በኘሮፖጋንዳ ወፍጮ ሐቅ አይጨፈለቅም

(ሙርቲ ጉቶ – ከፊንፊኔ)

1/ እንደ መነሻ

በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አመራር ውስጥ የሚገኘው ተስፋፊ ቡድን ጊዜ ያለፈበትን ቅዠት ለማሳካት አጠናክሮ የተያያዘውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመደገፍ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሰፊ የአሉባልታ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ተስፋፊው ቡድን ኘሮፖጋንዳሲቶችን በማሰማራት የጥላቻ መርዝ እየዘራ በኦሮሞ ሕዝብ፣ በክልሉ መንግስትና አመራር ላይ የጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ ዋጋ የሌለው የፖለቲካ ብልግና በመሆኑ የሚያስጨንቅ ባይሆንም የተጀመረውን ሀሰተኛ ኘሮፖጋንዳ  በሚገባቸው ቋንቋ መመከት ተገቢ ነው ብዬ በማመን ይህንን መጣጥፍ ለማቅረብ ተገድጃለሁ፡፡

የጽሁፌ መነሻ በኦሮሞ ሲተረት የሚሄድ ውሃ፣ የተኛ ውሃን ይቀሰቅሳል; (Bishaan deemu bishaan ciisu kaasa) እንደሚባለው የተስፋፊው ቡድን ኘሮፖጋንዳሲቶች በኦሮሞ ላይ የጀመሩትን የማጥላላት ዘመቻ ፍሬ ቢስነት ገላልጦ ለማሳየት ስለገፋፉኝ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘመናት ትግል አገራችን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከተሸጋገረች ወዲህ የሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጐት ማሟላትና ብዝሀነታችንን ማስተናገድ የሚችል ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዘርጋት በመቻሉ በክልልነት ከተመሠረቱት የአገራችን ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልልና የኢትዮጵያ የሶማሌ ብሔራዊ ክልል ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ክልሎች ረጅም ድንበርን የሚጋሩ ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቦቻቸው ለዘመናት አብሮ በመኖር በባሕል፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ኑሮ የተሣሠሩ ተመሳሳይ እምነት የሚከተሉ ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውም ይታወቃል፡፡

የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ማለትም የኦሮሞና የሶማሌ ብሔሮች አባላት ባለፈው ሥርዓት ተመሳሳይ ጭቆና ውስጥ የኖሩና በተመሳሳይ ኋላቀር የአርብቶ አደርነት ሕይወት ሲመሩ የቆዩ ከመሆናቸውም በላይ አልፎ አልፎ በግጦሽ፣ በውሃና በመሳሰሉ ጐዳዮች ሲጋጩም ችግራቸውን በውይይት ተነጋግሮ በባሕላዊ ህግ በጉማ ያጠፋው ይካስ እየተባባሉ ይቅርታ እየተደራረጉ በጋራ የመኖር መልካም  እሴት ያዳበሩ ሕዝቦችም ናቸው፡፡

መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ለአስከፊ ጭቆና የዳረገው የደርግ አገዛዝ  ከተገረሰሰ ወዲህ እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች ለአስተዳደር እንዲመች የተዘረጋ ድንበር አበጅተው በአንድ አገር ጥላ ሥር እየኖሩ፣ እየተደጋገፉ ሕይወታቸውን ለማሻሻልና አገራቸውን ከድህነት ለማውጣት ድርሻቸውን እያበረከቱ በዕድገት ጐዳና ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው በመጓዝ የጋራ ድሎችን ማጣጣም የጀመሩ ሕዝቦች መሆናቸውም ግልጽ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በጥባጭ እያለ ማን ንፁህ ይጠጣል? እንደሚባለው በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አመራር ውስጥ የሚገኘው ተስፋፊ ቡድን የሕዝብ የልማት ፍላጐት ከማሳካት ይልቅ  ምሥራቃዊና ደቡባዊ የኦሮሚያ ክልል የድንበር አካባቢዎችን በኃይል የመጠቅለል አጀንዳን የሙጥኝ በማለቱ የሁለቱ ተጐራባች ወንድማማች ሕዝቦች ሰላም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

ተስፋፊው ቡድን ልዩ ኃይል በሰላማዊ ሕዝብ ላይ በማዝመቱ የንፁሃን ሕይወት በየቀኑ የሚቀጠፍበት ሁኔታ በስፋት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ የተስፋፊ ቡድኑ ልዩ ኃይልና መላ ታጣቂ ሚሊሻ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ዘምቶ ግድያ  ከመፈፀም ባሻገር ንብረት በማውደምና በመዝረፍ፣ አስገድዶ በመድፈር፣ የኦሮሞ አካባቢን በኃይል ይዞ ሕዝብን በማፈናቀል ህገ ወጥ ሠፈራ በማካሄድ፣ በማሰቃየት ላይ በመዝመቱ እጅግ አሳሳቢ ሰብዓዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ ስቃይ እየደረሰበት ያለው የኦሮሞ ሕዝብ እሮሮና የድረሱልኝ አቤቱታ ሰሚ አጥቶ መፍትሄ ባለማግኘቱ፣ ከ4ኛው የፖርላማ ዘመን ጀምሮ በፖርላማ መድረክ ጭምር ለአገሪቱ መሪና ለፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የቀረቡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በማጣታቸው እነሆ ዛሬ ችግሩ ሰፍቶ በንፁሃን ዜጐች ላይ ከፍተኛ በደል በመድረስ ላይ ይገኛል፡፡

ይሄ ሁኔታ ይበልጥ እየሰፋ በመምጣቱ የኦሮሚያ ጨፌ በቅርቡ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ይህንን ጉዳይ አደባባይ ላይ አውጥተው የሕዝቡን ምሬት በመግለጻቸው፣ የክልሉ መንግስት አመራርም ችግሩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ በሰላም ለመፍታት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኝነት በማሳየቱና ኦሕዴድ ባካሄዳቸው የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች ላይ ከተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች አንዱም ይኸም በተስፋፊ ቡድኑ የድንበር ማስፋፋት ፍላጐት ሳቢያ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የጭካኔ ተግባር ማስቆም መሆኑን ከግምት በማስገባት ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑ እየታወቀ የሰላም ጥሪን አሻፈረኝ ያለው ተስፋፊ ቡድን በጦር መሣሪያ ብቻ ሣይሆን በኘሮፓጋንዳ ዘርፍም አዲስ ጥቃት ከፍቶ የኢትዮጵያ ህግና የወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማይፈቅደው ሁኔታ ሕዝቡን የሚያባላ የኘሮፖጋንዳ ወፍጮ ተክሎ በስድብና በስም ማጥፋት ዘመቻ ላይ አተኩሮ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡

ይህ አካሄድ በቶሎ ካልተጋለጠ የሚያደርሰው አደጋ ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ የእኔ ጽሁፍ ማጠንጠኛም ተስፋፊው ቡድን የድንበር ማስፋፋት ዓላማውን ለማሳካት ይረዳኛል ብሎ በኦሮሞ ሕዝብ፣በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በክልሉ ጨፌ፣ እንዲሁም የክልሉ ሕዝብ መሪ ድርጅት በሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ላይ የጀመረውን ፍሬ አልባ የኘሮፖጋንዳ ገለባ አበጥሮ በማሳየት አንባቢያን ዕውነቱን እንዲገነዘቡ ማስቻል ነው፡፡

2/የተስፋፊው ቡድን  የሶሻል ሚዲያ  ኘሮፖጋንዳ ይዘት በጥቅሉ ሲታይ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሶሻል ሚዲያ አውታሮች በተለያዩ የብዕር ስሞች  እየወጡ ያሉና በይዘታቸው ብቻ ሣይሆን በቋንቋ አጠቃቀም ጭምር የአንድ ግለሰብ ጽሁፎች የሚመስሉ የአሉባልታ ድሪቶ መጣጥፎች የተስፋፊውን ቡድን ፍላጐት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ተስፋፊው ቡድን በድንበር አካባቢ የሚገኙ የኦሮሞ አካባቢዎችን ወይም ዞኖችን ጠቅልሎ ለመያዝ ቆርጦ እንደተነሳና ይህንንም ለማሳካት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ሆኖ ሕዝቡን ከጥፋት ለመከላከልና ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት በቁርጥ ጥረት እየተንቀሳቀሰ ያለውን የኦሮሚያ ክልል አመራር በተለያዩ ቅጽል ስሞች እየፈረጀ በመወንጀል አመራሩ  የተስፋፊው ቡድኑን ሴራና ደባ ከማጋለጥ እንዲያፈገፍግና እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ለማድረግ የሚችል መስሎት በከንቶ እየተፍጨረጨረ መሆኑ ከአሉባልታ መጣጥፎቹ በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡

በተለይም የተስፋፊው ቡድን ሰሞኑን የከፈተው ሀሰተኛ ኘሮፖጋንዳ ዘመቻ የኦሮሚያ ክልል ጨፌን፣ ኘሬዜዳንቱንና አመራሩን እንደዚሁም የክልሉ መሪ ድርጅት የሆነውን ኦሕዴድ በጠባብነት፣ በኦነግነትና በመሳሰሉ የተለመዱ ማስፈራሪያዎች በመወንጀልና የኦሮሞ ሕዝብ፣ የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ኦሕዴድ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት አደጋዎች እንደሆኑ አድርጐ እስከ ማቅረብ የደረሰ እጅግ ተራና የዘቀጠ፣ አሉባልታ በማናፈስ እያደረጉ ያሉት ሙከራ የኦሮሚያ አመራር በፌዴራል ደረጃና በሌሎች ክልሎች ዘንድ በጥርጣሬና በስጋት እንዲታይ ለማድረግ ያስችለናል ብለው የሚያስቡ አርቀው ማየት የማይችሉ የፖለቲካ ደናቁርት መሆናቸውን በይፋ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን; እንደሚባለው ተስፋፊ ቡድኑ የኦሮሚያ አካባቢዎችን ቆርሶ መውሰድን የሥራዎቹ ሁሉ አውራ በማድረግ በጦር መሣሪያ የተያያዘውን መልሶ ራሱን የሚያቃጥል አደገኛ እሣት በመለኮስ በንፁሃን ደምና ሕይወት እኩይ አላማን ለማሳካት የተያያዘውን የእብደት ጉዞ በሀሰተኛ ኘሮፖጋንዳ ለመደገፍ እየተካሄደ ያለው የዘመቻ ኘሮፖጋንዳ በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ እጅግ የወደቀ፣ ተራና የስም ማጥፋት ሙከራ በመሆኑ ከመነሻው አላማውን የሳተ ነው፡፡ የራሱ የኘሮፖጋንዳው አራማጁን ተስፋፊ ቡድን ይበልጥ ከማጋለጥ ውጪ የሚፈይደው ነገርም አይኖርም፡፡

3/ የተስፋፊ ቡድኑ የኘሮፖጋንዳ ሙዚቃ ቅኝት ተጋልጦ ሲታይ፣

ከላይ በጥቅሉ ለመግለጽ እንደተሞከረው የተስፋፊ ቡድኑ ኘሮፖጋንዳሲስቶች የሰሞኑ ጩኸት የስድብ፣ የተራ አሉባልታና የእርግማን ክምር ባዶ ገለባና ፍሬ ቢስ በመሆኑ ከእንዲህ አይነት የዘቀጠ ቡድን ጋር ራስን ዝቅ አድርጐ መነታረክና መልስ መስጠት እንደማይገባ አምናለሁ፡፡ ሆኖም ግን በፀረ ኦሮሞ አቋም በፍፁም ጥላቻና የዘረኝነት ስሜት ቅጥረኞቹ ኘሮፖጋንዲስቶች ካነሷቸው በርካታ ጉዳዮች ውስጥ በጥቂቶቹ ላይ አተኩሮ ማብራሪያ መስጠት የተስፋፊውን አመራርና የኘሮፖጋንዳ አርበኞቹን  የዘቀጠ ሃሣብና የእነሱን ማንነትና ተልዕኮ ይበልጥ ለመረዳት የሚረዳ መሆኑን በማመን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በአጭር በአጭሩ እንደሚከተለው ማብራሪያ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡

3.1/ የኦሮሚያ ክልል በሶማሌ ክልል ላይ የመስፋፋት ዓላማ ያራምዳል እያሉ ስለሚያናፍሱት የበሬ ወለደ የሉባልታ፣

የተስፋፊው ቡድን ፕሮፖጋንዲስቶች ባገኙት አጋጣሚ የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሶማሌ ክልል ላይ ግዛቱን ለማስፋፋት እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ሲያነሱ ይሰማል፡፡ በቅርቡ በተደራጀ መንገድ በሶሻል ሚዲያ የተጀመረው ፀረ- ኦሮሚያ ኘሮፖጋንዳም  ይህንኑ ሃሣብ በማራገብ ላይ ይገኛል፡፡

የተስፋፊ ቡድኑ ከሀቅና ከእውነት በራቀ መንገድ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የክልሉን ግዛት ለማስፋት ባለው ፍላጐት የሶማሌ ክልል አጐራባች ወረዳዎችን በኃይል ለመያዝ እየተንቀሳቀሱ እንዳለና አንዳንድ የሶማሊ ክልል ወረዳዎች በእጁ እንደሚገኙ፣ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስም እየጠቀሱ የምሥራቅና የምዕራብ  ሐረርጌ አካባቢዎችን ከባቢሌ፣ ጭናክሰን፣ ፈዲስ እስከ ጭሮ /አሰበ ተፈሪ/ እና ቦርደዴ ድረስ የሶማሌ ክልል ወረዳዎች ሆነው እያለ ኦሮሚያ በኃይል ያስተዳድራቸዋል፣ በባሌና በጉጂም እንደዚሁ ኦሮሚያ የያዛቸው የሶማሌ ክልል አካባቢዎች አሉ እያሉ ሀሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ላይ ናቸው፡፡ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ኦሮሚያ እየገባ ግድያና ዝርፊያ እንደሚፈጽም እየታወቀ እነዚህ የሀሰተኛ ኘሮፖጋንዳ አራማጆች እስካሁን በሁለቱ ክልሎች መካከል ግጭቱ የተካሄደው ሙሉ በሙሉ  በሶማሌ ክልል ግዛት ውስጥ ነው እስከማለት የሚደርስ ውሸት ማራገባቸውን ቀጥለዋል፡፡

ይህንንም የሚሉት መላ ሐረርጌ፣ ባሌና እስከ ሞያሌ ያለው የኦሮሞ መሬት ሁሉ የሶማሌ ክልል ነው ብለው ስለሚያስቡና እነዚህንም አካባቢዎች በኃይል ጠቅልለው የመውሰድ ሕልም ስላላቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም ሲያረጋግጡ በድህረ ገጻቸው ላይ በወጣው አንድ ጽሁፍ አሰበ ተፈሪ የሶማሌ ክልል አካል የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን እርግጠኛ መሆናቸውን በድፍረት ገልፀዋል፡፡ ከዚህም አልፈው ጉጂ፣ከረዩና ገብራ የተባሉ  የኦሮማ ጐሳዎች አፋን ኦሮሞ ይናገራሉ እንጂ ኦሮሞ አይደሉም ብለው  እስከ መጻፍም ሄደዋል፡፡

ከዚህ በላይ በአጭሩ ያነሳሁትን የእነዚህ ዕኩይ ዓላማ አራማጆች ህልም ከሥር መሠረቱ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ለመሆኑ የግዛት ማስፋፋት ዓላማ ምንጩ የት ነው? እያስፈፀመ ያለውስ ኃይል ማነው? በተግባር ያለውስ ዕውነታ ምን ይመስላል… ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በመሠረቱ የግዛት ማስፋፋት ጥያቄ በአንድ አገር ነዋሪ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ሊነሳ አይችልም፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ሶማሊና የኦሮሚያ አካባቢ በምሥራቅ እስከ አዳማ፣ በደቡብ እስከ ሞያሌ የሶማሌ ሕዝብ መኖሪያ ነው የሚለው አስተሳሰብ በኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች ሳይሆን ከሶማሊያ መንግስት የመነጨና ለኛ ባዕድ የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ የሶማሊያ መሪዎች አሁን የሶማሊያ ግዛት ከሆነው አካባቢ እስከ አዳማ ያለውን የኢትዮጵያ ግዛት፣ ጂቡቲና ሰሜን ኬንያ ግዛትን በማዋሃድ ታላቋን ሶማሊያ የመፍጠር አላማ ሲያራምዱ ቆይተዋል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ያልተሳኩ ሁለት ታላላቅ ጦርነቶችን ከኢትዮጵያ ጋር አካሂደው በኢትዮጵያ ሕዝቦች የተባበረ ኃያል ክንድ ተሸንፈዋል፡፡

በተለይም ጄኔራል ዝያድ ባሬ በመፈንቅለ መንግስት የሶማሊያ መሪ ከሆነበት ዕለት አንስቶ የምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢን የሶማሊያ ግዛት ለማድረግ ያላደረገው ሙከራ አልነበረም፡፡ ከዚህም ባሻገር ዝያድ ባሬ የሐረርጌ፣ የባሌ፣ የአርሲ፣ የጐጂና የቦረና ኦሮሞ ብሔሩ ኦሮሞ ሳይሆን ሶማሌ ነው፣ አፋን ኦሮሞ የሚናገር ሶማሌ ነው /ሶማሌ አቦ/ እያለ የኦሮሞን ብሔራዊ ማንነት በመካድ ታላቅ ታሪክ ደባ ፈጽሟል፡፡ ስደተኛ ኦሮሞዎችን የምሥራቅ ኦሮሚያ አውራጃዎች አስተዳዳሪ እያለ በመሾም ደሞዝ የመክፈል ድራማ ይሠራ እንደነበረም ይታወቃል፡፡

በነገራችን ላይ በሽግግሩ ዘመን የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ድንበርን አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ አንድ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራር (በወቅቱ የነበረ የክልሉ ኘሬዚዳንት ይመስለኛል) የእኛ የሶማሌ ክልል ድንበር ናዝሬት ነው; ብሎ በድፍረት  እንደተናገረና በወቅቱ የውይይት መድረኩ ሰብሳቢ የነበረው ታጋይ ዳዊት ዮሐንስ ጤናና ዕድሜ ይስጠውና በአባባሉ ተበሳጭቶ የናዝሬት አካባቢ የኦሮሞ ሕዝብ መሬት መሆኑን እኛ አማሮችም እናውቃለን፣ ምን ማለት ፈልገህ ነው; ብሎ  በቁጣ መናገሩንና የክልሉን መሪ የሀፍረት ማቅ ማላበሱን አስታውሳለሁ፡፡

ስለዚህ የአባዬን ወደ እምዬ ; እንደሚባለው የተስፋፊ ቡድኑ በግዛት ማስፋፋት ላይ የተመሠረተ ሙት ዓላማ  የኦሮሚያ  ክልል አመራር አድርጐ በማቅረብ ኦሮሚያ በሶማሌ ክልል ላይ የመሬት ጥያቄ አለው፣ ይህንንም በኃይል ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋል እያሉ ለማደናገር እየተደረገ ያለው ሙከራ በአርቆ አስተዋይነት ነገሮችን ማየት ያለመቻል የጨቅላ አዕምሮ ባለቤቶች ከንቱ ሙከራ በመሆኑ አያስጨንቀንም፡፡ ከዚህም በመነሳት በአንድ ተስፋፊ ቡድን እኩይ ድርጊት የሱማሌ ክልል ወንድም ህዝብን  በከፉ አይን ለማየት አንሞክርም፡፡

በጥቅሉ ይህ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተከፈተ የጥፋት ዘመቻ መቸም ቢሆን ግቡን አይመታም፡፡ በሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ለዘመናት የዘለቀ የትስስር ገመድ ለመበጣጠስም አይችልም፡፡ ሁለቱ ክልሎች ሰፋፊ ናቸው፡፡ የክልሎቹ ነዋሪዎችም የአንድ አገር ሕዝቦች በመሆናችን ሶማሌ በኦሮሚያ ውስጥ፣ ኦሮሞም በሶማሌ ክልል ውስጥ እንደተለመደው በሰላም በመኖር እጅ ለእጅ ተያይዘን የጀመርነውን የዕድገት ጉዞ እንቀጥላለን ከፋፋይና ሕዝብ የሚያባላ እኩይ አላማ የሚያራምዱ በሞተ ፈረስ ጋልበው ሩቅ ለመድረስ የተነሱ ጀብደኞችና ጊዜያቸውን ሁሉ በድንበር ማስፋፋት ጉዳይ ላይ እያዋሉ ያሉ መርዛማ እባቦችም ከነመርዛቸው የሚጠፉበት  ወቅት እሩቅ አይሆንም፡፡

3.2/ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ድንበር ላይ የተነሳው  ውዝግብ መንስኤ ኦሮሚያ በሪፈረንደም ለሶማሌ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎችን አሳልፎ ለመስጠት አለመፈለጉ ነው እየተባለ በተስፋፊ ቡድኑ ደጋፊ የሶሻል ሚዲያ አውታሮች የሚናፈሰውን አሉባልታ በሚመለከት፣

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች መካከል በድንበር ሳቢያ የተፈጠረውን ረጅም ጊዜ የወሰደ ችግር ለማስወገድና ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት ሲባል የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፌዴራል መንግስት የይገባኛል ጥያቄ የቀረበባቸው አካባቢዎች በነዋሪዎቻቸው ነጻ ፍላጐት እንዲካለሉ ለማድረግ የጋራ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው በ1997 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) መካሄዱ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የይገባኛል ጥያቄ የቀረበባቸው አካባቢዎች  የሚኖሩ የኦሮሞና የሶማሌ ክልል ተወላጆች በነጻ ምርጫቸው ከሁለቱ ክልሎች ወደሚፈልጐት እንዲጠቃለሉ ለማስቻል በ422 ቀበሌዎች ሕዝበ ወሳኔ (ሪፈረንደም) ተካሂዶ የ312 ቀበሌዎች ነዋሪዎች ወደ ኦሮሚያ  ለመጠቃለል ሲመርጡ 11ዐ ቀበሌዎች ደግሞ ወደ ሶማሊ ክልል ለመጠቃለል የይሁንታ ድምጽ  መስጠታቸው  የሚታወስ ነው፡፡  ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት የሶማሌ ክልል ሕዝብን ከተለያዩ  ሩቅ አካባቢዎች ሪፈረንደም ወደሚካሄድባቸው አካባቢዎች ጭኖ በመውሰድና ለአንድ ሰው ሶስት መታወቂያ በማውጣት ጭምር ለማጭበርበር  ያላደረገው ሙከራ አልነበረም፡፡ ከሌላ አካባቢ ወደ ሞያሌ ብዙ ሰው ጭነት መኪናዎች በጭኖ በማስፈር ምርጫውን ለማሸነፍ ያደረገው ጥረት ለዚህ እንደ አብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ያም ሆነ ይህ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ይፋ እንደተደረገ የኦሮሚያ ክልል ወደ ሶማሌ ክልል መጠቃለል ያለባቸውን አካባቢዎች በሕዝቡ ውሳኔ መሠረት ምርጫ ቦርድ በሚያውቀው ሁኔታ ማስረከቡ የሚታወስ ሲሆን  የሶማሌ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎችን ብቻ ለኦሮሚያ መልሶ ሌላውን በማዘግየት ብቻ ሣይወሰን የሕዝቡን ውሳኔ ለመሻር በስፋት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ሪፈረንደሙ ከተካሄደበት ወቅት አንስቶ በየወቅቱ  በርካታ ሕዝብ ወደ ኦሮሚያ ክልል ድንበር አካባቢዎች እያሰፈረ፣ በታጣቂዎች የኦሮሞ አርብቶ አደሮችን እያፈናቀለና የሶማሌ ክልል ሰንደቅ አላማን በኦሮሚያ ድንበር ውስጥ በየዕለቱ እየተከለ የወረዳና የቀበሌ የአስተዳደር ስም እየሰጠ  ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በዚህም ሳቢያ የብዙ የኦሮሞ ተወላጆች ሕይወት ጠፍቷል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፣ ንብረት ተዘርፏል፡፡  ሕዝብ  ተፈናቅሏል፡፡ ሕገወጥ የመጤዎች ሰፈራም በብዛት ተካሂዷል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት ተስፋፊው ቡድን ልዩ ኃይል በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በማዝመት ከፍተኛ እልቂት ፈጽሟል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ችግሩን በትዕግስት በማየትና በሕጋዊ አግባብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት በማመልከት ጭምር ከመንቀሳቀስ በስተቀር ተስፋፊው ቡድን እንዳደረገው ሁሉ ኃይልን በኃይል ለመመከት አቅም ቢኖረውም አንዳችም የኃይል እርምጃ ሳይወሰድ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች በሕዝቡ ላይ  እየደረሰ ያለው ይህን አስከፊ በደል እንዲቆም ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰው በመጠየቃቸውና በተካሄዱት ሕዝባዊ መድረኮች ጐልተው ከወጡት የሕዝብ ጥያቄዎችና ቅሬታዎችም አንዱ ይኸው የድንበር አካባቢ ወገኖቻችንን ሕይወትና ድህንነት የመታደግ ጉዳይ በመሆኑ የኦሮሚያ  ክልል አዲሱ አመራር ይህንን ችግር ከሶማሌ ክልል አመራሮች ጋር ተነጋግሮ በሰላም ለመፍታት ቅድሚያ ተነሳሽነት ወስዶ በጠየቀው መሠረት ውይይት መጀመሩን ሰምቻለሁ፡፡

ይሁን እንጂ ተስፋፊው ቡድን ከኦሮሚያ የቀረበውን በሰለጠነ መንገድ ተነጋግሮ ችግሩን የመፍታት ፍላጐት በመጻረር ሀይል አሰማርቶ ችግሩ ይበልጥ እየተወሳሰበ የሄደበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል፡፡ ይህንን እውነታ እያወቁ የችግሩ ፈጣሪ ኦሮሚያ ነው፣ ኦሮሚያ በሪፈረንደም  የተመለሱ አካባቢዎችን  አሳልፌ አልሰጥም አለ፣ ውጊያው እየተካሄደ ያለው በሶማሌ ክልል ውስጥ ነው እያሉ በሐሰት ላይ የተመሠረተ ውሸት በማራገብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከሁሉ በላይ እስከ አሁን በሁለቱ ድንበር አካባቢ የተፈፀሙ ጥቃቶች በኦሮሚያ ታጣቂ በሶማሌ ክልል ውስጥ የተፈፀሙ ናቸው እየተባለ በተስፋፊ ቡድኑ የሚጮህለት ጉደይ አስገራሚ ብቻ ሣይሆን በሚገባ ከታዬ የወራሪዎቹን መሠረታዊ  ፍላጐትና የተሳሳተ አመለካከት ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡ የሶማሊ ክልል አመራር ኘሮፖጋንዲስቶች የተካሄዱት ውጊያዎች በሙሉ በሶማሌ ክልል ውሰጥ ነው ሲሉ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ጐጂና የመሳሰሉት የኦሮሚያ  ዞኖች በሙሉ  የሶማሌ ክልል ናቸው ማለታቸው እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡

እባካችሁ ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ፡፡

**********

Guest Author

more recommended stories