የቋንቋ ፖሊሲ ለካቢኔ ሊቀርብ ነው | የአማርኛን ፋይዳ ለማሳደግ ተመከረ

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው የቋንቋ ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው።

ረቂቅ ፖሊሲው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሀገራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ጋር በመተባበር በባለድርሻ አካላት ሲገመገም ነው የቆየው።

ትላንትና ከትናንት ወዲያ በተካሄደው የመጨረሻ ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ፥ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ 230 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በሚኒስቴሩ የቋንቋና የባህል ልማት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ሹምነካ እንዳሉት ፖሊሲው የግልና የጋራ የቋንቋ መብቶችን የያዘ ነው።

ከፊደል ቀረጻ ጀምሮ እስከ ትግበራ ያለው ሂደት በስርዓት እንዲመራ ፖሊሲው አጋዥ ይሆናል ሲሉ አቶ አውላቸው ለሪፖርተራችን ራሔል አበበ ነግረዋታል።

በመድረኩ የቋንቋና የህግ ማዕቀፍ፣ ቋንቋና አፍ መፍቻ ፣ ቋንቋና ከፍተኛ ትምህርት የሚሉና ሌሎችም 10 ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ፥ በቋንቋ ዙሪያ የህንድና የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የቋንቋ መብቶች በተገቢው መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑና እንዲደረጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል የተባለው ፖሊሲ ግብአት ከተሰበሰበት በኋላ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

ምንጭ፡- ፋና፤ ሚያዚያ 13 ፣ 2005
*************

በተመሳሳይ ቀን አዲስ ዘመን ‹‹አማርኛን ለሣይንስና ቴክኖሎጂ መጠቀም ያስፈልጋል›› በሚል ርዕስ ዜና ያቀረበ ሲሆን እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

የአማርኛን ቋንቋ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መጠቀሚያ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የባህርዳር ዩንቨርሲቲ አስታወቀ።

በአገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያሳተፈ የአማርኛ ቋንቋና ባህል ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚመክር አገር አቀፍ ዓውደ ጥናት በዩንቨርሲቲው ኦዲተሪየም አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው።

የዩንቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በዓውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት፤ ዩንቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት አገራዊና ክልላዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎችን በማበርከት ላይ ነው።

ዩንቨርሲቲው በአቋቋመው የአባይ የባህል ማዕከል በአገሪቱ በስፋት የሚነገረውን የአማርኛ ቋንቋ ፣የሳይንስና ቴክኖሎጂ መጠቀሚያ ቋንቋ በሚሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስና ለባህል ኢንዱስትሪው የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአንድ አገር ባህልና ቋንቋ የህብረተሰቡን ማንነት ጠብቆና ተንከባክቦ ለማቆየት፣ ትውፊታዊ እሴትን ለትውልድ ለማስተላለፍና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ዓውደ ጥናቱ በቋንቋው አጠቃቀም፣ የባህል ኢንዱስትሪው ልማትን እንዴት ማቀላጠፍ እንደሚገባ፣ የቀጣይ እጣ ፈንታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ምሁራን ሥራዎቻቸውን በማቅረብ ለፖሊሲ አውጭዎች ግብዓት የሚቀርብበት ሁኔታ እንደሚመቻች አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ በበኩላቸው፤ የአማርኛ ቋንቋ ለዘመናት የመንግሥታዊ መዋቅር፣ ወታደራዊ፣ ሲቪል ሰርቪስና ሌሎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች በየዘመናቱ ለነበሩ ነገሥታት፣ መንግሥታትና ሕዝብ በመሣሪያነት እያገለገለ ከዚህ ደረጃ መድረሱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በዓለም ላይ የተስፋፋውን ግሎባላይዜሽንና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የባህል፣ የኪነ ጥበብ፣ የማንነትና የማህበራዊ እሴቶች ወረራና ማዳከም ተቋቁሞ በሥነ ጽሑፍ፣ በልማትና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በመሆኑም ቋንቋው ለሁሉም አገልግሎት ለመስጠት የሚያበቃው እናት የመዝገበ ቃላት በማዘጋጀት፣ የቋንቋውን የቃላት ባንክ በማቋቋምና ሰፊ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የአገራችንን እድገት ለማፋጠንና ጥቅም ላይ ለማዋል መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በአፍ መፍቻ የሚነገር ቋንቋ በተፈጥሮ የተሰጠውን የአዕምሮ ዕውቀት በመመርመርና አዳዲስ የፈጠራ ክህሎትን በማዳበር የአዕምሮ መግለጫ ነው ነው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቋንቋ ተመራማሪና ምሁሩ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም ናቸው፡፡

ምሁሩ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ቋንቋ አዕምሮን በአግባቡ በመጠቀምና አዳዲስ ሁነቶችን በመፍጠር ቁሳዊና ሁለንተናዊ ልማትን በየዘርፉ ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ትልቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ አገራዊ ዓውደ ጥናት ላይ አፈ-ፈትነትና የትምህርት ልማት፣ የባህልና ፈጠራ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ የዕድገት አውድ ያለው እምቅ አቅም፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአማርኛ ልብወለዶች፣ ሰዋሰዋዊ አንቀጽ በአማርኛና ሌሎች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው የጋራ መግባባት እንደሚደረስባቸው ከወጣው መርሐ ግብር ተመልክቷል።

**********

Daniel Berhane

more recommended stories