ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ፡- 15 አመት ልታሠር እየታሰብኩ ልሠራ አልችልም [Amharic]

Interview of Ethio-Channal Newspaper’s owner and chief-editor Samson Mamo with the Amharic weekly, Addis Admas.

**************

ከጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ

አዲስ አድማስ፡ ለጋዜጣህ ከሼህ አል አሙዲንና ከኢህአዴግ ድጋፍ ታገኛለህ ይባላል?

ሳምሶን ማሞ፡ ከአራት አመት በፊት ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ሲጀመር በሳምሶን አድቨርታይዚንግ ነው የተመሠረተው፡፡ እኔ እድሜዬን በሙሉ ጋዜጠኛ ሆኜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ሌሎች ሥራዎች እንጀራ ሊያበሉኝ ይችላሉ፤ ውስጤን ግን እሚርበው ነገር አለ፡፡ ያ ደግሞ ሙያ ነው፡፡ የጋዜጣ ሥራ የጀመርነው ለዚያ ነው፡፡ በሚዲያ ስራ ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን ሬድዮና ቴሌቪዥንም እያሰብን ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ 40 ሰራተኞች አሉ፡፡ ዋናው የተመሠረተበት ዓላማ ለህዝብ መረጃ ለመስጠት ነው፡፡

ሌላ ታሪክ የለውም፤ እኛ በነፃነት ነው የምንሠራው፡፡ ብዙ ሰዎች ብዙ የሚያወሩት ነገር አለ፡፡ ለሚወራው ወሬ ሁሉ መልስ መስጠት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔ ከየት ተነስቼ የት እንደደረስኩ ማንም ያውቃል፡፡ ይህንን ጋዜጣ የጀመርነው መቶ በመቶ በራሳችን በጀት ነው፡፡ ጋዜጣውን ለማቋቋም ያነሳሳኝ ደሜ ውስጥ ያለው ፍላጐት እንጂ  የማንም ፍላጐት አይደለም፡፡ ከኢህአዴግም ሆነ ከሼህ መሐመድ ጋር በዚህ ጉዳይ አንተዋወቅም፡፡ ሼሁ ለእኔ ጋዜጣ ድጋፍ ቢያደርጉ ኖሮ ዛሬ  ማተሚያ ቤት ይኖረኝ ነበር፡፡ ሰው የተለያየ ነገር ይላል፤ እየሰማሁ እስቃለሁ፡፡ እኛ ሁለት ድርጅቶች አሉን፡፡ በነሱ ራሳችንን ለመቻል እየተንደፋደፍን ነው ያለነው፡፡ እንደሚታየው የሰው ቤት ተከራይተን እንሠራለን፤ የሰው ቤት ተከራይተን እንኖራለን፤ የተረፈን ነገር የለም፡፡

አዲስ አድማስ፡ መንግሥትን/ኢህአዴግን በመደገፍ ትታማለህ?

ሳምሶን ማሞ፡ ይሄ ስርአት መቀጠል አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእዚህን አገር ሀላፊነት ሊሸከም የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፡፡ እንደ ግለሰብ ለኢህአዴግ ጥሩ ስሜት አለኝ፡፡ በጣም ብዙ ችግር እንዳለበት እያወቅሁኝም ማለት ነው፡፡ መንግስትም ብዙ ችግሮች እንዳሉበት አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ችግሮቹን እየተጋራን — የመጋራት ሃላፊነት ስላለብን እንደዜጋ አገሬ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ ስለዚህ ይሄ መንግስት መቀጠል አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ መንግስት የሚቀጥል ከሆነ ደሞ ከነችግሩ መቀጠል የለበትም፤ ችግሩን ብንጋራውም መታረም አለበት፡፡  በዛ ላይ ጠንከር ያሉ ነገሮችን ነው የምሠራው፡፡ እስር ቤት አይደለም እንጦሮጦስ ቢያወርዱኝ ያንን መስራቴ አይቀርም፡፡ ከሌሎች ጋር የማንስማማው ይሄ መንግስት መረገም አለበት ብለው ስለሚያስቡ ብቻ ነው፡፡ ይሄ መንግስት መረገም የለበትም፡፡

እኔ በጋዜጣዬ ሁሉንም ወገን ማስተናገድ አለብኝ፤ ተቃዋሚዎች ከፈለጉ በሩ ክፍት ነው፤ የእነሱ ችግር አይመጡም ፤ ምክንያቱ ደግሞ የኢህአዴግ ጋዜጣ ነው ብለው ስለሚያስቡ ብቻ ነው እንጂ… ቢመጡ ምንጊዜም እናስተናግዳለን፡፡ በቅርቡ የማስታውሰው —- አቶ ገብሩ አስራት የእኛ ጋዜጠኞች ሲያነጋግሯቸው ፍቃደኛ ሆነዋል፡፡ ሁሉም የሚፈልጉትን ነገር ስሜታቸውን መግለጽ ይችላሉ፡፡ መንግስትን መውቀስም ማሞገስም ቢፈልጉ በሩ ክፍት ነው፡፡ እነሱ ግን እኛን አይጠሩንም፡፡ በዚህ ጋዜጣ የመንግስት ጥሩነት እንዲፃፍ አይፈልጉም፡፡ የዚህን መንግስት ጥሩነት ለመፃፍ ደግሞ እኔ እንደዜጋ እና እንደ ጋዜጠኛ ሃላፊነት አለብኝ፡፡ ጠ/ሚኒስትር መለስን የሚመርቅ ካለ መመረቅ መብቱ እንደሆነ ሁሉ፣ እሳቸውን የሚወቅስም ካለ ሁለቱንም ወገን እናስተናግዳለን፡፡ ሌላው ስለተቃዋሚዎች ጋዜጣ ላይ የሚወጣ ብዙ ማስረጃ እናገኛለን፡፡ በኢህአዴግም ላይ ካገኘን እንሠራለን፡፡ ማስረጃ ቢያመጡልንም እንሠራለን፡፡ ተቃዋሚዎቹ በፃፍንባቸው ጉዳይ ላይ ማስረጃ ለማቅረብ ግን አልቻሉም፡፡ እኛ ግን የሠራነው ነገር እውነት ነው፡፡ ሚስጥርም ቢሆን በመረጃ በትክክል ሠርተናል፡፡ ፍ/ቤት  ወደ ሰባት ክስ አለብን ጋዜጣዋ ከተጀመረች ጀምሮ ፍ/ቤት  ወደ ሰባት ክስ አለብን ፡፡

አዲስ አድማስ፡ ከማስታወቂያ ደንበኞችህ ጋር ስትጋጭ በጋዜጣ ላይ አሉታዊ ነገር ትጽፋለህ ይባላል?

ሳምሶን ማሞ፡ እኔ በግሌ የምጋጭበት ሁኔታ ተፈጥሮ አያውቅም!! ለማለት የፈለግሽው የሻዲ ለጋን በተመለከተ ከሆነ ከ10 አመት በፊት የሆነ ነገር ነው፤ እሱም ቀርቷል፡፡ ፓል ኦይልን በተመለከተ በተከታታይ የምንሠራቸው ስራዎች አሉ፡፡ ይሄንን ምርትም በተመለከተ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው ለመስራት ያሰብኩት፡፡ አሁን ድርጅቱን ማን እንደሚመራው አላውቅም፡፡ ግንኙነት የለኝም፡፡ ፍቅርም ጠብም የለኝም፡፡ በእርግጥ በአርቲስት አልማዝ ሃይሌ ጉዳይ አነጋግረናቸዋል፡፡

እሷን ደሀ ናት ብለው አጭበርብረው ሁለትና ሶስት ሺህ ብር እየከፈሉ፣ አምስት አመት ሙሉ ድፍን ኢትዮጵያ ሲያስተዋውቁ ነበር፡፡ ያንን እኔ ሀላፊነቱን ወስጄ አርቲስቶችን በማስተባበር እስከ ማሳመጽ ድረስ እሠራለሁ የሚል አቋም አለኝ፡፡

እኔ ሰው ቢሮ ሔጄ ማስታወቂያ ለምኜ አላውቅም፡፡ አንድ እንጀራ ለመብላት ብዙ አያስፈልገኝም፡፡ ከቢሮዬ አልወጣም፤ ጠረጴዛዬ ላይ የመጣውን ነው የምሠራው፡፡ ስለዚህ ምን ለማግኘት እጣላለሁ፡፡ ፓልም ኦይልን ከኮሌስትሮል ነፃ ነው እያልን ልናጭበረብር አይገባም፡፡ የአትክልት ዘይት ነው የሚሉት፤ ስለዚህ ሰው አትክልት ነው ብሎ ይገዛል፤ ነገር ግን ከሃምሳና ስልሳ በመቶ በላይ ቅባት ያለው ነው
፡፡ ስለዚህ ለጤና አደገኛ ነው፤ በአንዳንድ አገሮች እንደውም እንደ መርዝ ነው የሚቆጠረው፡፡ ስለዚህ ይህንን  እያጭበረበሩ መሸጥ ስለማይቻል እነሱን እንታገላለን፡፡ አረቄ እዚህ አገር ይሸጣል፤ መሞት ከፈለግህ ጠጣ ነው፡፡ የፓልም ዘይትም እንደዚሁ ነው፤ አውቀህ ምርጫህን መውሰድ ነው፡፡

አዲስ አድማስ፡ ማስታወቂያ ቢመጣስ አትሠራም?

ሳምሶን ማሞ፡ ማስታወቂያ እኔን አይመለከተኝም፡፡ እዛ ላይ የሚሠራው በሙሉ የሳምሶን ነገር አይደለም፡፡ የአስተዋዋቂው ድርጅት ነው፡፡ ማስታወቂያ ሌላ ነው፤ ህዝቡ ማወቅ ያለበትን ደግሞ  እናገራለሁ፡፡ እዛ  አስተዋውቃለሁ… እንጂ ምስክር አልሆንም፡፡

አዲስ አድማስ፡ ማስታወቂያውን መስራት ምስክርነት መሆን አይደለም?

ሳምሶን ማሞ፡ ማስታወቂያው የእኔ አይደለም፤ የሰዎቹ ነው፡፡ እኔ ዶክተር አይደለሁ፤ በማንኛውም ጉዳይ ላይ እነሱ የሚሠጡን ነገር አለ፡፡ እያንዳንዱን ነገር እኔ ማጣራት ካለብኝ ኤክስፐርት መሆን አለብኝ ማለት ነው፤ ግን  የሚመለከተው የመንግስት ክፍል የራሱን ማጣራት ያድርግ፡፡ እኔ ምን አውቃለሁ — የሰጡኝን እሠራለሁ፡፡

አዲስ አድማስ፡ የሳምሶን አድቨርታይዚንግ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ፣ የዜድ ፕሬስ ደግሞ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ንግድ ፍቃዳቸው አልታደሰም—-

ሳምሶን ማሞ፡ ሳምሶን አድቨርታይዚንግ በጣም ብዙ ግብር ነበረብን፤ ያንን እየከፈልን ስለነበር ነው፡፡ የዜድ ፕሬስ ሁለት መቶ ሺህ ብር ያልተከፈለ ነበረ —  አሁን እሱ አልቆአል፤ ከነጭራሹ ሊያስጠይቅ አይችልም፡፡ ደግሞ ከ2001 ሳይሆን ከ2002 ጀምሮ ነው፤ የአንድ አመት እድሳት ነበር የቀረው፡፡ የአንድ አመት ፍቃድ አለማሳደስ ግን 15 አመት አያሳስርም፡፡ የሳምሶን አድቨርታይዚንግ  አራት አመት ነው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ 1.7 ሚሊዮን ብር እዳ አለበት፤ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር ገደማ ከፍለናል፡፡ እኛ ፈቃድ ባለማደሳችን መንግስት የተጐዳውን ነገር ባስብ ምንም የተጐዳው ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ድርጅቱ ኃ/የተ/የግ/ማ ነው፤ ለእያንዳንዱ የሚከፈል … ደረሰኝ አለ፡፡  የሠራተኛ ደሞዝ ግብር፣ የጡረታ፣ ቫት  እነዚህ ሁሉ የጐዱኝ እኔን ነው እንጂ ንግድ ሚኒስቴር ያጣው  ምንም ነገር የለም፡፡ በሶስት መቶ ብር ሄዶ ፍቃድ ማውጣት ብቻ ነው፤ እነሱ ምንም አያገባቸውም፡፡ ፍቃድ አለማውጣት ትክክል ነው ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን እጅግ በጣም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶበት ይሄንን ድርጅት ለማጥፋት ተብሎ እየተሰራ ነው፡፡ አሁንም ድረስ እየተከታተሉን ነው ያሉት፡፡ ቂርቆስ ክ/ከተማ ንግድ ቢሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እየታገሉ ነው ያሉት፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች ስራ ማቆማቸውን ተናግረናል፡፡ ሆኖም ቢሮ ውስጥ ሊሠሩ ይችላሉ ብለው አሁንም ይመጣሉ – በየቀኑ፡፡ ስለዚህ ከጀርባ ግፊት እያደረገ ያለ ሀይል አለ፤ ያንን ሀይል ለማወቅ ጥረት እያደረግን ነው፤ ያንን ካላወቅን አንሠራም፡፡

አዲስ አድማስ፡ ካሽ ሬጅስተርም የላችሁም ተብሏል?

ሳምሶን ማሞ፡ በዚሁ ምክንያት ነው — የግብር እዳ ከፍላችሁ ሳትጨርሱ ካሽ ሬጅስተር አይሰጣችሁም ብለውን ነው፡፡

አዲስ አድማስ፡ በወዳጆቻችን ጥረት እንጂ አስረው ያሳድሩን ነበር ብለሀል፡፡ ያስፈቷችሁ እነማን ናቸው?

ሳምሶን ማሞ፡ ወዳጆቻችን አስፈቱን አላልኩም፡፡ ወዳጆቻችን ለሚመለከተው የመንግስት ባለስልጣን አሳውቀው አስፈቱን ነው ያልኩት፡፡ ለሁሉም አለቃ አለው፤ ህገወጥ ውሳኔ ነበር፡፡ ያንን እንዲያስተካክሉ እዛ የነበሩ ጓደኞቻችን ለሚመለከታቸው ሃላፊዎች አሳውቀው ነው የተፈታነው፡፡

አዲስ አድማስ፡ የተለቀቃችሁት ከመሸ በኋላ ነው…

ሳምሶን ማሞ፡ አንድ ሰው ስቅላትም ተፈርዶበት ቢሆን እስኪፈፀም ድረስ እርምጃው ህገወጥ ከሆነ እኮ ገመዱ አንገቱ ውስጥ እስኪገባ ድረስ መብቱ የተጠበቀ ነው፤ በስህተት ተፈርዶበት መሳሳታቸውን ካወቁ ተሳስተናል ብለው ማውረድ አለባቸው እንጂ አንዴ መስቀል ጀምረናል ብሎ ክርክር አያስፈልግም፤ ገመዱን ማውለቅ አለባቸው፡፡

ፖሊስ ጣቢያው ግን አንድ ጊዜ ጀምረናልና መስቀል አለብን ብለው ተረባርበውብናል፡፡ ለዜጐቹ የሚቆረቆር የፖሊስ አካል አይደለም የተንቀሳቀሰው፡፡ እኔ እጅግ በጣም ነው የገረመኝ፤ ማንም ሰው ላይ እንደዚህ ተደርጐ አይታወቅም፤ ይሄንን ያደረጉትን አካላት  አሳውቀን እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

አዲስ አድማስ፡ እርምጃ ከተወሰደና ጉዳዩን ካሳወቅህ ድርጅትህን መዝጋት ለምን አስፈለገ?

ሳምሶን ማሞ፡ እኔ ነገ 15 አመት ልታሰር ፍ/ቤት የምቀርብ ሰውዬ ስለድርጅቴ ህልውና ማሰብ እኮ የለብኝም፡፡ ድርጅቴ በእሳትም ቢቃጠል ጉዳዬ አይደለም፡፡ አሁን የእኔንና የባለቤቴን ህይወት የማቆየት ስራ ላይ ነኝ ያለሁት፤ በስጋት ላይ ነኝ፡፡ 15 አመት ልታሠር የታሰብኩ ሰውዬ፣ ዛሬ ተረጋግቼ ጋዜጣ ልሠራ አልችልም፤ ከእነዚህ ሰዎች ጋር እታገላለሁ፤ ከርቸሌ እስገባ ድረስ፡፡

አዲስ አድማስ፡ ከዚህ ቀደም የደረሰህ ማስፈራሪያ ወይም ማስጠንቀቂያ ነበር?

ሳምሶን ማሞ፡ በሌላ ጉዳይ ሊሆን ይችላል ግን በንግድ ፍቃድ ልከሰስ አይገባም፡፡ የራሴን መብት ካስከበርኩ በኋላ ደግሞ ሁለት ወጣቶች አሉ፡፡ የሦስት ሺህ ብር ቦታ ተከራይተው
የመካኒክ ስራ የሚሠሩ፡፡ እነሱ በአስራ አምስት አመት እስራት ነው የተቀጡት፡፡ በአሁኑ ሰአት ገንዘብ የሚከፍልላቸው… ዋስትና አጥተው ታስረዋል፡፡ እነሱን ፈልገዋቸው ነው ወይስ ከእኔ ጋር ለመቀላቀል ነው? አላውቅም፡፡ እኔ ግን በምከፍለው መስዋዕትነት በሌላው ህዝብ ላይ እንደዚህ አይነት ወንጀል እንዳይፈፀም እከላከላለሁ፡፡ ሌላውን ሰው አድናለሁ፤ እኔ መስዋዕትነቱን እከፍላለሁ፡፡ በዜጐች ላይ ህገወጥ ነገር እየሠሩ መኖር አይቻልም፡፡ መንግስት ጉዳዩን እንደሚያጣራ አምናለሁ፡፡ እኛ ንግድ ፍቃዳችንን አለማሳደሳችን ጥፋት ነው፡፡ እኛም እንደማንኛውም ዜጋ ህግ ማክበር አለን፡፡

በተረፈ በእንደዚህ አይነት መከራና ችግር… ዕድሜዬን ሁሉ ሰርቼ ያላፈራሁትን የሠጡኝን ወዳጆቼን ነው ያፈራሁት፡፡ ከእኔ ጋር ለታሠሩት 24 ተከሳሾች፣ እኔን ላከበሩኝና ላስተናገዱኝ — በተለያዩ ወንጀሎች ለተከሰሱት ሁሉ ልዩ ክብር አለኝ፡፡

*******************

Source: Addis Admas newspaper – Aug. 11, 2012.

Check the Human Rights archive for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories