዝግጅቶቻቸዉን በማቅረብ ላይ ሳሉ ነበር፡፡ ህዝቡም በምላሹ የግድ አንድ ነገር መደረግ ይኖርበታል በማለት ”አላሁ አክበር ”እያለ ብሶቱን ገለጸ፡፡ ይህ ገንፍሎ የወጣዉን የህዝበ- ሙስሊም ብሶት አቅጣጫ ለማስያዝ ዶ/ር አህመድ ቀሎ ለህዝቡ ገለጻ ካደረጉ በሁዋላ በአባቶች በኩል ደግሞ ዝነኞቹ ሃጂ ኢብራሂም አብዱሰላምና ሃጂ መሐመድ ሳኒ ሃቢብ ሕዝቡን አረጋግተው ጉዳዩን መልክ አስያዙት፡፡ በዚህም መሰረት ጉዳዩን የሚያስተባብር አንድ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡ የተመረጠዉም ኮሚቴ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች፣ ከአባቶች፣ ከወጣቶች፣ ከምሁራን፣ በመንግስትና ሲቪል ተቋዋማት ዉስጥ ከሚሰሩ ግለሰቦች የተዉጣጣ ሆኖ ብዙ አባላትን በያዙ የተለያዩ ኮሞቴዎች ተዋቀረ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ሃሳቦች ከተሰባሰቡ በሁዋላ ህዝቡ ሃላፊነቱን ለኮሚቴዎቹ አስተላለፈ፡፡ ኮሚቴዎቹ ደግሞ በበኩ ላቸው ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያሉበትን ችግሮች በጽሁፍ አስፍሮ ለመንግስት አቤቱታ የሚያቀርብ አንድ አካል ከወጣቶች፣ ከመንግስት ሰራተኞችና ከነጋ ዴው ክፍል የተማከሉ 7 ሰዎች መደቡ፡፡
እነርሱም ፦
1. አቶ መሐመድ አወል——- ከቴሌ ኮሙኒኬሽን (አላህ ይርኸመው)
2. ዶ/ር አህመድ ቀሎ——– ከአውራ ጎዳና
3. አቶ አብዱ አደም——– የግል ኩባንያ ባለቤት
4.አቶ ዩሱፍ አህመድ አሊ– የኢንዶ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ስራ-አስክያጅ (አላህ ይርኸመው)
5. አባ ብያ አባጆቢር ——- የህግ ጠበቃ
6. አቶ ኸሊል አብዶና እኔ —- ከወጣቶች ማህበር ነበርን፡፡ ሌሎችም በየመስኩ ሌላ ሃላፊነትን ወሰዱ፡፡

ቅድም እንዳልኩት ይህ ኮሚቴ በአስተዳደሩ በኩል ያሉትን ሁናቴዎች ከህጋዊ አሰራር አንጻር እየመረመረ ጥያቄዎችን ለጠ/ሚኒስትሩ ማዘጋጀትና ሁኔታዎች አቅጣጫቸዉን እንዳይስቱ መቆጣጠር ነበር፡፡ ባልሳሳት ከ10 ጊዜ በላይ ስብሰባዎችን ማታ ማታ በተለያዩ ግለሰቦች ቤቶች ዉስጥ በድብቅ በማካሄድ ረቂቁ ተሰርቶ ካለቀ በሁዋላ ከአባት ኮሚቴዎች ጋር ተገናኝቶ የመጨረሻው ዶክመንት ጸድቆ ከጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ቀጠሮ ተወስዶ የተወከሉት ግለሰቦች ለጠ/ሚኒስትሩ የአቤቱታ ደብዳቤዉን አቀረቡ፡፡ ጅምሩ ይህን ሲመስል ህዝቡን ማደራጀቱ ግን እራሱን የቻለ ንቅናቄ ነበር፡፡ በየእድሩ፣ በየት/ቤቱ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ትግሉን አገር-አቀፍ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ወደተለያዩ ቦታዎች ሰዎች ተልከዋል፡፡ እንደ ናዝሬት የመሳሰሉ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ከተሞችን የወጣት ማህበሩ አባላት ሲሸፍኑ፣ የተለያዩ ተወካዮች ደግሞ ከትግራይ፣ ከጎጃም፣ ከወሎ፣ ከቤጌምድር፣ ከሃረርጌ፣ ከጅማ ወዘተ ወደ አዲሳባ መጥተው ሂደቱን ተቀላቅለዋል፡፡

በድር:- እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ዝግጅት በሁዋላ የሰላማዊ ሰልፉ ጅምርና አካሄድ ምን ይመስል ነበር?

አቶ መሐመድ ሀሰን:- ጠ/ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮነን ሰልፉ እንዳይደረግ በቴሌቪዢን ተማፅነው ነበር፡፡ ለረጅም ዘመናት የፍትህ እጦት፣ በደልና ጭቆና ሰፍኖበት የኖረን ህዝብ ተው ማለት የማይቻልበት ወቅት ነበርና ተማጽኖዋቸው ሰሚ አልነበረዉም፡፡ ለሰላማዊ ሰልፉ የተደረጉት ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ እንዳሉ ለክርስትያኑ ወገን በራሪ ወረቀት ተበተነ፡፡ በእለተ ጁምዓ አላህ ይርኸመው አቶ መሐመድ አወል የኮሚቴዉን መግለጫ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈዉን አቤቱታና የሰላማዊ ሰልፉን ጥሪ በአንዋር መስጂድ ለተሰበሰበው ህዝብ አነበበ፤ እኔ ደግሞ በዚያው እለት በኒ ሰፈር መስጂድ ለተሰበሰበው ህዝበ-ሙስሊም መግለጫዉንና ጥሪዉን አነበብኩኝ፡፡

የተባለው ቀን ደረሰ! ሱብሃናላህ ያልተጠበቀ ተእይንት ነበር፡፡ ከሙስሊሙ ጎን ክርስትያኖችም ቆሙ፤ ሁናቴዉን ያኔ ላይ ሆነህ ስታጤነው ሙስሊሙ ለጦርነት የሚዘጋጅ ይመስል ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወታደሮች በማክ እየተጫኑ ቦታ ቦታ ያዙ፣ ጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶችም ስርዓትን ለማስያዝ መስመር ላይ ገቡ፡፡ ሰልፉ ተጀመረ፤ ሙስሊሙ እየዘመረ ወጣ ከመርካቶ ተነስቶ ሃብተጊዮርጊስ ድልድይ፤ በፒያሳ አቋርጦ ራስ መኮንን ድልድይን ተሻገረ አራት ኪሎ አካባቢ ሲደርስ ትንሽ ግርግር የሚጀመር መስሎ ነበር ወድያው ተረጋጋ፡፡ ሌላው ማንሳት የምፈልገው ነገር ሰልፉ በእግረኞች ብቻ ሳይሆን ብዙ ሙስሊሞች በመኪና ሆነው ሰልፉን ተከትለዋል ከመሃከላቸዉም መሳርያም የያዙ ብዙ ነበሩ፡፡

ለነገሩ የታጠቁ ብዙ አባቶችም ነበሩ፤ ጉዞው በሰላም ቀጠለ በየመንገዱ ዳር በቆሙና በየፎቁ በረንዳ ላይ ሆነዉና በመስኮት በኩል በሚመለከቱ ሰዎች በጭብጨባ የታጀበ ነበር ፡፡ አንድ ጫፉ መርካቶን ሳይጨርስ ሌላ ጫፉ ኢዮቤልዮ ቤተመንግስትን አቋረጠ፡፡ ህዝቡ አስፈላጊዉን መልእክት በዚህ ሰልፍ አማካኝነት አስተላለፈ፡፡ በጊዜው በሃገሪቱ ታሪክ ይህን ያህል ህዝብ ለሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ አያውቅም በጊዜው ከሶስት መቶ ሺህ በላይ የሚገመት ሕዝብ ተካፍሏል፡፡ ይህ ትእንት በተለያዩ የዉጭ ሃገር ጋዜጦች ትልቅ ሽፋን ተሰጠው፤ ብዙ ተባለለት ሃገር ዉስጥ ግን እንደተለመደው የሚድያ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ያልተጠበቀም አልነበረም፡፡ በዚህ ወቅት ትምህርቱን ከአሜሪካን ሃገር ጨርሶ የገባው አቶ አህመድ ሰኢድ አሊ (አላህ ይርኸመው) እንዲሁም አቶ መሐመድ አህመድ ሸሪፍ በተለይ በእንግሊዝኛ የሚታተመዉን Ethiopia Herald ጋዜጣ የሙስሊሞችን መብት በተመለከተ በሚያወጣቸው አሉታዊ ጽሁፎች ላይ በመተቸት፣ በመተንተንና ምላሾችን በመስጠት እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ላይ ስለ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መብት በመሟገትና ትምህርትን በመስጠት ትክክለኛዉን መንገድ በማመላከት ብዙ የደከሙ ነበሩ፡፡ አቶ አህመድ በሁዋላ የተቋቋመው መጅሊስ አማካሪ በመሆን ያገለገለ ሲሆን፤ አቶ መሐመድ አህመድ ሸሪፍ ደግሞ በሃገሪቱ በተለያዩ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ ከመቆየታቸዉም ባሻገር እኚህ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ልምድን ያካበቱት ታላቅና አስተዋይ ሰው በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ የበድር ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ፌዴሪሽን ተወካይ ሆነው ይገኛሉ፡፡

በድር መጽሔት፡- ለዚህ ታላቅ ሰልፍ የብዙዎች ርብርቦሽ እንደነበረ ገልጸዋል የተለየ አስተዋጽዎ ካደረጉት ዉስጥ የሚያስትዉስዋቸዉን እስቲ ቢያነሱልን?

አቶ መሐመድ ሀሰን፡- ትእይንተ ሕዝቡንና ጠቅላላው እንቅስቃሴ እንዲሳካ ትልቅ አስተዋጽዎ ካደረጉት መካከል በተቀዳሚነት ከአባቶች በኩል ሐጂ ኢብራሂም አብዱሰላም፣ መካከለኛ እድሜ ዉስጥ ከነበሩት የምሁራን ክፍል መሃል ደግሞ ዶ/ር አህመድ ቀሎ፣ አባቢያ አባጆቦርና አብዱ አደም፣ አቶ መሐመድ አወል የዚህ ታሪካዊ ክስተት ተቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሐጂ ኢብራሂም አብዱሰላም (አላህ ይርኸማቸው) ገና በወጣትነ ታቸው ከኤርትራ በፊት በሃገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል በተደረገው እንቅስቃሴ የነጻነት ትግል ወቅት ከፍተኛ አመራር ላይ የነበሩ ሰፊ የህይወት ልምድ የነበሯቸው የዉጪዉንና የሙስሊሙን አለም የሚያውቁና ራእይ የነበራቸው ነበሩ፡፡ ከነበራቸው ልምድ እንቅስቃሴያችንን መስመር በማስያዝ ትልቅ አስተዋጾ አድርገዋል፡፡ ብዛት ያላቸዉን ወንድሞች ከሃገር ወጥተው በተለያዩ ሃገሮች የመማር እድል እንዲያገኙ የሞራልና የገንዘብ አስተዋጽዎ ስለማድረጋቸው ዛሬ በአውሮፓ፣ በሳውዲና በአሜሪካ በካናዳ የምንገኝ የአካል ምስክሮች ነን፡፡ አላህ በጀነት ዉስጥ ከፍተኛዉን ቦታ እንዲሰጣቸው ዱዓዬ ነው፡፡ አቶ አብዱ አደም ዛሬ ኑሯቸው በካናዳ ሲሆን በጊዜው የግል ኩባንያ ባለቤት የነበሩና በወቅቱ የነበረው እንቅስቃሴ ዉጤት እንዲያመጣ ገንዘባቸዉንና ያለ ሃይላቸዉን ለሙስሊሙ Uማ ያበረከቱ ናቸው፡፡ እንዲሁም የዶ/ር አህመድ ቀሎ የበሰለ አመለካከትና ጥበብ በጊዜው ባይጨመርበት ኖሮ በወጣቶችና በአባቶች መካከል የነበረው አለመግባባት መልክ ይዞ ባልቀጠለ ነበር፡፡ ሀጅ ሻሚል ኑርሰቦ የወጣቱ ማህበር ሲመሰረት ጀምሮ የነበሩና በተለይ ወጣቱንና ነጋዴዉን በማገናኘት ለትግሉ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሲሆን ቀጥሎም የአወልያ ት/ቤት ዳሬክተር ከምስረታው አንስቶ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መሰረትን በመጣልና በማሳደግ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ታላቅ ባለዉለታ ናቸው፡፡

ከማስታዉሳቸው የወጣቶቹ ማህበራት ስራ አስክያጆች ዉስጥ እነ ጀማል አሊ፣ አብደላ ሀሰን፣ አብዶ በሽር፣ አብደላ አብዱልቃዲር፣ Uስማን መሃመድ፣ አህመድ ሼህ አወል፣ ሲራጅ ሱለይማን፣ ጀማል ሀሚድ፣ ማህሙድ አሊ ኢስማኤል፣ አህመዲን ዩሱፍ፤ ኢዘዲን መሐመድ (የቁዱስ ጋዜጣ አዘጋጅ)፣ አብዱሰመድ፣ ሰመረዲኒና ሰበሃዲን፤ ከሴቶች ደግሞ እነ ሲቲሚያ መሐመድ፡፡ በተጨማሪም ዛሬ በአሜሪካን የሚኖሩት እነ ሃጅ ነጂብ መሐመድ፣ አቶ አሊ አህመድ (አላህ ይርኸመው) እነ ኑሩ ይማም፣ እነ አህመድ ሁሴን (ሪንጎ)፣ በሽር መሐመድ ሳኒ፣ ታጁዲን ያህያ፣ አቶ ከዲር ከአንዋር መስጂድ፣ እነ አህመድ ዋሴ (ሚኒሶታ)፣ ጋሊብ አሊ ኢስማኤል፣ ሰኢድ ዩሱፍ (ጣልያን)፣ ብርሀኔ ካሳሁን ፈይሰል ተውፊቅ ፍስሀ አዱኛ ሙሀመድ ሀጅ ሙሀመድ ሳኒ ከድር ሙሀመድ (አላህ ይርኸመው) አቡበከር ሱለይማን በቀይ ሽብር ከተመቱት መካከል የክበቡ ቀኝ እጅ የነበረው አባስ (አላህ ይርኸመው) እንዲሁም አሁን ያላስታወስኳቸው ብዙ ወንድሞችና እህቶች የዚያ ትውልድ ብርቅዬ ልጆች ነበሩ፡፡ በአባቶች በኩል እነ ዩሱፍ አደም፣ አቶ ሙሳ ኪክያ፣ አቶ Uመር ኢማም፣ እነ ካሚል ሸሪፍ፣ እነ ባህሩ ሁሴን፣ እነ ኮሎኔል አህመድ አሚኑ ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ የኢድ በዓል አዘጋጅ ኮሚቴው ደግሞ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ለማሰባሰብ እንዲቻል በተቻለ መጠን ከተለያዩ የህብረተሰባችን ክፍሎች ተዋቅሮ የነበረ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ የማስታዉሳቸው እነ አደም አብደላ፣ ኑረዲን አህመድ፣ መሃመድ ናስር አብዱላ፣ ሸምሱዲን አህመድ፣ አየልኝ መሃመድ፣ በድሩ ሱልጣን (የቃጥባሬው ሼህ የልጅ ልጅ)፣ ሃሩን አባድር፣ ሉባባ አብዱሰመድ፣ ዚነት መሃመድ፣ ዘውዲቱእነዚህ ሁሉ እንግዲህ የተሳተፉበት ትግል ነበር፡፡ እንዳልኩት ኮሚቴዎች ሁሉ የተለያዩ ስራ ተከፋፍለው ይሰሩ ስለነበር ሁሉንም ማስታወስ ይቸግረኛል አዉፍ በሉኝ፡፡ ላስታወስኳቸዉም ሆነ ለዘነጋኋቸው አላህ ይመንዳቸው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልጨምር የዚህ ታሪካዊ ክስተት ዉጤት ምንድን ነው? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ትግል ሂደት ስለሆነ ያ ትውልድ ትናንትና ባደረገው እንቅስቃሴ በአላህ ፈቃድ የተወሰነ ድልን አስመዝግቧል፡፡ ይህ መሰረታዊ ቁም ነገር ከልብ መጤን አለበት፡፡ በንጉሱ ዘመን የቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ ነበር ወታደራዊዉ የኮሚኒስት አስተዳደር አገራችን ላይ የተንሰራራው፡፡ ይህ ስርዓት ደግሞ የሙስሊሞችን ትግል የሚያግዝ አልነበረም፤ ሆኖም ከቀረቡት ጥያቄዎች ዉስጥ የተወሰኑት በዚህ ስርዓት ተመልሰዋል፡፡ አልሃምዱሊላህ!! ትግሉ መቀጠል አለበት አሁን ሙስሊሞች ወደዝያ አስከፊ ወደነበረው የአስተዳደር ሥርዓት ዳግም እንደማይመለሱ የታወቀ ነው፡፡ የተቀረዉን በአንድ ነታችንና ባለን የአላማ ጽናት፣ የአላህ ስ.ወ ና የነብዩን (ሰ.አ.ወ) ትእዛዛት በፍጹም ታማኝነት ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ መታገል ብቻ ነው፡፡

በድር መጽሔት፡- በ1966 ለጠ/ሚኒስቴር ያቀረባችሁት ጥያቄዎች ምን ነበሩ?

አቶ መሐመድ ሀሰን፡- በሚያዚያ 1 ቀን 1966 ለጠ/ ሚኒስቴር እንዳልካቸው መኮነን የቀረቡ ጥይቄዎች 13 ሲሆኑ እነሱም በአጪሩ የሚከተሉት ነበሩ፦

1. መንግስት የኢስላም ሃይማኖት ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን በህገ መንግስቱ እንዲያሰፍር፣ በተግባርም እንዲያውል፤

2. ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የራሳቸን ማህበር እንዲያቋቁሙ መንግስት ፈቃድ እንዲሰጥ፤

3. የሸሪዓ ፍርፍ ቤቶች ነጻ ሆነውና ያለምንም ተጽእኖ እንዲቋቋሙና የራሳቸው በጀት እንዲኖራቸው እንዲደረግ፣ ይህም በተሻሻለው ህገ መንግስት እንዲካተት፤

4. የሙስሊሙ በዓላት በብሄራዊ ደረጃ እንዲከበሩ፤

5. የሙስሊም ወጣት ወንዶችና የሙስሊም ወጣት ሴቶች ማህበራት በአዋጅ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲቋቋሙ፤

6. ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን የርስት መሬት ባለሀብት የመሆን መብቱ እንዲከበር

7. ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመሬት ባለሀብት እንዳይሆኑ መከልከላቸው “አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው” የሚለውን ቃል በተግባር ሀሰት መሆኑን አመላካች በመሆኑ አዲሱ ካቢኔ ይህን መብት ተግባራዊ እንዲያደርግ፤

8. ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በመንግስት አስተዳደር፣ በፍትህ፣ በዲፕሎማቲክ፣ በውትድርናና በሲቪል አገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፉ እንዲፈቀድ፤

9. መንግስት የእስላምን መስፋፋት መደገፍ ይኖርበታል። ሙስሊም ሚስዮናዊያንም አገር አንዲገቡ መፍቀድ ይኖርበታል። ለስርጭት ስራዉም ገንዘብ መመደብ ይኖርበታል።

10. የኢስላም ትምህርት በብሄራዊ የመገናኛ ተቋማት – በሬዲዮና ቴሌቪዥን – መሰጠት ይኖርበታል።

11. “በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች” የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በሚለው እንዲተካ፤

12. በሁሉም ትምህርት ቤቶች የኢስላም ትምህርት እንዲሰጥ፤

13. መንግስት የመስጊዶችን ግንባታ እንዲፈቅድና ለግንባታው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችንም ከቀረጥ ነጻ አገር ውስጥ እንዲገቡ እንዲፈቅድ እንጠይቃለን።

ለመሆኑ ከነዚህ 13 ጥያቄዎች ከ33 አመት በኋላ ስንቶቹ መልስ አገኙ? ስንቶቹስ ገና እየጠበቁ ይገኛሉ? ይህን ለአንባቢያን እንተወዋለን።

በድር መጽሔት፡- በ2007 በድር ወደ ኢትዮጵያ በላከው የልUካን ቡድን አባል በመሆን አሁን ላለው የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስቴር የሙስሊሞችን አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ይህም ለሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በቀረቡት አቤቱታዎች ላይ አብረው ሰርተዋል ማለት ነው፡፡ እስቲ የሁለቱን ወቅትና ሁናቴ በማገናዘብ ልዩነቱን ያብራሩልን፡፡

አቶ መሐመድ ሀሰን፡- አዎ ከአጠቃላይ የመብት ማስከበር ጥያቄዎች መርህ አንጻር ልዩነት የለም፡፡ ጥያቄዎቹ ከቀረቡበትም ወራት አንጻር ልዩነት የላቸዉም ምክንያቱም ሁለቱም ጊዜ የቀረቡት በሚያዝያ ወር በመሆኑ (ሳቅ)፡፡ የመብት ጥያቄ ማንሳት በጊዜ አይገደብም፤ መብትን የሚመለከት ጉዳይ እስካለ ድረስ፡፡

ከ1966 በፊት የመንግስት ሀይማኖት የሚባል ነገር (state religion) ነበር፡፡ ከዋናው ጥያቄያችን አንዱ ሴኩላር የሆነ አስተዳደር እንዲኖር ነበር ያ ማለት ባጠቃላይ ያልነበረዉን እንዲኖር ለማድረግ ነበር ትግሉ፡፡ የ1999/2007 ጥያቄ ደግሞ የዜጎች የእምነት ነጻነት በህገ-መንግስቱ ተረጋግጦ እያለ ሙስሊሞቹ ላይ ሲደርስ ይሸራረፋል ወይንም ጭራሽ አይከበርምና ይህ ትክክል ያልሆነው አካሄድ ይቁም ነው፡፡

ምንም እንክዋን ይህንን ልበል እንጂ መብት በልመናና በአቤቱታ ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም ፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሁኔታዎች በሰላም አልስተካከል እያለ ካስቸገራቸውና የሕዝቦች ሙሉ ነጻነት ፍትህና ዲሞክራሲ ለሁሉም እስካልሆነ ድረስ የትግል አቅጣጫቸዉን አይቀይሩም ማለት ዘበት ይመስለኛል፡፡ የራስን ሃይማኖት ማስተማር በእርግጥ ሰብዓዊ መብት ሆኖ ሳለ ሌላዉን መቀናቀን የሌላዉን ተመሳሳይ እኩል መብት መግፈፍ ትልቅ ወንጀል ስለሆነ በጋራ ልንዋጋው ይገባል፡፡

በድር መጽሔት፡- የሌሎች እምነት ተከታዮችም በሰልፉ አብረዋችሁ እንደነበሩ አልፎ አልፎ ይጠቀሳል ከሙስሊሙ ዉጪ የሌላዉን እምነት ተከታዮች አብረዋችሁ እንዲሰለፉ የተጠቀማችሁበት ዘዴ ነበር?

አቶ መሐመድ ሀሰን፡- አዎ የኛ መሰረታዊ ፍላጎት ኢትዮጵያ ለልጆቿ እኩል ፍትህ እንድትሰጥና እኩልነት እንዲኖር ነበር አሁንም ነው፡፡ ቀድሞዉኑም ክርስትያኑም ወገን ቢሆን የሙስሊሙ መብት አለመከበር የማይቀበለው ቢሆንም እራሱም ቢሆን የከፋፍለህ ግዛው ሰለባ ከመሆን አልዳነም ነበር፡፡ በመሆኑም የሙስሊም ወገኖቹ እንቅስቃሴ ግልጽ ይሆንለት ዘንድ በራሪ ወረቀት በመበተንና በማስረዳት ሊነሳ የሚችለዉን የተንኮል ዘመቻ አስቀድመንም መንገድ ዘግተንበት ነበር፡፡ በ2ኛ ደረጃ ደግሞ በጊዜው ሲሶ መንግስት ለነበረችው ለቤተክህነት አስተዳደር ጉዳዩን ግልጽ ማድረግ ነበረብን፡፡ ለዚሁም በጊዜው የህግ ጠበቃ የነበሩት የኮሚቴው አባላችን አባ ብያ አባ ጆቢር ህዝበ ሙስሊሙ የተነሳበትን ዓላማ ሄደው ገልጸዋል፡፡ እሳቸዉን ፈልጋችሁ ብታነጋግሯቸው የበለጠ ማብራርያ ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌላው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምሁሩ ክፍል ነበር፡፡ እዚህ አካባቢ ችግር አልነበረም፤ ከገለጻው በሁዋላ ቀጥተኛ ተሳታፊነትና ትብብርን አግኝተናል፡፡

የአሁኑ ጠቅላይ ሚንስትርን ብንወስድ ከዩንቨርስቲው ማህበረሰብ ጋር መፈክር ከማዘጋጀት ጀምሮ የተባበሩ ናቸው፡፡ ከማስታዉሳቸው ምሁራንና ተማሪዎ መሃከል እነመለስ ተክሌ ፣ ፍቅሬ መርእድ፣ እሸቱ ጮሌ፣ አቦማ ምትኩ፣ ጌታቸው በጋሻው፣ መራራ ጉዲና፣ ገለታ ዲልቦ፣ ሽመልስ ማዘንግያ፣ ያእቆብ ወልደማርያም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለሃገርና ለወገን የነበራቸዉን ፍቅር በወቅቱ በሚገባ ገልጸዋል፡፡ በነገራችን ላይ አባብያ አባጆቢርና ዶ/ር ያእቆብ የጋራ የጥብቅና ቢሮ ከፍተው ይሰሩ ነበር፡፡

በድር መጽሔት፡- አቶ መሐመድ በአሁኑ ወቅት በድር የኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች አለማቀፍ ፌዴሬሽን የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ሃላፊ ሆነው እየሰሩ ነው ፡፡ ምንም እንክዋን አሁን ዋናው መነጋገርያ ርእሳችን ባይሆንም፣ የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ ካነሱ ዘንዳ የኢትዮጵያ ሙስሊሙችን የመብት ጥሰት የሚዘግብም ሆነ በደላቸዉን አሰምቶ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያደርግ አካል እንደሌለ ይታወቃል፡፡ እስኪ እርሶ በሚመሩት ኮሚቴ እይታ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሰብአዊ መብት ሁናቴ ምን እንደሚመስልና እናንተም ከሰራችሁት ዉስጥ በአጭሩና ጠቅለል አድርገው ይንገሩን?

አቶ መሐመድ ሀሰን፡- የሰብአዊ መብት ኮሚቴ የሙስሊሞች መብት ተጣሰ ብሎ ባመነ ግዜ ይህን የመብት ጥሰት ያጋልጣል መፍትሄ ይፈልጋል፤ ያፋልጋልም፡፡ በ2007 (እ.ኤ.አ) ወደ ኢትዮጵያ የሄደው በሐጅ ነጂብ መሐመድ የተመራው የልUካን ቡድን ይዞት የቀረበው የ23 ገጽ ዶክመንት ሥራ ዝግጅት ላይ ይኸው የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ መረጃዎችን በማሰባሰብ ረገድ ሠፊ ትብብር አድርጓል፡፡ ብዙ የመግባባት ነጥቦች ላይ ደርሰን ነበር፡፡ በሃገራችን ሴኩላር መንግስት አለ ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችል አይመስለኝም ፡፡ በተለይ ህገ-መንግስቱ በጽሁፍ ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባር ካልተቀየረ ነገሩ ሁሉ ታጥቦ ጭቃ ይሆናል፡፡ በድር ወደፊት በስፋት ተቀናጅቶ ወደ ተፈለገው ግብ እንደሚደርስ ተስፋ አለኝ፡፡ አሁን በድርን በፕሬዝደንትነት የሚመሩት ዶ/ር ዘኪ ሸሪፍ አላህ ጀዛቸዉን ከፍ ያድርገዉና በዚህ በኩል በጣም እየጣሩና እየሰሩ ናቸው፡፡

ባጠቃላይ የ66ቱ እንቅስቃሴ ቀጣይ ስራ አልተቋረጠም አሁንም እየተሰራ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ የሃገራችን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ገና ምላሽን ይፈልጋል፡፡ ዛሬ ሙስሊሞች በከፍተኛ የትምህርት ተቋዋማት ዉስጥ ከትምህርትህና ከሃይማኖትህ የሚል ምርጫ ተደቅኖባቸዋል፣ የአክሱም ተወላጅ ሙስሊሞች (አክሱማዊያን) ዛሬም የአምልኮ ቦታ (መስጂድ) የመስራትና በህብረት የማምለክ መብታቸው አልተከበረም፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሚወክላ ቸዉን አካል ራሳቸው የመምረጥ የማዉረድና የመቀየር መብታቸው ገና እንደተቆለፈ ነው፣ በቀላሉ NGO አቋቁመው ማህበራዊ ፍላጎቶቻቸዉን ለሟሟላት ቢፈልጉም መንገዱ እንዲርቃቸው ተደርጓል፡፡ ሌላም ሌላም ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኛም ለምሳሌ በመቀሌ ዩንቨርስቲ በተከሰተው አሳዛኝ ድርጊት ሁናቴዉን የሚያጣራ ተወካይ ወደ ቦታው ልከናል፡፡ በሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረዉ የትምህርት ሚንስትርን የደንብ ረቂቅ የሙስሊሙን መብት እንደሚጥስ የሚያሳስብ ልUካን ለመላክ ቅድምያ ደብዳቤ ለመንግስት ልከን መልስ እየጠበቅን ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ አሰራራችንን አለማቀፋዊ ለማድረግ መንገድ እየቀየስን ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በሃይማኖት ስለማይወሰን ከተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር አብረን በመስራት ላይ ነን፡፡ በአጠቃላይ ይህ ትግል ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሰብዓዊና የዜግነት መብታቸዉን ሙሉ በሙሉ እስከሚጎናፀፉ ድረስ ይቀጥላል፡፡ የትግሉ ተረካቢም እንግዲህ ይህ ትውልድ ነው ኢንሽአላህ! እኛ ሙስሊምች ነን፤ ሙስሊም ያለበት በአቅሙ ግዴታዉን ለመወጣት መሞከር ነው፡፡ ከኛ የሚጠበቀው በአላህ መንገድ በጥበብ ጥረታችንን መቀጠል ነው ድል በአላህ እጅ ነው፡፡ ኢንሻአላህ ጥረታችን ሁሉ ፍሬ ያፈራል፡፡

በድር፡- ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም የሚያስተላልፉት መለእክት ካለ?

አቶ መሐመድ ሀሰን፡- የመጀመርያው መልእክቴ በስልጣን ላይ ላለው መንግስት ነው፡፡Ethiopian Muslims - the 1974 (1966) demonstration ይኸውም ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጥል ከፈለግን ሁላችንም ለሰላምና ለእኩልነት ለሰብዓዊ መብት መከበር የበኩላችንን አስተዋጽዎ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እኛ በዲያስፖራ ያለነው ሙስሊሞች መንግስት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ቅንጣት ያህል ታማኝነትና ተወካይነት ለሌለው ለህብረተሰቡም ምንም አይነት ግልጋሎት ሊሰጥ ላልቻለ የመጅሊስ አስተዳደር ድጋፉን በመስጠት የዜግነትና የሙስሊምነት መብታችንን ተጋፍቷል፡፡ በነጻ ማህበራትን የማቋቋም መብታችንን በቢሮክራሲያዊ ማነቆ አዳክሟል፡፡ በተለያዩ የህይወት ዘርፎች የመወዳደር አቅም አሳጥቶናል፡፡ በማንነታችንና በእምነታችን ላይ በተሰነዘሩና እየተሰነዘሩም ባሉ ወንጀሎች ላይ ትኩረትን በመስጠት አመርቂ ምላሽ ሊሰጥ ባለመቻሉ ፍትህ ነፍጎናል፡፡ ህገ- መንግስቱ የሰጠውን የሃይማኖት እኩልነት ኢስላምና ሙስሊሞች ላይ ሲደርስ ተፈጻሚነት አጥቶዋል፤ የሚሉት በዋንኛነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ ሌሎችንም ተመሳሳይ ከህገ- መንግስታዊ ማእቀፍ የማይወጡ፣ ለሃገሪቱ ሴኩላራዊ ስርዓትና የዲሞክራሲ መርሆዎችን ከግንዛቤ ያስገቡ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ አቅርበናል፡፡ አሁንም በድጋሚ የምናሳስበው እነዚህ የህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች “መቻቻል” የሚለዉ ክቡር አብሮ የመኖር መርህ በተግባር እስካልተተረጎመ በስተቀር በአንድ በኩል ብቻ “መቻል” በሚለው አካሄድ ብዙ ልንዘልቅ አንችልም፡፡ በደሉ በዝቷል፤ ስለሆነም አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥና ከቃላት ሽንገላ ባለፈ ተግባራዊም እንዲሆን እጠይቃለሁ፡፡ ሙስሊሙ የራሱን ምርጫ አድርጎ ለእምነትና ለልማት ህገ-መንግስቱን ጠብቆ የሚያገለግለዉን ቢመርጥ መንግስትን የሚያስፈራው ጉዳይ ምን እንደሆነ በእውነቱ ሊገባኝ አልቻለም፡፡

በመቀጠል የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በሚመለከት 3 ነገሮችን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ እነርሱም፦ 1. የባህሪ ለዉጥ 2. መደራጀት 3. ዉይይት ናቸው፡፡ ትንሽ ላብራራ
1. የባህሪ ለዉጥ፦ በሃገሪቱ የፖለቲካ አስተዳደር ተሳታፊ የመሆን ጉዳይ ላይ ሙስሊሙ እንዲገለል ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ሁኔታው በተቀየረበት ጊዜ ሙስሊሙ ከሚኖርበት ቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የአስተዳደር ስልጣን ድረስ ተሳታፊ መሆን አለበት፡፡ የራሱ ምድር፣ የራሱ ሃብት ነው፡፡ ሌሎች መጥተው እንዲያስተዳድሩት እንዲመሩት እድሉን መስጠት የለበትም፤ ይህ በረጅሙ የጭቆና ዘመን ደም ዉስጥ የገባው ተውሳክ መወገድ ይገባዋል፡፡ የሃላፊነት የተጠያቂነትን ቀንበር መሸከም፤ መብትና ግዴታን አውቆ መጓዝ ከመብት ማስከበር አንጻር ወሳኝነት አለው ስለዚህ ከተገዢነት ስነ-ልቦና መላቀቅ አለብን፡፡

2. መደራጀት፦ ሙስሊሙ በየፈርጁ ተደራጅቶ ለመብቱ መስራትን መልመድ አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም ገዢዎችን እንደ ሙስሊሙ ህብረተሰብ መደራጀት የሚያስፈራቸው ነገር አልነበረም ማለት እችላለሁ ስለዚህም ነው ሙስሊሙን እንክዋን ሊደራጅ ቀርቶ ስለ መደራጀት እንዳያስብ የረጅም ጊዜ የስነ-ልቦና ጦርነት ሲያካሄዱበት የኖሩት፤ የዜግነት ስብእናዉን ያኮላሹት፡፡ ሙስሊሙም ይህንን ተገንዝቦ ዱዓ እያደረገና የአላህን እርዳታ እየከጀለ የያዘው ዲን (ኢስላም) የአንድነት እንጂ የመለያያና የመከፋፈያ መንገድ አለመሆኑን ተገንዝቦ በጎሳና በጎጥ ሳይከፋፈል እራሱን የሚያደራጅበትን መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ጥልቅ ግንዛቤ (critical awareness) ያስፈልገናል፡፡ መቸም የኢትዮጵያ ሙስሊም ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ያለፍንባቸዉና አሁንም ያሉብን ግፎች ሁሉ ካሁን በኋላ መቀጠል እንዳይችሉ ማድረግ የምንችለው ከአላህ እርዳታ ጋር እኛውና እኛው ነን፡፡ የወገናችን ብሶትና መከራ የሚሰማን ከሆነ ትግሉ መቀጠል አለበት፡፡ ሌላው ብሄራዊ ተቆርቋሪነት በሙስሊሙ ላይ ሊታይ ይገባል፡ ለፍትህና ለዲሞክራሲ የሚደረጉ ትግሎች ሙስሊም፣ ክርስትያን አልያም የሌላ እምነት ተከታይ መሆንን የግድ አይጠይቁም፡፡ ዉጤቱና ፋይዳውም ለሁሉም ነዉና፡፡

3. ዉይይት (dialog)፦ በበኩሌ በኢትዮጵያ በሙስሊሞችና ሙስሊም ባልሆኑ ወገኖች መካከል የዉይይት መድረክ በየወቅቱ ቢዘጋጅ መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡ እኛ ወንድማማቾች ነን በሃገርና በመብት አንጻር ጥቃታቸው ጥቃታችን በደላቸው በደላችን ነው፡፡ አንዳችንን አሳዝኖ ሌላችንን የሚያስደስት ፤ አንዳችንን ጎድቶ ሌላችንን የሚጠቅም ጉዳይ ከሃገራዊ አብሮ የመኖር እሳቤ አንጻር አለ ብዬ አላምንም፡፡ በብዙ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ አብሮ ይከፋናል አብሮም ደስ ይለናል፡፡ ከዚህ ዉጪ ያለው እንግዲህ የገዢዎች ታሪክ ነው፡፡ መወያየት ያሻናል ሲባል እንግዲህ ሁሉም የያዘዉን ይዞ ሲያበቃ በሰላም በመቻቻል በመከባበር አብሮ እንዲሰራና እንዲያድግ ስለሚረዳው ነው፡፡ በተንኮለኞች የህዝብ ሰላም እንዳይደፈርስ ጥንቃቄ ተደርጎበት በቅንነት፣ በዉይይትና በመከባበር ከተሰራ ለሃገሪቱ የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ሆነ ህዝቦች አወንታዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ የበለጠ የሚያስተዋውቅና አንዱ ስለሌላው ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ከማድረጉም ባሻገር የማሰብም ሆነ የመመራመር ነጻነትን ይሰጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

በድር፡- ስለሰጡን ሠፋ ያለ ማብራሪያ አመሰግናለሁ ጀዛክ አላህ ኸይር አቶ መሐመድ ሀሰን እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናልሁ።

**********

You can download here – በ1999 በሐጅ ነጂብ የተመራው ልዑካን ለጠ/ሚኒስተር መለስ ያቀረበው ዶክመንት (PDF: 186kb]

Daniel Berhane

more recommended stories