የኦሮሚያ ፖለቲካ እና የኢህአዴግ ‹‹K ካርታ››

(ታምሩ ሁሊሶ)

1. ትልቁ ግንድ

በጠበበው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ አንድ ̊ትልቅ ግንድ̋̊ ̋ ተጋድሟል፡፡ ተጫዋቾቹ ያን ትልቅ ግንድ በስምምነት ከሜዳው ለማውጣትና ዳር ማስያዝ አልቻሉም፤ገሚሱ ይህን ግንድ ተባብረን ዳር ካላስያዝን ጨዋታው አይሰምርልንም እኛም እንወድቃለን ሲል ሌላው ግድየለም እንዲያውም ግንዱ ያስፈልገኛል፤ በብልሃት ለመጫወት ያስችለኛል ይላል፡፡ አንዳንዱ ደሞ የግንዱን መኖርም መርሳት ወይ ደሞ ችላ ማለት የሚፈልግ አለ፡፡ እንዲያም ሁኖ አልፎ አልፎ ግንዱ የሚያደናቅፋቸው ግፋ ሲልም ሊጥላቸው የሚደርሱ ተጫዋቾች አልጠፉም፡፡ ̋ያ ትልቅ ግንድ ምንድነው ? ̊ ካልን የኦሮሞዎች የፖለቲካ ጥያቄ ነው፡፡

ነፍስ ካወቅኩና የሃገራችንን ፖለቲካ ማሰላሰል ከጀመርኩ አንስቶ እንደኦሮሞዎች የፖለቲካ ጥያቄ የሚያሳስበኝ ነገር የለም፡፡የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ በተለይ በወቅቱ የነበሩት የተወሰኑ የኦሮሞ ተማሪዎች እንቅስቃሴ አንዳንድ ጊዜ አስደንጋጭ ነበር፡፡እንደከተማ ልጅነቴ እንግዳ የሚሆኑብኝን ጥያቄዎች ያነሳሉ፡ራሳቸውን ባገለለ መልኩ አመፅ ያነሳሳሉ ፡ይታሰራሉ ፡ይፈታሉ ፡፡ በቢስነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩሊቲ ውስጥ ኢትዮጵያ ̊ ከባለጋራ ̋ አገር ጋር ኳስ ስትጫወት ቲቪ በምናይበት ክፍል ውስጥ በግልፅ ተቃራኒ ቡድንን የሚደግፍ አንድ ከባሌ መምጣቱ የሚነገርለት ሹሩቤ የኦሮሞ ተማሪ ልጅ ነበር፡፡ኋላ ላይ ከመመረቁ በፊት አንድ ክረምት እረፍት አንደሄደ ኦህዴዶች በግድ አስላጩት ተብሎ ካለሹርቤ አይቼዋለሁ፤ በመጠኑም የወትሮ ቁጣው ቀዝቅዞ ነበር ፡፡

ከትምህርት በኋላ በሥራ ጉዳይ ኦሮሚያን ሳያትና በመሬት ላይ ያለውን ሃቅ ስመለከት መበርገጌ ቀነሰልኝ፡በርግጥ ጊቢ ውስጥም በፅሞናና በዘመናዊ መንገድ ማንኛውም ፖለቲካዊ ይሁን ማህበራዊ ጉዳይ ተነስቶ የምከራከራቸው ኦሮሞ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ አሁንም አሉኝ፡፡

ተቀዛቅዞ ቆይቶ ምክንያቱ ከሥሩ ባይታወቅም የኦሮሚያ ፖለቲካ እንደአዲስ እየተቆሰቆሰ የሚራገብበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ የሞት ትራፊ የሆኑትና አንድ ሃሙስ የቀራቸው የሚመስሉት የአገር ውስጥ ጋዜጦችና መፅሄቶች ይፅፉበታል፤ያወያዩበታል፤ ከኮምፒተር ጀርባ የመሸጉ ዘመናዊ ታጋዮች ይሰዳደቡበታል፤ይዛዛቱበታል፡፡ ከዚህ ሁሉ ትርምስ መሃል በሰለጠነ መልኩ በውይይትና በክርክር ትልቁን ግንድ ሊያስፈልጡኝ ከሞከሩ ምርጥ ምርጥ የኦሮሞ ልጆች መካከል አንድ ሰው ከደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ ወደአዕምሮዬ ይመጣል፡፡

2. ፍቃዱ ሁንዴ

ለስደተኛ የማትመች ከምትባለውና የአፍሪካ ቁርጭምጭሚት (የአፍሪካ ቀንድ እንዲሉ) ላይ የምትገኘው ናሚቢያ በጀርመኖች የታነፀች ዊንድሁክ (በአገሬው አፍ ቨንቱክ) የምትባል ንፁኅና ሽቶ ሽቶ የምትል ዋና ከተማ አለቻት፡፡ከደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ በመውጣት ወዲያውም ብሄራዊ ነፃነቷን ያገኘችው ውቧ አገር ትንሹም ትልቁም ተደምሮ የያዘችው ኢትዮጵያዊ ከሃያ አይበልጥም ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ የቀይ ሽብር ዋና ተዋናይ ነበር የሚባለውና የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሃላፊ በነበረ ጊዜ ̋ዲያቢሎሱን ̊ መንግስቱ ሃይለማሪም ከ ̋ቅድስት ̊ እማሆይ ቴሬዛ ጋር እንዲገናኝ ማድረጉ የሚወራለትና ፀጉሩን ጥቁር ቀለም እየተቀባ ሁሌ ጎልማሳ የሚመስለው ዳዊት ወልደጊዮርጊስም ኑሮው እዚያው ነው፡፡ ምን እነደመከራቸው ባላቅም ከናሚቢያ ነጻነት በኋላ የመጀመሪያ የአገሪቱ ፕሬዚደነት የነበሩትን ዶር ሳምኒዮማን ያማክር ሁሉ ነበር አሉ፡፡

ባላፈው ዓመት የካቲት ማለቂያ ላይ ለሶስት ወራት ወደዚች ውብ ከተማ ስጓዝ የደረስኩት ከመሸ ነበር፡፡ እድሜ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ስነሳ ለጥቂት ቀናትያስታምመኛል ብዬ የቋጠርኩት የባህል ምግብ ከሌሎች ኮተቶቼ ጋር መንገድ ላይ ጠፍተውብኛል፡፡ ከተዘጋጀልኝ የእንግዳ መቀበያ ፊት ለፊት ሁሉን የያዘ ሱፐር ማርኬት ቢኖርም ቅሉ፤በእንግድነትና አዲስነት ፍራቻ ጾሜን አደርኩ፡፡ ሲነጋ እየተንጠራወዝኩ ለባበስኩና እየራበኝ ወደቢሮዬ ተወሰድኩ፡፡ ምግብ ወደማገኝበት ቦታ እንዲወስዱኝ ነግሬ ልወጣ ስል ቢሮው በር ላይ የተሰቀለውን የሰራተኞች ስም ዝርዝርና በዚያ ወቅት በምን ሁኔታና የት እንዳሉ የሚያመለክተውን ሰሌዳ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ድንገት ፍቃዱ ሁንዴ የሚል ስም አየሁ፡፡ አላመንኩም፡፡

̊ኢትዮጲያዊ እዚህ ቢሮ አለ ? ̋ ስል በደስታ ጩኸት ጠየቅኩኝ፡፡

ደንደሳሟና የሰው መስተነግዶ የገባት የቢሮው አስተዳደር ሠራተኛ ፍቃዱ የሚባል ኢትዮጲያዊ እንዳለ አሁን በዓመት ዕረፍት ላይ መሆኑን ነግራኝ ስልክ ትደውል ጀመር ፡፡ ፍቃዱ ዘንድ ነበር የደወለችው፤ኢትዮጲያዊ ቢሮ እነደመጣና የሚበላ ፍለጋ ሊወጣ መሆኑን ስትነግረው የትም ሳልወጣ ቢሮ እንድቆየው አስጠነቀቃት ፡፡ አምስት ደቂቃ ሳይቆይ እረፍቱን አቋርጦ ሲበር መጣ ፡፡ ተዋወቅን፤ እጅጉን ደስ አለኝ፤ የአገሬን ሰው በዚያች ሰዓት ማግኘት የማይታሰብ ነበር፡፡ እያከለበ ቤቱ ይዞኝ ሄደና ሚስቱ ያሰናዳችው የኢትዮጵያውያን ምግብ ላይ አሰፈረኝ ፡፡ ያን ቀን ሥራ ሳልገባ ከቤተሰቡ ጋር ስንጫወት እንድውል አደረገኝና ጀምበር ስታጋድል ከተማዋን ልናይ ወጣን፡፡ ቢራችንንም ያዝን ፡፡

ፍቃዱ የወለጋ ኦሮሞ ነው፤ ሻምቡ ተወልዶ አድጎ አዲሳባ የጎለመሰ ሲናገር ቀጥተኛና ቶሎ ተግባቢ ብዙውን ጊዜም አሳማኝ ሃሳቦችን በተገቢ ቋንቋና መጠይቅ የሚያነሳ ሰው ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲገፋው ኑሮ ጥግ ያስያዘው የቤተሰብ ሃላፊ፡፡ ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ሴት ልጆቹን ጥሩ በሚባል ትምህርት ቤት ቢያስተምርምና ከባለቤቱ ጋር የስደት ኑሮው የተዳላው ቢመስልም የጉልምስና ብቸኝነት እንደተጫነው ያስታውቃል፡፡ እኔ የጉልምስና ብቸኝነት ያልኩት አገሩ ላይ ከእድሜና ከእውቀት እኩዮቹ ጋር ቢራውን ጨብጦ ያንን ትልቅ ግንድ በሃሳብ በውይይትና በክርክር እንደልቡ የሚከካበት ቦታ መራቡን ነው፡፡

̋ ቅድሚያ ኦሮሚያ ̊በሚለው አቋሙ የማይደራደር የሚመስለው ፍቃዱ ከውይይት አንፃር ከማንም ጋር ቢሆን ችግር የለበትም ፡፡ አሁንም የኦሮሚያ ጥያቄ ወቅታዊ ግና ተገቢው ቦታና መልስ ሳይሰጠው የቆየ ጉዳይ ሲሆን የኢትዮጵያ አንድነትም መሠረቱ የቅኝ ግዛት ሃይል ነው የሚል እምነት ነው ያለው ፡፡

ፍቃዱ ከመሰደዱ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠራበት መሥሪያ ቤት በታታሪ ሠራተኝነቱና አሠሪነቱ በተጨማሪ ብዙ ጊዜ የሚታወቀው ከመንግስት ሹመኞችና ካድሬዎች ጋር ሲነታረክ የማይዋጥለትን ሃሳብ በቀጥታ ሲቃወም ነበር፡፡ በዚህም ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ብዙ ስም ተሰጥቶታል ፤ተዝቶበታል ፡ የኦሕዴድ ሰዎች ከኛጋ ተጠግተህ ካልሰራህ የሚያስጥልህ የለም ወይ አፍህን ዘግተህ አቀርቅረህ ኑር ሲሉ ደጋግመው መክረውታል፡፡እንዳሉትም ተደጋጋሚ የፈጠራ ክሶችና ስም ማጥፋቶች ይግተለተሉበት ጀመር፡፡ በመጨረሻ መቋቋም ሲያቅተው ከስድስት ዓመታት በፊት ቤተሰቡን ይዞ ወደናሚቢያ ተሰደደ ፡፡

ዘወትር ስለማስመሸው ሚስቱ ደስተኛ ባትሆንም ተረድታናለች፤የፖለቲካ ክርከሩን ከቤቱ ውስጥ ስለምንጀምረው ያንኑ ይዘን እንደምናመሽ ይገባታል፡፡ እርግጥ ሁልጊዜ አርብ ምሽት የሚያገኛቸው ሁለት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጓደኞች ነበሩት ፤የሰውዘርና ክፍሌ፡፡ የሰውዘር አማራ ሲሆን ክፍሌ ኦሮሞ ነው፡፡ አርብ አርብ ምሽት የሰውዘርና ክፍሌ ስለሚመጡ ውይይቱ ከወትሮው ሞቅ ደመቅ ይላል፡፡ እንዳየኋቸው ሶስቱም ይዋደዳሉ፤ይተሳሰባሉ፤ርግጥ ከሃያ የማይበለጡ ኢትዮጵዊያን ባሉባት አገር ከመዋደድና ከመተሳሰብ ሌላ አማራጭ ሊኖራቸው አይችልም፡፡የሰውዘር ፍቃዱን ̊ ቅድሚያ ለኦሮሚያ ̋ ብሎ እንዲያስብና የኢትዮጵያን አንድነት እንዲጠየፍ ያደረገው ዘረኛው ወያኔ ነው ብሎ ከልቡ የሚያምን ሰው ሲሆን ፤ክፍሌ ደግሞ ዛሬ የኦሮሚያ ብቻ የሚባል ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለና አሁንም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሁሉም ብሄር የነፃነትና ፍትህ ረሃብ ተጠቂ ነው፤ በመሆኑም ትግሉ አንድ ብሄር ላይ ያተኮረ መሆን የለበትም ባይ ነው፡፡

ሶስቱም በዕድሜ እጅጉን ቢበልጡኝም እንግዳ በመሆኔና ስለኢትዮጵያ አዲስ መረጃ የያዝሁ ይመስል ክርክሩና ውይይቱ ላይ በቂ ጊዜና ጆሮ ይሰጡኛል፡፡ የሚሰማኝ ካገኘሁ የሆነ የቻይና ሞባይል ነገር ነኝ ቶሎ ባትሪ አልጨርስም፤ፊቴ ላይ ቀዝቃዘቀ ቢራ ተቀምጦ ውሃ እስኪጠማኝ ድረስ እለፈልፋለሁ፡፡ሃሳቤን ሚዛናዊ ለማድረግ በማሰብ ኢህሃዴግ አመጣ የምላቸውን በጎ ነገሮች በመሃል ስከት የሰውዘር ያቋርጠኛል፡፡ማቋረጥ ባይችል እንኳን ተራው ደርሶ መናገር ሲጀምር ስለወያኔና ኢህሃዴግ ያነሳኋቸውን በጎ ነገሮች ነቅሶ አውጥቶ በመሰለው መንገድ አንሻፎ ይተረጉማቸዋል፤ የተቃውሞው ወሬ በነዚህ መሰል አዎንታዊ አስተያየቶች እንዳይበከሉ የተቻለውን ያደርጋል፡፡ የዚያኑ ያህል በኢህአዴግ ላይ መጥፎ ናቸው ብዬ የማምንባቸውን ነጥቦች ሳነሳ በደስታ ይፍነከነካል፡፡ ቢራውን ደጋግሞ ወዳአፉ ይሰዳል፤ ባለፈው ያልኳችሁ ጉዳይ እኮ ነው በማለት ሃሳቤን ያጠናክርልኛል፡፡

ፍቃዱ ብዙ ጊዜ ከሰውዘርጋር ባይስማማም የሚያነሳቸው የከርክር ነጥቦችም ለጊዜው የራሱንና ሌሎች ኦሮሞዎችን አንጀት ቂቤ ለማጠጣት ወይም የሰውዘርንና ሌሎች አማሮችን አንጀት ለማሳረር ሳይሆን፤ዛሬም ነገም ላምንበት እችላለሁ የሚላቸውን ነው፡፡

ከፍቃዱ ጋር በቆየሁባቸውና በበረሃዋ ገነት ቨንቱክ ቢራችንን እየተጎነጨን በሙሉ ነፃነት የኢትዮ-ኦሮሚያን ፖለቲካና ፖለቲካን ብቻ ድምፃችን እስኪዘጋ ስንከራከር በቆየንባቸው ጊዜያት እጅግ በጣም ብዙ አዳዲስ እውቀቶችን ያገኘሁ ሲሆን፤የኦሮሚያ ፖለቲካዊ ጥያቄን አለባብሶ ማለፍ ነገ ኢትዮጵያን ለአደገኛ አረም እንደሚያስመልሳት በድጋሚ ግንዛቤ ያገኘሁበት ወቅትም ነው፡፡ ፍቃዱ የሚያነሳቸው ሃሳቦች ሁሉ ትክክል ናቸው ብዬ ባላምንም እጅግ በሃሳብ የተራራቅን ብንሆንም ግን በስልጡንነት ከሰማይ በታች በምንም ነገር መወያየት እንደምንችል ተስፋም አስይዞኛል፡፡ በተለያ ዘይቤዎችና መንገዶች ሲገለፁ ከነበሩና ከማስታውሳቸው ቁም ነገሮች ውስጥ ቀጣዮቹ አሉበት

3. የጠለፋ ጋብቻ

አንድ አርብ ምሽት የህዝብ ሪፈረንደም ለኦሮሚያ ይገባታል አይገባትም የሚል ክርክር ነበረ፤ ክርክሩ እንዴት ሪፈረንደም ድረስ እንደመጣ ቢረሳኝም መነሻው የሰውዘር ̋ ወያኔ ከመምጣቱ በፊት ባንድ ተዋደን ፤ትግሬ አማራ ኦሮሞ ሳንባባል በፍቅር ነበር ኑሮዋችን ̊ ማለቱ ነበር፡፡

ፍቃዱ እንዲህ አለ፡- ‹‹የሰው…›› – የሰው ዘርን የሰው እያለ ነበር የሚጠራው –

‹‹እሱ እኮ አሁንም አለ፤ መች እነደሰው መዋደዱን አቆምነው ችግሩ ያለው ወደብሄራዊ ትልቁ ማንነት ስንመጣ ነው፤እኔ ኦሮሞው አንተ አማራውን ወነድሜን እወድሃለሁ፤እኔ ግን ኦሮሚያ አደለሁም ኦሮሞ ነኝ እንጂ፤ኦሮሞዎች ሆነው አማራን የሚጠሉ የሉም እያልኩህ አይደለም አሉ ኣማራም ሆነው የኦሮሞ ስም የሚያንገፈግፋቸው እናደሉ ሁሉ፤እሱ ጥላቻ ደግሞ ወያኔም ከመምጣቱ በፊት ነበር፡፡ ጥያቄው ያለው እኔነቴን የፈጠረው ትልቁ ብሔራዊ ማንነቴ ከሌሎች ትልልቅ ማንነቶች ጋር ተዋዶና ተፋቅሮ ኖሮ ነበር ወይ ነው፤እንዲያ ከሆነ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ግንኙነት ሃይል የፈጠረው በቀላል ቋንቋ ይቀመጥ ከተባለም የጠለፋ ጋብቻ ነው፡፡ የጠለፋ ጋብቻ ደግሞ ህጋዊ አይደለም፤ህጋዊ ያልሆነ ነገር ደግሞ ሊፈርስና ወደነበረበት ሊመለስ ይገባል::››

የሰውዘር ግራ ገብቶት ዝም እንዳለ ክፍሌ ጣልቃ ገባ፡

‹‹ታዲያ እኮ ያ የጠለፋ ጋብቻ ወልዶ ከብዶ ብዙ ልጆች አፍርቷል፤በሃይል የቆየው ትዳር ይፍረስ ቢባል እንኳን ወደነበረበት አይመለስም፤ ጎረምሳ ሳለህ በወጣትነቷ ጠልፈህ ያገባሃትን ሚስትህን በሽምግልና ዘመንህ ልፍታት ብትል ወደነበረችበት አትመልሳትም፡፡ ያለው አማራጭ የትዳሩን መዋቅር ማየትና ማጤን ነው ፤አሁንስ በትዳሩ ውስጥ ጠለፋ አለ ወይ ሃይልን መሰረት ያደረገው ግንኙነት ቀጥሏል ወይ የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው መመለስ ያለባቸው፡፡››

ፍቃዱ ቀጠለ:-

‹‹እሱንማ እኮ አብረን አየነው ክፍሌ፤ አባታቸው በሃይል አግብቶ ለወለዳቸው ልጆቹ ሃይል መጠቀሜ ትክክል ነበር፤እናንተን የመሰለ ልጆች አገኘሁ እያለ ሚስቱ ላይ ሲዘባነንባት ኖረ እኮ፡፡ ሚስቱን በሃይል ማግባቱ ሳያንስ እኔን የመሰሉ ፤የኔን ቋንቋ የሚያወሩ ያንችን የሚያጣጥሉ፤ በኔ ባህል የሚኮሩ ባንች የሚያፍሩ ልጆች ብቻ ውለጅልኝ ብሎ ሲያስገደድ እኮ ኖረ፡፡ ልጆቹ እሱን መስለው መወለድ ስላልቻሉ ከሌላ የወለዳቸውን አምሳያ ልጆቹን አምጥቶ እነሱን ካልመሰላችሁ እነሱን ካልሆናችሁ እያለ ልጆቼ አደለችሁም በማለት ሲያስጨንቅ የኖረ እኮ ጨካኝ ባል ነው፤ የማይቻለውን ነገር !! ይህ ባል ነው ለኦሮሚያ ኢትዮጵያዊነት፡፡››

ክፍሌ መለሰ፡-

‹‹እሱ አለማወቅና በጊዜው የነበረው ማሃይምነት ነው ፤ ልጆቹ ይህን ያባተቸውን አለማወቅና ማሃይምነት አልተከተሉም፡፡››

ፍቃዱም፡-

‹‹ትልቁ ችግር ታዲያ ምኑ ነው? እሱ እኮ ነው፤አባቴ በሃያሉና በጉልበቱ የገነባው ቤት ያኮራኛል መባሉ ነውኮ ችግሩ፤ በጉልበት የተገነባ ቤት ቢያንስ ሊያኮራ አይችልም:: ያሁኗን ኢትዮጵያ ኦሮሞውና ደቡቡ አደለም ህሊና ቢኖረው ሰሜኑም ባልተኩራራባት፤ ምክንያቱም የጉልበት ታሪክ አያኮራም›› ካለ በኋላ፤ አንድ እንግሊዛዊ ወጣት አግኝቶ ሲጨዋወቱ አያቶቹ የዓለምን ግማሽ በላይ ስለገዙ ምን እንደሚሰማው በጠየቀው ወቅት እንግሊዛዊው አንገቱን ደፍቶ ‹‹shame›› ብቻ ብሎ እንደመለሰለት አጣፍጦ አወራ፡፡

የሰውዘር የፍቃዱ ትነንታኔ ምቾት እንዳልሰጠው ያስታውቃል:-

‹‹ፍቃዱኮ ምን እንደምትል አይገባኝም፤አሁን አብረን እየኖርን ነው ያለነው፤ለምን የወያኔ መሣሪያ እንደምትሆን ነው የማይገባኝ፤ቅኝ ግዛት ስለሚያሳፍረው ነዋ የጀርመን ወጣት አሁን እንኳን ከጥቁር ጋር መብላትና መጠጣት ተጠይፎ በዘበኛ እንደውሻ ከበር የሚያባርርህ?›› ብሎ ዊንድሁክ ውስጥ ያሉ ነጮች ብቻ የሚዝናኑባቸውን ጥቂት ሬስቶራንቶች ጠቀሰና፡

‹‹መፍትሄው የምትለው ታዲያ አዛውንቱን ትዳር…እንዳንተው ትዳር ልበል እንጅ…ትዳሩን ማፍረስ ነው?›› የሰውዘር ጠየቀ፡፡

ፍቃዱ አላመናታም፡-

‹‹አዎ! በነገራችን ላይ ብዙ የሸመገለ ትዳር አታድርጉት ይህ የሃይል ጋብቻ የመቶና መቶ ሃምሳ ዓመት ታሪክ ብቻ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ኦሮሚያ ሪፈረንደም ያስፈልጋታል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ትዳሯን ህጋዊ ለማድረግ ወይም ለማፍረስ፡፡

ክፍሌ ጠየቀ፡-

‹‹ሌላስ አማራጭ ያለ አይመስልህም…?››

̋ፍቃዱም፡-

‹‹ሌላው አማራጭ እነሰውዘር ቁስላችንን ዐይተው ህመማችን ተሰምቷቸው ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል….›› አለና የሰውዘርን ዞር ብሎ አየው፡፡

የሰውዘር  ፈጠን ብሎ መለሰ፡-

‹‹እኔን ደሞ አገር አልባ ያደረገኝ ወያኔ ይቅርታ ሊጠይቀኝ ይገባኛል››

̋ፍቃዱ አልተዋጠለትም፡-

‹‹ወያኔ ግዴታ መጠየቅ ካለበት አንተ ባልከው ጥፋት አይደለም፡፡ ምንድነው ይቅርታ ለምን ማን ማንን የመሳሰሉትን የምናወራበት መድረክ በማሳጠቱ ነው መጠየቅ ያለበት…..̊  አለ፡፡

4. ፊንፊኔና አዳማ

አንድ ጊዜ ደሞ ስለኦሮሚያ ክልል መንግስት መቀመጫ ከተማ ሲወራ ፍቄ ይህን የአገር ቤት ትዝታውን አጫወተን፡- 

ጊዜው 1994 ዓ.ም. ነበር ፡፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ ወደአዳማ ይዛወር ተባለ፡፡ በሚሰራበት ሚንስትር መስሪያ ቤት የኦሮሞ ተወላጆች ተመርጠው በቅድሚያ የተወሰነውን ጉዳይ ይወያዩበት ተባለና ስብሰባ ተጠራ፡፡ የመድረኩ ሰው የኦሮሚያ ዋና ከተማ ወደአዳማ መዛወሩን ለማሳመን ቢጥርም ጥቂቶቹ የኦሮሞ ተወላጆች በኣፋቸው፤ ብዙዎቹ በሆዳቸው አንገታችን ለካራ ይላሉ፡፡ በስብሰባው መሃል ፍቃዱ እጁን አነሳ፡፡ ብዙዎቹ የሆዳቸውን ሃሳብ ከፍቃዱ ለመስማት ጓጉ፡፡

̊እኔ የኦሮሚያ መንግስት መቀመጫ አዳማ የሚለውን ሃሳብ እደግፈዋለሁ ̋ ሲል የመድረኩን ሰው ጨምሮ ብዙዎቹ ጤናውን ተጠራጠሩት፤አንዳንዶቹ ቸኩለው ̋ይቺ ሰውዬ ጉልበቷን አሟጠጠች፤አቅም ለመሰብሰብ ወደኦህዴድ ጉዞ መጀመሯ ነው!̊ ያሉም ነበሩ፡፡ ፍቃዱ ቀጠለ…..

‹‹አንደኛ ዛሬ ላይ ፊነፊኔ የኦሮሚያ ፊነፊኔ አደለችም፡፡ ፊነፊኔ እስኪ ምን አላት ኦሮሚያን የሚመስል? ምንም፡፡ ፊነፊኔ በኣሁን ሁኔታዋ የታላቁን ኦሮሞ ባህል ቋንቋና ትውፊት የሚሸከም አቅም የላትም አቅሟ የታላቁን ኦሮሞ ባህል ቋንቋና ትውፊት የሚበላና የሚውጥ ነው፡፡ የታላቁን ኦሮሞ ባህል ቋንቋና ትውፊት የምትበላና የምትውጥ ከሆነ ሰው የበላውን ነው የሚመስለውና በሂደት ኦሮሚያን ትምስላለች ትሉ ይሆናል፤ እሱን ተዉት ፊነፊኔን ራሷን የአውሮፓና አሜሪካ ባህል በቅርቡ ይበላታል፡፡ ስለዚህ ኦሮሚያን ለማሳየት ፊነፊኔ ጥሩ ቦታ አደለችም፡፡ ካልታየንባትና ካልደመቅንባት ደሞ ከተማችን አደለችም፤አትሆንምም!

ሁለተኛ አዳማን ማንም ሳይሻማን ሰፊዋን ኦሮሚያ የምናበቅልባትና የምንሰበስብባት ከተማችን ልናደርጋት እንችላለን፡፡ በዚያ አሁን ማንም ሊውጠን አይችልም ልንጎመራ ነው እንጅ ፡፡ በአዳማ ኦሮሚያን አጉልተን ማሳየት ይቻለናል፡፡ ኦሮሚያ የበለፀገ ባህሏንና ሌሎች የገዳና የእምነት ሥርዓቷን መልሳ ለመትከል የተከለለ ቦታ ያሻታል፤ አዳማ የቢያ ኦሮሞ ሥርና መብቀያ መሆን ትችላለች፡፡ ጥብቅ ሥር ያለው ደሞ ለመነቀል ጊዜ ይወስዳል፤ፊንፊኔን ለጊዜው ዙሪያዋን የኦሮሞ ከብት ብቻ ከተነፈሰባት ይበቃል!›› ብሎ ጨረሰ፡፡

የኦሮሞ ከብት የሚለው ኣባባሉ ብዙዎቹን ቢያስገርምምና ማንን ደሞ ይሆን ብሎ ቢያስጠይቅም ማንም አላጨበጨበለት ፤እሱም ጭብጨባ አልፈለገ-አዳማ ዋና ከተማ ሆነች፡፡ በርካቶች ይህን የተቃወሙ ታሰሩ ከሥራቸው ተባረሩ፡፡ በሶስት ዓመት ውስጥ ግን የኦሮሚያ ዋና ከተማ ወደፊንፊኔ ተመለሰች፡፡ አሁን ገና ጨሰ ፍቃዱ፡፡

5. የሰባ ከብትና ለም መሬት

አንድ ጊዜ ሞቅ ባለ ክርክራችን መሃል ፍቃዱን እንዲህ ስል ጠየቅኩት…..

‹‹ብዙው አማራ ወይም የከተማ ሰው ኦሮሚያ መገንጠል የለባትም ለምን የሚል ይምስልሃል…?››

እሱም፡-

‹‹መጀመሪያ አማራና አንተ ማን ናችሁና ነው፣ የኦሮሞ ህዝብ ቁጭ ብሎ መገንጠል የለባትም አለባት ባይ የሆናችሁት? ›› ሲል ጠየቀኝ፡፡

እኔም፡-

‹‹ብዙ ጊዜ ከተሜውና ሰሜነኛው በኦሮሞ የተፈጥሮ ሃብት ይጎመጃል የሚሉ ሰዎች ስላሉ ነው ››  ካልኩ በኋላ አንድ ኦሮሞ ጓደኛዬ ቆየት ባለ ጊዜ ያለኝን ነገርኩት ‹‹ኢትየጵያ በዓለም ላይ በሶስስት ነገር ትታወቃለች ፤በድርቅ፤ በሩጫና በቡና ፤ከነዚህ ውስጥ ድርቅ የሰሜኑ ኣማራና ትግራይ ሲሆኑ ሩጫና ቡና ግን የኦሮሞ ነው ፤ሰሜኑ እኛን ኦሮሞዎችን መላቀቅ የማይፈልገው ለም መሬታችንን እና የተፈጥሮ ሃብታችንን በመፈለግ ነው ….››

            ‹እና…. አሁንም የሰባ ከብትና ለም መሬት ፍለጋ ይምስልሃል የኣማራው ኢሊት መገንጠል የሚባለው ጉዳይ የሚያነገሸግሸው ….?›› ስል ጠየኩት

ፍቃዱም፡-

‹‹ታምሩ! የተፈጥሮ ሃብት በፍለጋ የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ተፈጥሮ ደሞ እርስበርስ ለመጋገብ የተሰራች እንጅ ላንዱ ብቻ ሁሉንም ኣሳቅፋ የተቀመጠች አደለችም፡፡ የኦሮሞ ረግረጋማ መሬት ላይ የትግራይ ድንጋይ ብርቅ ነው የኦሮሞው ጭቃም ለትግራይ ዋጋ ያለው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የዛሬዎቹ ባለአንድነቶች ለም መሬትና የሰባ ከብት አይደለም ችግራቸው እነ በረከት ስምኦን እንደሚሉን ፡፡ ይህም ለኦሮሚያ ፖለቲከኞች ትልቅ ጀንዳ ሊሆን የሚገባው አደለም፤ ምክንያቱም የተፈጥሮ ሃበት የተፈጥሮ በረከትና በማንኛውም ጊዜ ሊገኝ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ ድንጋይ ነው ያልከው ቦታ ነገ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ ፤ የኛ ጉዳይ ከዚያ ከፍ ያለ ነው፤ የኔ ጉዳይ ከዚህ እጅጉን የላቀ ነው ታሜ፤ የማንነት ጉዳይ ነው:: ልጆቼ I am Habesha የሚል ቲሸርት ለብሰው ትምህርት ቤት ሲሄዱ ሃበሻ አይደላችሁም ብዬ ለማስረዳት የሚወስድብኝን ጉልበትና ጊዜ አስቤ ተስፋ መቁረጤ ነው የኔ ጉዳይ ከገባህ!››

እውነትም አንድ ቀን እኔና እሱ ቁጭ ብለን እያወራን ሁለቱ ቆንጆ ልጆቹ I am Habesha የሚል ቲሸርት ለብሰው ወደጓደኛቸው የልደት ድግስ ሲሄዱ እያሳየኝ ነበር፡፡ ሲያሳየኝ ምንም አልተናደደም፤ ቲሸርቱንም ከደቡብ አፍሪካ የገዛለቸው ራሱ ነው ፤መናደድና ልጆችን ግራ ማጋባት አሁን ብዙ እንደማያስፈልግ አጫውቶኛል፡፡

6. መሬት የማይጣለው ካርታ

ፍቃዱ አፄ ምኒሊክን እንዲወዳቸውና እንዲያሞካሸቸው አይጠበቅም፡፡ እንዲያውም ሙልጭ አድርጎ ይሰድባቸዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ጣጣ መንስኤ ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኢህአዴግ ምኒሊክን ከሞቱ ከመቶ ዓመትም በኋላ እንዴት ለስልጣኑ እንደሚጠቀምባቸው ይገልፃል፡፡ ሲጠራቸውም ኬሻው በማለት ነው፤ ካርታ ጨዋታ ላይ ያለውን ‹‹ንጉስ K››ን እያስመሰለ፡፡

‹‹K ካርታ›› ለኢህአዴግ የማይጥለው የማሸነፊያ ካርታው ነው ፡፡ ይመዘዋል እንጅ መሬት ላይ አይጥለውም፡፡ ያ ካርታ ከእጁ ከወደቀ ጨዋታው ያልቃል፡፡

ባለፈው ይህ ካርታ ተመዞ ነበር እንዴ? እውነት ግን መቼ ይሆን ‹‹K ካርታ›› መሬት የሚወድቀው?

**********

 

Guest Author

more recommended stories