ዶ/ር አሸብር፡- ካፋ ለፕሬዚዳንትነት የሚመጥን ከሆነ ለእኔ ይገባኛል

ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፓን አፍሪካን ፓርላማ አባልከሪፖርተር ጋር በስልክ ያደረጉት ቃለ ምልልስ::

ሪፖርተር፡- ዶ/ር አሸብር ወደ አገር ውስጥ ጉዳይ እንመለስና ሕዝቡ ውስጥ እርስዎ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ በስፋት ይነገር ነበር፡፡ ለመሆኑ ከመንግሥት የተነገረዎት ነገር አለ ወይ? የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት እያሉ ተነግሮዎት ነበር ስለሚባል ነው፡፡MP Dr. Ashebir Woldegiorgis

ዶ/ር አሸብር፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት እያሉ ይኼ ተነገረኝ ይኼ አልተነገረኝም ብዬ የምናገረው የለም፡፡ ነገር ግን እንደ ዜጋና እንደ አንድ የካፋ ብሔር ተወላጅ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከሚሰጠኝ መብት አኳያ ገዥው ፓርቲ እስካሁን ፕሬዚዳንቶችን የሾመበትን አግባብ የሚረዳም ስለሆነ፣ ዶ/ር አሸብር ይገባዋል ወይም አይገባውም ብሎ ይወስናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዶ/ር አሸብር በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነትዎ ወቅት በነበረው ሙግት መንግሥት እርስዎን ያቁሙ እያለ ሲነግርዎት እርስዎ ግን ቀጥለውበት ነበር የሚባል ነገር አለ፡፡ ምን ያህል እውነት ነው? ግትር ነዎት ይባላል፡፡

ዶ/ር አሸብር፡- ይኼ በፍፁም መሠረተ ቢስ ወሬ ነው፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ የማከብረውን ሰውና በኃላፊነት የተቀመጠ አገር የሚመራ መሪ ፍፁም የምቀበል፣ የማከብርና ያለኝን የማዳምጥ ሰው ነኝ፡፡ ለምሳሌ በእግር ኳሱ ክርክር ጊዜ በወቅቱ ለአገሪቱ መሪ ጉዳዩን አቅርቤያለሁ፡፡ የያዝከው ጉዳይ ትክክል ነው፡፡ እንደ መንግሥት ጣልቃ መግባት ስለማንችል ነው፡፡ ፊፋ አመልክትና ውሳኔ ከዚያ ስታገኝ ውሳኔው ይከበርልሃል ተብዬ ተነግሮኝ ነበር፡፡ በመጨረሻ በራሴ ፈቃድ ፌዴሬሽኑን ስለቅ አሁንም በጣም የማከብረውና የማዳምጠው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ከመጀመሪያውም የሕግ የበላይነትን አረጋግጥ ብሎ ስለነገረኝ፣ በዕለቱም በፈቃዴ ሥልጣኑን የለቀቅኩት በነገረኝ መሠረት ነው፡፡ ይህም ማለት የማዳምጥና ምክር የምሰማ መሆኔን፣ ግትር ነው የሚለውም ሐሰት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እዚህ አገር እንኳን የማከብራቸው ነግረውኝ አይደለም ከዓይናቸው የሚወዱትንና የሚጠሉትን የማውቅላቸው የማከብራቸው ሰዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ሳይመካከርና ሳይደማመጥ መሥራት አይችልም፡፡ ያለበለዚያ በራሱ ጊዜ የሚጠፋና ፋይዳ ቢስ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ሰዎች ውስጥ ለውስጥና በይፋ ለፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ ዘመቻ መጀመራቸው ይሰማል፡፡ እርስዎስ?

ዶ/ር አሸብር፡- እኔ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ጠንቀቄ አውቀዋለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ሹመት በዘመቻ የሚሰጥ ድርጅት ሆኖ አላውቀውም፡፡ በቲፎዞም አይሰጥም፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዘመቻው ሥራ መጠመዳቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ የድርጅቱን ባህሪ ካለማወቅ የመጣ ይመስለኛል፡፡ እኔም በተፈጥሮዬ ሥልጣን ይሰጠኝ ብዬ ለዘመቻ የምሰማራ ሰው አይደለሁም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህ ሥልጣን ለካፋ ብሔር ይገባዋል፣ ሕዝቡም ለዚህ ጉዳይ ይመጥናል የሚል ከሆነ ለእኔ ይገባኛል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ትርጉም ደግሞ ለሌላ አካል ከሆነ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፕሬዚዳንትነቱን የማያሰጠኝ ከሆነ ወደፊት አየዋለሁ፡፡ ከዚህ በላይ መናገር አልችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እርስዎ ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ ተነግሮ ነበር ለሚባለው ጥያቄ እኮ መልስ አልሰጡም?

ዶ/ር አሸብር፡- ይህንን ወደፊት እመልሳለሁ፡፡ ለጊዜው በዚሁ ይብቃን፡፡

Read the full interview at EthiopianReporter – Aug. 14, 2013.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories