ቤኒሻንጉል:- 28 ሀላፊዎች ዜጎችን በማፈናቀል ተጠርጥረው ታሠሩ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን ያሶ ወረዳ የሚኖሩ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆችን ያለአግባብ አፈናቅለዋል ተብለው የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋዎ ጃኔ ትናንት እንደገለጹት ተጠርጣሪዎቹ ካለፈው እሁድ ጀምሮ የተያዙት በቅርቡ በያሶ ወረዳ ለረጅም ዓመታት የኖሩ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆችን በማፈናቀል ወንጀል ተጠርጥረው ነው፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት 28 ግለሰቦች በክልሉ የካማሽ ዞንና ያሶ ወረዳ ከፍተኛ አመራር አባላት ፣ፖሊሶችና ሌሎችም እጃቸው በጉዳዩ እንዳለበት የተደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Citizens evicted from Benshangul region ina shelter in Fenote-Selam [Photo - Addis Admass]
Evicted citizens in Fenot-Selam [Photo: Adis Admas] April 2013

ወንጀሉ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ቡድን አቋቁሞ የተጠናከረ ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት የምርመራውን ውጤት መሰረት በማድረግ ሲሆን፤ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መታየት እንደጀመረ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ሕገ-መንግሥቱን መሰረት በማድረግ እየተካሄደ በሚገኘው የፍትህ ሂደት በተለይ የአካባቢው ኅብረተሰቡ ትክክለኛ ማስረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ አቶ ጋዎ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ ያሶ ወረዳ አራት ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ ሁለት ሺ የአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች የተፈናቀሉት በሚያዚያ 2005 ዓ.ም ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ወደ ቀድሞው መኖሪያቸው መመለሳቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡

**********

Source: Addis Zemen – June 19, 2013.

Previous:
ከቤኒሻንጉል ክልል ዜጎችን ያፈናቀሉ ኃላፊዎች ተባረሩ
የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች እንዲመለሱ ተወሰነ
የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች ተመፅዋች ሆኑ
የቤንሻንጉል ፕ/ት: ተፈናቃዮቹ ኦሮሞዎችም ናቸው – አጣርተን እርምጃ እንወስዳለን
በቤንሻንጉል ክልል የሰፈሩ ዜጐች “ሕገወጥ” በሚል ተባረሩ

Daniel Berhane

more recommended stories