ጽጋቡ ገ/ማርያም (ወዲ ገሬ) – በቱር ደ ፍራንስ 2017 የብስክሌት ውድድር

(Fthawi Hurui)

በአለማችን ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው የብስክሌት ውድድር ነው። እ.ኤ.አ በ1903 ዓ.ም በፈረንሳይ አገር የተጀመረው እና <<Tour de France>> በሚል መጠርያ ስም በየአመቱ በዋናነት በፈረንሳይ ምድር የሚካሄድ ውድድር ቢሆንም አንዳንድ የአውሮፓ አገራትን ያቆራርጣል። ቱር ደ ፍራንስ ፣ በተለምዶ በየአመቱ ሀምሌ ወር ነው የሚካሄደው። የብስክሌት ውድድሩ ከግዜ ወደ ግዜ ታዋቂነትን እያተረፈና ተፎካካሪነቱን እያሳደገ መጥተዋል።

ይህ ውድድር በመጀመርያው አመት ፉክክር ስድስት እርከን (Stage) ያካተተና 2,428 ኪ.ሜ የሸፈነ ነበር። በዚህ የመጀመርያው ቱር ደ ፍራንስ ውድድር ጣልያን ተወላጁ ሞሪስ ጋሪን የተባለ በዜግነት ፈረንሳዊ የሆነ ብስክሌተኛ አሸናፊ መሆን ችለዋል። ውድድሩ በታሪኩ የተቋረጠው በሁለቱም የአለም ጦርነቶች ግዜ ብቻ ነው።

በዚህ አመታዊ የብስክሌት ውድድር ላይ የአፍሪካውያን ተሳትፎ ምን ይመስላል?

MTN-Qhubeka  የተባለው የደቡብ አፍሪካ ቡድን (ይህ ቡድን በዚህ አመት Dimentsion Data በሚል አዲስ ስም ተሳትፈዋል) እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም በዚህ ውድድር እንዲሳተፍ ከአዘጋጆቹ ጥሪ ሲደረግለት የመጀመርያው ኣፍሪካዊው ቡድን ነኝ ቢልም፣ ከዚህ ግዜ በፊት በዚህ ገናና ውድድር ላይ የተሳተፈ ሌላ የአፍሪካ ቡድን እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።

ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ እ.ኤ.አ በ1950 ዓ.ም ይህ ውድድር ሲካሄድ ከሞሮኮና ከአልጀርያ በተውጣጡ ብስክሌተኞች የተዋቀረ ቡድን ተሳታፊ ነበር። ነገር ግን በዚህ ወቅት ሞሮኮና አልጀርያ የፈረንሳይ ቅኝ-ግዢዎች ስለነበሩ በዚህ ውድድር የተሳተፈው ይሄው ቡድን የፈረንሳይ ግዛት አካል ሆኖ ነው።

ለዚህም ነው ይሄ አፍሪካዊ የብስክሌት ቡድን በታሪክ ተውጦ የቀረው። በዘንድሮው ቱር ደ ፍራንስ ኢትዮጵያዊው ጽጋቡ ገ/ማርያም ጨምሮ አምስት አፍሪካውያን ተሳታፊ ሆነዋል።

ፎቶ – ጽጋቡ ገ/ማርያም (ወዲ ገሬ) – በቱር ደ ፍራንስ 2017

ኢትዮጵያዊው ፋና ወጊ ብስክሌተኛ

ትውልዱ እና እድገቱ በትግራይ ዋና ከተማ መቐለ የሆነው ኢትዮጵያዊው ጽጋቡ ገ/ማርያም (ወዲ ገሬ) የአባቱና እና ታላቅ ወንድሙ ፈለግ ተከትሎ ነው በልጅነቱ ብስክሌት መንዳት የጀመረው። በአገር ውስጥ ትራንስ ኢትዮጵያ የሚባል የብስክሌት ቡድን አባል ሆኖ በትግራይ ክልል በሚካሄዱ የብስክሌት መድረኮች ላይ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ጀመረ።

አሸናፊነቱ በአገር አቀፍ ውድድሮችም እየደገመው መጣ። በዚህም መሰረት ሁለት ግዜ የአገር አቀፍ የጎዳና ላይ የብስክሌት ውድድር እንዲሁም ሁለት ግዜ የአገር አቀፍ ታይም-ትሪያል ሻምፕዮና መሆን ቻለ። ውጤታማነቱ በአህጉር ደረጃ በመቀጠል አንድ ግዜ የአፍሪካ ታይም-ትሪያል አሸናፊ መሆንም ችለዋል።

ጽጋቡ ገ/ማርያም እ.ኤ.አ በ2012 ዓ/ም MTN–Qhubeka ከተባለው የደቡብ አፍሪካ የብስክሌት ቡድን ጋር በመፈረም፣ የመጀመርያው ፕሮፌሽናል ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ ለመሆን በቃ። በአመቱ ከዚህ የደቡብ አፍሪካ የብስክሌት ቡድን ጋር በመሆን በ Tour de Taiwan አምስተኛው እርከን (Stage) ላይ አንደኛ በመውጣት በአለም አቀፍ የብስክሌት ፉክክር በማሸነፍ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ መሆን ቻለ።

በዚህ የ Tour de Taiwan ውድድር በአጠቃላይ ውጤትም ሁለተኛ ሆኖ ጨረሰ። ጽጋቡ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም የጣልያኑ የብስክሌት ቡድን የሆነው Lampre–Merida ተቀላቀለ። ለዚህ የጣልያን የብስክሌት ቡድን መፈረሙ በአለማችን እንቁ የብስክሌት ውድድር የሆነው Tour de France ተሳታፊ እንዲሆን እድል ሊያስገኝለት ችለዋል። እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም በዚህ ውድድር ላይ በመሳተፍ በታሪክ የመጀመርያ ኢትዮጵያዊ በመሆንም ስሙን ያሰፈረ አገራዊ ጀግና ሆነ።

በዚህ በመጀመርያ አመት ተሳትፎው በአጠቃላይ ውጤት 92ኛ ደረጃን ይዞ በመጨረስ የሚያበረታታ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።

ጽጋቡ በቱር ደ ፍራንስ 2017 ተሳትፎው

ጽጋቡ ገ/ማርያም እ.ኤ.አ በ2017 ዓ/ም የቱር ደ ፍራንስ የውድድር አመት Bahrain-Merida የተባለው የባህሬን የብስክሌት ቡድን ወክሎ ነው የተሳተፈው። በዚህ ለሁለተኛ ግዜ በተሳተፈበት የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ያስመዘገበው ውጤት በጣም አበረታች የሚባል ነበር።

የዘንድሮ ቱር ደ ፍራንስ ውድድር ዘጠኝ የሜዳ፣ አምስት ዳገታማ፣ አምስት የተራራ ላይ እና ሁለት የግል ታይም-ትሪያል ያካተተ በሀያ-አንድ እርከን (Stage) ተከፋፍሎ የተካሄደ በጣም ፈታኝ ውድድር ነበር። በዚህ ለሃያ-አንድ ቀን በዘለቀው እጅግ አድካሚ ውድድር ላይ ብስክሌተኞቹ በመሀል ለሁለት ቀን ብቻ እረፍት አድርገዋል። ብስክሌተኞቹ በዚህ መድረክ ላይ በየቀኑ በአማካይ ከሶስት ሰአት በላይ ነድተዋል።

በዚህ ከፍተኛ ብቃት የሚጠይቀው ውድድር ላይ ጽጋቡ ገ/ማርያም በተለይ በሁለት እርከኖች ላይ በጣም አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በአስራ-አምስተኛው እርከን (Stage 15) ፉክክር ላይ ጽጋቡ ገ/ማርያም ሀያ-ሶስተኛ በመውጣት ለአገሩና ለራሱ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችለዋል። በአስራ-ስምንተኛው እርከን (stage 18) አርባ-አራተኛ በመውጣት በድጋሚ የሚያኮራ ውጤት አስመዝግበዋል።

ጽጋቡ ባህሬን-መሪዳ ወክለው ከተሳተፉት ዘጠኝ ብስክሌተኞች መካከል በአጠቃላይ ውጤት ለቡድኑ ሁለተኛ ጥሩ ውጤት ያስመዘገበ ብስክሌተኛ ሆነዋል። ስሎቫንያዊው ብስክሌተኛ ብራኮቪች ጃኔዝ በዚህ ቱር ደ ፍራንስ ላይ በአጠቃላይ ውጤት (General classification) 45ኛ ደረጃን በመያዝ ፉክክሩን ጨርሰዋል። ኢትዮጵያዊው ጽጋቡ ገ/ማርያም ደግሞ 73ኛ በመውጣት ለራሱ፣ለቡድኑና ለአገሩ ኩራት መሆን ችሏል። ሁለት የዚህ ቡድን ብስክሌተኞች ደግሞ ውድድሩን ሳይጨርሱ አቋርጠዋል።

ይህ ለሃያ-አንድ ቀናት ያክል በፈታኝ ገፀ-ምድርና ሁኔታ የሚከናወን አለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር፣ ጀምሮ መጨረስ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ቢሆንም፣ ጽጋቡ በዚህ አመት ያስመዘገበው ድል ደግሞ ሊበረታታ የሚገባ ጥሩ ውጤት ነው። በተለይ ይህ ብስክሌተኛ የተራራ ውድድሮች ላይ የተሻለ ውጤት አምጥተዋል። ጽጋቡ ለወደፊት ለብዙ ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች በአለም መድረክ ጎልተው እንዲወጡ ፋና ወጊ ብስክሌተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ማጠቃለያ

ይህ በአለማችን ውዱና ታሪካዊው የብስክሌት ውድድር ዘንድሮ ለ104ኛ ግዜ ነው የተካሄደው።

በዚህ አመት የተካሄደው ቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ፉክክር እ.ኤ.አ ሓምሌ 1፣2017 በጀርመኗ ከተማ ደሰልዶርፍ (Dusseldorf) ጀምሮ፣ የተወሰኑ የጀርመን፣ቤልጅየምና ሉግዘምበርግ ከተሞችን እያቆራረጠ 3540 ኪ.ሜ የሸፈነው ውድድር፣ እ.ኤ.ኣ ሓምሌ 23/2017 መዝግያው በፈረንሳንይዋ ዋና ከተማ ፓሪስ አድርገዋል። ፉክክሩ በአጠቃላይ 21 መድረኮች (stages) ያካተተ ሲሆን 198 ብስክሌተኞች፣ እያንዳንዳቸው 9 ኣባላት ያሉዋቸው 22 ቡድኖች ተሳታፊ ነበሩ።

በመጨረሻ ፉክክሩን የፈፀሙ ብስክሌተኞች ቁጥራቸው ያነሰ ቢሆንም!በዚህ አመት ውድድር አምስት ግዜ የእርከን (stage) አሸናፊ የነበረውና እስከ አስራ-ሰባተኛው እርከን (stage) አረንጓዴውን ማልያ አጥልቆ የነበረው (በውድድሩ ከፍተኛ ነጥብ ላስገኘ ብስክሌተኛ የሚሰጥ ማልያ ነው) ጀርመናዊው ማርስል ኬትል በዚህ እርከን ላይ በደረሰበት ጉዳትና በአጠቃላይ በውድድሩ ስለተዳከመ ከፉክክሩ ራሳቸውን ካገለሉ ብስክሌተኞች መካከል አንዱ ነው። ኬንያ የተወለደ ቢሆንም፣ እንግሊዝን ወክሎ የሚጫወተው ክሪስ ፍሩም በአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ ሆኖ ጨርሰዋል።ክሪስ ፍሩም አምናም የዚህ ውድድር አሸናፊ ነበር።

*******

Guest Author

Guest Author

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago