Sendek| ካሮታዊው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ዕድገት [Amharic]

(በኤፍሬም ብርሀኑ)

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ራድዮና ቴልቪዢን ድርጅት የከፍተኛ ትምህርት ምሩቋን በዝቐተኛ ስራ ላይ መሰማራት ትክክለኛነት ብሎም ለሌሎች አርአያ ይሆናሉ ተብለው የተመረጡ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ሳይቀር በማወያየት የተሰራውን ፕሮግራም ከተመለከትኩ በኋላ ነው። የዚህ የኮብል ስቶን ጉዳይ ብዙ ሲያከራክርና ሲያወያይ መሰንበቱ አንባቢዎች የሚገነዘቡት ነው። የትምህርት ሚንስትሩም በዚሁ ጉዳይ ላይ ሰፊ ቃለ ምልልስ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ማድረጋቸውን ተመልክቻለሁ። እውነታው አንድ ለናቱ የሆነው የቴልቪዢን ጣቢያ እንዳቀረበው ይሆን? ብዙዎቻችን እንደምንስማማበት የማስበው እውነታው ከዚህ በእጅጉ የራቀ መሆኑን ነው።
ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ሀሳቦች ለማቅረብ እሞክራለሁ። እናንተም በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት ትሰጡበታላችሁ ብዪ ተስፋ አደርጋለሁ።

መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖረው ስለሚገባ ተሳትፎ
ነፍሳቸውን ይማርና ክቡር ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተባ አንደበታቸው የመንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖረው ስለሚገባ ተሳትፎ ክርክር በማድረግ ይታወቁ ነበር። እርግጥም መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ቅቡል ሐቅ ነው። ዋነኛው የመንግስት ተሳትፎ በገበያ መር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚታሰበው የፍላጎትና የአቅርቦት መጣጣም በማይቻልባቸው፤ እንዲሁም የግሉ ሴክተር ውጤታማ እንቅስቃሴ ሊያደርግባቸው በማይችልባቸው ዘርፎች ለምሳሌ የመንገድ፣ የሃይል አቅርቦት፣ የሃገር ደህንነት የመጠበቅ፣ የህብረተሰብ ጤና መጠበቅ፣ ትምህርት ማስፋፋት፣ በአጠቃላይ የህብረተሰብ አገልግሎት በእንግሊዝኛው (Public Goods) አቅርቦት ላይ የግሉ ሴክተር ውጤታማ ስራ ሊሰራባቸው የማይችልባቸው በመሆናቸው ምክንያት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል። ሁለተኛው መሰረታዊ ምክንያት በገበያ እንቅስቃሴ ያልተገባ ትርፍ ወይም ኪሳራ እንዳያጋጥም፤ የገበያ ስርአት አለመስተካክል (Market Failure) በሚኖርበት ግዜ መንግስት ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ይጠበቃል። ያልተገባ ኪሳራ በምንልበት ግዜ አንድ ምርት ወይም አገልግሎት ለማምረት የሚወጣው ወጪ በአምራቹ ወይም በሸማቹ ሳይሸፈን ሲቀር ማለት ነው። ለምሳሌ መጠጥ ጠጥቶ የሚያሽከረክር ሰው ጉዳት ሲያደርስ ጉዳት የሚደርስበት ሰው አልኮሉን በማምረትም ሆነ በመጠቀም ሂደት ውስጥ ተሳትፎው የሌለበት ነው። የአካባቢ ብክለት የሚያስከትሉ ጉዳቶችም፤ ከዚሁ የሚመደቡ ናቸው።
እዚህ ሁሉ ሀተታ ውስጥ መግባቴ አለምክንያት አይደለም፤ መንግስት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያጋጥመውን የገበያ አለመስተካከል ጣልቃ ገብቶ ያስተካክላል፤ መንግስት ራሱ ግን በኢኮኖሚ ውስጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ግን የሚያስተካክል የለም። ከጥራት ይልቅ፤ ብዛትን ትኩረት ያደረገው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
በመሰረቱ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስፈላጊነት ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ስንችል ነው፤ ለምን መስፋፋቱ ያስፈልጋል የሚለውን ሀሳብና ከዛም ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ከፍተኛ የህዝብ ሀብት ማፍሰስ ጠቃሚነት መመልከት የሚቻለው።
ትምህርት ለአንድ አገር እድገት የማይተካ ሚና ያለው ዘርፍ መሆኑ ፀሀይ በምስራቅ በኩል ትወጣለች ብሎ እንደማለት ነው የሚሆነው። ሆኖም ግን የትምህርት እቅድ በሚነደፍበት ጊዜ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም የወደፊት የእድገት እቅድ ጋር ተሰናስሎ መቅረብ ይገባዋል። ይህ በማይሆንበት ጊዜ አሁን እንደምንመለከተውና ነጋ ጠባ የኢትዮዽያ ራድዮና ቴልቪዢን ድርጅት ሊያስረዳን እንደሚሞክረው ሳይሆን፤ ለከፍተኛ ትምህርት እየተደረገ ያለው መስፋፋት ከጥቅሙ ጉዳቱ በእጅጉ አመዝኖ የምንመለከተው።

ትምህርት እንደግብዓት
የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ በራሱ እንደ መጨረሻ ግብ የሚታይ አይደለም። እነዚህ ምሩቃን በሲቪል ሰርቪሱ በአገልግሎት እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ገብተው አንቀሳቃሽ እንዲሆኑ ይጠበቃል። በሌላ አነጋገር ለነዚህ ሴክተሮች በግብዓትነት ያገለግላሉ ማለት ነው። ለዚህ ነው ጥራት ያለው ትምህርት ተምሮ ተወዳዳሪ የሆነ ብቃትና እውቀት ጨብጦ የማይወጣ ተመራቂ በቂ አገልግሎት መስጠት የማይችል፤ የሚሆነውና ዞሮ ዞሮ ለአጠቃላይ እድገቱ ገንቢ ሚና መጫወት እንዳይችል የሚያደርገው። አንድ ማሣያ እዚህ ጋር ልጥቀስ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሜካኒካል ኢንጅነሪኒግ ዘርፍ ለአምስት ዓመት ያክል ትምህርታቸውን ተከታትለው የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች አውሮኘላን ዲዛይን በማድረግ የመሳሰሉ ከፍ ያለ ሙያ ላይ እንዲሰማሩ ይጠበቃል። እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እነዚሁን ተማሪዎች ተቀብሎ ተጨማሪ የሁለት ዓመት ትምህርት ሰጥቶ በአይሮኘላን ጥገና ስራ ላይ ያሰማራቸዋል። ለወትሮው አየር መንገዱ የሁለት ዓመት ተጨማሪ ስልጠና የሚሰጣቸው በተግባረእድ በቴክኒክ ሙያ ሁለት ዓመት ሰልጥነው የሚወጡትን ነበር። ይህ ማለት እነዚህ ተማሪዎች ሶስት ተጨማሪ ዓመት ትምህርት ላይ ያሳለፉት ጊዜ ጠቃሚ አልነበረም ማለት ነው። ለዚያውም መስራት ከሚገባቸው ስራ ዝቅ ብለው መስራታቸው ታሳቢ ሆኖ ማለት ነው። ለአንድ ተማሪ አምስት ዓመት ተምሮ ሁለት ዓመት ከተማረው እኩል ስራ የሚሰራ ከሆነ እርሱ ለማሰልጠን የወጣው ወጪ ውሃ በላው ማለት ነው።

የሀገሪቱ የሠራተኛ ቅጥር ሁኔታ
ሌላው በስፋት የሚታየው አደገኛ ችግር የሠራተኛ ቅጥር
እና ጥቅማጥቅም ጋር ተያይዞ ያለው ነው። አንድ በዲኘሎማ የተመረቀ ተማሪ ሊሰራው የሚችለው ስራ በአሁኑ ጊዜ በዲግሪ አልፎ አልፎም በማስተርስ የተመረቁ ተማሪዎች ገብተው ሲሰሩበት እየተመለከትን ነው። ይሄ ወዴት ይወስደናል ስንል፤ ቀደም ሲል በዲኘሎማ ትምህርት ይገኝ የነበረው ደሞዝ ለማግኘት አሁን በትንሹ በዲግሪ ደረጃ መማር የግድ ሊሆን ነው ማለት ነው። በዚህ ምክንያት አላስፈላጊ የሆነ ወጪ እንዲሁም ሌላ ስራ ሊሰራ በሚችልበት ጊዜ በትምህርት እንዲጠፋ ይሆናል ማለት ነው። አንዳንድ መንግስታዊ የስራ ማስታወቂያዎችን ጋዜጣ ላይ ተመልክታችሁ እንደሆነ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀ ተማሪ በሶስት ሺህ እና በአራት ሺህ ብር ለመቅጠር ይፈለጋል። አገሪቱ ይህንን ለማድረግ የምታወጣው ወጪ ወደሌሎች ተጨባጭ የኢኮኖሚ እድገት ሊያመጡ ወደሚችሉ ተግባራት ለምሳሌ የህዳሴውን ግድብ ለመስራት ቢውል ስንት ጠቀሜታ ይኖረው ነበረ።

ተወዳዳሪነትን ማሳደግ
አገራችን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። በአፍሪካም ቢሆን ንግድንና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመሳብ ክፍለአሁጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስሮች በተፋጠነ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ብሩንዲን፣ ሩዋንዳን እና ታንዛንያን በንግድ ትስስር በማስተሳሰር ላይ ይገኛል። አንድ ኬንያዊ በቀበሌው መታወቂያው ብቻ በአባል አገራቶቹ ውስጥ እንደልብ የሚንቀሳቀስበት እንዲሁም የስራ እድል የሚያገኝበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ያለው። ኢትዮጵያ ወጣቶቻን ተገቢውን ጥራት ያለውን፤ ተወዳዳሪነትን በአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በክፍለአህጉር፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስገኝ ትምህርት መስጠት ካልቻለች፤ ከአሥር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በተለያየ የሙያ መስክ ተቀጥረው የሚሰሩ የሌላ አገር ዜጐች ልናይ ነው ማለት ነው፤ ይህ አፋጣኝ የሆነ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ነው።
ስለተወዳዳሪነት ስናነሳ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የግብርና ውጤቶችን ብቻ በማቅረብ ኢኮኖሚው ወደሚታሰበው መካከለኛ ገቢ ለማድረስ የማይቻል ነው የሚሆነው። ለዚህም በርካታ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፋትና፤ ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያስፈልጋል። በዚህ ሁሉ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ትልቁን ድርሻ ሊወጣ ይገባዋል። ዩኒቨርስቲዎቻችን ጥናትና ምርምርን በማድረግ የተሻሻለ የአሰራር ዘዴ በማምጣትና በማስተዋወቅ ምርታማነት የሚያድግበትን ሁኔታ መቀየስና ለኢንዱስትሪ እድገት ተገቢውን ሚናቸውን መጫወት ይገባቸዋል።
ዛሬ እነቻይና እና ህንድ የዓለም የኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ ደረጃ እየሳቡ የሚገኙት፤ ተወዳዳሪነታቸው ከፍ ያለ ስለሆነ ነው። የሰለጠነ የሰው ሀይል፤ ብቃት ያለው ስራ መስራት የሚችል የሰው ሀብት፤ በብዛት ማፍራት በመቻላቸው ጭምር ነው።

ማጠቃለያ
ለዚህም ነው ቅድም በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች በዝቅተኛ ስራ መሰማራት የአጠቃላይ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓቱን ውድቀት አንድ ማሳያ እንጂ የዜጐች ስራን የማክበር ወይም ያለመናቅ ጉዳይ ተደርጐ መታየት የሌለበት። ከሁሉ የገረመኝ ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያየ ጊዜ ስለትምህርት፤ እንደዚሁም ስለእውቀት አስፈላጊነት፤ እና ወጣቶች ያገኙትን እውቀት ቶሎ ወደ ተግባር እንዲለውጡ የመከሩባቸውን የተለያዩ ስብሰባዎችን በማቅረብ ለዚህ ኘሮግራም ማሳያ ማድረጋቸው ነው። ኘሮግራሙ እኔ እንደሚገባኝ ያተኰረው ስለእውቀት አላስፈላጊነት ነው እንጂ አስፈላጊነት አይደለም፤ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ማለት ይህ ነው።

****************

*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 17, 2012, titled “ካሮታዊው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ዕድገት”, authored by Ephrem Berhanu. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the Economy archive for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories