‹መድረክ›| ያለፈው ሰልፍ ድራማ ሊሆን ይችላል – እኛም አቅደናል

የ‹መድረክ› መሪዎች ‹ሰማያዊ› ፓርቲ ባለፈው ሳምንት ያካሄደው ሰልፍ አፈቃቀድና አዘጋገብ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው እንዲሁም እነሱም ሰልፍ ለመጥራት ዕቅድ እንዳላቸው አዲስ አድማስ ዘገበ፡፡

***********

ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ሰልፉ “የኢህአዴግ ድራማ” ሊሆን ይችላል አሉ

ባለፈው እሁድ በሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪነት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ፣ ከ97 ምርጫ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ መሆኑን የሚናገሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ላለፉት ስምንት ዓመታት እንኳን ሰልፍ ስብሰባም ማካሄድ እንዳልቻሉ በመግለጽ፤ የእሁዱም ሰልፍ “የኢህአዴግ ድራማ ሊሆን ይችላል” በማለት እንደሚጠራጠሩ ገለፁ ፡፡ የኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፣ ህገመንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚፈፀሙ ሰላማዊ ሰልፎች እንደማይከለከሉና ድሮም የነበረ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የመድረክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ እስከአሁን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ይቅርና አዳራሽ ለመከራየት እንኳን ሆቴሎች የመስተዳድሩን ፈቃድ አምጡ እያሉ ሲያስቸግሯቸው እንደነበር ገልፀው፤ የሰሞኑ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍም ምናልባትም ከአፍሪካ ህብረት ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ ያደረገው ጨዋታ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

“ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት እኛም ዕቅድ ይዘን እየተነጋገርን ነው” የሚሉት ፕ/ር በየነ፤ ኢቴቪ ሰልፉን መዘገቡን ብቻ በማየት መሻሻሉን ለማወቅ እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡ “ኢቴቪም ቢሆን ድራማውን እየሰራ ይሆናል” በማለት ዘገባውን የሰራው አንዳንድ የሚያስወነጅሉ ጉዳዩች ላይ በማተኮር ነው ብለዋል፡፡ “አላማቸውና መሻሻላቸው የሚታወቀው ወደፊት መቀጠሉ ሲታይ ነው” ብለዋል – ፕሮፌሰሩ፡፡ የመድረክ ምክትል ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ሰላማዊ ሰልፉ መካሄዱ ችግሮችን ካልፈታ ልክ በአረብ አገራት ላይ እንደታየው አይነት ችግሮች ሊከሰት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ “የህዝብ ችግር እስካልተፈታ ድረስ ህዝብ አንድ ቀን በቃኝ ሊል ይችላል – መብቱ ካልተከበረለትና የሚበላው ካጣ ችሎ የሚቀመጥበት መንገድ የለም፡፡ ይሄ ህዝብ መብቱ እንዲከበርለት፣ ነፃነት እንዲያገኝ፣ በልቶ እንዲያድር ይፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ ይህንን ችግር መፍታት ካልቻለ፣ ህዝቡ አሁንም “መሪውን ይበላል” የሚባለውን ሊተገብር ይችላል፡፡” የሚሉት ዶ/ር መራራ፤ እኛን አዳራሽ እየከለከሉ ለሌላው ሰላማዊ ሰልፍ የሚፈቅዱት የህዝብ ሙቀት ለመፍጠር በማሰብ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

“ምናልባትም የኢህአዴግ አዲስ አሰራር ከሆነ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ፣ በነካ እጁ ለመድረክና ለሌሎች ፓርቲዎችም እንዲፈቅድ ጥያቄያችን ነው” ብለዋል፡፡ አቶ ሬድዋን በበኩላቸው፤ ተቃዋሚዎች ሰልፍ ተከለከልን ማለታቸውን አይቀበሉትም፡፡ “በራሳቸው ምክንያት ሳይካሄዱ የቀሩ ካልሆኑ በስተቀር፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ በፊትም ነበር፤ አሁንም ተካሂዷል፡፡ ሃሳብን በነፃነት በአደባባይ ወጥቶ የመግለጽ መብት አዲስ አሠራር ነው ብለን አናስብም” ብለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዳራሽ ተከለከልን፣ ሰልፍ አልተፈቀደልንም የሚል ቅሬታ ያነሳሉ የሚሉት አቶ ሬድዋን፤ የአዳራሽ ጉዳይ የባለ አዳራሾች እንጂ የመንግስት አለመሆኑን ጠቅሰው፣ “መንግስት አዳራሽ አያከራይም፡፡ ለዚህኛው ፓርቲ አከራይ፣ ለዚህኛው አታከራይ የሚል ነገርም የለም” ይላሉ፡፡

በአደባባይ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን በተመለከተም፤ “ነፃና ክፍት በሆነ ሰዓትና ቦታ፣ ህጉን ጠብቀውና ፎርማሊቲውን አሟልተው እስካካሄዱ ድረስ የሚከለከሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ከዚህ በኋላም አይኖርም” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በአዘጋገብ ላይ ያሳየውን ለውጥ በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ሬድዋን፤ “ከዚህ በፊትም የማውቀው ኢቴቪ፤ ሁሉንም ወገን ለማናገር ጥረት ሲያደርግ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሲያጋጥም የነበረው ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ኢቴቪ እንዳይመጣና እንዳይዘግብብን፣ ከዘገበም ሙሉውን እንዳይቀርጽብን የሚል አቋም እንደነበራቸው ነው፡፡ ተቋሙ የሚሰጣቸውን እድል ያለመጠቀም፣ አትግቡብን የሚል የራሳቸው የሆነ ችግር እንዳለባቸው ነው የማውቀው፡፡ የሆኖ ሆኖ ፕሮግራሙን የሚያየው ተመልካች የራሱን ፍርድ መስጠት ይችላል” በማለትም መልሰዋል፡፡

“መድረክ” ለሰኔ 17 ህዝባዊ ስብሰባ ሊጠራ ነው

ዋና ኦዲተርና የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሰሞኑን ለፓርላማ ያቀረቡትን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በነገው ዕለት በመድረክ፣ በመኢአድ፣ በአንድነትና በሰማያዊ ፓርቲ ቢሮዎች የፓርቲዎቹ አመራሮች ውይይት እንደሚያደርጉና መድረክ ለሰኔ 17 ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚጠራ ተገለፀ፡፡

የመድረክ ስራ አስፈፃሚ አቶ አስራት ጣሴ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የፓርቲዎቹ አመራሮች በነገው ውይይት የሚደርሱበትን የጋራ መግባባት በመያዝ፣ መድረክ ለሰኔ 17 ህዝባዊ ስብሰባ ለመጥራትና በአዲስ አበባ ከተማ በመዘዋወር የመኪና ቅስቀሳ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡ ሙስና የስርአቱ መገለጫ በሆነበት፣ የህዝብ ሃብት እየባከነና የዲሞክራሲ መብቶች እየተጣሱ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ መንግስት እምቢተኝነቱን ትቶ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እንዲያደርግ ጥሪ እንደሚተላለፍለት ገልፀዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚቀርብለትን የውይይት ሃሳብ ተቀብሎ ወደ ውይይት ካልመጣ፣ 33ቱ ፖርቲዎች ሰላማዊ ትግሉን ተጠቅመው አገራዊ ንቅናቄ በማድረግ፣ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዳቸውንም አስረድተዋል፡፡

*********

Source: Addis Admas – June 8, 2013.

Daniel Berhane

more recommended stories