ኢትዮጵያዊቷ በአቡዳቢ በወለደች በ1 ሰዓት ለፍርድ ቀረበች [Amharic]

(በመስከረም አያሌው)

በአቡዳቢ በቤት ሰራተኛነት ትተዳደር የነበረችው ኢትዮጵያዊት ሴት ልጇን በተገላገለች አንድ ሰዓት ውስጥ ለፍርድ መቅረቧ እና በእስራት መቀጣቷ ተገልፀ።
ሰቨን ደይስ ኢን አቡዳቢ ድረ ገፅ እንደዘገባው፤ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ከጋብቻ ውጪ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈፅማለች የተባለችው ይህች ኢትዮጵያዊት በወለደች በአንድ ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ ከነ ልጇ እስር ቤት ገብታለች።
ኢትዮጵያዊቷ በእግር ብረት ታስራ ፍርድ ቤት መቅረቧን የገለፀው ዘገባው ፤በዳኞች ፊት ቀርባ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደምትፈልግ ደጋግማ

ስትማፀን ተሰምታለች ብሏል። ከኢትዮጵያዊቷ ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነት አድርጓል፤ የልጇም አባት ሊሆን ይችላል ተብሎ የተጠረጠረው በታክሲ ሹፍርና የሚተዳደር ባንግላዴሻዊም በድርጊቱ ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት የቀረበ ቢሆንም ጉዳዩ እስከሚጣራ ድረስም በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል።
ኢትዮጵያዊቷ ትዳር ያልመሰረተች ብትሆንም ማርገዟ የታወቀው ከወራት በፊት ለአሳሪዋ በመናገሯ መሆኑም ተገልጿል። አሳሪዋም ይሄንን እንደተረዳች ለፖሊስ ሪፖርት አድርጋ የሴትየዋን መውለድ ስትጠባበቅ ቆይታለች። ህፃኗ ስትወለድም ኢትዮጵያዊቷ ድርጊቷን መፈፀሟ ሙሉ ለሙሉ ሊረጋገጥ ችሏል። ኢትዮጵያዊቷ ለሶማሊያውያን ቤተሰቦች በቤት ሰራተኝነት በማገልገል ላይ ሳለች ባንግላዴሻዊውን እንደተዋወቀችውም ተገልጿል። ኢትዮጵያዊቷ በመጨረሻም ጥፋተኝነቷ ተረጋግጦ ልጇን ይዛ ወደ እስር ቤት ያመራች ሲሆን እስራቷን ከጨረሰች በኋላ ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ መቻሏን ግን እርግጠኛ አይደለችም። የእስር ቤቱ ባለስልጣናትም ሴትየዋ የእስር ጊዜዋን ከጨረሰች በኋላ ልጇን ይዛ አልያም ተነጥቃ ወደ ሀገር ቤት ልትመለስ ትችላለች እያሉ ነው።

****************

*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 17, 2012, titled “ኢትዮጵያዊቷ በአቡዳቢ በወለደች አንድ ሰዓት ውስጥ ለፍርድ ቀረበች”, authored by Meskerem Ayalew. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the Women archive or the Human Rights archive for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories