ትርጉም አልባ ሕዝባዊ ስብሰባዎቻችን | የኢትዮጵያውያን ጓዳ(ክፍል-2)

(ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ)

በሀገራችን እጅግ ከተለመዱና የመንግሥት አካላት ያለ ልዩነት ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውም ኾነ ሕግ ተርጓሚው ዋነኛ ተግባራት መሐከል አንዱና ዋነኛው ስብሰባ ሲኾን በስብሰባም ብዛት የተጥለቀለቁ ናቸው፡፡

ስብሰባ ከመንግሥት አካላት ውጭ በማህበራት፣ በፓርቲዎች፣ በአክሲዮን ማህበሮች – – – ወዘተ የተለመደ ነው፡፡ እንደሀገር ምንም እንኳ የሠለጠነ ኹለንተናዊ የውይይት ባሕል የለንም ብንልም የስብሰባ ብዛት ግን ለቁጥር ያዳግታል፡፡

ሚድያዎቻችን አብዛኛው ዜናቸውና ዶክመንተሪያቸው ስብሰባና ስብሰባን ማዕከል ያደረጉ ስለመኾናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ዜናዎቻችን በስብሰባና ስብሰባ ነክ በኾኑ ነገሮች ላይ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡ የሥልጣን ፖለቲካችን በእጅጉ በስብሰባና በስብሰባ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡

Photo – Collage of various Ethiopian meetings

ስብሰባ የግንኙነቶች ውጤት ነው፡፡ በውስጥም ኾነ በውጭ የርስ በርስ ነጠላም ኾነ የጋራ መስተጋብር ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ተቋማት የሚያደርጉት ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ ማዕከል – መሰባሰብ መደበኛ (formal) አንድ መጠሪያ ነው፡፡ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ በቀጥታ ከተግባሩ ጋር የተሳሰሩ 5 ዐምዶችና በቀጥታ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ነገር ግን ይበልጥ ሳቢና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ድምር መጠሪያ ነው፡፡

የስብሰባ ዐቢይ ዐምዶች ትስስር ምን ይዟል?

በማንኛውም ኹለንተናዊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚዘጋጅ ስብሰባ የአዘጋጅ፣ የይዘት፣ የመጠን፣ የተሳታፊ ብዛት፣ የመቼት (ቦታና ጊዜ) – – – ወዘተ ኹለንተናዊ ልዩነት ቢኖረውም በውስጡ ያለ ልዩነት 5 ዐምዶችን ይይዛል፡፡

እነዚህም፡

የስብሰባ አዘጋጅ

ስብሰባውን ያዘጋጀው ማን ነው? ዋነኛና ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው? በስብሰባው ዝግጅትስ ማን ምን ኃላፊነትና ድርሻ አለው? የሚለውን የሚይዝ ነው፡፡

የስብሰባ ዓላማ

ስብሰባው የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድነው? ምንስ ይጠበቃል? መዘጋጀቱ ለምን አስፈለገ? ለዝግጅቱ መሳካት በቀጥታ ምን ምን ያስፈልጋል? ለስብሰባው በተዘዋዋሪ መሳካት ደጋፊ የኾኑ ተግባራት ምን ምን ናቸው?

የስብሰባ አጀንዳ

ከስብሰባው ጠቅላላና ዝርዝር ዓላማዎች በመነሣት ለነጠላው መድረክ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ምንድናቸው? በምን? ለምን?

የስብሰባ መሪና ተሳታፊ

ስብሰባውን የሚመራው ማነው? በመምራት ሂደት በቀጥታ ከስብሰባው ዓላማና አጀንዳ ጋር ያለው ቀጥተኛ ግንኙነት ምንድነው? በስብሰባው ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ከዓላማው አንጻር ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅቱ ሥራ ምን ይመስላል? ተሳታፊዎች እነማን ናቸው? ለመድረኩ የሚገቡ/የሚመጥኑ ሰዎች ናቸው? በምን? ምንስ ሊያደርጉ ይችላሉ? የመሪዎችና የተሳታፊዎች በነጠላና በጋራ የንቃተ ህሊና ደረጃ ምን ይመስላል?

የስብሰባ ጊዜና ቦታ

ከስብሰባው 4 ዐምዶች በመነሣት ካለ አቅምና ከሚፈለገው አንጻር ስንት ጊዜ የሚወስድ ስብሰባ ነው? የት ነው የሚካሄደው? ቦታው የታሰበውን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ቦታ ላይ ነው የሚካሄደው? ተገቢው ሰዓት ለተገቢው ተግባራት ውሏልን? ብሎ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ አንድን ስብሰባ መጠየቅ ተገቢ እንደኾነ አያጠያይቅም፡፡

በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ እንዲህ አድርጎ እያንዳንዱን ማንኛውንም አይነት ስብሰባ ትርጉም ባለው መንገድ መመልከትና መገምገም ከቅድመ ስብሰባ፣ ከስብሰባና ከስብሰባ በኃላ መጠየቅ አስፈላጊ መኾኑ ከፋይዳ አንጻር የግድ ነው፡፡

ከዐምዶች አንጻር የሚታዩ ችግሮች

ከላይ የተጠቀሱትን ዐምዶች መሰረት አድርገን ከጽንሰ ሀሳብ ባሻገር በተግባር የሀገራችንን የስብሰባዎች አዘገጃጀት በተለይ ብዙ ተሳታፊዎችን የሚይዙ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ስንመለከት፡-

የስብሰባ አዘጋጅ

በበርካታ መድረኮች ላይ እንደምንታዘበው ስብሰባዎች ሲዘጋጁ በአዘጋጁና በባለድርሻ አካላት መሐከል ተቀናጅቶ፣ ተናቦና በመንፈስ ተግባብቶ ተመጋጋቢ ኹለንተናዊ ተግባራትን ከማከናወን አንጻር እጅግ ከፍተኛ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ መርሐ ግብሩ በጋራ የተዘጋጀ ይባልና በጓዳ ግን ፕሮግራሙን  የሚሰሩት ጥቂቶች ይኾናሉ፡፡

መርሐ ግብሩን በባለቤትነት ስሜት እንቅልፍ አጥተው የሚሰሩ ጥቂቶች የሚጠሩበት ግን ብዙዎች፤ የታችኛው ተራ ሰራተኛ ከተሰጠው ኃላፊነት በላይ በጫና ስር ወድቆ እንዲሰራ በማድረግ የላይኛውና መካከለኛው አመራር በጦርነት የድል አጥቢያ ጀብደኞች ጀግኖችን እንደሚውጡት የሚኾንበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ይህንንም ከበርካታ መንግሥታዊ ከኾኑ ተቋማት ጋር የጋራ ሥራ ለመስራት የሚጥር ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድንም ኾነ ተቋም በቀላሉ ሊያረጋግጠው የሚችል ጥሬ ሃቅ ነው፡፡

የስብሰባ ዓላማ

በርካታ የሀገራችን ስብሰባዎች በተለይ ሕዝባዊ ስብሰባዎች የሚዘጋጁበት ዓላማ ትርጉም ባለው መንገድ ከዋና ዓላማ፣ ከዝርዝር ዓላማ፣ ከተልዕኮና ከውጤታማነት የመለኪያ ነጥቦች አንጻር ተቀምጦ የሚሰራባቸው አይደሉም፡፡ እጅግ ከፍተኛ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚወጣባቸው ስብሰባዎች በጥቅሉ “የግንዛቤ ማስጨበጫ”፣ “የንቃተ ህሊና ማዳበሪያ”፣ “የልምድ ተሞክሮ መለዋወጫ”፣ “የመተዋወቂያ” – – – ወዘተ በሚሉ መያዣና መጨበጫ በሌላቸው ድፍን ቃላት የሚገለጹ ተራ የቃላት ፕሮፕጋንዳን ከመያዝ በዘለለ ጥልቀት ባለው መንገድ ታስቦባቸው የሚቀርቡ አይደሉም፡፡

ከዚህ ባሻገር የተግባራት ፋይዳ ከተግባር መንስኤና ውጤት አንጻር ተቀናጅቶ ያለማስቀመጥና በአቅም ግንባታ ግዙፍ ማዕቀፍ ስር ተሸጉጦ የማለፍ ጥረቶች የሚበራከቱበት ከመኾኑም ባሻገር የመዘጋጀቱን ግልጽ ዓላማና ግብ ከዝርዝር የመለኪያ ነጥቦች ጋር አያይዞ የማቅረብ ብሎም ከዋና አዘጋጁና ከተባባሪ ደጋፊ አካላት ጋር የሚኖረውን መስተጋብር ለይቶ የማስቀመጥ ሰፊ ክፍተት አለ፡፡

የስብሰባ አጀንዳ

ከስብሰባው ዋናና ዝርዝር ዓላማዎች በመነሣት አጀንዳዎችን ተመጋጋቢና ወጥነት፤ ጥራትና ጥልቀት ባለው መንገድ የማዘጋጀት ባሕል እጅጉን ዝቅተኛ ነው፡፡ የመድረኩ ዓላማ ተብሎ በሚገለጸውና በሚቀርቡ አጀንዳዎች ዙሪያ ልዩነቶችና ተቃርኖዎች በሰፊው ይስተዋላሉ፡፡

የስብሰባ መሪና ተሳታፊ

ከላይ የተነሱ ነጥቦችን መሠረት በማድረግ ለአጀንዳዎች ከንቃተ ህሊና፣ ከመረዳት፣ ከትምህርት ዝግጁነት፣ ከልምድ፣ ከትስስር እና ከተጋላጭነት አንጻር አግባብነት ያላቸውና በደንብ ጥናት የተደረገባቸው የስብሰባ መሪዎች፣ የአጀንዳ አቅራቢዎችና ተንታኞችን የማቅረብ፣ ተሳታፊዎችን የመለየትና የመጋበዝ ጉዳይ ከኹሉ የከፋው ችግር ኾኖ ይታያል፡፡

ከተሳታፊው እጅግ የወረደና የሚያስተዛዝብ ችሎታ ያለው ሰው ስብሰባ የሚመራበት አጋጣሚ በርካታ፤ ለርዕሰ ጉዳዩ ምንም ግንዛቤ የሌለውና ተጋላጭነቱም እጅግ ውስን የኾነ የሕብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት ስብሰባ በርካታ ነው፡፡ መሪው ከተመሪው ቢያንስ ለዛ ለሚቀርበው ነገር ከፍ ያለ አልያም በቅድመ ዝግጅት የቀደመ መኾን የሚገባው ቢኾንም በብዙ አጋጣሚዎች የተገላቢጦሽ የሚኾንበት ተመሪው መሪውን የሚመራበትና የሚያርምበት ይባስ ብሎ የሚቃወምበትና ከአጀንዳ ውጭ በኾኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚደረግበት ኹኔታ ብዙ ነው፡፡

በዚህም የተነሣ በብዙ ስብሰባዎች ከአጀንዳ ውጭ መውጣት፣ በትላልቅ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ እጅግ በወረዱ በጥቃቅንና አነስተኛ ፈጽሞ ሊነሱ በማይገባቸው ፋይዳ በሌላቸው ግለሰባዊ ጉዳዮች፣ ስሜቶችና አድናቆቶች በርክተው ይታያሉ፡፡

የስብሰባ ጊዜና ቦታ

ብዙ ሀገራዊ፣ ከባቢያዊና ከተማዊ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ሲዘጋጁ ከአስፈላጊውና ለርዕሰ ጉዳዩና ከተሳታፊው አንጻር ታሳቢ ያደረጉ የጊዜና የቦታ መረጣ ክፍተቶች በርካታ ሲኾኑ ከኹሉ የሚከፋው 2፡30 ይጀመራል የተባለ ስብሰባ 3፡45 መጀመር፤ የክብር እንግዳና የመክፈቻ ንግግር የሚያደርግን ለመጠበቅ የሚወሰደው ጊዜ፤ ንግግር አቅራቢዎች ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለው ትርጉም የሌለው የፕሮፕጋንዳ ሥራ ለመስራት የሚያጠፉት ጊዜ፤ ለአጀንዳዎች የሚሰጠው ጊዜ አጀንዳዎቹ ከሚፈልጉት አማካኝ ጊዜ እጅግ ያነሰ መኾን፤ የአቅራቢዎች ዝግጅት ዝቅተኛነትና የሰዓት አጠቃቀም የወረደ መኾን፤ ለተሳታፊዎች እድል ሲሰጥ ከተሳታፊው አንጻር የሚሰጠው ጊዜ ውስን አጠቃቀሙም እጅግ የወረደና ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው እድሉ ስለተገኘ ብቻ የሚባልባቸው – – – ወዘተ እንደኾኑ የሚታወቅ ነው፡፡

ይህ እንደው ከስብሰባው አንጻር ብቻ ያለውን አነሣን እንጂ የአበል፣ የቲሸርትና ኮፍያ ወጪ፣ የበራሪ ወረቀት፣ የመዝናኛ፣ የሻይ ቡና መስተንግዶ፣ የሰዓት አጠቃቀም – – – ወዘተ ጉዳይ እንደው ለመኾኑ ድሃ መኾናችን ገብቶናል? ሁለት ሰዓት ለማይሞላ ተራ የብዙ ሰዎች ስብስብ – ስብሰባ ተብሎ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይወጣል፡፡ እጅግ የወረደ የአንድ ሳምንት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ ወጪው የአንድ የመንግሥት ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ሙሉ ሠራተኛ የዓመት ደሞዝ ወጪ ያክል ይወጣል፡፡

ከስብሰባው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ግን ስብሰባውን የሚያደምቁ ተግባራት ወጪዎች ከቀጥተኛ የስብሰባው ተግባራት ወጪዎች በብዙ እጥፍ ርቀው ሲገኙ አመራሩም ኾነ ተሳታፊው ይህን ቆም ብለው ለማሰብ አለመቻላቸው የኛ ድሃነት ኹለንተናዊነት – በጥልቅና ውስብስብ ኹለንተናዊ የቁስ ብቻ ሳይኾን የሀሳብ ድህነት ውስጥ ያለን ስለመኾናችን ማሳያ ነው፡፡

በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በአቅም ግንባታ ስም ይወጣል፡፡ የድሃ ድሃ ከአለም ሀገራት ዋነኛ የድህነት ተምሳሌት ኾነን ሳለ በስብሰባ ለማስታወሻ ደብተር ወጪ፣ ለስክቢርቶ፣ ለአጀንዳዎች፣ ለባነር፣ ለበራሪ ወረቀት፣ ለመስተንግዶ – – – በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይወጣል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ለፕሮሞሽንና መሰል የስብሰባ ተግባራት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማውጣትን እና ለሪፖርት ብቻ ሲባል በቂ ዝግጅት ሳይደረግባቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ወጪ ለጥቂት ቀናት የወረደና የተዝረከረከ መርሐ ግብር ማውጣትን ከተላመዱት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ስብሰባ ለምን? በምን? ምን ለማግኘት? መለኪያውስ ምንድነው? ብሎ እያንዳንዷን ነገር ከዐምዶቹ አንጻር ይብዛም ይነስም ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴ መለኪያና መገምገሚያ አስቀምጦ ተግባብቶ፣ ተመጋግቦና በመንፈስ አንድ ኾኖ በሀገራዊ ቁጭትና ወኔ የመስራት ይሄ ነው የማይባል ትልቅ ሀገራዊ ችግር አለ፡፡

በአንድ ሀገር ውስጥ ያለን ሥርዓት ጤናማነትና ጤናማ አለመኾን መለያ የስብሰባ ብዛት፣ የስብሰባዎች ጥራትና ፋይዳን በመመልከት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ በመንፈስ ያልተዋሃዱና ውስጣቸው አንድነትና ሕብረት የሌላቸው ገዥዎች እጅጉን ስብሰባ ያበዛሉ፤ ስብሰባቸውም እጅግ ረዥም ጊዜ የሚወስድና ጥራት የሌለው ፋይዳውም ከጥቃቅንና አነስተኛ ሀሳቦች ንትርክና ለውጥ ውጭ በመሰረታዊ ዐበይት ጉዳዮች ላይ የማያተኩር በመሠረቱም አዲስና የላቀ የአስተሳሰብና አመለካከት ለውጥ የማይታይባቸው ይኾናሉ፡፡ ልክ እንደኛ!!!

ለምን በሀገራችን ስብሰባዎች እጅጉን ይበዛሉ? በመንፈስ መግባባት፤ ይህም ሊገለጽበት የሚችል ሳይነጋገሩ የመግባባት፣ ሳይገናኙ በርዕይና ግብ ላይ ተመስርቶ ተናቦ የመስራት፤ በቅንነት ከግለሰቦችና ቡድኖች በላይ ሀሳብ፣ ዕሳቤና አስተምህሮት ላይ ትኩረት አድርጎ የመወያየትና በሀሳብ የበላይነት የማመንና የመቀበል ብሎም በተግባር የመተርጎም ባሕል ያላደበርን በሀሳብ ድህነት በእጅጉ የተጥለቀለቅን በመኾናችን ስለመኾኑ አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

ሌላው በሀገራችን ከስብሰባ ችግሮች ኹሉ ትልቁ ስብሰባን እንደመጨረሻ የመውሰድ፣ ሥራን በስብሰባ ከማከናወን ይልቅ ስብሰባዎችን ሥራቸው – ሥራቸውን ስብሰባ ያደረጉ አካላት በርካታ ናቸው፡፡ በሳምንት በርካታ ስብሰባዎችን በመሰብሰብም ኾነ ሌሎችን በመሰብሰብ የሚያሳልፍ አመራር በርካታ ነው፡፡ ወር ሲደርስ ሄዶ ደሞዝ ይቀበላል፡፡ ምን ሰራህ? ቢባል መሰበሰቡንና ሌሎችን መሰብሰቡን ያስቀምጣል እንጂ አንዳች ይህ ነው የሚባል ትርጉም ያለው ፍሬን አያስቀምጥም፡፡ ዝቅ ሲልም በመሰብሰብና በመሰብሰብ ያገኛቸውን ጥቅማ ጥቅሞች አበልን ጨምሮ አነሰኝ ብሎ ያጉረመርም እንደኾን እንጂ ትርጉም ባለው መንገድ ሥርዓቱም እንደሥርዓት ቁብ አይሰጥም፡፡

ስብሰባዎች በራሳቸው መሣሪያዎች (means) እንጂ በራሳቸው ፈጽሞ ግቦች (Goals) ሊኾኑ አይችሉም፡፡ በስብሰባ መሠረታዊ ለውጥ ፈጽሞ ማምጣት ባይቻልም ለኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ አንድ ትልቅ መሣሪያ መኾኑን ግን መዘንጋት አያሻም፡፡

ይህም ቢኾን ትላንት ከትላንት ወዲያ የስብሰባ ብዛት ብዙ ነበር፡፡ ዛሬም ያው ነው፡፡ ለነገሩ ‘ድሃ ሕዝብ ስብሰባ ያበዛል፡፡ ድሃ ሕዝብ መሰብሰብ ይወዳል፡፡ ብዙ እጅግ ሰፊና ውስብስብ ኹለንተናዊ ችግሮች ያሉበት ሕዝብ ችግሩን የሚረሳው በመሰብሰብ ነው፡፡ የብዙ ታዳጊ ሀገራት ገዢዎች መሰብሰብና መሰብሰብን ዋነኛ ሥራቸው ስለኾነ ስብሰባን ሥራ – ሥራን ስብሰባ በማድረጋቸው ስብሰባ ይቀንስ ማለት እነሱን ሥራ አጥ ማድረግ ነው፡፡ ስብሰባና የስብሰባ ማብዛት ጉዳይ የገዥዎች የሥልጣን ፖለቲካ ሕልውና መጠበቂያ ነው፡፡ ድሃ ሕዝብ ወሬና ከወሬ ጋር የተያያዙ ወጎችን – ታሪኩ ያደርጋልና ብዙ የሚገርም አይደለም፡፡’ (“አብዮታዊት ነፍስ”፡ ገጽ 23) የሚሉ ትንታኔዎች መኖራቸውን ሳንዘነጋ ነው፡፡

ስለኾነም ስብሰባ ለምን? በምን? ምን ለማግኘት? በማን? ብሎ ከስብሰባ 5 ዐምዶች አንጻር ትርጉም ያለው ሥራ ሳይሰራና ቡድናዊ፣ ፓርቲያዊ፣ ከባቢያዊና ሀገራዊ ስብሰባዎች ሥርዓት ሳይዙ መሠረታዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የአ¦ሱም ሃውልት በጊዜ ሂደት ራሱ ይንቀሳቀሳል – መጥቶም ይጎበኘኛል ብሎ እንደሚጠብቅ ሞኝ መኾን ነው፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

************

* ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ – የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ (ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

Guest Author

Guest Author

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago