ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

ነሐሴ 16/2008

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከነሃሴ 10-15/2008 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በመገምገም በአንድ በኩል በእስካሁኑ ትግል የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝብ መብትና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በድርጅቱ የቀረበውን የአስራ አምስት ዓመታት የለውጥ ሂደት የሚመለከት የግምገማ ሃሳብ መነሻ በማድረግ በዚህ ሂደት በአገራችን የተመዘገቡ አዎንታዊ ለውጦችና በተጨባጭ የሚታዩ ድክመቶችን በዝርዝር ገምግሟል፡፡

በዚህ ግምገማ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭም መላ ህዝባችን እንደሚመሰክረው አገራችን ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በሁሉም የህይወት መስኮች ከፍተኛ ለውጥ እያመጣች ተጉዛለች፡፡ ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በዚህ የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የዜጎችና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው ተከብረዋል፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ አዲስ ዓይነት ፌደራላዊ የእኩልነት ስርዓት ተገንብቷል፡፡ የሃይማኖት እኩልነት ተከብሮ መንግስትና ሃይማኖት ተነጣጥለዋል፡፡ የዜጎችና የመላ ህዝባችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ህዝብ የሚጠቀምበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በመገንባት ረገድ ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡

አገራችን የተያያዘችው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግቦች በተሃድሶ የመጀመሪያ ዓመታት በግልፅ እንደተቀመጠው ፈጣንና ህዝብ የሚጠቀምበት ዕድገት ለማምጣት የሚያልሙ ናቸው፡፡ በዚህ መሰረት የነደፍነውን ግብርና መር የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ተከትለን በመጓዝ ኢኮኖሚያችን ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ተከታታይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ ችለናል፡፡ ከዚህም ዕድገት ህዝባችን ተጠቃሚ እንዲሆን ያላሰለሰ ትግል ተካሂዷል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠመንና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቀውን የድርቅ አደጋ ትርጉም ያለው የውጭ እርዳታ ሳናገኝ በራሳችን አቅም ልንቋቋም መቻላችን በአገራችን ምን ያህል የተጠናከረ የኢኮኖሚ ግንባታ ሲካሄድ እንደቆየ የሚያመላክት ነው፡፡

በከተሞች የኢንዱስትሪ ልማት በመስፋፋት ላይ ሲሆን፣ የአገልግሎት ዘርፉም እጅግ ፈጣን ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህን ከመሰለው ዕድገት ጋር በማይነጠል መልኩ የህዝብ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ መቆየቱም የተሃድሶ ጉዟችን ያስመዘገበው መሰረታዊ ስኬት ነው፡፡ መንግስት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣ ብቻ ሳይሆን ከዕድገቱ ብዙሃኑ ህዝብ ዋናው ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት በማመን ተንቀሳቅሷል፡፡ በገጠር አርሶ አደሩ ከመሬቱ ሳይፈናቀል እንዲለማ በማድረግ፣ በከተሞች ደግሞ ለወጣቱ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚበጅ ሰፊ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ልማት በማረጋገጥ ለውጥ ለማምጣት ተረባርቧል፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ተስፋ ሰጭ ጅምሮች ታይተዋል፡፡ ምንም እንኳ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የአገራችን ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ከመጨመሩና ሰፊ የወጣት ኃይል ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ ለውጡ ሁሉንም በሚያረካና ተጠቃሚነቱን በሚያረጋግጥ ደረጃ ሄዷል ባይባልም ከማንኛውም መሰል አገር በተሻለ ደረጃ የህዝብ ተጠቃሚነት እየሰፋ የሚሄድበት ሁኔታ ለመፍጠር ተችሏል፡፡

በማህበራዊ ልማት መስክ በተለይ ትምህርትን በማስፋፋት ረገድ አገራችን የተጓዘችበት ሂደትና ርቀትም እጅግ የሚያስመካ ነው፡፡ ዛሬ ከአገራችን ህዝብ 30 በመቶ ያህሉ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል፡፡ ትምህርት የለውጥ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የፍትሃዊ ዕድገት ማረጋገጫ እንደሆነ በማመን ይህን ያህል ብዛት ያለው ዜጋ በማስተማር ላይ መሆናችን በርግጥም በአገራችን የሚገነባው ስርዓት ህዝብን ያማከለ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በጤናው መስክ በተከተልነው መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ በአገራችን ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ በዚህ የተነሳ በ1983 ዓ.ም. አርባ አምስት ዓመት ብቻ የነበረው የዜጎች አማካይ ዕድሜ በአሁኑ ጊዜ ወደ 64 ከፍ ብሏል፡፡ መንግስት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት የሚደግፉ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማስፋፋት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት አገራችን ከቀን ወደ ቀን ተወዳዳሪ የሆነ የመሰረተ ልማት አቅርቦት በማሟላት ላይ ትገኛለች፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው ግምገማ መሰረት ባለፉት 15 ዓመታት እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ ውጤቶች ሊገኙ እንደቻሉ አረጋግጧል፡፡ ይህም በአገራችን ዋነኛ ተልዕኮው ህዝብን ማገልገልና በዚህ ቅኝት መንቀሳቀስ እንጂ የግል መጠቀሚያ ያልሆነ መንግስት ለመገንባት የተደረገው ጥረት ያስገኘው መልካም ዕድገት እንደሆነም አስምሮበታል፡፡ ቀጣዩ ሂደት ይበልጥ ፍሬያማ የሚሆነው ይህን የለውጥ አቅጣጫ ከማንኛውም ጉድፍ ጠብቆና ተከላክሎ በማስቀጠል እንደሆነም አረጋግጧል፡፡

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይህን መነሻ በማድረግ ባካሄደው ግምገማ በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ አገራዊ ለውጡ በስኬት ሲጓዝ የቆየው መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ በመቻሉ የሆነውን ያህል ይህ ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት ይደነቃቀፋል፡፡ መልካም አስተዳደርም ይጠፋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ካለ ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት ወስኗል፡፡ ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅታችን ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ወስኗል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትነ እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችም አዘጋጅቷል፡፡

ድርጅታችን ኢህአዴግ መላ የአገራችን ህዝቦች በአገራችን የፈነጠቀውን የልማትና የዴሞክራሲ ጮራ ተማምነው በለመለመ ተስፋቸው ወደፊት በሚመለከቱበት በዚህ ወቅት በድርጅትና በመንግስት አካላት ዘንድ የታየው ይህ ስህተት ተስፋቸውን እንዳያጨልመው ያደረጉትን ትግል ከታላቅ አክብሮት ጋር ይመለከተዋል፡፡ መንግስት ከህዝብ ጋር በከፈታቸው መድረኮች ሁሉ ህዝቡ ተስፋውን የማያለመልሙ ድክመቶች እንዲታረሙ ሲታገል እንደቆየም ይገነዘባል፡፡ ምንም እንኳ በድርጅታችንና በመንግስት አመራር ዘንድ ሲከሰት የቆየው ያልተስተካከለ ዝንባሌ ይህ የህዝብ ድምፅ በአግባቡ እንዳይሰማና ችግሮቹም በፍጥነት እንዳይቀረፉ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም መላ የአገራችን ህዝቦች በየአካባቢው የሚታዩ ስህተቶች ይወገዱ ዘንድ ጠንከር ባለ አኳኋን ያካሄዱት ትግል ስራ አስፈፃሚው ለወሰዳቸው የለውጥ አቋሞች ጠንካራ መሰረት ሆኖ አገልግሎናል፡፡

ድርጅታችን ኢህአዴግ ገና ከጥዋቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመገንባት ሲነሳ በአንድ በኩል መንግስታዊ ስልጣንን የህዝብና የአገር መገልገያና ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ ለማድረግ በማሰብ ቢሆንም ባለንበት የዕድገት ደረጃ ጠንካራና ጤናማ መንግስት የመገንባት ጉዳይ ከፈተናዎች ውጭ ይሆናል ብሎ አያምንም፡፡ ይልቁንም እንደእኛ ባሉ የሽግግር ኢኮኖሚ ውስጥ ባሉ አገሮች ሁሉ በአንዳንዶች ዘንድ መንግስትን ከህዝብ አገልጋይነት መስመር እያስወጡ የግል መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት የማያቋርጥ ፈተና እንደሚሆን ያምናል፡፡ ባለፉት ዓመታት በአገራችን የህዝብ መብትና ጥቅም ቅድሚያ አግኝቶ የተከበረበት ስርዓት ለመገንባት ባካሄድነው ትግል ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ወይም ኪራይ ሰብሳቢነት ትልቁ ፈተናችን እንደሆነ ለአፍታም ቢሆን ሳይነሳ የቀረበት ጊዜ የለም፡፡ መላው የአገራችን ህዝቦችም ቢሆኑ ካላአግባብ መጠቀም የሚሹ ሰዎች የመንግስት ስልጣንን የግል ብልፅግና ማረጋገጫ ለማድረግ በመሻት በሚፈጥሩት እንቅፋት የለመለመ ተስፋቸው ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል ያላነሱበት ጊዜ የለም፡፡

እነሆ ዛሬ ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሰረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግስትና በድርጅት ማዕቀፍ እንደሚታይ ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ተገንዝቦ ይህንኑ ለማስተካከል የሚያስችል እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ እንቅስቃሴው በአዲሱ በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ በሚጠበቁ የለውጥ ፕሮግራሞች ተጠናክሮ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

አገራችን ኢትዮጵያ ከዘመናት የማሸለብና የማሽቆልቆል ጉዞ ተላቃ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል በለውጥ ጎዳና ስትገሰግስ ቆይታለች፡፡ በተለይ ደግሞ የተሃድሶ እንቅስቃሴው ከተጀመረ በኋላ ባሉት አስራ አምስት ዓመታት ፈጣን ብቻ ሣይሆን የህዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የጀመረበት ዕድገት ስታስመዘግብ ቆይታለች፡፡ ይህ ለውጥ ድርጅታችንና መላ የአገራችን ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ያመጡት ለውጥ ነው፡፡ ወጣቶችና ሴቶች፣ አርሶ አደሮችና ሰራተኞች፣ ምሁራንና ልማታዊ ባለሃብቶች ከድርጅታችንና ከልማታዊ መንግስታችን ጋር ተደጋግፈው ዕውን ያደረጉት ለውጥ ነው፡፡ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን አገራችንን ወደፊት ለማረማመድ የሚያስችል ከፍተኛ ልምድ የተገኘበትም ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ የለውጥ ጉዞ ካለአግባብ የመጠቀም አዝማሚያ በሚፈጥረው ዕንቅፋት ምክንያት የህዝባችንን የተሟላ እርካታ ያላረጋገጥን ቢሆንም ህዝባችን የጀመረውን ፀረ-ጥገኝነት ትግል አጠናክሮና በዚህ ረገድ ድርጅታችን የነደፈውን የለውጥ መርህ-ግብር በፅናት ተግባራዊ እስካደረግነው ድረስ መሰናክሎችን አልፈን ወደ ዘላቂ ዕድገት እንደምናመራ በፅኑ እንተማመናለን፡፡ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት አጋጥሞን የነበረውን ተመሳሳይ ዝቅጠት አልፈን ዓለምን ያስደነቀ ለውጥ እንዳስመዘገብነው ሁሉ የወቅቱን ድክመቶች ቀርፈን ለሌላ ተመሳሳይ ድል እንደምንበቃም ያምናል፡፡

በመሆኑም የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴና እንደገና የመታደስ ጥረት ለላቀ ፍሬ እንዲበቃ መላ የአገራችን ህዝቦች ሰላማዊና ህጋዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ የውጭም ሆነ የውስጥ ፅንፈኛ ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ኃይሎች ህዝቡ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉ የገነባውን ስርዓት በቀጣይነት ለማሻሻል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መጠጊያ አድርገው ሁከትና ትርምስን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት በፅናት እንዲመክትና በሀገራችን ህዝቦች ብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነትና አብሮነት በአስነዋሪ የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳቸው ለማላላት የሚያደርጉትን አፍራሽ እንቅስቃሴ እንዲያመክነው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በአሁኑ ወቅት የሚታዩትን ውስንነቶች በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በመፍታት በምርጫ ካርድ የተሰጠውን ኃላፊነትና አደራ ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ እራሱን ገምግሞና አጥርቶ ለመንቀሳቀስ የጀመረውን የአስራ አምስት አመታት የተሃድሶ ጉዞ ግምገማ በየደረጃውና በሁሉም ተቋማት በጥልቀት እንደሚካሄድ ያስታውቃል።

ህዝባዊነታችን ለህዳሴያችን !
ክብርና ሞገስ ለትግላችን ሰማዕታት !

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ነሃሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም
አዲስ አበባ

*********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories