(ዮናስ ዘኦሎምፒያ)

ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ግንኙነት በውጭ የሚገኘው ኃይል በአጠቃላይ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ አንደኛው ክፍል የኢትዮጵያን ክፋት የማይመኝና በጀመርነው የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ እንዲሳካልን የሚፈልግ ነው፡፡ ይህ ክፍል በሁሉም የዓለም ማዕዘናት የሚገኝ ሲሆን፣ አንዳንዱ ከልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ሌላው ከልማታዊ አቅጣጫ፣ ሌላው ደግሞ ከሊበራል አስተሳሰብ በመነሳት ነጻነታችንን አክብሮ ቢቻል ከየራሱ አቋም ጋር በሚጣጣም አቅጣጫ እንድንጓዝ የሚፈልግ ነው፡፡ በመሆኑም የአመለካከት አንድነትም ሆነ ልዩነት ቢኖርም ባይኖርም ከዚህ ክፍል ጋር በሰላምና በጋራ ጥቅሞች ዙሪያ መስራት እንደሚቻል መቀበል ይቻላል፡፡

ከዚህ ለየት ባለ አኳኋን የሚታየው የአክራሪ ኒዮ ሊበራል ኃይሉ ሲሆን፣ ይህም ከራሱ መጽሐፍ በስተቀር ሌላ እንዲነበብና መመሪያ እንዲሆን የማይፈልግ፣ የራሱን መመሪያ በሌሎች ላይ በውድም በግድም መጫን የሚፈልግ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በመሆኑም ስለ ዓለም አቀፍ የቀለም አብዮት ስናስብ አንቀሳቃሽ ሞተሩ ይህ ኃይል እንደሆነ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ይህ አክራሪ የኒዮ ሊበራል ኃይል ዓለምን በራሱ አምሳል ለመቅረጽና ለእርሱ ብቻ የምትመች እንድትሆን ለማድረግ ሁሉንም ዓይነት ማስገደጃ መሳሪያዎች መጠቀም የለመደ ነው፡፡ የማስገደጃ መሳሪያ ከመጠቀሙ በፊት በማባበል ከተሳካለት በዚሁ ተማምኖ የበላይነቱን ያረጋግጣል፡፡ ይህ አልሰራ ካለው ደግሞ ኃይልን ከዚህም አልፎ ቀለም አብዮትን እንደ ዋነኛ ማስፈጸሚያ ይጠቀምበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ትክክለኛም ይሁን የተሳሳተ የራሳቸውን አቅጣጫ መከተል የመረጡ አገሮች ሁሉ ነጻ መንገድን በመምረጣቸው ብቻ ይህን የመሰለው አብዮት ሲቀጣጠልባቸው ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የቀለም አብዮት አብዛኛውን ጊዜ ከምርጫ ወቅቶች ጋር ተያይዞ የሚቀሰቀስ ቢሆንም አልፎ አልፎ ከምርጫ ውጪ ከሚከሰቱና በቀለም አብዮተኞች ዘንድ መልካም አጋጣሚ ተደርገው ከሚወሰዱ ምርጫ ነክ ያልሆኑ ቀውሶች ጋርም ተያይዞ የሚቀሰቀስበት አጋጣሚ አይታጣም፡፡

ለምሳሌ በቻይና ከኦሎምፒክ በፊት በቲቤት ጥያቄ ሽፋን የተቀሰቀሰው የክሪምሰን አብዮት ሰሞንኛ የነበረው የዩክሬን አብዮትና በሀገራችንም ከአክራሪነት ጋር ተያይዞ ለመሞከር የታለመውና ግና በጥንስሱ የተቀጨውን አብዮት የመሳሰሉቱ በዚህ ክልል እንደሚታዩ በመስኩ ጥናት ያደረጉ ሰዎች ይገልጻሉ፡፡ ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን አጠቃላይ የቀለም አብዮትን ሳይሆን ከምርጫ ጋር የተያያዘውን የቀለም አብዮት የሚመለከት በመሆኑ ከራሳችን ምርጫ ጋር ተያይዞ የውጭ የቀለም አብዮተኞች እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ወደ መመልከት እናምራ፡፡

ማስረጃ አንድ

የተፈጥሮ ሀብትን በትክክለኛ መንገድ ለሕዝብ ጥቅም መዋሉን በመከታተል ለሀገራት እውቅና የሚሰጥ ‹‹ዘ ኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ትራንስፓረንሲ ኢንሺየቲቭ(the extractive Industries Transparency initiative – EITI) የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም አለ፡፡ ይህ ተቋም የተመሰረተው በቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እ.ኤ.አ. 2003 ነው፡፡ ዋና አላማውም በተፈጥሮ ዘይት፣ በጋዝና በማዕድን ልማት ዘርፍ ግልፅነት በማስፈን ሙስናን መዋጋት ሲሆን፣ አባላቱም መንግሥታት ሲቪል ማህበረሰቡና የማዕድን ኩባንያዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያም የዚሁ የዓለም አቀፍ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግልፅነት ኢኒሽየቲቭ አባል ለመሆን እ.ኤ.አ በ2010 ጥያቄ ብታቀርብም «መንግሥት ያወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ሲቪል ማህበረሰቡን የሚያሰራ አይደለም» በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎት እንደነበር ይታወሳል፡፡ እርግጥ አሁን ነገሮች እየተስተካከሉ በመሆኑ ወደ ሥራው እየተገባ ቢሆንም ይህንን በመከተል ኢትዮጵያ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ያወጣችው አዋጅ እራሷን ከዓለም አቀፉ አክራሪ የገበያ ኃይል ለመከላከልና እራሷን ከቀለም አብዮት ለመታደግ እንዲቻላት እንጂ በእርግጥም ሥራንና ድጋፍን እንዲሁም ትክክለኛውን የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ሥራዎች ታሳቢ አድርገው ለመጡ ኃይሎች ሁሉ በሯ ክፍት እንደሆነ በተደጋጋሚ አረጋግጣለች። ይህንኑ የኢትዮጵያን ፅኑ አቋም የተረዳውና በእርግጥም ቀደም ብሎ ኢኒሽየቲቩ የነበረው ግንዛቤ የተሳሳተ እንደነበር በማመን ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበለትን ጥያቄ ለመቀበል እያቅማማ ነበር። በዚህ ጊዜም፣ በሀገራት በሚደረጉ የቀለም አብዮት እንቅስቃሴዎች ላይ ከላይ በተመለከተው አግባብ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ስም እጁን የሚያስረዝመው ሂዩማን ራይትስዎች የተባለው ተቋም ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያ ለኢኒሽየቲቩ ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ ይደረግ ዘንድ ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡

በባህር ላይ በሚዝናኑ አባላት የተሞላው ተቋም ባላየውና ባላረጋገጠው ስለአላማው ሲል በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና የመናገር ነፃነት አፈና ስም ኢትዮጵያን የወቀሰው በጭፍን ነበር። ለገበያ አክራሪነት በራቸውን በዘጉ ሀገራት ላይ ቢዘባበትም፤ አሁን አሁን ግን እየተነቃበት በመገኘቱና አንዳንዴም የወረወራቸው ጠጠሮች ነጥረው ወደራሱ እየተመለሱ መሆናቸው ይመስላል ሰሚ እንዲያጣ ምክንያት ሆኖበታል። በመሆኑም ኢትዮጵያን በተመለከተ ለኢኒሽየቲቩ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆኖ ኢትዮጵያም ሂዩማን ራይትስዎች በሚለጥፍባት ሳይሆን በተግባር ያስመሰከረችው ሥራ ተገልፆ ጥያቄዋ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡

ማስረጃ ሁለት

ዘገባውን ያስነበበው የቀለም አብዮት አራማጅ ሀገራት አራጋቢና ባለቤትነቱም ለገበያ አክራሪነት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የሌላቸው ምዕራባውያን ቱጃሮች የሆነው ፋይናንሻል ታይምስ ነው ።ጥናት አደረገ የተባለው ተቋም ደግሞ የምዕራባውያኑ የገበያ አክራሪ ኃይሎች ማዕከል የሆነው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህ ተቋምና ጋዜጣ «በአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ» መርሆ ስለቀለም አብዮት ሰራን ያሉትና ያስነበቡን ነገር እስከዛሬ የት ከርመው ነው የሚያሰኝ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ጥናታቸውና ዘገባው የተመለከተው ሀገር አንድ ያደረገውን ብሄራዊ መዝሙራችንን (የህዳሴ ግድባችንን) በተመለከተ ስለሆነ፡፡ «ታላላቅ ግድቦችን በመስራት ላይ የሚገኙ ታዳጊ ሀገራት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል፡፡» በሚል ዳርዳርታ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲን ጠቅሶ ዘገባውን የጀመረው ፋይናንሻል ታይምስ በኢትዮጵያ ካለው የግልገል ጊቤ ሦስት ጀምሮ እስከ ብራዚሉ የአማዞን ቤሎሞንቴ ያሉ የግድብ ፕሮጀክቶች «በርካታዎችን ከመኖሪያቸው የሚያፈናቅሉ ለብዝሃ ህይወት አደጋም እንዲጋለጡ የሚያደርጉ ናቸው» ሲል ገልጧል፡፡

የህዳሴው ግድብ በተጀመረና ‹‹እኛው ባለሙያ፣ እኛው የፋይናንስ ምንጭ፣ እኛው ግንበኛና መሐንዲስ ሆነን እንሰራዋለን›› አዋጅ ሰሞን የተባለው ይህ «ምክር ተኮር»የልብ ትርታ ማዳመጫ፣ ዛሬም እየተባለለት ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ መስራት መቻላችንን በሚያረጋግጥ ደረጃ ላይ የደረሰው የህዳሴ ግድብ እየገሰገሰ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን«የትም አይደርስም» የሚለውን የግብጽ ፕሮፓጋንዳና ፀረ ልማታዊ አስተሳሰብ ተንተርሰው የተነዙት ወሬዎች መክሸፋቸው በተረጋገጠበት በአሁኑ ወቅት ግብፅ የጀመረችውን ኢፍትሐዊና ያረጀ ያፈጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከመጪው ምርጫ ጋር አያይዘው ጉዳዩን ለቀለም አብዮት የሚያመቻቹ ፅንፈኛ የገበያ አክራሪዎችና የዜሮ ድምር ፖለቲካ ስብስቦች ያሻቸውን እያሉ ነው። ምንም ቢሉ ግን የትም የማያደርሳቸው እንደሆነ የሚያረጋግጡ ወሳኝና በግልፅ የሚታዩ ሁነቶች ሞልተዋል፡፡

ጉዳያችን ግልጽ ይሆን ዘንድ ወደኋላ መለስ ብለን ደግሞ የቀለም አብዮት አጋፋሪዎቹን የምርጫ 2002 የቀለም አብዮት እንቅስቃሴ እናስታውስ። የመጀመሪያ ተኩስ ሂውማን ራይትስዎች ‹‹በኦጋዴን ባልታወጀ ጦርነት በጅምላ ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው›› በማለት ባቀረበው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውንጀላ መልክ የቀረበ ነበር፡፡ በመቀጠልም የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የጋዜጠኞች መብት አስጠባቂ ነን ባይ ተቋማት ወዘተ… ከየጠቅላይ መምሪያቸው ተመሳሳይ ውንጀላ በማሰማት ህብረተሰቡን ከሚያየውና ከሚያውቀው እውነታ በተለየ የፈጠራ ወሬ ቅሬታ እንዲያድርበትና ለወጠኑት የቀለም አብዮት በመሳሪያነት የሚያገለግል እንዲሆን መንቀሳቀሳቸው አይዘነጋም፡፡

በዚህ የተስፋ መቁረጥ ሁኔታ ውስጥ የገባው የውጭው የቀለም አብዮተኛ ኃይል ጊዜ ጠብቆ ምርጫ 2007 እየተቃረበ በሄደበት በአሁኑ ጊዜ በግላጭ የምርጫውን ውጤት የማስቀየር ፋይዳ ይኖራቸዋል ብሎ ያመነባቸውን ርካሽ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎች ወደመጠቀም አምርቷል፡፡ እራሳቸውን በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ቅፅሎች አስውበው ማቅረብ የለመዱት ዓለም አቀፍ መያዶችም ከየጎራቸው ተጠራርተው ሰፊ ዘመቻ ለማካሄድ በማሟሟቅ ላይ መሆናቸውን የሚያሳብቁ መግለጫዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ከውጭና ከውስጥ በተቀናጀ አኳኋን በመካሄድ ላይ ያለው ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አላማው ድንገት የሚቻል ቢሆን በአንድ ወቅት ሊካሄድ ለታሰበው የቀለም አብዮት ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማንጠፍ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ከነባራዊው ሁኔታ ያልተገናዘበና የኢትዮጵያን በጎ በማይመኙ ኃይሎች ታቅዶ እየተካሄደ ያለ ዘመቻ በተጨባጭ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻለ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡

የቀለም አብዮተኞች በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለውን የዴሞክራሲና የነፃ ገበያ ሥርዓት ግንባታ እያወቁ ግፊት የማድረጊያ ሌሎች ስልቶችን በመጠቀም እንዲዘምቱ ያደረጋቸው ጉዳይ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለዚህ ዓይነቱ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የዳረጋት ምክንያትስ ምን ይሆን? ብሎ ጉዳዩን ለመረመረ ሰው ጉዳዩ ከሥርዓቱ ነፃ ገበያ አለመሆን ወይም ከዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እጦት ጋር እንደማይያያዝ ለመገንዘብ አይቸግርም፡፡

የቀለም አብዮት ኃይሎች በኢትዮጵያ እጃቸውን አስገብተው እንዲፈተፍቱ የሚያደርጋቸው ዋናው ነገር በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እጦት አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ሁለት አስርት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአስተማማኝ መሰረት ላይ እየተገነባ ነው። ጉዳዩ ሰብዓዊ መብት የማስከበር አስፈላጊነት የቀሰቀሰው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብ ሳትጠብቅ በህዝቦቿ ትግል ሰብዓዊ መብትን አስከብራለችና፡፡

ለምርጫ 2007 የታለመው የቀለም አብዮት እንዳይሳካ የሚያደርገው ሁለተኛው ምክንያት የአገራችን ህዝቦች ከ97ቱ የከሸፈ ሙከራ በቂ ትምህርት ወስደው ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ውድድር ብቻ ራሳቸውን ያዘጋጁ መሆናቸው ነው፡፡ በ97 ምርጫ ላይ የቀለም አብዮተኞቹ ህዝቡን አነሳስተው ብዙ ጥፋት ካደረሱ በኋላ ሁኔታው በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጓል፡፡ እንደሚታወሰው የቀለም አብዮተኞቹ ህዝቡ የከፈለውን መስዋዕትነት ከፍሎ በኃይልና በአመጽ ወደ ቤተ መንግሥት እንዲያስገባቸው በመፈለግ በቆሰቆሱት ሁከት ሳቢያ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና ለሕግ መከበር ሲታገሉ የነበሩ የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ 193 ያህል ወገኖች ክቡር ሕይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ሆነዋል።

ይህ ሳይበቃ ህዝቡን አንዴ ሱቅ አትክፈት፣ ሥራ አትውጣ፣አትገበያይ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ ቀብርና ፍታት አብረህ እንዳትቆም እያሉ ለማነጣጠል ከንቱ ሙከራ በማድረግ ለጥፋት ብቻ እንደተዘጋጁ አስመስክረዋል፡፡ ህዝቡ ከዚህ ሁሉ የወሰደው ትምህርት ቢኖር አንዳንድ ተቃዋሚዎቹ በተሳሳተ መንገድ የሚነጉዱ እንጂ ለለውጥ ያልተዘጋጁ መሆናቸው ነበር። ስለዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ይሄን ስም አድሰው ለዴሞክራሲና ለሕግ መርሆ ሊገዙ ይገባቸዋል።

አሁን ባለንበት ደረጃም የተቃዋሚው ስብስብ እገሌ….. የተባለ ፓርቲ ከእገሌ….. ድርጅት(ፓርቲ ጋር አንዴ «ለመጣመር»፣ሌላ ጊዜ ደግሞ «ለመዋሃድ»፣ይህ አልሆንላቸው ሲል ደግሞ «ግንባር» አለያም «መድረክ» ወይም «ህብረት» ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው የሚለው ዜና በቅጡ ወደ ሕዝቡ ጆሮ ሳይዳረስ፣ የስምምነታቸው መፍረስና የእርስ በርስ መወነጃጀላቸው ጉዳይ ቀድሞ ይደርሳል። የጋራ ስምምነታቸው ለበጎ ሆኖ በጠራ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ መርህ ላይ የተመሰረተ የነጠረ የፖለቲካ ፕሮግራም ኖሮአቸውና ለሕዝቡም ጥሩ አማራጭ ሆነው ቢቀርቡ ይህ ሁሉ ጉድ ባልተሰማ ነበር። ግን እሱ እየሆነ አይደለም። ሁሉም ራሱን ይፈትሽ።

*********

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – ሐምሌ 2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories