Sendek | 62 በመቶ ታራሚዎች በአዕምሮ ጭንቀት እየተሰቃዩ ነው

– በአዲስ አበባ 62 በመቶ ታራሚዎች
በአዕምሮ ጭንቀት እየተሰቃዩ ነው
– በየዓመቱ ስምንት በመቶ ሕዝብ ራሱን ያጠፋል

(በፀጋው መላኩ)

ሰሞኑን ጤና ጥበቃ ከ2012/12 – 2015/16 ብሔራዊ የአዕምሮ ጤና ስትራቴጂ ይፋ ባደረገበት ወቅት በለቀቀው መረጃ በአዲስ አበባ (ቃሊቲ) የሚገኙት የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ከሚገኙት ታራሚዎች መካከል 61 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት በከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት (High Level of mental Distress) የተጠቁ መሆናቸውን ገልጿል። ሪፖርቱ ታራሚዎቹን ለአዕምሮ ጭንቀት ከሚዳርጓቸው ምክንያቶች መካከል በጠባብ ክፍል ውስጥ መታፈግ፣ በግዳጅ ለብቻ እንዲገለሉ ማድረግ (Enforced Solitud
e)፣ ብዙም እንቅስቃሴ አለማድረግ በቀጣይ ህይወት ላይ ተስፋቢስ መሆን፣ ከለመዱት ማኅበራዊ ህይወት መለየት፣ በቂ የሆነ የጤና አገልግሎትን በተለይም የአዕምሮ ጤንነተን የሚመለከት አገልግሎት በማረሚያ ቤቶቹ አለማግኘት በዋነኝነት ተጠቅሷል።

በማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች ራሳቸውን የሚያጠፉበት ሁኔታ መኖሩን የገለፀው ይሄው መረጃ ከተጠቀሱት ችግሮች ጋር በተያያዘ ታራሚዎች በድብርት (Depression) ውስጥ ይገባሉ ብሏል። የእያንዳንዱን ታራሚ የአዕምሮ ችግር ለመፈተሽና ተጠቂዎቹን ለመከታተል የአቅም ውስንነት ያለ መሆኑን የገለፀው ይሄው የጤና ስትራቴጂ፤ በተመሳሳይ መልኩ ችግሩንም ለማቃለል የአቅም ውስንነት መኖሩን በስትራቴጂው ላይ አስቀምጧል። ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግም የፌዴራሉ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያቤት ከፍትህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር በቀጣይ በጋራ የሚሰራ መሆኑን አስታውቋል። በዚህም ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ በቀጣይ በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ የሚያልፉትንና እስር ቤት ውስጥ ያሉት ታራሚዎች የአዕምሮ ጤንነትን ለመከታተል የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ለመፈራረም ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።
በሌላ ዜና በዚሁ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ በተሰጠው ማብራሪያ በኢትዮጵያ ከእያንዳንዱ መቶ ሺ ህዝብ 7 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው በየዓመቱ ራሱን ያጠፋል። 3 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ራሱን የማጥፋት ሙከራ (Suicide attempt) የሚያደርግ ነው።

በኢትዮጵያ ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ቢኖርም የአዕምሮ ህክምናው ተለይቶ አገልግሎት እየሰጠ ያለው አማኑኤል ሆስፒታል ብቻ ነው። በቅርቡም ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የኰተቤ ሆስፒታልም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ከአልኰል፣ አደንዛዥ ዕጾችን አጠቃቀምና ከበርካታ ውስብስብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጐች ለአዕምሮ ጤንነት መጓደል የሚጋለጡ መሆኑን ይሄው ስትራቴጂክ ሠነድ ያመለክታል። በኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የተጠቁ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ለአዕምሮ ህመም ተጋላጭነታቸው ከፍ ብሎ የተገኘ መሆኑን የገለፀው ይሄው ሠነድ፤ ይህም በዋነኝነት ከጭንቀት ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃው ያትታል። የፀረ ኤች አይ ቪ መድሐኒቱን ከሚወስዱት ዜጐች መካከልም 38 በመቶ የሚሆኑት በከፍተኛ ድብርት እንደሚሰቃዩ የተደረገው ክትትል ያመለክታል ብሏል።
****************
*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 24, 2012. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the drop down menu for posts on related topics.

Daniel Berhane

more recommended stories