Dec 26 2014

የተጠለፈው ሔሊኮፕተር ፖለቲካዊ እንድምታ ምን ሊሆን ይችላል?

(ቢልልኝ ሀብታሙ አባቡ)

አንድ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሆነ ሔሊኮፕተር ተጠልፎ በኤርትራ ምድር ማረፉ በዚህ ሳምንት ተሰምቷል፡፡ የጠለፋውን አጠቃላይ አገራዊና አለም አቀፋዊ እንድምታ ለማየት ድርጊቱ ከግለሰቡ ስሜት የሚመነጭ ተራ የዜጋ ክህደት ነው ወይስ በአገራቱ መካከል በተፈጠረ መሻከር የተነሳ የፖለቲካ ትግላቸው አንድ አካል የሚለውን ለይቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ መሰረት በቅድሚያ የድርጊቱ ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ጠቃሚ ነው፡፡ የድርጊቱን መነሻ ለማወቅ ፓይለቱ ለድርጊቱ ያነሳሳው የራሱ የግለሰቡ ተራ የሆነ የግለሰብ ስሜት ነው ወይስ ከጀርባው የተለየ ተልዕኮ አለ የሚሉትን ሁለት መነሻዎች ለይቶ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሰረት ከሁለቱ አንዱን መምረጥ የሚያስችሉ የአሳብ መነሻዎችን ማየት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ለዚህ ዋናው መነሻ ግለሰቡ ከሌሎች አገሮች ኤርትራን ለመድረሻ የመረጠበት ምክንያት እና ግለሰቡ የኤርትራን ድንበር አቋርጦ ሲሄድ በሰላም መስተናገዱ ምንአልባት ግለሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ ከኤርትራ መንግስት ጋር ረዘም ላለ ጊዜ በድብቅ ሲሰራ እንደቆየ ሊያመላክት ይችላል፡፡ የኤርትራ መንግስት እንደጠላት ከሚያያት አገር የጦር ሄሊኮፍተር ድንበሩን አቋርጦ ሲገባ የአፀፋ ምላሽ አለመስጠቱ አስመራው አስተዳደር ድርጊቱ እንደሚፈጸም ቀደም ብሎ ያውቅ እንደነበረ ሊያመላክት ይችላል፡፡ እነደዚህ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ጠላት ያለው በራሱ ጉያ እንጂ በሚሊየን ኪሎሜትር ርቀት ላይ እንዳልሆነ ያመላክታል፡፡ የተጠናከረውን የኢትዮጵያ መንግስት ደህንነት አልፎ ተልዕኮውን ማሳካቱ የኤርትራ መንግስት በጉዳዩ ላይ ለረጅም ጊዜ ሲሰራበት የቆየ ተልዕኮ እንዳልቀረ ያመላክታል፡፡ Photo - Hijacked Ethiopian Mi 35 Attack Helicopter

የኢትጵያ መንግስት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?

በዋናነት ውድ ዋጋ ያለው ሀብት በመወሰዱ ሳይሆን በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ረጅም ጊዚያትን ያስቆጠረ የሻከረ ግንኙነት ሁለቱም ገዥዎች በመካከላቸው ባሉ ማህበራዊና ታሪካዊ መሰረቶች የተነሳ በተፈጠረ “የአወቅኩሽ-ናቅኩሽ” ስሜት ጋር ተደማምሮ የኢትዮጵያን መንግስት ከፍተኛ እልህ ውስጥ ሊያስገባው የሚችል ክስተት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሰት ችግሩን ለመፍታት የሚጠቀመው ስትራቴጂ በጣም ዝቅተኛ መስዋዕትነት ከሚያስከፍሉ እርምጃዎች ወደ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሊያስከፍሉ የሚችሉ እርምጃዎች ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው እርምጃ በጭምምታ እንደሚሰማው ንብረቱ በድርድር ማስመለስ ሊሆን ይችለል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጪው አለም ብዙም ደንታ ለሌለው የአስመራው አስተዳደር ጥያቄውን በቀላሉ ሊቀበል ይችላል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ የመጀመሪው እርምጃ ካልተሳካ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሊወሰድ የሚችለው ሁለተኛው እርምጃ በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ የፖለቲካ መድረኮች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የአስመራውን አስተዳደር በዲፕሎማሲ በማዳከም ውሳኔውን የሚቀይርበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ያም ሆኖ አለም ኤርትራን ከሚፈልጋት በላይ የአስመራው አስተዳደር አለምን አይፈልጋትም በሚል መውሰድ የሚቻል በመሆኑ የሻቢያ ደንታ ቢስነት ለድርድር አቅም ሊሆንለት ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ የኢትዮጵያ መንግስት ጫና ይፈጥርባቸዋል ተብለው የሚገመቱ የዲፕሎማሲ መንግዶች በሚፈለገው መልኩ የኤርትራ መንግስት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር አይችሉም፡፡ እነደዛ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የራሷን ዜጎች በማስታጠቅ ከማጥቃት ጀምሮ በቀጥታ ጦርነት እስከማንበርከክ ድረስ ሊደርስ የሚችል የመጨረሻውን እርምጃ ለማውሰድ ሊገደድ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ጦርነቱ ከመገባቱ በፊት ከኤርትራ ይልቅ በኢትዮጵያ በኩል በቅድሚያ የሚታዩ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

የመጀሪያው ጉዳይ ከኤርትራ በከፋ መልኩ ኢትዮጵያ ለውጪ ጠላት እጅግ በጣም ተጋላጭ የሆነች አገር መሆኗ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በሶማሊያ በቋፍ ያለው የደህንነት ጥያቄ ራሱን የቻለ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከአባይ ልማት ጋር በተያያዘ ከኤርትራ ጋር የምታደርገው ግብግብ የግብፅን ተሳትፎ ሊጋብዝ የሚችልበትን እድል ሊከፍት ይችላል፡፡ በአገር ውስጥ የተጀመሩት የልማት ስራዎች ከፍተኛ ወጨ የሚጠይቁ በመሆናቸው ከኤርትራ ጋር ጦርነት መግባቱ እንደአላስፈላጊ ወጪ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በሌላ መልኩ ከታዬ ደግሞ ኢትዮጵያ አሁን ባላት አለም አቀፋዊ የጦርነት ተሳትፎ በምስራቅ አፍሪካ ጠንከር ያለ የጦር ሀይል ማጎልበቷን ሊያመላክት ስለሚችል ወደ ጦርነቱ ለመግባት ድፍረት ሊሰጣት ይችላል፡፡ የኤርትራ መንግስት በጎረቤት አገራት ያለው ጥሩ ያልሆነ ግንዛቤ ሊጎዳው የሚችልበት ሰፊ እድል አለ፡፡ በዚህ ደረጃ ችግሩን ለምፍታት ከተንቀሳቀሱ ቀጠናው ወደለየለት የትርምስ አደጋ ሊገባ አንደሚችል በአለም አቀፍ ማህበረሰቦች ግምት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር በቀጠናው ላይ ፍላጎት ያላቸው አለም አቀፍ አገራት ተሳትፎ ሊያደርጉ የሚችሉበትን እድል ሊፈጥር ይችላል፡፡

——-

1 Comments

ስለጽሑፉ ምን ይላሉ? አስተያየቶን ያካፍሉን፡፡