ምርጫ 97 ነፃ ነበር ከአሁኑ ይሻላል የሚለው ተቀባይነት የለውም – ፕ/ር መርጋ በቃና

Highlights:-

* ምርጫ 97 ሲቪክ ማህበራት ሥነ ዜጋን ለማስተማር በሚል በሰፊው ገብተውበት ነበር፡፡ ነገር ግን ይሰሩት የነበረው ስራ ለፓርቲዎች እስከመመልመል የደረሰ ነበር፡፡ ትምህርት ሳይሆን ዘመቻ ነበር ሲያካሂዱ የነበሩት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወክለው ቅስቀሳ ነበር የሚያካሂዱት፡፡ በግልፅ እከሌን ምረጡ! ይሉ ሁሉ ነበር፡፡

* ባለፈው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጥያቄ ነው የስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት እዛው ክልል በመሄድ የሰጠነው፡፡ የእነሱ የስራ ቋንቋ አማርኛ ነው ፡፡ እኛ በአምስት ቋንቋ ነው የሰጠነው፡፡

የተጠቀምነውም አገር በቀል ብቻ አይደለም ፡፡ ሱዳን ጠረፍ ያለን እንደመሆናችን አረብኛ ቋንቋ ነው የምንሰማው ስለዚህ በደንብ እንዲገባንና እንድንሰማው በአረብኛ ቋንቋ ይሰጠን ብለው በአረብኛ ቋንቋ ነው ትምህርቱን የሰጠናቸው፡፡ በደቡብ ብሄር ብሄረሰብም በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በስድስት የኮሌጅ ቋንቋዎች ነው የሰጠነው፡፡ ክልሎች በጠየቁን መሰረት 32 ቋንቋ ድረስ የተጓዝንበት ሁኔታም አለ፡፡

* [ምርጫ ቦርድ] ባለ ራዕይ ቦርድ ነው!የቀጣዩ ሃያ፣ ሰላሳ፣ አርባ ዓመት ምርጫ ምን መምሰል አለበት ብሎ በማሰብ የሚሰራ ነው፡፡

*ከሌሎች በርካታ አገሮች በሎጀስቲክ ሻል ያልን ብንሆንም በጣም ደከም ብለን የምንታይበት በሰው ኃይል አሰላለፍ ነው፡፡

*ስለዚህ በሚቀጥሉት 15 እና 20 ዓመት ምርጫ ቦርድ ከየትኛውም ተቋም ያልተናነሰ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ቴክኖሎጂ ነው የሚቀረን፡፡ አሁን የቴክኖሎጂውንም ጥናት ጀምረናል፡፡

[ስለምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት የሚነሳው] ጥያቄ በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡ የሰለቸንም ነው፡፡….አንድ ፓርቲ ነው ይሄን የሚያቀርበው፡፡ እሱም ፓርቲ ማርሹን እንደየወቅቱና እንደ ፍላጎቱ የሚቀያይር ነው፡፡ ሲበዛ ሁለት ይሆናል፡፡ ከሁለት በልጦ አያውቅም፡፡……[ከእነሱም ሙሉ በሙሉ አይደለም] በፓርቲዎቹ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን ማለቴ ነው፡፡

* በአመለካከት ከታሰረ እንጂ በወንጀል ከታሰረ ለማስፈታት ቃል አንገባም፡፡ በአመለካከቱ የታሰረ ከሆነ መቼ ታሰረ አምጡ ያገባናል እንላለን፡፡ በወንጀል የታሰረ ከሆነ ግን በወንጀል ህግ እንጂ በምርጫ ቦርድ ህግ አይዳኝም፡፡ ምክንያቱም ቦርዱ በምርጫ ህግ ነው የሚመራው፡፡ ወንጀለኞችን አንከታተልም፤ አያገባንም።

* 75 [ፓርቲዎች] አሉ፡፡ ነገር ግን የህግ ጉዳይ ያላሟሉና ስልጣንን ሞኖፖላይዝ ያደረጉ እንዲሁም ራሳቸው ባወጡት ደንብ መሰረት ለ18 ዓመታት ጠቅላላ ጉባኤ ያልጠሩ አንዳንድ ፓርቲዎች ይገኙበታል፡፡

* ከ75ቱ ፓርቲዎች በተለያየ ደረጃ ማለትም 52ቱ በክልል 23ቱ ደግሞ በአገር አቀፍ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

——–

የ2007 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ ዝግጅትንና ቦርዱ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲሁም በኢትዮጵያ ባለፉት ሥርዓቶች የነበረውን የዴሞክራሲና የጠቅላላ ምርጫ ሂደቶች አስመልክተን ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መርጋ ይህንኑ ጨምሮ በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሰጡት ማብራሪያ አለ። እነሆ…

ሰላማዊት ውቤ፦ ሕገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ በሀገራችን የተካሄዱ ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከማጎልበት አኳያ የነበራቸው ሚና ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር መርጋ፦ ምንም እንኳን በምርጫ ቦርድ ውስጥ የገባሁት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ቢሆንም በዜግነቴ መከታተል ስለነበረብኝ በፊት የነበሩትንም ምርጫዎች ለመቃኘት ሞክሪያለሁ፡፡ በአጠቃላይ በዕድሜዬም ኢትዮጵያ ከየት ተነስታ ነው እዚህ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት የደረሰችው የሚለውን መናገር እችላለሁ፡፡ ከፊውዳሉ ንጉሣዊ አገዛዝ ሥርዓት፤ ጭራሽ መድብለ ፓርቲ የሚባል ሥርዓት ከማይሰማበት ኮሚኒስት ወታደራዊ ሥርዓት ወጥቶ ወደ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት መግባት ከባድ ሥራ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በምግብ ረሃብተኝነት ነበረ፡፡ በእኔ እይታ ግን የምግብ ብቻ ሳትሆን የዴሞክራሲ ረሃብተኛም ነበረች፡፡ ይሄን ለማለት ያስቻለኝ ባለፉት አራት ዙር ጠቅላላ ምርጫዎች ሕዝቡ እያሳየ ያለው የዴሞክራሲ አስተሳሰብና የዴሞክራሲ ዕድገት ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዙር ጠቅላላ ምርጫዎች የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የዕድሜ ልዩነት ሳይደረግ በመምረጥና መመረጥ ዕድሜ ላይ የደረሰ ሁሉ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ ይሄ ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ ሕዝቡ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት፣ ልማት፣ ማህበራዊ ባህላዊና ዕለታዊ እንቅስቃሴ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ተሳትፎው እየጨመረ ነው የመጣው ማለት ይቻላል፡፡

ዴሞክራሲ ሂደት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ አሁንም በታዳጊ አገሮች ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ይሄ በበለጸጉ አገሮችም ይታያል፡፡ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ላቲንአሜሪካ፣ ኢስያም ሄደናል፡፡ አፍሪካንም ሙሉ በሙሉ አዳርሰናል፡፡ ምርጫን በመታዘብ፣ የልምድ ልውውጥ በተቀያየርንበት፣ በየውይይት መድረኩ በስልጠናና ጥናቶች ከቦርድ አባላትና ከላይ እስከ ታች ካሉ ባለሙያዎቸና የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ብዙ እንቅስቃሴና ልምድ አግኝተናል፡፡ በዚህ በኩል የእኛ እንቅሰቃሴ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናን፡፡ ከሁሉ በላይ የሕዝቡ ተሳትፎ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

በፓርላማ የመጀመሪያው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ከ 547 የፓርላማ ወንበር ውስጥ በሴቶች የተያዘው 13 ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ ተነስቶ አሁን በ4ኛው ላይ 152 ደርሷል፤ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ የሴቶች በመራጭነት መሳተፍ ከ48 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ ወጣቱ ተሳትፎ ላይ ችግር የለም፡፡ እንደውም አሁን በማህበር ተደራጅተው ከእነርሱ ጋር ብዙ እየሰራን ነው፡፡ በሁሉም ክልሎች ስለ ምርጫ ህግ እና ስለ ዴሞክራሲ ጉዳይ ዞረን አስተምረናቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ሕዝቡ እያወረዱልን ነው ያሉት፡፡ የሴቶች ማህበር፣ የመምህራን ማህበር በተመሳሳይ እዛም ወጣቶች አሉ፡፡ የዴሞክራሲ ዕድገቱ በጣም እየላቀ ነው የመጣው፡፡

ሰላማዊት ውቤ፦እስከአሁን የተካሄዱት አራት አገር አቀፍ ምርጫዎች ብሔር ብሔረሰቦች የሥልጣን ባለቤት እንዲሆኑ ከማስቻል አኳያ የነበራቸው ሚና ምንድነው?Prof. Merga Bekaka - Ethiopia election board

ፕሮፌሰር መርጋ፦ ፌዴራል ሥርዓቱ ራሱ እኮ ብሔር ብሔረሰቦችን መሰረት አድርጎ የተደራጀ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኛ ጠቅላላ ምርጫ ብቻ ሳይሆን አምስት ዓይነት ምርጫ ነው የምናካሄደው፡፡

በየአምስት ዓመቱ ጠቅላላ ምርጫ እናካሂዳለን፡፡ ይሄ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት የምናስመርጥበት ነው፡፡ ሁለተኛው የአካባቢ ምርጫ ሲሆን፤ ይሄ በዞን፣ ከተማ፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ፣ ቀበሌ ምርጫ የምናካሄድበት ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው የብሔር ብሔረሰቦች ፍላጎታቸው፤ የዴሞክራሲ ጥማታቸው በምርጫው ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሆኑ ያላቸው ፍላጎት የሚለካው፡፡ ዛሬ ብሔር ብሔረሰቦች፤ ከዚህ የበለጠ ትምህርቱን እንፈልጋለን፤ የራሳችንን ወኪል መምረጥ እንፈልጋለን፤ አልስራልንም ይውረድልን እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡

ሦስተኛ የሕዝበ ውሳኔ አለ፤ የሕዝብ ፍላጎት ምንለካበት፡፡ አራተኛ ማሟያ አለ፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች አንፈልግም ካሉ በተዘረጋው የምርጫ አሰራር መሰረት ማሟያ ይጠይቃሉ፡፡ እስከዚህ ድረስ ነው ብሔር ብሔረሰቦች በጣም ልቀው የሄዱት፡፡ ከዚህ አኳያ በራሴ ዕይታ እንደ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢነቴ ብሔር ብሔረሰቦች የዴሞክራሲ ጠንካራ ኃይል ናቸው፤ የዴሞክራሲን ጥቅምና መብትን አውቀዋል፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር ከፍተኛ ፍላጎትም አላቸው፡፡

በአጠቃላይ 75 ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉን፡፡ 23ቱ አገር አቀፍ ሲሆኑ፤ 52ቱ የክልል ፓርቲ ናቸው፡፡ ይሄ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ወኪል ራሳቸው ለመምረጥና ለዴሞክራሲ ያላቸው ፍላጎት መለኪያ ነው፡፡ ፓርቲዎች ከየት ነው የተፈጠሩት ቢባል ከነዚሁ ብሔር ብሔረሰቦች ነው፡፡ ባለፉት 8 ዓመታት የተማርኩት የእዚህ ሕገ መንግሥት ጠንካራ ጦር ተብለው የሚወሰዱት ብሔር ብሔረሰቦች መሆናቸውን ነው፡፡

ሰላማዊት ውቤ፦በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ እንከን የለሽም ዴሞክራሲያዊም ነበር ይባላል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንዲህ አይነት ምርጫ በቀጣይ ሊኖር አይችልም የሚል አንድምታ ያለው ሃሳብ ይሰጣሉ። የ1997 ዓ.ም ምርጫ ምን ነበር ልዩ የሚያደርገው? ወይም ተደጋግሞ እንደሚገለጸው በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ምርጫ ማካሄድ አይቻል ይሆን ?

ፕሮፌሰር መርጋ፦ ይሄ ጥያቄ በጣም በጣት የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ 52 ክልላዊ ፓርቲዎች አንድም ጊዜ እንደዚህ ያለ ጥያቄ አንስተውም አያውቁም፡፡ ምንአልባት ከ23ቱ ፓርቲዎች በጣም በጣት የሚቆጠሩት ሊያነሱት ይችላሉ፡፡ ምንም ይሁን ምን የ97 ምርጫ እንዴት ነበር? ከዛ በኋላስ 2002 ምርጫ እንዴት ነበር? የሚለውን ብንመልስ ጥሩ ነው፡፡

ምርጫ 97 ሲካሄድ እኔ እዚህ አልነበርኩም፡፡ ምርጫውን ስንጀምር እንደ አዲስ ቦርድ ምርጫ 97 እንዴት አለፈ? ከ 97ቱ ምርጫ ተምረን ቀጣዩን እንዴት ነው የምናሻሽለው? የሚለውን እሳቤ ይዘን ነው የተነሳነው፡፡ የተሻለ ለማድረግ ከአንደኛ ምርጫ 2ኛ፣ ከ2ኛው፣ 3ኛ ምርጫ፤ ከ3ኛም 4ኛ ምርጫ እያሉ እርስ በእርስ ማወዳደር ያስፈልጋል፡፡

እኛ በ1999 ዓ.ም መጥተን በ2000 ዓ.ም የአካባቢ ምርጫ ያዘጋጀነው ይሄን ሁሉ ታሳቢ በማድረግና በመገምገም ነው፡፡ ስለዚህ ከ1997 ምርጫ ምን ተምረናል? ብለን ነው የተነሳነው፡፡ በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ንብረት ወድሟል፤ ሕይወት ጠፍቷል። ለዚህ አስተዋፅኦ ያደረገው ምንድነው ብለን ጥናት ስናካሄድ ፤ አንደኛ የምርጫ ሕግ ነበር፤ ሕገ መንግሥቱ አለ፡፡ ሕገ መንግሥቱ የወለዳቸው ተመሳሳይ ሕጎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አንድም የአስፈፃሚ ደንብና ምዝገባ አልነበረም፡፡ ይህ አንድ ቁልፍ ነገር ነው፡፡

ሁለተኛ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ይሰጥ የነበረው በጣም ኋላ ቀር በሆነ ባህላዊ መንገድ ብቻ ነበር፡፡ ለምን ቢባል በአካዳሚክ ሕግ አስተምር ስትባል የማስተማሪያ መጽሐፍ መኖር አለበት፡፡ ሆኖም ይሄ መጽሐፍ አልነበረም፡፡ ብዙ ዕውቀት የጨበጡ የሃይማኖት አባቶች እንኳን የሚያስተምሩት መጽሐፍ ይዘው ነው፡፡ይሄ ባለመኖሩ በትግራይ ክልል ይሰጥ የነበረው የምርጫ ትምህርት ከኦሮሚያ የተለየ ነበር፡፡ የኦሮሚያው ከአፋር እየተባለ ትልቅ ልዩነት የታየበት ነው፡፡ ትምህርት አሰጣጡ ላይ ትልቅ ችግር ነበር፡፡ መራጩ ሕዝብ የምርጫ እውቀት አልነበረውም፡፡ የምርጫ ሕግ የሚባል አያውቅም፡፡ ይሄን ባለማወቁ የተወሰኑ ቡድኖች ወይም ግለሰቦችና መስመር የለቀቁ ፓርቲዎች በአንዳንድ ቦታ የተለያዩ ችግሮች ፈጥረዋል።

ሌላው የአቅም ግንባታ ስልጠና በፍፁም አልነበረም፡፡ ቁሳቁሱም ስልጠናውም አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰራተኞችም በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት አልሰጡም፡፡ ስልጠና አልነበራቸውም፡፡ እየሰሩ የነበሩት በባህላዊ አሰራር ነበር፡፡ ጠንካራ የሰው ኃይል አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው አምስት ብቻ ነበሩ፡፡ ሌላው በሙሉ በትምህርት ደረጃው ስድስተኛ፣ ስምንተኛ፣ 12ኛ ክፍል ነበር ፡፡ ባለሙያ የሚባል ጭራሽ ምንም አልነበረም፡፡ ሥነ ዜጋ ትምህርትና የሕዝብ ግንኙነት የሚመራ አልነበረም፡፡ እንዲሁም የፖለቲካ ዲፓርትመንት የለም፡፡ ጭራሽ ዲፓርትመንቶች አልተፈጠሩም ነበር፡፡ የተቀናጀ የእውቀት ሥራ አልተሰራም፡፡ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አልነበሩም፡፡ ምርጫው ላይ ሳይሆን ሎጂስቲኩ ላይ ብቻ ነበር ርብርብ ይደረግ የነበረው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ብዙ ነገሮች ያሻሻልነውና ወደ ዘመናዊነት የቀየርነው፡፡ ይሄ ሁሉ ባልነበረበትና ብዙ ነገር ማሻሻላችን በሚታወቅበት ሁኔታ ችግር አልነበረም ብሎ ለመግለፅ ያስቸግራል።

ሲቪክ ማህበራት ሥነ ዜጋን ለማስተማር በሚል በሰፊው ገብተውበት ነበር፡፡ ነገር ግን ይሰሩት የነበረው ስራ ለፓርቲዎች እስከመመልመል የደረሰ ነበር፡፡ ትምህርት ሳይሆን ዘመቻ ነበር ሲያካሂዱ የነበሩት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወክለው ቅስቀሳ ነበር የሚያካሂዱት፡፡ በግልፅ እከሌን ምረጡ! ይሉ ሁሉ ነበር፡፡

ከዛ ተምረን ብዙ ነገር ያሻሻልነው አሁን ነው፡፡ ክልሎች እንኳን በሥነ ሥርዓቱ የተስተናገዱበት አና እኩል ያልተሰራበት ነበር፡፡ ክልሉ ልክ ሌላ አገር እንደሆነ ሁሉ በሶማሌ ክልል ውስጥ ምርጫ ለብቻ ይካሄድ ነበር፡፡ በምርጫ ህጉ ግን ጠቅላላ ምርጫ በአንድ ወቅት በመላ ሀገሪቱ በሁሉም ክልል ይካሄዳል ነው የሚለው፡፡ይሄነን ህግ እንኳን ማስጠበቅ አልተቻለም፡፡ ነፃ ነበር፤ ከአሁኑ ይሻላል! የሚለው ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡ ህጋዊም አስተዳደራዊም አይደለም፡፡

እኛ እንደ ቦርድ የሀገራችንንና የውጭ ልምድ ደምረን ስናይ ሰማይና ምድር በመሆን ፍጹም አይገናኝም። እኛ ስልጣን ከያዝን በኋላ ሜክሲኮም፤ ህንድም ሳውዝ ኮሪያም፤ አሜሪካን በኒዮርክ ትላልቅ የአሜሪካ ባለስልጣናቶች በተሳተፉበት ተሞክሮችን አቅርበን አድናቆት ተገኝቶበታል፡፡

ከምርጫ 97 በኋላ ሕጉ ራሱ ተሻሽሎ፣ ዓለም አቀፍ መርሆዎቹን አስገብቶ በጣም አሳታፊ በሆነ ሁኔታ ወጥቷል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች በሕዝብ ከተመረጠው ገዢ ፓርቲ ጋር በሚያስማማቸው ጉዳይ ተባብረው የሚሰሩበት ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ያቀፈ ሕግም ተሻሽሏል፡፡

ሰላማዊት ውቤ፦ ህገ መንግስቱ ከፀደቀ በኋላ ያሉት 20 ዓመታት ብሄር ቤሄረሰቦችና ህዝቦች በስልጣን ባለቤትና በዴሞክራሲ ተሳትፎ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከማስቻል አንፃር የነበረውን ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?

ፕሮፌሰር መርጋ፦ በጣም! በጣም! በጥሩ ሁኔታ ነው የምገመግመው፡፡ እነሱ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደስ ይለኛል፡፡ ለምርጫ ቦርድ የሚያቀርቡት ጥያቄ፣ ምርጫ ላይ በመሳተፍ የዴሞክራሲ እውቀት ለማግኘት የሚያቀርቡት ሃሳብ ራሱ በጣም ደስ ይላል፡፡ ባለፈው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጥያቄ ነው የስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት እዛው ክልል በመሄድ የሰጠነው፡፡ የእነሱ የስራ ቋንቋ አማርኛ ነው ፡፡ እኛ በአምስት ቋንቋ ነው የሰጠነው፡፡

የተጠቀምነውም አገር በቀል ብቻ አይደለም ፡፡ ሱዳን ጠረፍ ያለን እንደመሆናችን አረብኛ ቋንቋ ነው የምንሰማው ስለዚህ በደንብ እንዲገባንና እንድንሰማው በአረብኛ ቋንቋ ይሰጠን ብለው በአረብኛ ቋንቋ ነው ትምህርቱን የሰጠናቸው፡፡ በደቡብ ብሄር ብሄረሰብም በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በስድስት የኮሌጅ ቋንቋዎች ነው የሰጠነው፡፡ ክልሎች በጠየቁን መሰረት 32 ቋንቋ ድረስ የተጓዝንበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ የሚያሳየው ለብሄር ብሄረሰቦች ምን ያህል እንደጠቀማቸው፤ እውቀት እንዳገኙበትና ፍላጎታቸው እንደጨመረ ነው፡፡ ለዚህ እገዛ ያደረገው የምርጫና የዴሞክራሲ ጉዳይን፣ ከሲቪክ ማህበራት ሴቶችን፣መምህራን፣ወጣቶችን መርጠን ማስተማራችንና በዚሀ አጋጣሚ ግንዛቤው በህብረተሰቡ ውስጥ መስፋቱ ነው፡፡

ሰላማዊት ውቤ፦ ከሌሎች አገሮች አንፃር የደረስንበት ምርጫ የማስፈፀምና አጠቃላይ የምርጫ ዘመቻዎችን የማስተናገድ የምርጫ ቦርድ አቅም ምን ይመስላል?

ፐሮፌሰር መርጋ ፦ ከሌሎች በርካታ አገሮች በሎጀስቲክ ሻል ያልን ብንሆንም በጣም ደከም ብለን የምንታይበት በሰው ኃይል አሰላለፍ ነው፡፡ የእኛ ምርጫ ከሌሎች ጋር እኩል መታየት አለበት፡፡ ለይተን ሥራ ማስጀመር ነው የሚጠበቅብን፡፡ ክልሎችን በጣም እናጠናክራለን፡፡ ማንኛውም የምርጫ ቁሳቁስ፣ ወረቀት፣ የምርጫ መዝገብ ፣የመራጮች መታወቂያ ካርድ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ሁሉ አዘጋጅተናል፡፡

የመራጮች መዝገብ፣ መታወቂያ ካርድ፣ የመራጮች ድምዕ መስጫ አዘጋጅተናል፡፡ የሰው ኃይል አሰላለፍ ከቀየርን በኋላ ግን በየትኛውም መልኩ ወደ ቴከኖሎጂ ለመግባት መሰረት ጥለናል፡፡በነገራችን ላይ ይሄ ቦርድ ምርጫ ሲመጣ ለምርጫ ብቻ አይደለም የሚሰራው፡፡ ባለ ራዕይ ቦርድ ነው!የቀጣዩ ሃያ፣ ሰላሳ፣ አርባ ዓመት ምርጫ ምን መምሰል አለበት ብሎ በማሰብ የሚሰራ ነው፡፡ ጥሩና ዘመናዊ መስሪያ ቤት ፈጥሮ ለመውጣት የሚሰራ ነው፡፡

ስለዚህ በሚቀጥሉት 15 እና 20 ዓመት ምርጫ ቦርድ ከየትኛውም ተቋም ያልተናነሰ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ቴክኖሎጂ ነው የሚቀረን፡፡ አሁን የቴክኖሎጂውንም ጥናት ጀምረናል፡፡ ከዚህ በኋላ ደረጃውን የጠበቀ ይሆናል፡፡ ጋናዎች በቴክኖሎጂ ይበልጡናል፡፡ ኬንያም ጀምራለች፡፡ የእኛ መሬት አቀማመጡ፣ ስፋቱ፣ የብሄር ብሄረሰቦችን ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ ማክበሩ ላይ ከማንኛውም አገር እንሻላለን፡፡ ምን አልባት ናይጄሪያ ናት የምትበልጠን፡፡ ሎጀስቲክ ላይ ኢትዮጵያ ራሷን የቻለች ናት፡፡ በሰው ኃይላችንም እንዳልኩት ብዙ አሻሽለናል፡ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ አሁን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ ከዚህ አዲስ ቅጥርና ክልሎችን ካጠናከርን በኋላ በሁለት እግራችን ቆመን አስፈላጊውን ሜዳ በመዘርጋት ከማንኛውም አገር የማይተናነስ ምርጫ ማካሄድ ነው ዓላማችን፡፡

ሰላማዊት ውቤ ፦ በ2007 የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማስተናገድ እየተደረገ ካለው እንቅስቃሴ በተጓዳኝ አንዳንድ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማሉና መነሻቸው ምንድን ነው? የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትስ ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር መርጋ ፦ይሄ ጥያቄ በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የለውም፡፡ የሰለቸንም ነው፡፡ ግን አንዳንድ ፓርቲዎች አይደሉም፡፡ አንድ ፓርቲ ነው ይሄን የሚያቀርበው፡፡ እሱም ፓርቲ ማርሹን እንደየወቅቱና እንደ ፍላጎቱ የሚቀያይር ነው፡፡ ሲበዛ ሁለት ይሆናል፡፡ ከሁለት በልጦ አያውቅም፡፡ ቦርዱ በአለፈው የጊዜ ሰሌዳ ለፓርቲዎች ሲያቀርብ ነበር፡፡ ለሀገር አቀፍ እዚህ አዲስ አበባ፣ ለክልሎች ደግሞ አዳማና ሃዋሳ ከተማ አዘጋጅተን ነበር፡፡ ሁሉም አላነሱም፡፡ አንድ ፓርቲ ረግጦ ሄዷል፤ እሱ እንኳን አላነሳም ፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች በቦርዱ ገለልተኝነት ያምናሉ፡፡ ከላይ ገለልተኞች ናችሁ፤ ታች ምርጫ አስፈፃሚዎችን አስተካክሉልን? ብለው ልናስተካክል ቃል ገብተንላቸዋል፡፡ ተቃዋሚዎች «ገዥውም ፓርቲ በጣም ያስቸግረናል፤ እነእገሌ፤ እነእገሌ እያለ ይከሳል» ይላሉ፡፡ ቦርዱ ደግሞ መረጃ አምጡ!ያለመረጃ የሚሆን የለም ብሎ ይመልሳል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርሳቸው ይወነጃጀላሉ እንጂ ሦስቱም ቦታ አንድም ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም ብለው አላነሱም፡፡ በአመለካከት ከታሰረ እንጂ በወንጀል ከታሰረ ለማስፈታት ቃል አንገባም፡፡ በአመለካከቱ የታሰረ ከሆነ መቼ ታሰረ አምጡ ያገባናል እንላለን፡፡ በወንጀል የታሰረ ከሆነ ግን በወንጀል ህግ እንጂ በምርጫ ቦርድ ህግ አይዳኝም፡፡ ምክንያቱም ቦርዱ በምርጫ ህግ ነው የሚመራው፡፡ ወንጀለኞችን አንከታተልም፤ አያገባንም። ከዚህ ውጪ ዝም ብለው እንደመጣላቸው የሚለጥፉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ቅድም ያልኳቸው ሁለት ፓርቲዎች ሙሉ አይደሉም በፓርቲዎቸ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን ማለቴ ነው፡፡ ይሄን አጠቃልዬ መናገር ይከብደኛል፡፡

በቦርዱ ገለልተኝነት ላይ የሚነሱት ጥያቄዎች የግለሰቦች ጥያቄዎች ናቸው። እንዲህ የሚሉ ግለሰቦች ደግሞ ሁልጊዜም አይጠፉም፡፡ ከዚህ ባሻገር ገለልተኛ አይደለም የሚል ካለ ገለልተኛ ያልሆንበትን ምክንያት ያምጣ። ምን አድርገን ነው ገለልተኛ ያልሆነው?

እኛ ለ75 ፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅና ሰጥተናል፡፡ የ75ቱም ፓርቲዎች አባት ነን፡፡ በአባታዊ አገልግሎት ሜዳ ስናመቻች፤ የአቅም ግንባታ ስልጠና ስንሰጥ፤ የጋራ ምክክር ስናደርግ ሁሉንም እኩል ነው የምንጠራቸው፡፡ የመንግስት ገንዘብ አስፈቅደን የምናከፋፍለው ፍትሃዊ በሆነ ቀመር ከእነሱ ጋር ተወያይተን ነው፡፡ የአየር ሰዓትም እንደዛው ከእነሱ ጋር ሳንነጋገር የምናደርገው የለም፡፡ ስለዚህ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም የሚል ፓርቲ አይደለም ግለሰብ ካለ የት ቦታ ነው ? ያምጣና መልስ እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ውጪ ተቀባይነት የሌለውን ጥያቄ አጠቃላይ ባናደርገው ይሻላል።

ሰላማዊት ውቤ፡- የምርጫ ዝግጅቱ ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር መርጋ ፦ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ዓመቱን ሙሉ ዝግጅት ላይ ነን፡፡ የቅድመ ምርጫ ምዕራፍ፤ የአቅም ግንባታ ስልጠና ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከህግ ባለሙያዎች፣ ከዳኞች፣ ከአቃቤ ህግ፣ ከፖሊሶች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጠንካራ ውይይት አድርገናል፡፡

በተለይ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከሴቶች፣ ከመምህራን፣ ጠንካራ ግንኙነት ፈጥረናል፡፡ እነሱ ዕቅዱን ወደ ወረዳ ለማውረድ እኛ ልንደግፋቸው ቃል ተገባብተናል፡፡ እንቀጥልበታለን። ባጆች በጊዜ አዘጋጅተን በወቅቱ እየሰራንበት ነው፡፡ በሎጀስቲክ ብዙ ርቀት ሄደናል፡፡ የመራጮች መዝገብ በመላ አገሪቱ አልቋል፡፡ አሁን በየክልሉ በካርቱን እየተሸነሸነ ይገኛል፡፡ የመራጮች ካርድ ከኦሮሚያ ክልል በቀር የሁሉም አልቋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ህትመቱ አሁንም እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የፖስተር ህትመቱ አልቋል፡፡ የምርጫ (ሳጥን) ኮሮጆ 52 ሺህ ተዘጋጅቷል፡፡ የወረቀት ችግር የለብንም፡፡ ለእጩዎች ምዝገባ ማሽኖቻችን ተፈትሸው ስራ እየሰሩ ነው፡፡ በአጠቃላይ በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡

ሰላማዊት ውቤ፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት አጠቃቀም፣ ድልድልና የስልጠና ፕሮግራማችሁ ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር መርጋ፦ ስልጠናን በተመለከተ ባለፈው በ2006 ዓ.ም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ዘጠኝ ጊዜ ስልጠና ሰጥተናል፡፡ ከፋፍለን ነው የምንሰራው፡፡ ይህን በፕሮግራማችን መሰረት አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ የገንዘብም ሆነ የአየር ሰዓት ድልድል የምናከፋፍልበት ባለፈው ጊዜ የነበረ ቀመር አለ፡፡ ቀመሩ ባለፈው ጊዜ ጥሩ ጠቀሜታ አስገኝቷል። ስለዚህ ይቀጥል ወይም አዲስ ቀመር ይዘጋጅ የሚለውን መጀመሪያ ቦርዱ ይወስናል፡፡ ነገር ግን አዲስም ሆነ ነባር የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ሳይወያይ ወደ ሥራ አይገባም፡፡

ስለዚህ በሰዓቱም ይሁን በገንዘብ አከፋፈሉ አሁን የቦርዱ ውሳኔ ይሄን ይመስላል የምንልበት ሁኔታ ባይኖርም በእርግጠኝነት ቀመር እንደሚዘጋጅለት ነው መናገር የምችለው፡፡ ቀመሩ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ይቀርባል፡፡ የእነሱ አስተያየት ይወሰዳል፡፡ ከዛ በኋላ ቦርዱ አጽድቆ ተግባራዊ ያደርጋል።

ሰላማዊት ውቤ፦በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል ፓርቲዎች አሉ?

ፕሮፌሰር መርጋ፦ 75 አሉ፡፡ ነገር ግን የህግ ጉዳይ ያላሟሉና ስልጣንን ሞኖፖላይዝ ያደረጉ እንዲሁም ራሳቸው ባወጡት ደንብ መሰረት ለ18 ዓመታት ጠቅላላ ጉባኤ ያልጠሩ አንዳንድ ፓርቲዎች ይገኙበታል፡፡ ለዴሞክራሲው ስንል በሆደ ሰፊነት ነው የምንይዛቸው፡፡ ቦርዱ ደንብ አያወጣላቸውም፡፡ በደንባቸው መሰረት ነው የሚገዙት እንጂ ቦርዱ ደንብ አይቀይርላቸውም፡፡ አንዴ እነሱ በዚህ እንገዛለን ብለው ደንብ አውጥተው ካመጡ ደንቡን መሰረት በማድረግ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ከህግ ይወጣል አይወጣም የሚለውን በህግ ባለሙያዎቻችን ካጠናን በኋላ በቦርዱ እውቅና ያገኛል፡፡ ከዛ በኋላ በዚህ ትገዛላችሁ ነው የምንለው፡፡ በተለይ ለረጅም ዓመታት ጠቅላላ ጉባኤ ያልጠሩትን ከዚህ ከ2007 ምርጫ በኋላ ነው በደንብ የምናያቸው፡፡ አሁን ምርጫ ስለሆነ በሆደ ሰፊነት እንይዛቸዋለን ብለን እንገምታለን፡፡

ከ75ቱ ፓርቲዎች በተለያየ ደረጃ ማለትም 52ቱ በክልል 23ቱ ደግሞ በአገር አቀፍ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እንግዲህ እነኝህ ሁሉ ባለ መብት ናቸው፡፡ ሜዳውን የምናመቻቸው ለ75ቱም እኩል ገብታችሁ ሩጡ፤ ብቁ ተወዳዳሪ ሆናችሁ ቅረቡ ብለን ነው፡፡ ብዙዎቹ እንደሚሳተፉም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ የምናመቻቸው ሜዳ ለዚህ ፓርቲ ለዚያ ፓርቲ ብለን ሳይሆን ለ75ቱም ነው፡፡

ሰላማዊት ውቤ፦ ከምርጫ ስነ ምግባር ጋር ተያይዞ ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር መርጋ፦ የምርጫ ስነ ምግባር ህጉ በጣም አሳታፊ ነው የሚያደርጋቸው፡፡ የምርጫ ህጉ ብቻ አይደለም ያለው፤ ህገ መንግስቱ የወለዳቸው እና የምርጫ ህጉ ተሻሽሎና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በደንብ ጨብጦ የወጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ራሱ ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡ ብዙ ፓርቲዎች የበዙት በዛ ነው፡፡ የመደራጀት መብት አላቸው፡፡ ህጉን መሰረት አድርጎ መቅረብ ነው፡፡ የስነ ምግባር አዋጅ (ኮድ ኦፍ ኮንዳክት) አለ። ይህ ራሱ ህግ ነው፡፡ ህግ ስለሆነ በዛ ይገዛሉ፡፡

የስነ ምግባር ኮድ ለብቻ ፓርቲዎች አላቸው፡፡ በስነ ምግባር ላይ የፈረሙና ያልፈረሙ አሉ፡፡የፈረሙት በጋራ ምክር ቤታቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ያያሉ። የፖለቲካ ፓርቲ እዚህ ቦታ ላይ እንዲህ ተበደልኩ እንዲህ ሆንኩ ካለ ተወያይተው የጋራ አጣሪ ኮሚቴ ይፈጥራሉ፡፡ የጋራ ውይይት በማድረግም የጋራ መፍትሄ ይሰጣሉ፡፡ ይሄ ነው ልዩነቱ ፡፡ ያልፈረሙት እዛ ውስጥ የሉም፡፡ የጋራ ምክር ቤቶች ባለፈው እንዳነሱት እስከ ታች መውረድ አለባቸው፡፡ ይሄ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ነው፡፡ ከእኛ ጋር የጋራ ምክክር መድረክ ነው ያላቸው፡፡

ስለዚህ እኛ በራሳችን ለምሳሌ የቢሮ ችግር ያጋጠመው ከሆነ፣ ደጋፊዎቹን ሰብስቦ ለማወያየት አዳራሽ ቢያስፈልገው፤ ችግር ቢያጋጥመው እንገባለን፡፡ የእኔ አባል በአመለካከቱ ታሰረ ካለ ይመለከተናል፡፡ የት ቦታና መቼ ታሰረ ? የትኛው ክልል ነውስ? ብለን መፍትሄ እናመጣለን፡፡ የክልል መስተዳድር አካላት ጠርተን ፓርቲዎች ይሄን ቅሬታ አቅርበዋል፤ ይሄኛው ችግር መፈታት አለበት እንላለን። በ2006 ዓ.ም ከእነሱ ጋር ሁለት ጊዜ ውይይት አድርገናል፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቹ እዚህ ቦታ እንዲህ ሆኛለሁ አይሉም፡፡ ላሉት ወዲያው መልሱን ሰጥተናል፡፡ በዚህ በኩል በቂ ውይይት አድርገናል፤ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥረናል ማለት እንችላለን፡፡ አሁንም ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር እንቀጥልበታለን፡፡

***********

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን፣ ሕዳር 5-2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories