አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ለ2ዐ ዓመታት ተፈትኖ የወደቀ አካል በቃህ ሊባል ይገባዋል!
መውጫው መንገድ ፀንቶ መታገል ብቻ ነው!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ለዘመናት በጭቆናና በችጋር ፍዳውን ሲይይ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትሕና የዕድገት ፀሐይ ቀን በኢትዮጵያ ምድር እንድትወጣ ተስፋ ሰንቆ ነበር፡፡ በርካታ የሚያማልሉ ተስፋዎች ደግሞ እውን ሆነው ለማየት እንደተለመደው በጉጉት መጠበቁን ቀጠለ፡፡ የኢህአዴግ የአገዛዝ ዓመታት እየተደራረቡ ሲያልፉ፣ የዚያኑ ያህል የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭቆናና ድህነት እጥፍ ድርብ እየሆነ መጣ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓለም አንቀሮ የተፋው አቢዮታዊ ዴሞክራሲና እርሱን መሠረት አድርገው የሚነደፉ ደካማ ፖሊሲዎች መሞከሪያ ጣቢያ ሆነ፡፡ ከ2ዐ የመከራ ዓመታት በኋላ ማሳረጊያው የአንድ ፓርቲና የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነትን ማንገስና አፈናና ድህነትን ማባባስ ሆነ፡፡
ብዙ የተተረከለት የልማት መስመርና የኢኮኖሚ መስፈንጠር ውጤቱ ምን እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በርሀብና በጭንቅ ውስጥ ወድቆ በተግባር እየመሰከረ ነው፡፡ ኢህአዴግ መሬት ባልረገጠ፣ በተዝረከረከና የኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅናና አመኔታ በነሳቸው ፖሊሲዎች ኢትዮጵያን ለ2ዐ ዓመት ሲያተራምስ መቆየቱ ሳይበቃው አሁን ደግሞ ሕዝቡን ወደ ፍፁም የኢኮኖሚያዊ ድቀትና የአፈና አዘቅት ውስጥ ከቶታል፡፡
ለዓለፉት ዓምስት ወራት እየተካሄደ ያለው ‹መንግሥታዊ› ቧልት የዚሁ ጉዳይ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ በቁጥጥር ፍቅር ልክፍት የወደቁት አምባገነን መሪዎቻችን ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን፣ ማህበራዊውንና የኪነ-ጥበብ ዘርፉኑም ሳይቀር በአንድ በውል በሚቆጣጠሩት ቋት ውስጥ ለመክተት ከላይ ታች እየረገጡ ይገኛሉ፡፡ በዚሁ አቢዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የመቆጣጠር አባዜያቸው ሕዝብን፣በተለይ የንግዱን ማህበረሰብና ባለሞያዎችን ሳያማክሩ በሥራ ላይ ባዋሉት እውር ድንብር ውሣኔ ድሮም ቋፍ ላይ የነበረውን ‹የነፃ ገበያ› የባሰ ውዥንብር ውስጥ ጥለውታል፡፡ ሕዝቡ ባልተጠናው የዋጋ ገደብ ምክንያት የኑሮ ውድነት ባደቀቀው ቁስሉ ላይ ጨው ተነስንሶበት በህይወትና በሞት በሀከል ይገኛል፡፡ አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብም በኢህአዴግ የናጠጡ የንግድ ተቋማት ተገፍትሮ ከጨዋታ ውጭ እየሆነ ይገኛል፡፡ የቀረው የንግዱ ማህበረሰብም ቢሆን ኢህአዴግ በየጊዜው በሚፈጥረው ትርምስ ለራሱም ሆነ ለሀገር ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዳያደርግ ተገድቧል፡፡ ኢህአዴግ በሚከተለው ዝርክርክ የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲ በዓለማቀፍ ገበያ ከነዳጅና የሸቀጦች ዋጋን መጨመር ጋር ተያይዞ የብርን ዋጋ ወደ ገለባነት ደረጃ እየቀየረው ይገኛል፡፡ የዚህ ሁሉ የተተረማመሠ አሠራርና የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ውጤትን የሚሸከመው ከባድ የችጋር ጫና ያጎበጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ገዢዎቻችን ለሚያደርሱት የኢኮኖሚ ድቀት ይቅርና ለሚቀጥፉት ህይወትም እንኳን የሚጠየቁበት ሥርዓት አልተገኘም፡፡
በባከኑት 2ዐ አመታት ውስጥ የደረሰውና እየደረሰ ያለው የኢኮኖሚ ድቀት ገዢዎቻችን አገር የመምራት ብቃት ፈጽሞ እንደሌላቸው ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፡፡ አገር መምራት ባለመቻላቸው በሚፈፅሙት የመደነባበር ተግባር አገራችንን ያልተጠኑና ከሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄዱ ፖሊሲዎች መፈተሻ አድርገዋታል፡፡ የዚህ ሁሉ ገፈት ቀማሽ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ሁሉ አይበቃህም ተብሎ በሰሞነኛ የማማለያ ፕሮፓጋንዳቸው መድረሻ አሳጥተውታል፡፡ ሰሞነኛውም ፕሮፓጋንዳቸው በዋናነት አባይ ላይ ያተኮረ መሆኑን ሁሉም የሚረዳው እውነት ነው፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በፕሮግራሙ እንዲሁም በቅርቡ ባወጣው የስትራቴጂ ሰነዱ በግልጽ እንዳስቀመጠው አባይን አይደለም ሌሎቹም ወንዞቻችን ተገድበው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም መዋል እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ልዩነታችን እንደ ሶማሊያው ዘመቻ፣ እንደ ውሃ ማቆርና እንደ ዋጋ ተመኑ ሁሉ ሕዝብ ሳይመክርበት፣ የሚገባው ሁሉን አቀፍ ጥንቃቄ ሳይደረግበትና ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሙያዎች በወጉ ሳይመክሩበ የምንላችሁን ብቻ ተቀበሉ የሚል ዘመቻ መጀመሩን ነው፡፡ እንዲሁም ለግድቡ መስሪያ ሌሎች አዋጭ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቶች ባለመነደፋቸውና አሣታፊ ውይይት ባለመደረጉ በአጠቃላይ ሕዝቡ ይቅርና የጉዳዩ ባለቤቶች ነን ባዮቹ የኢህአዴግ መሪዎች እንኳን እለት እለት ውዥንብር ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው የኑሮ ውድነት ያደቀቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከየትም ብሎ ገንዘብ እንዲያመጣ ጫና እየተደረገበት ያለው፡፡ ገንዘብ ሰብሳቢውም በሙሰኛነቱ የሚታወቀው ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት መሆኑ ለሕዝቡ ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ ያም ሆኖ እንደ መንግሥት ፕሮፓጋንዳ ከሆነ ግድቡ ተሰርቶ ከአሁኑ ሥራ ላይ የዋለ ይመስላል፡፡ ግድቡ ለፍፃሜ ቢበቃስ እንደተባለው 525ዐ ሜጋ ዋት ያመነጫል ወይ? የሚገኘው የኃይል አቅርቦት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአምስት ዓመት በኋላ ከድህነት እንደሚያወጣው መናገሩ ሌላው ሕዝብን መደለያ ተውኔት ነው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ለዘመናት በድህነት አረንቋ የተዘፈቁ አገሮች አንድ ግድብ በመገንባት ከድህነት ሊወጡ አይችሉም፡፡ ይህን መሰሉ ውዥንብር ያስፈለገው የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየርና በመንግሥት ላይ ያለው ብሶት ገንፍሎ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት በፕሮፓጋንዳ ብዛት ለማምከን ነው፡፡
ከዚህም በላይ ሕዝቡ የሚያደርገው መዋጮ በነፃነትና በንፁህ ፍላጐት መሆኑ ቀርቶ ያለ እምነቱና ያለ ፍላጎቱ የወር ደመወዙን እንዲያዋጣ እየተገደደ ይገኛል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ በውል ላልተረዳው የኢህአዴግ ሰሞነኛ የማዘናጊያ ፕሮፓጋንዳ በእድር፣ በቀበሌና በመሥሪያ ቤት ጭምር ተጠፍንጎ እንደደርጉ የእናት ሀገር ጥሪ ያለፈቃዱ ሰልፍ እንዲወጣ እየተገደደ ነው፡፡ ሀገሪቷ የምትመራው በሰሞነኛ የቴሌቪዥንና የሬዲዬ ፕሮፓጎንዳ ነው፡፡
ከሃያ ዓመታት የአፈና አገዛዝ በኋላ ሥርዓቱ በሁሉም አቅጣጫ የመለወጥ ፍንጭ ፈጽሞ አይታይበትም፡፡ በዚህ ዓመት በተለያየ ወቅት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የአፈናና የወከባ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ሕዝቡ በሚገባ ያውቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው መረን የለቀቀ ተግባር ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡ በጋሀድ እንደሚስተዋለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢህአዴግን ደግፎ ካልሆነ በስተቀር የተለየ ሃሳብ ማራመድ እንደማይቻል ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ ያለው አንባገነናዊ አገዛዝ ተማሪዎች የተመደበችላቸውን ውሱን በጀት ሳይቀር መንጠቅ፣ ነጥቆም ጥያቄ ሲነሳ በጭካኔ ማፈን፣ተፈጥሮአዊ መብቱ አድርጎታል፡፡ ከግንቦት 22/2ዐዐ3 ዓም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው አፈና በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ታፍነው የተወሰዱ ተማሪዎች ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ትምህርት ገበታቸው በአስቸኳይ ይመለሱ፡፡ ተማሪዎቹ በተመደበላቸው ውሱን የምግብ በጀት ላይ ጥያቄ ማንሳትና ቅሬታም ማቅረብ እንደ ከፍተኛ ወንጀል ተቆጥሮ አሰቃቂ የሆነ ድብደባ፣ እንግልትና የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው መደረጉ ሥርዓቱ አሁንም የሕዝብን መብት ረግጦ ለመቀጠል እንደወሰነ ያሳያል፡፡ ከሁሉ የከፋው ነገር ለተማሪዎችና ለመምህራን እውቀት መገበያያ ብቻ ሊያገለግል ይገባ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል የሥርዓቱ ደጋፊዎች ፈቃዳቸውን ሁሉ የሚፈጽሙበትና ደም የማፍሰስ ሱሳቸውን የሚያረኩበት መድረክ መሆኑ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ ተማሪዎቹ እንኳንስ ባጀታቸውን በሚመለከት ይቅርና አጠቃላይ አገራዊ ጉዳዬችን በሚመለከት የተቃውሞ ሰልፍ ቢጠሩ ህገ-መንግሥታዊ መብታቸው ነው፡፡ በህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 3ዐ ንዑስ አንቀጽ 1 በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ኢህአዴግ ህገ-መንግሥቱን ካወጣ ከ16 ዓመታት በኋላም ላወጣው ገዥ-ሰነድ አልገዛም ማለቱን ደጋግሞ በተግባር አስመስክሯል፡፡
በተግባር ላለፉት ሃያ ዓመታት የታየው አሁንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ ሆኖ የወጣው ጉዳይ ኢህአዴግ አገርን ለመምራት ብቃትም ሆነ በጎ ፈቃድ እንደሌለው ነው፡፡ ሀገራችን ልትሸከም ከምትችለው በላይ የግርድፍ ፖሊሲዎች መሞከሪያ መሆኗ በቃ እንላለን፡፡ ሕዝቡ የተቃውሞ ሃሳቡን እንዳይገልጽ የሚደረግበት አፈና በአስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል፡፡ የግንቦት ሃያ የሃያ ዓመት ትሩፋቶች አፈና፣ርሃብና ሰቆቃ መሆን ባልተገባቸው ነበር፡፡ አገራችን ከምትገኝበት የውድቀት አፋፍ ልትወጣ የምትችለው በኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ብርቱና ሠላማዊ ትግል ነው፡፡ ለኢህአዴግ አገራችንን መተው ከነአካቴው ከአፋፉ ወደ ገደሉ እንዲጨምራት ሆን ብሎ መፍቀድ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ባለፈው ታሪካችን የምናውቀው አንድ ክፍለ አገር ወይም የተወሰነ አካባቢ በርሀብ ሲጠቃ ነበር፡፡ አሁን እድሜ ለሃያ አመታት የኢህአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አገዛዝ ችጋር በየእንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማጀት ቤቱን ሠርቷአል፡፡ ከዚህ ድህነትና የነፃነት እጦት መውጫው መንገድ ሕዝቡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ሰው ተናጋሪ ሆኖ መታገልና የኢህአዴግን አገዛዝ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከጫንቃው ሲያወርድ ብቻ ነው፡፡ አንድነት ሕዝቡ በፀና ሠላማዊ ትግል ከሚገኝበት ቅጥ ያጣ ድህነት እና ጭቆና ነፃ ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል አበክሮ ይደግፋል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሰኔ 2 ቀን 2ዐዐ3 ዓም
አዲስ አበባ
I don’t think EPRDF have failed in it’s twenty years truck record better to find any other option to say as EPRDF is doing excellent I don’t think this will help what so ever rather this will undermine the Andnets credit as they are denying a clear facts.
Long live EPRDF led Ethiopia and those Andnets need to think trice before saying a word because here in Ethiopia things are changing fast and every corner of the country is now being flooded with literate personnel and there is no much room to bias the najority as it was often practiced