Aug 02 2016

ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ - ለሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሃይማኖት የተሰጠ ምላሽ

(እውነቱ አሸናፊ)

እኔ ታጋይም የኢህአዴግ አባልም አልያም የሰራዊት አባልም አይደለሁም፤ የምኖረውም በስደት ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ከአገሬ ብዙም ሩቅ አይደለሁም በተደጋጋሚም እመላለሳለሁ:: በአገራችን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ምክንያት እየታየ ያለው የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ትክክለኛ በመሆኑ በፅኑ ደጋፊ ነኝ:: በዚህም ይህን ስርዓት እንድንገነባ መንገዱን ላሳዩን ለታላቁ መሪያችን ክቡር አቶ መለስ ያለኝ ክብርና ፍቅር ወሰን የለውም:: ነብሳቸው በክብርና በገነት እንድታርፍም የዘወትር ፀሎቴ ነው:: ስለራሴ ይህን ካልኩ በኋላ ይህን እንድጽፍ ወደአስገደደኝ ነገር ልግባ::

በቅርቡ ሁሌ እንደማደርገው ወደ አገሬ ቤተሰብ ለመጠየቅ ሂጀ ነበር፡፡ አንድ ቀን ከጓደኛየ ጋር ሻይ እየጠጣን በአንድ ካፌ ቁጭ ብለን ‹‹ህገ መንግስቱን የሚጻረረው የሠራዊት ግንባታ ሰነድ ከሥራ ይታገድ (ሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሃይማኖት)›› የሚል ጽሑፍ ሪፖርተር[1] ጋዜጣ ላይ አየሁና ቀልቤን ስለሳበው ለማንበብ ወሰንኩ እዛው ቁጭ ብየም ጨረስኩት::

ወዲያው የመጣልኝ ሃሳብም ያንን መጽሐፍ አግኝቼ ማንበብ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል የሆነ አብሮ አደግ ጓደኛየ ጋር ደውየ መጽሐፉ ካለው እና ከሰራዊት ውጪ ለሆነ አባል የማይከለከል ከሆነ (ጀነራሉ በፅሁፋቸው ለህዝብ ይፋ ያልሆነ አስመስለው ስላቀረቡት) እንዲያመጣልኝ ስጠይቀው ምክንያቴን እንኳ ሳይጠይቅ እሱ እንደሌለውና ከጓደኛው ጠይቆ እንደሚያመጣልኝ ነገረኝ:: እንዳለውም በነገታው አምጥቶ አንበበህ መልስልኝ ጓደኛየ ይፈልገዋል ስትመለስ ሳትሰጠኝ እንዳትሄድ (ወደ መጣሁበት ኬንያ ማለቱ ነው) እንጂ የፈለግከውን ጊዜ ማቆይት ትችላለህ ብሎ ተረጋግቼ እንዳነበው ሰጠኝ::

እኔም የሚበቃኝን ጊዜ ወስጀ ከህገመንግስቱ ከብሄራዊ ደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር እያገናዘብኩ ለሶስት ቀናት በጥልቀት ፈተሸኩት:: ያገኘሁትንና የገባኝን ነገር ደግሞ ለጀነራሉ ፅሁፍ በአቅሜና በገባኝ ልክ ለምን አልመልስም በሚል ተነሳስቼ ይህን የኔ የራሴና የማንም ጣልቃ ገብነት የሌለው ፅሁፍ ሳቀርብ፤ ከማንኛውም አካል ለሚቀርብልኝ ጤነኛ አስተያየት ለመቀበል አስፈላጊ ከሆነም ተጨማሪ ማብራርያ ለመስጠት ዝግጁ መሆኔን አሳስባለሁኝ:: እንደዚህ አይነት ጽሁፍ በመፃፍ ረገድ የመጀመሪያየ ስለሆነም የጀነራሉን ሆነ የሌላን ክብር እንዳልነካ የተቻለኝን ጥንቃቄ ለማድረግ ሙከራ አድርጊያለሁ፤ ከተገኘ ግን አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ::

በየትኛውም ሀገር ያደገም ይሁን ያላደገ፣ ሊበራልም ይሁን ልማታዊ፣ ዘውዳዊም ይሁን ካፒታላዊ፣ ዲሞክራሲያዊም ይሁን ኢ-ዲሞክራሲያዊ፤ ሁሉም ምንም አይነት ባህሪ ይኑራቸው አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ቢኖር የሰራዊት ግንባታ አላማቸው ሁሉም እንደየባህሪያቸውና ፖለቲካዊ አቋማቸው ለስርአቱና ለፖለቲካው ቀጣይነት የመጨረሻ ምሽግ/ዘብ ሆኖ እንዲቆም ማድረግ ነው:: ከዚህ ተነስቶ ምልመላውም በተለይ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች በተቻለ መጠን ከፖሊቲካውና ከስርአቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚዎችና እንጠቀማለን ብለው ከሚያስቡ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሆን ይደረጋል:: ለዚህም ነው በብዙ አገሮች (በኛ አገርም በንጉሱ ጊዜ) አብዛኛው ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የወታደር ወይም የመኮነን ቤተሰብ ሲሆኑ የሚታየው::

ይህን ለማድረግ የትኛውም አገር ሰራዊት እንዴት መገንባትና ባህሪው ምን መሆን እንዳለበት የተለያዩ ደንቦችና መመሪያዎች ያወጣሉ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ እንዲሰርፀው፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ የስርፀት (ኢንዶክትሪኔሽን) የስርኣቱ ፖለቲካ ልእልና እንዲያገኝ ከፍተኛ ስራ ይሠራበታል:: ይህም ሆኖ ግን የተለያዩ ደንቦች፣ መመሪያዎችና እያንዳንድዋን እንቅስቃሴ የሚመራ የተለያዩ ማንዋሎች ያዘጋጃሉ:: በማንኛውም መለኪያ ግን፤ መርህ የሌለው የሰራዊቱን ግንባታ ሊኖር አይችልም:: በኛ አገር የሆነው ነገር ይኸው ነው:: ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት – ለምሳሌ በአሜሪካን አገር ከሊበራሊዝም ውጪ የሚያምን ቀርቶ የሚያስብ በወታደሩ ቤት በትንሹ ምንም አይነት የመኮነንት ማዕርግ አያገኝም – ከጅምሩም ቢሆን ወደ ሰራዊት የመግባት እድሉ የተዘጋ ነው:: ይህ በተለያየ ዘዴ ተግባራዊ ይሆናል::

ይህ የማድረግ ሃላፊነት ያለውም በወቅቱ ስልጣን ላይ ያለው ፖሊቲካዊ አስተሳሰብ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም:: በወቅቱ ስልጣን ላይ ያለው፤ ስልጣን የወጣበት መንገድ ምን ይሁን ምን፤ ስልጣኑ ከያዘ የስልጣን እድሜው እንዲራዘም እንጂ በእንዝህላልነት አሳልፎ የሚሰጥ አካል (ፓርቲ ይሁን ግለሰብ) ታይቶ አይታወቅም፡፡ አለም ላይ ሌላ ተአምር ካልተፈጠረም ለወደፊቱም አይኖርም::

ስለሆነም ሰራዊት ሲገነባ በአለም ላይ ካሉት ርእዮተ ዓለሞች ውጪ ሊሆን ኣይችልም:: በአሁኑ ጊዜ አብዮታዊ(ልማታዊ) ዲሞክራሲ አልያም ሊበራል (በአፍሪካ “ጥገኛ”) ዲሞክራሲ ነው መሆን የሚችለው፡፡ ከሁለቱም ውጪ ሊሆን አይችልም:: ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ሰራዊት የሚገነባው ለጦርነት በመሆኑ እና ጦርነት ደግሞ የፖለቲካ ከፍተኛውና የመጨረሻ መገለጫ በመሆኑ ነው:: ለዚህም ነው መከላከያ የስርዓቱ/ፖለቲካው የመጨረሻ ምሽግ የሚሆነው፤ በጦርነቱ የተሸነፈ ፖለቲካ/ስርዓት የመጨረሻ ውድቀቱ በመሆኑ::

እውነቱ ይህ ከሆነ፤ ማለትም፡- ሰራዊት የስርዓቱ ጠባቂና የመጨረሻ ምሽግ/ዘብ ከሆነ፣ ጦርነት የፖለቲካ የመጨረሻ መገለጫ ከሆነ፣ ሰራዊቱ ስርዓቱ ይጠቅመኛል እስከመጨረሻ እዋደቅለታለሁ ብሎ በእምነት የሚሰለፍ መሆን ይጠበቅበታል ማለት እስከሆነ ድረስ፤ በመርህ ላይ የተመሰረተ ጥራት ያለውና በግልፅ የተቀመጠ የግንባታ አቅጣጫ ባይኖር እንጂ መኖሩ ሊያስገርም አይችልም:: ካልሆነ የተበተነ አስተሳሰብ ያለው ለህዝቡና ለስርዓቱ አደጋ የሆነ አለቆቹ ባኮረፉ ቁጥር የሚያኮርፍ፤ እርስ በርሱ የማይተማመን (የታጠቀ ስለሆነም የሚጋጭ) አለፍ ሲልም የግልበጣ (ኩዴታ) ሀይል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ማንም የሚፈልገው አይደለም::

እንግዲህ የአገራችንና የመንግስታችን መነሻም ይኸው ነው:: በአገራችን በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ እየተከተልነው ያለው እና በኢትዮጵያ ህዝቦች ተቀባይነት አግኝቶ ስልጣን ላይ ያለው አስተሳሰብ አብዮታዊ (ልማታዊ) ዲሞክራሲ ነው:: ይህ ስርዓት እንደማንኛውም ስርዓት ቀጣይነት እንዲኖረውና ሁሌም በአሸናፊነት እንዲቀጥል ይፈልጋል እንጂ፤ በእንዝህላልነት ራሱን አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ የሚታሰብ አይሆንም:: ስለሆነም ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ – በተለይ ደግሞ በሃይል (በትጥቅ) ስልጣኑ ማጣት ስለሌለበት – ለስርዓቱ ጠበቃ የሚቆምለት የመከላከያ ሃይል ያስፈልገዋል:: የሚቋቋመው የመከላከያ ሰራዊት ደግሞ በህገመንግስቱ በግልፅ የተቀመጠለትን ተልእኮ የሚፈፅም ተደርጎ ይቀረፃል:: ይህን ለማድረግ ደግሞ መንግስት ትክክለኛ ብሎ ያመነበት የግንባታ ኣቅጣጫ ይከተላል:: የተደረገውም ይኸው ነው::

አንድ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ አስተሳሰብን የሚከተል መንግስት፤ ሰራዊቱን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብና እምነት መገንባቱ ምንም ጥፋት ያለውና አከራካሪ አይሆንም:: መከራከር ካለብን ይህ አቅጣጫ በትክክልም በሰራዊቱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የአስተሳሰብ ልእልና ሊያመጣ አይችልም ጉደለት አለው ስለሆነም ሰራዊት እንዲዋደቅለት አያደርገውም የሚል ሃሳብ ካለ ነው::

ይህን ለመመዘን ደግሞ ዋናው መነሻ የሆነውና የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰራዊቱ እንዲቋቋም ይሁንታ ከሰጡበት እና ምን ዓይነት ሰራዊት እንደሚያስፈልገንና ምን መስራት እንዳለበት ግልፅ ተልእኮና ግዳጅ ከሰጡበት ህገ-መንግስት መነሳት ያስፈጋል::

በመሆኑም ህገ-መንግስቱ ለሰራዊቱ ያስቀመጠው ተልእኮና ክልከላ እንዲሁም የህገ-መንግስቱ መርሆዎችና አላማዎች ምን እንደሆኑ በማየት ከዚህ አንፃር በመንግስታችን የተዘጋጀው “የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ” የሚለው መፅሃፍ እንዴት ከህገ-መንግስቱ የማይወጣ/የማይፃረር እንደሆነ ለማየት ያስችላል::

1. ህገመንግስታችን ምን ይላል?

1.1. የህገ-መንግስቱ መርሆዎች

1.1.1. የህዝብ ሉኣላዊነት አንቀፅ ፰::

1.1.2. የህገ-መንግስት የበላይነት አንቀፅ ፱::

1.1.3. የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊነት አንቀፅ ፲::

1.1.4. የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት አንቀፅ ፲፩::

1.1.5. የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት አንቀፅ ፲፪::

1.2. ለፈደራል መንግስት ከተሰጡት ስልጣንና ተግባሮች አንቀፅ ፶፩ ላይ (መከላከያን በተመለከተ)

1.2.1. ንኡስ አንቀፅ ፩ ሕገ-መንግስቱን ይጠብቃል፤ ይከላከላል::

1.2.2. ንኡስ አንቀፅ ፮ የሀገርና የሕዝብ የመከላከያና የደህንነት እንዲሁም የፌደራል መንግስት የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል::

1.2.3. ንኡስ አንቀፅ ፲፬ ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ ጥያቄ መሰረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል::

1.3. የመከላከያ መርሆች አንቀፅ ፹፯

1.3.1. የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ሚዛናዊ ተዋፅዖ ያካተተ ይሆናል::

1.3.2. የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ይሆናል::

1.3.3. የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል::

1.3.4. የመከላከያ ሰራዊቱ በማንኛውም ጊዜ ለሕገ-መንግስቱ ተገዢ ይሆናል::

1.3.5. የመከላከያ ሰራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል::

1.4. የህገ-መንግስቱ ዓላማዎች አንቀፅ ፹፰ እስከ ፺፪ በጥቅሉ

1.4.1. የህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ መከበር::

1.4.2. የህዝቦች የራስ እድል በራስ የመወሰን መብት ማክበር::

1.4.3. የህዝቡን ወሳኝነትና ዙሪያ መለስ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት::

1.4.4. ማህበራዊ ፍትህ ማረጋገጥ::

1.4.5. የሀገራችንን ጥቅምና ነፃነት ማስጠበቅ::

1.5. ለመከላከያ ሰራዊቱ የተቀመጡ ክልከላዎች በአዋጅ የተቀመጡ

1.5.1. ማንኛውም የሰራዊት አባል ሰላማዊ ሰልፍ አያደርግም:: ሌሎች በጠሩት ሰልፍም አይሳተፍም::

1.5.2. ማንኛውም የሰራዊት አባል የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሊሆን አይችልም::

1.5.3. ማንኛውም የሰራዊት አባል በስውርም ሆነ በግልፅ የፖለቲካ ቅስቀሳ አያደርግም::

1.5.4. ማንኛውም የሰራዊት አባል አንድን የፖለቲካ ድርጅት ወይም ተመራጭ በመደገፍም ሆነ በመቃወም ቅስቀሳ አያደርግም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች አርማ ወይም ለቅስቀሳ የሚጠቀሙባቸውን ምልክቶች በማንኛውም ቦታ አይዝም/አይጠቀምም::

1.5.5. የመምረጥ መብት ቢኖረውም በግል ይሁን ፖለቲካ ፓርቲ ወክሎ ስልጣን ለመያዝ አይወዳደርም::

1.5.6. ማንኛውም የሰራዊት አባል ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ መዋጮ አያደርግም፤ በመደገፍም ሆነ በመቃወም አቋም አይወሰድም::

1.5.7. ማንኛውም የሰራዊት አባል የስራ ማቆም አድማ አያደርግም::

1.5.8. ማንኛውም የሰራዊት አባል ከላይ ከተጠቀሱት ውጪ ህገ-መንግስቱ ለዜጎች የሰጠው መብት ሙሉ በሙሉ የሚከበሩለት ይሆናል ይላል::

ከዚህ በመነሳት የህገ-መንግስቱ ኣላማዎች መርሆዎች እንዲሁም በህገ-መንግስቱ የተቀመጡትን እንዲኖር ምክንያት የሆኑትን ተልእኮዎች በብቃትና በላቀ ሁኔታ ለማሳካት እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ቀጣይና አስተማማኝ ለማድረግ፤ ከሰራዊቱ የሚከተሉት ጉዳዮች እንደሚጠበቅ ሳይታለም የተፈታ ነው::

እነሱም:-

* ህገ-መንግስቱን መሠረት አድርገው በአዋጅ የተቀመጡትን ክልከላዎች በእምነት ይዞ በፅናት ተግባራዊ ማድረግ::

* የህዝብ ተሳትፎ በመገደብ፤ ስልጣን በጥቂት ገዢዎች ቁጥጥር ስር ገብቶ ህዝቡ ለአፈና፣ አድልዎና ፍትህ ማጣት ወዘተ የተጋለጠ እንዲሆን ለማድረግ የሚጥሩትን ሃይሎች ከህዝብ ጋር በመሆን መመከትና መታገል::

* ህዝባዊነቱንና አብዮታዊነቱን የሚሸረሽር አደጋ እንዳይከሰት ጥራቱንና ጥንካሬውን መጠበቅ፤ ራሱን ከህዝብ በላይ/የተለየ አድርጎ ማየት የለበትም፤ የራሱ ጥቅምም ሆነ ህልውና ከህዝቡ ጥቅምና ህልውና ጋር የተሳሰረ መሆኑ ማመንና መገንዘብ::

* ህዝቡ ከሚኖርበት ሁኔታ በተለየ ሁኔታ ለመኖር፣ ባለ ትጥቅ በመሆኑ የተለየ ጥቅም ለማግኘት የሚመኝ መሆን የለበትም::

* ለሰራዊቱ የሚረጋገጥለት መብት ለህዝቡ በሚረጋገጥ መብት ላይ የሚመረኮዝ መሆኑን በሚገባ የሚያምን መሆን ይኖርበታል::

* ማንኛውንም እምነት፣ ማህበረሰብ፣ ብሔርና ብሔረሰብ በመደገፍም ሆነ በመቃወም የሚወስደው አቋም ሳይኖር ሁሉንም በእኩል አይን ማየትና ማስተናገድ::

* ማንኛውንም የታጠቀም ይሁን ያልታጠቀ ተቃውሞ፣ በሃይል እስካልመጣ ድረስና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በሃይል ለመናድ ወይም በሃይል ስልጣን ለመያዝ እስካልመጣ ድረስ፣ ለአንዱ ወግኖ ሀይል መጠቀም የለበትም::

* ሀገሪቱ የደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊስዋ ግልፅ ያደረገችውን የአገሪቱ ተቀዳሚ አጀንዳዎች ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ግንባታ ነው፡፡ ማንኛውም ከውጪም ይሁን ከውስጥ የሚመጣን ማንኛውም ዓይነት ተቃውሞም፤ እነዚህ ቅድሚያ የሰጠናቸው ስራዎች እስካላደናቀፈ ድረስ ሁሉም በጠረጴዛ ዙሪያና በሰላማዊ መንገድ እልባት ማግኝት አለባቸው፣ ከድህነት በላይ ጠላት የለንም፣ በሚል በግልፅ ተቀምጧል::

እነዚህ ህገ-መንግስታችና የህገ-መንግስቱ ውጤት የሆኑት የተለያዩ ፖሊስዎችና ስትራተጂዎች ለሰራዊታችን የሚያቀምጧቸው ግዴታዎችና ተግባራት ናቸው፡፡ እነዚህን በብቃትና በላቀ ሁኔታ ለመወጣት የራሱ የሆነ የግንባታ አቅጣጫ እንደሚያስፈልገው ግልፅ ነው:: ለዚህም ነው ‹‹የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ›› የሚለው መፅሐፍ መዘጋጀቱ ተገቢ የሚሆነው::

ከዚህ ተነስተንና በመዘጋጀቱ ተገቢነት ከተማመንን፤ የተዘጋጀው መፅሃፍ ምን ይላል? ከህግ-መንግስቱና ህገ-መንግስቱ መነሻ አድርገው ከተዘጋጁት ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች እንዴት ይተሳሰራል? መነሻው ዓላማውና አቅጣጫው ምንድን ነው? ጥያቄ የሚያስነሳ ምን ይዘት አለው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንሞክር::

2. ‹‹የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ›› የሚለው መጽሐፍ ምን ይላል?

2.1. መጽሐፉ በመግቢያው፤ የአንድን አገር ሰራዊት ለመገንባት መነሻው ጦርነት የፖለቲካ ተቀፅላና ከፍተኛ መገለጫ መሆኑ እና ሰራዊት ደግሞ ዋነኛው የጦርነት መሳሪያ በመሆኑ፤ ከዚሁ አንፃር መገንባት እንደሚያስፈልግ በስፋት ያስቀምጣል::

2.2. የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ዓላማ::

ሀ. አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታችንን በሀይል ለማጥፋት ከሚሞክሩ የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶች የሚከላከል፣ ከስርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ከሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ፣ የማያቋርጥና ያልተሸራረፈ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አመራርን የሚያገኝ የመከላከያ አቅም መፍጠር::

ለ. ከሌሎች የትግል አግባቦች ጋር ተደርቦ የጦርነት አደጋን የሚያስወግድ፣ የጦርነት አደጋን ማስወገድ በማይቻልበት ሁኔታ ደግሞ ለስርዓታችን ደህንት አይኑን ሳያሽ የሚዋደቅና ተዋድቆም የሚያሸንፍ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችለው አመለካከት፣ እምነት፣ ልምድና ባህሪ ያለው የመከላከያ አቅም መፍጠር ተብሎ በግልፅ ተቀምጧል::

2.3. የሰራዊቱ የፖለቲካ ግንባታ አቅጣጫ ሰራዊቱ የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ሃይል እንዲሆን የሚያስችል::

* የመካላከያ አቅም ለመገንባት የጦርነት አቅሞች፣ የኢኮኖሚ አቅሞች፣ የፖለቲካ ሁኔታና የአለም አቀፍ ሁኔታና ተፅእኖ ወሳኝ ነጥቦች መሆናቸው::

* የሰራዊት ፖሊቲካ ግንባታ መነሻው፣ ዓላማው እና አፈፃፀም በዝርዝር ያሰቀምጣል::

* የሰራዊቱን ወታደራዊ ግንባታ ምንነት፣ ከምን እንደሚነሳ እና እንዴት መፈፀም እንዳለበት ይዘረዝራል::

* በሰራዊት ግንባታ በኢኮኖሚ መካከል ያለው ትስስር፣ በአነስተኛ ወጪ ጠንካራ ሰራዊት እንዴት እንደሚገነባና ያለውን መደገጋፍ ያብራራል::

እነዚህ መሰረት አድርጎ ነው ሰራዊት እንዴት መገንባት እንዳለበት የተቀመጠው፡፡ ከዚህ አንፃር በተለያዩ ሰዎች በተለይ ደግሞ በቀድሞ ታጋይና የኢፌዴሪ አየር ሀይል አዛዥ የነበሩት ሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት በቅርቡ በዘረጉት ፅሑፋቸው፤ ይህ መፅሃፍ ከህገመንግስቱ ያፈነገጠና ሰራዊቱን የጥቂት ሰዎች መጠቀሚያ የሚያደርግ በመሆኑ ይታገድ በሚል ላቀረቡት አቤቱታ ላይ ምክንያቴ ብለው ያቀረቧቸውን ነጥቦች እስቲ እንፈትሻቸው እና ምን ማለት መሆናቸውን እንይ::

ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች፤ በሁለቱ (በህግ-መንግስቱና በሰራዊት ግንባታ መፅሐፉ) መሀል የሚቃረን ነገር እንደሌለ የሚያሳዩ ናቸው:: መንግስት ይህን መጽሐፍ ማውጣት አልነበረበትም ሊያስብልም አይችልም:: አልፎም መንግስት ሰራዊቱን በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አመለካከት መገንባት የለበትምም ለማለት የሚያስችልም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ሰራዊት የሚገነባው፣ ፖሊስና ስትራተጂ የሚነድፈው ከሚከተለው ርእዮተ አለም አንጻር ብቻ በመሆኑ:: ታድያ ጀነራሉ ምን እያሉን ነው?

ለነገሩ ለእሳቸው አሁን አሁን የከፍተኛ ትምህርት በማግኘታቸው ነገሮች ሁሉ ተገለባብጧቸው ችግር ላይ መሆናቸውን፤ በቅርቡም ደርግንና ኢህአዴግን መለየት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ‹‹ደርግነት እየመጣ ነው›› ብለው ሊያሳዩን ሞክረዋል፡፡ ስለሆነም የአሁኑን እና የደርግን ልዩነት መለየት ያልቻለ ሰው፤ በአሁኑ ህገ-መንግስትና በሰራዊት ግንባታ ልዩነት መኖሩ እንዴት ሊገባው ይችላል?

እስቲ ለማንኛውም ያነሱዋቸው ነጥቦች እንይ::

1. በተደጋጋሚ የሚያነሱት እና ከአሁን በፊት ደርግ መጥቷልና የሀገራችን ህዝብ ተጠንቀቅ ብለው በከፍተኛ ሁኔታ ህዝቡን ሊያነሰሳ ይችላል ብለው (ህዝቡ እሳቸው ከሚሉት በላይ የሚጠቅመውና የማይጠቅመው መለየት የሚችል ስለሆነ አልተሳካም) ባቀረቡት ፅሁፋቸው እንዳሉት፤ የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች በግላጭ ፀረ-ህገ-መንግስት ድርጊቶች እያከናወኑ ነው ብለው ይከሳሉ::

ለዚህ ማስረጃ ብለው ያቀረቡት ዋናው ነጥብ ደግሞ፤ በአንድ ወቅት መቐለ ላይ የግንቦት 20ን 25ኛ ዓመት በአል ምክንያት በማድረግ በትግራይ መገናኛ ብዙሃን በትግራይ የትምህርት ተቋማት ለሚማሩ ወጣቶች ለወጣቱ ትውልድ የትግል ሂደትና የዓላማ ፅናት ተሞክሮ ለማስተላለፍ ታስቦ የተዘጋጀው ፓናል ላይ፤ ኤታማጆር ሹሙ ተገኝተው የትግል ተሞክሮኣቸውን ማስተላለፋቸው ነው::

ይህ ድርጊት ለጀነራል አበበ ጨርቃቸው ያስጣለ ፀረ-ህገመንግስት ተግባር ነው:: እንዴትና የትኛውን የህገ-መንግስቱን አንቀፅ እንደሚፃረር ባያሳዩንም:: መቼም እንደ ህግ ምሁርነትዎ በህግ ላይ በአጠቃላይ የሚባልና አንቀፅ ያልተጠቀሰበት ክስ ሲቀርብ ገና ከርስዎ መስማት ለራስዎም ሳያስገርምዎ አይቀርም:: ሌሎች ከዚህ ያነሱ ክስዎችዎም አንቀፅ ጠቅሰው እስካልገለፁልን ድረስ ተቀባይነት የላቸውም:: መቼም በዚያ ፓናል፤ እሳቸው እድሜያቸውን ሙሉ ለህይወታቸው ምንም ሳይሳሱ ተመርተውና መርተው የትግሉ ሁኔታ በዝርዝር ስለሚያውቁና ከማንም ታጋይ በበለጠና ባልተናነሰ ተሞክሮኣቸውን ሊያስተላልፉልን ይችላሉ ተብሎ ተጋብዘው መገኘታቸው የሚያስጠይቃቸው አይሆንም::

ሊያነጋግር የሚችለው ተገኝተው ያስተላለፉት መልእክት ይሆናል ብዬም፤ እድሜ ለቴክኖሎጂ ምን ብለው ተናግረው ይሆኑ ብየ ኢንተርኔትን ጎርጉሬ በወቅቱ ሙሉ ቀን የነበረውን ስብሰባ ሙሉውን በዩቲዩብ አገኘሁትና አደመጥኩት፡፡ ስብሰባው በትግርኛ ነበር፡፡ ግን የመናገር እንጂ የመስማት ችግር የለብኝምና ለመረዳት አልቸገረኝም:: እዚህም ምንም ዓይነት የተቀመጡትን ክልከላዎች የሚጥስ ሀሳብ ቀርቶ ቃልም አላገኘሁም፤ ይህን ለማረጋገጥ ፍላጎት ያለው አካል ካለ ሙሉ ይዘቱ ቪድዮውን በዩቲዩብ ገብቶ ማዳመጥ ይችላል::

ከዚህ ጋር አያይዘውም ለወሬ ማጣፈጫ እንዲሆን ሆን ብለው አስበው፤ መከላከያ ወይን ጋዜጣን ስፖንሰር አድርጓል ብለዋል፤ ይህ ውሸት ነው (ቢያደርግ ስህተት ነው አይደለም የሚለውን አቆይተን)፡፡ ግን ስፖንሰር ያደረገበትን መጽሔት ወይም ጋዜጣ አያቀርቡም፡፡ እርስዎ የጠቀሱት ወይን መጽሔትን ከሆነ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡ ይህ አካል ደግሞ በመንግስት በአዋጅ የተቋቋመ፣ ህጋዊ ሰውነት ያለው፣ ራሱ ሊከሰስና መልስ ሊሰጥ የሚችል፣ እንደማንኛውን በአገራችን የሚንቀሳቀሱ የንግድ ድርጅቶች ራሱን በሚያዋጣው ሚድያ የማስተዋወቅ መብት ያለው፣ በራሱ በጀት የሚተዳደር ድርጅት ነው:: ይህ ደግሞ በህግ ምን ማለት መሆኑ ከሚያውቅ – ለዚያውም በዚህ ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ እየሰራ ያለ ከፍተኛ ምሁር – ጠፍቶት ሳይሆን ሆን ብሎ ጥላሸት የመቀባት አላማ ስለመሆኑ ግልፅ ነው::

2. ሌላው ጀነራሉን መጽሐፉ ከህገ መንግስቱ ያፈነገጠ ስለሆነ እንዲታገድ ብለው እስከማሳሰብ ያደረሳቸው እና አገር እየፈረሰች ነው ብሎ ያስጨነቃቸው፤ በተለይ ደግሞ:- ‹‹አሁን ስራ ላይ ካሉ ከፍተኛ መኮንኖች፣ በጡረታ ከተሰናበቱ፣ እንዲሁም “እንከን በሌለው መተካካት” ከተገለሉ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር በተለያዩ ግዜያት የመወየያት እድል ገጥሞኛል፡፡ከወርቃማው የ1997 አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ህዝቦችን ለመቆጣጠር የተወሰዱት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ፖለሲዎች፣ መመሪያዎች፣ አሰራሮችና ተግባሮች ወደ መከላከያ ተቋም ገብቷል እንዴ›› የሚል ጥያቄ እንዳጫረባቸው፤ የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚል መጽሐፍ ካነበቡ በኋላ ግን መሰረታዊ ችግሩ መጽሐፉ መሆኑን በከፊልም ቢሆን ሊገለጠላቸው እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

መጽሐፉ ከህገ መንግስት ያፈነገጠ ስለመሆኑ ከመጽሐፉ የጠቀሱት ደግሞ ‹‹እኛ የያዝነው አላማ እና ተግባራዊ እያደረግነው ያለ መደብ በሃገራችን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጦች እንዲካሄድ ይህ ስርአት ስር እንዲሰድ ማድረግ ነው››፣ ‹‹እኛ የምንገነባው የመከላከያ ኃይል የአብዮታዊ ዲሞክሪሲያዊ ስርአታችን ዘብ ነው ብለን በግልፅ እና በጥሬው ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው›› ይላል በማለት ምን ዓይነት እብሪት እንደሆነባቸው ይገልፃሉ:: አለፍ ብለው ሲጠቅሱ ደግሞ መጽሐፉ ‹‹የምንገነባው የመከላከያ ሃይል ዓላማው የስርዓታችን ደህንነት መጠበቅ ነው ሲባል የሚገነባውና የሚመራው የስርዓቱ መሪ የሆነው አካል ብቻ መሆን አለበት ነው›› ይላል ብለው ሌሎች ነጥቦችንም አንሰተዋል፡፡

አዎ እውነት ነው፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት ሀሳቦች ከህገ መንግስት ጋር የሚጋጩበት ሁኔታ ግን በፍፁም አያሳዩም፡፡ እብሪትም አይደሉም:: በህገ መንግስት አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚል ቃል የለም ሊሉን ፈልገው ከሆነ ሎጂኩ የሚያስኬድዎ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም እርስዎ የሚያምኑትና እንዲሆን የሚፈልጉት ሊበራል ዲሞክራሲም አልተገለፀም::

አረ ለመሆኑ ኢህአዴግ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ስልጣን ሲይዝ እኮ የሀገራችን ህዝቦች ያፀደቃችሁትን ህገ-መንግስት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርእዮተ አለም ነው ተግባራዊ የማደርገው ብሎ በግልፅ ቋንቋ አሳውቆ እንጂ፤ በደፈና ህገ-መንግስት ብሎ በመናገር ብቻ አይደለም:: ታድያ የማንን ፍላጎትና ፖለቲካ የሚያሟላ ሰራዊት እንዲሆን ተፈለገ? መቼም አብዮታዊ ዲሞክራሲ ስለተነሳ ኢህአደግ ማለት ነው ይሉን እንደሆነ እንጂ መጽሐፉ በግልፅ ቋንቋ ሰራዊቱ የሚገነባውም ሆነ የሚመራው የስርዓቱ መሪ በሆነ አካል ብቻ ነው ብሎ አስረግጦ አስቀምጧል:: የስርዓቱ መሪ ደግሞ በህገ-መንግስት በተቀመጠው አግባብ ብቻ ወደ ስልጣን የመጣ ማለት ነው:: ስለሆነ ጀነራል በግልፅ አይንገሩን እንጂ ጥላቻዎ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋርና ከህገ-መንግስቱ ጋር እንደሆነ እንዳይጠራጠሩ::

3. ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ እንዲህ ይላል “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለማንሳት የሚያስችሉ የተዘበራረቁ ጉዳዮች አሉ፡፡

‹‹“እኛ” ብለው ስለሰራዊታችን ግንባታ የሚጽፉት አመራሮች “የቁርጥ ቀን” ደራሽ እንዲሆንላቸው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሽፋን በማላወስ እኛን አገልግሉ ከማለት ውጭ ያስቀመጡት የተለየ የግንባታ ዓላማዎች እና አቅጣጫዎች የሉም፡፡ ከሞላ ጎደል “በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና የብሔራዊ ደህንነት ፖሊሲ” ሰነድ ላይም የተቀመጡ ናቸው፡፡ በአደባባይ ለህዝብ በዚያ ሰነድ ላይ ግን “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ኢህዴግ የመጨረሻ መከላከያ ምሽግ አይልም” ይሉናል፡፡

ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል:: እዚህ ላይ ምን እንዲያሳይ ብለው እንዳስገቡት የሚያውቁት እርሳቸው ቢሆኑም፤

አንደኛ፡- መጽሐፉ የብሄራዊ ደህንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊስን ተግባራዊ ማድረግ የሚችል ሰራዊት እንዴት እንደሚገነባ የግንባታ መመሪያ እንጂ ፖሊሲውን የሚተካና የተለየ አዲስ ሃሳብ የሚያመጣ ስላልሆነ ተመሳሳይ ነው፡፡ ጥላቻዎ ከመፅሃፉ ሳይሆን ከፖሊሲው ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም::

ሁለተኛ፡- ፖሊሲው መከላከያ የአብታዊ ዲሞክራሲ የመጨረሻ ምሽግ ነው አይልም የሚል መከራከያ ደግሞ ፖሊሲው እኮ የብሄራዊ ደህንነትና የውጭ ግኑኝታችን የምንመራበት እንጂ መከላከያ ሰራዊት እንዴትና ለምን እንደምንገነባ የሚገልፅ አይደለም ስለሆነም ውሃ የሚቋጥርና ለክርክርዎ የሚጠቅም አይደለም::

እዚህ ላይ እኛ የምትለው ቃል የጠሏት ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹እኛ›› የምትለው ሃረግ የገባችው አብዮታዊ ዲሞክራሲ የምንከተል ለማለት ነው፡፡ ምን ሃጥያት አለው? እናንተ የሚለው ሐረግ ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የማትቀበሉ ለማለት የተለመደ እኮ ነው፡፡ በመሆኑም ሰራዊቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚጠብቅ ይሆናል ሲባል ግን ሌላ አመለካከት ያለው ፓርቲም ይሁን ግል ህገ-መንግስቱ በፈቀደለት መንገድ ብቻ ከተንቀሳቀሰና አመለካከቱ የህዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ወደስልጣን ከመጣ እንደዛው በሚከተለው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እንደሚገነባና እንደሚመራ በግልፅ በመፅሃፉ ተቀምጧል::

4. ሌላው ያነሱት ደግሞ ‹‹ሰራዊቱ የጥቂት ሰዎች ‹‹ጠባቂ›› እንዲሆን – በተለያየ መንገድ በጭንቀት፣ በልመና የተደጋገመው ጸሎት አይሉት ምህላ በጣም እንደሚሰለች ይገባኛል፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡ እኔም ስልችት እያለኝ ደጋግሜ ያነበብኩት የመከላከያ ተቋሙ በምን መልኩ ከህገ-መንግስታችን ተጻራሪ ሆኖ እየሰራ መሆኑን እንዲያሳይ ነው እንጂ፡፡ መጽሐፉ ሕገ-መንግስታችንን በውል መጥቀስ የጀመረው በገጽ 87 ነው፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ “የቁርጥ ቀን” መከላከያ መሆኑን በተደጋጋሚ ካስረገጠ በኋላ በ2.1 ሕገ-መንግስታችን እንደ ሰራዊታችን ግንባታ መነሻ በማለት ማብራራት ይጀምራል፡፡ መዘባረቁን በማያሻማ ሁኔታ እየቀጠለ ፀረ ዲሞክራቲክ አስተሳሰብ ደግሞ ከደርግነት ባላነሰ መንገድ ሲገልጸው እንደገና “ኢህአዴግ ከሌለ ይህች ሀገር የለችም” በሚለው አባባል ሲያመላልሰው ይታያል›› በማለት ያትቱና ለዚህ ደግሞ በመፅሃፉ በገፅ 88-89 የተገለፀውን ሰፋ አድርገው ይጠቅሳሉ::

እዚህ ላይ በመጽሐፉ ላይ ህገ-መንግስት የሚለው ቃል አመኖሩ እንዴት ነው ከህገ-መንግስቱ በተፃራሪ መጓዙን ሊያሳይልዎት የሚችለው? ለመሆኑ ህገ-መንግስቱ በቁምነገሩ ሳይሆን በስሙ ሆነ እንዴ የሚለካው? በስሙ ነው ካሉ ደግሞ (በኔ እምነት ግን አይደለም) ህገ-መንግስት ቃል መነሳት የሚጀምረው በገፅ 21 እንጂ በ87 አይደለም:: በቁምነገሩ ነው ከተባለ ግን (መሆንም ያለበት) መጽሐፉ ሰራዊት ለምን እንደሚገነባ በማብራራት ጀምሮ የሰራዊት ግንባታ አላማው (ተፈላጊ ውጤት) በማስቀመጥ መነሻው ዘርዝሯል፡፡ እዚህም ዋና መነሻው ህገ-መንግስታችን ስለመሆኑ አስረግጧል ቀጥሎ ደግሞ አቅጣጫዎችን በሚገባና በስርዓት ደርድሮ አስቀምጧል:: ስለሆነም የህገ-መንግስቱ ስም መነሳት ባለበት ቦታ ላይ ተነስተዋል እንደመዝሙር በየቦታው ስለተነሳ ብቻ እነት ነው ብየም አላምንም:: ለነገሩ እርስዎም ያምናሉ አልልም ቀዳዳ ያለ ለማስመሰል እንዲጠቀሙበት ስለፈለጉ እንጂ:: በዚህም በሁሉም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ከህገ-መንግስቱም ይሁን ህገ-መንግስቱ መነሻ አድርገው የወጡት ፖሊስዎች፣ ስትራተጂዎና መመሪያዎች እንዳይፃረርና እንዳይጋጭ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ፅሁፍ ነው::

ለመሆኑ የጥቂት ሰዎች ጠባቂ እያሉን ያሉት እኛ የሚል ቃል በመግባቱ ነው ወይስ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የጥቂት ሰዎች ነው እያሉን ነው:: እኛ የሚለውን ቃል ከሆነ (በበኩሌ አይመስለኝም) እኛ ለምን እንደገባ ከፍ ብየ ገልጨዋለሁኝ:: ስለሆነም ኢትዮጵያ የምትከተለው አብዮታዊ ዲሞክራሲንና ደጋፊዎች ለማንሳት እንጂ እርስዎ እንደሚያስቡት አምርረው የሚጠሉዋቸው ሰዎች ማለት አይደለም:: አብዮታዊ ዲሞክራሲ የጥቂት ሰዎች ነው እያሉን ከሆነ ግን ተሳስተዋል ምክንያቱ እርስዎና መሰሎችዎ እንደ ምርጥ አጋጣሚ በምታዩት ምርጫ 97 ሳይቀር በህዝብ የተመረጠና በአሸናፊነት የወጣ አስተሳሰብ ነው:: እርስዎስ የጥቂት መሆኑ ምን ማረጋገጫ አለዎት ወይስ አሁን ትምህርት ከጨመሩ በኋላ የመጣብዎትን አርሶ አደሩን የማሳነስ አመለካከት አርሶ አደሩ ስላልተማረ የሚጠቅመውና የማይጠቅመው ለይቶ ስለማያቅና ስለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስለማያውቅ ነው የመረጠው ሊሉን ወይ ደግሞ በፅሁፍዎ እንዳሉት ፀረ-ህገመንግስት በሆነው የፀጥታ ሃይል ነው ያሸነፈው እያሉን ነው::

5. ሌላው ከፅሁፍዎ እንደተረዳሁትና ከሰራዊት ግንባታ መጽሐፍ ተችትዎ ወጣ ያለ የመሰለኝ፤ ግን ደግሞ የእርስዎ ዋናው መገለጫ የሚሆነው፤ እንዲሁም ጥላቻዎና ትችትዎ የትና ከማን ጋር እንደሆነ ወደገለጹበት ሀሳብ ልውሰድዎና እንዲታገድ የፈለጉት ምን እንደሆነ ላሳይዎት፡፡

* በፅሁፍዎ ላይ ‹‹ሶስት ሆነን ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታና ስለአንድ መሪ ስናወራ የልማት መሪም አርበኛም (Champion) ናቸው በሚል ተስማማን፡፡ አንዱ ተነስቶ የልማት አርበኛ ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲያዊ ሻምፒዮን ናቸው አለ፡፡ ሶስተኛው ተነስቶ “እስኪ አብራራው” አለው፡፡ በጥርናፈ (Centralism) ያምናል አለን:: አፈርን! ተሳቀቅን! ግን ስለዴሞክራሲ ያለው አመለካከት እስከዚያ ድረስ የወረደ መሆኑን በየቀኑ የምናየው ክስተት በመሆኑ አዝነን፤ ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው አልን›› ብለዋል፡፡

እዚህ ላይ፤ ማዘን ለሚያስቡላት አገር ምንም አያደርግላትምና አማራጭ ይዘው ቢታገሉ ይሻልዎታል እያልኩኝ ላሳስብዎ:: ከዚህ ውጪ ግን ይህ ሁሉ እያናገርዎት ያለውና ዋና ጥላቻዎ እዚህ ላይ ነው ደጋግመው ሰራዊቱ የጥቂት ሰዎች ጠባቂ ነው እያሉ የሚገልፁት የመለስና ተከታዮቹ ነው፡፡ መለስ ደግሞ የልማት እንጂ የዲሞክራሲ አርበኛ አይደለም እያሉን ነው፡፡ ሶስታችሁ መለስ ዲሞክራሲያዊ አይደለም ስላላችሁ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ያምናል ማለት አይደለም፡፡ የሚያስደነግጠውና የሚያጠራጥረው የኒዮ-ሊበራል አቀንቃኞች ዲሞክራሲያዊ ቢሉት እንጂ፤ ፀረ-ዲሞክራሲ ቢሉት የሚጠበቅ እንዲሁም ክብሩንና ተቀባይነቱን ከፍ የሚያደርግ ነው::

የልማት እንጂ የዲሞክራሲ አርበኛ አይደለም እያላችሁን ነው፡፡ ታድያ በአገራችን – እናንተም የመሰከራችሁለት – ልማት ከዲሞክራሲ ውጪ የሚመጣ ከሆነ፤ ለምን ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ እያላችሁ ትናገራላችሁ? እንጀራ ለማግኘት ከተቻለ የኢትዮጵያ ህዝቦች እኮ ራሳቸው አምርተው ራሳቸው እንዲችሉ ነው የሚፈልጉት:: ብቻ ይህ ልማትም የመጣው በዚህ ፀረ-ህገመንግስት በሆነው የፀጥታ ሃይል ነው እንደማትሉን ተስፋ አደርጋለሁ::

* ሌላው ማንነትዎና ጥላቻዎ ደግሞ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርእዮተ-ዓለም ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ እንደገለፁት በዚህ ፅሁፍዎም በግልፅ በሚከተለው መልኩ አስቀምጠዋል::

‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚል “ምትሓተኛ” አስተሳሰብ እንዳለና እጅግ እንደላቀ ልዩ ነገር “Mystify” ተደርጎ የማይተነተን፣ የማይታወቅ፣ ሰው በጭፍን እንዲያምነው የሚደረግ ሙከራ አሳሳቢ ነው›› እያሉን ይቆዩና፤ ትንሽ ሳይቆዩ ማለትም ፓራግራፍ እንኳ ሳይቀይሩ ደግሞ ‹‹እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ይሁን ሊበራል ዲሞክራሲ ሁሉም ካፒታሊሰታዊ ስርዓት ለመገንባት ዓላማ አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት ያውም እስከ “ነጭ ካፒታሊዝም” ተብሎም ነበር›› ይሉናል::

ምን ዓይነት መደናበር እንደሆነ ግራ ያጋባል:: እንዴ!? ሊበራል ዲሞክራሲ ካፒታሊዝም የመገንባት አላማ እንዳለው ከተረዳዎት ታድያ ጥያቄዎ የቱ ላይ ነው? ሊበራል ዲሞክራሲም አመሪካኖች ስላሉት እንቀበለው እንጂ እሱም ያልተነተነና የማይታወቅ ነው እንዴ? ሁለቱም ተመሳሳይ ዓላማ አላቸው ብለው ካመኑ ምኑ ላይ ነው ታድያ Mystify እያሉን ያለው? ይህ ጉዳይ ለራስዎም የገባዎት አይመስልም::

አዎ ትክክል ነዎት:: አብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ በለፀገው ካፒታሊዝም ለመግባት፤ እንደእኛ ባሉ ያላደጉ አገራት ሊበራል ዲሞክራሲ ጥገኛ አስተሳሰብና ተግባር የሚያስከትል እንጂ የሚያሳድግ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ ሃብትና ቴክኖሎጂ ያከማቸ የግል ባለሃብት ስለሚፈልግ:: በኛ አገር ሁኔታ ደግሞ ጉልበትና መሬት ነው ያለን የተሻለ ገንዘብም ቴክኖሎጂም ያለው በመንግስት ስለሆነ:: ስለሆነም ያለንን ሰፊ መሬትና ርካሽ ጉልበት ተጠቅመን ሃብትና ተክነሎጂ ማምጣት አለብን፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አማራጭ ሳይሆን ብቸኛ መንገድ ነው ተብሎ ተቀምጧል:: ካልሆነ ይህቺ አገር ልማትና እድገት አይታሰብም ነው ብሎ ያስቀምጣል::

እዚህ ላይ አይደለም በዚህ ምክንያት አብዮታዊ ዲሞክራሲ አያዋጣም ብሎ መቃወምና አማራጭ ማቅረብ ያባት ነው፡፡ አልተነተነም ምተሀተኛ ነው ብሎ በድፍን ማስቀመጥ ግን ከጭፍን ጥላቻና መደናበር አያልፍም:: እዘህ ላይ መንግስት በተመረጡ ሴክተሮች እጁን ሲያስገባ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ እየረዘመ ለሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር እያጋለጠ ነው ሊባል ይችላል:: መንግስትም በዚህ ጉዳይ ይስማማል፡፡ ግን አማራጩ ይህን በጋራ ታግሎ ማሸነፍ እንጂ ሊበራል ዲሞክራሲ ለዚች አገር አማራጭ ሊሆን አይችልም ብሎ ያምናል፡፡ በተግባርም እየሆነ ያለው ይኸው ነው:: ይህ ከደርግ ጋር ሊያመሳስለው የሚችል አመላካከት ሊሆን አይችልም::

ሌላ እኔ የሚያስገርመኝ ግን በተለይ ከ1993ቱ ከህወሓት ማ/ኮሚቴና ከሰራዊቱ ከፍተኛ አመራርነት ከወጣችሁ በኋላ እየሆናችሁት ያለውን ስመለከት፤ እነዚህ ሰዎች በስልጣን በነበሩበት ወቅት ሲፈፅሙት የነበረውን ነገር አሁን ተመልሰው ችግር ነበረ የሚሉት እውነትነቱ የት ላይ እንደሆነ አይታየኝም:: በረጅሙና እልህ አስጨራሹ የትግል ወቅት እስከ 1993 ምንም ሳትሉ የመጣችሁት ስልጣን ስለነበራችሁ ለስልጣን ስትሉ ሳታምኑበት ነው የመጣችሁት ማለት ነው እንዴ? የሚል ጥያቄም ያጭርብኛል:: ምክንያቱም በኦነግ ላይ የተወሰደው እርምጃ በራሳችሁ ፊርማና ትእዛዝ የተፈፀመ ሆኖ እያለ ኣሁን እየተነሳ ያለው ጥያቄ ይገርመኛል ወይስ እንደ አቶ ገብሩ አስራት መስቀል አደባባይ ወጥታችሁ ይቅርታ ለመጠየቅ መዘጋጃ ነው:: ይህ ነው ደግሞ ለዚህ በተደጋጋሚ የምታነሱት ህዝብ ፅድቁ ቀርቶበት በቅጡ በኮነናችሁት የሚያስብለው::

ማጠቃለያ

ሜ/ጀ አበበ የሚፈልጉት ሰራዊት ምንም ዓይነት ፖሊቲካዊ ግንዘቤ የሌለው የፖሊቲካ ስርዓቱ ባህሪያትና ጠቀሜታ የማያቅ በጭፍን የተባለውን ብቻ የሚሰራና ስለህዝብ አጀንዳ የሌለው የተነጠለ ባህታዊ እንዲሆን ነው የሚፈልጉት:: ይህን ደግሞ ፈፅሞ በየትኛውን ሁኔታና አገር የሌለ ራስዎ ስልጣን የመያዝ እድል ቢገጥመዎትም ያለዎትን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ሰራዊት እንደሚገነቡ የታወቀ ነው:: ይህ ፅሁፋቸው የሰራዊት ግንባታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚል መፅሃፍ እንደሽፋን ቀረበ እንጂ በአብዮታዊ ዲክራሲያዊ አስተሳሰብ የተቀረፀው የብሄራዊ ደህንነትን የውጭ ጉዳይ ፖሊስችን ከፍ ሲልም ህገ-መንግስቱም ከእገዳው እንደማያመልጡ የሚያሳይ ነው::

አገራችን የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ አገር ትሁንልን፡፡

አምላክ ከውሸት፣ ከማጭበርበርና መደናበር ይጠብቀን፡፡

******** 

[1] በጽሑፉ የተጠቀሰው የሜ/ጄነራል አበበ ተ/ሃይማኖት ጽሑፍ በሪፖርተር ጋዜጣ 15ኛ ገጽ ላይ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ ሪፖርተር ጽሑፉን በዌብሳይቱ ላይ ሳያትመው ቀርቷል፡፡ በመሆኑም ሆርን አፌይርስ ጽሑፉን ከጸሐፊው በማግኘት ተገቢውን አርትኦት በማድረግ ትላንተ ማተሙ ይታወሳል፡፡

9 Comments
 1. gutama

  ይህን የመሰለ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እዉቀት ይዘው እያለ ዲሞክራሲው ደግሞ ያልከውን ታእምራዊ ለዉጥ አምጥቶ እያለ ለምን በስደት ኬኒያ መኖር ፈለግ? አየህ ውሸት? የስደቱን ቦታ ለኛ ልቀቅልንና አንተ ወደ ወዳጅህ ገነት ግባ።ምን አስፈራህ ሰራዊቱ ምሽግህ ይሆናል።

  Reply
 2. tizibt

  ጸሃፊያችን እጅግ በጣም እናመሰግናለን ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ በሰስደተት ነው የምኖረው የሚለውን እባክዎን ያርሙ በስደት የሚኖር ሰው እንዲህ እንደርስዎ የተመቸው አይደለምና! ለዚህም ነው በሃገር ውስጥ ያለው የወገን ችግር ያልታየዎት እና ልማታዊ መንግስታችንን እጅግ በጣም ያሞካሹት ማን ያውቃል ተጠቃሚም ሆነው ይሆናላ በስደት ላይ ሆነው የሚያመላልስዎት ለማንኛውም ልማቱን የርስዎን ያህል ባላገዝፈውም መልካምነቱን አልክድም ነገር ግን በአጠቃላይ ሲታይ ኢፍትሃዊ ነው ከዚህ በላይ ስለ ልማቱ ማውራት አልፈልግም ምክንያቱም ጊዜው አይበቃምና
  በጀነራል አበበ ጽሁፍ ላይ ያደረጉት ትችት ላይ ግን እንደርስዎም ጠልቄ ባልጽፍ የሚከተለውን የርስዎን ጽሁፍ በድጋሚ እንዲያነቡት እና ሌሎችንም እንዲያጤኑት አደራ እላለሁ

  “የህዝብ ተሳትፎ በመገደብ፤ ስልጣን በጥቂት ገዢዎች ቁጥጥር ስር ገብቶ ህዝቡ ለአፈና፣ አድልዎና ፍትህ ማጣት ወዘተ የተጋለጠ እንዲሆን ለማድረግ የሚጥሩትን ሃይሎች ከህዝብ ጋር በመሆን መመከትና መታገል::”
  በእርግጥ ሰራዊታችን ይህንን ያደርጋልን????????????

  እግዚያብሄር ኢትዮጲያን ይባርክ አንድነትዋን ይመልስ
  ማስተዋልን ይስጠን አሜን!!!!!

  Reply
 3. Daniel S.

  ገለልተኛ ለመምሰል ያደረግኽው ጥረት አልተሳካልህም። ትግርኛ የመናገር እንጂ የመስማት ችግር የለብኝም” ነበር ያልከው?!?? ቂቂቂ… የጻፍከው በሙሉ በያንቀጹ ትግርኛ ትግርኛ እንደሚል እየነቀሰ ማን ባሳየህ?!
  ኬንያም ከሆነ ያለኽው አንድም አምባሳደር ስታፍ ነህ ወይም ስደተኛውን ሰላይ ነህ። ካልሆነም እውነት ለማስመሰል የተጠቀምክበት አፍንጫ ስር ያለሽ ንልሀት ነሽ።
  እውነቱን በእውነተኛ ማንነት ብትናገር ማ ምን ያደርግሀል በዲምክራሲ ሀገር!?!!

  Reply
 4. Tsion Hailay

  ይሄን ሁሉ እንቶ ፈንቶ፣ አንድ ሚሊ ግራም እውነት የማይወጣው እንድ ሜትሪከ ቶን ድሪቶ ስለደረትክ ግብህን የመታህ ይመስልሃል፡፡ ሲጀምር “ሰራዊት ስርዓቱን ማገልገል አለበት” የሚለውን አስተሳሰብ ትክክለኛነት ለማሳየት የያጣቀስከው የንጉሱን ስርዓት ነው፤ የንጉሱ ስርዓት ደግሞ ዲሞክራሲያዊ አይደለም፣ አይመጥንም ተብሎ ተወግዷል፤ ስለዚህ የወደቀ ስርአት አንስተህ ለመሞገት መሞከርህ ቀፎነትህን ያሳያል፡፡ ሲቀጥል “ሰራዊት ስርዓቱን ማገልገል አለበት” የሚለው አስተሳሰብ የፀረ-ዲሞክራሲ ስርአቶች አስተሳሰብ ነው፡፡ የጠቀስከው የንጉሱ ስርአት ደግሞ ፀረ-ዲሞክራሲ ነው፡፡ ህግ መንግስቱ ዲሞክራሲያዊ ነው ብለህ ካመንክ ሰነዱ ህግ መንግስቱን ይፃረራል የሚለውን ሃሳብ መደገፍ አለብህ፡፡

  Reply

ስለጽሑፉ ምን ይላሉ? አስተያየቶን ያካፍሉን፡፡