“ሰው ሰው የሚሸቱ” መሪዎች ያስፈልጉናል

የለንደን ስኩል ኦፎ ኢኮኖሚክስ ዳይሬክተር የነበረው “Anthony Giddens” ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የለውጥ ሂደት በሰጠው ትንታኔ በ1989 ዓ.ም (እ.አ.አ.) የታየውን የሶፌት ህብረት መፈራረስ እንደማሳያ ይጠቅሳል። በወቅቱ በተለያዩ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ወጥቶ ነበር። ሆኖም ግን፣ በዓለም ታሪክ ከታዩት አብዮቶች ሁሉ በተለየ፣ በጣም ዝቅተኛ ሁከትና ብጥብጥ (violence) የተከሰተበት እንደሆነ ይጠቀሳል። ቀድሞ የማይደፈር ይመስል የነበረው አምባገነናዊ ሥርዓት እንዳልነበረ ሆኖ ሲፈራርስ፣ በወቅቱ የአሜሪካ ፕረዜዳንት የነበሩት “Ronald Reagan” እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር፡-

“Technology will make it increasingly difficult for the state to control the information its people receive. … The Goliath of totalitarianism will be brought down by the David of the microchip.” — Ronald Reagan, speech at London’s Guildhall, 14 June 1989.

በእርግጥ በ1989 ዓ.ም ሁከትና ብጥብጥ የተከሰተበት ብቸኛ አጋጣሚ የቴሌለቭዢን ጣቢያዎችን ለመቆጣጠር ጥረት በተደረገበት ወቅት ነበር። እንደ “Anthony Giddens” አገላለፅ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ቀድሞ መቆጣጠር በወቅቱ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር እንደሆነ ይጠቅሳል። ምክንያቱም፣ ከ25 አመት በፊት በተለያዩ የዓለም ሀገራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥርና ተደራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት ነበር። በመሆኑም፣ “ከቀድሞው ግዜ በተለየ ዜጎች ንቁ፥ ፈጣን (active, reflexive) እንዲሆኑ አስችሏቸዋል” ይላል። ስለዚህ፣ ባልተለመደ መልኩ አብዮቱ በሁከትና ብጥብጥ ያልተደናቀፈበት ምክንያት በቴሌቪዥንና ሌሎች የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የሕብረተሰቡ ንቃተ-ህሊና በከፍተኛ ሁኔታ በመዳበሩ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ሌላው ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ፣ ሁከትና ብጥብጥ የተከሰተባቸው ቦታዎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መሆናቸው ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ቴሌቪዥን በወቅቱ ለነበሩት አምባገነን መንግስታት በስልጣን ላይ ለመቆየት ቁልፍ ሚና ስለ ነበረው ነው። በምስራቅ አውሮፓ የነበሩት ኮሚኒስታዊ አምባገነን መንግስታት በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ስላልነበራቸው፣ ከሕዝቡ ውስጥ ተገፍተው የወጡና በፕሮፓጋንዳ ላይ ብቻ የተመሰረተ ሕልውና የነበራቸው ናቸው። በወቅቱ ዋና የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ የነበረው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከቁጥጥራቸው ከወጣ ግን የሥርዓቱ ማብቂያ ይሆናል። በመሆኑም፣ ሁከትና ብጥብጥ የተከሰተው ይህ አምባገነንነት የተጠለጠለበት ገመድ፥ የቴሌቪዥን ጣቢያን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ትግል ነው።

Photo – President Obama, White House, Oval office, 2015

በመሰረቱ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የአምባገነን መንግስታት ጠላት ነው። በዘርፉ የሚታየው ለውጥና መሻሻል የዜጎችን የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና በማዳበር ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የአምባገነን መንግስታትን መሪዎች ከነባራዊ እውነታ እንዲነጠሉ በማድረግ ጭምር ለአምባገነናዊ ሥርዓት መፍረስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታል። በዚህም፣ አምባገነን መንግስታት በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ለውጥ እና የነገሮችን መለዋወጥ መገንዘብ ይሳናቸዋል። “እንዴትና ለምን” ለሚሉት ጥያቄዎች “Anthony Giddens” የሚከተለውን ምላሽ ይሰጣል፡-

“Political power based upon authoritarian command can no longer draw upon reserves of traditional deference, or respect. …In a world based upon active communication, hard power – power that comes only from the top down – loses its edge. Information monopoly, upon which the political system was based, has no future in an intrinsically open framework of global communications. A deepening of democracy is required, because the old mechanisms of government don’t work in a society where citizens live in the same information environment as those in power over them.” Anthony Giddens: Runaway World – Democracy

ከ25 ዓመታት በፊት በምስራቅ አውሮፓ የነበረው መረጃና ግንኙነት በዋናነት በስልክ እና ቴሌቪዥን ላይ የተመሰረተ ነበር። ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አገልግሎት የተጀመረው በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው። እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድረገፆች ደግሞ የመጡት ከ15 አመታት በኋላ ነው። ዛሬ ላይ ያለው የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በ1989 ዓ.ም (እ.አ.አ.) ከነበረው ጋር ፈፅሞ ሊወዳደር አይችልም።

ዛሬ በየትኛውም የዓለም ክፍል የተከሰተ ነገር በቅፅበት ውስጥ ለመላው ዓለም ሊዳረስ ይችላል። የመረጃ ልውውጥ ስርዓቱ ፈጣን፣ አሳታፊና ተደራሽ ነው። አብዛኛው የአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና የዳበረ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ስለዚህ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ የሆነ ሁኔታ አለ ማለት ነው። ነገር ግን፣ አንዳንድ የጥናት ውጤቶች ደግሞ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እየታየ ያለው እምርታ፣ እንደ ምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ከዴሞክራሲ ጋር አብሮ ላይሄድ ይችላል በማለት ይጠቁማሉ። በመሆኑም፣ “the rise of democracy and the power of the information revolution combine to leverage each other” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ በሁሉም ሀገራት ተግባራዊ ላይሆን ይችላል በማለት ይገልፃሉ።

ቻይና እና ኩባን እንደ ማሳያ በመውሰድ የተሰራው ጥናት፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ዘርፉን በመቆጣጠር ረገድ የረጅም ግዜ ልምድ ያላቸው ሀገራት በኢንተርኔት አገልግሎት ላይም ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚችሉ ይጠቅሳል። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ዓይነት የቁጥጥር ዘዴዎች እንዳሉ የተጠቀሰ ሲሆን አብዛኞቹ አሁን በኢትዮጲያ መንግስት ተግባራዊ እየተደረጉ ካሉት ጋር ተመሣሣይ ናቸው። ሆኖም ግን፣ የጥናቱ ማጠቃላያ መንግስት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ዘርፉን በዘላቂነት መቆጣጠር እንደማይችል ይገልፃል።

መንግስት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ዘርፉን በዘላቂነት መቆጣጠር የማይችልባቸው ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፤ አንደኛ፡- የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ያለማቋረጥ በየግዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ስለሆነ መንግስት የመንግስት ቁጥጥርና ክትትል ስርዓት ከዚህ ፍጥነት ጋር አብሮ መሄድ አይችልም። ሁለተኛ፡- “John Perry Barlow” የተባለው የዘርፉ ታዋቂ ምሁር እንደተናገረው፡ “the global social space we are building to be naturally independent of the tyrannies [governments] seek to impose on us.” በዚህ መሰረት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረታዊ ዓላማ ከመንግስት እገዳና ገደብ ነፃ የሆነ ማህብረሰብ መፍጠር እንደመሆኑ፣ እያንዳንዱ የለውጥና የመሻሻል ጥረት የመንግስትን ቁጥጥርና ክትትል የማስቀረት ግብ አለው። ስለዚህ፣ መንግስት የመረጃና ግንኙነት ዘዴዎችን በመቆጣጠር የዴሞክራሲ ጥያቄን ማስቀረት አይችልም።

እንደ “Anthony Giddens” አገላለፅ፣ የምስራቅ አውሮፓ አምባገነን መሪዎች ስለሚመሩት ህዝብ ኑሮ እና የአኗኗር ዘይቤ የነበራቸው ግንዛቤ በጣም ውስን ነበር። መሪዎቹ ስለ ሕዝቡ ከሚያውቁት በላይ ሕዝቡ ስለ መሪዎቹ ጠንቅቆ ያውቃል። በተለይ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እየተሻሻለ በሄደ ቁጥር የዜጎች ንቃተ-ህሊና እና ግንዛቤ እየዳበረ መሄዱ ይቀጥላል። በዚህም፣ ዜጎች ስለራሳቸውና ሌሎች ሀገራት ኑሮና የአኗኗር ዘይቤዎች፣ ስለመንግስታዊ ሥርዓትና አሰራር የተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል። ይህ የዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ጥያቄ፣ የተሻለ ሕይወት የመኖር ጉጉት በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ እንዲሰርፅ ያደርጋል።

በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎት ለአምባገነን መንግስታት ስጋት የሚሆንባቸው አራት የተለዩ ምክንያቶች አሉ። እነሱም፡- የብዙሃኑ ተጠቃሚ መሆን፣ የሲቪል ማህበራትና ተከራካሪ ቡድኖች፣ የኢኮኖሚ ቡድኖች እና ዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ መንግስት ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ የሚፈራው መሰረታዊ ነገር የዜጎችን የእርስ-በእርስ ግንኙነት እና ከሌሎች ጋር ያላቸውን የመረጃ ልውውጥ ነው። ምክንያቱም፣ የሌሎች ሀገራት ሕዝቦችን ኑሮና አኗኗር የመታዘብና የማወቅ እድል ያገኘ ሰው በራሱ ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ይሻል።

ከዚህ ተፈጥሯዊ የለውጥና መሻሻል ሂደት ጋር አብሮ የማይሄድ መንግስት፣ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን ስሜት የማይረዳ መንግስት ነው። በዚህ መሰረት፣ ዴሞክራሲያዊ ሆነ አምባገነናዊ መንግስት፣ ከሕዝቡ ፍላጎትና ምርጫ ጋር አብሮ እስካልሄደ ድረስ ከስልጣን ይወርዳል። አምባገነናዊና በዴሞክራሲያዊ መንግስታት መካከል ያለው ብቸኛ ልዩነት የመጀመሪያው በሕዝብ አመፅና ተቃውሞ ሲወድቅ ሁለተኛው በሕዝብ ምርጫ ከስልጣን የሚወርድ መሆኑ ነው።

እስካሁን ድረስ አምባገነን መንግስታት ከሕዝቡ ንቃተ-ህሊና ጋር አብሮ መሄድ ሲሳናቸው፣ በዚህም ለለውጥና መሻሻል እንቅፋት ሲሆኑ በሕዝብ አመፅና ተቃውሞ እንዴት ከስልጣን አንደሚወርዱ የ1989 ዓ.ም (እ.አ.አ) የምስራቅ አውሮፓ አብዮት እንደ ማሳያ በመውሰድ ተመልክተናል። በተመሣሣይ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግስታትም ከህዝቡ ፍላጎትና ምርጫ ጋራ አብሮረው መለወጥና መሻሻል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ምክንያት ከላይ እንድተጠቀሰው፣ የመረጃና ግንኙነት ዘዴዎች የአብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ንቃተ-ህሊና እና የአኗኗር ዘይቤ ስለሚቀይሩትና በዚህም ምክንያት የሚነሳውን የለውጥና መሻሻል ፍላጎትን ማስቀረት ስለማይቻል ነው። ሁለተኛ ምክንያት ደግሞ ምሉዕ የሆነ መንግስታዊ ሥርዓት ስለሌለ ነው።

የመጀመሪያውን ምክንያት ከምስራቅ አውሮፓ አምባገነን መንግስታት ጋር በተያያዘ ተመልክተናል። ሁለተኛውን ምክንያት ደግሞ የምዕራባዊያንን ዴሞክራሲ እንደማሳያ በመጠቀም እንመለከታለን። በእርግጥ የአስተዳደር ሥርዓቱ አምባገነን ሆነ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሥራና አሰራሩን ከሕዝቡ ፍላጎትና ምርጫ ጋር አብሮ እንዲሄድ ያለማቋረጥ መቀየርና መሻሻል ይኖርበታል። ይህን የማያቋርጥ የለውጥና መሻሻል ሂደት “Anthony Giddens” “democratising democracy” በማለት ይገልፀዋል።

እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር ለመጠየቅ አደባባይ በመውጣት ከአካል ጉዳት እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት ይደርስባቸዋል። በዚህም፣ ሕዝቡ የመንግስት ሥራና አሰራር ያማርራል፣ መንግስታዊ ሥርዓቱ እንዲሻሻል ወይም እንቀየር አጥብቆ ይጠይቃል። በተመሣሣይ፣ እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ባሉ ዴሞክራሲያዊ ሀገራት አብዛኛው ሕዝብ በመንግስት ሥራና አሰራር ይማረራል። መሪዎቹ ለራሳቸውና ለትላልቅ ኩባንያዎች ጥቅም እንጂ ለአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የቆሙ እንዳልሆኑ በመተቸት ከስልጣን እንዲወርዱ ይጠይቃል።

እንደ “Anthony Giddens”አገላለፅ፣ የዚህ ምክንያት በሕዝቡና በመሪዎቹ መካከል ሰፊ ልዩነት በመፈጠሩ፣ የመሪዎቹና ሕዝቡ ኑሮና አኗኗር የተራራቀ መሆኑ ነው። መሪዎች ዋና ትኩረታቸውን በፖለቲካዊ ሥራ ላይ ብቻ ሲሆን የእለት-ከዕለት ተግባራቸው ሰዋዊ ባህሪውን ያጣል። የመሪዎች ንግግር በፕሮቶኮል የታጠረ ሲሆን ስሜት-አልባ ይሆናል። በአጠቃላይ፣ እንደዚህ ያሉ መሪዎች “ሰው-ሰው አይሸቱም!” የሚባሉ ዓይነት ናቸው። ፅንሰ-ሃሳቤን ይበልጥ ለመረዳት እንዲቻል የአሜሪካውን ፕረዜዳንት ባራክ ኦባማን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ብዙውን ግዜ ባራክ ኦባማ ከጥቁርነቱ እና ተናጋሪነቱ በዘለለ በአሜሪካዊያን ዘንድ ያለው የማይተካ ሚና ሲነገር አይደመጥም። ኦባማ የመጀመሪያው ጥቁር ፕረዜዳንት ለመሆን የበቃው በአሜሪካ ማህብረሰብ ውስጥ የጎደለውን ማህበራዊ እሴት የተላበሰ የግል ስብዕና ስላለው ነው። በተለይ በወጣት አሜሪካዊያን ዘንድ ተወዳጅ የሆነ መሪ ነው። በተለያዩ መድረኮች የሚያደርጋቸው ንግግሮች የሚስቡና ጠንካራ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ በግል ባህሪው “ሰው-ሰው የሚሸት መሪ” የሚባል ነው።

በተለይ ደግሞ ፕረዜዳንት ኦባማ ለህፃናት ያለው ፍቅር እና ይህን የሚገልፅበት ሁኔታ ለተመለከተ ስለ ፕረዜዳንቱ የግል ስብዕና በግልፅ መረዳት ይቻላል። ለዚህ ማሳያ የሚጠቀሰው “Michael Skolnik” የተባለ ግለሰብ በቲዊተር (Twitter) ገፁ፡ “We’ll never truly be able to measure the impact that President #BarackObama has had on our children” በማለት ያወጣው ፅሁፍና ይህን ተከትሎ የተከሰተው ነገር ነው። ይህ ግለሰብ ለተከታዮቹ ፕረዜዳንት ኦባማ ከህጻናት ጋር የተነሳቸውን ፎቶዎች #ObamaAndKids በሚል መለያ እንዲለጥፉ በጠየቀው መሰረት የቤተ-መንግስቱ ፎቶግራፈር “Pete Souza” ያወጣቻቸው ፎቶዎች እጅግ በጣም የሚገራርሙ ናቸው። በእርግጥ “Democratising democracy” የሚለው የ“Anthony Giddens” ፅንሰ-ሃሳብ የሚያወራው ስለ እንደዚህ መሪዎች ነው። እንደ እሱ አገላለፅ ዴሞክራሲ ማለት ነፃ ምርጫና የፓርላማ ክርክር ብቻ አይደለም። ከዚያ በተጨማሪ፣ “ሰው-ሰው የሚሸቱ መሪዎች ያስፈልጉናል!”

**********

Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago