የኢህአዴግ ም/ቤት መደበኛ ስብሰባ ተጀመረ

የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ጷጉሜ 03 ቀን 2006 ዓ.ም ጀመረ፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና ከ2006 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ጋር በማያያዝ የመንግስትና የድርጅት ሁኔታን መገምገም ጀምሯል፡፡

ምክር ቤቱ በግምገማው ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጥ በማምጣት ረገድ የተደረሰበትን ደረጃ በዝርዝር መመልከት መጀመሩን የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለኢትተጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን በልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመቀየር ሂደት ውስጥ በታዩ ጥንካሬዎችና ድክመቶች ላይም ረትኩረት ሰጥቶ መገምገም መጀመሩን በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

በዚህ ረገድ ባለፉት 13 ዓመታት የተከናወኑ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ተግባራትን ተከትሎ የልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ደረጃ በደረጃ እየጎለበተ የመጣ ቢሆንም ከሚፈለገው ፍጥነት አኳያ ብዙ የሚቀረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየደረጃው የሚገኘው አመራር በተለይም ከፍተኛ አመራሩ የነበረውን ሚና ምክር ቤቱ በዝርዝር መመልከት መጀመሩን ነው በመግለጫው የተብራራው፡፡

የኢህአዴግ ምክር ቤት ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት ረገድ ባለፉት አራት ዓመታት የተፈጸሙ ተግባራትን በመገምገም የርብርብ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ አንዱ መሆኑ መግለጫው አመልክቷል፡፡

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ ሁሉንም የልማት አቅሞች አንቀሳቅሶ በመምራት የልማት ሠራዊት በመገንባት ረገድ የተገኙ ስኬቶችና እጥረቶችን ለመለየትና በሌሎች ጉዳዮች ላይም ግምገማውን ቀጥሏል ብሏል መግለጫው፡፡

የምክር ቤቱ ስብሰባ በነገው ዕለትም እንደሚቀጥል የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከላከው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡

********
ምንጭ፡-
ኢቢሲ፣ ጳጉሜን 3/2006.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories