ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለ ባቡር ኔትወርክ በዓድዋ ያደረጉት ንግግር[+audio]

እኔ እርግጠኛ ነኝ ….. ምናልባት በኛ እድሜ ላይደርስ የሚችል ነገር ካልሆነ በስተቀር ….. ኢትዮጲያ የእድገት ጉዞ ጀምራለች፤ ያ የእድገት ጉዞ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ባቡር ጊዜውን ጠብቆ እዚህ ዓደዋ ላይ እንደሚደርስ ጥያቄ የለውም፡፡ አሁን ጥያቄው ምን አቅም አለን እንዴት አድርገን እናደርሳለን ፍላጎት ብቻውን ውጤት ስለማይሆን፡፡ ፍላጎት ጥሩ ነው፤ ራዕይ ማስቀመጥ ጥሩ ነው፡፡ ራዕይ አለን ነገር ግን ደግሞ አቅምም ነው፡፡

ባቡር እንደምታውቁት በእያንዳንዷ ኪሎሜትር በፈረንጆቹ ሜዳ ከሆነ 4 ሚልየን ዶላር በኪሎሜትር ተራራ ከሆነ እንደዚህ ወደ ሰሜን አካባቢ – በእርግጥ ደቡብ ብዙ ተራራ አለ ሰሜንም ምስራቅም አለ ግን – ተራራማ በሚሆንበት ግዜ ተራሮች ስለሚቆፈሩ በዚያ ውስጥ ስለሚታለፍ – ያው ባቡር እንደምታውቁት እንደ መኪና ዳገት አይወጣም ቀጥ ብሎ ሰንጥቆ ነው የሚሄደው ስለዚህ በጥሰን ነው መሄድ የምንችለው – ያ ደግሞ በኪሎሜትር ከ7-8 ሚልየን ዶላር ነው፡፡ ያ ማለት 7 ግዜ 20 ከ140-160 ሚልየን ብር ነው በኪሎሜትር፡፡ አስቡ እዚች ከተማ ውስጥ አንዷ ኪሎሜትር ምን ማለት እንደሆነች ታውቃላችሁ፡፡ እዛች ላይ ከ140-160 ሚልየን የሚሆን ብር ማውጣት አለብን ማለት ነው፡፡ ይሀ ለመንገዱ ብቻ ነው በላዩ ላይ የሚሽከረከረው ደግሞ ሌላ ወጪ ነው፡፡

ስለዚህ ይሄ ነገር ያው አቅማችን እየጎለበተ ሲሄድ…አቅም ማለት የእናንት አቅም ነው፤ የመንግስት አቅም ማለት የህዝብ አቅም ነው፡፡ የህዝቡ አቅም ደረጃ በደረጃ እያደገ ሲመጣ…እኛም እኔ አሁን ዓደዋን የዛሬ ሶስት አራት አመት በፊት ስድስት አመት በፊት መጥተን ነበር፡፡ አሁን ያለችው ዓደዋ እና የዛሬ ስድስት አመት የነበረችው ዓደዋ ሰማይና ምድር ነው፡፡ ስለዚህ እናንተ አደጋችሁ ማለት ባቡሩ ሊመጣ እየተቃረበ ነው ማለት ነው፡፡ከህዝብ እድገት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው ማለት ነው የመንግስት አቅም የህዝብ አቅም ስለሆነ፡፡

ከዚህ አኳያ ሳየው መምጣቱ አይቀርም ግን ደረጃ በደረጃ…መጀመሪያ ዋናውን የኢትዮጲያ ከተማ አዲስ አበባ ከወደብ ጋር ማገናኘት… ምክንያቱም ሁላችንም ጉሮሯችን የሚታነቀው ወደቡ ሲታነቅ ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ወደቡን ከፍተን ጉሮሯችን ክፍት ማድረግ በሂደት ደግሞ ፖርት ሱዳን እንዳላችሁት ወደብ መጠቀም ጀምረናል አሁን በትንሽ በትንሹ እያሳደግነው እንሄዳለን፡፡ የዛን ግዜ ወደ ሰሜኑ ሰሜን ምዕራብ የኢትዮጲያ ክፍል እንደዚሁ እየዘረጋን መሄዳችን አይቀርም ከሱዳን ጋርም ተስማምተን፤ አብዛኛውበሱዳን መስመር ላይ ነው የሚሰራው እንግዲህ የሱዳኖችንም አቅም ይጠይቃል ማለት ነው፤ የእኛ አቅም ብቻ የትም አያደርሰንም ሱዳኖችም በዛው መጠን አቅማቸው እያደገ ሲሄድ በጋራ ሆነን የምንሰራው ስራ ይሆናል፡፡

መምጣቱ አይቀርም ግን እኔ ደግሞ ያልሆነ ቃል ልገባላችሁ አልችልም አይገባኝምም፡፡ አቅም በጣም ይፈታተናል ባቡር፡፡ በጣም አቅም ሰለሚፈታተን የተወሰነ ግዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እኛም እየለማን በትእግስትም እየጠበቅን እየሰራን ስንሄድ ባቡር ሊመጣ ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምናልባት ደግሞ ሰላም ከፈጠርን የሚቀርብ ነገር እንዳለ ታውቃላችሁ፡፡ እና የዛን ግዜ ሊፈጥን ይችላል፡፡ ለማንኛውም ይሄ ነገር ሊመጣ የሚችል እንደሆነ ሰንቀን መቸም ራዕይ ትልቅ ነገር ነው ራዕይ ሰንቀን መታገል ያለብን ይሆናል ማለት ነው፡፡

**************

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories