(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

ጭር ሲል አይወድም፡፡ የሚተነኳኮል ካገኘማ በምን እድሉ፡፡ አስኪቀዋወጡ ያራግበዋል፡፡ ምድርና ሰማዩ ሲደበላለቅ ብቻ ዳር ቆሞ ይስቃል፤ አሊያም በሰው ልጆች ሞኝነት ይደነቃል፤ ወዲያውም ሌላ ቀውጢ ፍለጋ ይኳትናል፡፡ እብድ ነዋ! ከማንነቱ የተራራቀ፤ ማህበረሰብ ከተግባባበት እውነታ ውጪ ሆኖ የሚኖር፤ ያመነበትን ሁሉ ያለምንም ሀፍረት የሚያደርግና ሁሌም የሚቀውጥ ዓይነት፡፡ እንግዲህ እብድ ጥለኞች መሀል ከገባ የሱ ገላጋይነት ዲንጋይ ማቀበል፤ በሚፈጠረው ነገር መርካት ነው፡፡ አለቀ ሌላ ምንም ሀሳብም ሆነ መላ የለውም፡፡

ታዲያ የዘመናችን ፖለቲካም እንደዚህ እየሆነ ያለ አይመስላችሁም? አንዳንዱ የቀጠና የጎበዝ አለቃ ራሱን አድርጎ ይሾምና በሰው ሀገር ጉዳይ ጥልቅ፡፡ ጓዳ ድረስ ይገባና አሸማጋይ ይመስል ጦር አቀብሎ ሲጠዛጠዙ ለሱ በሚመቸው ሁኔታ ሀገሪቱን ለመቀጥቀጥ መዶሻ ያዘጋጃል፡፡ ሌላው ደግሞ በስመ እገዛና እርዳታ አሊያም የሁለትዮሽ ትብብር በራሱ ዜጎች ላይ ያላደረገውን በነዚህኞቹ ይሞክርና ማንነታቸውን ያሳጣቸዋል..ብቻ ስንቱ የእብድ ገላጋይ አለ መሰላችሁ፡፡

ወዲህ መለስ ደግሞ በውስጥ ጉዳይ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በየሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ፤ ወርድና ቁመት ልክ መስፋቱ አሰልቺ ስራ ይሆንበትና ሳያውቅላት ሀገሬ እኔ አውቅልሻለሁ የሚልም አለ፡፡ ምድረ ፈላስፋ በየበረሃውና በየጫካው እውኑን አልሞ ይበጃል ያለውን አስተሳሰብ ሀገሬ ካልተገበረችው ሞቼ እገኛለሁ ሲል አታሞ መደለቅ! እሱን መሳዮች ያሰባስብና ለሀገሬ የሚበጀው በዚህ መንግድ ስንሄድ ነው እያለ መለፈፍ! አልሆን ሲለውም ግብግብ ውስጥ በመግባት ጊዜን የማባከን ስራ የሚሰራም ጎዳና ይቁጠረው፡፡

እሱም አንድ ነገር ነው ደግሞ በእውቀትና በልምድ የዳበረ አእምሮ አለኝና ይህን ሀገር መምራት ያለብኝ እኔ ካልሆንኩ ምኑን ሀገር ሆነች እያለ የህዝብ ስሜት፤ ፍላጎትና ውጥን ልብ ሳይለው እርስ በርስ ሲጠዛጠዝ የሚውልም ሞልቷል፡፡ ታዲያ በስመ የእንቶኔ ፋውንዴሽን የተቋቋሙ በጎ አድራጊዎች ደግሞ ሽንጣቸውን ይዘው ይሟገቱላቸዋል፤ ገንዘብ ይሰቷቸዋል፤ ለህዝባችን የቆሙ ይመስል እኛኑ እርስ በርስ ማቀጣቀጥ!

እኛም ሞኞቹ ዱላ አንስተን ስንከሻከሽ ሀገር መሽቶባት ማደሪያ ስታጣ ወዮታችን ራሱ ወዮ ነው፡፡ ወዲያም እድሜ ልኩን የህዝብ ወንበር ላይ ተጣብቆ መምሻውን ሀገሩን የሚያሻት ስንት ጉደኛም አለ፡፡ እልፍ ሲልም ከዚያችው ወንበር ስር ተወሽቆ የሚመራትን ሀገር ላብ የሚመጥ፤ ከነመሰሎቹ ጋር እየዶለተ የሚቸበችባትም እንዲሁ፡፡

መደማመጥ የሌለበት ፖለቲካ ትርፉ ያው መበተን ነው፡፡ እረኛ እንዳሌላቸው በጎች መቅበዝበዝ፤አቅጣጫው እንደጠፋበት ኮምፓስ ነፋስን መከተል! ነገር ግን ህዝብ ሁሉንም ያውቃል፡፡ ለህዝብ ልብ ልብ የሰጡ ሀገራት ዜጎቻቸውን ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆኑ አሸናፊ ማድረግ ችለዋል፡፡ በፖለቲካ ርእዮቶች መግባባት ሲያቅታቸው ባለመግባባታቸው ተግባብተው በህዝብ ጥቅሞች፤ ብልጽግናና ንቃተ ህሊና መዳበር ላይ ግን አብረው ለስኬቱ ይዋደቃሉ፡፡

እከሌ የሰራው ልብስ አይመጥነኝም አሊያም እሱ ስለነካው ብቻ አልለብሰውም አይሉም፡፡ ይደምቁበታል፡፡ ልዩነቶቻቸውን ደግሞ የአንደኛው እስኪያሸንፍ በአደባባይ ያታግሉአቸዋል፡፡ አሸናፊው ሲለይና ህዝብ ሲከተለው ውሁዳኑ እጅ መስጠታቸውን ያውጃሉ፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እነሱ ጋር የማይሳራ ኋላቀር ተረት ተረት ነው፡፡

እንዲህ ያለውን ልብና አመል በሰጠን ብዬ ተመኘሁ፡፡ ምኞቴ መሬት ጠብ አይልም ይሰጠናል፡፡ ያለፋን እንደሁ እንጂ ይሰጠናል፡፡ በተለይ እኔ የተገኘሁበት ታላቁ የገዳ ስርዓት ባለቤት የኦሮሞ ህዝብ ለዚህ እጅግ ቅርብ ነው፡፡ እነዚህ ዛሬ የሰለጠኑቱ የሚከተሉት እሴቶች ጥንት ከኛ ጋር ነበሩና፡፡ ዛሬም ሰከን ብለን ካጤናቸው ከእሴቶቻችን ብቻ በመማር የዚህ ሀገር ፋኖ የማንሆንበት ምን ምክንያት ይኖራል ስልም አሰብኩ፡፡

በርግጥ የእብድ ገላጋዩ ብዙ ነው፡፡ የሚያቀብለንን ዲንጋይ እየያነሳን ሀገር ከገነባንበት ግን ጥል ሳይሆን ሰላም፤ መቃቃር ሳይሆን መወዳጀት፤ መቀማማት ሳይሆን የቄሳርን ለቄሳር የእግዜርን ለእግዜር በሚለው አስተሳሰብ የሚገባውን ለሚገባው በመስጠት፤ በመፈራራት ሳይሆን በተጨባጩ ዓለም በመተማመን የእኩልነት ሀገር መገንባት እንችላለን፡፡

አሁን ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ድርጅት በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ሊከፍት እንደሆነ የመንግስት ትልልቅ ሰዎች ባሳወቁ ጊዜ ያየሁትን የእብድ ገላጋይ ብዛት ቁጥሩን ያይደለ ሀሳቦቹን በመተቸት ምንኛ ስንቀጣቀጥ እንደሚደሰቱ ላሳይ፡፡ ትናንት የክልላችን ህዝብ ጥያቄ የአፋን ኦሮሞ እድገት ነበር፡፡ የፌዴራላችን ሁለተኛ የስራ ቋንቋ ለመሆን አያንስም የሚል ብዙ ድጋፍ ያለው ጥያቄ ነበር ምድሪቱን የሞላት፡፡

እሰየሁ ነው ፈጣሪ በሰጠው አፉ እንዳይናገር ልጓም በነፍጠኛው የገዢ መደብ ተበጅቶለት የነበረ ህዝብ ሁለት አስርታት ሳይሞላ ለዚህ ጥያቄ መብቃቱ ለኔ ኩራት ነው፡፡ ይገባልም፡፡ ታዲያ በዚህ ፌዴራላዊ ሀገር ውስጥ ትልቅ እንዲሆን የምንፈልገውና ትልቅ እንደሆነ የምናምነው ቋንቋ በሁሉም ክልሎች የሚዲያ ጽ/ቤት ሲኖረው ቋንቋችን በነ እከሌ ምድር ላይ መጫወቻ እንዲሆን አንፈለግም የሚለው ወገን አንድ ዲንጋይ ሲወረውር፤ የነ እንቶኔው ቱባ ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄዎች መመለስ ሲያቅታችሁ ስድስት ድስት ትጥዳላችሁ በማለት የማላገጫ ሌላ ዲንጋይ ማቀበል! አንዳንዱ ደግሞ እንትና ሀገሪቱን ለኦሮሞ ልትሰጥና ልታጠፋችሁ ነው ሲል ሌላውን ወንድም ህዝብ ሌላ ዲንጋይ ማስጨበጥ ተያያዙት፡፡ እንደው በሞቴ ማን የማንን ሀገር ለማን እንደሚሰጥ ነው ግራ የሚሆነውኮ!

ደግሞ በዚያኛው ሰሞን ፊንፊኔ ላኦሮሚያ በህገ መንግስቱ በገባችው ቃል መሰረት ልዩ ጥቅም ታስጠብቅ ዘንድ መነሳሳት ሲጀመር ወዮ እነ እከሌ ከፊንፊኔ ተጠራርገው ሊጠፉ ሆነ ሲሉ ጠጠር፤ ጠባብነት የተጠናወተው አመራርና ህዝብ ይህን ጉዳይ አራገበው በማለት ዲንጋይ፤ ፊንፊኔ የነ እከሌ መቀመጫ አለ እንጂ ራሷን ኦሮሞ ወይም የኦሮሞ ሲል ህገመንግስቱ አላስቀመጠም ሲሉ ዓለት ማቀበል ላይ ከረሙ፡፡ ሰሚ አይኖርም እንጂ!

ደግሞ የህዝባችን ተጠቃሚነት እጅጉን ወደኋላ የቀረው በደላላ ባለሃብቶች፤ በጥገኛ ባለስልጣኖችና በብልጣብልጥ አይዲዮሎጂስቶች ረቂቅ የኢኮኖሚ ምዝበራ ነውና መስመር እናሲዘው ሲባልና ወጣቶቻችን እትብታቸው በተቀበረበት ቀዬ በቅሚያ ከተሰሩ ህንፃዎች ስር ድድ ሲያሰጡ መዋል የለባቸውም፤ አቅማቸው ፈቅዶ የመይማሩበት የግል ትምህርት ቤት አጥር ስር መኮልኮል የለባቸውም፤ የማይታከሙበት የናጠጡ ሀኪም ቤቶች በራፍ ላይ አላፊ አግዳሚውን ሳንቲም መጠየቅ አይኖርባቸውም፤ የአያቶቻቸው መሬት ላይ በተሰሩ የተንጣለሉ ቪላዎች ዘበኛ ለመሆን ግልምጫና ጡጫ አይገባቸውም ቢባል የፌዴራል ስርዓቱ አፈረሱት የሚል ጦር ሲያቀብሉ ታዩ፡፡ ጥንተ ነገርን እንደማኮላሸት ሀገርን ማፍረስ እንደሌለ አያውቁት እንደሁ ደፍሬ ልናገር ወሰንኩ፡፡

ብቻ ስንቱ ይነገራል ወዳጆቼ! ወደ ቀደመ ነገር እንመለስና እኛ ኦሮሞዎች እነዚህ የእብድ ገላጋዮች የሚያቀብሉንን ዲንጋይ እያነሳን ሀገራችንን መገንባት የሚችል ስብእና ያለን ህዝብ እንደሆንን ለማሳየት ቆርጦ መነሳት ይገባል፡፡ ሀገሪቱ የሁላችንም ነች፡፡ ሁላችንም የምንኖርባት ግን የተፈጥሮንና የተግባባንባቸውን እንዲሁም ውል አድርገን የተፈራረምንባቸው ህጎችን አጥብቀን በሀቅ በማስፈጸም ነው፡፡ ፍትሀዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሲባል በተነሳ ንትርክ መሀል ገብቶ እንደ ገላጋይ ዲንጋይና ጦር ማቀበል ሳይሆን፤ እድሜ ልካችንን ፖለቲካ በመተንተን ብቻ ሳይሆን ከፊሉን ጊዜም ሀገር ለመገንባት በማዋል፤ ወገን ተጠቃሚ በሚሆንባቸው መስኮች በመሳተፍ፤ ለብልጽግና ማናቸውንም መስዋእትነት በመክፈል፤ ለወንድማማችነትና እኩልነት በመዋደቅም ልናሳልፍ ይገባል፡፡

ያኔ ህዝባችን ሀገሩን የሚወዳት፤ማህበራዊ እድገቱ የሚጠበቅባት፤ የሚጠላለፍባት ሳይሆን ወደእድገት ጎዳና የሚተላለፍባት ሰፊ መንገድ ትሆናለች ስል አለምኩ፡፡ ቸር እንሰንብት!

************

Guest Author

Guest Author

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago