ሙስናን በስልክ ለመጠቆም የሚያስችልና ከለላን የሚያመቻች ቻርተር ረቂቅ ቀረበ

ኅብረተሰቡ የሙሰና ወንጀሎች ሲፈፀሙ ሲያይ ወይም ሲጠረጥር በፍጥነት የሚያጋልጥበት የዜጎች ረቂቅ ቻርተር መዘጋጀቱን የፌዴራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በረቂቅ ቻርተሩ ላይ ግብዓት ለማሳባሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ማክሰኞ ሚያዝያ 29 /2005 በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ በውይይቱ በመክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ቻርተሩ እያንዳንዱ ዜጋ የሙስና ወንጀሎችን ለማጋለጥና ለመከላከል ከኮሚሽኑ ጋር እንዴት መሥራት እንዳለበት የሚያመለክት ነው።

በዚህም ዜጎች በመስርያ ቤታቸውና በአካባቢያቸው የሙስና ወንጀሎችን ሲያዩና ሲጠረጥሩ ለኮሚሽኑ በስልክና በአካል በማሳወቅ ቶሎ ክስ የሚመሰረትበትን ሁኔታ ቻርተሩ በዋነኝነት አካቷል።

የሙስና ወንጀል ጠቋሚዎችም ከሥራቸው ላይ እንዳይፈናቀሉና ጥቃት እንዳይደርስባቸው ኮሚሽኑ ሙሉ በሙሉ ከለላ ይሰጣል ሲሉም አስረድተዋል።

በፌደራል የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የዜጎች ቻርተር ላይ ሰፊ ማብራሪያ በአቶ ተስፋዬ ሻሜቦ የጥናትና ለውጥ ተቀዳሚ ዳይሬክተር የተሰጠ ሲሆን በረቂቅ ቻርተሩ ላይም የህንድ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይና የአውስትራሊያ ተሞክሮ ተካቷል፡፡

በኮሚሽኑ የሥነ ምግባር ትምህርት ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ በበኩላቸው ቻርተሩ የባለ ድርሻ አካላትን ግብዓት ካሰባሳበ በኋለ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ቻርተሩ ዜጎች ለሀገሪቱ የፀረ-ሙስና ትግል ተባባሪነታቸውንና አጋርነታቸውን የማሳደግ አላማ አለው፡፡

ቻርተሩ ተግባራዊ ሲሆን ለእያንዳንዱ ዜጋ ሙስናን በማጋለጥ በኩል ያለውን መብትና ግዴታ በይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ተብሏል ።

*************

Source: ERTA – May 7, 2013. Originally titled “ዜጎች የሙስና ወንጀሎችን የሚያጋልጡበት ረቂቅ ቻርተር ለውይይት ቀረበ”.

Daniel Berhane

more recommended stories