አቶ ሙክታር ከድር የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ሆኑ

የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ አቶ ሙክታር ከድርን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር፣ አቶ ለማ መገርሳን አፈጉባኤ አድርጎ በመመምረጥ ተጠናቀቀ፡፡

ጉባኤው በኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር በወይዘሮ አስቴር ማሞ የቀረቡትን የአቶ ሙክታር ከድርና የአቶ ለማ መገርሳን ሹመት በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቋል።

ተሿሚዎቹ የተመረጡት የትምህርት ደረጃቸው የሥራ ታታሪነታቸውና የማስፈፀም ብቃታቸውን ከግምት ውሰጥ በማስገባት ነው ተብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር እንደገለፁት በምክር ቤቱና በሕዝብ  የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣትና የክልሉን ልማትና መልካም አስተዳደር የማስፈን ስራ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ይሰራሉ።

በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራር ላይ አቶ አለማየሁ የያዙትን የማይናወጥ አቋም ከዳር ለማድረስና የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ስር የሰደደውን ድህነትና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የገጠርና ከተማውን ሕዝብ በአንድነት ያቀፈ ንቅናቄ በመፍጠር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሥራ እድል ፈጠራና ሌሎች ተጓዳኝ ዘርፎች ላይ ርብርብ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር በየደረጃው በሚገኙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች በመዘርጋት ውስብስብና ሊፈቱ ያልቻሉ የመልካም  አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለማስወገድ የተጀመረውን ፈጣን ልማት እንደሚያስቀጥሉ ገልፀው በንግድ ፣በመሬትና ኢንቨስትመንት፣ በልማት ድርጅቶች የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስናን ምንጭ ለማድረቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው የክልሉን የሰባት ወራት የሥራ እቅድ አፈፃፀም ሪፓርት፣ሥራ አስፈፃሚዎችን ለማደራጀት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 163/2003 ለማሻሻል የተዘጋጀውን ረቂቅ ሰነድ ፣የኦህዴድ ባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥና የመጋላታ ኦሮሚያን ረቂቅ አዋጅ ጨምሮ የክልሉ ርእሰ መስተዳድርና ዋና አፈጉባኤ፣የኦሮሚያ ሬዲዮና ቲቪ ዋና ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቋል።

*******
* ምንጭ፡- ኢዜአ፣ መጋቢት 18/2006. 

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories