የተቃዋሚዎች ድምፅ – በሙስና ቅሌት ዙርያ

(አዲስ አድማስ)

“ኢህአዴግም እንደ ድርጅት ሙሠኛ ነው” ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ -የመድረክ አመራሮች አባል

የመንግስት መዋቅር በሙስና የተዘፈቀ ነው የሚል ትችት በተደጋጋሚ ትሰነዝራላችሁ፡፡ ኢህአዴግ ዋናዎቹን ትቶ በትናንሽ ሙሰኞች ላይ ነው የሚያተኩረው፣ይህ ደግሞ ሙስናን እየተከላከለ ነው አያሠኘውም ትላላችሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ሠሞኑን በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ሃላፊዎችና ባለሃብቶች ላይ የተወሠደው እርምጃ የዚህ ትችትና ምክር ውጤት ነው ማለት ይቻላል? ይህ እንግዲህ አንደኛ በጣም የገዘፈን ነገር እንዲሁ መነካካት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግና ስርአቱ፣ አባሎቼና ደጋፊዎቼ የሚላቸው አሉ፡፡ እነሡ ሃገሪቱን በሙሉ እንዲበዘብዙ ድጋፍ ይሰጣቸዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የሠሞኑ እርምጃ መነካካት ነው፡፡ ዋናውን የሙስና ሠንሠለት ለመበጣጠስ የጀመረው እንቅስቃሴ ነው ለማለት ገና ነው፡፡ እስካሁን ባሳለፈው 21 የስልጣን አመታት አንዳንዴ በፖለቲካውም በዲፕሎማሲውም ሲጨንቀው ከሹመኞቹ ውስጥ ጭዳ የሚያደርጋቸው አሉ፡፡ እነዚያን እየሠዋ ይሄው እርምጃ እየወሠድኩ ነው፤ በማንም ላይ ቢሆን መረጃ እስካለ ድረስ እርምጃ ለመውሠድ ዝግጁ ነኝ የሚል የፖለቲካ ጨዋታ አለው፡፡ በሽግግሩ ወቅት ከአቶ ታምራት ላይኔ አንስቶ፣ አቶ ስዬ፣ ሌሎቹንም ከህወሃት ጋር የተጋጩትን ሲያስር ሲፈታ ነው የኖረው፡፡ በዚያ ሠሞን ኢህአዴጐች ጉባኤ እያካሄዱ ነበር፡፡ ይህ እርምጃ ደግሞ ከጉባኤው ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ጉዳይ እንዳለበት ምልክትም ሊሆን ይችላል፡፡ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃንም እንዲነሡ ተደርጓል፡፡ የገቢዎች ባለሥልጣን እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት ነገር ስላለው ከለጋሾች ጋር ያነካካል፡፡

እናም ጫናውን ትንሽ ለማስተንፈስም ጭምር ያደረጉት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ እርምጃው በዚህ ላይ ብቻ የሚቆም ከሆነ በመሠረቱ የሚያደላው ፖለቲካዊ ፋይዳው ነው፡፡ ሙስና እንግዲህ አዲስ አበባንም ሆነ ሌሎች ከተሞችን ያጣበበ ነው፡፡ ሁሉም ጋ ሄደው እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ እሠየው የሚያሠኝ ነው፡፡ በኛ እምነት ይሄ ሁሉ ከበርቴ ሚሊየነርና ቢሊየነር ዝም ብሎ እየፈላ ያለው፣ የሃገሪቱን ህዝብ ሃብትና ገንዘብ እየበዘበዘ ነው፡፡ ሙሰኝነቱ ነው አብዛኛውን እዚህ ያደረሠው፡፡ ኢህአዴግም እንደ ድርጅት ሙሠኛ ነው፡፡ ኪራይ ሣይከፍል የሚጠቀምባቸው ትላልቅ ህንፃዎች አሉ፡፡ እነሱ የህዝብ ንብረቶች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ ከዋናው ፅ/ቤቱ አንስቶ ሌሎች ስራዎችን የሚሠራባቸውን ቢሮዎች እንደማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ኪራይ እየከፈለ ነው የሚጠቀመው? ይህ እንግዲህ በምርመራ ጋዜጠኞች መጣራት ያለበት ነገር ነው፡፡

እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን እንደማይከፍሉ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ የተለወጠ ነገር ከሌለ እያንዳንዱ የኢህአዴግ ካድሬ ገብቶ የሚኖርባቸው ያኔ ከደርግ የወረሣቸዉ ትልልቅ ቤቶች ኪራይ ይከፈልባቸዋል? እኔ እስከማውቀው ድረስ ሣይከፍሉ ነው የሚጠቀሙት፡፡ መረጃው በጋዜጠኞች ሊቀርብ ይገባዋል፡፡ ቦሌ ያሉ የድሮ ትልልቅ መኳንንት የሠሯቸውን ቪላ ቤቶች፣ ከትግሉ መልስ እየተሽቀዳደሙ እንደገቡበት ነው የምናስታውሠው፡፡ ከዚህ በላይ ሙሠኝነት አለ እንዴ? የህዝብ ንብረት እኮ ነው ወይ ለባለቤቶቹ አልተመለሠ? ኢህአዴግ ሙሠኛ ነው ልንል የሚያስችሉን እነዚህ ነጥቦችና ሌሎችም ናቸው፡፡ ሙሠኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ መሠረቱ በጣም ሠፊ ነው፡፡ አደገ የሚባለው ኢኮኖሚ፣ ተሠሩ የሚባሉት ሠማይ ጠቀስ ፎቆች መሠረታቸው ሙሠኝነት ነው፡፡

ከበርቴ ነን ከሚሉት የአንዳንዶቹን መነሻ እናውቃለን፡፡ ራሱ ገዥው ፓርቲ የሚያንቀሣቅሳቸው የኢንዱስትሪና የንግድ ድርጅቶች ሣይቀሩ የሙስና ጉዳይ ያለባቸው ናቸው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ዘግይቷል ቢሉም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ላይ ሰሞኑን የተወሠደው እርምጃ ኢህአዴግ የሙስና ችግሮችን ለማፅዳት መቁረጡን አያመለክትም? በአሁኑ ደረጃ እርምጃ መውሠድ ጀምሯል ማለት አንችልም፡፡ ምክንያቱም አሁንም ትላልቅ አሣዎች አሉ፡፡ በዚህ ዘመን እኮ የኢህአዴግ አባል ወይም ደጋፊ መሆን ማለት ከበርቴ መሆን ነው፡፡ ብዙዎቹ በዚህ መሠረት ተጠቅመዋል፡፡ እንዳሁኑ ዓይነት እርምጃዎች ከቀጠሉ መሠረቱ ሊናጋ ነው ማለት ነው፡፡ ፓርቲው የህዝብ ሃብትን ለራሱ እየተጠቀመ ከመሆኑም በላይ ወዳጆቹን እንዴት እየጠቀመ ነው የሚለውንም ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ራሱን ማፅዳት ጀመረ ማለት ይቸግራል፡፡ እንዲያ ከሆነ ከውስጥ ትልቅ ቀውስ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡

“ይሄ የዶሮ ትራፊ ነው፤ ትልቁ ገንዘብ የት ነው ያለው?” ኢ/ር ሃይሉ ሻውል

የመኢአድ ፕሬዚዳንት በሙስና ተጠርጥረው የተያዙት ሠዎች ጉዳይ የፖለቲካ ግንኙነት ያለው ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ አምባገነን መንግስት ባለበት ሁሉ የሚደረግ ነው፡፡ በደርግ ጊዜም የማይፈለግ ሠው እንደዚህ ይደረግ ነበር፡፡ በእርግጥም የተያዙት ሠዎች የተጠረጠሩበት ጉዳይ እውነት ከሆነ እርምጃው ይቀጥላል ብዬ አምናለሁ፡፡ በሙስና የደለቡትን አንስተው ያሣዩን ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ነገሩን ሙስና ብቻ ብሎ ለመቀበል ይቸግራል፡፡ በቅርቡ ለፓርላማ በቀረበው ሪፖርት ላይ፣ የፌዴራል ኦዲተሩ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት መኖሩን ጠቁሟል፡፡ ዛሬ እነዚህ ሠዎች ቤት አንድ መቶ ሺህ ብር ተገኘ፤ ሲባል ይሄ የዶሮ ትራፊ ነው፤ ትልቁ ገንዘብ የት ነው ያለው? ከዚህ ቀደም የአለም ሚዲያዎች ብዙ ቢሊዮን ዶላር ከሃገር እንደወጣ ነግረውናል፤ እኔ ቁጥሩን አላስታውሠውም፡፡ ይህንንና አሁን የተነገረውን ስናስተያይ ገና ጫፉም አልተነካም፡፡

“አሣ ማጥመጃው ትልልቅ አሣዎችን የሚያጠምድ ከሆነ እንተባበራለን” ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም

አለማቀፍ የህግ ምሁር በሙስና በተጠረጠሩት ላይ መንግስት በወሠደው እርምጃ ምን አስተያየት አለዎት? የተወሠደው እርምጃ የሚቀጥል ከሆነ በእውነት የሚመሠገን ነው፡፡ የተወሠደው እርምጃ ግን ካለው ሁኔታ ጋር ሲመዛዘን ኢምንት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን የታየው ኢምንቱ ነው፡፡ ይህ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ እሠየው የሚያስብል ነው፡፡ ለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተባበር አለበት፡፡ ለፖለቲካ ጥቅም ወይም በፖለቲካ ግጭት ምክንያት የተፈጠረ ከሆነ ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡ ዝም ብሎ ጊዜ ማባከን ነው፡፡ መዘንጋት የሌለበት ግን ከእነዚህ የበለጡ ትላልቅ አሣዎች ዛሬም አሉ፡፡ እነዚህ አሣዎች እስካሁን ድረስ አልተነኩም፡፡ አሣ ማጥመጃው እነዚህን ትልልቅ አሣዎች የሚያጠምድ ከሆነ፣ እኛም እሠየው ብለን እንተባበራለን፡፡ አንዳንዶች የጉምሩክ አሠራር በራሱ ለሙስና ምቹ ነው ይላሉ፡፡ እርስዎስ? በእርግጥም ጉምሩክ አሠራሩ በራሱ ለሙስና በር ከፋች ነው፡፡ ራሱ ከሣሽ ነው፣ ዳኛ ነው፡፡ መጀመሪያውኑ ለሙስና አመቺ ሆኖ የተዋቀረ ነው፡፡ ያዋቀሩት ሠዎች ግልፅ ባልሆነ መንገድ የህዝቡን ሃብት ለመንጠቅ ያደረጉትም ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጥ ነው አሁን መንግስት ይህን ነገር ማጥፋት ከፈለገ መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ አለበት፡፡ መዋቅሩን በሙሉ መለወጥ አለበት፡፡ አንድ ሁለት ሠው በመክሠስ ብቻ ችግሩ የሚወገድ አይደለም፡፡ ሃገራችን ከዚህ ቀደም ሙስናን በተመለከተ በአለማቀፍ ደረጃ በጣም ጥሩ ሪከርድ ነበራት፡፡ አሁን በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አመዘጋገብ ወደ 3ኛ ደረጃ ተጠግታለች፡፡ ይሄ በጣም አሣፋሪ ነው፡፡

“ገቢዎች ከመንግስትም በላይ ስልጣን የተሰጠው አካል ነው” አቶ ሙሼ ሠሙ – የኢዴፓ ሊቀመንበር

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሰሞኑን በሙስና በጠረጠራቸው ትላልቅ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ላይ የወሠደውን እርምጃ እንዴት ይመለከቱታል? ለኛ ይሄ ነገር የተለየ እውቀት የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ስቴት ካፒታሊዝም ወይም መንግስታዊ ከበርቴ የምትለው ስርአት አይነተኛ መገለጫው ነው፡፡ ነጋዴውን ህብረተሠብ የሚያሸማቅቅ፣ የመንግስትን ሚና የሚያጐለብት ነው፡፡ የንግዱን ማህበረሠብ የመንግስት ባለስልጣን ጥገኛም እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ጉዳዩን ለማስፈፀም፣ ስራውንም ለመስራት ሣይወድ በግዱ የመንግስት ባለስልጣናት አሽከር ይሆናል፡፡ ነጋዴውና የንግዱ ማህበረሠብ እየተዳከመ መንግስት እንዲተካው ነው ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡ መጨረሻ ላይ ይህ ስርአት ወዴት ነው የሚሄደው? ሂደቱ የመንግስት ባለስልጣናትን ከበርቴ የሚያደርግ ነው፡፡

ምክንያቱም ነጋዴው ችግሮቹን የሚፈታበትን መንገድ የሚያመለክት አይደለም፡፡ ባለሃብቱ በጥርጣሬ ነው የሚታየው፡፡ ታማኝ አይደለም፣ ብቁ አይደለም፣ ስርአት የለውም እየተባለ ነው፡፡ ግለሠብ ነጋዴውን በጥርጣሬና በስጋት የማየት አዝማሚያ አለ፡፡ ስግብግብ፣ ሌባ፣ ወንበዴ ወዘተ— ተደርጐ ነው የሚታየው፡፡ አሁን የተያዙት ባለስልጣኖች ይሄ ሁሉ ጉድ እያለባቸው ነው ነጋዴውን ሲያስፈራሩት፣ ሲዝቱበትና ኪራይ ሠብሣቢ ሲሉት የኖሩት፡፡ ስርአቱ ለእነዚህ ባለስልጣኖች መደራደሪያ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ የፈለጉትን ነጋዴ በፈለጉት ጊዜ ጠርተው እያሸማቀቁና ስሙን እያጠፉ ህገወጥ በሆነ መንገድ መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡ ይሄ ለኔ ሠዎችን የማሠርና ያለማሠር ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የስርአቱን የአስተሣሠብ ለውጥ የሚፈልግ ነው፡፡

የመንግስት ሹመኞችና ባለስልጣኖች የነጋዴውን ማህበረሠብ እንደ ሌባ፣ አታላይ፣ አጭበርባሪ፣ ኪራይ ሠብሣቢና ጠላት አድርገው የሚያዩበት ሁኔታ እስካልተለወጠ ድረስ ሙስናው ይቀጥላል፣ የመደራደሪያ በር ነው የሚከፍተው፡፡ አሁን የወሠዱት እርምጃ የሚደነቅ ነው፡፡ በሂደት ግን ውሣኔውንም የምናየው ይሆናል፡፡ አሁን የተደረገው “የበረዶ ጫፍ ነው” (Tip of the ice burg) እንደሚሉት ፈረንጆቹ፡፡ ትልቁ ጫፍ ገና ውሃው ውስጥ ነው ያለው፡፡ እንጀራ ጋግራ ከምትሸጥ ሴት ጀምሮ ገንዘብ የሚሠበሰብ መስሪያ ቤት፣ በዚህ ደረጃ መርከስና መበስበስ ውስጥ ከገባ፣ ሥርዓቱ ለአደጋ መጋለጡን ነው የሚያሳየው፡፡ በአጠቃላይ ስርአቱ የተጋረጠበት አደጋ መገለጫው ይሄ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም በፊት ሙስና ነበረ፤ ግን በመቶ ሚሊዮኖች አልነበረም፡፡ ነጋዴው አቤት የሚልበት ነፃና ገለልተኛ አካል ነበረው፤ አሁን ግን መስሪያ ቤቱ የራሱ ፖሊስ አለው፡፡

ዳኛ ነው የፈለገውን ነገር ይፈርዳል፡፡ አቃቤ ህግ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ከዚህ መስሪያ ቤት ጋር መስራት ይቻላል? ይሄ እኮ ከመንግስትም በላይ ስልጣን የተሠጠው አካል ነው፡፡ እነዚህ ሠዎች ዳኛ ናቸው፣ ፍርድ ቤት ናቸው፣ አቃቤ ህግ ናቸው፣ ፖሊስ ናቸው፡፡ ስርአቱ እንደፈለጉ እንዲፈልጡ እንዲቆርጡ ስልጣን ስለሠጣቸው፣ የድፍረታቸው ድፍረት ቤታቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማስቀመጣቸው ተነግሮናል፡፡ ስርአቱን እንዳለ በገንዘብ፣ በጉቦ መቆጣጠር የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሣቸውን ነው የሚያመለክተው፡፡ አንድ ሌባ የሠረቀውን ነገር ቤቱ የሚያስቀምጠው እኮ በጣም ደፋር ሲሆን ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የስርአቱ መገለጫ ነው፡፡ የተወሠደውን እርምጃስ እንደ መልካም ጅማሮ ማየት ይቻላል? ልትወስደው ትችላለህ፡፡ ግን ዋናው ችግር ግለሠቦቹ ላይ አይደለም፤ ሥርዓቱ ላይ ነው፡፡ ማህበረሠቡ ሙስናን የሚፀየፍ ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ተገቢውን ክፍያ እያገኙ ስራቸውን እንዲሠሩ ማድረግ ነው ጠቃሚው፡፡ ይሄን ሠውዬ ብታስረው ገና የእሡ ርዝራዦችና መሠሎቹ በየመስሪያ ቤቱ አሉ፡፡

ይሄ ነገር እኮ ሲባል የከረመ ጉዳይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አንድ እጄን ታስሬ እየሠራሁ ነው እስከማለት ደርሠው ነበር፡፡ ይሄ የሚያሣየው ምን ያህል ስር የሠደደ ችግር እንደሆነ ነው፡፡ ግለሠቦችን ማሠር ሙስናን ለመዋጋት አንድ መገለጫ ነው፤ ዋናው ነገር ግን የአስተሣሠብ ለውጥ ነው፡፡ ፍትሃዊ የሆነ የህግ ስርአት ሊበጅ ይገባል፡፡ ለአንድ መስሪያ ቤት የእግዚአብሔርን ያህል ጉልበት ተሠጥቶት እንዴት ሙስናን መዋጋት ይቻላል፡፡ ህገ ወጥ ነገር ለመስራት ሁሉም ነገር ተመቻችቶለታል፡፡ ይህ እያለ እንዴት ነው ሙስናን መታገል የሚቻለው፡፡ እርግጥ ስርአቱ በሽታውን ተረድቶ እርምጃ ለመውሠድ መነሣሣቱ የሚበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ እየተጋነነ እየተወራ ነው፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎችም እንዲበረግጉ እየተደረገ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ መንግስት ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ሠዎቹ እንደየጥፋታቸው ፍትህ ፊት ቀርበው ተመጣጣኝ ቅጣት የሚያገኙበትን መንገድ መከተል ነው እንጂ ድራማ መስራት አይጠቅምም፡፡ ማጋነን፣ ነገሩን ከሚገባው በላይ መለጠጥ፣ ማህበረሠቡ በዚህ ጉዳይ የተዛባ መረጃ ኖሮት ያልተገባ ነገር እንዲናገር ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ተገደው የገቡ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ሌሎች ደንግጠውና በርግገው ሃገር ጥለው እንዲሄዱ የሚያደርግ መሆን የለበትም፡፡ እነዚህ ሠዎች አሁንም ገና ተጠርጣሪ ናቸው፡፡ ስርአት ባለው መንገድ ተይዘው የሚቀጡ ከሆነም መቀጣት አለባቸው፡፡ አሁን ግን የሚወራው ያለቀ ጉዳይ ተደርጐ ነው፡፡ ቀድሞ በፕሮፓጋንዳ ግለሠቦቹን ወንጀለኛ አድርጐ ደምድሞ፣ ፍርዱ ትርጉም እንዲያጣ ማድረግ አይገባም፡፡ እነዚህ ሠዎች እኮ በአንድ ጊዜ ስማቸው ወርዷል፣ የፕሮፓጋንዳው ሠለባ ሆነዋል፡፡ ሌሎችም እንዲበረግጉ ሆኗል፡፡ ነገር ግን መንግስት “እነዚህ ግለሠቦች ተይዘዋል፣ ሌላው ነጋዴ ተረጋግቶ ስራውን ይስራ” ማለት ነበረበት፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲታይ የዚህ ሁሉ መሠረታዊ ችግር ይሄ መስሪያ ቤት የተሠጠው ከእግዚአብሔር ያልተናነሠ ስልጣን ነው፡፡ መንግስት አሁንም በነጋዴው ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት ይለውጥ፡፡

**********

Source: Addis Admass

Daniel Berhane

more recommended stories