ከአዲሱ የቡና ግብይት ጥራትና ቁጥጥር አዋጅ ማሻሻያዎች በጥቂቱ

(ስንታየሁ ግርማ)

የኢፌዴሪ መንግስት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ኢትዮጵያን በቡና ኤክስፖርት ከአለም ሁለተኛ ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በ2017 ዓ.ም በዘመናዊ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ያደገ ኢኮኖሚ ከድህነት የተላቀቀ ህብረተሰብ ተፈጥሮ ማየትን ራዕዩ አድርጎ የሰነቀው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን በደንብ ቁጥር 364/2008 ተቋቁሞ ወደስራ ገብቷል፡፡

ባለስልጣን መ/ቤቱ በ2009 በጀት ዓመት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የቡና ግብይት ጥራትና ቁጥጥር አዋጅ ረቂቅ በማዘጋጀት ማሻሻያ ከተደረገበት በኃላ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፀድቋል፡፡

መንግስት ለቡና ምርትና ምርታማነት ማደግ እና የግብይት ስርዓት መቀላጠፍ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ደግሞ 20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ህይወታቸው የተመሰረተው በቡና ላይ ነው፡፡ ከኤክስፖርት ውስጥም 26 በመቶ ይሸፍናል፡፡ ቡናችንም ‹‹ጥቁር ወርቅ›› የሚል አለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል፡፡

ምንም እንኳን ኤክስፖርት በመጠንም በገቢም በየጊዜው በአብዛኛው እያደገ ቢመጣም ያለን እምቅ አቅምና የምናገኘው ጥቅም አይመጣጠንም፡፡ የማእከላዊ ስታትስቲክስ የ2007 ዓ.ም መረጃ እንደሚያመለክተው የአገራችን የቡና ምርታማነት 7.48 ኩንታል በሄክታር ሲሆን ይህ ምርታማነት ከሌሎች ከፍተኛ ቡና አምራች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ የብራዚል ከእኛ በእጥፍ ያህል በልጦ 15.6 ሲደርስ የኮሎምቢያ 12 ኩንታል በሄክታር እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በግብይት ዘርፉም የሚታዩ ማነቆዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ የቡና የውጪ ንግድ አዝማሚያ ከባለድርሻ አካላት የተለያዩ ምክክሮችና ግምገማዎች ከተካሄዱ በኃላ የሚከተሉት ችግሮች ተለይተዋል፡-

* የቡና ግብይት እሴት በማይጨምር ሰንሰለት መራዘሙ

* የቡና ዋጋ የተረጋጋና ተገማች መሆን አለመቻል፣

* ወደውጪ በሚላከው ቡና ተመጣጣኝ ገቢ አለማግኘት፣

* የአምራች ላኪዎች የኤክስፖርት ድርሻ ዘገምተኛ መሆኑ፣

* የግብይትና የሎጂስቲክ ችግሮች ከፍተኛ መሆናቸው፣

* የቡና ጥራት ችግር እየተባባሰ መምጣት፣

* አለም አቀፍ ተወዳዳኒነት የሚያረጋግጥ አደረጃጀት አለመኖሩ ይገኙበታል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አሰራር እና አደረጃጀት በአዋጁ ውስጥ ተካቷል፡፡ እሴት የማይጨምር ረዥም የቡና ግብይት ሰንሰለትን ለመቀነስ የቡና ግብይት በማጠቢያና በመቀሸሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲካሄድ በመፍቀድ፣ ማጠቢያና መቀሸሪያ ኢንዱስትሪዎች በሌሉበት ወይም በርቀት ባሉበት ወይም በከተማ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ አማካይ የሆነ ቦታ ተወስኖ ግብይቱ እንዲካሄድ በማድረግ፣ ከወረዳ ጀምሮ የነበረውን አላስፈላጊ ቁጥጥር፣ ከሚፈለገው በላይ ናሙና የመውሰድና ሌሎች ጊዜና ወጪ አባካኝ ሂደቶችን በማሳጠር፣ ለአርሶ አደሩ በየምርት ዘመኑ በየአካባቢው በመንግስትና በግል ዘርፍ በጋራ እየተጠና የዝቅተኛ መነሻ የመሸጫ ዋጋ ዋስትና በመስጠት፣ የቡና የጥራት ደረጃ ከወጣ በኃላ በ3 ቀናት ጊዜ ውስጥ በመኪና ላይ እያለ እንዲሸጥ በማድረግ፣ የአገናኝ አባል አገልግሎት ግዴታ ሳይሆን አማራጭ በማድረግ ለተጠቀሰው የተንዛዛ የግብይት ሰንሰለት አዲሱ አዋጅ መፍትሄ ይሰጣል፡፡

አዋጁ የቡና ጥራትን ለማሻሻል የልማትና የግብይት አማራጭ ስርአቶችን በመፍጠር ገበያው ለጥራት ልዩነት ያለውና አበረታች የሆነ ዋጋ እንዲሰጥ የሚያበረታቱ የመፍትሄ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን ይቀይሳል፡፡ የልዩ ቡና ሰርተፊኬሽን አሰራር በመፍጠር፣ የአቅርቦትም ሆነ የኤክስፖርት ቡና ለሚያዘጋጁ፣ ለሚያቀርቡና ለሚልኩ አካላት አስፈላጊውን ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር በመስጠት እና የሀገሪቱን የቡና ጥራት ደረጃ አክብረው እንዲሰሩ በማድረግ አዋጁ ከቡና ጥራት ጋር ለተያያዙ ማነቆዎች መሰረታዊ መፍትሄ ይሰጣል፡፡

የቡና ዋጋ ተገማችና የተረጋጋ አለመሆንን በተመለከተ የቡና ግብይት የሚጠይቀውን ብቃትና ስነ-ምግባር አክብረው የሚሰሩ አቅራቢዎችንና ላኪዎችን በመስፈርት በመለየት፣ በመደገፍና ግዴታቸውን በማመልከት፣ ከብሄራዊ ባንክ ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር፣ አቅም ያላቸውን አቅራቢዎች ወደ ላኪነት እንዲሸጋገሩ እድል ይሰጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አቅራቢዎች ከላኪዎች ጋር በትስስር እንዲሰሩ በመፍቀድና አልሚ ባለሃብቶች ከአርሶ አደሮች ጋር በትስስር እንዲሰሩ በማድረግ መሰረታዊ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በላክነው ቡና መጠን ተመጣጣኝ ገቢ አለማግኘታችንን እና የግብይት ሥርዓታችን የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ገበያዎችን ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉን በተመለከተ አምራቾች ከግብይት ተዋንያን ጋር ተሳስረው ዱካው የታወቀ፣ ጥራት ያለውና ቀጣይነቱ የተረጋገጠ ልዩ ቡና እንዲያመርቱና እንዲያዘጋጁ በማድረግ፣ በሴቶች አምራችነት፣ አቅራቢነትና ላኪነት ወይም እሴት ጭመራ በትስስር የተመረተ ቡና የተሻለ ዋጋ ከፍለው መግዛት ለሚፈልጉ ገበያዎች ማቅረብ እንዲቻል በማድረግ እንዲሁም የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ገበያዎችን ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ የሰርተፍኬሽንና የፕሮሞሽን ስራዎችን ለመስራት የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀቶችን አዋጁ በማካተቱ ሃገሪቱ ከቡና የምታገኘውን የውጪ ምንዛሬ ከፍ ማድረግ ያስችላል፡፡

የተንዛዛ የቁጥጥር ስርዓትን በማስቀረት የአልሚ ላኪዎች ቡና በየቦታው ሳይቆም ከወረዳ ቀጥታ ኤክስፖርት ማዘጋጃ እንዲደርስና አንድ ጊዜ ብቻ የጥራት ምርመራና ቁጥጥር እንዲደረግበት በመደንገግ፣ አልሚ ባለሀብቶች በዙሪያቸው ካሉ አርሶ አደሮች ጋር የልማትና ግብይት ትስሰር (Out Grower Scheme) እንዲፈጥሩ የሚያስችል የህግ ድንጋጌዎችን በማካተት፣ አስቀድሞ የተጠቀሱት ሁለቱ አካላት ምርታማነታቸውን በማሳደግ ከፍተኛ መጠንና ጥራት ያለው ቡና በቀጥታ ወደ ውጪ በመላክ የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል የቡና አልሚ ላኪዎችን የኤክስፖርት ድርሻ ማሳደግ ያስችላል- አዋጁ፡፡

አዲሱ አዋጅ እሴት ጭመራን ከማበረታታት አንፃር ማሻሻያዎችን አካቷል፡፡ በቡና ላይ እሴት ጨምረው ወደ ውጭ ለሚልኩ ኢንዱስትሪዎች የኤክስፖርት ደረጃ ያለው ቡና ከምርት ገበያው፣ ከህብረት ስራ ማህበራት፣ ከአልሚ ባለሀብቶች ወይም አርሶ አደሮች በትስስር መንገድ እንዲገዙ በአዋጁ ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም በቡና እሴት ጭመራ ላይ የተሰማሩ አካላት ተወዳዳሪነታቸው ከፍ እንዲልና የተሻለ የውጪ ምንዛሬ እንዲገኝ የመፍትሄ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡ በሃገር ውስጥ የኤክስፖርት ደረጃ ያለው እሴት የተጨመረበት ቡና በውጪ ምንዛሪ የሚሸጡባቸውን የገበያ አሰራሮችን በመፍጠር የቡናችንን ጥራትና ተፈጥሮአዊ ጣዕም ማስተዋወቂያ አዲስ መንገድ አመቻችቷል፡፡

በቡናው ዘርፍ ያሉ የግብዓትና የሎጂስቲክ ችግሮች በአዲሱ አዋጅ እልባት እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ቡና የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ መስፈርት ማሟላት የሚኖርባቸው ሲሆን የብቃት መስፈርቱን የሚያሟሉት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ አዋጁ ደንግጓል፡፡ የቡና የጭነት ዋጋ ህጉን ለማስፈጸም በሚወጡ ሌሎች መመሪያዎች በቁርጥ ዋጋ ስሌት የሚመራበት አሰራር እንደሚወሰን፣ የመኪና ዱካ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ የደላላ ጣልቃ ገብነት አማራጭ እንጂ አስገዳጅ አለመሆኑም በአዋጁ የተደነገገ ሌላው ማሻሻያ ነው፡፡

በቀደመው ህግ ውስጥ የተጠቀሱት ከጨረታ ማዕከላት ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎች በአዲሱ አዋጅ አደረጃጀቶች እንዲተኩ ተደርገው ተሻሽለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሚኒስትር መስሪያ ቤት ጋር የተያያዙ ስልጣናትና ሃላፊነቶች በዚህ ህግ ወደ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል፡፡

በዚህ አዋጅ ያልተካተቱ ከተለዩት ችግሮች ጋር የሚያያዙ ሌሎች የመፍትሄ ሃሳቦችና አሰራሮች በተጓዳኝነት በተያዙት በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ማቋቋሚያ ማሻሻያ ደንብ፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማሻሻያዎችና ሌሎች የዘርፉ አስፈጻሚ አካላት በሚፈጽሟቸው የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ ይካተታሉ ፡፡

ከላይ ከተጠቃቀሱት ነጥቦች አንፃር ሲታይ አዲሱ የቡና ግብይት፣ ጥራትና ቁጥጥር አዋጅ የቡናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚካሄደውን ትግል በድል ለማጠናቀቅ እንደሚያግዝ እምነት ተጥሎበታል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ፣ አቅራቢው፣ ላኪው፣ እሴት ጭመራው ላይ የተሰማራው ባለሃብት፣ አስፈፃሚው አካልና ሌሎችም በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

አዲሱ አዋጅ በክልል ደረጃ ስልጣን የተሰጠው የቡና ጥራት ተቆጣጣሪ በመጀመሪያ ደረጃ ወይም በሌሎች የግብይት አማራጮች የሚካሄደውን የእሸትና የጀንፈል ቡና ግብይት በጥራት ላይ ተመስርቶ መፈጸሙን ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርግ ስልጣንና ሃላፊነት ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ተቆጣጣሪ አካሉ የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን፣ በተፈቀደ የቴክኒክ አሰራር ቡና ስለማዘጋጀቱ፣ እንዲሁም ስለቡና አያያዝና አከመቻቸት ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡

አምራቾችና በሌሎች የግብይት አማራጮች ህጋዊ ትስስር የፈጠሩ ተዋንያን ቡናቸውን በቀጥታ ወደ ኤክስፖርት ማዘጋጃ ማዕከላት እንዲያጓጉዙ አዲሱ አዋጅ ይፈቅዳል፡፡ ይህም ከወረዳ ጀምሮ የነበረውን አላስፈላጊ ቁጥጥር፣ ከሚፈለገው በላይ ናሙና የመውሰድና ሌሎች ጊዜና ወጪ አባካኝ ሂደቶችን በማስቀረት የዘርፉን ተዋንያን ተወዳዳሪነትን ያሳድጋል፡፡

የቡና ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማዕከል የደረሰውን ቡና ደረጃ አውጥቶና ገበያው የሚፈልገውን መሰረታዊ መረጃ ለግብይት አስፈጻሚ ወይም በተለየ የግብይት አማራጭ የተፈጸመ ከሆነም ለገዥና ሻጭ የሚልክ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለሃገር ውስጥና ለውጪ ሃገር በተሰጡ የቡና ደረጃዎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደሶስተኛ ወገን ሆኖ የመዳኘት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም ቅሬታ አቅራቢዎች ከደረጃ አመዳደብ ጋር በተያያዘ ለሚያነሷቸው ቅሬታዎች የተሻለ መፍትሄ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ በሌላም በኩል የቡና ጥራት ምርመራ አገልግሎት እንዳስፈላጊነቱ እየታየ ከምርት ገበያ በተጨማሪ ሌሎች አካላት እንዲሰጡ ባለስልጣን መ/ቤቱ መፍቀድ የሚችልበትን የህግ ማእቀፍ አዲሱ አዋጅ አካቷል፡፡

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አምራቾች ከአቅራቢና ላኪ በተጨማሪ ከኤክስፖርት ቡና ቆዪና ከአልሚ ባለሃብቶች ጋር የቡና ሽያጮችን እንዲያከናውኑ ተፈቅዷል፡፡ ይህም ቡና አምራች አርሶ አደሮች ከአልሚ ባለሃብቶች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠርና በሌሎች የግብይት አማራጮች ለኤክስፖርት ቡና ቆይ በመሸጥ ለቡናቸው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ቡና ቆልተውና ፈጭተው ለውጪ ንግድ የሚያቀርቡ ላኪዎች ዱካዉ የታወቀ እና ጥራቱን የጠበቀ ቡና በተሻለ ዋጋ እንዲገዙ በማስቻል በቡና እሴት ጭመራ ሂደት ላይ ሲነሳ የነበረውን የተሻለ ቡና የማግኘት ችግር ያስቀራል፡፡

የቡና ግብይትን በሌሎች የግብይት አማራጮች መፈጸም እንደሚቻል በምርት ገብያው የአገናኝ አባላት አገልግሎት አስገዳጅነትን በማስቀረትና አሉታዊ ተጽዕኖውን በመቀነስ አቅም ያላቸው ነባርና አዲስ ላኪዎችና አቅራቢዎች በራሳቸው እንዲገበያዩና እንዲተሳሰሩ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የአቅርቦት ቡና ሳይራገፍ መኪና ላይ ሆኖ እንዲሸጥ የሚፈቅድ ቀልጣፋ፣ ወጪና ጊዜ ቆጣቢ አሰራር በማካተት በመጋዘን አገልግሎት የተፈጠረውን አሉታዊ ተጽዕኖ መቀነስ ያስችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለቤትነትን ገላጭ በሆነ አግባብ ብቻ ቡናን ማቆየት እንዳለባቸው ግዴታ በማስቀመጥ የቡናውን ዱካ ማወቅ እንዲቻል ያደርጋል፡፡

አዲሱ አዋጅ ቡና አልሚ ባለሃብቶች አነስተኛ ይዞታ ካላቸው ቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር የልማትና ግብይት ትስስር በመፍጠር የእሸት ወይም የጀንፈል ቡና ግብይት ማካሄድ እንዲችሉ፣ በመጠን ከፍተኛና ጥራት ያለው ቡና በትስስር አምርተው በቀጥታ ወደ ውጪ በመላክ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ያስችላል፡፡

የኤክስፖርት ደረጃ ያለው እሴት የተጨመረበት ቡና ተፈጥሯዊ ባህሪና ጣዕም ለማስተዋወቅ ሲባል በህግ በሚፈቀደው መሰረት በሀገር ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ብቻ ግብይት እንዲካሄድ በመፍቀድ ገቢ እንዲገኝ ማድረግ ከመቻሉም በላይ የቡናችንን ተፈጥሯዊ ባህሪና ልዩ ጣዕም ማስተዋወቂያ አዲስ አማራጭ ዘርግቷል፡፡

ማንኛዉም ቡና አምራች ወይም አዘጋጅ ወይም ከህጋዊ አካል የገዛ ባለስልጣን መ/ቤቱ ወይም አግባብ ያለው የክልል አካል በሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ መሰረት በዝግጅት ሂደት የሚወጣውን የቡና ገለባ አዘጋጅቶ ለሀገር ውስጥ እና ለወጪ ገበያ እንዲያቀርብ በአዋጁ የግብይት መብት ተሰጥቶታል፡፡

አስገዳጅ ሁኔታዎችን በተመለከተ

የእሸትና ጀንፈል ቡና ግብይት በማዘጋጃና ማበጠሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲከናወንና ኢንዱስትሪዎቹ በሌሉበት ወይም ከአርሶ አደሩ በርቀት በሚሆኑበት ጊዜ ደግሞ በክልል አካላት በሚወሰኑ አማካኝ ቦታዎች ግብይታቸውን እንዲያከናውኑ በግብይት ተሳታፊዎቹ ላይ ግዴታ ተጥሏል፡፡ ይህ ድንጋጌ አርሶ አደሮችና አቅራቢዎች ገበያው እንደሚርቃቸው ባወቁ ህገ-ወጥ ደላሎች ቡናቸው እንዳይሰበሰብ ከማድረጉም በላይ በፍጥነት ወደ ማዘጋጃዎች እንዲደርስ ያደርጋል፡፡

በአምራቹ የተመረተ፣ በልማትና በግብይት ትስስር የተገዛ እና በህብረት ሥራ ማህበራት የተሰበሰበ ቡና በቀጥታ ወደ ኤክስፖርት ማዘጋጃዎች መላክ እንዳለበትና ቡናው ከመዘጋጀቱ በፊት ደረጃ እንዳይሰጥ ያደርጋል፡፡ ይህም ከወረዳ ጀምሮ የነበረውን አላስፈላጊ ቁጥጥር፣ ከሚፈለገው በላይ ናሙና የመውሰድና ሌሎች ጊዜና ወጪ አባካኝ ሂደቶችን በማስቀረት የአምራቾችን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል፡፡

በቡና አልሚ ባለሃብትና አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች መካከል የገበያ ብቻ ሳይሆን የልማትም ትስስር መፈጠሩን በማመልከት አልሚ ባለሃብቱ የኤክስቴንሽን ድጋፍ ለአርሶ አደሮቹ ማድረግ እንዳለበት ደንግጓል፡፡ ከዚህም ሌላ በገበያ ትስስሩ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተፈጠረ ስለሆነና ለአባላቱ የተሻለ ክፍያ ማስገኘት አለበት ተብሎ ስለሚታመን አልሚ ባለሃብቱ ከወቅቱ የገበያ ዋጋ በላይ ለአርሶ አደሮቹ የመክፈል ወይም በውል ስምምነታቸው መሠረት ከሽያጭ በኋላ ትርፍ ለአርሶ አደሮቹ የማከፋፈል ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ እነዚህ ግዴታዎች በአልሚ ባለሃብቱ ላይ ሲጣሉ ከአርሶ አደሮች ጋር የተሳሰረው አልሚ ባለሃብት የተሻለ የገበያና የብድርና እድሎች እንዲሁም ከግብር ጋር የተያያዙ ማበረታቻዎች ማግኘቱ ግምት ውስጥ ገብቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ ህግ ቡና አምራች ያመረተውን ወይም በልማትና ግብይት ትስስር የገዛውን ወይም የሰበሰበውን ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም በሌላ ህጋዊ የግብይት አማራጭ የምርት ዘመኑ ሳያልፍ የመሸጥ ወይም ወደ ውጭ የመላክ ግዴታ ያስቀምጣል፡፡ የቡና ጥራት ጥበቃ ሂደት አምራቹ ያመረተውን ምርት በምርት ዘመኑ ውስጥ በመሸጥና ባለመሸጡም ላይ እንደሚወሰን ህጉ ታሳቢ ያደርጋል፡፡

አስቀድሞ ይሰራበት የነበረው ቀይ እሸት ቡናን በ24 ሰአት ውስጥ ወደ ቡና ማዘጋጃ የማስገባት ግዴታ ወደ 8 ሰአት ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህ አሰራር ቀይ እሸት ቡና በፍጥነት ወደ ማዘጋጃዎች እንዲደርስ በማድረግ የቡና ጥራት በተሻለ ሁኔታ እንዲጠበቅ ያስችላል፡፡ አቅራቢዎች ያዘጋጁትን ቡና በራሳቸዉ የሚልኩበት አማራጭ ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም የምርት ዘመኑ ሳያልፍ የመሸጥ ወይም ወደ ውጭ የሚልኩ ከሆነም አዘጋጅቶ የመላክ ግዴታዎችን ያስቀምጣል፡፡ ይህም አቅም ያላቸው አቅራቢዎችን ወደ ላኪነት በማሳደግ የተሻለ የውጪ ምንዛሬ ያስገኛል፡፡ አዲስ በሚፈቀዱ የግብይት አማራጮች የሚሸጥ ቡና የእርጥበት ይዘት ቁጥጥር አቅራቢዉን የሚመለከት መሆኑን ደንግጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አቅራቢው የዘመኑን የቡና ግብይት ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ስለማጠናቀቁ በክልል ሥልጣን ከተሰጠው አካል የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት ወይም ማሳደስ እንዳለበት በአዋጁ በማስቀመጥ ህገ-ወጥ ግብይትን ለመቀነስ ተሞክሯል፡፡ ቡና ላኪዎች የሽያጭ ዉል ለባለስልጣኑ ያሳውቁበት የነበረው 15 ቀን ወደ 3 ቀን በመቀነሱ ባለስልጣኑ የተሻለ የቁጥጥር ስራዎችን ለመስራትና መረጃን በተሻለ ጊዜ እንዲያገኝ ያስችላል፡፡

የሀገር ውስጥ ቡና ችርቻሮ ነጋዴዎች ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው፣ የሀገር ውስጥ ፍጆታ ቡና ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ጅምላ ነጋዴ ብቻ የመግዛት፣ የወጪ ቡና አለመግዛት ወይም አለማጓጓዝ፣ በችርቻሮ ለመሸጥ ንግድ ፈቃድ በወሰደበት መቸርቸሪያ ሱቅ ወይም ቦታ ብቻ የመሸጥና የቡና ግዢና ሽያጭ መረጃ መያዝና ሲጠየቅ ማሳየትን የሚመለከቱ ግዴታዎች ተካተዋል፡፡

ቡና ቆልቶ ወይም ፈጭቶ ከመሸጥ ጋር የሚያያዙ ተቆልቶ ወይም ተፈጭቶ ወደ ውጭ የሚላከው ቡና እሽግ ላይ የተመረተበት ሀገር፣ የጥራት ይዘት፣ የተመረተበትና የመጠቀሚያ ጊዜ፣ የቡናው ዓይነት እና የንግድ ስያሜን የመግለፅ ግዴታ በአዋጁ ተካቷል፡፡ በተጨማሪም አዋጁ ወደ ውጭ የሚላከው የተቆላ ወይም ተቆልቶ የተፈጨ ቡና እና ማሸጊያው በሀገሪቱ የጥራት ደረጃ መስፈርት እና በቡና ገዥ ኩባንያ ፍላጎት መሠረት የማዘጋጀት ግዴታዎችን ያስቀምጣል፡፡ በዚህም የሃገራችን ቡና ዱካው በሚታወቅበት፣ የጥራት ደረጃው የሚለይበት እንዲሁም ቀጣይነት ባለው መልኩ ለአለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ሃገሪቱ ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጪ ምንዛሬ እንድታገኝ ያስችላል፡፡

ቡናን በምግብነት ወይም በመጠጥነት አዘጋጅቶ የመሸጥ አግልግሎት የሚሰጡ ነጋዴዎች ከህገ-ወጥ ቡና ዝውውርና ግብይት ራሳቸውን እንዲጠብቁና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተገቢውን የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው የሚያሳስቡ ግዴታዎች በአዋጁ ተካተዋል፡፡ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ፍጆታ ቡና ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ጅምላ ነጋዴ ብቻ የመግዛት፣ የወጪ ቡና አለመግዛት ወይም አለማጓጓዝና የቡና ግዢና ሽያጭ መረጃ የመያዝና ሲጠየቅ ማሳየትን የሚመለከቱ ግዴታዎች እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ በዚህም ቡና በምግብነት ወይም በመጠጥነት አዘጋጅቶ የመሸጥ አገልግሎት ሰጪዎች በህገ-ወጥ የቡና ዝውውርና ግብይት መሰማራት አለመሰማራታቸውን መቆጣጠር ይቻላል፡፡

በዚህ ህግ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን በደንብ ቁጥር 364/2008 መቋቋሙን ግምት ውስጥ በማስገባት ይህን የቡና ግብይት፣ ጥራትና ቁጥጥርን ህግ የማስፈጸም ሃላፊነትን ለባለስልጣኑ መስጠት በማስፈለጉ ይህ ድንጋጌ የባለስልጣኑ ስልጣን በሚል ተሻሽሏል፡፡ ለባለስልጣኑ የተሰጠው ሌላው አዲስ ስልጣን ለናሙና ወይም ለንግድ ትርኢት ጉዳዮች ቡና ወደ ውጭ ሀገር እንዲላክ የሚፈቅድ ሲሆን ባለስልጣን መ/ቤቱ ቁጥጥር እንዲያደረግና የነበረውንን ክፍተት እንዲሞላ ስልጣንን የሚሰጥ ነው፡፡

ባለስልጣኑ ወይም አግባብ ያለው የክልል አካል ህገ-ወጥ ቡና ሊገኝበት ይችላል ተብሎ በበቂ ሁኔታ የተጠረጠረ መጋዘን፣ መኖሪያ ቤት፣ የመንግስት ድርጅት፣ ማጓጓዣ ወይም ማንኛውንም ሌላ ቦታ በፍርድ ቤት ትእዛዝ መፈተሸ ይችላል፡፡ በተጨማሪም በህጉ መሰረት አስቸኳይ ሲሆን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የመፈተሽ፣ የማሸግ፣ የማገድ፣ የመያዝ ስልጣኑን በሚፈጽምበት ጊዜ ከፍትህና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር መሆን እንዳለበት በህጉ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የተያዘ ቡናን ህጋዊነትን በተመለከተ የመወሰን ስልጣን የባለስልጣኑና አግባብ ያለው የክልል አካል ብቻ መሆኑን አዋጁ በግልፅ አስቀምጧል፡፡

አዲሱ አዋጅ በቀደመው ህግ ላይ ያልተጠቀሰውን በህገ-ወጥ ቡና ዝውውርና ግብይት ላይ የተባባሪዎች ሚና ላይ ትኩረት በመስጠት ህገ-ወጥ ቡና መሸጥ፣ መግዛት፣ ማከማቸትና ማዘጋጀት፣ መቁላትና መፍጨት፣ ማጓጓዝ፣ ቡናው እንዲሠወር ወይም እንዲበላሽ መተባበር ክልክል መሆኑን ደንግጓል፡፡ የታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ባሉባቸዉ አካባቢዎች በባለስልጣን መ/ቤቱ ወይም አግባብ ባለዉ የክልል አካል ካልተፈቀደ በስተቀር ቀይ እሸት ቡናን ለጀንፈል ቡና ዝግጅት መግዛት በአዋጁ መሰረት ክልክል ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ቀይ እሸት ቡና ጥራቱን ጠብቆ መዘጋጀቱን በማረጋገጥ የሃገሪቱን ከልዩ ቡና የተሻለ ገቢ የማግኘት እድል ያሰፋል፡፡

በቡና ንግድ ላይ የተሰማራ ሰው ስራውን ለማከናወን የማያስችል ከአቅም በላይ የሆነ ችግር የገጠመው ስለመሆኑ አሳማኝ ማስረጃ ካላቀረበ በስተቀር በዉክልና ማሰራት አይችልም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በቡና ንግድ ላይ በዉክልና ለመሰማራት የሚፈልግ ሰው አግባብነት ካለው አካል ፍቃድ ሳይኖረዉ ተወክሎ መሰማራት አይችልም፡፡ ይህ ክልከላ ባለመደንገጉና የህግ ክፍተት በመፈጠሩ ህገ-ወጥ ደላሎችና የመንደር ሰብሳቢዎች ቡና በየመንደሩ እየዞሩ እንዲገዙ እድል ፈጠሮ ነበር፡፡ በሌላም በኩል በውጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ የውክልና አሰራሮች ተፈጥረው ነበር፡፡ በመሆኑም ህጉ እሴት የማይጨምሩ ተዋንያንን ከግብይት ስርዐቱ ከማስወገዱም በላይ የቡና ንግድ ብቃት ማረጋገጫ የማስፈለጉ ጉዳይ ተወካዮችንም እንደሚመለከት ታሳቢ ያደርጋል፡፡

ህጉ ቡናን በማጓጓዝ ሂደት ላይ ከፕሎምፕ መበጠስ፣ ከሸራ መቀደድ፣ ጥራትና አይነት መቀየር፣ መጠን መጨመርና መቀነስ ጋር እንዲሁም ቡናን ከሌላ ነገር ጋር አዳብሎ መያዝ ጋር የሚያተኩሩ አዳዲስ ክልከላዎችን አካቷል፡፡

በተጨማሪም ህጉ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ሃላፊዎችና ሰራተኞች በውስጥ አዋቂ ንግድና በአድሎአዊ ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው የቡና ገበያን እዳያዛቡ ክልከላዎችን ያስቀምጣል፡፡ አዲሱ ህግ በነባሩ ህግ ላይ የነበሩትን የገንዘብ ቅጣቶች በእጥፍ በማሳደግ የቅጣቶቹን አስተማሪነትና ፍትሃዊነት አሳድጓል፡፡ ለገንዘብ ቅጣቱ ማደግ ህገ-ወጥ የቡና ዝውውርና ግብይት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየጨመረ መምጣቱና የህገ-ወጥ ቡና ግብይትን ማዳከም ማስፈለጉ፣ የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት፣ የግብይት ተሳታፊዎች ኢኮኖሚያዊ አቅምና ሌሎች ምክንያቶች ግምት ውስጥ አስገብቷል፡፡

ከዚህም ባለፈ ጥፋቶቹን ድርጅቶች ፈጽመው የተገኙ ሲሆን የእስር ቅጣቱ ወደ ገንዘብ በወንጀል ህጉ መሰረት ተቀይሮ የድርጅት ወንጀል ተሳታፊዎች ከፈጸሙት ወንጀል ጋር የሚመጣጠን ቅጣት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

በቅንጅት በመስራት የቡናችንን ህዳሴ እናረጋግጣለን!

**********

Guest Author

Guest Author

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago