ግንቦት 2ዐን በማስመልከት ከኢህአዴግ የተሰጠ መግለጫ

22ኛውን የግንቦት 2ዐ ድል በማስመልከት ከኢህአዴግ ም/ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

በጋራ ተሳትፏችን የተጀመረው የዴሞክራሲ፣ ልማትና፣ ሰላም ጉዟችን ተጠናክሮ ቀጥሏል!!

የዛሬ 22 ዓመት ግንቦት 2ዐ ቀን አስከፊው የደርግ ስርአት በመላ የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከፍተኛ ትግልና መስዋእትነት መገርሰሱ ተበሰረ፡፡ በወቅቱ ከአስከፊው ስርአት ውድቀት ባሻገር እጅግ ደማቅ በሆነ ድምፅ የተበሰረው ለዘመናት በድህነትና ኋላቀርነት ስትማቅቅ የነበረችው አገራችን ህዳሴ ጭምር ነበር፡፡

እነሆ ዛሬ ከ22 ዓመታት በኋላ ግንቦት ላይ ሆነን ያሳለፍነውን ጉዞ ስንገመግም አገራችን በርግጥም መላ የአገራችን ህዝቦች የተዋደቁላቸውን ዓላማዎች ለማሳካት በምትችልበት አቅጣጫ በፍጥነት በመገስገስ ላይ መሆንዋን መገንዘብ እንችላለን፡፡ ለዚህ አዲስ ዘመን ያበቁን ሰማእታት ክብር ይግባቸውና ዛሬ የአገራችን አስከፊ ገፅታ እየተቀየረ፣ የዜጐቿ ህይወት እየተለወጠና የመልካም ነገሮች ተምሳሌት እየሆነች በመሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ዛሬ የአገራችን ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ለብልEPRDF logoፅግናና ለዳበረ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በመረባረብ ታሪካቸውን እንደ አዲስ በጋራ ተሳትፏቸው መፃፍ ጀምረዋል፡፡

የጨበጥነው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር አገራችን ለጀመረችው የህዳሴ ጉዞ መሰረት ነው፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግ ያነገባቸው የልማትና የዴሞክራሲ መስመሮች ከአገራችን ህዝቦች ፍላጐት የተቀዱና ግባቸውም የህዝባችንን ጥቅም ማረጋገጥ መሆኑ በእስከዛሬው ስኬቶቻችን ተረጋግጧል፡፡ በየጊዜው እየጠሩና እየታደሱ የሄዱት መስመሮቻችን በተከታታይ ላስመዘገብነው ፈጣን ዕድገት አብቅተውናል፡፡

መላ የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን ብሄራዊ ጭቆና አንኮታኩተው ህዝቦቿ በእኩልነትና በመፈቃቀድ የሚኖሩባትን ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት አገር ለመመስረት በቅተዋል፡፡ የአገራችን ውድቀት ዋነኛ ምንጭ ብዝሃነትን ማስተናገድ አለመቻል መሆኑን በመገንዘብ ከዚህ አኳያ የተወሰዱት ጠንካራና ህዝባዊ አቋሞች የአገራችን ህዝቦች በአንድ ላይ እንዲቆሙ እና እጅ ለእጅ ተያይዘው ለጋራ ጥቅም እንዲራመዱ አስችለዋል፡፡ ይህንን ፀጋ ህገመንግስታዊ መሰረት እንዲኖረው በማድረግ የጋራ ቃልኪዳናቸውንም ከማንኛውም ጥቃት በመጠበቅ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!

የዛሬውን ግንቦት 2ዐ የምናከብረው የትግላችን ታላቅ መሪ የነበረው ጓድ መለስ በሌለበት ነገር ግን የርሱን ራዕይና ህልም እውን ለማድረግ በጋራ ቃልኪዳናችንን አፅንተን በምንረባረብበት ወቅት ነው፡፡ የጓድ መለስ መስዋእትነት እንደተለመደው ለትግላችን ህያውነትና ቀጣይነት በቁርጠኝነት እንድንታገል ተጨማሪ አደራ ጥሎብን አልፏል፡፡ ከደረሰብን ድንገተኛ ሃዘን ወጥተን ድርጅታችንን አጠናክረን ታሪካዊውን 9ኛ ጉባኤያችንን እጅግ በተሳካ ሁኔታ አከናውነን ወደፊት በመራመድ ላይ እንገኛለን፡፡

በ9ኛው የድርጅታችን ጉባኤ ውሳኔዎች ላይ እንደተመለከተው በታላቁ መሪያችን ቀያሽነት የተቀጣጠለው የተሃድሶ እንቅስቃሴ የወለደው የህዳሴ ጉዟችን በመላ የአገራችን ህዝቦች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቃላችንን አድሰናል፡፡ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችንን ለማሳካት ይበልጥ እንደምንረባረብና አገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የጀመርነውን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ እንቅስቃሴ አጠናክረን እንደምንቀጥል በጠንካራ መንፈስ ወስነን በመረባረብ ላይ እንገኛለን፡፡ ለዚህም መሠረቱ የግብርናችንን ምርታማነት በማሳደግ የህዝባችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ አስምረን ሰፊ ንቅናቄ ለማቀጣጠል የሚያስችሉንን ዝግጅቶች የጉባኤያችንን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ በማካሄድ ላይ እንገኛለን፡፡

በጉባኤያችን ማግስት በተካሄደው የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋና የአካባቢ ምርጫ ያገኘነውን የተሟላ ህዝባዊ ድጋፍ ተጠቅመን ይበልጥ የምንተጋበትና ራዕያችንን ለማሳካት የምንረባረብበት ሰፊ ዕድል ተፈጥሮልናል፡፡ በልማት መስክ ያስመዘገብናቸውን አንፀባራቂ ድሎች በመልካም አስተዳደር መስክም ለማረጋገጥ ለመረባረብ ቆርጠን ተነስተናል፡፡ ይህንንም ከጉባኤውና ከምርጫው በፊት ጀምረነው እንደነበረው በቀጣይም በየደረጃውና በየጊዜው ከህዝቡ ጋር እየተመካከርን ዳር ለማድረስ ወስነን ወደ ተግባር ገብተናል፡፡

አገራችን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ትሸጋገር ዘንድ በዘርፉ የሚታየውን ኪራይ ሰብሳቢነት ለመታገልና የአገራችን ባለሃብትም ደረጃ በደረጃ ወደ ልማታዊ አቅጣጫ እንዲያመራ ለማስቻል ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መስጠት እንዳለብን ሁሉ መመለስ ያልቻሉት ላይም ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን፣ ጉባኤያችን በወሰነው መሰረት እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረናል፡፡ በቅርቡ በከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶችና ደላሎች ላይ የተወሰደው እምርጃ ኢህአዴግ ዛሬም እንደትናንቱ የአገራችንን ህዝቦች ጥቅም ከጥቃት ለመከላከል በፅናት መቆሙን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ይህንኑ እንቅስቃሴ ልማታዊነትን በሚያበረታታ እና የሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚነት በመፃረር ብቻ ሊኖር የሚችለውን ኪራይ ሰብሳቢነትን በሚያቀጭጭ አግባብ አጠናክረን የምንገፋበት ይሆናል፡፡

በመካሄድ ላይ ለሚገኘው የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ህዝቡ ላደረገው ትብብርና ላሳየው ተነሳሽነት ኢህአዴግ ምስጋናውን እያቀረበ በጀመረው አግባብ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመታገል በሚደረገው እንቅስቃሴ ከድርጅቱና ከመንግስት ጐን በመቆም ወሳኝ ሚናውን እንዲጫወት በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!

የህዳሴ ጉዟችን አርማና የታላቁ መሪያችን ማስታወሻ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ በቅርቡም የወንዙን ተፈጥሯዊ አቅጣጫ በማስቀየር ለግድቡ ግንባታ አመቺ ሁኔታ የመፍጠር ታሪካዊ ክንዋኔ ይከናወናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በታላቁ መሪያችን እንደተገለፀው የህዳሴ ግድባችን ሃሣብ አመንጪዎቹም፣ መሃንዲሶቹም፣ ወጪውን የምንሸፍነውም እኛው በመሆናችን ለግድቡ ግንባታ የሰጠነውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረን እንድንቀጥል ኢህአዴግ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

የዘንድሮውን ግንቦት 2ዐ የምናከብረው በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ 5ዐኛ የወርቅ ኢዮቤልዩ ታጅበን ነው፡፡ ለአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት የሆነችው አገራችን ዛሬም ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአፍሪካ ሰላምና፣ ለአፍሪካ ህዝቦች የላቀ ወንድማማችነት የበኩሏን በማበርከት ከወንድሞቻችንና እህቶቻችን ታላቅ አክብሮት በማግኘት ላይ ናት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢህአዴግና እርሱ የሚመራው መንግስት ለፓን አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ ህዳሴ እንደወትሮው ሁሉ በፅናት የሚታገሉ መሆናቸውንና የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስከበር በሁሉም አለማቀፍ መድረኮች ዘብ እንደሚቆሙ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች!

ድርጅታችን ኢህአዴግ የአገራችንን ልማት በማፋጠን የናንተን ህይወት ለመለወጥ ዛሬም በቁርጠኝነት ይታገላል፡፡ ከኢህአዴግ ጐን ተሰልፋችሁ ባለፉት 22 ዓመታት ያደረጋችሁት ተጋድሎ ውጤት የጀግኖቻችሁ ደም ከንቱ ሆኖ እንዳልቀረ የሚመሰክር ህያው ሃውልት ነው፡፡ ይህንን በደምና በላብ የተገኘ አዲስ የህዳሴ ዘመን ለማስቀጠልና የአገራችንን ታሪክ እንደ አዲስ ለመፃፍ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ወሳኝ ድርሻችሁን በመወጣት በጀመራችሁት መንገድ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ኢህአዴግ የተለመደ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች!

ግንባራችን በርካታ ፈተናዎችን አልፎ አገራችንን በህዳሴ ጐዳና ላይ እየመራት የሚገኘው በመካከላችን ባለው ጠንካራ የትግል አንድነት ሳቢያ ነው፡፡ በፈታኝ መድረኮች ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን በድል እንደወጣነው ሁሉ ከፊታችን የተደቀነውን የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል ዛሬም እንደትናንቱ በግንቦት 2ዐ መንፈስ ቃላችንን ማደስ ይጠበቅብናል፡፡ በስራችሁ ያሉት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባሎቻችንም የድርጅታቸውን መስመር አንግበው ለፈጣን ልማትና ለመልካም አስተዳደር የሚያደረጉትን ርብርብ በግንቦት 2ዐ ድል ታጅበው ለስኬት እንዲያበቁ ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርብላቸዋል፡፡

የተከበራችሁ አጋር ድርጅቶች!

በፌደራላዊ ህገመንግስታችን ላይ የተመሰረተው አጋርነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደና በመካከላችን ያለው ወዳጅነት ከጊዜ ወደጊዜ እየጐለበተ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ያቆራኙን የግንቦት 2ዐ ዓላማዎች እንዲሳኩና የአገራችን ህዳሴ ከግብ እንዲደርስ ዛሬም በከፍተኛ የአጋርነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ የልማታችንና የሰላማችን ጠንቅ የሆኑ የጥፋት ተግባራትን ለመታገል የምታደርጉትን ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ ያደንቃል፡፡ ዛሬም ለጋራ ልማታችንና ለሰላማችን አጋርነታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ የቆረጣችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች!

ያመናችሁበትን ዓላማ ለማራመድ ትችሉ ዘንድ የግንቦት 2ዐ ድል የፈጠረላችሁን ዕድል ተጠቅማችሁ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የምታደርጉትን እንቅስቃሴ ኢህአዴግ ያደንቃል፡፡ በዚህ አቅጣጫ እስከተጓዛችሁ ድረስ በመካከላችን ያለው የአስተሳሰብ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በምንስማማባቸው የጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ኢህአዴግ ከናንተ ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት በድጋሚ ያረጋግጥላችኋል፡፡ በተለይም ያለፈው የአዲስ አበባ፣ የድሬዳዋና የአካባቢ ምርጫ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ በማዕከልና በየደረጃው በነበረው የጋራ ምክር ቤት አማካኝነት ለነበራችሁ ተሳትፎ ኢህአዴግ ያለውን አድናቆት ይገልፃል፡፡

በመጨረሻም ኢህአዴግ ለመላ የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መልካም የግንቦት 2ዐ በዓል እንዲሆንላችሁ ያለውን መልካም ምኞት ይገልፃል፡፡

በግንቦት 20 የተጎናፀፍናቸውን ድሎች በሁሉም መስክ አጠናክረን በመቀጠል የሀገራችንን ህዳሴ በጋራ ተሳትፏችን እውን እናደርጋለን!!

ዘለአለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!

ግንቦት 20 ቀን 2005
የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት
አዲስ አበባ

******************

Source: EPRDF

Daniel Berhane

more recommended stories