የፀረ ብዙሕነት አክቲቪስቶች ታክቲካዊ አጀንዳ

(አሉላ ሰለሙን)

ጃዋር መሐመድ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ የጸረ ብዙሕነት ፖለቲካል አክቲቪዝም (ancient Ethiopian anti-diversity political activism) ጋር አብሮ መስራት ይቻል እንደኾን ብሎ ኢኒሸቲቩን በመውሰድ የሙከራ ሥራ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ከአንድ ሁለት የኢሳት ቲቪ መታየት (tv show appearance) በኋላ ሂደቱ ብዙም ሳይጓዝ ተጨናገፈ። ምክንያቱም ጃዋር ኦሮሞ ፈርስት ነኝ። ኢትዮጵያዊነት በኃይል የተጫነብኝ ማንነት ነው።” ብሎ በአልጀዚራ ስትሪም ውይይት ቀርቦ በይፋ አወጀ። በዚህም የተከፉ የጸረ ብዙሕነት ፖለቲካል አክቲቪስቶች በጃዋር ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ከፈቱ። የብሔር ማነንት፣ ቋንቋ እና ባህል ላይ ያነጣጠሩ ዘለፋዎች አልበቃ ብሎ እስከ ክስ እንመሰረትበታለን ዛቻ ድረስ ሄዱ። ይህን ተከትሎ፣ ጃዋር የአብሮ መስራቱ ሂደት እንደማይቀጥል በግልጽ አሰረድቷል። አሁን ኢትዮጵያ የምትከተለው ብሔር መሰረት ያደረገ የክልሎች አከላለል የፌደራል ስርዓት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ ወዘተ የመግለጽ እንዲሁም ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል መብትን ካልተቀበሉ አብሮ መስራት እንደማይቻል በተጨማሪም የጥንታዊት ኢትዮጵያ መሪዎች በብሔሮች ላይ የፈጸሙት በደል ስሕተት መኾኑ አምነው መቀበል እንዳለባቸው እንደ ቅድመ ኹኔታ አስቀመጠ።

የምንልክ የ100 ዓመት መታሰቢያ በሰማያዊ ፓርቲ ቤት መከበር እና ያንን በዓል በማስመልከት በአንድ መጽሔት ላይ አንድ ታዋቂ አርቲስት ምላሱን ወለም አለው። “ምንልክ ያካኼደው ጦርነት ለእኔ ቅዱስ ጦርነት ነው” በማለቱም የተነሳ በጃዋር በሚመራው ስብስብ እና በጸረ ብዙሕነት አክቲቪስቶች ሌላ እሰጥ አገባ ተነስቶ የአርቲስቱ የሙዚቃ ኮንሰርት እስከ መሰረዝ ተደረሰ።

በዚህ ያልቆመው መሳሳብ ቀጥሎ፣ የመጻፍ ሐሳብን የመግለጽ መብት እና ሁከት ሊያነሳሳ የሚችል የጥላቻ ንግግር (hate speech) ለይተው በማውያቁ የኛ ሀገር አንዳንድ ደናቁርት “የነጻ” ፕሬስ ጋዜጠኞች በአንድ መጽሔት ላይ የኦሮሞ ብሔርን የሚነካ በጻፉት ጽሑፍ ነገሩ ተካረረ። የጃዋር ስብስብ እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጸረ ብዙሕነት አክቲቪስቶች ግኑኝነት እጅጉን ሻከረ። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቁጣም አስከተለ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር የመላ ኢትዮጵያ የስፖርት ውድድር ባህር ዳር ላይ የተደረገው። የከተማውን ነዋሪ ሕብረተሰብ በማይወክል ኹኔታ የጸረ ብዙሕነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ጥቂት ስዶች በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ማንነት የሚነካ አጸያፊ ቃላት ተጠቅመው ነገሩን ወደ ጠርዝ ገፉት።

ሂደቱ ቀጥሎ፣ ኹኔታዎች እንዲኽ በተጋጋሉበት የጸረ ብዙሕነት ፖለቲካል አክቲቪስቶች ስሕተቶችን አምኖ ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ በስድቡ ገፉበት። የተለያዩ አንቱታ ያተረፉ አዛውንት ምሁራን ጸሐፊዎች እና የጥነታዊት ኢትዮጵያ የጸረ ብዙሕነት አክቲቪዝም አሳልጣኞች (mentors) ሳይቀር ኦሮሞን የሚያንቋሽሹ ጽያፍ ጽሑፎች በመጻፍ ተጠመዱ። መስፍን ወልደ ማርያም እና ጌታቸው ኃይሌ ከምሁራን ተክሌ ይሻው ከፖለቲከኞች፣ ሄኖክ የሽጥላ ከገጣሚዎች የስድብ ናዳቸውን ማውረዱን ተያያዙት። እነዚህ ሰዎች አሁን ካለው የኢህአዴግ መንግስት ጋር ያኳረፋቸው የብሔሮች መብት እውቅና መስጠት በተለይ የኦሮሚያ ክልል አሁን የያዘው ክልላዊ ቅርጽ ዋናው ምክንያት እንደኾነ ጃዋር እና ተከታዮቹ ጠንቅቅው ያውቃሉ። የተክሌ ይሻውን “ወያኔ የሰጣቸው ክልል ነው። መሬቱ የኛ ነው።” ንግግር ልብ ይሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር፣ የአዲስ አበባ እና አዋሳኝ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የተቀናጀ የልማት ማስተር ፕላን ውዝግብ የተነሳው። የውዝግቡ መነሻ በዋናነት የኦሮሚያ ዞን ከተሞችን መሬት፣ አስተዳደር እና ተያያዥ ጥቅሞች ወደ አዲስ አበባ ይገባል በሚል ስጋት ነበር። በነገራችን ላይ የጸረ ብዙሕነት አክቲቪስቶች በማስተር ፕላኑ ደስተኞች ነበሩ። አዲስ አበባ ሰፍታ የኦሮሚያ አዋሳኝ ዞኖቹን በመጠቅለል በአስተዳደር፣ በጥቅም በቋንቋ እና ማንነት ብትይዝ “እሰይ ስለቴ ሰመረ” ነው ለእነሱ። ነገር ግን በማሰተር ፕላኑ ላይ ሁለቱም ጎራዎች የእነ ጃዋርም ኾነ በጸረ ብዙሕነት የተያዘው አቋም ስሕተት ነበር። ሁለቱም በያዙት የቆየ መካረር እና በዚሁ ጉዳይ በተያዘ የተዛባ አረዳድ ነገሮች ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ኼደው በክፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኦሮሞ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ። የተማሪዎቹ ሰልፍ ሕጋዊ ባይኾንም ፍጹም ሰላማዊ ነበር። በሰላማዊ ሰልፉም ተማሪዎች በዋናነት ፣ የምንልክ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በሰማያዊ ፓርቲ መከበር፣ አርቲስቱ ምንልክን አስመልክቶ ያደረገው ንግግር፣ ሎሚ የተባለ የግል ፕሬስ መጽሔት ላይ የተጻፈ፣ በባህርድር የስፖርት ዝግጅት ላይ ማንነት የሚነኩ አጸያፊ ንግግሮች ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ አተኩረው ተቃውሞቸውን አሰምተዋል። ነገር ግን በሂደት በተለይ በአምቦ ከተማ ከዩንቨርሲቲው እና ትምህርት ቤቶች ቅጥር ጊቢ ወጥቶ በመፍሰስ ሰላማዊ ሰልፉ ወደ ለየለት ሁከት ተቀየረ። በዚህም የተነሳ ብዙ ንብረት ወደመ። የመንግስት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ሂደቱን ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃ የሰው ህይወትም አለፈ።

ከዚህ ሂደቱ ቀጥሎ በውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች የተቃውሞ ሰልፎች አካሄዱ። የጸረ ብዙሕነት ከአዲስ አበባው ማስተር ፕላንም ኾነ እነሱ በቀሰቀሱት ግጭት በተፈጠረው ሂደት ላይ ተቃውሞ ባለማሰማታቸው ከጃዋር ከፍተኛ ወቀሳ አስተናገዱ። በነገራችን ላይ በኦሮሚያ ሁከት እንዲነሳ ካደረጉ ምክንያት አንዱ የኾነው ጋዜጠኛ ክስ ተምስረቶበት እስር ላይ ይገኛል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጸረ ብዙሕነት ፖለቲካል አክቲቪስቶች ‘ጋዜጠኛው ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብቱን ነው’ የተጠቀመው በማለት እየተከራከሩለት ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሰሞኑን በአሜሪካ ቆይታው ሕጋዊ ኦሮሞነቴን አረጋግጫለኹ በማለት ይፋ ያደረገው ኤርትራዊው ደራሲ ተስፋይ (ገዳ) ገብረአብ  ኦሮሞን አስመልክቶ በጻፈው ጽሑፍ የጸረ ብዙሕነት አክቲቪስቶች የስድብ እና ተቃውሞ ውርጅብኝ ሰለባ ኾኗል። በዚህም የተነሳ በጃዋር ተከታዮች እና የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጸረ ብዙሕነት አክቲቪዝም መሃከል ሌላ የከረረ ጸብ እና ጉዳት ደረሰ። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ነው የሂደቱ አንድ አካል ኾኖ የአመንስቲ ኢንተርናሽናል “ኢትዮጵያ ኦሮሞን ትበድላለች” የሚል ሪፖርት ተከትሎ በከፈቱት የ “ኦሮሞ በመኾኔ” ዘመቻ በመሃከላቸው የተፈጠረውን ጉዳት ለማስተመም የጸረ ብዙሕነት አክቲቪስቶች የዘመቻው ባለቤት ኾነው የቀረቡበት ሂደት የተከሰተው።

ጃዋር ያስቀመጣቸው ቅድመ ኾኔታዎች በይደር ተከድነው ሳይነኩ እንደተቀመጡ ናቸው። በዚያ ዙሪያ የጸረ ብዙሕነት አክቲቪስቶች ከጃዋር ጋር ከተስማሙ ከእኔም፣ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረ ሰቦች ከኢህአዴግ ተስማሙ ማለት አይደል። ሂደቱ ወዴት ይወስደናል? አብረን አንይ።

ሰላም።

——-

Alula Solomon

more recommended stories