ኢትዮጵያዊነትና የኢህኣዴግ የብሄር ፖለቲካ

(ጆሲ ሮማናት)

ኢህኣዴግ ስልጣን በያዘበት ሰኣት ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠቱ ትክክል ነው ብቻ ሳይሆን ሌላ ኣማራጭ ኣልነበረም፡፡ የተለያዩ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት ሲደርስባቸው የነበረው ጭቆና ብሃራቸውንና ሃይማኖታቸውን መሰረት ያደረገ ነበር፡፡ የሃይማት ጭቆናው መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ እንዲሆኑ በማድረግ ሃገሪቱ ማንኛውን ሃይማኖት በእኩል ኣይን ማስተናገድ የምትችልበት ስርኣት በመፍጠር ተፈቷል፡፡ በተመሳሳይም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ሁሉም በእኩል የሚገባቸውን እውቅና ኣግኝተው በባህላቸውና በቋንቋቸው ኮርተው እንዲኖሩ የሚያደርግ ፖለቲካዊ መፍትሄ ኣግኝቷል፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄው እነዚህ ብሄርና ብሄረሰቦች በጊዜ ሂደት ድህነት እየጠፋ፣ መሰረተ-ልማት እየተገነባና በመካከላቸው የኢኮኖሚ ትስስር እየጠነከረ በሄደ ቁጥር ከብሄርተኝነት ይልቅ ወደ ትልቁ ጥላ ኢትዮጵያዊነተ (የድሮው ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በኣዲስ መልኩ የተፈጠረች የብዙሃን ኢትዮጵያ) ይመጣሉ የሚል ነው፡፡

ሆኖም ግን ባለፉት 20 ኣመታት በሂደት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሄርተኝነት እየዳበረ መሄዱ ገሃድ ነው፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ኣንዳንድ “ብሄር የለንም” (ብሄራችን ኢትዮጵያ ነው) የሚሉ ሰዎች እንደሚሉት ፖሊሲው ያመጣው ችግር ሳይሆን እነዚህ ብሄር የለንም ከፈለጋችሁ የመሃል ኣገር ሰው በሉን የሚሉ ዜጎች ብሄርተኝነትን እየኮነኑ በራሱና በማንነቱ መኩራት የሚፈልግ ሰውና በኣፍ መፍቻ ቋንቋው የሚያወራ ሰው በዘረኝነትና ጠባብነት በመፈረጅ የድሮው ኣግላይ ስርኣት እንዲመለስ ሌት ተቀን ሲለፍፉ መሰማታቸው የፈጠረው ሁኔታ ነው፡፡ የድሮው ስርኣት እንዲመለስ የሚጎተጉቱ ሃይሎች በታዩ ቁጥር እነዚህ ድሮ በኢትዮጵያዊነት ስም ይደርስባቸው የነበረው ጭቆና እያስታወሱ ወደ ብሄርተኝነቱ እያጋደሉ መሄዳቸው የግድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ የድሮዉን ኣግላይ ስርኣትና ኣስተሳሰብ ኣድናቂ ሃይሎች (ባንዴራዉም ይጨምራል) ድሮ ሌሎች ላይ የደረሰውን ጭቆና እውቅና ባለመስጠት ሁኔታውን ኣባብሰውታል፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ብሄራችሁን ኣትጥሩ” – “ብሄራችሁ ኢትዮጵያ ነው” የሚሉ ሰዎች በዝተዋል፡፡ ባለፈው ጃዋር መሃመድ “መጀመርያ ኦሮሞ ነኝ” – “ኢትዮጵያዊነቱ እኔ ላይ የተጫነ ማንነት ነው” ካለ በኋላ ጉዳዩ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ከጃዋር ጋር “ኢትዮጵያዊነቱ እኔ ላይ የተጫነ ማንነት ነው” በሚለው ላይ ባልስማም በመጀመርያ ኣባባሉ ግን እስማማለሁ፡፡ እኔም መጀመርያ ትግረዋይ ነኝ – ትግረዋይ ኢትዮጵያዊ፡፡ ምናልባት እኔና ጃዋር በሁለተኛው ጉዳይ ላይ የተለያየ ኣስተሳሰብ እንዲኖረን ያደረጉን ብዙ ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ጃዋርን ኢትዮጵያዊ ነኝ በል ብዬ መከራከር የምችለው ኢትዮጵያ የምትባለው ጥላ ሁላችንንም በእኩል ማቀፍ ስትችል ነው፡፡ ኣጋጣሚ ሆኖ እኔ የኣሁኗ ኢትዮጵያ እንደዛ ነች ብዬ ኣምናለሁ (ቢያንስ በሂደት እየተፈጠረች ነው) – ጃዋር ደግሞ ኣያምንም- ይሄው ነው ልዩነቱ፡፡ ኣሁንም “ኢትዮጵያዊነት”ን የምንረዳው በድሮው ኣስተምህሮ ከሆነ ብዙ ሰዎች የጃዋርን ሃሳብ የማይጋሩበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

እኔ “ትግረዋይ ነኝ” ማለቴ ኢትዮጵያዊ ኣይደለሁም ማለት ኣይደለም፡፡ ኣንድ የውጪ ሰው ከየት ነህ ብሎ ቢጠይቀኝ “ኢትዮጵያ” ነው የምለው፡፡ ኣንድ ኢትዮጵያዊ ከየት ነህ ካለኝ ግን ከ”ትግራይ” ነው የምለው፡፡ ድሮውስ በኣለባበሱ፣ በመልኩና በኣነጋገሩ የየት ብሄር/ብሄረሰብ መሆኑ ማወቁ በጣም ቀላል በሆነበት ኣገር የዚህ ብሄር/ብሄረሰብ ኣባል ነኝ ማለቱ ጥፋቱ ምንድንነው?

እኔ “ትግረዋይ ኢትዮጵያዊ” ነኝ ማለቱ (ሌሎችን እስካልጠላሁ ድረስ) የሚያመጣው ችግር ምንድነው? በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ “ብሄራችሁን ኣትጥሩ” ከሚሉ ብዙ ሰዎች ጋር ጠበቅ ያለ ክርክር ኣድርጊያለሁ፡፡ በሚገርም ሁኔታ የሁሉም መጨረሻ የመከራከርያ ነጥብ “እኔ የተወለድኩት ከእንትን እና ከእንትን ብሄረሰብ ነው፡፡ ኣባቴ እንትን ነው እናቴ ደግሞ እንትን – ስለዚህ እኔ ምንድንነኝ ልበል? ኣንዱን እንዳልመርጥ ሁለቱንም እወዳቸዋለሁ” የሚል ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ መከራከር እንችላለን – እኔ እነሱ ብሆን ግን የበለጠ ኩራት ይሰማኝ ነበር፡፡ እነዛ የኣባቴንና የናቴን ማንነት እኮራባቸው ነበር እንጂ ኣልከዳቸውም፡፡ ምናልባት ግን እንደዛ የሚሉ ሰዎች እነሱ ራሳቸውን ማካተት የሚፈልጉት ብሄር ይሄ የድሮው ድፍን ኢትዮጵያነት የሚለው ላይ የሚገለጽ ሊሆን ይችላል፡፡

በነገራችን ላይ ኣብዛኞቹ “ብሄራችሁን ኣትጥሩ” “ኢትዮጵያዊ ነኝ በሉ” የሚሉ ሰዎች ለምን የኣንድ ብሄር ተወላጆች ብቻ ሆኑ (ብሄራቸውን መጥራት ያልፈለግኩት ስለማይፈልጉት ነው)፡፡ ይሄ ራሱ ብዙ ጥያቄዎችን ይመልሳል፡፡

*************
The author Jossy Romanat in a co-blogger in this blog. He is a social scientist residing in Canada and can be reached at [email protected].

Jossy Romanat

more recommended stories