ልማትና ዴሞክራሲ፡ የመለስ ዜናዊ ፍልስፍና- ክፍል-1

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ “ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው” በማለት ለቢቢሲ ሬድዮ በሰጠው አስተያየት ዙሪያ ሁለት ተከታታይ ፅሁፎችን፤ በመጀመሪያ ኃይሌ አስተያየቱን በሰጠበት አግባብ ዙሪያ፣ በመቀጠል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሆነው ነፃነትና ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር ስላለው ቁርኝት በዚሁ ድረገፅ ላይ አውጥቼ ነበር፡፡ በእርግጥ በአስተያየቱ መሰጠቱ፣ ወይም ደግሞ በማህበራዊ ድረገፆች መነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ለእኔ ይኽን ያህል አሳሳቢ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ አሁን ሀገራችን የምትመራበት “የልማታዊ-ዴሞክራሲያዊ መንግስት” መርህ በራሱ በተመሣሣይ እሳቤ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም፣ በጉዳዩ ዙሪያ ተከታታይ ፅሁፎችን በማቅረብ በአንባቢዎች ዘንድ የጠራ ግንዛቤ ለመፍጠር የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ፡፡

የሀገሪቱ የወደፊት የልማት አቅጣጫ፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በተለይ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚ ስለዴሞክራሲ የነበራቸው አመለካከት፣ ምንም እንኳን እንደ አትሌት ኃይሌ ጠርዝ ላይ የወጣ ባይሆንም፣ በተለይ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ስላለው ግንኙነት የተዛባ ግንዛቤና አመለካከት እንደነበራቸው በቂ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን፣ ከተወሰኑ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በስተቀር፣ አብዛኞቹ በመካከለኛ እና ዝቅተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ያሉ የመንግስት አመራሮች “ዴሞክራሲ እና ልማት ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም” ወደሚለው አፅናፍ አዘንብለዋል፡፡ የጠራ ግንዛቤ በመፍጠሩ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት የነበረባቸው የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን (Political elites) የውጪ ሀገር ፀሃፊዎች ስም እየጠቀሱና “ዴሞክራሲ…ልማት….እድገት” በሚል “የቃላት-ስንጠቃ” ከማድረግ የዘለለ አስተዋፅዖ እያበረከቱ አይደለም፡፡

እኔም የፅሁፌን መነሻ ሃሳብ “ልማት ወይም የኢኮኖሚ እድገት ከዴሞክራሲ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው ወይስ የለውም?” በሚለው ጥያቄ በመጀመር በተመሳሳይ የቃላት-ስንጠቃ ውስጥ መግባት አልሻም፡፡ በመሆኑም፣ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ንፅፅሩ በዋናነት በለውጥ ክስተቶች (effects) መካከል ሳይሆን ለለውጡ መነሻ በሆኑ መሰረታዊ ምክንያቶች (fundamental causes) ላይ ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት፣ ንፅፅሩ በልማት/እድገት (Development and/or Economic Growth) እና ዴሞክራሲ (Democracy) መካከል ሳይሆን ለልማትና እድገት መነሻ መሰረት በሆነው “ማህበራዊ ልማት” (Social Development) እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት በሆነው “ነፃነት” (Liberty) መካከል ይሆናል፡፡

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ልማትና እድገት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ላይ የሚስተዋሉ የለውጥ ክስተቶች እንጂ በራሳቸው የለውጥ መነሻ ምክንያቶች አይደሉም፡፡ ልማትና እድገት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ለሚታየው ለውጥና መሻሻል መነሻ ምክንያት መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ “ልማትና እድገት” በአንድ ግዜ በራሳቸው መነሻ ምክንያትና መድረሻ ውጤት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህ፣ የሀገራችን እድገትና ብልፅግና በተሳካ የለውጥ ሂደት የሚመጣ እንጂ በራሱ የለውጥ መነሻ ምክንያት አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ፣ የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ “African Development: Dead Ends and new beignnings” በሚል ርዕስ ጀምረውት በነበረው ጥናታዊ ፅሁፍ ውስጥ፣ ለአንድ ሀገር ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት መነሻ ስለሆነ ማህበራዊ ልማት ጠቃሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በጠ/ሚ መለስ ፅሁፍ “The Neo-Liberal Political Economy and Social Capital” በሚለው የመጀመሪያ ክፍል መደምደሚያ ሃሳብ (Conclusion) ላይ ማህበራዊ ልማት “…ወደ ቁሳዊ ሀብትነት እና ጥቅም ከመቀየራቸው በፊት፣ ልማት እና እድገት በመሰረቱ ማህበራዊ እሴቶች፣ ሕጎች እና ልማዶች ናቸው። …ማህበራዊ ልማት ማለት፣ ለተፋጠነ ልማት እና እድገት አስፈላጊ የሆኑ እሴቶችን፣ ልማዶች እና ደንቦችን መፍጠር እና በሕብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፁ ማድረግ ነው። ስለዚህ፣ ማህበራዊ ልማት የሀገር ልማት እንዱ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ቁልፍ መሳሪያ ነው…” የሚል ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ “ማህበራዊ እሴቶች” የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያበረታቱና በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እምነቶች፣ መርሆች፣ እና መመሪያዎች ሲሆኑ በዋናነት፡- ከፍተኛ የሥራ ፍቅር እና ልማድ፣ ክፍተኛ የሆነ በእራስ የመተማመን መንፈስ፣ እራስ የመቻል፣ በየግዜው እራስን ማሻሻል፣ አዲስ ነገር የመፍጠር ፍላጎት፣ ከሌሎች ለመማር እና ልምድን ለማካፈል ፍቃደኛ መሆን፣ ቁጠባ እና የመሳሰሉትን ናቸው። በመቀጠል፣ ለልማት ምቹ የሆኑ “ማህበራዊ ልማዶች” በሚለው ሥር ለተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ትግል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ የአሰራር እና አመራር ሂደቶች፣ ለምሳሌ፡- እንደ ሰዓት ማክበር፣ በዕቅድ መመራት፣ በአከባቢው ማህብረሰብ ሕጎች መገዛት፣ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር፣ የፀረ-ሙስና ግድታን መወጣት እና ሥነ-መግባር ከጎደለው ተግባር መቆጠብ እና ሌሎች መጥቀስ ይቻላል። በመጨረሻም፣ ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ “ማህበራዊ ደንቦች” በሚለው ሥር የማህብረሰቡ አባላት፣ መንግስት ወይም ሌሎች አካላት፣ ለእድገቱ ተፃራሪ በሆኑ ተግባራት ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚያግዱ እና ማዕቀብ የሚጥሉ ማህበራዊ ሕጎችን ያካትታል፡፡

ስለዚህ፣ በጉዳዩ ላይ የምናደርገው ውይይት እንዲሁ በጥቅሉ “ልማት/እድገት እና ዴሞክረሲ” በሚል ግርፍ እይታ ሳይሆን በመሰረታዊ መነሻ ምክንያቶች ላይ ማዕከል ባደረገ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ፣ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ስለአንድ ሀገር ልማትና እድገት ስናወሳ በዋናነት “እነዚህ ለልማትና እድገት ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች፣ ልማዶችና ደንቦች አሉን ወይ?” በሚለው ላይ መሆን እንዳለበት እሙን ነው፡፡ በቀጣይ ክፍል ከላይ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሰረት ስለሆነው “ነፃነት” እና ከማህበራዊ ልማት ጋር ስላለው ቀጥተኛ ግንኙነት የምዕራብ አውሮፓ እና የሩቅ-ምስራቅ ሀገራት ስልጣኔን እንደ ማሳያ በመውሰድ እንመለከታለን፡፡

ይቀጥላል…
*********

Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago