UDJ/Andinet| ፓርቲው እስከ2004 የረባ አባል አልነበረውም [አኩርፈው የወጡ ከፍተኛ አመራር]

ጠንካራና ትልቅ ተቃዋሚ እየተባለ የሚሞካሳሸው ‹አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ› Eng. Zeleke Redi - UDJ/Andinet party = ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ - የአንድነት ፖርቲ አመራርታችኛው መዋቅሩ ‹የለም› ሊባል በሚችል ደረጃ እንደሚገኝ አንድ ከፍተኛ አመራር ጠቆሙ፡፡

የአንድነት ፓርቲ መሪዎች ‹አምባገነን ናቸው› ያሉት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ግልፍተኛ፤ አቶ አሥራት ጣሴ ደግሞ መሠሪ ብለዋቸዋል፡፡

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የቀድሞ ፓርቲያቸውን ‹ብርሃን ለአንድነትና ለዲሞክራሲ› ፓርቲ ከ‹አንድነት› ፓርቲ ጋር እንዲዋሐድ ካደረጉ በኃላ የአንድነት ፖርቲ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ (ማለትም የአባላትና የአደረጃጀት ጉዳዮች) ሆነው በታህሳስ 2004 የተሾሙ ሲሆን፣ ሰሞኑን ግን አኩርፈው ወጥተዋል፡፡

ከ‹አንድነት› ፓርቲ የወጡበትን ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ፤ ፓርቲው ቢያንስ እስከ ታሕሳስ 2004 የረባ ታችኛው መዋቅር እንዳልነበረው፡-

‹እኔ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊነትን ስረከብ እገሌ የሚል አባል አልተረከብኩም። ዛሬ ግን አድራሻው በግልፅ የሚታወቁ አባላት አደራጅተናል። ›

‹እኛ ፓርቲውን ስንረከበው ሊዘጉ የተቃረቡ ሶስት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ብቻ ነበሩት። አባላትም በተመለከተ ይሄ ነው የምትለው ነገር አልነበረም። ›

ሲሉ የገለጹ ሲሆን፤ የአንድነት ፓርቲን ድርጅታዊ እና የአመራር ችግሮች ለሰንደቅ ጋዜጣ ሲዘረዝሩ ከተናገሩት መሀልም፡-

* ‹ዶ/ር ነጋሶ ዲሞክራሲያዊ የግል ባህሪ የላቸውም።…. አቶ አሥራት ባይገነፍልም የሚፈልገውን ነገር አድብቶ ያደርጋል:: የወደፊቱ የወጣቱ ፈተና እነዚህን አዛውንቶች ዲሞክራሲ ማስተማር ነው።›

* ‹ወደፊት የሚፈነዱ መሸፋፈኖች አሉ።…. በተለይ አንድነት ስለመድረክ፤ መድረክ ስለአንድነት ያለው ሁኔታ ላይ ብዥታ አለ።›

* ‹ምርጫው ውስጥ አንገባም የተባለበት አካሄድንም የአንድነት ፓርቲ አባላት በጥሞና እንዲያዩት እመክራለሁ።›

* ‹ከዲያስፖራ የሚላክ ገንዘብ አለ። [ነገር ግን] ለፓርቲው ማን ምን ያህል ይረዳል የሚለው በግልፅ አይታወቅም።›

(ሙሉውን ቃለ-መጠይቅ ከታች ያንብቡ፡፡)

********

(ሰንደቅ ጋዜጣ – ሚያዝያ 17/2005)

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርት ከፍተኛ አመራር አባል ነበሩ። ኢንጂነሩ በፓርቲው መዋቅር ውስጥ የስራ አስፈፃሚ አባልና የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢም ነበሩ። ኢንጂነር ዘለቀ በጋዜጦች ልዩ ልዩ ሐሳቦችን በመፅሀፍ ይታወቃሉ። ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ወደ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እንዲሁም በ1997 ዓ.ም ቅንጅት ተመስርቶ ሲንቀሳቀስ የጅማ እና አካባቢዋን ነዋሪ በማስተባበር የቀድሞውን ቅንጅት ውጤታማ ካደረጉ የፓርቲው አባላት አንዱ ነበሩ።

ቅንጅት ከፈረሰም በኋላ ተስፋ ባለመቁረጥ ብርሃን ለአንድነትና ለዲሞክራሲ (ብአዴፓ) ውስጥ በአመራር አባልነት ሲሳተፉ ቆይተዋል። በመቀጠልም ብርሃን ለአንድነት ለዲሞክራሲ ፓርቲ ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ጋር እንዲዋሐድ ጥረት ካደረጉ የፓርቲው አመራሮች አንዱ ነበሩ።

በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ከቆዩ በኋላ ከሰሞኑ በራሳቸው ፈቃድ ከፓርቲው አመራርነት ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብተዋል። ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ለዚህ ያልተጠበቀ ውሳኔአቸው ስላበቃቸው ጉዳይ ከባልደረባችን ዘሪሁን ሙሉጌታ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሰንደቅ፡- ከፓርቲ አመራር በገዛ ፈቃድዎ ለመልቀቅ የወሰኑት ለምንድነው?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- ፓርቲው ጉባኤ አካሂዶ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲያካሄድ እጩ ፕሬዝዳንት ነበርኩ። ነገር ግን በዶ/ር ነጋሶ ተበልጬ በድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ እንድሰራ ተደረገ። የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ከሆንኩ በመጀመሪያ ያደረኩት ከየቦታው ያሉ የአመራር አባላትን ወደ ማዕከል በማምጣት እንዲሰለጥኑ ተደርጓል። እንደምታስታውሰው የአመራር አባላቱ ከያሉበት መጥተው ሰሌን አንጥፈው እየተኙ ስልጠናውን ሌት ተቀን ተከታትለዋል።

ከስልጠናው በኋላ የአመራር አባላቱ በየክልሉ እራሳቸውን እንዲችሉ በመደረጉ በሰሜንና በደቡብ የሀገሪቱ ቀጠናዎች ቢሮዎች ተከፈቱ። የተከፈቱትን ቢሮዎች መልሶ ማየት ቀጣዩ እቅዳችን ቢሆንም የፓርቲው ጥቂት የአመራር አካላት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም።

የሚገርመው ነገር እኛ ፓርቲውን ስንረከበው ሊዘጉ የተቃረቡ ሶስት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ብቻ ነበሩት። አባላትም በተመለከተ ይሄ ነው የምትለው ነገር አልነበረም። እኛ ከመጣን በኋላና ስልጠናውን ከሰጠን በኋላ ከ25 ያላነሱ ጽህፈት ቤቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተን እያንቀሳቀስን ነው። እነዚህን ቢሮዎች እራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ ናቸው እና እነዚህን ሰዎች ለማበረታታት ሄደን ዞረን ማየት ይገባን ነበር። ነገር ግን ሊሆን አልቻለም።

ሰንደቅ፡- ለምንድነው ያልተቻለው?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- ገንዘብ የለም እንዳትል ደመወዝ ሲከፈል ታያለህ። አንዳንድ ጊዜ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ከሆንክ የተወሰኑ ሰዎች ደመወዛቸውን ትተው ቢያንስ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ስራ ሊያሰሩበት በተገባ ነበር። ነገር ግን መልካም ፈቃደኝነቱም የለም። ቢሮ ያሉት አመራሮች ደመወዛቸው እንዲጎልባቸው የሚፈልጉ አይመስለኝም። ለትግሉ ሳይሆን ለፅህፈት ቤቱ የሚወጣው ገንዘብ ሞቅ ያለ ነው።

በተለይ የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አስራት በአብዛኛው ለስራ ማከናወኛ ገንዘብ እንዲወጣ አይፈልግም። ምክንያቱ ይሄነው ለማለት አስራትን መሆን ሊጠበቅብኝ ይችላል። በእርግጥ ለትግሉ ማከናወኛ ገንዘብ የለም እየተባለ ደመወዝ ሲከፈል ታያለህ። ከዲያስፖራ የሚላክ ገንዘብ አለ። ነገር ግን እኔ እንደ አንድ የስራ አስፈፃሚ አባል የተሟላ መረጃ እንዲኖረኝ እንኳ አይፈልጉም። ስለዚህ ገንዘብ ለፓርቲው ማን ምን ያህል ይረዳል የሚለው በግልፅ አይታወቅም።

ሰንደቅ፡- በዚህ በኩል በፓርቲው ውስጥ ግልፅ የሆነ የፋይናንስ ሥርዓት የለም ማለት ነው?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- ግልፅነት ቢኖርማ እኔም አውቀው ነበር። እኔ በግሌ ግን ከሌላው አባል በተጋነነ መልኩ የተለየ ባልልህም አስተዋፅኦ ሳደርግ ቆይቻለሁ። አስተዋፅኦዬ ግን ከአመራሮቹ ጋር አላግባባኝም። እነሱ እኔ ለፓርቲው በግሌ የማደርገውን የፋይናንስ አስተዋፅኦ ቢሮ ገብቶ ከቢሮ ይውጣ ይላሉ። እኔ ግን የአንድት ፓርቲ ቢሮክራሲ እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ለፓርቲው የምሰጠውን ገንዘብ ወደ ፓርቲው ገብቶ እንደገና ለምኜ እንዲወጣ አልፈልግም። ፓርቲው ለእኔ የሚከፍለኝ ደመወዝ በቀጥታ ለአደረጃጀቱ እንዲውል አስወስኜ ያንኑ ገንዘብ እኛን አስፈቅደህ አውጣ ይላሉ። ስለዚህ በዚህ ረገድ የአሰራር መጣጣም አልነበረንም። በእርግጥ ፓርቲውን አቅሜ በፈቀደው መጠን ሳግዝ ቆይቻለሁ። የማደርገው ድጋፍ ወደፓርቲው ገብቶ በፓርቲው ቢሮክራሲ ውስጥ አልፎ መሄዱን አልፈለኩም። በተለይ እነ አቶ አስራት የዘረጉት ቢሮክራሲ ስለማያሰራ በእጄ ላይ ያለውን ገንዘብ ላመንኩበትና ለፈለኩት ስራ እንዲውል ነው ፍላጎቴ። ከአመራሩ ጋር ካቃቃሩኝ ምክንያቶች አንዱ ይሄ ጉዳይ ነው።

ሰንደቅ፡- ይሁን እንጂ አንተን በኢህአዴግ ደጋፊነት የሚጠረጠሩ አመራሮችም እንዳሉ ይነገራልና ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- “ኢህአዴግ ነው” የሚለው ፍረጃ የተለመደ ታፔላ ነው። ጠልፈው ሊጥሉት የሚያስቡትን ሁሉ “ኢህአዴግ ነው” ብለው ይፈርጁታል። ንፁህ እነሱ ብቻ አድርገው ነው የሚያስቡት። እኔን “ኢህአዴግ ነው” ብለውኝ ከሆነም በመጨረሻ የሚያፍሩት እነርሱ ናቸው። እኔ ኢህአዴግ መሆን ብፈልግ አንድነትን በአቋራጭ የምጠቀምበት ምክንያት የለኝም። ብፈልግ ግን እችላለሁ። ከመጀመሪያ ጀምሮ የቅርብ ጓደኞቼ ኢህአዴግ ሲሆኑ እኔ ግን አልፈልግም በማለት ነበር ወደ ኢሰመጉ የገባሁት። እናም “ኢህአዴግ ነው” የሚለው ፍረጃ ወጣት ተተኪዎችን ለመቅጨት የሚደረግ መፍጨርጨር ነው። ማህበራዊ ህይወት የግሌ እንደመሆኑ መጠን ዕድሉን አግኝቼ የኢህአዴግ ባለስልጣናትን በመቅረብ ስለዚች አገር ምን እያሰቡ እንደሆነ ማወቅ እፈልግ ነበር። ያለመታደል ሆኖ የምቀርበው አንድም ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣን የለም። በአንፃሩ አንድነት ፓርቲ ውስጥ ገብቼ ስርዓቱን በመታገሌ በገንዘቤና ንብረቴ ላይ በርካታ ጉዳት ደርሶብኛል። ሆቴሌ በታጣቂዎች ተዘርፏል። ከመኪናዬ ውስጥ አምስት መቶ ሺህ ብር ተዘርፌአለሁ። ደቡብ ኢትዮጵያ ለፓርቲ ስራ በሄድኩበት ወቅት መኪናዬ ተደብድባለች እና በስርዓቱ በርካታ ችግር ሲገጥመኝ ቆይቷል። ፍረጃው ግን ወጣት ታጋዮችን ለመጥለፍ የሚደረግ ጥረት ነው። እንደውም በአንድነት ውስጥ የኢህአዴግን ሚና እየተወጡ ያሉት እነሱ ናቸው። በእስከዛሬው ሂደት እስቲ ማንን ተኩ? ከዚህ ይልቅ በራስ ተነሳሽነት ወደ ፓርቲ የመጣነውን ሁሉ ገፍተው እያስወጡን ነው። ዶ/ር ነጋሶ ተቃዋሚ ፓርቲ ከተቀላቀሉ ጀምሮ አንድ ያፈሩት ተተኪ ወጣት አመራር የለም። አስራት በራሱ ለረጅም ጊዜ አመራር ላይ ቢቆይም ማንን አበቃ?

ሰንደቅ፡- እነሱ ሥልጣን ለማስረከብ ፈቃደኛ ነን። ነገር ግን የሚረከብ “ሰው የለም” ነው የሚሉት?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ሰው መቼ ያስቀምጣሉ? እኔ ሰው አይደለሁ? ዝንጀሮ ነኝ እንዴ? ከእነሱ ይጠበቅ የነበረው እኔን ለአመራር ማብቃት እንጂ እንድወጣ መግፋት አይደለም።

ሰንደቅ፡- እርስዎ የእነሱን ቦታ (ስልጣን) መውሰድ ይፈልጋሉ ማለት ነው?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- ምንሊያደርግልኝ? እኔ ሊቀመንበር የመሆን ፍላጎት ቢኖረኝ ቀደም ሲል በመሰረትነው ፓርቲ ሊቀመንበር መሆን እችል ነበር። እና ስልጣን አልፈልግም። እኔ ትግሉን አቅሜ በፈቀደው መጠን መርዳት ነው የምፈልገው።

ሰንደቅ፡- እርስዎ ስልጣን የማይፈልጉ ከሆነ ታዲያ ወጣቶች ስልጣን መያዝ አለባቸው የሚሉት ለምንድ ነው?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- ወጣቶች ከመጡ ፈጣን ለውጥ ያመጣሉ ብዬ ስለማምን ነው። ወጣቶች የትግሉን በትር ይያዙ ማለት ለውጥን ከማፋጠን እንጂ ከስልጣን ጥም ጋር መያያዝ የለበትም። በወጣቶች ዙሪያ የተንኮል ፖለቲካ የለም። እኔ ለምሳሌ በምንም አይነት የተንኮል ገመድ አቶ አስራትን (የፓርቲው የጽ/ቤት ኃላፊን) ጠልፌ ልጥለው አልችልም። ምክንያቱም የኔ ትውልድ ጠልፎ ለመጣል ቢያስብ እንኳ የሚያሴረው ፊትለፊት ነው። የእነ አስራት ትውልድ ግን የት ቦታ አስሮ ጠልፎ እንደሚጥልህ አይታወቅም። እና የእኔ ገመድ አሁን ያሉትን አመራሮች ጠልፎ አይጥልም።

ሰንደቅ፡- አቶ አስራት ጣሴን ደጋግመው የሚያነሷቸው በመካከላችሁ የግል ጥላቻ አለ?

ኢንጅነር ዘለቀ፡- የግል ጥላቻ የለንም። አብረን እንበላለን አብረንም እንጠጣለን። ነገር ግን አቶ አስራት ወጣቶችን ከዙሪያቸው ለማራቅ የሚያደርገው ጥረት ያስገርማል። በእርግጥ ሰውዬው ክፉ ቃል አይወጣውም። በአንፃሩ ዶ/ር ነጋሶ ግልፍተኛ ናቸው። ዓለም አቀፍ ግልፈተኞች ቢሰባሰቡ ዶ/ር ነጋሶ አንደኛ ነው የሚሆኑት። በትንሽ ነገር ግንፍል ነው የሚሉት። አቶ አስራት ባይገነፍልም ማድረግ የሚፈልገውን ነገር አድብቶ ያደርጋል።

ሰንደቅ፡- ለዶ/ር ነጋሶ በፃፉት የመልቀቂያ ደብዳቤዎት ላይ “ነፃነት” አስፈላጊ መሆኑን በደብዳቤዎ መግቢያ ገልፀዋል። በእርግጥ እርስዎ በፓርቲው ውስጥ ነፃ አልነበሩም ማለት ነው?

ኢንጅነር ዘለቀ፡- ያጣሁት ነፃነት ብዙ ነው። ይህቺ አገር እንደ ሀገርና ሕዝብ ያጣችውን ነገር እኔም አጥቼአለሁ። ለምሳሌ እኔ የምፈልገው ሕዝቡን አስተምረን “እምቢ” በማለት መብቱን መጠየቅ የተለማመደ ሕዝብ መፍጠር ነበር። ነገር ግን እነሱ ያሉትን ነገር ብቻ እንዲፈፀም ይፈልጋሉ። እኔ አጎብዳጅ ሆኜ “እሺ” የሚል ባህል ቢኖረኝ እነሱን “እሺ” እያልኩ ከምቀጥል የኢህአዴግን አገዛዝ “እሺ” ማለቱ ይቀለኛል።

ሰንደቅ፡- የፓርቲ ስነስርዓት ወይም ዲስፕሊን የሚባል ነገር አለ፤ ከዚህ አንፃር የፓርቲውን ደንብ ማክበር ተገቢ አይደለም?

ኢንጅነር ዘለቀ፡- ይሄማ ሌላ ጉዳይ ነው። የፓርቲን ደንብ ማክበር ግዴታ ነው። ነገር ግን መስራት ሲከለክሉህ ወይም እንዳትሰራ እንቅፋት ሲሆኑብህ እሺ ብለህ መቀጠል አስቸጋሪ ነው። እኛን እንዳንሰራ በማድረግ (የድርጅት ጉዳይ ኃላፊነት የተሰጠንን አካላት) በመጨረሻ ማጋለጥ ነው አላማቸው። እንዳትሰራ አሲረው ከያዙ በኋላ “አልሰራም” ብለው ለማቅረብ ነው የሚፈልጉት።

ሰንደቅ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፓርቲው ስራ ይልቅ ወደ ግል ስራዎ አተኩረዋል የሚል ወቀሳም አለ? ምናልባትም ለአሁኑ ውሳኔ ካበቁዎት ምክንያቶች አንዱ “አልሰሩም” የሚለው ግፊት ሚዛን ደፍቶ ይሆን?

ኢንጅነር ዘለቀ፡- በእኔ በኩል የተሰጠኝን ኃላፊነት ተወጥቻአለሁ ብቻ ሳይሆን እንዳልወጣ ተደርጌአለሁ ነው የምለው። ፓርቲው ሰውና ገንዘብ ይፈልጋል። ያም ሆኖ እኔ በፓርቲው ውስጥ የድርጅት ጉዳይ ስገባ 24 ሰዓት ልሰራ እንዳልሆነ ይታወቃል። ይሄም በመሆኑ ስራዬን የሚያግዝ ሰው መድቤአለሁ (አብቅቼአለሁ) ማለት እችላለሁ። ምክትሌም የግል ስራውን እንዲተው በማድረግ በስራው ላይ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስደርጌአለሁ። ከዚህ አንፃር ኃላፊነቴን አልተወጣሁም ብዬ አላምንም።

እኔ እንደ ዶክተር ነጋሶ 24 ሰዓት ቢሮ መቀመጥ አልፈልግም። እሳቸው ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው ያመጡት ለውጥ የት አለ? በፊዚክስ አስተሳሰብ ግድግዳን ልትገፋ ትችላለህ፣ አንድ ዓመት ሙሉ ግድግዳውን ስትገፋው ግድግዳው አንድ ሴንቲ ሜትር እስካልሄደ ድረስ የገፋኸው መጠን በርቀቱ ሲበዛ ዜሮ ነው የሚሆነው። እናም እነዶክተር ነጋሶ 24 ሰዓት በቢሮ ተቀምጠው አንድነትን መቼ ለወጡት? እና እኔ 24 ሰዓት ተቀምጠው የምሰራው ለምንድ ነው? ከመቶ በላይ ሰራተኞች ቀጥሬ የማስተዳድር ሰው እንደመሆኔ መሯሯጥ አለብኝ። ስለሆነም የፓርቲውን ስራ በቅርብ እየተከታተልኩ በጎን ደግሞ የራሴን ስራ እሰራለሁ።

ሰንደቅ፡- በፈቃድዎት ከፓርቲው ከመውጣትዎ በፊት ለምን በውስጥ ሆነው አይታገሉም ነበር?

ኢንጅነር ዘለቀ፡- ሁለት ነገር በአንዴ መታገል አስቸጋሪ ነው። ከውስጥ የፓርቲውን አምባገነናዊ አመራር ከውጪ ደግሞ አምባገነናዊ ስርዓትን በአንድ ጊዜ መታገል ያስቸግራል። ለዚህ ነው በውስጥ መቆየት ያልፈለኩት።

ሰንደቅ፡- በፓርቲው ውስጥ ቡድናዊ ዝንባሌ የመፍጠር ሁኔታ እንዳለ እየተነገረ ነው ከጽ/ቤት ሰራተኞች እስከ አመራሮች የመቧደን ነገር አለ?

ኢንጅነር ዘለቀ፡- የሚገርመው ይሄ ጉዳይ በስብሰባ ላይ ይነሳ ነበር። ሰራተኞች ወደ ስራ ለማሰማራት የሚፈጠሩ እንቅፋቶችና አተካራዎች ነበሩ። በተለይ በእኛ ቋሚ ኮሚቴ ላይ የሚደርሱት ተፅዕኖዎች ከፍተኛ ነበሩ። አስቀድሜ እንደነገርኩህ አንድ የሴራ ገመድ አለ ጠልፎ የሚጥልህ። በዕርግጥ የሚወጉህን ቦታ እነሱ ያውቁታል። የቱጋ እንደሚያምህ ጭምር ያውቁታል። ከዚህ አንፃር ቡድናዊ ዝንባሌዎች አሉ። እኔ ከአቶ አስራት ጣሴ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊነትን ስረከብ እገሌ የሚል አባል አልተረከብኩም። ዛሬ ግን አድራሻው በግልፅ የሚታወቁ አባላት አደራጅተናል። ይህ ሲባል ግን አሁንም ብዙ አልሰራም። ያላሰሩን ደግሞ አመራሮቹ ናቸው።

ሰንደቅ፡- ሰማያዊ ፓርቲ ለመግባት አስበዋል ይባላል እውነት ነው?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- በአሁኑ ወቅት የትኛውም ፓርቲ ውስጥ አልገባም። በመጀመሪያ ደረጃ አላውቃቸውም። ነገር ግን ሰማያዊ ፓርቲን የመሰረቱት ወጣቶች ስለሆኑ የተሻለ ስራ ይሰራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም አሁን ምንም የሚያግዳቸው የሴራ ፖለቲካ የለም። ሲሄዱም እኔ አሁን አላሰራ ያሉኝን ሰዎች ጠልተው ነው የሄዱት። የሚደግፋቸው ከተገኘም የተሻለ ነገር ሊሰሩ ይችላሉ። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወደየትኛውም ፓርቲ መግባት አልፈልግም። መቼም ፓርቲዎች እንደ እግር ኳስ ክለብ ስላልሆኑ በየጊዜው ዝውውር አላደርግም።

ሰንደቅ፡- በማመልከቻዋ ላይ ከፓርቲ አመራርነትዋ እንጂ ከአባልነት መልቀቅዎን አይገልፁም ለምን?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- አልወሰንኩም። ዶ/ር ነጋሶ አባል ሆነህ መቀጠል ትችላለህ ብለውኛል። በመሰረቱ ዶ/ር ነጋሶ ግዙፍ ስህተት ነው የሰሩት። እኔ አባል ሆኜ መቀጠሌን እሳቸው ስለፈቀዱና ስላልፈቀዱ የሚሆን አይደለም። ይሄ የእኔ ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቴ ነው። በእርግጥ እነሱ አባል በማባረር ቀዳሚ ናቸው። ሰሞኑን 33 ፓርቲዎች ከሚሉት ውስጥ አንዱ እነሱ ያባረሩዋቸው ወጣቶች የመሰረቱት ሰማያዊ ፓርቲ ነው። አሁንም ይሄንን ቃለ-ምልልስ ለምን ሰጠህ ብለው ሊያባርሩኝ ይችላሉ። በእኔ በኩል ቀድሜ እራሴን ከአመራርነት አባርሬአለሁ። ነገር ግን እያንዳንዱ የአንድነት አባል የፓርቲውን አመራር አበክሮ እንዲያውቅ እፈልጋሁ። የአንድት አባሎች እጅግ ጠንካራ ዓላማ ያላቸው ናቸው። በአመራሩ ግን እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ ሀገር አልታደልንም።

ሰንደቅ፡- በመጪው ነሐሴ ወር ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራል። እስከዚያ ጊዜ እንኳ ድረስ ለምን አልታገሱም?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- በመጀመሪያ እስከ ጉባኤውም አያደርሱኝም። ፍራቻቸውም ያ ይመስለኛል። እና እዚያ ድረስ የሚያደርሱኝ አይመስለኝም። በነገርህ ላይ ዶ/ር ነጋሶ ከኢህአዴግ የወጡት በግንፍልተኝነታቸው እንጂ አስበውበት አይመስለኝም። ሊነቀፉ አይፈልጉም፣ መተቸት አይፈልጉም። ዲሞክራሲያዊ የግል ባህሪ የላቸውም። የወደፊቱ የወጣቱ ፈተና እነዚህን አዛውንቶች ዲሞክራሲ ማስተማር ነው።

ሰንደቅ፡- የአመራር መልቀቂያ ደብዳቤዎት ላይ በፓርቲው ውስጥ “ጥቂት አምባገነን አመራሮች” የሚል ቃል አይቻለሁ። በእርግጥ ገዢውን ፓርቲ አምባገነን እያሉ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ አምባገነን መሪዎች አሉ መባሉን እንዴት ያዩታል?

ኢንጂነር ዘለቀ፡- (ሳቅ) ለአምባገነንነቱ አትጠራጠር አምባገነን ናቸው። አምባገነን ማለት እርሱ የሚፈልገው ብቻ እንዲደረግለት የሚፈልግ ማለት ነው። አምባገነን ማለት ከስሩ ሌላ ሰው እንዳይመጣ የማያደርግ ነው። በአንድ ትልቅ ዋርካ ስር የፋፉ ተክሎች አይበቅሉም። ምክንያቱም የዋርካው ጠፈጠፍ እንዳይበቅሉ ያደርጋቸዋል። ብርሃን እንዳያገኙ በማድረግ ቀጭጨው እንዲቀሩ ያደርጋል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ከውስጣቸው ሰው እንዲወጣ የማይፈልጉ ከሆኑ አምባገነን ናቸው ማለት ነው። ከኮሚኒስትታቸው አስተሳሰብ ብዙ የተለወጡ አይመስለኝም።

በአጠቃላይ ወደፊት የሚፈነዱ መሸፋፈኖች አሉ። በተለይ አንድነት ስለመድረክ፤ መድረክ ስለአንድነት ያለው ሁኔታ ላይ ብዥታ አለ። ከዚህ ባለፈ ምርጫው ውስጥ አንገባም የተባለበት አካሄድንም የአንድነት ፓርቲ አባላት በጥሞና እንዲያዩት እመክራለሁ። ህዝብን ሳይይዝ ኢህአዴግን እንደራደር ማለት ፈፅሞ የማይሆን ነገር መሆኑን መረዳት አለብን። ዲሞክራሲ በድርድር ወይም በልመና አይመጣም። በእርግጥ ጠንካራ ብሔራዊ ም/ቤት እንዳለን አምናለሁ። ስራአስፈፃሚው ላይ ችግር መኖሩን አባላቱ እንዲገነዘቡልኝም እፈልጋለሁ።

*************

Daniel Berhane

more recommended stories