ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 2 | ያለፉ የምርጫ ተሞክሮዎችና ለኢህአዴግ ማሸነፍ ዋነኛ ምክንያቶች

(/ አስጨናቂ /ፃድቅ)

(የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለማንበብ በዚህ ሊንክ ማግኘት ይችላሉ)

1. ምርጫ-97 ፡-የሀገራችን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተምሳሌት፤

የሀገራችን የምርጫ ጉዳይ ሲነሳ ስለ 1997ቱ ምርጫ መጥቀስ የግድ ነዉ፡፡ የ97 ምርጫ በራሱ ሰፊ ትንታኔ ለማድረግ የሚያበቃዉ የደለበ ታሪክ ያለዉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚያ በሻገር ግን ለሌሎች ምርጫዎች ሁሉ እንደ መነሻማና ማነጻጸሪያ(reference) ሊያገለግል እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ የ97 ምርጫ ከዚያ በፊት ተካሂደዉ ለነበሩት ሁለት ሀገራዊ ምርጫዎች ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ለተደረጉትም ሆነ ወደፊትም ለሚደረጉ ምርጫዎች ሁሉ ማነጻጸሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ነዉ፡፡ መሰረታዊ ለዉጥ ካልታየና ሁኔታዎች አሁን ባለዉ መንገድ ከቀጠሉ የ97 ምርጫ ማነጻጸሪያነቱ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ትዉልዶችም ሊሆን የሚችል ነዉ፡፡

የ97 ምርጫ በመራጩ ህዝብ፤ በገዢዉ ፓርቲ፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ በአለም አቀፍ ህብረተሰብ ሚዛን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠዉ ምርጫ ነዉ፡፡ የተጠቀሰዉ የ97 ምርጫ ተቀዋሚዎች ህዝብን ከጎናቸዉ በማሰለፍ ህጉን አክብረዉ በሰላማዊ መንገድ ከተወዳዳሩና በመንግሰት በኩልም አሉ የተባሉትን እንከኖች በማስወገድ ለነጻ፤ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተሻለ ምቹ ሁኔታ ከፈጠረ ተቃዋሚዎች የማሸነፍ ዕድላቸዉ ዝግ እንዳማይሆን ቢያንስ በርካታ መቀመጫ ሊያገኙ እንደሚችሉ ያሳየና ለወደፊቱም ተስፋ ያጫረ ነዉ፡፡ በገዥዉ ፓርቲ በኩልም ህዝብ ካልፈለገዉ በማንኛዉም ግዜ ከስልጣን ሊያወርደዉ እንደሚችል በተግባር ያረጋገጠበት መልካም አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ መራጩ ህዝብም ቢሆን ከፈለገ በስልጣን ላይ ላለዉ ገዥዉ ፓርቲ ለቀጣዮቹ የምርጫ ዘመናት ይሁንታ ሊሰጠዉ እንደሚችል ካለፍለገ ደግሞ በማንኛዉም የምርጫ ወቅት አሸቀንጥሮ በመጣል ዕድሉን ላሻዉ ሌላ ፓርቲ ሊሰጥ እንደሚችል ህገመንግስታዊ መብቱን በተግባር ያረጋጋጠበት ነዉ ማለት ይቻላል፡፡

ከ97 ምርጫ በፊት መራጩ ህዝብ ምርጫ በደረሰ ቁጥር የምርጫ ካርድ አዉጥቶ በዕለቱ ድምጹን ከመስጠት ባለፈ ገዥዉን ፓርቲ በሌላ ፓርቲ መቀየር የሚያስችል ስልጣን እንዳለዉ በሚገባ አስቦበበት የሚያዉቅ አይመስለኝም፡፡ በምርጫ ካርድ የፈለገዉን ለመንግስት ስልጣን ለማብቃት ያልፈለገዉን ደግሞ የመሻር ስልጣን እንዳለዉ በወሬ ደረጃ ሲነገር ከመስማት ባለፈ እንዲህ እንዴ ዘጠና ሰባቱ ምርጫ በተግባር ሊተረጎም የሚችል አድርጎ አስቦ የሚያዉቅ አይመስለኝም፡፡ ዘጠና ሰባት ላይ ግን ሆን ብሎና አስቦ ይሁን ወይም ደግሞ በደመነፍስና በስሜት ተገፋፍቶ ተቃዋሚዎችን ወደ ስልጣን ለማዉጣት የተቃረበ ዉሳኔ መወሰኑን መራጩ ህዝብ የተረዳዉ ዘግይቶ በኋላ ላይ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ መራጭ ዜጋ ያቺኑ የምርጫ ወረቀት ላይ ምልክት አድርጎ ወደ ዕለት ጉዳዩ ከመሄድ ዉጭ መንግስትን ለመቀየርም የሚያስችል ወሳኝ ስልጣን በእጁ ዉስጥ የነበረ መሆኑን ለመረዳት የበቃዉም እጅግ ዘግይቶ ገና የ97ን ምርጫ ዉጤት ካወቀ በኋላ ነዉ፡፡

የ97 ምርጫ ትልቁ ፋይዳ ኢህአዴግ ከፍተኛ ትንቅንቅ አድርጎ በመጨረሻም ማሸነፍ መቻሉ ወይንም ተቀዋሚዎች ለትንሽ ተበልጠዉ መሸነፋቸዉ ሳይሆን መራጩን ህዝብ ህገመንግስታዊ ስልጣኑን የት ድረስ እንደሆነ በተግባር ማረጋጋጥ ማስቻሉ ነዉ፡፡ በርግጥ ምርጫ -97 አስተማሪነቱ ለተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን ለገዥዉ ፓርቲም ጭምር ነዉ፡፡ የኢህአዴግን ሁኔታ ለብቻ ካየነዉ ከተቃዋሚዎች ባልተናነሰ ቀላል የማይባል ትምህርት ሳይሰጠዉ አልቀረም፡፡ ኢህአዴግ በራሱ የተሳሳተ ግምገማ ማንም የማይቀናቀነዉ የህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለዉ ራሱን በማሳመን “ከስልጣን ማንም ደፍሮ አያወርደኝም” በሚል አጉል የራስ መተማመን በመኩራራቱና አለቅጥ በመዘናገቱ የራስ መተማመኑን በመግፈፍ ለድንጋጤ የዳረገዉ ምርጫ ነበር -ምርጫ 97፡፡

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ምርጫ 97 ለተቀዋሚዎችም ለኢህአዴግም ሆነ ለመራጩ ህዝብ እኩል አስተማሪ ሆኖ እያለ ተቃዋሚዎች ግን የኢህአዴግን ያህል ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ በኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚታይ አንድ የብቃት ልዩነት ማሳያ ሊሆን የሚችለዉም ይሄዉ ከራስ ድክመት የመማርና ያለመማር ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪ ተለዋዋጭ በሆኑ ከባባዊ ሁኔታዎች ዉስጥ እንደአስፈላጊነቱ በመተጣጠፍ ራስን ቀይሮ ከአዲስ ሁኔታ ጋር ተስማምቶ ለመስራት በመቻል ረገድ ሰፊ ልዩነነት በመካከላቸዉ መኖሩ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ የኢህአዴግ ትልቁ ጥንካሬ ሽንፈት ሲገጥመዉ ብቻ ሳይሆን ድል ሲቀናዉም ጭምር ራሱን መገምገሙና ከአዲስ ተለዋጭ ሁኔታ ጋር ፈጥኖ ራሱን ማስማማት መቻሉ ነዉ፡፡

ኢህአዴግ በ97 ምርጫ አሸንፎም እያለ ለምን በርካታ ወንበር ለመልቀቅ እንደቻለ ከምርጫ በኃላ በሚገባ ገምግሟል፡፡ በ2002 በዝረራ አሽንፎ እያለም ራሱንም ተቃዋሚዉንም የአካባቢ ሁኔታዉንም በሚገማ ገምግሟል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በ2007 ለምን መቶ በመቶ እንዳሸነፈም ሳይገመግም አልቀረም፡፡ ማንኛዉም በስልጣን ላይ ያለ ጠንካራ ፓርቲ እንደሚያደርገዉ ኢህአዴግ ገና ከአምስት ዓመት በኋላ ለሚመጣ ምርጫ ዝግጅት ማድረግ የሚጀምረዉ የአሁኑ ምርጫ በተጠናቀቀ ማግስት ጀምሮ ነዉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን በዚህ ጉዳይ አልታደሉም፡፡ ለምን ማሸነፍ እንደተሳናቸዉ ለመገምገም አቅሙም ፍላጎቱም የላቸዉም፡፡ በ97 ምርጫ ለምን የተሻለ የህዝብ ድምጽ ማግኘት እንደቻሉ መገምገም ቀርቶ ለምን በቀጣዮቹ ሁለት ምርጫዎች በዝረራ ለመሸነፍ እንደበቁም በሚገባ ለይተዉ አላወቁም፡፡ ፡ያን ከማድረግ ይልቅ የኢህአዴግ ጫናና ወከባ፤የምርጫ ቦርድ ተአማንነት፤ ነጻ ሚዲያ ጉድለት ወዘተ እያሉ ማማረርንና ቢሶት ማሰማትን ነዉ የመርጡት፡፡ ለዚህም ነዉ ኢህአዴግን ሊገዳደሩ ቀርቶ እንደ ፓርቲ ህልዉናቸዉን ጠብቀዉ ካንዱ ምርጫ ዘመን ወደ ሌላዉ መዝለቅ እንከዋን የተሳናቸዉ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በፓርቲዎች መካከል የጋራ አጀንዳ ለማስያዝ በተደረገዉ ድርድር አንዳንዶቹ ፓርቲዎች የፓርቲ እዉቅና ያገኙበት ወረቀት ፊርማዉ ገና ሳይደርቅና እንደ ፓርቲ የህዝብ ድጋፍ ማግኘታቸዉን እንኳን እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ ዋነኛ የሀገራዊ ጉዳይ የቱ እንደሆነ መለየት ተስኗቸዉ እጅግ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ለሀገራችን ከ“ኢትዮጵያ” ዉጭ ሌላ መጠሪያ ስም ካልሰጠን ቢለዉ መዛታቸዉ ነዉ፡፡ ከንደዚህ ዓይነት ፓርቲ ህዝቡ ምን አዲስ ነገር ሊጠብቅ ይችላል ተብሎ ነዉ ምርጫ ቦርድ እዉቅና የሰጠዉ?ተቃዋሚዎች ከራሳቸዉና ከሌሎች መሰል ፓርቲዎች ድክመት ልምድ ለመቅሰም ቢያቅታቸዉ እንኳን ቢያንስ የጋራ ተቀናቃኛቸዉ ከሆነዉ ከገዥዉ ፓርቲ ጥንካሬ ልምድ ሊቀስሙ በተገባቸዉ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ድክመት የሌለበት ድርጅት ስለሆነ ሳይሆን ችግር ሲገጥመዉ እንዴት ባለ ፍጥነት ራሱን አርሞና አድሶ በአዲስ ኃይል እንደሚንቀሳቀስ ከሱ ሊማሩ በተገባ ነበር፡፡ ስንት አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄና አጀንዳ እያለ ለኢትዮጰያ ሌላ መጠሪያ ስም ለመስጠት ቢሎ ዓላማ አንግቦ የተነሳ ቡድን ነገ ህዝቡ ንቆት ድምጹን ሲነፍገዉ ራሱን እንደ ደህና ፓርቲ ቆጥሮ “ምርጫ ተጭበረበረ ”ምናምን ከማለት አይቆጠብም፡፡ እንደዚህ አይነቶቹ ናቸዉ እንግዲህ ለቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን አሸነፈዉ መንግስት ለመመስረት የሚያልሙት፡፡ እነዚህን መሰል ድርጅቶች ናቸዉ ኢህአዴግ ስልጣን አልለቅም ብሎ አስቸገረ በማለት የሚያማርሩት፡፡ እነደዚህ ዓይነት ድርጅቶች ተወዳደሩ አልተወዳደሩ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታዉ አንዳችም ጥቅም አያበረክቱም፡፡ አንዳንዶቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንኳን ኢህአዴግን የመሰለ ስር የሰደደ ጠንካራ መሰረትና ልመድ ለዉ ፓርቲ ከስልጣን ማዉረድ ቀርቶ ስልጣን ባለቤት አጥታ መንገድ ላይ ወድቃ ቢያገኝዋት እንኳን ምን ሊያደርጓት እንደሚችሉ ጠንቅቄዉ የማያዉቁ ናቸዉ፡፡

ስለ97 ምርጫ ሲነሳ ተቃዋሚዎችና የግል ተወዳዳርዎች ከዚያ በፊት በተካሄደዉ የ1992 ምርጫ በጥምር አግኝተዉ ከነበረዉ ሰላሳ መቀመጫ(12+18=30) ወደ 172 በማሳደግ በርከት ያለ የፓርላማ መቀመጫ(ከ547 ዉስጥ አንድ ሶስተኛ ወይም 31 % ) ማግኘት ቢችሉም ዕድሉን ለመጠቀም ባለመፈለጋቸዉ ህዝብ የሰጣቸዉን ድምጽ መና አስቀርተዉታል፡፡ በአንጻሩ በርካታ ወንበር ለመልቀቅ የተገደደዉ ኢህአዴግ ከምርጫዉ ዉጤት ከተቃዋሚዎች በበለጠ ተጠቃሚ መሆን ችሏል ማለት ይቻላል፡፡ ተቃዋሚዎች ባላሰቡበት ሁኔታና ባልተዘጋጁበት ሰአት በርካታ ወንበር ማግኘታቸዉ አስከዛሬም እንዳያገግሙ ላደረገ ጎዳት ዳረጋቸዉ እንጂ አልጠቀማቸዉም፡፡ ምክንያቱም የህዝቡን ድምጽ ንቀዉ ምርጫዉን መቀለጃ አድርገዉ ያገኙትን ወንበር ሳይጠቀሙበት በመቅረታቸዉ ነዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ህዝቡን ክፉኛ በማስቀየመቻዉ ከዚያ በኋላ በነበሩት ምርጫዎች ሁሉ ተቃዋሚዎች የገጠማቸዉ የወንበር ድርቅ የዚያ ዉጤት መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ሙሉ በሙሉ ያሸነፉበትን የአዲስ አባባን መስተዳዳር ለመረከብና ለህዘቡ ቃል በገቡለት መሰረት ለመፈጸም ፍላጎት አላሳዩም ነበር፡፡ የቅንጅት አመራራች “የምንታገለዉ ህዝብን የትክክለኛ ዲሞክራሲ ባለቤት ለማድረግ ነዉ፡፡ ” እንዳላሉ ስልጣን እንደሚይዙ እንኳን ገና እርግጠኛ ሳይሆኑ እርስ በርሳቸዉ በስልጣን ሽኩቻ መቧጨቅ ጀመሩ፡፡

ተቃዋሚዎችም ያገኙትን ድል አጣጥመዉ በያዙት መቀመጫ ተጠቅመዉ በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ተነሳሽነት በማጎልበትን ራሳቸዉን ነለሌላ ምርጫና ለሌላ ድል ከመዘጋጀት ይልቅ ከመንግስትነት ውጭ ያለውን አማራጭ ሁሉ ለመቀበል ባለነፍቀዳቸዉ ከሁሉም ሳይሆኑ ከመቅረታቸዉም ሌላ ዳግም በአንድነት ለመቆም በማያስችላቸዉ ደረጃ ለክፍፍል ተዳርገዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ከንቲባነት ሃላፊነት በፓርቲዉ የታጨዉ ብርሃኑ ነጋ “እኔ የምፈልገዉ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ነዉ እንጂ የከተማ ሹም መሆን አይደለም” ቢሎ በማኩረፍ ሌሎችንም አስተባባሮ ብዙ ሰበብ ከደረደሩ በኋላ አዲስ አበባ መስተዳዳርን ሳይረከቡ እንደቀሩ ይታወቃል፡፡ የዚያን ግዜዉ የቅንጅት ነገር ሲታወስ ልክ በጦር ሜዳ ወታደሮቹን በአዉላላ ሜዳ ለጠላት አጋልጦ እንደሸሸ የጦር ጄኔራል ነዉ ያስቆጠራቸዉ፡፡ የፓርቲዎች ህዝባዊ አመኔታ ደግሞ ልክ እንደ ልጃገረድ ክብረ-ንጽህና ሊቆጠር የሚችል ነዉ፡፡ ረዉ -አንዴ ከተገሰሰ በቦታዉ መመለስ የማይቻል፡፡ በቅንጅት ሁኔታ እጅግ የተቆጣዉ መራጩ ህዝብ ”ከነዚህስ ያዉ አንዴ የለመድነዉ ኢህአዴግ ይሻለናል፡፡ እሱኑ እያረምነዉና እየገሰጽነዉም ቢሆን እናሰራዋለን” በማለት የተቃዋሚዎችን ነገር እርም! ለማለት የበቃዉም በራሳቸዉ በተቃዋሚ መሪዎች ስህተት ነዉ፡፡ ቅንጅት ህዝብን ክፉኛ አሳዝኖ ከዚያን ግዜ ወዲህ መቼም ቢሆን እንዳይታመን ሆኖ ቆለዉ ተገፎ ይሄዉ አስከ ዛሬ በሱ ጦስ ህዝቡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በጅምላ አመኔታ እንዳይኖረዉ አደረገ፡፡

በወቅቱ ኢህአዴግ የደረሰበትን አጓጉል ሽንፈት ለመደበቅም ሆነ ሰበብ ለማብዛት አልሞከረም፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ መራጩ ህዝቡ ኢህአዴግን ሊቀጣዉ ወይንም አንድ ነገር ሊያስተምረዉ እንዳሰበ ኢህአዴግ በሚገባ ተገንዝቧል፡፡ ስለሆነም በሽንፈቱ ማግስት ወደ ህዝቡ ቀርቦ “ያልመረጣችሁኝ ስለ አልሰራሁላችሁ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እኔን አለመምረጣችሁም ተገቢ ነዉ፡፡ ፊላጎታችሁን አከብራለሁ፡፡ ስህተቱ የእኔ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ” ነበር ያለዉ፡፡ ኢህአዴግ ሽንፈቱን ማመኑን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ በመሄድ ቅንጅትን ”እባክህን መስተዳድርሩን (አ.አ) ተረከበኝ” ቢሎ በይፋ አስከመማጸን ደርሷል፡፡ ለህዝቡም“የመረጣችሁት ቅንጅት የሚባለዉ ፓርቲ መስተዳድሩን ላስረክበዉ እየጠበኩት ብሆንም አስካሁን ሊረከበኝ አልቻለም ” በማለት በይፋ አስከመናገር ደረሰ፡፡ በወቅቱ (በምርጫዉ ዕለት ይመስለኛል) የቅንጅትንም ሆነ የኢህአዴገን መሪዎች እዚሁ አዲስ አበባ ተገኝቶ በየተራ ቃለ መጠይቅ ያደረገዉ ታዋቂዉ የቢቢሲ ሃርድ ቶክ ጋዜጠኛ ስተፈን ሳኩር(Staphun Sackur) ቅንጅት ምርጫዉ ተጭበርብሯል በሚል ያለ አንዳች ምክንያት ለምን በኢህአዴግ ላይ እንዳማረረ ግራ መጋባቱን አሁን በህይወት ለሌሉት ለአቶ ኃይሉ ሻዉል በትዝብት መልክ እንዳነሳባቸዉ እናስታዉሳለን፡፡

ለኢህአዴግ “የአ/አ መስተዳዳርን ተረከበኝ”ጉትጎታ ቅንጅት የሰጠዉ ምላሽ ግን በህዝቡም በኢህአዴግም ሆነ በዉጭዉ ማህበረሰብ ዘንድ ፈጽሞ ያልተጠበቀና ሊደረግ የማይገባም ከመሆኑ ሌላ ቅንጅት ለህዝብ የነበረዉን ንቀትም ያረጋገጠ ነበር፡ ፡የዉጭ ዜጎች በአፍሪካ በምርጫ ሽንፈቱን በጸጋ መቀበሉ ሳያንስ “ስልጣን ተረከቡኝ” ቢሎ ተቃዋሚን የሚለማመጥ የመጀመሪያዉ ብቸኛ ገዥ ፓርቲ ቢኖር እህአዴግ ብቻ እንደሆነ በአግራሞት ሲገልጹ ነበር፡፡ ቅንጅት በእጁ የገባዉን መልካም አጋጣሚ ከመጠቀም ይልቅ ፓርላማ ላለመግባትና አዲስአበባን መስተዳድር ላለመረከብ ቦይኮት ካደረገ በኋላ በቀጥታ ያመራዉ ምርጫዉ ተጭበርብሯል በሚል ወጣቱን አነሳሰቶ ሁከት መፍጠር ነበር፡፡ ከምርጫዉ ማግስት ጀምሮ በቅንጅት ጦስ በሀገሪቱ የደረሰዉን ምስቅልቅል መቼም ቢሆን አንዘነጋዉም፡፡ ከዚህ ሁኔታ በኋላ ቅንጅትም ሆነ ሌለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዴት ሆኖ ነዉ የህዝብን አመኔታ በድጋሚ ሊያገኝ የሚችለዉ?

የግንቦት 97 ምርጫ ለኢህአዴግ ትልቅ ትምህርት ሆኖት ከዚያ በኋላ ባሉት ግዜያት የህዝቡን የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ አንድ ባንድ መልስ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ በአዲስ አበባም ሆነ በመላዉ ሀገሪቱ ተአምር ሊሰኝ የሚችል ለዉጥ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በ97 ምርጫ በርካታ ወንበር ማጣቱን እንደ ዉድቀት ሳይሆን የቆጠረዉ ይልቁንም ጠንክሮ በመስራት ከምንግዜም በበለጠ የህዝብ ድጋፍ እንዲያገኝ ያስቻለዉ መልካም አጋጣሚ አድርጎ ነዉ የቆጠረዉ ማለት ይቻላል፡፡ ከ97 በኋላ በተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ ኢህአዴግ ማሸነፍ የቻለበት ዋነኛ ምክንያትም ከፊሉ ህዝብ በተቃዋሚዎች ላይ ይዞት የቆየዉ ጥርጣሬና አለመተማማን ሊቀረፍ ባለመቻሉ ተቃዋሚዎችን ከመምረጥ ኢህአዴግን መምረጡ እንደሚሻል በማመኑ ሲሆን ሌላዉ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ኢህአዴግ በርግጠኝነት ለለዉጥ መዘጋጀቱን በመተማማን በፍላጎታቸዉ አዎንታ በመስጠታቸዉ ነዉ፡፡ የተቀረዉ ደግሞ በሀገሪቱ በሚደረገዉ ምርጫ እርካታ በማጣት ይልቁንም ምርጫን ተከትሎ በሚከሰቱ ሁከቶች በመሰላቸት በግደለሽነትና በምንቸገረኝነት ብዙም ሳያምንበት የመገላገል ያህል ለኢህአዴግ ድምጹን በመስጠቱ ነዉ፡፡

የኢህአዴግን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ በሚመለከት “ኢህአዴግ ምርጫዉን አጭበርብሯል” ከሚለዉ ወቀሳ ይልቅ የራሳቸዉ የተቃዋሚዎች ድክመትና የመራጩ ህዝብ ለምርጫዉ ያሳየዉ ግደለሽነት በምክንያትነት የበለጠ ሚዛን የሚደፉ ይመስለኛል፡፡ ይህ የመራጩ ህዝብ ግደለሽነት አስቀድሜ አንደጠቆምኩት በምርጫዉ ላይ እርካታ ከማጣት የመነጨ ነዉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ 100% የተባለዉ የ2007 ምርጫ ዉጤትን በተመለከተ እንኳን እኔ ኢህአዴግ ራሱ የሚያምንበት አይመስለኝም፡፡ ዉጤቱ ብዙ ነገር ያበላሸበት በመሆኑ መቶ በመቶ በሚባለዉ የምርጫ ዉጤት ኢህአዴግ ብዙም ደስተኛ እንዳልነበር እገምታለሁ፡፡

በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ዉስጥ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1957ዓ/ም ጀምሮ በሶስቱም መንግስታት ዘመን በተከናወኑት በድምሩ ዘጠኝ (9) የፓርላማ ምርጫዎች ሁሉ የ1997ቱ ምርጫ በመራጭ ዜጎችና በዉጭ ታዛቢዎች ግምገማ መሰረት በእዉነተኛ መድበለ ፓርቲ ስርአት ዉስጥ ብቻ የሚታይ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሆነ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ ስለ 97 ምርጫ ልዩ መሆን ተቃወሚ ፓርቲዎችም ሳይቀሩ ያረጋገጡት ነዉ፡፡ ለምሳሌ ኢዴፓ ስለ 97 ምርጫ ሁኔታ የሰጠዉ ምስክርነት አስቀድሜ ከጠቀስኩት ጋር የሚስማማ ነዉ፡፡ ኢዴፓ በደርጅታዊ መግለጫዉ ምርጫ ዘጠና ሰባት በኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ታሪክ ተጠቃሽ ነው፡፡ ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው ለዚህ ታሪካዊነት እንዲበቃ ያደረጉት ሃይሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ ገዢው ፓርቲ፣ ተቃዋሚዎች ሲሆኑ በተለይ ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ በተፈጠረው አበረታች ሁኔታ መብቱን ላለማስነጠቅ በምርጫ ንቁ ተሳትፎ ያደረገው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የምርጫው ሒደት የፈጠረው መነቃቃት፣ መከባበር፣ አውቅና መስጠትና ይህ ቀረሽ የማይባል ንቁ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ትንሳኤ እንደነበር ለመዘንጋት አይቻልም፡፡ ” ኢዴፓ በምርጫዉ ባገኘዉ ዉጤት ባይረካም የምርጫዉን ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ሳያረጋገጥ አላለፈም፡፡

የ1997 ምርጫ ከፍተኛ ዉድድር የታየበት በሀገሪቱ ዉስጥ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ከተከናወኑት ምርጫዎች ሁሉ ዲሞክራሲያዊ፤ ነጻና ግልጽነት የሠፈነበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ምርጫዉ ተቃዋሚዎች 173 የሚጠጋ በፈዴራል ደረጃ የፓርላማ መቀመጫ ያስገኘላቸዉ ሲሆን በአንዳንድ ክልሎችም ቀላል የማይባል መቀመጫ ማግኘት ችለዉ የነበረ መሆኑ ሲታሰብ ያገኙት ድል በቀላሉ ሊያዩት የሚገባ አልነበረም፡፡ በ97 ምርጫ በዚያ መልኩ ተቃዋሚዎች በርከታ መቀመጫ የማፈሳቸዉ ምክንያት መንግስት የምርጫዉን ህግ ከማሻሻል ጀምሮ ምርጫዉ ያለ እንከን እንዲከናወን ለማድረግ በርካታ ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ እንደነበር ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ ምርጫ 97 ሲታወስ ከምርጫዉ በኋላ የተከሰተዉ አሳዛኝ ክስተት አብሮ መነሳቱ ባይቀርም ነገር ግን ከችግሩ ይልቅ ከዲሞክራሲ አንጻር የነበረዉ ፋይዳ በሀገሪቱ ምርጫ ታሪክ የበለጠ ቦታ ሊሰጠዉ ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡

ከ1997 ምርጫ በኋላ የተከናወኑት ሁለቱ አጠቃላይ ምርጫዎች ማለትም የ2002 አና የ2007 የምርጫ ዉጤት ሲታይ ወደ ፓርላማ ለመግባት ለተቃዋሚዎች ፍጹም የማይሞከር ያስመሰለ ምርጫዎች ነበሩ፡፡ በተለይ የ2007 ምርጫ አንድም ተቃዋሚም ሆነ በግል ተወዳዳሪ ፓርላማ መግባት እንዳይችሉ ያደረገ ብቸኛ ምርጫ ነዉ፡፡ ይህ ምርጫ የሀገራችን የዲሞክራሲ ሁኔታ ተሻሽሎ ለማየት ለምንመኝ ዜጎች ምቾት የማይሰጥ አሳዛኝ ክስተት ነዉ ማለት እችላለሁ፡፡ እነዚያን ሁለት ምርጫዎች በምንም መልኩ ቢሆን በመልካም ጎናቸዉ ማስታወስ አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ ደጋግሞ ደጋግሞ ቢያሸንፍ ፈጽሞ የማይከፋቸዉ ዜጎች እንኳን ሳይቀሩ በነዚህ ሁለት ምርጫዎች ዉጤት በእጅጉ ቅር መሰኘታቸዉንና በሃፍረት መሸማቀቃቸዉን ከቶ መደበቅ አይቻልም፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይህን “የ100% ድል ” እንደ ጀግንነትና እንደ ኢህአዴግ ብቃት መለኪያ ሲቆጥሩት እንደመስማት የሚያናድደኝ ነገር የለም፡፡ ኢህአዴግ በነበረዉ ጥንካሬ ማሸነፍ መቻሉ ብቻ ሳይሆን ማሸንፍ እንዳለበትም የሚያከራክር ባይሆንም መቶ በመቶ አሸነፍኩ ማለቱን ልናደንቅለት የሚገባን አይመስለኝም፡፡ ምርጫዉ ተጀምሮ አስከሚጠናቀቅ በነበረዉ ሂዴት ዉስጥ የሆነ ቦታ ላይ አንዳች እንከን ካልኖረ በስተቀር የዚህ ዓይነት ዉጤት ሊመጣ አይችልም፡፡

2. ኢህአዴግ “አበቃለት!” ሲባል ወድቆ የመነሳቱ ነገርና ከዉድቀት የማዳን ሃላፊነትን በሚመለከት፤

2.1 ኢህአዴግ ከአደጋ ለመዉጣት እያደረገ ያለዉ ጥረት ዳግመኛ ይሳካለት ይሆን?

ኢህአዴግ ስለ ራሱ ደጋግሞ ከነገረንና እኛም በተግባር ያራጋገጥንለት አንዱ ጠንካራ ባህሪዉ ከባድ ችግር ባጋጠመዉ ግዜ ሁሉ እንደምንም አድርጎ ከአደጋዉ ወጥቶ ጭራሽ ከቀድሞዉ በበለጠ ጠነክሮ መገኘት መቻሉ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ከእንግዲህ አበቃለት ቢለዉ ስልጣን ለመረከብ ሲቋምጡ የነበሩትን ሁሉ ”ታመምኩ እንጂ አልሞትኩም!” በሚል ጭራሽ ጉልበት አበጅቶ ሲያዩት ክፉኛ አይናደዱበትም ማለት አይቻልም፡፡ 1993 መጨረሻ ላይ ይፋ በሆነዉ የድርጅቱ መሰነጣጠቅና ቁልፍ አመራሮቹ ድርጅቱን ለቀዉ መዉጣት ወሬ ሲሰማ ብዙዎቻቻን ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ሊያበቃለትና “ነበር” ወደ ሚባልበት ደረጃ ለመቀየር አንድ ሀሙስ ብቻ ቀርቶታል ባልንበት ወቅት ላይ እንዴት እንደሆነ ባልተረዳነዉ ፍጥነት ከወደቀበት ተነስቶ አቧራዉን አራግፎ “አለሁ” ሲለን ከመደነቅ ዉጭ ሌላ ምንም ማለት አልቻልንም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የ97 ምርጫ ወቅትም በ93ቱ ቀዉስ የተዳከመዉን ኢህአዴግ ያለጥርጥር እንደሚሸነፍ ተስፋ አድርገዉ የነበሩ ፓርቲዎች እነሱ እንደጠበቁት ኢህአዴግ በቀላሉ ወድቆ በዚያዉ የሚቀር አለመሆኑ በተግባር ለመረዳት ያስቻለ አጋጣሚ ነበር፡፡

ካለፈዉ ሁለት ዓመት ጀምሮ በሀገሪቱ ዉስጥ የተፈጠረዉ መጠነ ሰፊ ቀዉስም ቢሆን ሁኔታዉ ለኛ አጅግ አስጊና አስደንጋጭ መሆኑ ባይቀርም ለኢህአዴግ ግን እንደ ማንቂያ ደወልና ራሱን ፈትሾ ተጠናክሮ እንዲመጣ ምክንያት ከመሆን ባለፈ ለህልዉናዉ ያን ያህልም አስጊ እንዳልነበር እንድንረዳለት ሊያሳየን ከሚሞክረዉ መረጋጋትና ዘና የማለት ሁኔታ መረዳት ችለናል፡፡ ኢህአዴግ ሁኔታዉን ለማቃለል እንደሞከረዉ ሳይሆን ተጨባጭ ሁኔታዉ የሚያሳየን ዉስብስብና አንዱ ችግር መፍትሄ ሳይበጅለት ሌላ ችግር በላዩ እየተደረበና በዓይነትም እየጨመረ የመጣበትና መፍትሄዉም ዘለግ ያለ ግዜና ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ መሆኑን ነዉ፡፡

አሁን ድርጅቱና መንግስት ከገጠሙት በርካታና ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንጻር የድርጅቱ ወድቆ የመነሳት ችሎታ ከዚህ በኋላም በምን ያህል ደረጃ ሊሳካለት እንደሚችል በርግጠኝነት መናገር ሳይከብድ አይቀርም፡፡ ኢህአዴግ በወደቀና አደጋ ባጋጠመዉ ቁጥር ”አንሱኝ አግዙኝ“ የሚለዉን ተማጽኖ ሰምተን አስካሁን ለማገዝ ባደረግነዉ ጥረት ብዙ ጉልበት ጠይቆናል፡፡ የአሁኑ ሁኔታዉ ግን አወዳደቁ እንደማያምርና በቀላሉ ሊወጣ ወደማይችልበት ወደ ጥልቁ ጉድጓድ እየወደቀ እንዳይሆን እንድንገምት አድርጎናል፡፡ ለዚህ ስጋትና ጥርጣሬ መነሻ የሆነኝ አሁን ድርጅቱን እንደ ገዥ ፓርቲ እየገጠሙት ያሉት ችግሮች በባህሪያቸዉ ከዚህ ቀደም ከተከሰቱት በበለጠ እጅግ ዉስብስብ መሆናቸዉና መፍትሄአቸዉም አስቸጋሪና ፈጽሞ የማይቻል በመምሰሉ ነዉ፡፡ ከነዚህ ችግሮች ለመዉጣት የበለጠ አዳጋች ያደረገዉም ከችግሮቹም በላይ የራሱ የኢህአዴግ ዉስጣዊ ድክመት መኖር ነዉ፡፡ ይህ የድርጅቱ ችግር በጥቂት ግለሰቦች ወይም የአመራሩ አካባቢ ብቻ የሚታይ ቢሆን ኖሮ ብዙም አሳሳቢ ባልሆነ ነበር፡፡ ነገርግን እንደ ድርጅት ስር የሰደደ፤ ማንንም ከማንም ሳይለይ የድርጅቱ አመራራም ሆነ ተራዉ አባል እንዲሁም የመንግስት ሹማምንት ሁሉ ላይ ተቋማዊ በሚመስል መልኩ የተጣባ አደገኛ ዝንባሌ በመሆኑ ነዉ፡፡ ይህ የኢህአዴግ ሰዎች ያልተለመደ መጥፎ ዝንባሌ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ጥብቅና የመቆም የቆየ መሪህ ዉጭ ከህዝባዊነት አመለካካት እያፈነገጡና ሀገርናና ህዝብን በሚጎዳ ደረጃ ለራስ ጥቅም መንሰፍሰፍ በስፋት መለመዱ ነዉ፡፡ መንግስት ራሱ የሾማቸዉ ባለስልጣናቱና እሱን የተጠጉ ግለሰቦች በስንት ምልጃና ልመና በህዝብ ስም ከዉጭ የተገኘ ብድር ሳይቀር ወደነዚህ ግለሰቦች ኪስ ሲገባና የመንግስት ስልጣንን መከታ ባደረገ በተደራጀና በተቀነባበረ መንገድ በሚካሄድ ዝርፊያ ህዝቡን አስመርረዉ ሀገሪቷን አጽሟ አስከሚቀር እየጋጧት መሆኑን እያየ ዝርፊያዉን ለማስቆም እንደ መንግስት የሚጠበቅበትን ያህል ቁርጠኝነቱ ያለማሳየቱ ዋነኛዉ መነሻ ምክንያት ድርጅቱ ራሱን በራሱ እጅ እንደመቁረጥ አድርጎ በሚያስቆጥርበት ደረጃ የራሱን ተሿሚዎች አደብ ማስገዛት አስቸጋሪ ስለሆነበት ነዉ፡፡

ትላንት የተፈጸመ ዝርፊያ ገና እልባት ሳይሰጠዉ አዳዳስ ዝርፊዎች ብቅ ይላሉ፡፡ አንዱ ዘራፊ ገና እርምጃ ሳይወሰድበት ሌሎች በርካታ ቁጥር ያላቸዉ ዘራፊዎች ብቅ ይላሉ፡፤አንዱ የዝርፊያ መንገድና ስልት ሳይዘጋ ሌሎች የተራቀቁ አዳዲስ ስልቶች በስራ ላይ ይዉላሉ፡፡ የሚዘረፈዉ ገንዘብ መጠን ራሱ በየግዜዉ እጅግ እየጨመረ ሲሄድ እየታየ ነዉ፡፡ ዘራፊዎች ምን ያህል ለህዝብና ለሀገሪቱ የጠላትነት እርኩስ መንፈስ እንደተጠናወታቸዉ ማረጋጋጫ የሚሆነዉ የሰረቁትን ገንዘብ ወደዉጭ ማሸሻቸዉ ነዉ፡፡ ቻይናና ህንድን የመሳሳሉ ሀገሮች በዉጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎቻቸዉ ሰርተዉም ይሁን ሰርቀዉ ያገኙትን የዉጭ ምንዛሪ ሁሉ ወደሀገራቸዉ በመላክ ሀገራቸዉን እንዴት እንደሚያግዙ ስንሰማ የኛዎቹ ዘራፊዎች ግን እንኳን ከዉጭ ማምጣት ይቅርና እዚሁ ከህዝብ ጉሮሮ እየነጠቁ ወደ ዉጭ ሲያሸሹና በዘረፉት የደሃ ህዝብ ንብረት በተለያዩ ሀገሮች ግዙፍ ተቋማትን ማቋቋማቸዉን ስንሰማ ምን ያህል የህዝብ ጠላቶች እንደሆኑ በቀላሉ ለመረዳት እንችላለን፡፡ መንግስት በየዓመቱ የሚመድበዉ እጅግ የተቆለለ ባጄት ለባለ ባጄት መስሪያ ቤቶች ሲመድብ ሙሰኛ ዘራፊዎችም ከበጄቱ ከ2 አስከ 3 ከመቶ የማያንስ ሊዘርፉ እንደሚችሉ ታሳቢ እያደረገና ለዝርፊያዉም ቅድመ እዉቅና እየሰጠ አስመስሎበታል፡፡ በየዓመቱ በዘራፊዎች የሚዘረፈዉ ገንዘብ መጠን በትንሹ የአንዳንድ ክልሎችን ዓመታዊ ባጄት ቢበልጥ እንጂ የሚተናነስ አለመሆኑን ተረድተናል፡፡ ይሄ ሁሉ ዝርፊያ የሚደረገዉ ከዉጭ በመጣ ጠላት ሳይሆን እዚሁ መሃላችን ባሉና ይልቁንም ጸረ- ድህነት ትግሉን በግንባር ቀደምነት መርተዉ ከድህነት ያወጡናል ብለን እጅግ የተማመንባቸዉ የገዥዉ ፓርቲና የመንግስት ባለስልጣኖቸችን ጭምር የተሳተፉበት መሆኑን ስታሰብ ሁኔታዉ ለኛ አሳዛኝ ከመሆን አልፎ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብናል፡፡

መንግስታችንም ይሄ ሁሉ ዝርፊያ ሲደረግ እያወቀ ከማስፈራትና ከመድረክ ላይ ዉግዘት ባለፈ አንዳችም የሚቆነጥጥ እርምጃ ሳይወስድ ለብዙ ግዜ ሲያደፍጥ ከርሞ ነዉ ሁኔታዉ ከባሰበት በኋላ አሁን ገና መንቀሳቀስ የጀመረዉ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ከስንት ዓመት በፊት የባለስልጣናት ሀብት መዝግቦ ይፋ ለማድረግ ቃል የገባዉን መፈጸም ያልቻለበት ምክንያት ከዚህ ደሃ ህዝብ መዘረፍ ይልቅ ጥቂት ዘራፊና ሙሰኛ ባለስልጣናትና ግለሰቦችን ስምና ክብር መጠበቁ በልጦበት ላለማጋለጥ ታስቦ እንደሆነ ህዝቡ በስፋትና በቁጭት የሚናገረዉ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ በህዝብ ላይ እየደረሰ ባለዉ መጠነ ሰፊ ጥፋት ላይ ባሳየዉ ዳተኝነት እጅግ የተማረረዉ ህዝብ ኢህአዴግ እየወደቀ ካለበት ጥልቅ ጉድጓድ እንዲወጣ ቀድሞ እንዳደረገዉ አሁንም ያግዘዋል ለማለት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስንት በደል እየደረሰበትም ከኢህአዴግ ዉጭ ሌላ ፓርቲ አንፈልግም እያለ ኢህአዴግን ደጋግሞ ሲመርጠዉ ለቆየዉ ምስኪን ህዝብ ትንሽ እንኳን ከበሬታ መሳየት በተገባዉ ነበር፡፡

2.2 ኢህአዴግን ከዉድቀት የማዳን ሃላፊነት የማን ነዉ?

ኢህአዴግ እየተከተለ ባለዉ የተሳሳተ መንገድ ለከፋ አደጋ አንዳይጋለጥ ማረምና ከድክመቱ ተላቆ ወደ ትክክለኛዉ መስመር በመመለስ ከዉድቀት እንዲታደግ ማድረግ የማን ሃላፊነት ነዉ ?በሚለዉ ላይ ሁሉን የሚያስማማ አንድ ወጥ መልስ መጠበቅ እንደማይቻል ግልጽ ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ “ከእንግዲህ ወዲያ ኢህአዴግን ለማስተካካል ቢፈለግ እንኳን መመለስ የማይችልበት አደገኛ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ ኢህአዴግን ለማዳን መሞከር ትርፉ ድካም ነዉ” የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሆነዉ ሌሎች ወገኖች ድግሞ ይሄ ስራ የጥቂት የፓርቲዉ አመራሮችና አባላት ግዴታ እንጂ እኛን የሚመለከት አይደለምና ያልበላንን የምናክበት ምክንያት አይኖርም የሚሉም አሉ፡፡ ኢህአዴግ ጫናዉ በዝቶበት ራሱን ማስተካካል አቅቶት የቁልቁለት ጉዞ በጀመረበትና በሱ ጦስም ሀገሪቱ ለአደጋ ልትጋለጥ እንደሚትችል በተሰጋበት ወቅት ሁሉ “ኢህአዴግ የተፈጥሮ ሞቱን እየሞተ ስለሆነ ዝም ብላችሁ ተመልከቱት እንጂ ልታድኑት አይገባም” በሚል የሚመክሩ ሰዎች ችግሩን በሚገባ የተረዱት አልመሰለኝም፡፡

ኢህአዴግ ለከፋ አደጋ ተጋርጦ እየታየ በዝምታ ማየት ተገቢ የማይሆነዉ በሌላ ምክንያት ሳይሆን ሀገር እየመራ ያለ ድርጅት በመሆኑ ነዉ፡፡ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ በብዙ ጉዳዮች ከኢህአዴግ ጋር እንዲቆራኝ ተደርጎ በመቆላለፉ የኢህአዴግ ለአደጋ መጋለጥ ማለት ሁላችንም ለአደጋ መጋለጥ ማለት መሆኑ አያከራክርም፡፡ የኢህአዴግን አጉል አወዳዳቅ ማየት የማይፈልጉ ወገኖች ሀገሪቱንም ይዞ አብሮ ገደል እንዳይገባ ገና በጠንካራ ቁመና ላይ በነበረበት ወቅት ጀምሮ ገንቢ አስተያየትና እርምት ለመስጠት መሞከራቸዉ ለኢህአዴግ የተለየ ፍቅር ወይም ጥላቻ ስለነበራቸዉ ሳይሆን ለሀገሪቱ መጻኢ ዕድል በማሰብ ነዉ፡፡ የኢህአዴግን ዉድቀት እንዲፋጠን የሚፈልጉ ወገኖች ሌላዉ ቀርቶ በተጀመረዉ የጸረ- ሙስና ትግል መንግስትን ለማገዝም ሆነ ለማበረታት አይሹም፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ጀምሮ በሌሎች የልማት ስራዎቸ ሁሉ ኢህአዴግ ስሙ በመልካም እንዳይነሳ ስለሚፈልጉ ለሀገር ጠቃሚ የሆነ አንድም ጉዳይ ላይ መሳተፍ አይፈልጉም፡፡ ሙስናንና የመልካም አስተዳዳር ችግርን በጋራ መታገል ማለት ኢህአዴግን በተለየ እንደመጥቀም ቢሎም እድሜዉን እንደማራዘም አድርገዉ ነዉ የሚቆጥሩት፡፡ ስለዚህ የዚህ አመለካከት ተሸካሚ የሆኑ አንዳንድ ወገኖች መንግስትን ማገዝ ማለት ሀገሪቱን ማገዝ ማለት መሆኑን ለመቀበል ስለማይፈልጉ ኢህአዴግን ከዉድቀት ለማዳን ጥረት ማድረግ ሳይሆን አስከነአካተዉ ዉድቀቱ እንዲፋጠን ተጨማሪ ቀዉስ መፍጠሩ ነዉ ተገቢ መስሎ የሚታያቸዉ ፡፡ ቢቻላቸዉ ኢህአዴግን ወደ ገደል ገፍትረዉ ከመጣል የማይመለሱ ወገኖች ኢህአዴግንም ሆነ ሀገሪቱን ከቀዉስ ማዉጣት የኢህአዴግን አድሜ እንደማራዘም አድርገዉ ስለሚቆጥሩ በሀገሪቱ ዉስጥ ቀዉስና ሁከት ተባብሶ እንዲቀጥል ነዉ የሚሹት፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግን ለመጉዳት ሲባል ኢህአዴግ የሚመራት ሀገር አብራ ብትወድም ግድ አይሰጣቸዉም፡፡

አብዛኛዎቻችን ኢህአዴግን የየዕለቱ ዋነኛ አጀንዳችን ማድረጋችን ብጨንቀን እንጂ ወደን አይደለም፡፡ ስለ ኢህአዴግ አዘዉትረን መነጋገራችን ኢህአዴግን ሲያበላሽ መዉቀሳችንና መልካም ሲሰራ ደግሞ ማመስገናችን ወዘተ ሁሉ ያለመክንያት አይደለም፡፡ ስለ ኢህአዴግና በኢህአዴግ ዙሪያ ነጋ ጠባ መብከንከናችን ኢህአዴግ ዝም ብሎ የፖለቲካ ፓርቲ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ በሀገሪቱ ቁጥር ስፍር የሌላቸዉ እንደአሸን የፈሉ ሌሎች ፓርቲዎችና ፓርቲ መሰል ቡድኖች በሞሉበት ሁኔታ ስለ ኢህአዴግ ብቻ ነጋ ጠባ መጨነቃችንና የዉይይት አጀንዳ ማድረጋችን ዋናዉ ምክንያት የመቶ ሚሊዮን ህዝብና የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ በእጁ የሚገኝ ለሀገሪቱ እድገትም ሆነ ዉድቀት ሃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ገዥ ፓርቲ በመሆኑ ነዉ፡፡ ስለዚህ ገዥዉ ፓርቲን በግል የመረጥነዉም ያልመረጥነዉም ብንሆን ሁላችንም እኛ እንደምንፈልገዉ እንዲያስተዳድረን ልንነግረዉና ልናርመዉ ይገባል፡፡ ከመስመሩ እንዳይወጣም ልንቆጣጠረዉ ይገባል፡፡ ይህን የምናደርገዉ ለራሳችንና ለሀገራችን ስንል እንጂ ለኢህአዴግ ብለን አይደለም፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን የዜጎችን ጩሄት ይሰማል ተብሎም ተስፋ ይደረጋል፡፡ ለኢህአዴግ በመልካም ስራዉ የበለጠ እንዲጠነክር ድክመቱን ደግሞ እንዲያርም አስተያየት የሚሰጡ ዜጎች ሁሉ ይህን የማድረግ የተለየ ሃላፊነት ስለአለባቸዉም አይደለም፡፡ እንዲዉም በአብዛኛዉ ለኢህአዴግም ሆነ ለሀገሪቱ ይበጃል በሚል ቀና አስተያየት የሚሰጡ ዜጎች ከምኑም የሌሉበትና ከየትኛዉም ፓርቲ ዉገና ገለልተኛ የሆኑ እንደሆኑ እገምታለሁ፡፡ ኢህአዴግ እነዚህ ዜጎች ለሚሰጡት አስተያየት ምን ያህል ጆሮዉን ያዉሳል በሚለዉ ላይ አርግጠኛ ሆኖ መናገር ይከብዳል፡ኢህአዴግ ቢያንስ ከነእንከኑም ቢሆን በስልጣን ላይ ለሁለት አሰርተ ዓመታት በላይ እንዲቆይ ለፈቀደለት ህዝብ ከበሬታ ሊኖረዉ ይገባል፡“እኔ ከለለሁ ምን ይበጃችኋል ? ወይኔ ልጂቼ!”እያለች ለልጆቿ ብቸኝነትና አይዞ ባይ አጥተዉ መቸገር በዓይነ ህልናዋ እየታያት እንደሚታዝን የዋህ ርህሩህ እናት ኢህአዴግም “እኔ ስልጣን ላይ ከሌለዉ የኢትዮጵያ ሀዝብ ምን ይበጀዋል?”እያለ መቀለድ ያለበት አይመስለኝም፡፡ ፡“እኔ በስልጣን ላይ ከለለሁ ሀገሪቱ ትበታታናለች!” የሚል አቋም አሁንም ካለዉ ይህን አቋሙን እንዲያስተካካል እንመክራለን፡፡ ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ የሚደረገዉም ለኢህአዴግ ተብሎና የኢህአዴግን ስልጣን ለማደስ ተብሎ እንዳልሆነም ሊያዉቅ ይገባል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ የኢህአዴግን እንከኖች እያየ በይቅርታ ማለፉ ኢህአዴግ አንዳችም ችግር ስለአልነበረበት ሳይሆን ከዛሬ ነገ ይታረማል በሚል እምነት መሆኑን ተረድቶ ከእንግዲህ ከህዘብ ጋራ ላለመቀያየም ራሱን ለህዝቡ ሙሉ በሙሉ ለማስገዛት ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል፡፡

ኢህአዴግ እኛ እንደ አሰብነዉ ሊሆንልን ካልቻለ በሚቀጥለዉ ምርጫ አለጥርጥር እናወርደዋለን እንጂ ኢህአዴግን ስለ ጠላን ብቻ ሀገራችን ለአደጋ አናጋልጥም፡፡ በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ድምጻችንን ነፍገነዉ ኢህአዴግን በሌላ መተካት እየቻልን በእልህና በንደት በሁከት መንገድ የምንሄድበት ምክንያት ጭራሽ ሊኖር አይገባም፡፡ ኢህአዴግንም ሆነ ሀገሪቱን ማዳን ሲባልም የኢህአዴግን መፈክር ማጮህ ማለት ሳይሆን ህገወጡንና የሁከት መንገዱን አሻፈረኝ ብለን ሰላማችንና ደህንነታችንን ለአደጋ ሳናጋልጥ ለቀጣዩ ምርጫ በትእግስት መጠበቅ ማለት ነዉ፡፡ መታገስ አቅቶን በትንሽ በትልቁ በቁጣ ተነሳስተን ወደ አልተፈለገ ሁከት ብንገባ ከጉዳት በስተቀር አንዳችም በጎ ነገር ማምጣት እንደማንችል ልንዘነጋ አይገንም፡፡ የህዝብን ምሬት ያባባሱና ህዘብን ለቁጣ የዳረጉ ሁኔታዎችን ለማስተካካል ኢህአዴግ ብስለት የተሞላበት መፍትሄ ያስቀምጣል ብለን ተስፋ ስለምናደርግ የሀገራችንን ሉአአላዊነት አደጋ ላይ ወደሚጥል ሁከት ተገፋፋተን መግባት አይኖርብንም ፡፡ ስለዚህ ስርአቱንም ሆነ ሀገሪቱንም ከአደጋ ለማዳን ስንል ኢህአዴግን ሃላፊነት እንደሚሰማዉ መንግስት ለችግሮቻችን በርግጠኝነት መፍትሄ እንዲያመጣ ተማምነን ቢቻል እገዛ ሊናደርግለት ይገባል ካልሆነም ተጨማሪ ችግር ከመፍጠር ራሳችንን ልናቅብ ይገባል፡፡

3 በሀገራችን የመራጭ ዜጎች የፓርቲ ዉገና ዝንባሌ ፤

3.1 መራጮች አንድን ፓርቲ የሚወግኑበትና የሚመርጡበት መነሻ ምክንያቶች፤

በሀገራችን ዜጎች ከበርካታ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች መካካል ወደ አንዱ የማድላታቸዉና አንዱን ደግፈዉ ሌላዉን ገሸሽ የሚሉበት መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ የሚተነትን ጥናት ስለመኖሩ ባላዉቅም በቅርብ ከማዉቀዉና ከታዘብኩት በመነሳት የሀገራችንን መራጮች ዝንባሌ ቢያንስ በግምት ደረጃ ማስቀመጥ የምችል ይመስለኛል፡፡ ወደኛ ሁኔታ በቀጥታ ከመሸጋጋሬ በፊት ግን በቅድሚያ ለማናጻጸር እንዲያመች የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ በመጠኑ መጥቀሱ ተገቢ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የአሜሪካ ዜጎች ለአንድ ፓርቲ የሚሰጡት ድጋፍ ወይም ዝንባሌ በአብዛኛዉ በዘልማድና ከቤተሰብ በሚወራረስ ወገንተኝነት ነዉ፡፡ ሁለቱ እድሜ ጠገብ ፓርቲዎች ማለትም ሪፖብሊካንና ዲሞክራት ፓርቲዎች መካካል አንዱን የመመረጥ ጉዳይ ከአያት ቅድሜ አያት እየተወራረሰ የመጣ ይመስላል፡፡ ልጆች ያለምንም መጠራጠር ወላጆቻቸዉ ሲደግፉ ለነበረዉ ፓርቲ ድጋፊ ይሰጣሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ዉገና ልክ እንደሃማኖት ወላጆች የክርስትና ወይም እስልምና እምነት ተከታይ ከሆኑ ልጆችም የእነርሱን አርአያነት ተከትለዉ ክርስትያን ወይም እስላም እንደሚሆኑት ዓይነት የሚወረስ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ በዘልማድ ከሚደረግ የፓርቲ ዉገና ሌላ ግለሰቦች ለራሳቸዉና ለቤተሰባቸዉ ሊሰጥ ከሚችለዉ ጠቀሜታ አንጻር መነሻ በማድረግ የተሻለ የሚሉት ዓይነት ፖሊሲ ያለዉን ፓርቲ ወይም ዕጩ የመምረጥ ልማድ አዳብረዋል፡፡ ፡ለምሳሌ ታክስን ብቻ ብናይ ከፍተኛ ታክስ በማስከፈል የተሻለ አገልግሎት ለህዝብ የሚሰጥ ፖሊሲን የሚደግፉ የመኖራቸዉን ያህል በአንጻሩ አነስተኛ ታክስ ብቻ ማስከፈልን እንደ ትክክለኛ ፖሊሲ የሚመርጡ በሌሎች ዜጎች የሚመረጡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በሁለቱ ፓርቲዎች መካካል በተለያዩ ፖሊሲዎች ረገድ ግልጽና በሚገባ የሚታወቅ ልዩነት እንዳለ መራጭ ዜጎች ጠንቅቄዉ ስለሚያዉቁ ከስሜታዊነት በጸዳ ሁኔታ ያሻቸዉን የመምረጥ ባህል አዳብረዋል፡፡ በሌላ በኩል ስልጣን ይዞ ሲያስተዳዳር የነበረን አንድ ፓርቲ በሆነ ጉዳይ ላይ አንድ ግዜ ከጠሉት ለብዙ ግዜ የማይመርጡበት ሁኔታም ይታያል፡፡ ለምሳሌ በኢንግሊዝ ከማርጋሬት ታቼር በኋላ ኮንሴርቫቲቭ ፓርቲ ለብዙ ግዜ ሳይመረጥ ቆይቶ ሁኔታዉ ሊቀየር የቻለዉ በዴቭድ ካሜሮን ግዜ ነበር፡፡

ወደ ሀገራችን ሁኔታ ስንመለስ በእኔ እይታ የሀገራችን የፓርቲ ዝንባሌና ዉገና ወይም ደጋፊነትን በአራት ምድብ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

ሀ)-የመጀመሪዉ ምድብ ፤ከአንድ ፓርቲ ጋር በረዥም ግዜ ቆይታ ከመላመድ የሚመነጭና ራስን የዚያ ፓርቲ ቋሚ ደጋፊ የማድረግ ዝንባሌ ሲሆን ከዚያ ፓርቲ ዉጭ የሚገኙ ሌሎች ፓርቲዎችን ተገቢነት የመጠራጠርና ለሀገሪቱም ሆነ ለህዘቡ ከነሱ ባልተናነሰ ደረጃ አስፈላጊ መሆናቸዉን ጭምር ለመቀበል ያለመፍቀድ ልማድ ነዉ፡፡ በዚህ ደረጃ የሚመደቡ የፓርቲ ደጋፊዎች መካካል የየራሳቸዉ በቂ ምክንያት ያላቸዉ ባይጠፉም አብዛኛዉን ግዜ ግን አንድን ፓርቲ ከሌላዉ አብልጠዉ የሚደግፉት የረባ አሳማኝ ምክንያት ሳይኖራቸዉ በዘልማድ ነዉ( tradition—not issues)፡፡ በዘልማድ ላይ የተመሰረተ የፓርቲ ዉገና ፓርቲዉን በሌላ የተሻለ ፓርቲ መቀየርን እንደ ክህዴት የሚቆጥሩ በመሆናቸዉ የተሻለ አማራጭ ፓርቲ ቢመጣም የድሮ ፓርቲያቸዉን በሌላ ለመቀየር በጭራሽ አይፈልጉም፡፡ ደጋፊዎቹ አንዴ ከአንድ ፓርቲ ጋር ራሳቸዉን ያቆራኙና ምናልባትም የፓርቲዉ አባል በመሆናቸዉ የተነሳ ዝንፍ የማይልና ስር የሰደደ ቋሚ የፓርቲ ዉገና ስለአላቸዉ (Declared party affiliation)ፓርቲያቸዉ ጥሩ ቢሰራም ባይሰራም ያለምንም ቅድሜ ሁኔታ መደገፍ ( unconditional support) እንዳለባቸዉ የሚሰማቸዉ ናቸዉ፡፡ እነሱ ከሚደግፉት ፓርቲ ዉጭ ሌላዉ ሁሉ ትክክል አይደለም በሚል የተለያዩ ቅጽያ ስም እየተለጠፈባቸዉ ህብረተሰቡ እንዲያወግዛቸዉ ሰፊ ዘመቻ ያደደርጋሉ፡፡

ይህን መሰሉ የፓርቲ ዉገና ለፓርቲዉ ጠቃሚ መሆኑ ባያጠያይቅም የሰከነ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አንጻር ሲታይ የዜጎችን ዲሞክራሲያዊ መብት ሊጎዳ የሚችል አደገኛ ባህሪይም ይታይበታል፡፡ ምክንያቱም ከፓርቲያቸዉ ጋር እጅግ በመላመዳቸዉ የተነሳ ፓርቲያቸዉን ወደ ማምለክ ደረጃ የሚደርስ የመንፈስ ቁርኝት በመፍጠራቸዉ ከፓርቲያቸዉ ዉጭ ሌላ ፓርቲ አሸንፎም እያለ ስልጣን እንዲይዝ በጭራሽ አይፈቅዱም፡፡ ስለዚህ በምርጫዉ የማይሳካላቸዉ ከመሰላቸዉ የምርጫ ድምጽ ያጭበረብራሉ፡ ወይንም ደግሞ ተቀዋሚዉን ለማጉላላት ሰበብ እንዲሆናቸዉ ሆን ብለዉ ራሳቸዉ ሁከት እንዲቀሰቀስ ያደርጋሉ፡፡

የአንድ ፓርቲ ቋሚ ወገንተኝነት ባለበት ሁኔታ አብዛኛዉ መራጭ ህዝብ ገና የምርጫ ቅስቀሳ ሳይጀመር አስቀድሞ ማንን መምረጥ እንዳለባቸዉ የወሰኑ ናቸዉ፡ ፡በረዥም ዘመን ስር የሰደደ (long-established partisan loyalties) የፓርቲ ዉገና ወይም ቋሚ ወገንተኝነት በምርጫ ላይ ያለዉ አፍራሽ አንድምታዉ ቀላል አይደለም፡፡ መራጮች በአንድ ምርጫ ጣቢያ በእጩነት የቀረበዉ ሰዉ ማንም ይሁን ማን እነሱ ከሚደግፉት ፓርቲ የተወከለ ስለሆነ ብቻ የፓርቲ ዉገናዉን በማየት ብቻ ያለማንገራገር ይመርጡታል፡፡ ከምርጫዉ ሰሞን ቀደም ቢሎ ግለሰቡን በአካል የማያዉቀትና ስሙን እንኳን ሰምተዉ የማያዉቁት በሌላ ከተማ በሙስና አስቸግሮና በመልካም አስተዳዳር እጦት ህዝብን ሲያማርር ቆይቶ ወደ ሌላ ከተማ የመጣ ስንት ጥፋት እያለበትም ለህዝቡም ከዚህ ቀደም በአካል የማይታወቅ እንግዳ ሆኖም እያለ የሚደግፉት ፓርቲ እጩ አድርጎ ስለአቀረበዉ ብቻ በጭፍን ይመርጡታል፡፡ ለምሳሌ በ97 ምርጫ ወቅት እኔ በወቅቱ እኖርበት በነበረዉ አንድ የምርጫ ወረዳ ኢህአዴግ ያቀረበዉን በህዝቡ እጅግ ተወዳጅና በሙያቸዉም ለሀጋራቸዉ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ታላቅ ከበሬታ ያተረፉ አንድ ፕሮፈሰር ያቀረበ ቢሆንም ነገር ግን ለመመረጥ የበቃዉ አንድ ብዙም በህዝቡ እዉቅና ያልነበረዉ የቅንጅት እጩ ነዉ፡፡ በወቅቱ አብዛኛዉ መራጭ(በዚያ ምርጫ ወረዳ) ቅንጅትን መምረጥ የግድ አድርጎ ስለቆጠረ ብቻ ለኦሮሚያም ሆነ ለመላዉ ሀገሪቱ በበለጠ ሊሰሩ ይችሉ የነበሩትን እጩ ኢህአዴግ ስለአቀረባቸዉ ብቻ የተሟላ ድምጽ ማግኘት ተስኗቸዉ ተሸነፉ ሲባል በወቅቱ አግራሞት ፈጥሮ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ኢህአዴግ ያቀረበዉ እጩ የግድ መመረጥ አለበት በሚል እንደ መሪህ በመቆጠሩ በተለያዩ አካባቢዎች ስንትና ስንት አንቱ የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች እያሉ በአቅምም ለህዝብ ባለ ተአማኒነትም የጎላ መልካም ሰብኢና ያልነበራቸዉ አንዳንድ የኢህአዴግ ዕጩዎች ሲመረጡ አይተን ታዝበናል፡፡ ይሄ እንግዲህ አንድን ፓርቲ በጭፍን የመጥላትና በጭፍን የማምለክ በሽታ ዉጤት ሲሆን የዲሞክራሲ ባህላችን አለመዳበርና ዜጎች በራሳቸዉ ጉዳይ በነጻነት ለመወሰን አለመቻል ማሳያ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ክስተት ካልተለወጠ በስተቀር በዚህች ሀገር ዲሞክራሲ ከቶ ሊያብብ አይችልም ፡፡

ለሀገሪቱ ዲሞክራሲ ማበብ የተሻለ የሚሆነዉ ከአንድ ፓርቲ ጋር አድሜ ልክ ተቀራኝቶ ያለአንዳች ማመዛዘን በጭፍን ከመምረጥ ልማድ በመዉጣት የተሻለ ሊሰራ ይችላል የተባለን እጩ መምረጡ ነዉ፡፡ መራጮች ለአንድ ፓርቲ ብቻ ድምጽ መስጠት እንዳለባቸዉ የሚያስቡ ከሆነ ምርጫዉ ፉክክር የማይታይበት ስለሚሆን ከዓመት ወደ ዓመት እየተፋዘዘ ስለሚሄድ በሂዴት ሀገሪቱን ለችግር ሊዳርጋት ይችላል፡፡ በቋሚነት የሚደግፉት ፓርቲ በእጩነት ያቀረበዉ ከስነምግባርም ከብቃትም አንጻር ብቁ አለመሆኑን ከተረዱ ሌላ ዕጩ እንዲመድብላቸዉ መጠየቅ ይገባቸዋል እንጂ ፓርቲዬ በእጩነት ያቀረበዉን ምንም ይሁን ምን መደገፍ አለብኝ የሚል አመለካካት እጅግ ጎጂ ነዉ፡፡ ዜጎች በፓርቲ ፖሊሲዎች ላይ ተመስርተዉ በራስ መተማማን መንፈስ የሚደግፉትና ድጋፍ የሚነሱበት ሁኔታ ከሌለና የግድ አንድን ፓርቲ ብቻ መደገፍ አለብኝ የሚል አቋም ከያዙ ለዲሞክራሲያችን ማበብ የሚበጅ አይሆንም፡፡

ለ)-በሁለተኛ ምድብ ሊጠቀስ የሚችለዉ የፓርቲ ዉገና ፓርቲዉ በግል ህይወታቸዉ ላይ ባመጣዉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለዉጥ ወይም መሻሻል መነሻ በማድረግ የሚደግፉ ናቸዉ፡፡ ይሄ ምክንታዊና ተገቢም የሆነ የፓርቲ ዉገና ይመስለኛል፡፡ እነዚህ መራጮች ፓርቲያቸዉ መልካም ሲሰራ ይደግፉታል፤ ሲያበላሽ ደግሞ የምርጫ ወቅትን ጠብቀዉ በሌላ ይተኩታል፡፡ መስፈርታቸዉ ብቃት( performance) ነዉ፡፡ ፓርቲዬ ካልተመረጠ ሞቼ እገኛለሁ፤ እሸፍታለሁ በማለት ችግር አይፈጥሩም፡፡ አንድን ፓርቲ ከሌላዉ የሚለዩት በዘር፤ በቋንቋ ወይም በአንድ አካባቢ ህዝብ ስም ስለተደራጀ የግድ መደገፍ አለብኝ በሚል አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት የፓርቲ ደጋፊዎች ከነሱ ፓርቲ ዉጭ ሌላ ፓርቲም ህዝብ ከፈቀደለት ስልጣን የመያዝ መብት እንዳለዉ ስለሚገነዘቡ ፓርቲያቸዉ በምርጫ ስለተሸነፈ አመጽ የሚያስነሱ አይደለም፡፡ በሀገራችን አንድን ፓርቲ በጭፍን ከመደገፍ ልማድ ተላቀን በምክንያት የሚደግፉ የፓርቲ ደጋፍዎችን ቁጥር ማብዛት ያለብን ይመስለኛል ፡፡

ሐ)-. በሶስተኛ ደረጃ ሊጠቀሱ የሚችሉት በብሄር ማንነት (ethnicity )ላይ ተመስርተዉ “የእንትን ህዝብ ፓርቲ !”ወዘተ ስለተባለ ብቻ በብሄር ወይም በቋንቋ ላይ ተመስርተዉ የሚደግፉ ናቸዉ፡፡ የዚህ ዓይነት ፓርቲዎች ጠባብ ዓላማ ያነገቡና መላዉን የሀገሪቱን ህዝቦች በእኩልነት ለማገልገል ባህሪያቸዉ የማይፈቅድላቸዉ ከአንድነት አመለካካት ይልቅ ልዩነትና ቢሶት ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸዉ ከብሄራቸዉ ዉጭ ደጋፊ አይኖራቸዉም፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች በተለያዩ ህዝቦች መካካል በረባ ባልረባዉ ሲከሰቱ ለነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች የዚህ ዓይነቶቹ ድርጅቶች እጅ እንደሚኖርበት መገመት አያዳግትም፡፡

መ)-በአራተኛ ደረጃ ለየትኛዉ ፓርቲ ደንታ የሌላቸዉ ማንም ቢመረጥ ባይመረጥ የማያሳስባቸዉ ፤የምርጫዉን ፋይዳም በቅጡ የማይረዱ መራጮች ሲሆኑ በምርጫ ወቅት ለስሙ ያህል ምርጫ ጣቢያ በመገኘት በዘፈቀደ ለአንዱ ሰዉ ድምጽ ሚሰጡ ካልሆነም ደግሞ ባዶ ወረቀት ምርጫ ኮሮጆ ዉስት ወርዉረዉ የሚመለሱ ናቸዉ፡፡ የዚህ ዓይነቶቹ ቁጥራቸዉ ጥቂት ቢሆንም ቢያንስ ግን በምርጫዉ እርካታ የሌላቸዉና ማንን መምረጥ እንዳለባቸዉ የሚቸገሩ እንደሆኑ መገመት አያዳግትም፡፡

3.2 ብዙዎቹ መራጭ ዜጎች ኢህአዴግን ለተጨማሪ ግዜያት በስልጣን እንዲቆይ የሚፈልጉት ለምንድነዉ?

ገዥዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ለተጨማሪ ዓመታት በስልጣን ላይ መቆየት ይገባዋል ቢለዉ የሚያምኑ ወገኖች በቁጥር ደረጃ ይሄን ያህል ናቸዉ ቢሎ መግለጽ ባይቻልም በርካታ እንደሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ እነዚህ ወገኖች የኢህአዴግን በመንግስትነት መቀጠል መመኘታቸዉ ከኢህአዴግ ጋር የተለየ ቡድናዊ ቁርኝት ወይም የጥቅም ትስሰር ስላላቸዉ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ወገኖች የግል ጥቅምን መነሻ ካደረገ ወገንተኝነት ይልቅ ሀገራዊ ፋይዳዉን የሚረዱና ከስሜታዊነት በላይ በቂ አሳማኝ ምክንያት ያላቸዉ ናቸዉ ብለን እንገምታለን፡፡ ኢህአዴግን በስልጣን የተወሰነ ግዜ እንዲቆይ የሚሹ ወገኖች ፖለቲከኞች ወይም ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ በአብዛኛዉ ከፖለቲካ ፈንጠር ያለ አመለካካት ያላቸዉ ዜጎችም ጭምር ናቸዉ፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ ቢያንስ ለአንድ የምርጫ ዘመን በስልጣን ላይ መቆየት ይገባዋል ቢለዉ የሚያስቡ ሰዎች ኢህአዴግ በሌላ ፓርቲ መቀየር በጭራሽ የማይገባዉና መቀየርም የማይቻል ስለሆነም አይደለም ፡፡ ምናልባትም ደግሞ ኢህአዴግን የሚያስተቸዉ አንዳችም እንከንና ድክመት ስላልነበረዉም እይደለም፡በተለይም ኢህአዴግና ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በሙስናና መልካም አስተዳዳር እጦት ክፉኛ በሚብጠለጠሉበት በአሁኑ ወቅት ላይ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እንዲሰነብት መመኘት ከእብደት ወይም ከጅልነት የሚያስቆጥር ሊሆን ይችላል፡፡

ኢህአዴግ በስልጣን እንዲቆይ የሚፈልጉ አብዛኛዎቹ መነሻቸዉ የሀገሪቱ የዘመናት ዋነኛ ችግር ሆኖ የቀየዉንና ለዉርደትና አንገት ለመድፋት የዳረገንን ድህንነትና ኋላቀርነትን በመቅረፍ ረገድ እጅግ የተሳካ ስራ እየሰራ በመሆኑ ለወደፊቱም አጠንክሮ እንዲቀጥልና መካካለኛ ገቢ ካላቸዉ ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ያነገበዉን ራዕይ የማይቀለበሰበት ደረጃ ላይ አስከሚያድርስ ድረስ ተጨማሪ ዕድል እንስጠዉ ከሚል ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስርአቱን እንደ ስርአት በእጅጉ የሚያምኑበት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከፋም ለማም ያሁኑ ስርአት እንዲቀጥል እንጂ በሌላ ባእድ በሆነ አዲስና የማይታወቅ ስርአት እንዲተካ ስለማይሹም ነዉ፡፡ አሁን ካለዉ ፌዴራላዊ ስርአት ጋር በቅጡ ለመላመድ እንኳን ምን ያህል ዉጣ ዉረዶች ማለፍ የግድ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን አዲስ ፓርቲ ስልጣን ይዞ ሌላ ባዕድና እንግዳ የሆነ አዲስ ስርአት ለመትከል በሚያደርገዉ ሙከራ ብዙ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አላቸዉ፡፡ ስለዚህ የአሁኑ ስርአት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጂ በግርግር እንዲቀለበስ ወይም በሌላ እንዲቀየር ስለማይሹ አብዛኛዎቹ ዜጎች ኢህአዴግን በሌላ ለመቀየር የማይደፍሩበት ሌላዉ ምክንያት ይህ ነዉ፡፡ በተጨማሪ የሀገሪቱን ህዝቦች በአንድነት ሊያቆምና ሉአላዊነታችንንና ብሄራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ረገድ ለግዜዉ ከኢህአዴግ ዉጭ እምነት የሚጣልበት ዓይን የሚሞላ ሌላ አማራጭ ፓርቲ እንደሌለ ስለሚታወቅም ጭምር ነዉ፡፡ አስካሁን ያለዉ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየንም ይሄንኑ ሃቅ ነዉ፡፡ ወደፊት ስርአቱን ለማፍረስና ህገመንገስቱን ቀዳዶ ለመጣል ሳይሆን የተጀመሩ መልካም ስራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥልና የተበላሹ ነገሮችን የሚያስተካከል የተሻለ ጠንካራ አማራጭ ፓርቲ ከተገኘ ህዝቡ ኢህአዴግን አዉርዶ አዲስ ፓርቲ በቦታዉ እንደሚተካ ምንም ጥርጥር የለዉም፡፡ አሁን ባለዉ ሁነታ ግን ከኢህአዴግ ዉጭ ሌላ አማራጭ ማግኘት አጠራጣሪ ነዉ፡፡ ስለዚህ ዜጎች እጅግ እየመረራቸዉም ቢሆን ኢህአዴግን በስልጣን እንዲቆይ የሚፈቅዱት ከነ እንከኑም ቢሆን ኢህአዴግ ይሻላል ከሚል እንጂ በሌላ መተካት ትክክል ስለአልሆነ ወይም ስለማይቻል ወይንም ደግሞ ኢህአዴግ አንዳችም እንከን ስለሌለዉ አይደለም፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ግዜ ጀምሮ በተለይም ባለፉት አስራ አምስተ ዓመታት ተአምር ሊሰኙ የሚችሉ የልማት ስራዎችን በመስራት ሃገሪቱን በከፍተኛ ፍጥነት እያለማት መሆኑን አምነን መቀበል የግድ ቢሆንም ነገር ግን በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን የምንመርጠዉ ለልማት ስራ ብቻ ብለን ሊሆን አይችልም፡፡ ኢህአዴግ አንደ መንግስት ከልማቱ በተጓዳኝ መስራት የሚገባዉ በርካታ ሃላፊነቶች አሉትና በነዚያ ጭምር ነዉ ገምግመን ልንመርጠዉ የምንችለዉ፡፡ ፍትህንና የህግ የበላይነትን ማስፈን የመንግስት ሃላፊነት ነዉ፡፡ ዜጎችን እጅግ ያስመረረዉን ሙስና ከስሩ መንግሎ ማጥፋት ባይችል እንኳን ቢያንስ እንዲቀንስ ማድረግ የመንግስት ተቀዳሚ ሃላፊነት ነዉ፡፡ የዲሞክራሲ መብቶችን በቁጥቁጥ ሳይሆን በተሟላ ሁኔታ እንዲከበር ማድረግ የመንግስት ተቃዳሚ ሃላፊነት ነዉ፡፡ የሰብአዊ መብትና የሚዲያ ነጻነት ወዘተ ሁሉ በተግባር እንዲከበር ማድረግ ዳቦ ከማቅረብ ያልተናናሰ የመንግስት ሃላፊነቶች ናቸዉ፡፡ ዜጎች ዳቦ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲዉም ሰብአዊ መብቱም የሚዲያ ነጻነቱም ሌላዉም ሁሉ እኩል ያስፈልጋቸዋልና፡፡ እነዚህ ሁሉ እንዲሟሉ ማድረግ የኢህአዴግ ሃላፊነት ነዉ፡፡ ከአንግዲህ ወዲያ ኢህአዴግ ልማትን ብቻ እያቀላጠፈ ሌላዉን ችላ ማለት አይችልም፡፡ ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ህዝብ በትክክል የሚፈልገዉ ምን እንደሆነ ማወቅ መቻል አለበት፡፡ በ2002ና በ2007 በዝረራ ለማሸነፍ ያበቃዉ ጉዳይ ለ2012 በድጋሚ ለመመረጥ ያስችለኛል ብሎ መጠበቅ አይኖርበትም፡፡ ኢህአዴግ ከልማቱ ጋር እኩል ለማስከድ አዳጋች ቢሆንበትም እንኳን እንደምንም ብሎ ሌሎችን የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ኢህአዴግ የአሜሪካዉ ትራምፕ ከክሊንተን ይልቅ ለመመረጥ የበቁበትን ምክንያት ለማወቅ መሞከር ይኖርበታል፡፡ ትራምፕ ከክሊንተን የተሻለ የአመራር ልምድ፤እዉቀትና የፖለቲካ ብስለት ፤ተናግሮ የማሳመን ችሎታ ወይም ዝና ስለነበራቸዉ አይደለም፡ዋናዉ ምስጥር የአሜሪካዉያንን የወቅቱ ፍላጎት ምን እንደሆነ ጠንቅቀዉ መረዳት በመቻላቸዉ ነዉ፡፡ ቃል በገቡት መሰረት መተግበሩ ቢያዳግታቸዉ እንኳን ቢያንስ ክሊንተንን አሸንፈዉ ለመመረጥ ግን አልሰነፉም፡፡

መራጭ ዜጎች አንዱን ፓርቲ ለይተዉ ድምጽ የሚሰጡት እንዲሟላላቸዉ የሚፈልጉትን ጥቅም በሚቀጥለዉ አምስት ዓመት ከሌላዉ በተሻለ ሊያሟላ የሚችለዉን በመለየት ነዉ፡፡ በስልጣን ላይ ያለዉ ገዥዉ ፓርቲም የዜጎችን ፍላጎት ካላሟላ በስተቀር ድጋሚ ለመመረጥ እንደማይችል ይገነዘባል ተብሎ ይታመናል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ገዝዉ ፓርቲ ከሰራዉ በበለጠ እንደሚሰሩ ቃል በመግባት ነዉ የምርጫ ፉክክር ዉስጥ የሚገቡት፡፡ መራጩ ህዝብ ፓርቲዎቹ ስለ ራሳቸዉ ምንም ይበሉ ምን ይጠቅመኛል ቢሎ ካላሰበ በስተቀር የትኛዉንም ፓርቲ አይመርጥም፡፡ አንቶኒ ዳዉንስ (Anthony Downs)የተባለዉ ምሁር ዲሞክራሲን ከኢኮኖሚ ሃሊዮት አንጻር በተነተነበት (An Economic Theory Of Demovracy) በተሰኘዉ ስራዉ ላይ ይህንኑ ያረጋጋጣል፡፡ (“Each citzen votes for the party he believes will provide him with a higher utility income than any other party during the coming election period.To discover which party this is,he compares the utility incomes he believs he would recieve were each party in office.The difference between these two expected utility incomes is the citzen`s eapected party differential.If it is positive,he votes for the incumbents; if it is negative ,he votes for the oppositio;if it is zero,he abstains.)

የኢትዮጵያ ህዝብ (መራጩ ህዝብ ) በቅድሚያ እጅግ በርካታ ከሆኑ ጉዳዮች መካካል በጣም አንገብጋቢና ቁልፍ ሀገራዊ አጀንዳ ወይም ጥያቄ የቱ እንደሆነ ለይቶ ማወቅ የሚገባዉ ሲሆን በመቀጠልም እነዚህን ቁልፍ ብሄራዊ አጀንዳዎች በተሻለ በተግባር መልስ ሊሰጥ የሚችለዉ የትኛዉ ፓርቲ እንደሆነ ለይቶ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ አስካሁን ህዝቡ ያሻዉን ፓርቲ ሲመርጥ የቆየዉ በዚህ አስተሳሳሰብ ተመርቶ ይሁን ወይንስ በዘፈቀደ ነዉ በሚለዉ ላይ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡

ግዙፍ የሆኑ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በተግባር መልስ እየሰጠ ለመጣ እንደ ኢህአዴግ ላለ ፓርቲ ሌሎች የህዝብ ጥያቄዎችን ሁሉ ዘግቶና ችላ ቢሎ እንደቀድሞዉ ስለ ልማት ብቻ እየዘመረ በድጋሚ እመረጣለሁ ቢሎ በርግጠኝነት መተማማን አይገባዉም፡፡ አንድ መንግስት እንዲያከናዉን የሚጠበቅበት አንድ ሺህ አንድ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉና መንግስት በተአምር በሁሉም ጥያቀዎች ላይ በእኩል ደረጃ መልስ መስጠት እንደማይችል ግልጽ ነዉ፡፡ ነገር ግን ህዝቡ የሚያስፈልገዉ ልማት ስለሆነ ከዚህ ዉጭ ሌላዉ ጥቅም የለዉም ቢሎ የህዝብ ፍላጎት ላይ ገደብ በማድረግ በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ጥሩ ዉጤት ሲላመጣ ብቻ ያ ፓርቲ ወይም መንግስት ተወዳጅ ሊሆን አይችልም፡፡ ገዥዉ ፓርቲ ቅድሚያ የሚሰጣቸዉንና አብይ የሆኑት ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ መስራት የሚገባዉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የህዝብ ጥያቄ አስከሆነ ድረስ ንቆ የሚተወዉ አንዳችም ጉዳይ ሊኖር አይገባም፡፡

ኢህአዴግ እስካሁን እየሰራ የመጣዉ ግዙፍ ስራዎች ወደፊትም ሊሰራ በእቅድ የያዛቸዉ ዕቅዶቹ የህዝብን የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ለመመለስና ሀገሪቱን ለማሳድግ በማሰብ እንጂ ለቀጣዩ ምርጫ ለመመረጥ ያግዙኛል በሚል ስሌት (ብቻ) እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ኢህአዴግ በዚያ መንገድ አሰበም አላሰበምም እንደ መንግስት የሠራቸዉ ስራዎች በምርጫ ወቅት ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ሊያስገኙለት እንደሚችሉ ጥርጥር የለዉም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በስልጣን ዘመኑ የሠራቸዉ ስህተቶችም የሕዝብ ድጋፍ ሊያሳጡት እንደሚችሉ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ኢህአዴግንም ሆነ ሌላን ፓርቲ መምረጥ ወይም አለመምረጥ ዉሳኔዉ የመራጩ ህዝብ ነዉ፡፡ የኢህአዴግ ተግባር እንደ ገዥ ፓርቲ ለህዝብ ይበጃል ብሎ የሚያስበዉን ጠንክሮ መስራት ብቻ ነዉ፡፡ ጥሩ ከሰራ ህዝቡ ራሱ አዉቆ ይመርጠዋል፡፡ ካልሰረና ነገር ካበላሸ ደግሞ ህዝቡ በሌላ ይለዉጠዋል፡፡

4 ኢህአዴግ አስካሁን ለምን በተከታታይ ሊያሸንፍ ቻለ? ለወደፊቱስ ይሳካለት ይሆን?

ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ማሸነፍ የቻለበትን ምክንያት የሚጠቅሱ አንዳንድ ወገኖች በምክንያትነት ከሚዘረዝሯቸዉ መካካል የዉጭ መንግስትት ፍጋፍ መኖር ፤ አፋኝ የሆኑ ህጎች በስራ ላይ መዋል፤ የምርጫ ህጉና ምርጫ ለማስፈጸም የተቋቋመዉ የምርጫ ቦርድ ግልጽ አድሎ በማድረጉ ፤ነጻ የሆነ ሚዲያ አለመኖር ወዘተ በሚል ይዘረዝራሉ፡፡ የጸጥታ ኃይሎችንም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱ አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ኢህአዴግን በስልጣን መቆየት ከራሱ ዉስጣዊ ጥንካሬ የመነጨ መሆኑን አምነዉ ለመቀበል አይፈልጉም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በተግባር የተረጋገጠዉንና በሰፊዉ የተመሰከረለትን ፈጣን የልማት ዕድገት ኢህአዴግን በተደጋጋሚ ለመመረጥ በቂ ምክንያት እንደሆነ ለመቀበልም አይፈልጉም፡፡ በድህነት አረንቋ ተዘፍቃ ዝንተዓለም ለኖረች ሀገር ከልማት ስኬት በላይ ሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ሊኖር እንደማይችል ተገንዝቦ ህዝቡ የኢህአዴግን የልማት ስኬት በማየት ደጋግሞ ቢመርጠዉ የህዝቡን አላዋቂነት የሚያሳይ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን ለመሰነበት ያስመዘገበዉ የልማት ስኬት የረዳዉ መሆኑን በምክንትነት መቀበል የማይፈልጉ ወገኖች ይሄዉ ፈጣን ልማት በማንኛዉም ወቅት ላይ እንቅፋት ገጥሞት መዳከም ቢያሳይ ለኢህአዴግ ከስልጣን መሰናበት ዋነኛ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም አሁንም እነዚሁ ወገኖች ለመቀበል አይፈልጉም፡፡

ኢህአዴግ የህዝብ አመኔታ ያተረፈለትና አስካሁን በስልጣን ለመቆየት ከረዱት ተግባራቱ ሁሉ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰዉ ችግር ፈቺ የሆኑና ዘርፈብዙ ዘላቂ አድገት የሚያመጡ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ለተግባራዊነቱ መትጋቱ ነዉ፡፡ ከዚህ አኳያ ኢህአዴግን ትልቅ ከበሬታ ያሰጠዉና ለጥረቱ በወዳጅም በጠላትም እኩል እዉቅና ያስገኘለት የልማት ስኬቱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ልማት ለኢህአዴግ የህዝባዊ አመኔታ ማግኛ ቁልፍ መሳሪያ ( legitimacy by reducing poverty through state-directed development)መሆኑንና ለወደፊቱም እንደሚሆን መካድ አይቻልም፡፡

ኢህአዴግ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ጠንካራ ዉጤቶችን ማስመዝገቡ የሚታወቅ ቢሆንም በልማቱ ላይ እንዳገኘዉ ስኬት የሚስተካካል አይደለም፡፡ በኢህአዴግ አመራር ሰጭነት ሀገሪቱ ያስመዘገበችዉ ፈጣን አድገት ከኛም አልፎ የዓለም ማህበረሰብ ያረጋጋጠዉ ሀቅ ነዉ፡፡ በዋነኛነት የመንግሰት ቅርብ ክትትል ያልተለየዉ በማእከላዊነት ታቅዶ እየተከናወነ ባለዉ ልማት በአጭር ግዜ ዉስጥ ድህነትን በመቀነስ ሀገሪቱን መካካለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች ተርታ የማሰለፍ ዉጥኑን እዉን ለማድረግ አቅዶ በቁርጠኝነት መንቀሳቀሱና በተግባርም አበረታች ዉጤት ማስመዝገቡ ነዉ፡፡ ሊበራል ዲሞክራሲን ገሸሽ በማለት በምትኩ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር የሙጥኝ ያለዉ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በቀድሞዉ መሪዉ በመለስ ዜናዊ የሀሳብ አመንጭነት በተጀመረዉ ልማታዊ መንግስት ፍልስፍና በመመራት አስደናቂ የሆነ ስኬት ማስመዝገብ ችሏል፡፡

የኢህአዴግ ባለስልጣናት በምርጫ ቅስቄሳ ወቅትም ሆነ በሌሎች ግዜያት ሲገልጹ እንደተደመጠዉ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸዉ በሀገሪቱ ዉስጥ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ እንደሆነና ለዚህም ሲባል በማዕከል ከተነደፈዉ ከአምስት ዓመቱ እድገትና ትንስፎርሜሽን ዕቅድ ዉጭ እንደማይታሰብ አበክረዉ ያስገነዝባሉ፡፡ በኢህአዴግ እምነት የልማታዊ መንግስት ፍልስፍናን አጠንክሮ በቀጠለዉና ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ያለዉ ልማት ሳይደነቃቀፍ ወደፊትም አስከቀጠለ ድረስ የህዝብን አመኔታ ለማግኘት እንደማያዳግተዉ ነዉ፡፡ በተጨማሪ በሁሉም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ህዝባዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠልና ዜጎች ከልማቱ ትሩፋት ተጠቃሚነታቸዉ እየጨመረ መሄድ የኢህአዴግን ህዝባዊ ቅቡልነቱ ማጠናከር ከመቻሉ ሌላ የስርአቱን ዲሞክራያዊነት መገለጫ ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል ኢህአዴግ በርግጠኝነት ያምናል፡፡

የምርጫ ዉጤት ላይ ወሳኙ መለኪያ አኮኖሚያዊ ስኬት በሆነበት የሀገራችን ሁኔታ ገዝዉ ፓርቲና ተቃዋሚዎችን በቀላሉ ለመለየት ያስችላል፡፡ ገዥዉ ፓርቲ የሰራዉን በማስረጃ በማስደገፍ በቀላሉ የድጋፍ ድምጽ ይሰበስብበታል ፡፡ በአንጻሩ ተቀዋሚዎች ያላቸዉ ዕድል ለወደፊቱ ሊሰሩ ያሰቡትን ቃል በመግባት ብቻ የተወሰነ ስለሚሆን የሚናገሩትና ቃል የሚገቡት የገዥዉ ፓርቲን ያህል በመራጮች ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል፡፡

አስካሁን በሀገራችን የተካሄዱትን ምርጫዎችን ለአፍታ መለስ ብለን ለማስታወስ ብንሞክር ከገዥዉ ፓርቲ አንጻር ሲታይ የኋለኛዉ ምርጫ ከቀደመዉ ምርጫ በተሻለ የልማትና ስኬቶች የታጀበ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ኢህአዴግ ሁልግዜም ወደ ምርጫ ክርክር ሲገባ በኩራት ሊገልጻቸዉ የሚችላቸዉ አዳዳስ የልማት ስኬቶች እጥረት አጋጥሞት አያዉቅም፡፡ ኢህአዴግ በሀገር ግንባታ በተለይም በልማቱ ዘርፍ የሠራቸዉ እጅግ ግዙፍ ስራዎቹ ሌሎቹን እንከኖቹን ህዝቡ በይቅርታ እንዲያልፍለት የረዳዉ ይመስለኛል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ከልማት ዉጭ ባሉ ሌሎች አጀንዳዎች ላይ የሚታይበትን እንከኖች ላይ በማተኮር አጋነዉ በማቅረብ የኢህአዴግን “አይረቤነት” መራጩ ህዝብ እንዲገነዘብላቸዉ መጣራቸዉ ባይቀርም ነገር ግን በሚገርም ሁኔታ ጠንካራ የልማት ስከቶቹ እነዚህን ትችቶች ሁሉ እንዲደበዘዙ ለማድረግ አስችሎታል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ኢህአዴግ ማስተካከል የሚገባዉ ችግሮች እንዳሉበት እየተረዳም ቢሆን ኢህአዴግን ለመምረጥ የተደፋፈረዉ በተጨባጭ በሰራቸዉ ግዙፍ የልማት ስራዎቹ በመርካቱ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ኢህአዴግ የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ እየመለሰና አዳዲስ የህዝብ ፍላጎቶችን በሂዴት ለመመለስ ዝግጁ የሆነ ስርአት መገንባቱን በኩራት ይገልጻል፡፡ ስርአቱ ዙሪያ-መለስ የህዝብ ተሳትፎ ያልተለየዉና በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉት የበለጠ ትኩረት የሰጠ ፍትሃዊ ስርአት እንደሆነ ደጋግሞ ይገልጻል፡፡ በርግጥ በኢህአዴግ አመራር ዘመን ሀገሪቱ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበች መምጣቷ ላይ አንዳችም ጥርጥር ባይኖርም ከልማቱ ጋር በተጓዳኝ መታየት የነበረባቸዉ ሌሎች የዲሞክራያዊ ስርአት ፀጋዎች ላይ በቂ ትኩረት አላደረግም ወይንም በግልጽ የሚታይ መሻሻል አላሳየም በሚል የሰላ ትችት ሳይቀርብበት የቀረበት ግዜ የለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ገዥዉ ፓርቲ አስካሁን ካከናወናቸዉ ግዙፍ የልማት ስራዎች አንጻር ሲመዘን የህዝባዊ ቅቡልነት ችግር ጨርሶ የለበትም ባይባልም ነገር ግን ዜጎች ከስርአቱ ተጠቃሚነታቸዉ ይበልጥ እየጨመረ በሄደ ቁጥርና የመንግስትን ጥረትም ይበልጥ እየተረዱለት በመጡ ቁጥር ህዝባዊ ቅቡልነቱ የበለጠ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ግልጽ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ለበርካታ ቀዉሶች እየተጋለጠ ባለበት ሁኔታም ቢሆን ህዝባዊ ቅቡልነቱ ከመሸርሸር ባለፈ የተፈራዉን ያህል አስካናካተዉ እንዳይናድ ያገዘዉ ነገር ቢኖር በልማቱ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉ ነዉ፡፡

አብዛኛዎቻችን እንደምናስታዉሰዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስከ ምርጫ 97 ኢህአዴግን በምርጫ በክርክር ወቅት በሀፍረትና በተሸናፊነት መንፈስ አንገት ለማስደፋት በማሰብ በርካታ እንከኖችን በመዘርዘር ተሟግተዋል፡፡ ከዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጉድለት ጀምሮ የሚዲያ ነጻነት አለመኖር፤ የምርጫ ሜዳ ጎርባጣነት፤ የፌዴራላዊ ሰርአቱ እንከኖች ፤የህገመንግሰቱ ጉድለቶችን ጨምሮ የኢህአዴግ ድክመት ነዉ ያሉትን ሁሉ አንድም ሳይቀር በመዘርዘር ኢህአዴግን ለማሳፈርና ቢሎም የህዝብ ድጋፍ ለማሳጣት ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ኢህአዴግን ለመምቻነት የተጠቀሙበት ዋነኛዉ የኢህአዴግ እንከን የሚሉት የባህር በር ጉዳይን ነበር፡፡ ይህ አጀንዳ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ኢህአዴግን ለማስጠላት ሳይጠቅማቸዉ አልቀረም፡፡ ከ97 በኋላ በተደረገዉ የ2002 ምርጫ ወቅት ይህንኑ ጉዳይ በድጋሚ ለመጠቀም መሞከራቸዉ ባይቀርም ነገርግን እንደቀድሞዉ እምብዛም የረዳቸዉ አይመስለኝም፡፡ የ2007 ምርጫ ደግሞ በባሰ ሁኔታ ተቃዋሚዎችን ለሽንፈት የዳረገ ሆኗል፡፡

በ2007 ምርጫ ክርክር ወቅት ሌሎቹን ትተን ሁሉንም ህዝብ በአንድነት ሊያቆም የሚችል አጀንዳ ነዉ የተባለለትን የወደብ ጉዳይን በማራገብ እንኳን የህዝቡን ድምጽ ከኢህአዴግ ነጥቀዉ የራሳቸዉ ለማድረግ ተስኖአቸዉ ነበር፡፡ የወደብ ጉዳይ መጫወቻ ካርድነቱ ዋጋ አጥቷል እያልኩ አይደለም፡፡ የባህር በር ጉዳይ መቼም ቢሆን ብሄራዊ አጀንዳ ከመሆን የሚቀር አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ይህችን ብቻ ይዞ ወደ ምርጫ መምጣት ትርፍ አያስገኝለትም፡፡ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የህዝብን ቀልብ መሳብ መቻል አለበት፡፡ ሌሎች ብሄራዊ አጀንዳዎችና ፖሊሲዎችንም ማስፈጸም የሚችል ካልሆነ በስተቀር አንድ ጥሩ አጀንዳ መርጦ በዚያች ብቻ መንግስት መሆን አይችልም፡፡ ተቃዋሚዎች ለኢህአዴግ የልማት ስኬት ህዝቡ የሰጠዉን ከፍተኛ ዋጋ ሊረዱ አልፈቀዱም፡፡ ለዘመናት በድህነት የኖረ ህዝብ ከልማቱ ትልቅ ከበሬታ እንደሚኖረዉና ከልማት በላይ የሚያስቀድመዉ አጀንዳ እንደሌለዉ ተቃዋሚዎች ለመረዳት አልፈቀዱም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች የልማቱን አጀንዳ ችላ ብለዉ ከዚያ ዉጭ ባሉ የሉአላዊነት ጥያቄዎችና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ላይ ጫና ሰጥተዉ ቢቀሰቅሱም ህዝቡ ሊመርጣቸዉ አልቻለም፡፡

5 ኢህአዴግ በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኝ ገዥ ፓርቲ (incumbent)መሆኑ ብቻዉን ለቀጣዩ ምርጫተለየ እገዛያደርግለት ይችላል?

አንድ ስርአትና አገዛዝ ዲሞክራትክ ሊባል የሚገባዉ ቢያንስ አንድ ሁኔታ ሲሟሟላት እንዳሆነ ይታመናል፡፡ ከዚህ አንጻር ፒዜዎርስኪ (Przeworski)እና ሊሞንግ (Limongi ) የተባሉ ምሁራን እንደሚገልጹት አንድ አገዛዝ “ዲሞክራሲያዊ” ሊባል ከተፈለገ በቅድሚያ ሰላማዊ የስልጣን መተካካት ወይም አንድ መንግስት በሌላ የመተካት (alternation of office) ሁኔታ ሊኖር የግድ ነዉ፡፡ እንደ ሳሙኤል ሃንትንግተን (Huntington) እምነት ደግሞ ስርአቱ ዲሞክራሲያዊ ሊሰኝ ከተፈለገ ቢያንስ ለሁለት ግዜ ያህል ህግ አዉጭዉ (ፓርላማ)በሌላ ተቀይሮ በተግባር መታየት ይኖርበታል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ዲሞክራሲያዊ ናቸዉ በሚባሉ ሀገሮች ሳይቀር ገዥ ፓርቲዎች ዘለግ ላለ ግዜ በስልጣን ላይ መቆየት መቻላቸዉ ሲታይ ሌላ ህገወጥ አሰራር መኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር በድፍኑ ስርአቱን ወይም አገዛዙን ዲሞክራሲያዊ አይደለም በሚል ለመደምደም አያበቃም፡፡ ከዚህ አንጻር ጥቂቶቹን ለአብነት ለመጥቀስ ያህል፤ የህንዱ ብሄራዊ ኮንግሬስ ፓርቲ ከ1952 አስከ1976 በድምሩ ለ24 ዓመታት፤የኛዉ ኢህአዴግ (EPRDF)ደግሞ ከ1983 አስከ 2009 በድምሩ ለ26 ዓመታት፤ የጣሊያን ክርስትያን ፓርቲ (CDP) ከ1948 አስከ 1992 በድምሩ ለ44 ዓመታት፣የጃፓን ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (LDP)ከ1958 አስከ 1993 በድምሩ ለ35 ዓመታት፤የስዊድሽ ሶሻል ዲሞክራትሰ (SAP) ከ1932 አስከ1976 በድምሩ ለ44 ዓመታት በመጨረሻም ዴንማርክ ሶሻል ዲሞክራትስ ከ1924 አስከ 2001 በድምሩ ለ77 ዓመታት በስልጣን ላይ መቆየት ችለዋል፡፡

ኢህአዴግ በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኝ ገዥ ፓርቲ መሆኑ በራሱ በቀጣዩ ምርጫ ላይ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግለት አያጠራጥርም ፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ የመንግስት ስልጣን ላይ መኖሩ ለምርጫዉ ሳይጠቅመዉ እንዳልቀረ ለመገመት እያዳግትም፡፡ ከታወሚ ፓርቲዎች ከምርጫዉ ሰማግስትጀምሮ ሲቀርቡ የነበሩ አበቱታዎች ሁሉ የዚህ አባባል ትክክለናነት ማረጋጋጫ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲ በመሆኔ ምክንት አንዳችም የተጠቀምኩት ነገር የለም እንደማይለን እተማመናለሁ፡፡ መቶ በመቶ ማሸነፍ የቸልኩትም በላቤ በወዜ ወጥቼና ወርጄ ፤ለፍቼ ደክሜ ያመጣሁት ዉጤት እንጂ ለምርጫ እንዲያግዘኝ የመንግስት የሆነን አንድም ነገር አልተጠቀምኩም እንዳማይለንም እርግጠኛ ነኝ ፡፡

በስልጣን ላይ የሚገኝ ፓርቲ (incumbent) ህገ መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሚካሄድበት ሀገርም ቢሆንም ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለየ በምርጫ ላይ በድጋሚ የማሸነፍ ሰፊ እንዳለዉ ብዙዎች ይስማማሉ፡፤ለምሳሌ በአሜሪካ ከ1976 ጀምሮ ለአስራሰባት ግዜያት በተደረጉት የኮንግሬስ አባልነት ምርጫዎች 90 ከመቶ (90%) የሚሆኑት በድጋሚ የተመረጡ ናቸዉ፡፡ ይህ ሁኔታ በፖለቲካ ሳይንቲስቶች “the Incumbency Effect.”ተብሎ የሚጠራ ነዉ፡፡ በሀገራችን በ97 ምርጫ ቅንጅት የያዘዉን ይዞ ለአንድ ምርጫ ዘመን ያህል ቆይቶ ቢሆን ኖሮ የ2002 ምርጫን አቅጣጫ ሊያስቀይር ይችል እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ በስልጣን ላይ የሚገኝ ገዥ ፓርቲም ሆኖ ግልጽ የሆነ የብቃት ችግር የታየበትና በአመራሩ ወቅት ለአንዳንድ ከፍተኛ ቀዉሶች የተዳረገበት ሁኔታ ካለ የዚህ ዓይነቱ ፓርቲ ሌላ ህገወጥ መንገድን ካልተከተለ በስተቀር የመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኝ ስለሆነ ብቻ ቀጣይ ምርጫዉን ሊያሸንፍ አይችልም፡፡

በስልጣን ላይ ዘለግ ያለ ግዜ የቆየ ፓርቲን(ገዥ ፓርቲን) በምርጫ አሸንፎ ስልጣን መንጠቅ በስልጣን ላይ በተነጻጸር ለአጭር ግዜ የቆየ አዲስ ፓርቲን በምርጫ የማሸነፍ ያህል የቀለለ እንደማይሆን ስለዚህ ጉዳይ የተጻፉ ድርሳናት ያረጋጋጡት ጉዳይ ነዉ፡፡ ፡አስካሁን በምዕራቡ ዲሞክራሲያዊ አገሮች ስለተካሄደዉ ምርጫ በተደረገ ጥናት መሰረት በስልጣን ላይ ለረዥም ግዜ የቆየ ፓርቲ ድጋሚ የመመረጥ ዕድሉ 85% እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በፓርላሜንታዊ ስርአት ዉስጥ በስልጣን ላይ ብዙ ያልቆየ መንግስታዊ ፓርቲን በምርጫ መርታት የተለየ አስቸጋሪነት አይኖረዉም፡፡ በአንጻሩ በስልጣን ላይ ዘለግ ላለ ግዜ እንደ ገዥ ፓርቲ የቆየና ስር የሰደደ ነባር ገዥ ፓርቲን (An entrenched Incumbent) ለመርታተት ገና አዲስ ወደ ስልጣን የወጣን እንደመርታት ቀላል አይሆንም ፡፡ ፈጽሞ የማይቻል ነዉ ባይባልም ነባር ገዥ ፓርቲን ከስልጣን መዉረድ አዳጋች መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ በሀገራችንም ኢህአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየ ገዥ ፓርቲ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ዘለግ ለለ ግዜ በመቆየቱ ምክንያት ከዓመት ወደ ዓመት እየተጠናከረና ስር እየሰደደ መሰረቱም እየሰፋ የሄደ ፓርቲ በመሆኑ ኢህአዴግን ከስልጣን ለማዉረድ ተቃዋሚዎች ፈታኝ እንደሚሆንባቸዉ ግልጽ ነዉ፡፡

በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኝ ፓርቲ ወይም ገዥ ፓርቲ የመሆን ፋይዳዉ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ “incumbency effect”የሚባለዉ ክስተት ገዥዉ ፓርቲ በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት በብዙ ረገድ ተጠቃሚ የሚሆንበትና ሌሎች ከመንግስት ስልጣን ዉጭ ላሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአንጻሩ ትልቅ ተግዳሮች የሚሆንበት ሁኔታ ነዉ፡፡ ይህ ከስተት በተደጋጋሚ እንዳረጋጋጠዉ በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ወይም በህግ አዉጭ ዉስጥ አባል የሆነ የገዥዉ ፓርቲ አባል በተለየ ጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ካልሆነ በስተቀር አብዛኛዉን ግዜ በምርጫ ደጋግሞ የሚያሸነፍበት ሁኔታ መኖሩ ነዉ፡፡ አንድ ግዜ ፓርላማ መግባት ከተቻለ በተደጋጋሚ ለማሸነፍ ሰፊ ዕድል ይኖራል፡፡ ፈረንጆቹ “the incumbent always wins.”እንደሚሉት ማለት ነዉ፡፡ አስቀድሞ የፓርለማ አባል ሆኖ መገኘት ለቀጣዩ ምርጫ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለዉ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ ይህን ጠቀሜታ በከፊል ለመጥቀስ ያህል ፤

* የተለያዩ የመንግስት ሪሶርሶችን፤ የመንግስትን መዋቅርና ፋይናናስና ሎጂስትክስ ለመጠቀም ሰፊ ዕድል ስለሚኖረዉ በድጋሚ ለመመረጥ በሚያስችለዉ መንገድ ለመጠቀም ሁኔታዉ ምቹ ይሆንለታል፡፡

* ለሚዲያ ያለዉ ተደራሽነት ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ምክንያትም ራሱን ለማስተዋወቅ በአንጻሩ ተፎካካሪዎችን ለማሳጣት ሰፊ ዕድል አለዉ፡፡ በተለይ የሀገሪቱ ሚዲያ በአብዛኛዉ በመንግሰት በተያዙበትና ሌሎች አማራጭ ነጻ ሚዲያዎች እንደልብ በማይኖሩበት ሁኔታ ለገዥዉ ፓርቲ ጠቀሜታዉ የጎላ ይሆናል፡፡

* ገዥ ፓርቲ በስልጣን ላይ ስለሚገኝ ለህዝቡ የልማትና ማህበራዊ ጥያቄዎች በተግባር መልስ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ብቃቱን በተግባር በማስመስከር የህዝብ ድጋፍ በተሻለ ለማግኘት ሰፊ እድል አለዉ፡፡

* ገዥዉ ፓርቲ አንደ መንግስት ሁሉንም መዋቅር ለመጠቀም እድሉ ሲላለዉ በመንግስት ገንዘብ በርካታ ባለሙያዎችን በመቅጠርም ሆነ ማበረታታቻ በማድረግ የፓርቲዉ ደጋፊ ለማድረግ ሰፊ ዕድል አለዉ፡፡

* ራሱ የሚያደራጃቸዉ ልዩ ልዩ ህዝባዊ አደረጃጃቶችና ማህበራትና ፎሬሞች በአብዛኛዉ በስልጣን ላይ ላለዉ ፓርቲ ደጋፊ መሆን መቻላቸዉ ያጋጣሚ አይደለም፡፡

* በስልጣን ላይ የሚገኝ ፓርቲ በብዙ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ልምድ ለመቀሰም እድል ሲላላዉ ፤በየጥኛዉም ሀገራዊና አለምአቀፍ ጉዳዮች ላይም የተሻለ መረጃ ስለሚኖረዉ ፤ከመረጃ ሙሉዕነትም የተነሳ በሀገራዊ አጀንዳዎችና ችግሮች ላይም ተጨባጭነት ያላቸዉን መፍትሄዎችን ለማስቀመጥ ከተቃዋሚዎች የተሻለ ዕድል አላቸዉ፡፡ በዚህ ምክንያትም በምርጫ ክርክር ወቅት ከተቃዋሚዎች በተሻለ ተጨባጭነት ያላቸዉን ማብራሪያዎችን በራስ መተማማን በመቅረብ በቀላሉ የመራጮችን ልብ ለመማረክ ያስችለዋል፡፡

* ከመራጩ ህዝብ ጋር በተለያዩ መድረኮች የመገናኘት ዕድል ሲላለዉም ከህዝቡ ጋር በየግዜዉ በመወያየት ህዝቡ በትክክል ምን እንደሚፈልግ የተሻለ ግንዛቤ ይኖረዋል፡፡

* በስልጣን ላይ መገኘቱ በሚፈጥርለት አጋጣሚ በመጠቀም በዉጭዉ ማበህበረሰብና መንግስታት ጋር ሳይቀር ሰፊ የግኑኝነት መረብ በመዘርጋት ጠንካራ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል፡፡ በስልጣን ላይ ዘለግ ላለ ግዜ የቆየ ፓርቲ የተረጋጋና ጠንካራ መንግስት ተደርጎ ስለሚቆጠር በዉጭ ለጋሽ ድርጅቶች በተሻለ የመመረጥ አድል ሲላላዉ ለልማቱ የሚያግዘዉን የዉጭ አርደታና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በቀላሉ ማግኘት ይችላል፡፡

አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አንድ ፓርቲ በስልጣን ላይ መገኘቱ በድጋሞ ለመመረጥ ሰፊ ዕድል የሚከፍትለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን ገዥዉ ፓርቲ እንደ መንግስት መሪነቱ በሚገባ ሀገር ማስተዳዳር የተሳነዉ ደካማ ፓርቲ ከሆነ ለብዙ ነቀፌታዎች በቀላሉ ስለሚጋለጥ በሚቀጥለዉ ምርጫ ለሽንፈት ሊዳረግ ይችላል፡፡ በመንግስት ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ብቃት የጎደለዉና ታማኝነት የሌለዉ ከሆነ አፋኝ መንገዶችን ካልተከተለ በስተቀር በቀጣዩ ምርጫ በድጋሞ የመመረጥ ዕድሉ እጅግ ጠባብ ይሆንበታል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ፓርቲ ገዥ ፓርቲነቱ በድጋሚ ለመመረጥ አንዳችም የሚሰጠዉ ጥቅም አይኖርም፡፡ ስለዚህ በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ (incumbent) ጠቀሜታ ጉዳይ ሲነሳ ጠንካራ ለሆነ ገዥ ፓርቲ እንጂ በአጋጣሚ ሁኔታዉ ፈቅዶለትና በግርግር ስልጣን ላይ ለወጣ ፓርቲ አይደለም፡፡ ስለዚህ ደካማ የሆነ ገዥ ፓርቲ ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ ስለሚሆን በስልጣን ላይ መገኘቱ ከሚሰጠዉ ጠቀሜታ በበለጠ አደጋ ሊሆንበት ስለሚችል በቀላሉ በምርጫ ተሸናፊ ይሆናል፡፡

——

የዚህን ፅሁፍ ያለፉና ቀጣይ ክፍሎች

* ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 1 | የኢህአዴግ የወቅቱ ተአማኒነትና የቀጣዩ ምርጫ ዕጣ ፋንታዉ

* ኢህአዴግና ቀጣዩ ምርጫ 3 | በመጭዉ ምርጫ የኢህአዴግን ዕጣ ፈንታ ሊወስኑ የሚችሉ የስጋት ምንጮችና ተግዳሮቶች (ገና ያልታተመ)

—-

*የኮ/ አስጨናቂ /ጻዲቅ ሌሎች ጽሑፎች ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

***********

Colonel Aschenaki Gebretsadik

ኮ/ል አስጨናቂ በአየር ኃይል ዉስጥ ከ1970ዓ/ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቀይተዉ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸዉ፡፡ በአየር ኃይል ዉስጥ በዘመቻና መረጃ መምሪያ ኃላፊነት፤ በአየር ምድብ አዛዥነትና በአይር መከላከያ ኃላፊነትና በሌሎች የሃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በኤርትራ ጦርነት ወቅት በሰሜን አየር ምድብ በምክትልነትነና የአየር መከላከያዉን ስራ በተለይ በሃላፊነት በማስተባበር ሲሰሩ ነበር፡፡ ኮ/ል አስጨናቂ ከቀድሞዋ ሶቭት ህብረት በወታደራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪ አላቸዉ፡፡

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago