‘አንድነት’ ከሆያሆዬ ወጥቷል – አቅጣጫው ዴሞክራሲያዊ Dominant ፓርቲ መሆን ነው

(አሥራት አብርሃም – የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ‹‹የአንድነት እስትራቴጂ ከሁሉም ይለያል!›› በሚል ርዕስ በፌስቡክ ገጹ ያተመው)

በምርጫው እንደሚሳተፉ እርግጠኛ ሳይሆኑ የምርጫ ምልክት ከወሰዱ ፓርቲዎችና በሂደቱ በደመነፍስ ከገቡ ፓርቲዎች አንድነት በእርግጠኝነት የተሻለ አቅጣጫ ያስቀመጠ ፓርቲ ነው። የፖለቲካውን ምህዳር ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በማስፋት በምርጫው ላይ በሙሉ ልብ ለመሳተፍ ወስኗልና።Andinet UDJ party logo

አንድነት በባዶ መሬት ህዝቡን ሳያደራጁ ህዝባዊ አመፅ ከሚጠሩትም በእጅጉ የተሻለ እቅድ ያለው ፓርቲ ነው! አሥር ሰው ይዞ ፓርቲ መመስረት ይቻል ይሆናል አሥር ሰው ይዞ ስርዓት መቀየር ግን የሚታሰብም፤ የሚቻልም አይደለም።

ስለዚህ እስኪ በመጀመሪያ ህዝቡ ከጫፍ እስከጫፍ ይደራጅ፤ እስኪ በምርጫው ሂደት በንቃት እንዲሳተፍ እናድርገው፤ ከዚያ ባግባቡ የተደራጀ ህዝብ ምን ማድረግ እንደሚችል ለማየት ቀላል ነው የሚሆነው።

መምረጥ የሚችል ዜጋ ሁሉ በትክክል የህዝብ ታዛቢዎች ይምረጥ፤ የምርጫ ካርድ በነቂስ ወጥቶ ይያዝ፤ እንደገናም በነቂስ ወጥቶ ይምረጥ ይህን ሁሉ ሂደት ከታለፈ በኋላ ምርጫው የሚዘረፍ ከሆነ ያኔ ይህ የተደራጀ ህዝብ ህዝባዊ እምቢተኝነት ለማካሄድ በቂ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል።

የአንድነት እቅድ ይሄ ነው፤ ሌላ እቅድ አለኝ የሚል ካለ መብቱ ነው፤ አንድነት በእኔ እቅድ አጨብጫቢ ሆኖ ይሰለፍ ማለት ግን ተገቢ አይደለም፤ ተቀባይነትም የለውም። አንድነት በመላ ሀገሪቱ ሰፊ መዋቅር ያለው፣ ስለአባላቱና ስለህዝቡ ሀላፊነት የሚሰማው ፓርቲ ንው።

ከዚህም ባሻገር የነገው መንግስት መሆን የሚያስችለው ቁመናና ስብስብ ያለው ፓርቲ ነው። በዚህ ምክንያት በእርሱ ክብደት ድልድዩን አንቀጠቀጥነው ለማለት ለሚመኙ ሁሉ የሚመች ፓርቲ አይሆንም፤ ከሆያሆዬ ፖለቲካ ነጥሮ ከወጣም ቆይቷል።

ስለዚህ በዚህች ሀገር ለውጥ እንዲመጣ በትክክል የሚፈለግ ከሆነ በአንድነት መንገድ ጠንክሮ መሰለፍና መጓዝ ነው፤ አንድነት አብሮ ለመስራት እጅግ በጣም ግልፅ የሆነ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በፕሮግራምም በአደረጃጀትም ተመሳሳይ ለሆኑ ፓርቲዎች የውህደት አጀንዳ አስቀምጦላቸዋል፤ አንድነት ከእነዚህ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁነት ለመዋሃድ ዝግጁ ነው፤ በመሆኑም ግንባር ቅንጅት እያለ ጊዜው በከንቱ የሚያጠፋበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም፤ አንዳንዶቹ ውህደት የሚጠሉትአጀንዳው የስልጣን እንጂ ሌላ ስላልሆነ ነው። በፕሮግራም ግልፅ የሆነ ልዩነት ካላቸው ጋር በትብብርና በሌላም መንገድ አብሮ መስራት ይቻላል።

አንድነት እንደ አቅጣጫ ይዞት ያለው መንገድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ህዝቡን ከጫፍ እስከጫፍ በማደራጀትና መዋቅር በመዘርጋት ዴሞክራሲያዊ ‘Dominant’ ፓርቲ መሆን ነው።

*********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories