የዘዉጌ ዋልተኝነት (Ethnic Polarization) እና የኢትዮጵያ አደገኛ ሁኔታ

(ይታገሱ ዘዉዱ)

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው በመመረጣቸው ደስ በሎኛል፡፡ ለምን ቢባል የአገሬ ሰዉ ናቸዉ…………. ኢትዮጲያዊ …… ወዲህም ጥቁር አፍሪካዊ! የደስታየም ምክንያት ጥቁር አፈር ያበቀላቸዉ የጥቁር ህዝብ ልጅ በመሆናቸዉ ብቻ ነዉ ፡፡ ጥቁር በአለም መድረክ ላይ ከፍ ከፍ ሲል ደስ ይለኛል፡፡

ነጮቹ እንደሚሉት የጥቁር ዘረኛ  (Black-ish ) የመሆን ጉዳይ አይደለም ፡፡ ጥቁር ህዝቦች ለበርካታ ዘመናት ግፍ ተፈጽሞባቸዋል …….በባርነት ተግዘዉ በደምና በላባቸዉ ባቆሙት አገር ላይ ዛሬም ድረስ ከዉሻ አንሰዉ በየአደባባዩ በዘረኛ ነጮች ደማቸዉ ይፈሳል፡፡ ጥቁር አፍሪካዉያን በቅኝ ተገዝተው በገዛ መሬትና ሃብታቸዉ  ላይ ነጭ እንዳሻዉ ሲጭን ሲጋልብቸው ኖሯል፡፡

ዛሬ በመላዉ አፍሪካ ላለዉ አስከፊ ድህነት፣ ማህበራዊ ቀዉስ፣ ዘረኝነት፣ የስነ-ልቦና መዳሸቅ፣ የስነም-ግባር መዘቀጥት፣ አንባገነናዊ ስርዓት መፋፋት፣ ማባርያ ለሌለዉ የእርስ በርስ ጦርነት፣ አዋራጅ ስደት፣ ስፍር ቁጥር ለሌለዉ የጥቁር ህዝብ ስንክ ሳር ከቀኝ ገዥዎች ሰንኮፍ (colonial legacy) ቀድሞ ሊጠቀስ  የሚችል ነገር ከቶ  ምን ሊኖር ይችላል?

ስለሆነም ጥቁር በአለም አደባባይ የፊት ገጽ ላይ በመልካም ስም እና ስብእና በመዓረግ ሲገለጽ ደስ ይለኛል! እንኳንስ ለአገሬ ሰዉ ሊያዉም በግሌ ትህትናዉ ለሚማርከኝ ኢትዮጵያዊ ይቅርና፣ ለማላዉቀዉ ለማያቀኝ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አሸናፊነት እንደ አቡነ ተክልዬ በአንድ እግሬ ተተክዬ አድሬያለሁ፡፡

ለሌላ ለምንም ሳይሆን ……. የጥቁር ሰዉ ድል ድሌ ስለሆነ ነዉ ያን ማድረጌ፡፡  በዶ/ር ቴድሮስ  አሸናፊነት ኢትዮጵያ አገሬ እንኳን ደስ አለሽ! አፍርካዬ እንኳንም ደስ አልሽ! አንባቢ ሆይ ይህን በማለቴ ግን  ስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ደጋፊ አድርገህ እንዳትፈርጀኝ አበክሬ አሳስባለሁ!

ከዶ/ር ቴድሮስ  አሸናፊነት ባሻገር ግን በጽሞና ሊጤን የሚገባዉ አደገኛ ሁኔታ በፖለቲካዉ መስክ ሲስተጋባ ሰንብቷል አዲስ ክስተት ባይሆንም ፡፡ ጉዳዩ ከሃገር ዉጪ የሚኖሩ ኢትዮጲያዊያን እና ትዉልደ ኢትዮጲያዊያን ብቻ የሚመለከት የባህር ማዶ ሰዎች ግርግር  ተደርጎ መወሰድ ያለበት አይመስልም፡፡ በሃር ማዶ የተከካዉና የተቦካዉ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ሲጋገር በተደጋጋሚ የሚስተዋል  ፖለቲካዊ እዉነታ ነዉ ፡፡

በተለይም በቋንቋና በብሄር ተቧድኖ  ለተቀዋሞ እና ለደጋፍ መሰለፍ  የዘዉጌ ዋልተኝነትን  (ethnic polarization) በማጦዝ  የማንወጣዉ የእርስ በርስ ጥላቻና ቀውስ ዉስጥ እየዘፈቀን መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባዉ አደገኛ ሂደት ነዉ፡፡ እንዴት ነዉ ነገሩ፣ መጨረሻችን ምን ሊሆን ነዉ የሚያስብል ይመስለኛል፡፡

ጎበዝ ትንንሽ ክስተተቶች ናቸዉ እየሰፉ ሄደዉ የቀዉስና የእልቂት ምክንያት የሚሆኑት፡፡ የጥላቻዉ እና የመገፋፋቱ ስሜት ከምህዋረ ዜና እና ከማሃበራዊ ሚዲያዉ አልፎ  በስፖርት ማዘዉተርያዎች መጸባረቅ ጀምሯል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መቐለ ላይ የተከሰተዉን የኳስ ሜዳ ግርግር ማስታወሱ በቂ ይመስለኛል፡፡

ግነት በሌለበት እዉነታ የኢትዮጵያዉያን የዘዉግ ክፍፍል (ethnic fractionalization) ከግለሰብ አስተሳሰብ አልፎ  ወደ ቡድናዊ ስሜት በከፍተኛ ደረጃ አድገዋል፡፡  አገራዊ ማንነት  በዘዉጌ ስሜት ተለዉጣል፡፡ ይህ ባይሆን ሁላችን ልኮራበት የሚገባ ጉዳይ  በዘዉግ ማንነት ተመዝኖ አስደንጋጭ በሆነ አከኋን ኢትዮጵያዊነት በአለም መድረክ ባልተዋረደ ነበር፡፡

ይህ እንዲሆን በርግጥም ኢትዮጵያን የሚያስተዳድራት ገዥ ሃይል በአላማ ሰርቷል ……. ተሳክቶለታልም፡፡ ከ 26 ዓመታት በኋልም ከተጓዘበት አገርን አደጋ ላይ ከሚጥል የተሳሳተ የፖለቲካ መስመር ለመዉጣት ፍቃደኛ የሆነ አይመስልም፡፡ ገዥዉ መንግስት ኢትዮጵያዊነት የሚል ስሜትን አጥብቆ  ይፈራል፡፡

ለዚህ ቀልል ማሳያ  ሚሊዮኖች በፍቅር የሚከተሉትን፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያከብር እና የሚዘክርን የጥበብ ሰዉን (ድምጻዊ ቴድሮስ ካሳሁን) ቃለ-መጠይቅ በዘዉጌ ማንነት አልተቃኝም በማለት መንግስት በሚቆጣጠረዉ ምህዋረ ዜና ለህዝብ እንዳይተላለፍ ከልክሏል፡፡ ይህ አይነቱ አሰራር የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን እቺ አገር የማናት የሚስብል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ይህን የመሳሰሉ ክስተቶች ናቸዉ ተከማችተዉ ወደ አልተፈለገ ዉዝግብና መገፋፋት የሚያመሩት፡፡

ከገባንበት አዙሪት፣ ሊመጣ ከሚችለዉ አደገኛ የእርስ በርስ ግጭትና ቀዉስ ለታደገን የሚችለዉ በህዝቦች መካከል እኩልነት፣ ፍትህ እና እዉነተኛ ፍቅር መኖር ሲችል ነዉ፡፡ የህዝቦች መስተጋብር እና ደማቅ ፍቅር የሚመሰረተው ከቂም በቀል በጸዳ ልቦና መቀራረብ ሲቻል ነዉ ፡፡

ለዚህ መሳካት በቅድምያ እዉነተኛ የእርቅ  መንፈስ በህዝቦች መካከል ሊሰፍን ይገበዋል፡፡ የስርአቱ ባለቤቶች ለ26 ዓመታት ከቀለዱት “ማን ከማን ተጣላና እናስታርቅ” ይሉት አይነት  አሰልቺ ኩሸት ተላቀዉ የኢትዮጵያን ለማዳን ሲባል በህዝቦች መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ ማደረግ ይኖርባቸዋል፡፡

መንግስት ከህዝብ ጋር እልህ መጋባቱን ማቆም ይኖርበታል፡፡ የመንግስት ሰዎች ከእያንዳንዱ ፖለቲካዊ ክስተት ተገቢዉን ትምህርት ወስደዉ ተገቢዉን የእርምት እርምጃ ማስከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ካለ ቅጥ እየተለጠጠ የመጣዉ የዘዉጌ ዋልተኝነት አገር የሚያጠፋና የህዝብን እልቂት የሚያስከትል አደጋን አዘሎ  እየተከተለን  መሆኑን ልንስተዉ አይገባም፡፡

ስለሆነም መንግስት የዶ/ር ቴድሮስ አሸናፊነትን ከግንቦት 20 ማድመቂያነት ባለፈ የተስተዋለዉን ተቀዋሞም አጢኖ የመግባባትና የመቀራረብ ስራዎችን ለመስራት ቢችል ባህር ማዶ ያሉ ወገኖች እና አክቲቪስት ነኝ ባዮችን ከጠርዘኝነት መስመር ወደ መሃል ለመሳብ ይችል ይሆናል፡፡

ይሄ የሚሳካዉ ግን ከዘዉግ ባሻገር በኢትዮጵያዊነት ለማሰብ የሚችል አቅም ያለዉ የመንግስት ሃይል ሲኖር ብቻ ነዉ፡፡ አሁን ያለዉን አገራዊ ቀዉስም ሆነ መጪዉን አደገኛ ሁኔታ መታገልና ማሸነፍ የሚቻለዉ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ዳርቻ ያሉ ህዝቦችን በኢትዮጵያዊነት መፈስ ማስተሳሰርና በእኩልነት ማሰተዳዳር ሲቻል መሆኑን አበክሮ  መረዳቱ ቁልፍ ጉዳይ ነዉ፡፡

ያኔ ሃቀኛ ዴሞክራሲያዊና እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያ ደምቃ ትታያለች፡፡ ያኔ በአለም መድረክ የሚገኝ ድል የጋራ ደስታችን፣ ሽፈታችንም የወል መከራችን ይሆናል፡፡ ለዚሁሉ መሳካት ግን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደም ሆናል!

*************

Guest Author

Guest Author

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago