ኢትዮጵያ ከንፋስ ኃይል አንድ ሚሊዮን ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አላት [Amharic]

ኢትዮጵያ ከንፋስ ኃይል ብቻ አንድ ሚሊዮን ሜጋ ዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት በጥናት መረጋገጡን የውሃና ኢነርጂ ሚነስትሩ አስታወቁ። የአገሪቱን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃና የመስኖ ልማት ተጠቃሚ በማደረግ ረገድ ባለፉት 21 ዓመታት አመርቂ ወጤቶች መገኘታቸውንም ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ባለፉት 21 ዓመታት በመጠጥ በውሃና ኢነርጂ ልማት የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከንፋስ ኃይል 10 ሺ ሜጋ ዋት ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም እንዳላት ይታወቅ እንደነበረ አስታውሰው፤ በቅርቡ በተደረገው ጥናት ሀገሪቱ ከንፋስ ኃይል አንድ ሚሊዮን ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደምትችል በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ከንፋስ ኃይል ማመንጨት የምትችለው የኤሌክትሪክ ኃይል ምን ያህል እንደሆነ ለማረጋገጥ ከቻይና መንግሥት በተገኘ ድጋፍ ጥናት መካሄዱን ገልጸው፣ ጥናቱን አንድ የቻይና ኩባንያ ማድረጉንም አብራርተዋል።በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንድ ሚሊዮን ሜጋዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት በጥናት መታወቁን ጠቁመው፤ ይህንንም የሀገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ ደረጃ በደረጃ በማልማት ሀገሪቱንና የጐረቤት አገሮችን ተጠቃሚ የማድረጉ ጥረት እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ፤ መንግሥት ከንፋስ የሚገኘውን የኤሌክትሪክኃይል ከሌሎች ኃይል ምንጮች ከሚፈጠረው ጋር በመቀላቀል የመጠቀም ዕቅድ አለው። ይህም በግድቦች ውስጥ የውሃ መጠን በቀነሰ ጊዜ እንደ አማራጭ ሥራ ላይ ሊውል ይችላል።

« ከንፋስ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማልማትከወጪ አኳያ ለሀገሪቱ አይከብድም ወይ? በማለት ጋዜጠኞች ላቀረቡት ጥያቄ አቶ አለማየሁ በሰጡት ምላሽ፤በዋጋው ረገድ ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ይልቅ ከንፋስ ኤሌክትሪክ ኃይልን ማመንጨት ይወደዳል። ሆኖም ከታዳሽነቱና ከግንባታው ጊዜ አኳያ ሲታይ ዋጋው የተጋነነ አይደለም። ይህ ማለት ግን « በሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ የንፋስ ኃይሉን በማልማት በንፋስ ኃይል ላይ ብቻ ጥገኛ ትሆናለች ማለት አይደለም» ብለዋል።
እንደሚኒስትሩ አገላለፅ « የንፋስ ኃይሉ ከአንድ አካባቢና ቦታ የሚገኝ አይደለም። በንፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ካላቸው አካባቢዎች መካከል በአዳማ 300 ሜጋ ዋት፤ አሸጐዳ 500 ሜጋ ዋት በሽንሌ 600ሜጋ ዋት ማመንጨት ይቻላል።

በአሁኑ ገዜ በአሽጐዳ 30 ሜጋ ዋት በአዳማ 51 ሜጋ ዋት ከንፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል እየመነጨ ነው። የአሽጐዳን 120 ሜጋ ዋት፤ የአዳማን ደግሞ 200 ለማድረስ እየተሠራ ነው።

በሌላ በኩል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት 21 ዓመታት መጠነ ሰፊ ሥራዎች እንደተሠሩ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ውስጥ መቶ በመቶ ለማድረስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች በማሳካት ረገድ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከተቀመጠው ጊዜና ግብ በላይ ማከናወን ተችሏል የውሃ ሽፋኑ ማደግ ጤናማና አምራች ዜጋ በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

ኢትዮጵያ በመስኖ ሊለማ የሚችል አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዳላት ገልጸው፤ ይህን መሬት በመስኖ ለማልማት ባለፉት 21 ዓመታት በርካታ ግዙፍ ግንባታዎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል። እነዚህ የመስኖ ልማት ሥራዎችም የአርብቶ አደሩንና የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።

ምንጭ:- አዲስ ዘመን – ሜይ 26-2012/ግንቦት 18-2004

Source: Addis Zemen – May 26, 2012
******************

Check the Energy archive archive for related posts.

Daniel Berhane

more recommended stories