ኢ/ር ይልቃል:- በ2007 ምርጫ 99.6% እንዳናሸንፍ ነው የምንፈራው

Highlights:
* በአጠቃላይ ወደ አርባ ሺ አባላት አሉን፡፡

* ጃዋር ምን አገባው፤ ጃዋርም ኢህአዴግም ሃይማኖቱን የፖለቲካ መጫወቻ እያደረጉት ነው፤ ልቀቁት ነው እያልን ያለነው።

* እኔም በሳል ነኝ ብዬ ነው የማስበው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን እኮ ነው የምወዳደረው፤ ወጣት በሳል አይደለም ካልከኝ አንተ ወጣት ትንቃለህ ማለት ነው።

* የኦሮምኛ ቋንቋን ለማሳደግ ከፈረንጅ አገር የላቲን ቃላት የእንግሊዝኛ ፊደል ከማምጣት ግዕዝ ፊደልን ቢጠቀም የኦሮምኛ ቋንቋ አማርኛ ተናጋሪውን በቀላሉ እንዲለምደውና እንዲያድግ ማድረግ ይቻላል። ቋንቋውን የበለጠ ለማሳደግ ይጠቅመዋል። ለቋንቋው ከፈረንጅ ፊደል ይልቅ ከሰሜን ኢትዮጵያ የመጣው ግዕዝ ይሻለዋል። 

* [በሰልፉ ላይ ምንያህል ህዝብ እንደተገኘ] ቁጥሩን በግልፅ አላውቅም፡፡ እንደ ኢህአዴግ ወይንም እንደዛ ጋዜጠኛ ደፋር አይደለሁም፡፡ ወይንም እንደተናገሩት ባለስልጣናት፡፡ እኔ መሃንዲስ ነኝ ለቁጥር አልደፍርም፡፡

—–

(ብሩክ በርሄ እና የማነ ገብረሥላሴ)

ከቢሯቸው የተገኘነው ከረፋፈደ ነበር፡፡ ልናግራቸው እንደምንፈልግ በስልክ ባሳወቅናቸው ጊዜ የታማኝነት ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ገለጹልን፡፡ ለመደራደር ሲጠየቁም መቅረፀ ድምፅ የሚያስፈልገን እኛ ጋዜጠኛው ብቻ ሳይሆን እርሳቸውም እንደሆኑ ነገሩን፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በአንድ ወቅት ከአንድ መገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ መቀስ በዝቶበታል የሚል ነው፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ከቢሯቸው ስንገናኝ ግን ነገሩ ሌላ ሆነ፡፡ መቅረፀ ድምፁ ወደ ቪዲዮ ካሜራ ተቀይሯል፡፡ ነገሩ እኛን ጨምሮ በወቅቱ አብሮን የነበረው የፎቶ ግራፍ ባልደረባችንም ግራ አጋባ፡፡ ጉዳዩን በቀናነት አጤንነው፡፡ ወይ መቅረፀ ድምፅ አጥተው አልያም ምስሉን ለዶክመንት ፈልገውት ይሆናል ስንል፡፡ ለማንኛውም ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች የበዙበትን ቃለ መጠይቅ እንብዛም ባልተለመደ መልኩ ቢታጀብም በሚገባ ማካሄድ ችለናል፡፡

ከተመሠረተ አንድ ዓመት ከመንፈቅ የሞላው ሰማያዊ ፓርቲ በግንቦት ወር ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አገሪቱ ውስጥ ያሉ ወጣቶች እና ሴቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የሚገልጸው ፓርቲው ሰልፉን ተከትሎ ከመንግሥት ማግኘት የሚገባኝን ምላሽ አላገኘሁም ይላል፡፡ በመሆኑም ከሦስት ወር ምላሽ ጥበቃ በኋላ በሚቀጥለው ወር ዳግም ሰልፍ ለመጥራት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ እኛም በፓርቲው ምስረታ፣ በጠራው ሰልፍ ምላሽ ላይ፣ በቀጣይ እቅዶቹ እንዲሁም በአጠቃላይ የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው አቅርበ ነዋል።መልካም ንባብ፡፡Yilkal Getnet - Chairman of Semayawi (Blue) party - Ehiopia

አዲስ ዘመን፡- ሰማያዊ ፓርቲ በሃገሪቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴዎች እንዴት ይገልጹታል?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ሰማያዊ ፓርቲ ከተመሠረተ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አካባቢ ይሆነዋል፡፡ ሕጋዊ ሰርተፍኬት አውጥቶ ሙሉ እውቅና ካገኘ ግን አንድ ዓመት አካባቢ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ አካባቢ ባለው የምዝገባ አሠራር ችግር ምክንያት ሰርተፍኬት ለማግኘት ወደ ስምንት ወር ወስዶብናል፡፡ በሕጉ መሠረት ግን ከሦስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማለቅ ነበረበት፡፡ አጠቃላይ ሥራችንን ከጀመርን ግን አንድ ዓመት ያህል ሆኖናል፡፡ ከዚያን በፊት ግን ሦስት ወር ሞልቶት ሕጋዊ ሰርተፍኬት ካልተሰጠው እንደተሰጠው ይቆጠራል የሚል አዋጅ ስላለ በዚያ መሰረት እራሳችንን አሳውቀን ወጣን፡፡ በሂደትም ሰርተፍኬቱ ተሰጠን፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በአብዛኛው ሴቶች እና ዋጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ፓርቲ ነው፡፡ ይሄንን ስንል በኢትዮጵያ ውስጥ ሰባ ከመቶ የሚሆነው የሕዝብ ቁጥር ከ35 ዓመት በታች ነው፡፡ ይሄ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያምንበት መረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ከሕዝብ ቁጥር ውስጥ 70 ከመቶ ከሆነ ይሄን ትኩረት አድርጎ መሥራት አንደኛ ዴሞክራሲና ፖለቲካ የውክልና ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛ ይሄንን ሕዝብ በፖለቲካ ማንቃትና ማደራጀት ለአገር የሚኖረው ጥቅም ቀላል ባለመሆኑ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይችላል፡፡ የሴቶቹም ቁጥር 51 በመቶ ያህል ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ አተኩሮ መሥራት በኢትዮጵያ ወደፊት ለዴሞክራሲ እና ነፃነት ለሚደረገው ትግል መልካም ሥራ እንሠራለን ብለን እናስባለን፡፡ በክፍለ ሀገርም መዋቅሮች አሉን፡፡ አደረጃጀታችን በብዛት ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ እንደበፊቱ የግድ ቢሮ ከፍቶ እዛው ቁጭ በማለት የሚደረግ አይደለም፡፡ የወጣት ፓርቲ ነው ስንልም አደረጃጀታችንም አሠራራችንም የትኩረት አቅጣጫችንም በፊት ከነበረው ሁኔታ ለየት ባለ መልኩ ዝግጅት እያደረግን እየሠራን እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ምን ያህል አባላት አሏችሁ? በቴክኖሎጂ የምታደርጉትስ ግንኙነት በቂ ነው?

ኢንጂነር ይልቃል፡- አንድ ሰው የፓርቲው አባል ሲሆን የሚያስፈልገው መታወቂያ አለ፡፡ አጠቃላይ መረጃውም ተመዝግቦ ይቀመጣል፡፡ በፊት እንደሚደ ራጀው እዚያው ተቀምጠክ ስብሰባ ተሰብስበክ ኮሚቴ እንደዚያ ማድረግ ላይጠበቅብክ ይችላል፡፡ ሲመዘገቡ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ነው፡፡ ነገር ግን በድሮ ጊዜ እንደሚደረገው እከሌ ክፍለ ከተማ ላይ ተሰብስበዋል በሚለው ዓይነት የአደረጃጀት ስልት አይደለም፡፡ አውሮፓ ሆነህ እዚያ መገበያየት እንደምትችለው ዕቃ ታመጣለህ፣ መረጃ ትሰጣለክ፣ ትፈራረማለህ እና ውል ትገባለህ ለማለት ፈልጌ እንጂ ዝም ብሎ ፌስ ቡክ ላይ ያለ ሠው ሁሉ የእኛ አባል ነው ማለታችን አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ወደ አርባ ሺ አባላት አሉን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግንቦት ወር ባካሄዳችሁት ሰልፍ ምን ውጤት አገኛችሁ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- እስከአሁን ምንም እዚህ ግባ የሚባል ያገኘነው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በሰልፉ ወቅት የመጨረሻ ንግግር ሳደርግ መልስ እንዲሰጠን አሁንም ለሦስት ወር ጊዜ ሰጥተን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ ችግር አለ፡፡ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ጉዳዩ እጅግ መዘበራረቅ በዝቶበታል፡፡ ይሄም የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፖሊሲው ልክ ባለመሆኑ የተነሳ በዚያ የሚታዩ ችግሮችና ውጤቶች አሉ፡፡ ሥራ አጥነት፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የዋጋ ንረትን የመሳሰሉ ችግሮች አሉ፡፡ በመሆኑም በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጠይቀናል፡፡ በሁለተኛነት በአገሪቱ ሙስና ተስፋፋ ይባላል፡፡ በአገሪቱ ሙስና የተስፋፋው በፖለቲካው፣ በማኅበራዊውና ኢኮኖሚው የአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም የበላይነት በመኖሩ የታፈነ ሀገር ስለሆነ ፍፁም ኃይልና ሙስና እንዲኖር አድርጓል ነው፡፡ ሚዲያውንም በመዝጋቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ለእዚህ ማሳያ ከሚሆኑት መካከል ብዙ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እሥር ቤት ናቸው፡፡ በዚያ ሂደት ውስጥ አንድ የሰረቀ ሰው በማባረር የኢትዮጵያን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሙስና እንዲጠፋ ከተፈለገ ሚዲያ በሰፊው መንግሥትን መተቸት አለበት፡፡ ስለመንግሥት ባለሥልጣናት ድክመት እና ጥንካሬ መጻፍ አለበት፡፡ ይሄ በሚሆን ጊዜ በቀላሉ ሌብነት ንፋስ ይገባዋል፡፡ የተለየ የፖለቲካ ፓርቲ አማራጭ እንዳለው ሲያስብ ያለው ገዢ መንግሥት እራሱን ዘላለማዊና የተለየ ፍጡር አድርጎ ማሰብ ያቆማል፡፡ ስለዚህ ሲቪክ ማኅበራትን ባይዘጋ፤ሲቪክ ማኅበራት ደግሞ ማኅበረሰቡን ማስተማር እና ለኃላፊነት ማብቃት በሚችሉ ጊዜ እነዚህ ነገሮች መጥፋት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ቁርጠኛ ነው፤ ሚኒስትር እከሌን አሠረ እየተባለ ስላላገጠ እነዚህን ነገሮች አያጠፋም፡፡ እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች እና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ጠይቀናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የአፈና ውጤት ናቸው፡፡

ከእዚያ በተረፈ መንግሥት እና ሃይማኖት አይገናኝም፤ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው ይላል መንግሥት፡፡ ነገር ግን በተግባር ያየነው ባለፈው ሁለት ዓመት ሊሆን ነው ኢህአዴግ የራሱ የሚለውን ርዕዮተ ዓለም በሃይማኖት ውስጥ ገብቶ ይሄኛው ዋህቢያ ነው፤ ይሄኛው ሰለፊ ነው፤ ይሄኛው አክራሪ ነው፤ በቀበሌ ምረጡ እንደዚህ አድርጉ እለ፤በውስጥ ጉዳይ ገብቶ የማይሆን ነገር ወደ ዳር እየገፋውና ምናልባትም ሁሉም የአስልምና ተከታይ በሚባል ሁኔታ ቅሬታ ውስጥ ገብቷል፡፡ መሪዎችንም አሠረ፤ የፍርድ ሂደቱን ማንም አያይም፤ ምን ምስክር እንደሚሰጥ አይታወቅም እተባለ በኢ ቲ ቪ የሚወራውን ካልሆነ በስተቀር እውነታውን ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዝግ በመሆኑ በልቡ የሚያውቀው ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ ከአሥራ ስምንት ዓመት እስከ ሰማኒያ ዓመት ዕድሜ ድረስ ሁሉ በየሳምንቱ እየወጡ ሲጮሁ ጥቂት አክራሪዎች ናቸው እያለ እየሄደበት ነው፡፡ እናም ኢህአዴግ ጉዳዩን የያስክበት መንገድ ልክ አይደለም፤ ከኃይማኖት ላይ እጅህን አንሳ፤ እራስህ ፈቃድና እውቅና ሰጥተሃቸው ስትደራደር ከቆየህ በኋላ አክራሪዎች ናቸው ወይንም ሽብርተኞች ናቸው ብሎ ማሠር እፍረት ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት ካለ ቆራጥነት ማነስ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ስለማይበጅ እነዚህን ሰዎች መፍታት የራሳቸውንም መሪዎች እንዲመርጡ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚያን በኋላ ግን ችግር ሲያመጡ በሂደት ሚዲያውም ሕዝብም ያየዋል፤ዓለም አቀፍ ተቋማትም እራሱ የእስልምና እምነት ተከታዩም እነዛ ሰዎች ወዴት እንደሚሄዱ ያያል፡፡ ያኔ ሁላችንም እንታገለዋለን፡፡ የሚባለው ስጋት ካለኮ ማንም ቂል አይደለም፡፡ አገሩን ለሽብርተኛ አሳልፎ የሚሰጥ የለም፤ ማንም ሰው ቢሆን አገሩ እንድትተራመስበት አይፈልግም፡፡ እነርሱ እንደሆኑ ሀብታሞች ናቸው ብድግ ብለው የዘረፉትን ብር ይዘው ወደየትም አገር ይሄዳሉ፡፡ እኔና አንተ እኮ ይሄ ሀገር ቢተራመስ መውጫ መግቢያ የምናጣው፡፡ እነዚህን አራት ጥያቄዎች እንዲመልስ የምንጠይቀው፡፡ ሰዎች ከሚኖሩበት ቦታ ማፈናቀል ይቁም፡፡ በእስልምና እምነት አስተባባሪ ኮሚቴ ብሎ እውቅና ሰጥቶ ሲደራደርባቸው የነበሩ ሰዎችን እንዲፈታ፡፡ ጋዜጠኞችን እና የፖለቲካ መሪዎችን እንዲፈታ፡፡ በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት በኩልም ያለውን ችግር የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማሻሻል ለውጥ እንዲያደርግ ጠይቀነዋል፡፡ እስከአሁን ድረስ ግን ምንም ዓይነት ውጤት አላገኘንም፡፡ እንዳሁም እኛ ሰልፍ ባደረግን በንጋታው በቴሌቪዥን መልስ ሲሰጥ አክራሪዎች ናቸው፡፡ ፖለቲካና ኃይማኖትን የሚደባልቁ ናቸው፡፡ የተለዬ አጀንዳ አላቸው፡፡ የወጣው ሰው ሁለት ሺ ብቻ ነው በማለት ነገሩን ከማጥላላት ያለፈ በቆራጥነት አንድ የፖለቲካ ኃይል መሆናችንን፤ያ ሁሉ ሕዝብ የጠየቀውን ተገንዝቦ፤ እንደነርሱ ከጫካ ባንመጣም እኛም አገር ለመምራት የምንወዳደር መሆኑን አስቦ እንኳን እውቅና ለመስጠት አልፈለገም፡፡ ይሄም በመሆኑ በሚቀጥለው ነሐሴ 26 ሦስት ወር ስለሚሞላ የጠየቅናቸው ጥያቄዎችም መልስ ስላላገኙ መልስ እንዲሰጡን በድጋሚ በሰልፍ እንጠይቃለን፡፡ ለዚያም በቂ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ጂኦ ፖለቲክስ አንፃር አክራሪነት እና የኃይማኖት ፅንፈኝነት የአገሪቱ አደጋ ነው ብለው አያምኑም?

ኢንጂነር ይልቃል፡- አምናለሁ እንጂ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በተደረገ የመጅሊስ እና ዑለማዎች ምክር ቤት አባቶች ስብሰባ ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለስልጣን እንደ ምርኩዝ እየተጠቀሙብን ነው ብሎ እናንተን ይከሳሉ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ምን እኛኮ የማንከሰሰው ነገር የለም፡፡ የትኛውም አገዛዝ ከርሱ የተለየ አመለካከት ያላቸውን በሙሉ ምን እንደሚል እናውቃለን፡፡ እንረዳዋለን፡፡ ደርግ እነርሱንኮ አስገንጣይ ወንበዴዎች ነበር የሚላቸው፡፡ አገር ከሀዲዎች፤ የእናት ጡት ነካሾች፤

አዲስ ዘመን፡- አሁን የምጠይቅዎት ከመንግስት ውጪ ያሉትን ነው፤ የኃይማኖት አባቶች እየከሰሷችሁ ነው የሚል ነው ጥያቄው?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ደህና አሁን እኔ እውነቱን ነው የማየው፡፡ የሚከሰን ሰው እንዲኖር አንድ የፖለቲካ አመለካከት ስታራምድ ያንተን የፖለቲካ አስተሳሰብ ከመንግስት የተጠጋ የኃይማኖት መሪ የለም ብዬ አላምንም፡፡ እንዳውም እኮ የኢህአዴግ ዋነኛው አላማ ኮሚኒስት በመሆኑ ሁሉንም ተቋማት በመቆጣጠር ችግር ያመጣውኮ ይሄ ነው፤ የኢህአዴግ የቁጥጥር ሂደት ፖለቲካዊ ፈትል ይሰጠውና ለችግሩ ሌላ ይዘት ይሰጠዋል፡፡ አሁን እንደነገርኩህ እኔ በእምነት ውስጥ ትርምስ እንዲፈጠር ስለምፈልግ ነው? አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ለስልጣኑ ስለሚሰጋ የኔን እንቅስቃሴ ረግጦ ማለፍ ይቀለዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ግን እንየው እስኪ፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ካለ ከኢህአዴግ በፊት እኔ እታገለዋለው፡፡ ለምንድነው ወደ ስልጣን ለመሄድ? በኢትዮጰያ ውስጥ ያለውኮ የድህነት እንትን ገደብ የለውምኮ፡፡ ከአለም እኮ ሦስተኛዋ ደሃ አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ መንግስትን ለመንቀፍ ችግር ጠፍቶ ነው? ይሄ ችግርኮ ሲፈጠር እኛ የለንበትም፡፡ እናም እኚህ ሰዎች መንግስት ተቆጣጥሯቸው፣ መንግስት በተለያየ ሁኔታ የራሱን አመለካከት ያለው ከፍል/ሴክት/ ተቆጣጥሮ ያንን ለመጫን (ኢንፖዝ) የሚያደርገው ነገር አልጠቀመም፡፡ እማየውን ነው እኔ የምናገረው፡፡ አንድ ሰው ያለኝን ሳይሆን፤ እንዲህ ሆኖ እዚህ ቤት ስጋት ተፈጥሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው በየቀኑ እየወጡ የማየው፡፡ ከትልቅ እስከ ሽማግሌ፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ ሰው ሲሞት አያለሁ፡፡ ገንዘብ ሲጠፋ አያለሁ፡፡ ጊዜ ሲጠፋ አያለሁ፡፡ ይሄ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየበዛ ሲሄድ አያለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ marginalized ባደረገ ጊዜ ውሎ አድሮ ልክ ኢህአዴግ በያዘበት የችግር አፈታት ከሆነ ነው አገሬ ችግር ውስጥ የምትገባው፡፡ በእውነት ልንገርህ አይደለም ኢህአዴግ ለፖለቲካ ቁጥጥር ሲል ሁሉን ነገር የሚያደርገው ነገር ከርሱ ቁጥጥር ውጪ ወጥቶ አገሩን እንዳያጠፋውና የታሪክ ተጠያቂ እንዳይሆን፡፡ አንዳንድ ሰዎች መንግስት የሚደግፉና ከመንግስት የተለየ ቅርበት ያላቸው ናቸው፡፡ ኢህአዴግ እኮ የሚደግፈው አለ፤ስለ ልማታዊ አመለካከት ያለው ኃይማኖተኛ ይፈልጋል፡፡ በኃይማኖት ቀናት ሁሉ ስለ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የሚያወራ ኃይማኖት መሪ ይፈልጋል፡፡ ግን የኃይማኖት መሪ ከፖለቲካ ጋር ነፃ ነው፤ የኔንም ፓርቲ ሊደግፍ ይችላል፤ ላይደግፍ ይችላል፡፡ እምነቱን ግን ከፖለቲካው ጋር አያይዞ የሚያወራበት በተለይም ተቋሙን ሲሆን አንተም እኔም ፖለቲከኛ ሆነን እምነት ሊኖረን ይችላል፡፡ ግን ያን እምነታችንን ተቋሙ ላይ ተጭነን ሌላ አይነት ነገር ስናመጣ ልክ ነውና «አንዳንድ» እየተባለ የሚገለጸውም ነገር አንዳንድ ቢሆኑ ኖሮ እኛ ጥፋተኛ ሆነን እነዛ ሰዎች ትክክል ሆነው ችግሩ ተፈቶ ቢሆን እሰየው ነበር፡፡ በእውነት ግን ያለው ችግር እርሱ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ካለው የቁጥጥር…፤

አዲስ ዘመን፡- እናንተን እያወገዙ ያሉት እኮ በ2005 ዓ.ም በሙስሊሙ የተመረጡ የሃይማኖት አባቶች ናቸው፡፡ በየደረጃው ከቀበሌ አስከ ፌዴራል ያሉ ናቸው ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- በኢህአዴግ ቀበሌ ውስጥ እኮ ነው የተመረጡት፡፡ ችግሩ ያለው እኮ እነዚህ ሰዎች በኢህአዴግ የካድሬ መዋቅር ነው፡፡ ቀበሌም የመንግስት መዋቅር ነው አይደል? መንግስት እና ኃይማኖት ግንኙነት የላቸውም፡፡ እኛ ኃይማኖታችንን የምንፈጥረው የኃይማኖታችን አካሄድ በሚለው መሰረት ነው፡፡ ለነሱ መንግስት የተለየ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ኃይማኖታችን በነፃነት አልፈጠርንም፡፡ መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል ነው ዋናው ጥያቄ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ደግሞ የኃይማኖት አባቶች የሚሉት ምርጫው በቀበሌ መደረጉ አንደኛ በመስጊድ ሴቶችን (በተፈጥሮ ምክንያት) ተሳታፊ ለማድረግ ስለማይቻል ከሚል ጋር በተያያዘና ስፍራውም ለፀሎትና ሌሎች ኃይማኖታዊ ጉዳዮች ማከናወኛ በመሆኑ ምርጫው በቀበሌ ይደረግ ተብሏል፡፡ በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?Yilkal Getnet - Chairman of Semayawi (Blue) party - Ehiopia

ኢንጂነር ይልቃል፡- እኔ የምልህ እኮ እነዛ ሰዎች ትክክል ሆኖ 29 ሰው ባይታሰር፣ ይሄ ሁሉ ሰው በየሳምንቱ ባይወጣ፣ ንብረት ባይጠፋ፤ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እኮ ሌላ ነገር አጥቶ 24 ሰዓት የሚያወራው ለምንድነው? ይሄ የሀገር ችግር ሆኗል፡፡ ዘዴና ቅስት ሌላ ነገር ነው፡፡ ለፖለቲካ ቁጥጥር ሲባል ኢህአዴግ አስር ሰው ቀርፆ የሚለው ነገር ውሸት ነው፡፡ እኛ በትክክል የምናምነው፤ አቋሜ ነው በግልፅ እንደ ድርጅትም ነው የምነግርህ፡፡ ኢህአዴግ የእስልምና እምነት ላይ ገብቶ የሚያዳክረው ነገር ለአገራችን ስጋት ነው፡፡ ሽብር የሚመጣው በኢህአዴግ በኩል ነው፡፡ ካለብን የቀጣና አንፃር ወደ እልህ፣ ወደ ፅንፈኝነት እና ወደ ሌላ ነገር የሚገፋው ኢህአዴግ ነው፡፡ አሁን እኔም ወደዛው የምሄድ እየመሰለኝ እየሰጋሁ ነው፡፡ ያንን ነገር አቁም ነው የምንለው፡፡ በድፍረት፡፡ ይሄ ማሰር፣ መወንጀል፣ ፊልም መቅረፅ የራሱ ነው፡፡ አገሬ ስለሆነ የሚመጣውን ነገር በታሪክም ስለምጠየቅ ነገም የሚሆን ነገር ኢህአዴግ ይሄዳል፡፡ ከኢህአዴግ በፊት የነበሩት ኢህአዴግን ምን እንደሚሉት እናውቃለን፡፡ ኢህአዴግ እኔንም እንደሚፈርጀኝ ይታወቃል፡፡ ማንዴላ ከእስር ቤት እስኪወጣ ድረስ አሸባሪ እንደነበር ታውቃለህ? ስለዚህ ሽብርተኝነት ምናምን እያለ ኢህአዴግ የሚያላግጠው ነገር ጉዳያችን አይደለም፡፡ እኛ እንዳውም የምንታገለው እሱን ነው፡፡ ለራሱ የፖለቲካ ስልጣኑን ለማራዘም ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ሕጎችን እያወጣ አገሩን እያፈነ፣ ሙስና እየተስፋፋ፣ስራ አጥነት እየተባባሰ፤ በጎሳ የነበረው አሁን ደግሞ በኃይማኖት ገብቶ ኢትዮጵያን አንገቷን እያነቃት ነው፡፡ለኢህአዴግ ደግመን ደጋግመን የምንጠይቀው ነገር ይሄንኑ ነው፡፡ በፅሑፍ ጠይቀነዋል፡፡ አሁን ደግሞ በሰልፍ ጠይቀናል፡፡ደግመን ደግሞ እንጠይቀዋለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ በሰላማዊ ሰልፍ ማንሳታችሁ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጣልቃ መግባት አይሆንም ወይ? የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ህግ ይከበር እያሉ ህግን መጣስ ተገቢ አይደለም የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምድንነው?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ሕግ መጣስ አይደለም፡፡ አንድ ሰው በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ላይ ገብተህ ይሄ አንቀፅ ትክክል አይደለም፣ ዳኛው የወሰነው ትክክል አይደለም፣ ይሄ እንደዚህ ነው፣ እንደዚያ ነው፣ መረጃው ትክክል ነው፣ አይደለም ስትል እንጂ አጠቃላይ እንደው አንድ ሰውኮ ጥፋተኛ ሆኖ እስኪገኝ ተጠርጣሪ ነው፡፡ መንግስትም ተጠርጣሪ ነው የሚላቸው፡፡ ወንጀለኛ አይላቸውም፡፡ እኛ የጠረጠርክበት ሂደትና አጠቃላይ ሂደቱ ፖለቲካዊ መነሳሳት ነው፡፡ ለምሳሌ ሰዎቹ ከመታሰራቸው በፊት ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጅሃዳዊ ሃረካት ብሎ ሰራባቸው፡፡ ፖሊሱ እየወጣ፣ ዳኛው እየወጣ ወንጀለኛ አደረገ፡፡ ያንንኮ ነው እኛ ልንቃወም የወጣነው፡፡ መንግስት በኃይማኖት ገበቷል ስንል አስቀድሞ ወንጀለኛ(criminalize) አድርጓቸዋል ነው ያልነው፡፡ ሰዎችንም አሰቃይተሃል ነው ያልነው፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ተግባሩ ፀረ ሕገ-መንግስት ነው፡፡ ሰዎች በፍርድ ቤት እስከሚረጋገጥባቸው ድረስ ንጹህ ሆኖ የመታየት መብት አላቸው፡፡ ወገንተኛ የሚያደርግ ነገር ስለያዝክ ልክ አይደለም ብለን ነው ለመቃወም የወጣነው፡፡ ስለዚህ በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አይቻልም የሚባለው ጉዳይ ትክክል አይደለም፡፡ የቀረበው መረጃ ውሸት ነው፡፡ እንደዚህ ነው ብሎ በሕጉ ጉዳይ ላይ ቴክኒካል አስተያየት መስጠት እንጂ ፖለቲካዊ ትርጉም (ስቴትመንት) መስጠት ወንጀል ነው ማለት ትክክል አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ግን በትልቁ የተስተጋባው መፈክር «የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ» የሚል ነው?

ኢንጂነር ይልቃል፡- በትክክል።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ ገና በሕግ የተያዘን ጉዳይ ወንጀለኛ ነው ወይንም አይደለም ሳይባል፤ ፍርድ ቤቶች በአንቀፅ 78 ነፃ ናቸው እየተባለ፤ እነዚህ ሰዎች ነፃ ናቸው ማለታቹ ከሕገ መንግስቱ ጋር አይቃረንም ወይ? እነርሱስ በያዙት አቋም ዳኛው ላይ ተፅእኖ አይፈጥርም? በጩኸትና ሁካታ የታሰረ ሰው ይፈታል ወይ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- አንደኛ የታሰሩት በኛ እምነት አልኩህ እኮ፤ አሁን አንተ የምትጠይቀኝ፤ why you give me double standard ለኔ? ኃላፊነቱንና ሕግ የማስከበር ሂደቱን መንግስት መውሰድ እያለበት ለምንድነው በመንግስት ቴሌቪዥን ሰዎቹ ገና ሳይፈረድባቸው ወንጀለኛ አድርጎ ፊልም የሚያሰራባቸው? ይሄን ተቃውሜ ስመጣ አንተ ወንጀለኛ ታደርገኛለህ፡፡ ሕግ የጣስኩ አድርገህ፡፡ መንግስት ነው በመንግስት ቴሌቪዥን የመንግስት ባለስልጣናት እየወጡ እነዚህን ሰዎች ወንጀለኛ ሲያደርጉ ምንም ያላለው፡፡ ለምን አደረጋቹ ብለህ መጀመሪያ እነሱን ጠይቃቸው እስኪ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ እኔ አንድን ሰው ብሰድብ ያ ሰው ይከሰኛል፡፡ እየከሰሰኝ እያለ መልሶ ቢሰድበኝ እኔም እከሰዋለው፤ አሁን መንግስትን በፍርድ በተያዘ ጉዳይ ዘገባ አስተላልፏል ብላችሁ እየከሰሳችሁ ነው፡፡ እናንትም በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ ታነሳላችሁ፤ስለዚህ ጥፋትን በጥፋት ነው ወይስ እርሱ እንዲስተካከል ነው የምትታገሉት?

ኢንጂነር ይልቃል፡- እኛኮ የሰጠነው አስተያየት በእስልምና እምነት ላይ የገባኸው ነገር አለ፡፡ መጀመሪያ እውቅና ሰጥተሃቸው ስትደራደር ቆየህ፤ በዚህ ጉዳይ ተስማምተናል፤ በዚህ ጉዳይ አልተስማማንም እያልክ በመግለጫ ስትነግረን ቆየህ፡፡ ከዛን በመጨረሻ ደግሞ ሽብርተኛ አደረግሃቸው፡፡ መጀመሪያውንም የአንድ ኃይማኖት ደግፈክ ስልጠና ሰጠህ፤ ከዛ በቀበሌ ምረጡ አልህ፡፡ እምቢ አሉ፡፡ ከዛን ደግሞ ወንጀለኛ አደረግክና ፊልም ሰራህባቸው፡፡ ይሄ ሂደት አጠቃላይ የፖለቲካ መነሻ ነው፤ ለኢትዮጵያ አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የሕግ ጉዳይ ነው፡፡ ልቀቃቸው፡፡ ይሄ ጉዳይ በአስተዳደር እና በፖለቲካ የሚፈታ ነው፤ መንገድ ጥሰሃል፤ ኃይማኖትን እና ፖለቲካን አንድ በማድረግ የመጣ ነገር ነው፡፡ ይሄን አቁም ነው ያልነው፡፡ ይሄ ደግሞ አቋም ነው፤ አምነንበታልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሰማያዊ ፓርቲ ሕገ መንግስቱን እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ያስከብራል ብላችሁ ታምናላችሁ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- አዎ፡፡ ባናምንማ እዚህ ኮትና ሱሪ ለብሰን አንተ እየጠየቅክ እኛም እንደዚህ እያየን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- መገለጫው ሊሆን የሚችለው ምንድነው?

ኢንጂነር ይልቃል፡- መገለጫው? ቢሮ ተከራይተን፣ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት አጠገብ ቁጭ ብለን፣ አዲስ ዘመን እየመጣ፣ እኛ ሰርተፍኬት አውጥተናል፣ ሰልፍ እየወጣው ለምሳሌ ባለፈው ከመዘጋጃ ቤት ወረቀት አምጥቼ በሺ የሚቆጠር ሰው ወጥቶ እየመራሁ በእግሬ እየሄድኩ ነው የምሰራው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሰማያዊ ፓርቲ ሕገ መንግስቱን አምኖ ይቀበላል? ለተግባራዊነቱስ ይሰራል?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ሕገ መንግስቱኮ በጣም ጥሩ ጥሩ አንቀጾች አሉት፡፡ ሕገ መንግስቱን እናከብራለን፤ በሕገ መንግስቱ መሰረት አምነን ነው የተደራጀነው፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግስቱ በራሱ በሚፈቅደው መሰረት ስልጣን ስንይዝ በሕገ መንግስቱ ውስጥ እንዲሻሻል የምንፈልጋቸው አንቀጾች አሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንዲሻሻሉ? ግን ተግባራዊ ታደርጋላችሁ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- በሚገባ፡፡ መንግስትንም የምንከሰው እኮ የምታወጣው ሕግ ሁሉ ፀረ ሕገ መንግስት እየሆነ መጥቷል ብለን ነው፡፡ አሁን ለምሣሌ እነዚህን ሰዎች ስታስር ሕግ ጥሰሃል፡፡ በኃይማኖት እና በፖለቲካ ገብተህ ሕገ መንግስቱን ጥሰሃል፤ ሰዎች ከፍርድ በፊት እንደ ነፃ የመቆጠር መብታቸውን የሚያሳየውን ሕግ ጥሰሃል እያልን ነው የምንከሰው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአንቀፅ 11 መሰረት ኃይማኖት እና መንግስት የተለያዩ ናቸው ነገር ግን ጣልቃ ገብተሃል እያላችሁ ትከሳላችሁ፣ እንዲሁም የመናገር፣ የመሰብሰብ መብት ይከበር ብላቹ ነው የወጣችሁት፡፡ ነገር ግን በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ ሦስት ያልተፈቀደ ሰንደቅ አላማ ይዘው የወጡ ነበሩ፡፡ በዕለቱ የተንፀባረቁ መፈክሮችም የሌሎችን ክብር የሚነኩ ነበሩ፡፡ ለምሣሌ «ወኔ የሌለው የአገር ሸክም ነው»፣ «አትነሳም ወይ ይሄ ሀገር ያንተ አይደለም ወይ?» የሚሉና ሌሎችም ፀያፍ ቃላት መሰማታቸው ተገቢ ነበር?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ወኔ የሌለው የአገር ሸክም ነው እና አትነሳም ወይ ይሄ አገር ያንተ አይደለም ወይ? የሚሉት ተገቢ መፈክሮች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ የልማት አርበኛ ምናምን ይላል አይደል እንዴ? ለዚህ ትውልድ ወኔም ያስፈልጋል፡፡ ወኔ ቢስ ትውልድ እንዲኖር አልፈልግም፡፡ ወኔ ያለው፣ የተግባር ሰው፣ ወደፊትን ማየት የሚችል፣ በራሱ የሚተማመን ዜጋ እንዲፈጠር እንሰራለን፡፡ ወኔ ቢስ ትውልድ የአገር ሸክም መሆኑ ምን ያጠራጥራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- መልእክቱ እኮ በሰልፍ ላልተገኘው ሰው ነው አይደል?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ኢንቴንሽኑም ሞቲቭም አንተ ነህ የምትለው፡፡ ማን አለ እስኪ? ለሁለቱም ትርጉም የምትሰጠው አንተ ነህ፡፡ እኔ ያልኩህ ወኔ የሌለው የአገር ሸክም ነው፡፡ ደግሞም በሰልፍ ያነቃቃል፡፡ ደስ ይላል፡፡ ወጣቱ እንዲያውቅና መብቱን እንዲያስከብር እንፈልጋለን፡፡ ባንዲራ መያዝና አለመያዝ ለሚለው የያዘ ሰው አላየሁም፡፡

አዲስ ዘመን፡- መያዝ አለመያዝ ሳይሆን የኮከብ አርማ የሌለው ይዘው ነው የወጡት ለሚለውስ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- እኔ አላየሁም፡፡ አንድ ማወቅ ያለብን እኔ ግብር ከፋይ ነኝ፤ ሰልፉን ሳሳውቅ ዋናው አላማዬ በሰልፉ ወቅት የሚፈጠር ችግር ካለ ይሄንን ነገር መልክ አስይዝ ለማለት ነው፡፡ እኔ የምወጣው ለነዚህ ጥያቄዎች ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የወጣ ካለ አንተ ጠብቀኝ ብዬ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ችግር ከተፈጠረም መንግስት ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ይሄንን ማድረግ እየተገባው ካላደረገ የሚጠየቀው መንግስት ነው፡፡ እንደዛ አይነት ባንዲራ ይዞ የወጣ ካለ በባንዲራ ሕግ ይከሰሳል፡፡ የፖሊስ ስራው ይሄንን መቆጣጠር ነው፡፡ ገንዘብ የከፈልነውም ይሄንኑ እንዲያደርግ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጥተው ሁለት ሰው ሊሆን ይችላል ያንን ያደረገው፡፡ ስለዚ እኔን መወንጀል አይችልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሰልፉ ላይ ምንያህል ህዝብ ተገኘ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ቁጥሩን በግልፅ አላውቅም፡፡ እንደ ኢህአዴግ ወይንም እንደዛ ጋዜጠኛ ደፋር አይደለሁም፡፡ ወይንም እንደተናገሩት ባለስልጣናት፡፡ እኔ መሃንዲስ ነኝ ለቁጥር አልደፍርም፡፡ ቁጥሩ ላይ ብዙ ተብሏል፡፡ ነገር ግን ለኔ ዋናው ነገር ከስምንት ዓመት በኋላ በአደባባይ ወጥቶ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መብቱን መግለፁ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሰልፋቹ ላይ ፅንፈኛ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በብዛት እንደተገኙ ይነገራል፡፡ የአንድ ሃይማኖት ወካይ መስሎ ለመታየት የተደረገው ጥረት ተገቢ ነውን?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ፊልሙን አይቼዋለው፡፡ በኋላ ላይ እንደዚህ አይነት አሉባልታ ስሰማ፡፡ የነበሩት በብዛት ወጣቶች ናቸው፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ነበሩ፡፡ ሴት፣ ወንድ፣ ክርስቲያን፣ ሙስሊም ሁሉም ነበር፡፡ የሚሰሙት መፈክሮች በብዛት አጀንዳ ያልናቸውን በሙሉ ማንፀባረቅ ችለናል፡፡ በጣም የወደድኳት መፈክርም «ወኔ የሌለው የአገር ሸክም ነው» የሚለውን ነው፡፡ መንግስት ሲያጠፋ በወኔ እንጠይቃለን፡፡ ኢህአዴግ ስለሚለኝ ሳይሆን የማወራው ስለ እውነታው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጨዋና በሕግ የሚያምኑ በመሆናቸው ሰልፉ ያለምንም ችግር በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ ኢህአዴግ ግን በተለያየ መንገድ ጉዳዩን ወደ ፖለቲካ መነዘረው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አህአዴግን አሁን አጀንዳችን አናድርገውና በሰልፉ ወቅት የነበረው ስብጥር ነው ከተባለ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አይቃረንም ወይ?

ኢንጂነር ይልቃል፡- ተቃራኒው ያንተ ሃሳብ ነው፡፡ ፊልሙን አሁን ላሳይክ እችላለው፡፡ ግን የኃይማኖታቸው ነፃነት እንዲከበር የሚጠይቁ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከጥያቄውም አንዱ ነው፡፡ ይሄ ጥያቄም ጎላ ብሎ ይሰማ ነበር፡፡ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ መሆኑን መረዳት አለብክ፡፡ እኛ ፖለቲከኞች ኢህአዴግ ታገልኩለት ከሚለው አንዱ የእምነት ነፃነት ነው፡፡ አሁን ግን በእምነት ውስጥ ኢህአዴግ ዘባረቀና የእምነት ነፃነት ነፈገ ነው ያልነው፡፡ ፓርቲያችን ጉዳዩን በግልፅ አጀንዳ አድርጎት ወጥቷል፡፡

አዲስ ዘመን፦አሁንም ከእዚህ ሳንወጣ በሰላማዊ ሰልፉ ጎልቶ የወጣውን ነገር የሃይማኖት ጉዳይ ነው፤ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሃይማኖትና ፖለቲካ መለያየት አለባቸው የሚል አቋም አላችሁ?

ኢንጅነር ይልቃል፦አዎ፡፡

አዲስ ዘመን፦ለምንድ ነው ታድያ ይህንን በሰልፉ ማሳየት ያልቻላችሁት?

ኢንጅነር ይልቃል፦አሳየን እንጂ !በትክክለኛ መንገድ ነው ያሳየነው። ነገርኩህ እኮ፤ አሁንም የምነግርህ ህገ መንግስቱ ሃይማኖትና መንግስት ስለ መለያየታቸው እንጂ ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው አይልም። የሃይማኖት ነጻነት የእምነት ነጻነት ነው። አንድ ሰው የፈለገውን አመለካከት የመያዝ መብት ደግሞ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው።እንዲገባህ ብዬ ነው። የዴሞክራሲ ጥያቄ ደግሞ የፖለቲካ ጥያቄ ነው።አንድ ሰው በእምነቱ ጭቆና ሲደርስበት ለዛ መብት መታገል የፖለቲካ ጥያቄ ነው። ይህንን በደንብ እወቁት። ነገር ግን ወንጀል የሚሆነው፤ ህገ ወጥ ጸረ ህገ መንግስት የሚሆነው ልክ ኢህአዴግ እንደሚያደርገው በሃይማኖት ውስጥ መንግስት ጣልቃ ገብቶ አስቀድሞ ሲያስር፤ በመስጊድ መከናወን ያለበት ምርጫ ቀበሌ ሲያስመርጥ፤ ወንጀል እየሰራ ፊልም ሲሰራ፤ አንድ ዓመት ሙሉ ያን ሁሉ ህዝብ ተቃውሞውን እያሰማ ጥቂቶች ናቸው እያሉ ነገሩን በጉልበት ለመምታት ሲሞክር ፤ ጠርዝ እየያዘ አገር የሚበጠብጥ ነገር ይሄ ሲሆን ነው። ይሄ እንዳይሆን ደግሞ የፖለቲካ ሃይሎች ሃላፊነት አለብን፤ ይሄ ጥያቄ ወደ ከባድ ቀውስ ተሻጋግሮ አገሬን ወደ ቀውስ ከማስገባቱ በፊት ኢህአዴግ ቢሰማ ደግሜ ደጋግሜ እነግረዋለሁ።

አዲስ ዘመን፦ኢህአዴግን አጀንዳ አናድርገውና ኢትየጵያውያን ሙስሊሞች እኮ ብዛታቸው ብዙ ሚሊዮን ነው፤ እርስዎ ደግሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ሰልፍ እየወጡ መሆናቸውን እየገለጹ ነው። ታድያ እነዚህ ሰልፍ የሚወጡት ከጠቅላላ የእምነቱ ተከታዮች ጋር ሲነጻጸሩ ጥቂቶች አይደሉምን?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አይደሉም፤ በሰልፍ ውስጥ ይህን ያህል ህዝብ ዓርብ ዓርብ ሰልፍ መውጣት በጣም ከባድ ቁጥር ነው እንዳታሳንሱት፤ በጣም አደጋ ነው። እኔ እንደ አገር ነው የምነግራችሁ፤ በጣም ብዙ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ለምሳሌ የእስልምና እምነት እኮ በመላው አገሪቱ ተሰራጭቶ ነው ያለው፤በመላው አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፍ አለ ማለት ይቻላል? በእርስዎ እምነት የት አካባቢ ነው ተቃውሞ እየተሰማ ያለው?

ኢንጅነር ይልቃል፦አዲስ አበባ ላይ በጣም ብዙ ናቸው፤ ሁሉም ቦታ ላይም አሉ ፤ግን ይጋባል ይሄ መጥፎ ነው። ኢህአዴግ በያዘው ሁኔታ ችግሩ ሊባባስ ይችላል።

አዲስ ዘመን፦የእስልምና ምክር ቤት ምርጫ ቀበሌ ውስጥ መደረጉ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እንደገባ አድርገው እያቀረቡት ነው፤ግን እኮ በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ምርጫው በቀበሌ እንዲደረግ ተስማምተዋል፤ በምርጫውም ተሳትፈዋል፤ የእርስዎ ፓርቲ ምርጫው በቀበሌ መሆን አልነበረበትም የሚለውን ቡድን ብቻ ነው የሚደግፈው ማለት ነው፤ስለዚህ ፓርቲዎ በእስልምና ሃይማኖት ላይ ጣልቃ የገባ አይመስሎትም?

ኢንጅነር ይልቃል፦ እንዴት ማለት ?

አዲስ ዘመን፦ ምርጫው በቀበሌ እንዲደረግ ብዙ አማኞች ተስማምተው ያደረጉት ሆኖ ሳለ እናንተ ዕውቅና እየነፈጋችሁት ነው?

ኢንጅነር ይልቃል፦ መንግስትና ሃይማኖት ተቀላቅለዋል የምላችሁ እኮ እዚህ ላይ ነው፤ቀበሌ የመንግስት መዋቅር አይደለም እንዴ ? በመንግስት መዋቅር የሚደረግ ምርጫ ትክክል አይደለም ብለው የእምነቱ ተከታዮች እስከ አሁን እያመጹ ነው። ስለዚህ እነሱ በሚፈቅዱትና ሃይማኖቱን በሚፈቅደው ይሁን ነው የምንለው።

አዲስ ዘመን፦ በጠራችሁት ሰልፍ ላይ ያነሳችኋቸው አጀንዳዎች በእኩል ደረጃ ለማንጸባረቅ ነበር ዓላማችሁ፤ ነገር ግን የሃይማኖቱ ነገር ነው ጎልቶ የወጣው?

ኢንጅነር ይልቃል፦ ነውር አይደለም እኮ …

አዲስ ዘመን፦ ምናልባት ግን አጀንዳ ተነጥቃችኋል ማለት ይቻላል?ወይስ እናንተ የሌሎችን አጀንዳ ነጥቃ ችኋል?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አጀንዳ መንጠቅ የለም ፤አጀንዳችን ነው አልኳችሁ እኮ፤ ያንን ጥያቄ ለሙስሊሞቹ ነው ይዘን የወጣነው ስንል ለምን አይገባችሁም። እኛ እኮ አልደባበቅ ነውም።ሙስሊሞች ያነሱት ጥያቄ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ በመግባቱ ሰዎችንም ፍታ ፤በሃይማኖትም ጣልቃ አትግባ አንድ ትልቅ ጥያቄ ነው።እንደውም በእኔ አመለካከት ሙስሊሞቹ አንሰዋል፤አንድ ዓመት ሙሉ እንደመጮሃቸው በጣም ብዙ እጠብቅ ነበር። ስለዚህ አልተነጠቅንም ፤አጀንዳውም የእነሱ ነው እኛም እንደ ጥያቄ አንስተነዋል። ይሄ በግልጽ የሄድንበት ነው፤ምንም የሚያሳፍር ነገር የለውም ።እንዲገባችሁ እፈልጋለሁ አምኜበት ነው የምሰራው።

አዲስ ዘመን፦በሰልፉ ላይ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለምን በተመሳሳይ መልኩ አልተስተናገዱም።

ኢንጅነር ይልቃል፦ብዙ ጥያቄዎች ተነስተዋል። እንዲነሱም እንፈልጋለን ፤የፖለቲካ እስረኞች እንዲነሱ እንፈልጋለን፤በባለፈው ሰልፍ በደንብ ካልተነሳ በሚቀጥለው ጎላ ብሎ እንዲነሳ እናደርጋለን። ሁሉም ሰው አንዲወጣ በደንብ እንቀሰቅሳለን፤እናንተም አግዙን።

አዲስ ዘመን፦በቅርቡ እርስዎ በአንድ መጽሄት ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የ35 አገሮች አምባሳደሮች «የዓረቡ ዓለም ዓይነት ህዝባዊ ዓመጽ በኢትዮጵያ ይከሰታል ብለህ ታምናለህ»? ብለው ጥያቄ እንዳቀረቡለዎት ጠቅሰዋል።ለመሆኑ የዓረቡ ዓለም ዓይነት ዓመጽ በአገራችን ይከሰታል ብለው ያምናሉ?

ኢንጅነር ይልቃል፦እንዲህ ዓይነት ነገር ባይመጣ ደስ ይለኛል። በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ከዓለም ድሃዋ አገር ነች። ስለዚህ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር እፈልጋለሁ። ነገር ግን አንድ መርሳት የሌለብን ነገር የሰላማዊ መንገዶችና የፖለቲካ ትግሉ በታፈነና ችግር በበዛ ቁጥር እንዲህ ዓይነት ነገር (የዓረቡ ህዝባዊ ዓመጽ) ሊፈጠር ይችላል።እንዲህ ዓይነት ነገር ደግሞ ሊነሳ የሚችለው ህዝቡ በሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተስፋ ሲቆርጥ ነው፤እንዲህ ዓይነት ነገር በህዝብ ውሳኔ የሚመጣ ነገር ነው ። ነገር ግን ይሄ አደገኛ ነው። ደግመን ደጋግመን የምንናገረው ይህ አገር የወጣት አገር ነው፤ድህነት በርክቷል፤ብዙ ማህበራዊ ቀውስ አለብን እነዚህ ነገሮች እንዳይመጡብን፤በፍጥነት ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስም ወደማንፈልገው አቅጣጫ እንገባለን እባክህ መንግስት …ብለን እየጠየቅን ነው ያለነው።

አዲስ ዘመን፦ በቀጣዩ ምርጫ ፓርቲያችሁ በህጋዊ መንገድ ተወዳድሮ ለማሸነፍ የሚያስችል ፖሊሲና መርሃ ግብር አለው?

ኢንጅነር ይልቃል፦አንድ ፓርቲ ሲመዘገብ ይነስም ይብዛም የራሱ ፖሊሲ ይኖረዋል። የሰማያዊ ፓርቲ ፖሊሲን ከድረ ገጻችን መመልከት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ በቀጣዩ በ2007 ለሚደረገው ምርጫ ዝግጅቱን እንዴት ነው የምታዩት?

ኢንጅነር ይልቃል፦ በሰፊው እየሰራን ነው፤ እናሸንፋለን ብለን እናስባለን፤ እንደውም ችግራችን እኛ አሁን ኢህአዴግ ሁሉንም ነገር ድብልቅልቅ ስላደረገው 99ነጥብ6 እንዳናሸንፍ ነው የምንፈራው(ሳቅ) ምክንያቱም የምናደርገው ትግል ከዲክታተራዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመሸጋገር ጉዳይ ስለሆነ ህዝቡ ሚሰጠውን ድምጽ የህዝበ ውሳኔ ዓይነት ነው የሚመስለኝ።እውነቴን ነው።

አዲስ ዘመን፦ በፓርቲያችሁ የአባላት ምዝገባና ሌሎቸ ስራዎች ኦን ላይን የሚደረጉ ናቸው ፤በዚህ መንገድ ብቻ የፓርቲውን ፖሊሲዎች በተገቢው መንገድ አስተዋውቋል ማለት ይቻላል?

ኢንጅነር ይልቃል፦ በዚህ ረገድ ችግር አለብኝ….

አዲስ ዘመን፡- ታድያ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በቀጣዩ ምርጫ በዚህ ያህል ድምጽ እናሸንፋለን ማለት ትችላለችሁ?

ኢንጅነር ይልቃል፦ እንደነገርኳችሁ እኮ ነው፤ ኢህአዴግ መቶ በመቶ መንገዱን ከዘጋብንና ሚዲያውም ከሌለ፤ «አንተም አሸባሪ ነህ» ካለኝ ምንም ነገር አይኖርም። ሁኔታው እንዳለ ይቀጥላል፤ መንገዶች ከተስተካከሉ እናንተ ጋዜጠኞች ከጻፋችሁ ኢቲቪም ሃሳባችንን ከተጋራን የያዝናቸው ሃሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብ ቀልብ የሚገዙ ናቸው።በዚህ ረገድ ችሎታ አለው።

አዲስ ዘመን፦ ችግር እየፈጠረባችሁ ያለው ኢህአዴግ ብቻ ነው ማለት ነው?ውስጣዊ ችግር የለባችሁም?

ኢንጅነር ይልቃል፦ የለንም። ሰማያዊ ፓርቲ ነው የምትሉኝ አይደል?

አዲስ ዘመን፦ ብዙ ተቀዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ነው ያስቸገረን ሲሉ ስለምንሰማ ነው?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አንደ አገር እንደሚያድግ አገር የአሰራር የአመለካከት ከኋላ ቀርነት ወደ ዘመናዊነት ስለምንሸጋገር ያለቀለት የመላዕክት ስብስብ አድርጌ አላይም። ሰዎች በተሰበሰቡበት ሁሉ የሃሳብ ትግል አለ። ኢህአዴግ ቢወገድ እንኳን የኢትዮጵያ አጠቃላይ ችግሮች ይወገዳሉ ብዬ አላስብም፤ የፖለቲካ ዕድገት በጊዜ ሂደት የሚመጣ ነው። የህብረተሰብ ዕድገትም ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን እንገነዘባለን። ኢህአዴግ በሩን በመዘጋቱ ዕድገታችን ተገትቷል ነው እንጂ የምንለው ከዓለም ጫፍ ያለን ድሃ አገር በአንድ ጊዜ ሰማይ እንነካለን ብለን አናስብም፤ እንደዛ ዓይነት ቅዠት የለንም።ተስፋ እናደርጋለን፤ ተስፋ ስናደረግ ግን በጭፍንነት አይደለም።

አዲስ ዘመን፦ እናንተ ኢህአዴግ በሃይማኖት ላይ ጣልቃ ገብቷል ትላላችሁ፤ ብዙ ሰዎች ደግሞ እንደውም ኢህአዴግ የእምነት ነጻነትን ያረጋገጠ፤ በተለይ ከዚህ በፊት ባለፉት ስርዓታታት ጭቆና ይደርስበት የነበረውን የእስልምና ሃይማኖት ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ጭቆናው እንደተወገደ ይነገራል። አንድ አንድ ሰዎች ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ከመጠን በላይ መስጊዶችን እንዲስፋፉ ያደረገና የሙስሊም ደጋፊ መንግስት ነው ሲሉ ይከሱታል? ኢህአዴግ በእስልምና ሃይማኖት ላይ ምን ለማግኘት ጣልቃ የሚገባ ይመስለዎታል?

ኢንጅነር ይልቃል፦ ስልጣን ላይ ለመቆየት ነው ተቋማትን የሚቆጣጠረው፤ ቀላሉ ቋንቋ ይሄ ነው። ምክንያቱም መቆጣጠር ይፈልጋል። ኢኮኖሚን፤ መሬትን ግለሰብንና ሁሉንም ሌሎች ዘርፎችን መቆጣጠር የሚፈልግ ፓርቲ ነው። ስለዚህ የእስልምና እምነትም ተቋምን እንደ ተቋም ተቆጣጥሮ የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ ይፈልጋል። ያ ነው ችግሩ። ኢህአዴግ እሱ በሚፈልጋቸው ካድሬዎች እሱ የሚለውን ነገር በዛ ሃይማኖት ውስጥ አንዲያልፍ ይፈልጋል ። ያ የመቆጣጠር ፍላጎት ነው ችግር ያመጣው። እውነቱን ልገራችሁ ይህ ጉዳይ ከኢህአዴግ ባለስልጣናት በላይ ያሰጋኛል። ይህ ችግር ሊፈታ የሚችለው በቁጥጥር እኔን ብቻ ስማኝ በማለት ሳይሆን ነገሮችን ግልጽ በማድረግ ነው። ለመገናኛ ብዙሃንም ለህዝቡም ክፍት ማድረግ አለበት። ይህ ሲሆን ለፍርድም ይመቸናል። አሁን አንድ ሰው በአደባባይ ሽብርተኛ ተብሎ በአደባባይ እውነታዎች እየተረጋገጡበት ምን ዓይነት ሞራል ያለው ሰው ነው ያንን ሰው ደግፎ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት የሚፈልገው። የኢህአዴግ ምስጥራዊነት ፓርቲው ግራ ዘመም ከመሆኑ የመነጨ መሆኑም ይታወቃል። ያ ደግሞ ሁሉንም ነገር በመቆጣጠር ያምናል። ሶስቱንም የመንግስት አካላት ማላገጫ አድርጓቸዋል። አሁን ደግሞ ሃይማኖቶችና ሲቪል ማህበራትና የሙያ ማህበራትን በሙሉ ተቆጣጥሯል?

አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት በርካታ ዓለም አቀፍ ምሁራን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለሽብርተኝነት በጣም የተጋለጠ እንደሆነና እንደ ቱኒዝያና ግብጽ በመሳሰሉ አገራትም ከህዝባዊ ዓመጹ በኋላ አብዮቱን ጠልፈው ስልጣን ላይ የወጡት የሃይማኖት ጽንፈኝነትን የሚያቀነቅኑ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ ከምትገኝበት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር ተያይዞ አክራሪነት በትንሽም ቢሆን አደጋ የሆነበት ሁኔታ መፈጠሩንም ያመለክታሉ ። ከዚህ ሃሳብ ጋር ይስማማሉ ?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አዎ እስማማለሁ።

አዲስ ዘመን፦ ታድያ እነዚህን ምልክቶች ለመከላከል መንግስት ለሚወስደው እርምጃ ድጋፍ ለምን አያደርጉም ?

ኢንጅነር ይልቃል፦ እሱን ያባባሰው እኮ ኢህአዴግ፤ ያን ስጋታችንን ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያዋለው ነው። ከራሱ የቁጥጥር ባህሪ ተነስቶ ነገሩን ወደ ማይሆን ጠርዝ እየገፋው ነው።ኢህአዴግ ይህንን ጉዳይ የያዘበት መንገድ ትክክል አይደለም። ጉዳዩን ለመገናኛ ብዙሃንና ለሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ክፍት ያድርገው። ኢህአዴግ ለፖለቲካ ጥቅም ሲል ሽብርተኛ እያለ የሃይማኖት መሪ እያሰረ ሽብርን ታገለ ይባላል?

አዲስ ዘመን፦ በቅርቡ በውጭ አገር የሚገኙ የኦነግ አበላትና ደጋፊዎች የሙሰሊሙ ህዝብ እንቅስቃሴ የአካባቢውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ሁኔታን ለመቆጣጠርና ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የሙስሊሞቹን ትግል መደገፍ የኦነግን ትግል መደገፍ መሆኑን ጃዋር ሙሃመድ የተባለ ኦነግ አመልክቷል፤ ፓርቲያችሁ ደግሞ ይህን ትግል እያገዘ ነው ያለውና በተዘዋዋሪ የኦነግን እንቅስቃሴ እያገዘ ነው ማለት ይቻላል?

ኢንጅነር ይልቃል፦ ሁለቱም አይገናኙም፤ ጃዋር ምን አገባው፤ ጃዋርም ኢህአዴግም ሃይማኖቱን የፖለቲካ መጫወቻ እያደረጉት ነው፤ ልቀቁት ነው እያልን ያለነው።

አዲስ ዘመን፦ አብዛኛው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወጣቶች መሆናቸውን ገልጸውልናል፤ለፓርቲው ጥንካሬና ወደፊት ለሚኖራችሁ አቅጣጫ በሳል የፖለቲካ ሰዎችን ማሳተፍ አትፈልጉም፤ወይስ አሏችሁ?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አሉን እኔም በሳል ነኝ ብዬ ነው የማስበው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን እኮ ነው የምወዳደረው፤ ወጣት በሳል አይደለም ካልከኝ አንተ ወጣት ትንቃለህ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፦ እንደዛ ማለት አይደለም፤ ከአንድነት ፓርቲ «መርህ ይከበር» በሚል ከወጡት አንጋፋ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹን ያገለለ የሚመስል ነበርና ምናልባት የፖለቲካ ልምድ ራሱ ትልቅ ሚና ስላለው ነው?

ኢንጅነር ይልቃል፦ በመጀመሪያ ከአንድነት ፓርቲ የወጡት እነ ፕሮፌሰር መስፍንና ሌሎች ትላልቅ ሰዎች ናቸው።

አዲስ ዘመን፦ እነ ፕሮፌሰር መስፍን በፓርቲው ብዙ ተሳትፎ ሲያደርጉ አይታዩም ብዬ ነው?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አይ ሲወጡ እኮ ነው የምልህ፤ ሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ብቻ አይደለም፤ ፓርቲው ዋና ትኩረቱ በወጣቶች ላይ ነው እንጂ በፓርቲው ውስጥ በጣም ትላልቅ ሰዎች አሉ። አማካሪዎች አሉ። እዚህ እየመጡ ትምህርት የሚሰጡ ትላልቅ ሰዎች አሉ። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፤ ዶክተር ያዕቆብ ሃይለማርያም፤ ፕሮፌሰር በፍቃዱ፤ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እዚህ ፓርቲው መጥተው ትምህርት ሰጥተው ያውቃሉ።እነ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ እዚህ ውይይት ሲደረግ ንግግር አድርገዋል። እነ ታድዮስ ታንቱም ይህንን ስብስብ እንዲያድግ ትምህርት ይሰጣሉ። እነሱ በሃሳብ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። እናም ሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች የተማሩና ልምድ ያላቸው መሪዎች እንዲሆኑ ይፈልጋል። ፓርቲው ሁሉንም የህበረተሰብ ክፍል ያቀፈ ነው፤ነገር ግን ወጣቱን ቢነቃነቅ በፖለቲካው ላይ ለውጥ ያመጣል ብለን እናስባለን።

አዲስ ዘመን፦ የሰማያዊ ፓርቲ ፖሊሲ ዋና መርሆች ምንድን ናቸው፤በተለይ ስለ መሬት ባለቤትነትና፤ስለ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት እንዲሁም ስለ አስተዳደራዊ ዘዴ ቢነግሩን ?

ኢንጅነር ይልቃል፦ ሰማያዊ ፓርቲ በግለሰብ ነጻነት ላይ ያምናል፤ የግለሰብ ነጻነት ሲከበር ሌሎች መብቶችም ይከበራሉ ብለን እናምናለን፤ መሬት ትልቅ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው፤ የአገሪቱ አርሶ አደር ነጻነት ሊኖረው ይገባል፤ሲፈልግ ሊያወርሰው፤ ሊያከራየው የተሻለ ስራም እሰራበታለሁ ካለ ሊሸጠው ይችላል።ስለዚህ መሬቱ የግሉ የራሱ መሆን አለበት ብለን እናምናለን።

ኢትዮጵያ ከድሮ ጀምሮ የፌደራላዊ አስተዳደር ባህል አላት፤ የዚህ አካባቢ ንጉስ የዚህ ንጉስ እየተባለ እንደውም በተነጻጻሪ የተሻለ የፌደራሊዝም ስርዓት ነበረ። ለራሳቸው ግብር ያስገብራሉ፤ የተወሰነውን ለማዕከላዊ መንግስት ገቢ ያደርጋሉ። ትንሽ ጉልበት ሲያገኙ ንጉሰ ነገስት ይሆናሉ፤ ሲጨቆኑ ደግሞ «ጎበዝ ተከተለኝ» ብለው ይነሱ ነበር፤ ስለዚህ አገራችን ለፌደራላዊ ስርዓት እንግዳ አይደለቸም። እናም የአስተዳደር ስርዓቱ ያስፈልገናል።

ነገር ግን የፌደራል ስርዓቱ ዘርን ማዕከል አድርጎ መሆን የለበትም። በጎሳ መከፋፈል አንፈልግም።ቋንቋን፤ ባህልን፤ አሰፋፈርን፤ መልካአ ምድራዊ አቀማመጥን፤ የዜጎችን ስነ ልቦናና ሞራል ግምት ውስጥ ያስገባ የፌደራሊዝም ስርዓት እንዲኖር እንፈልጋለን። ከኬንያ ድንበር ከቦረና አምጥተን ቋንቋው ኦሮምኛ ስለሆነ ብቻ የሸዋ ኦሮሞ ልናደርገው እንችልም፤ ሸዋ ደብረ ብርሃን አዲስ አበባ እዚህ አጠገቡ እያለ ከዜጌና ከመተማ ሰው ጋር ነህ ልንለው አንችልም። ወይም ደግሞ ሚዛን ቴፒን ጅማን አዲስ አበባን እና ዝዋይን አቋርጠህ ከሃዋሳ ጋር ልታደርገው አትችልም። ጎሳን ብቻ መሰረት ማድረግ ለአስተዳደርም ለአገር ግንባታም ምቹ አይደለም። ውሎ አድሮም ከፋፋይ ነው ፤ጣሊያን የፈጠረው ነው ይሄ ካርታ። ልዩነቱን እያጣጣሙ አንድነትን እያበረታታን እንጂ በልዩነት ላይ ተመስርቶ የሚደረገውን ነገር አንከተለውም።

አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ ፓርቲያችሁ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉ ታበረታታላችሁ ማለት ነው?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አዎ፤ ቋንቋቸውና ባህላቸውን ለማሳደግ ከቡድን የሚነሳ ነገር የለም። የግለሰብ መብት በቅድሚያ ካልተከበረ የማይከበር የመብት ዓይነት የለም።

አዲስ ዘመን፦ በአንድ ወቅት እርስዎ የኦሮምኛ ቋንቋ መጠቀም ያለበት የላቲን ፊደል ሳይሆን ግዕዝ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተው ነበር፤ እንዴት እንደዛ ሊሉ ቻሉ?

ኢንጅነር ይልቃል፦ እንደዛ አይደለም አነጋገሩ፤ ከፊል ነገር አለው። በአሁኑ ወቅት እንደውም ብሄር ብሄረሰቦች በጭቆና ስር ላይ ናቸው። ጭቆናው ዓይን ባወጣ ሁኔታ አሁን ላይ ነው ያለው።

የኦሮምኛ ቋንቋን ለማሳደግ ከፈረንጅ አገር የላቲን ቃላት የእንግሊዝኛ ፊደል ከማምጣት ግዕዝ ፊደልን ቢጠቀም የኦሮምኛ ቋንቋ አማርኛ ተናጋሪውን በቀላሉ እንዲለምደውና እንዲያድግ ማድረግ ይቻላል። ቋንቋውን የበለጠ ለማሳደግ ይጠቅመዋል። ለቋንቋው ከፈረንጅ ፊደል ይልቅ ከሰሜን ኢትዮጵያ የመጣው ግዕዝ ይሻለዋል። በአገሩ ያሉትን ሰዎች ቋንቋውን በቀላሉ እንዲለምዱት በማለት ነው አስተያየቴን የሰጠሁት።

አዲስ ዘመን፦ ሰማያዊ ፓርቲ የአገሪቱ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለው በፍቅርና በአንድነት እንዲኖሩ እንደሚሰራ ነው ከንግግርዎት የተረዳነው። ቅድም በሰማያዊ ፓርቲ እየተገኙ ትምህርት ከሚሰጡት ሰዎች አንዱ ታድዮስ ታንቱ መሆኑን ገልጸውልኛል። ታድዮስ ታንቱ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ለተከታታይ ጊዚያት የትግራይን ህዝብ በጋዜጣ ሲሰድብ የነበረ ነው።ምንድነው የሚያስተምረው?

ኢንጅነር ይልቃል፦ ታድዮስ መሳደቡን አላውቅም።

አዲስ ዘመን፦ እንደውም«የትግራይ ህዝብ ነቀርሳ ነው ከኢትዮጵያ መወገድ አለበት፤ ሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ሂትለር በአይዶች የወሰዱትን ዓይነት ጭፍጨፋ በትግራይ ህዝብ ላይ መውሰድ አለባቸው» ሲል ጽፏል። የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የነበረው ደግሞ እስክንድር ነጋ ነው፤ ይህንን ሰውም«የነጻነት ታጋይ» እያላችሁ ከእስርቤት እንዲለቀቅ እየጠየቃችሁ ነው። ለነገሩ እስክንድር ነጋ በዚህ ድርጊቱ ተከሶ አይደለም በአሁኑ ወቅት በእስርቤት ላይ የሚገኘው። እንዴት ነው ታድያ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት እየሰራን ነው የምትሉት ?

ኢንጅነር ይልቃል፦ የእኔ አቋም ትግራይ የኢትዮጵያ መሰረት ነው፤ ኢትዮጵያውነት እየተስፋፋ ባህሉ፤ ቋንቋው እምነቱ ከሰሜን ወደ ደቡብ ነው እየተስፋፋ የመጣው። እኔ ባደግኩበት አከባቢ በአማርኛና በትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ብዙ መዋረሶች አሉ፤ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይስፋፋ ልዩነት ላይ ማተኮር ጥሩ አይደለም። እውነት ለመናገር ታድዮስ ታንቱ በዛን ጊዜ እንደዛ ስለማለቱ እኔም አላነበብኩም፤ እንደዛ ዓይነት ነገር ከጻፈም በጽሁፍ መልስ መስጠት ነው የሚሻለው፤ እንዳዛ ዓይነት ጽሁፍ ስለጻፈ እዚህ ፓርቲ አይመጣም ቢባል ኢ ዴሞክራሲያዊ ነው።ያን አመለካከቱን ግን ትክክል እንዳልሆነ እነግረዋለሁ።እዚህ ሲመጣ እኮ ትግሬንም ጨምሮ ከሁሉም አካባቢዎች የመጡ ሰዎችን ነው የሚያገኘው። እንደዛ ብሎ ከሆነ እኔ ልክ አይደለህም እለዋለሁ። አሜሪካ ውስጥ እኮ ነጭ አክራሪዎች አሉ። በቴሌቪዠን ይናገራሉ አትናገሩ አይባሉም። ትክክል እንዳልሆኑ ደግሞ ሌላ ሰው ይናገራል። የሃሳብ ትግል ማለት ይሄ ነው።

አዲስ ዘመን፦በአገራችን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል እንዲያብብ ሰማያዊም ይሁን ሌሎች ተቀዋሚ ፓርቲዎች ምን ዓይነት አሰራር መከተል አለባቸው?ምንስ መደረግ አለበት?

ኢንጅነር ይልቃል፦ አንደኛ ትግል ዋጋ እንደሚያስከፍል አውቆ በቆራጥነት ምንም ነገር አስቸጋሪ ሁኔታ ቢበዛ፤ ዓላማቸውን ለማሳካት መስራት አለባቸው። ኢህአዴግም እንደ አንድ የፖለቲካ ሃይል ይሄን የማታለል፤ የማደናገር በውሸት የመክሰስ ፖሊሲውን እና ሌላ አማራጭ እንዳይወጣ በእንጭጩ በተለያየ መንገድ ከመቅጨት ይልቅ በሆደ ሰፊነት በመቻቻል መስራት ቢመርጥ መልካም ነው። ብዙ ባለስልጣን አልፏል፤ ብዙ መንግስት ተለውጧል፤ የመጪውንም እያሰብን በሆደ ሰፊነትና የአገርን ጉዳይ ብናስቀድም ይመረጣል።

አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።

*************

Source: Addis Zemen – Aug. 5-7, 2013.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories