በቀጣዮቹ 3 ዓመታት 48 የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ስራ ይጀምራሉ [Amharic]

በቀጣዮቹ ሶሰት ዓመታት ውስጥ 48 የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ስራ እንደሚጀምሩ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ከእነዚህ ፋብሪካዎች ውሰጥ በአሁኑ ወቅት ሃያዎቹ በግንባታ ላይ ይገኛሉ።  ኢንስቲትዩቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳለው ፋብሪካዎቹ ወደ ስራ ሲገቡም በአጠቃላይ 40 ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሃገራችን ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ምቹ እንደሆነች ይነገራል። ዘርፉ የሚፈልገውን ከፍተኛ መጠን ያለው የጥጥ ምርት ለማምረት የሚያስችል ሰፊ መሬትም በሃገሪቱ አለ። ነገር ግን እስከ አሁን በዘርፉ የተፈለገውን ያህል ጥቅም አግኝታለች ለማለት አያስደፍርም። ለዚህ ማሳያው ደግሞ አብዛኛው የለበስናቸው ልብሶች ስሪታቸው ከውጭ የገቡ መሆናቸው ነው። ዘርፉ ካለው ሰፊ የገበያ ተፈላጊነት አንፃር አሁን ላይ በውጭና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ባለሃብቶች በሰፊው እየተሰማሩበት ይገኛል።

እስከ አሁን ድረስ 91 የሚደርሱ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ግንባታቸውን አጠናቀው በስራ ላይ እንደሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይናገራል። ከእነዚህ በተጨማሪ ነው እንግዲህ በመጪዎቹ ሶስት አመታት ብቻ 48 የሚሆኑ አዳዲስና የማስፋፊያ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሚገነቡት።

በኢንስቲትዩቱ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍቃዱ ከእነዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከፊሎቹ የፋብሪካ ግንባታ እያከናወኑ እንደሆነ ይናገራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 4ቱ ስራ ጀምረዋል።

ዘርፉ እስከ 2002 ድረስ በነበሩት ስድስት ተከታታይ አመታት እድገቱ በአማካኝ በ51 በመቶ የተወሰነ ነበር። በ2003 ግን ይህ አሃዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተመንድጎ በ168 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል። ከውጭ ንግድ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ቢሆን በተመሳሳይ መልኩ አድጓል።

በ1997 በጀት ዓመት ሃገሪቱ ከውጭ ንግድ ከዘርፉ ታገኝ የነበረው ገቢ ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የዘለለ አልነበረም። አሁን በ2004 በጀት ዓመት ግን ባለፉት አስር ወራት ብቻ የተገኘው ገቢ 70 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል።

አቶ ፍቃዱ ማናቸውም የበለፀጉት ሃገራት ወደ ኢንዱስትሪ ሲሸጋገሩ መነሻቸው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ እንደነበር ታሪክ አጣቅሰው ይናገራሉ። ሃገራችንም ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ከዚህ አኳያ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት አሁን በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

በአጠቃላይ በ2007 ሃገሪቱ ከዘርፉ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ከሃገር ውስጥና ከውጭ ንግድ ገቢ ለማግኘት ታስቦ ነው እንቅስቃሴ እየተካሄደበት ያለው።

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሰፊ የሰው ሃይል የሚፈልግ ዘርፍ ነው የሚሉት አቶ ፍቃዱ ባለፉት አመታት ብቻ ከ40 ሺ ለማያንሱ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ይናገራሉ። አሁንም አዳዲሶቹ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምሩ ደግሞ ከ40 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

ነገር ግን ዘርፉ የሚታይ በጎ ነገሮች እንዳሉት ሁሉ ማነቆዎችም አላጡትም። በተለይ ለፋብሪካ የሚውሉ የግብዓት አቅርቦት እንደ ጥጥ ያሉ ምርቶች በስፋትና በጥራት ያለመኖር እንደ ችግር ተጠቃሽ ናቸው። የተማረ የሰው ሃይልም ቢሆን የተፈለገውን ያህል በበቂ ሁኔታ የለም።

የኢንዱሰትሪ ሚኒስቴር እንደሚለው ደግሞ አሁን ያለው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ በተለይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች ለማሳካት ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ጠቋሚ ምልክት እየታየበት ስለመሆኑ ነው የሚናገረው። ሆኖም አሁን ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ ከሌሎች ባለድርሻ አካላቶች ጋር በመሆን በቅንጅት አጠናክሮ እንደሚሰራ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ መላኩ ታየ አስረድተዋል።

ሌሎች የግብዓት አቅርቦቶችና እንደ ክርና ማግ ያሉ አክሰሰሪዎች እዚሁ በሃገር ወስጥ የሚመረቱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገም ነው። የተማረ የሰው ሃይሉም ቢሆን አሁን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኩል በስፋት ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱሰትሪ ልማት ኢንስቲትዩትም ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። የገበያ ትስስርና ፋብሪካዎች ከውጭው አለም ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን አደረጃጀት ለመፍጠርም ከፋብሪካዎች ጋር በጥምረት እየተሰራበት እንደሆነ አቶ መላኩ ተናግረዋል።

**************

Source: Fana Broadcasting – June 5, 2012.

Check the dropdown menu at the top for related posts.

more recommended stories