ጠ/ሚ ኃይለማርያም፡- በዋነኛ ሰብሎች 250 ሚ. – ባጠቃላይ ከ300 ሚ. ኩ. በላይ ማምረት የቻለ አገር ሆኗል

* ‹‹በትጥቅ ትግልም የተሳተፈ፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና እድገት እንዲመጣ ለማድረግ መስዋዕት የከፈለ ትውልድ አለ። ከእርሱ ትውልድ ተቀብሎ ደግሞ 2ተ ኛው ትውልድ ሥራ ጀምሯል።››

* ‹‹አንዳንድ ሀገሮች ያኔ 25 እና 30 ሚሊዮን እርዳታ ሲሰጡን ትልቅ እርዳታ ተደርጎ ነበር የሚታየው። ዛሬ እኛ የደረስንበት ደረጃ ሲታይ ደግሞ የህዳሴ ግድብን የመሰለ ወደ 4ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ግድብ በራሳችን ለመስራት መጀመራችን…››

* ‹‹በቅርቡ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት በምንም ተዓምር ይህን ግድብ መጥቼ ማየት አለብኝ፣….እናንተ ለእኛም ሞራል ሆናችሁናል፣ ከእናንተ ቀጥሎ እኛም መስራት አለብን ብለው አቋም ይዘው ግድቡን መጎብኘት አለብኝ ብለው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፣ በቅርቡም መጥተው ያያሉ።››

* ‹‹በዘንድሮ ዓመት በዋና ዋና ሰብሎች የባለፈው ዓመት የዘንድሮን ሳይጨምር 2006 ዓመት ላይ ማለት ነው በዋና ዋና ሰብሎች 250 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል፤ ከዚያ በላይ ደግሞ የስራስር ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የቅመማ ቅመምና ቅባት እህሎች፣ ቡና የመሳሰሉት ሲጨመሩበት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማምረት የቻለ አገር ሆኗል። ይሄ በህዝብ ቁጥር በሚከፋፈልበት ጊዜ ሀገሪቱ ራሷን በምግብ እህል መቻሏን ያስረዳል።››

– – – – – 

አዲስ ዘመን፡- ሕገመንግሥታችን የአገራችንን የቁልቁለት ጉዞ ቀልብሶ የኢትዮጵያ ህዳሴ መሰረት እንዲጣል ያደረገ ነው ይባላል፤ ይህ ምን ማለት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡ – በኢትዮጵያ ህዝቦች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ የኢትዮጵያን ህዳሴ ሊያረጋግጥ የሚችል ድል ተገኝቷል። ሕገ መንግሥታችን በዚህ ድል ላይ የተገነባ ሕገመንግሥት ነው፤ ከድሉ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና ተወካዮቻቸው በርካታ ውይይት ካደረጉ በኋላ በተወካዮቻቸው አማካኝነት አንድ ላይ ተሰባስበው ያጸደቁት ሠነድም ነው።

ወደ ጥያቄው ለመምጣት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዚህ ሕገመንግሥት ምን ዓላማ አስቀምጠው ነበረ? ምን እንዲሳካላቸው ፈልገው ነበር? የሚለውን በደንብ ማየት ጥሩ ነው። ዓላማቸውን ለማሳካት የፈለጉትን ነገር በሕገመንግሥቱ መግቢያ በሚገባ አስቀምጠዋል። ስለዚህ በመግቢያው ላይ ልክ ጥያቄው እንደቀረበው የኢትዮጵያ ህዝቦች የፈለጉት ሶስት መሰረታዊ ነገር ነበር። አንደኛው በሀገራችን ለበርካታ ዓመታት የሰላም እጦት ያስቃይ ስለነበር ከዚህ መውጣትና ዘላቂ ሰላም በሀገራችን እንዲሰፍን ለማድረግ ይሄ ሕገመንግሥት መሰረት ይጥልልናል፤ በሕገመንግሥቱ ተመርተንና ተግብረነው ሀገራችን ዘላቂ ሰላም ማግኘት ትችላለች የሚል ራዕይ አስቀምጠው ነበር።

ሁለተኛው ነገር ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ በሀገራችን እውን እንዲሆን ማድረግ ይገባል የሚል ነው፤ በጥያቄውም ላይ እንደቀረበው የኢትዮጵያ ቁልቁለት ጉዞ ተብሎ የሚገለፀው ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ሀገራችን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ በርካታ ትርምሶች እንደነበሩባት፣ ዴሞክራሲም የተነፈገች ሀገር ነበረች። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝቦች የፈለጉት ሁለተኛ ነገር ቢኖር ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ማድረግ ነበር። የቁልቁለት ጉዞ ይቁም ብለው ሲሉ ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ህዳሴዋ እንዲረጋገጥ ከተፈለገ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ወሳኝ ነው ለማለት ነው።

ሶስተኛው ጉዳይ ዘላቂ ሰላምም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲም ኖሮ ፈጣንና ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት እድገትና ልማት ካልመጣ በስተቀር በድህነት ውስጥ ሆኖ ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ አይቻልም ከሚለው ጋር ይያያዛል። ከዚህም አኳያ የኢትዮጵያ ህዝቦች ያስቀመጡት ሌላ ጉዳይ ቢኖር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገታቸው የተፋጠነ እንዲሆንና ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት እንዲገኝ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው ነው። እነዚህን ሶስት መስፈርቶች በማየት ነው የህዳሴ ጉዞአችን ከቁልቁለት ጉዞ ገድቦን ምን ያህል ህዝቡ የተመኘውን ነገር አሳክቷል፤ አሁን ደግሞ ወደ ህዳሴ ጉዞ እንዲመነደግ ለማድረግ የቻለው በምንድን ነው የሚል ጥያቄ ማንሳት ጥሩ ነው።

ከዚህ ተነስተን ስናይ ባለፉት 20 ዓመታት ሀገራችን ብዙዎች በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የሚመኙት በሰላም ወጥቶ መግባትና እርስ በርስ ተፈቃቅሮ የመኖር ሁኔታ ፈጥሯል። ይህን እኛ ብቻ ሳንሆን የዓለምም ህዝብ እየመሰከረው ያለ ሀቅ ነው። እንዲያውም አንዳንዶች እንደሚሉት ኢትዮጵያ በቀጣናው በርከት ያለ የሰላም ማጣት ባለበት እንደ ሰላም ደሴት ሆና ለሌሎች ሰላም ጭምር የምትተጋ ሀገር ሆናለች። ዓለም የሚመሰክርላትን፣ የኢትዮጵያ ህዝቦችም የተመኙትን ዘለቂ ሰላም ላለፉት 20 ዓመታት ልናረጋግጥ ችለናል።

ስለዚህ የኋሊት ጉዞ ቀርቶ ወደ ፊት ዘላቂ ሰላም ጀምረናል። ይሄ ጉዞአችን ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ እና ህዝቦች ባስቀመጡት ራዕይ መሰረት እስከተጓዘ ድረስ ዘላቂ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው። የሰላም መናጋት ሊመጣ የሚችለው በአንድና በአንድ ጉዳይ ብቻ ነው። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፈራረስ የሚፈልግ ኃይል ካለ እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ችግር ውስጥ ከገባ የኢትዮጵያ ህዝቦች የተመኙት ሰላም ላይረጋገጥ ይችላል።

ስለዚህ ሕገመንግሥቱን በምናይበት ጊዜ የሰላም መረጋገጥ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ባለፉት 20 ዓመታት የመጣ በጣም ትልቅ ውጤት ነው። ከሁለተኛው የህዳሴ ጉዞ ልናስተሳስር የምንችለውና የሚገባን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲኖር ተመኝተው ነበር። በሕገመንግሥቱም ውስጥ አስቀምጠው ነበር። ይሄ ባለፉት 20 ዓመታት እንዴት ነው የተተገበረው? በእርግጥ ዴሞክራሲ ዋስትና ያለው እንዲሆን የዴሞክራሲ ባህል በሀገሪቱ መገንባት አለበት።

አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ የዴሞክራሲ ባህል እየተገነባ መጥቷል፤ ስንጀምር ከነበረበት አሁን በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል። ይሄ ህፃናትን ከማስተማር ጀምሮ ተግባራዊ መሆን አለበት። በተለይ ትምህርት ቤቶች የዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብና አተገባበር የሚያስተምሩ ትልቅ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት የዴሞክራሲ ባህል በሀገራችን እንዲገነባ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋልና ልጆቻችን በየክፍሎቻቸው የፓርላማ ልምምድ በመማርም ጭምር ዴሞክራሲ ባህል እንዲሆን ያደረጉበት ሁኔታም ይታያል። ከሁሉ በላይ ግን ህዝቡ በማናቸውም የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ከፍተኛና ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበት፣ የመሰለውን የሚተችበት እንደዚሁም ያልመሰለውን አልቀበልም ብሎ የሚናገርበት መብቱ እየተጠበቀለት የመልካም አስተዳደር ጉዞ የጀመርንበት እንደሆነ ይታወቃል። ይሄ ቀጥተኛ ዴሞክራሲ ከየትኛውም ሀገር በተለየ መልኩ በሀገራችን የታችኛው መዋቅር እስከ ላይኛው ድረስ ህዝቡ እንዲሳተፍ ያደረገ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

ከዚያም በላይ የዴሞክራሲ ተቋማት የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥውና የተቃዋሚ ፓርቲዎች) ህዝብ ፊት እየቀረቡ፣ ፖሊሲዎቻቸውን እያስረዱ በየጊዜው እስከ አሁን አራት ምርጫዎች ተካሂደዋል፤አሁን አምስተኛ ልናካሂድ ነው፤ ባለፉት 20 ዓመታት በየ5 ዓመት በሚካሄድ ምርጫ ተሳትፎ የተደረገበትና ህዝቡ የፈለገውን ለመምረጥ የቻለበት ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል።

ስለዚህ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ አሁንም መቀጠል አለበት፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እስከተከበረና ተጠናክሮ እስከቀጠለ ድረስ ህዝቡ የተመኘውና ለህዳሴ ጉዞአችን በርካታ አስተዋፅኦ ያደረገው ዴሞክራሲ የመጎልበት ጉዳይ እንደ አንድ ትልቅ ጥያቄ የተመለሰበትና በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ እያደገ የመጣ እንደሆነ ማየት ይቻላል።

በሶስተኛ ደረጃ ለህዳሴ ጉዞአችን ፈጣን፣ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ልማት ማረጋገጥ በባለፉት 20 ዓመታት ምን ይመስል ነበር ተብሎ ሲታይ ለመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት እድገታችን በሚፈለገው መልኩ ፈጣን እንዲሆን በተደረገው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከባለፉት 10 ዓመታት ወዲህ የማያቋርጥ ተከታታይ የሆነ ባለ ሁለት አሃዝ እድገት በማስመዝገብ ሀገራችን በዓለም ደረጃ ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ ጥቂት ሀገሮች መካከል የተገኘች ሀገር ሆናለች። ስለዚህ ባለፉት 20 ዓመታት ሀገራችን ህዝቡ የተመኘውን የፈጣን እድገት ጉዞ ጀምራለች። ይሄ የእድገትና የህዳሴ ጉዞ ለሚቀጥሉት 40 እና 50 ዓመታት ያለማቋረጥ በዚሁ ፍጥነት መቀጠል አለበት፤ ይህ ህዝቡ ወደ በለፀገ የኢኮኖሚ ደረጃ እንዲገባ ያደርጋል። ከዚያም አልፎ በመሃከሉ ለሚቀጥሉት 10ዓመታት በዚሁ ፍጥነት ከተጓዘ የሀገራችን ህዝቦች አሁን በያዙት ወይም በሰነቁት ራዕይ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ለመሰለፍ በሚችሉበት ሁኔታ የተጓዝንበት ጊዜ ነበር ለማለት ይቻላል።

ስለዚህ ባለፉት 20 ዓመታት የህዳሴ ጉዞአችን ህዝቡ ባሰቀመጣቸው ሶስቱም መስፈርቶች ሲታይ የቁልቁለት ጉዞው ቆሞ፣ ሽቅብ የመጓዝ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም እያደግን እንደሆነ አሁንም ግን ድህነት በምንፈልገው ደረጃ ያልተሻገርነው ጉዳይ እንደሆነና ይህን ለመሻገር በተከታታይ ለሚቀጥሉት 10 እና 15 ዓመታት ጭምር መስራት እንዳለብን መረዳት ይኖርብናል።

አዲስ ዘመን፡ አገራችን የምትገኘው በአስቸጋሪ ጂኦፖለቲካዊ ቀጣና ሆኖ ሳለ በእድገትና በሰላም መጓዝ ችላለች፤ ይህ ለቀጣናው ያበረከተው አስተዋጽኦ ምንድን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባፀደቁት ሕገመንግሥት እየተመሩ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ያደረጉት ለራሳቸው ሲሉ ነው። መጀመሪያ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም መኖር አለበት። ዋናው የህዝቡ ፍላጎት ዘላቂ ሰላም በሀገራችን እንዲሰፍን ማድረግ ነው። ከእኛ ዘላቂ ሰላም መስፈን ሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ሌሎች ይጠቀማሉ ወይ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ አዎን ይጠቀማሉ።

የተለያየ ችግር በተለያየ ምክንያት ያጋጠማቸው ለምሳሌ ጎረቤቶቻችን ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን በከፍተኛ ደረጃ በሰላም እጦት ችግር ውስጥ የወደቁ ሀገሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በሀገሯ በማስፈኗ ምክንያት በሌሎችም ሀገሮች ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ የመጣች ሀገር ናት። በእርግጥ ጎረቤቶቻችን ሰላም በማጣታቸው ምክንያት ወደ እኛ የሚተርፍ ነገር እንደሚኖር ታሳቢ በማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ህዝብ ጎረቤቶቻችን በሰላም እጦት ምክንያት ከኢኮኖሚ እድገት፣ ከተጠቃሚነትና ከዘላቂ ልማት እየራቁ ሲሄዱ ለሀገራችን የሚተርፍ ነገር ሊኖር ስለሚችል ይህን ለመቅረፍ በበለጠ ተሳትፎአችንን አጎልብተን እኛ በውስጣችን የተገኘውን ሰላም ተጠቅመን ጎረቤቶቻችንም የሰላም ሀገር እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል።

በዚህ ዙሪያ መንግሥታችን እያደረገ ባለው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለው የመከላከያ ሠራዊታችን ነው። መከላከያ ሠራዊታችን በሕገመንግሥቱ መሰረት የተቀረፀ፣ ህዝባዊ መከላከያ ሠራዊት ነው። ትልቁ የመከላከያ ሠራዊታችን አቅም ሕገመንግሥቱ ነው። መከላከያ ሠራዊታችን ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ሆኖ ሕገመንግሥቱን በማክበርና በማስከበር ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍል ሠራዊት ነው። ስለዚህ ሕገመንግሥቱ ህዝቡ የፈለጋቸውን ሶስቱን ጉዳዮች የያዘ ሕገመንግሥት ነው። ዘላቂ ሰላም የህዝቦች ነው፤ ሠራዊታችንም ህዝባዊና የህዝብ ሠራዊት እንደመሆኑ መጠን በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ያለ ሠራዊት ነው። በተመሳሳይ የመከላከያ ሠራዊታችን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ በሀገራችን እንዲገነባ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው።

በሶስተኛ ደረጃ ፈጣን እድገቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ሀገሪቱን የመከላከል፣ ማንኛውም አይነት ሰላማችንን፣ ዴሞክራሲያችንንና ከዚያም አልፎ ልማታችንን የሚያስተጓጉል ኃይል በሚኖርበት ጊዜ ይህን ለመመከት ለሰላማችን የቆመ ኃይል ነው። የተለያዩ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሰላማችን ለማወክ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በአስተማማኝ ሁኔታ የመከተ ሠራዊት ነው፤ ለባለፉት 20 ዓመታት ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሠራዊት ነው።

ይሄ ዋናው ተልዕኮ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም መንግሥታችን የሚሰጠውን ተልዕኮ ተሸክሞ ጎረቤቶቻችንን፣ ከዚያም አልፎ በአፍሪካ የሰላም አጦትን የሰላም አስከባሪ ኃይል በመሆን ተሳትፎ እጅግ አመርቂ ውጤት ያመጣ ሠራዊት ነው። ሰለዚህ የመከላከያ ሠራዊታችን አሁን ባለው ሁኔታ በአፍሪካ ትልቁ የሰላም አስከባሪ ኃይል ሆኖ በዓለምም በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት(አሚሶም) አንደኛ እየሆነ ያለ ሠራዊት ነው።

ስለዚህ የዓለም ህብረተሰብም፣ የአፍሪካ ወንድምና እህቶቻችንን ጭምር ለመከላከያ ሠራዊታችን በጣም ትልቅ ክብር የሚሰጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚሁ በተጓዳኝ መከላከያ ሠራዊታችን ለሀገራችን መገለጫ ከመሆኑ አንፃር ሀገራችንም ከዚህ ተነስታ የሰላም የብልፅግና ለሌሎችም የምትተርፍ መሆኗን እንዲመሰከርላት አድርጓል።

ከዚህ አንፃር በሕገመንግሥቱ የተቀረፀው መከላከያ ሠራዊታችን ምን ያህል የሕገመንግሥት መሰረት ያለውና ውጤታማ እንደሆነ ማየት ይቻላል፤ 20 ዓመት ስናከብርም በዚህ ሕገመንግሥት ላይ የተቀረፀ ሠራዊት ውጤቱ የ20 ዓመቱ ውጤት ጭምር ተደርጎ መታየት አለበት ብዬ ነው የማምነው።

አዲስ ዘመን፡- በህገመንግስታችን ስለ አካባቢ ጥበቃ በአንቀጽ 92 በግልፅ ተቀምጧል፡፡ አገራችን የአፍሪካ አጀንዳ የሆነውን የአረንጓዴ ልማት አስተሳሰብ ይዛ ስትከራከርም ይታያል የልማታችን ቁልፍ መለያም አረንጓዴ ልማት ነው ይባላል፡፡ ይህ ድሃ ለሆነች አገር በእርግጥ ወቅታዊ አማራጭና አስፈላጊ ነው ወይ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- በዚህ ጉዳይ ሁለት አይነት አስተሳሰቦች እንዳሉ በጥያቄው በቀረበው መልኩ ማየት ይቻላል። የአካባቢን ጉዳይ በምንመለከትበት ጊዜ በበለፀጉ አገሮች Green House gas (አካባቢን የሚበክል ጋስ ) በመርጨት ዙሪያ ከፍተኛ ድርሻ ያለው፣ ከመሬት ውስጥ የሚወጣው ፎሲል ፊዩል የምንለው ወይም ደግሞ ካርበን ያለው ነዳጅና ጋስ ነው። እንግዲህ የሀገሮች ልማት በነዳጅና ጋስ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ከእኛ ቀድመው ያደጉና የበለፀጉ ሀገሮች ብዙዎቹ ለኃይል ምንጭ የሚጠቀሙት ይህን አካባቢ የሚበክል የኃይል ምንጭ ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ አካባቢን የሚበክል የኃይል ምንጭ ሳንጠቀም እነርሱ ከለሙት ፍጥነት በላይ መልማት ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው ነው መመለስ ያለበት።

እነርሱ የተከተሉትን መንገድ የግድ መከተል የለብንም፤ ዋናው ጉዳይ እነርሱ የተከተሉትን ብንከተል ነው የበለጠ የምንለማው ወይስ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲታይ የራሳችንን የአረንጓዴ ልማት መንገድ ብንከተል ነው የምንለማው የሚል ጥያቄ አንስተን መመለስ አለብን። ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የምትሆነው የአረንጓዴ ልማት ጎዳና ስትከተል ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከፍተኛ እምቅ የሆነ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ያላት ሀገር ናት።

ስለዚህ ሌሎች ነዳጅ እና ጋስ ከመሬት አውጥተው በለሙበት መንገድ እንድንሄድ የሚያስገድደን ነገር የለም። ይሄን ሰፊ የሆነ የታዳሽ ኃይል እምቅ ሀብት ተጠቅመን ሀገራችንን ማልማት እንችላለን የሚል ትልቅ ቁርጠኝነት በመንግሥታችን በኩል አለ። በአረንጓዴ ልማት ጉዳይ ለአካባቢ ብክለት ተፅዕኖ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ጎዳና መከተል አለብን የሚል ስትራቴጂ ለዓለም ቀርፀን ያሳወቅነው በዚህ ምክንያት ነው።

እኛ መሬት ውስጥ የሚገኘው ነዳጅና ጋስ ቢኖረን ጥሩ ነው። ነገር ግን ባይኖረንም ይህን ያክል ብዙ የሚያሳስበን አይሆንም፤ ሌሎች ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ስላለን። ስለዚህ ይሄ በአንድ በኩል አንድ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ደሀ ሀገር ብንሆንም ለሌሎች የሞራል ስንቅ እንዲሆናቸው በድህነታችንም ጭምር ዓለምን የሚበክልና የሚረብሽ የጋራ መኖሪያችን የሆነችውን ምድር የሚያቃጥል ወይም ሙቀቷን በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምር የአካባቢ በካይ ጋሶች በሌላ ሀገር ጭምር የሚለቀቁትን በታዳሽ ኃይል እንዲቀየሩ ምሳሌ መሆን አለብን።

ይህን ፈረንጆቹ Responsible Global citizen ይላሉ፤ ኃላፊነት የሚሰማው የዓለም አቀፍ ዜጋ ሆንን ማለት ነው። በምድሪቱ ኢትዮጵያዊ ብንሆንም በዓለም ነዋሪዎች ነን፤ የዓለም ዜጎች እንደመሆናችን መጠን ኃላፊነት የሚሰማቸው የዓለም ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚለውንም መልዕክት አስተላልፈናል። ይህን ያደረግነው ትላልቆቹ ሀገሮች ደሃ የሆኑት እንደ ኢትዮጵያ ያሉት እንኳ በዚህ መንገድ ከሄዱ እኛ ደግሞ ወደ ታዳሽ ኃይል ምንጭ መምጣት አለብን ብለው የሞራል ጥያቄ እንዲነሳባቸው ለማድረግም ጭምር ነው።

ከዚህ ተነስቶ ኢትዮጵያ የሞራል የበላይነት ይዛ ይህን ውጊያ ለመቀጠል፣ አካባቢን የሚበክል ነገር የዓለም ትልቆቹ ሀገሮች በሚሞክሩበት ጊዜ ትክክል አይደለም የሚለውን በአግባቡ ለማስረዳትና ከዚህም ዓለም እንዲማር፣ ከእኛ ምሳሌ እንዲወስድ ማድረግ አንዱ ዓላማችን በመሆኑም ጭምር ነው።

ዋናው ጉዳይ ግን ሌሎች በሄዱበት መንገድ መሄድ አጥፊ ነው፤ አንደኛ ከፍተኛ የነዳጅ ፍጆታ ይዘን የምንለማበት እድል የለንም፤ ምክንያቱም በውጭ ምንዛሪ የሚገዛ ነው፤ ከእዛ ውጪ ግን እኛ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ስላለን ይህን ተጠቅመን በተለይ ሀገራችን አሁን በጀመረችው የተፈጥሮ ሀብትና የደን ልማት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃና ከግብርና ጋር የተያያዘው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ እንደመሆኑ፣ ይህን የራሳችንን ንፅፅራዊ ጠቀሜታ ይዘን ለዓለም ህብረተሰብ ምሳሌ በመሆን በፈጣን ሁኔታ ማደግ እንደሚቻልም ጭምር አሳይተን መጓዝ አለብን በሚል ነው።

አዲስ ዘመን፡ ዘመኑ የኢትዮጵያ ህዳሴ እንደሆነ ተደጋግሞ ይገለፃል፡፡ በዚህ ረገድ መላው ህዝብ አንድ ላይ እንዲቆም ጥሪ ሲደረግ ይሰማል፡፡ የአገራችን ህዳሴ የረጅም ጊዜ ተልእኮ ከመሆኑ አኳያ ከህብረተሰቡ፣ በተለይ ደግሞ ከምሁሩና ከወጣቱ ምን ይጠበቃል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሁላችንንም በከፍተኛ ደረጃ ይኮረኩራል ብዬ የማስበው ቃል በተደጋጋሚ የምናነሳው ህዳሴ የሚባል ቃል ነው። እንደተባለው የኢትዮጵያ ህዳሴ የረጅም ጊዜ ጉዞ ነው። ህዳሴያችንን ከጀመርን የተወሰኑ ዓመታት አሳልፈናል። አሁንም በተከታታይ ለ30፣ 40 እና 50 ዓመታት መጓዝ ይጠይቀናል፤ ወደ በለፀጉት ሀገራት ተርታ መሰለፍ የትውልዶች ጉዞ እንደሆነ ይታወቃል።

ስለዚህ ይህኛው እኛ ያለንበት ዘመን ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ የህዳሴ ጉዞ መሰረት ጥሎ በዚህ መሰረት ላይ ሌላው የሚመጣው ትውልድ እንዲገነባ ለማድረግ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ማለፍ ያስፈልጋል። ስለዚህ ይሄ የቅብብሎሽ የህዳሴ ጉዞአችን ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ባለንበት ደረጃ ከተመፅዋችነት፣ ከጦርነት፣ ከእልቂትና ከረሃብ ከመሳሰሉ ክፉ ገፅታዋ እየቀየራት መጥቷል። የህዳሴ ጉዞ በመጀመራችን ምክንያት ባለፉት 20 ዓመታት በተደረገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መጥፎ ገፅታ እየተቀየረ ነው። ይህን የሰራው ይሄ ትውልድ ነው። በትጥቅ ትግልም የተሳተፈ፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና እድገት እንዲመጣ ለማድረግ መስዋዕት የከፈለ ትውልድ አለ። ከእርሱ ትውልድ ተቀብሎ ደግሞ 2ተ ኛው ትውልድ ሥራ ጀምሯል። ይሄ ትውልድም በተመሳሳይ መልኩ በትጥቅ ትግሉ መስዋዕት እንደከፈሉ ትውልዶች አይነት የጦርነት መስዋዕትነት አይነት እንኳ ባይሆን በተደጋጋሚ እንደሚባለው የልማት፣ የዴሞ ክራሲና የመልካም አስተዳደር ማስፈን ከድህነት ጋር በሚደረግ ጦርነት የበኩሉን መስዋዕትነት ከፍሎ ማለፍ አለበት። የሚቀ ጥለው ትውልድም በተመሳሳይ መንገድ ይህንኑ ጉዞ በቅብብሎሽ ማስኬድ አለበትና የረጅም ጊዜ ጉዞ ነው የሚባለው ከዚህ ተነስቶ ነው።

ስለዚህ አሁን ያለን ኢትዮጵያውያን የዚህ ትውልድ ባለቤቶች ይህን የህዳሴ ጉዞ ሳይንገራገጭና ሳይስተጓጎል ወደፊት እንዲጓዝ ለማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን። አሁን የተጀመረው ሰላም፣ ልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጉዞ በተጀመረው ፍጥነት እንዲቀጥልና ከዚያም በላይ እንዲፈጥን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። ይሄ ጥረት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በየተሰማራበት መስክ በሚያደርገው አስተዋፅኦ የሚከናወንና የሚሳካ ነው። ስለዚህ የእኔ መልዕክት በዚህ ዙሪያ ሁላችንም በየተሰማራንበት መስክ ሀገራችን የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ የበለጠ እንዲቀላጠፍ እና የሚፈለገው ብልፅግና እስኪመጣ ድረስ ሳንታክት ወደፊት በመጓዝ መታገል፣ አስተዋፅኦአችንንም ማበርከት አለብን የሚል ነው።

አዲስ ዘመን፡ የአንድ አገር እድገት መለያው የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን ያከናወነቻቸውንና ወደፊትም ለማከናወን ያቀደቻቸውን ሥራዎች አያይዘው ቢገልፁልን?የእድገቱ ቁልፍ የሰው ኃይል ልማት ነውና እኛ ምን ያህል ተሳክቶልናል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- የአንድ ሀገር ዋነኛ የልማት ኃይል የሚባለው ሰው ነው። በእኛ ሁኔታ መንግሥታችን ይህን በመገንዘቡ በመጀመሪያ ትኩረት ያደረገው ለትምህርት እና ለጤና ጉዳዮች ነው። በዚህም በጣም የሚያበረታታ አይነት ድልና ውጤት ተገኝቷል። አሁን ባለንበት ደረጃ መላው የሀገራችን ህፃናት ትምህርት ቤት ገብተው እየተማሩ ነው። ይህ ማለት የዛሬ 12 ዓመት መላው የሀገራችን ህፃናት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይጨርሳሉ ማለት ነው። መካከለኛ ገቢ በምንደርስበት ጊዜ መላው የሀገራችን ወጣቶች ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚጨርሱ ስለሆነ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ሙሉ ሆኗል ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ራዕይ ይዘን ስንሰራ አሁን ባለው ደረጃም ቢሆን ከግማሽ ሚሊዮን ያልተናነሰ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ማስቀጠል ይቻላል። ከታች በ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ አልፈው የመጡ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣቶች አሉ። ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ብዙዎች ሳይንቲስቶች፣ ቴክኖሎጂስቶች፣ መሀንዲሶች፣ ሀኪሞች እና ተመራማሪዎች እንደሚሆኑ ምንም ጥያቄ የለም።

የወደፊት የቴክኖሎጂ ምንጮቻችን የሚሆኑት እነርሱ ናቸው። አሁን ባለንበት ደረጃ ምንአልባት በቴክኖሎጂ ኋላቀር አገር ተብለን ልንፈረጅ እንችላለን። ነገር ግን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማትና የፈጠራ ፖሊሲያችን ደረጃ በደረጃ የሌሎች ሀገሮችን ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገራችን በማስገባት በማላመድ፣ በመጠቀምና እነዚህን በማሻሻል ዙሪያ በምንሰራው ሥራ ቴክኖሎጂው እየተሸጋገረ ይመጣል። እናም በሂደት የራሳችንን ማመንጨት እንጀምራለን። ሰለዚህ ከቴክኒክና ሙያ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚያልፉ ወጣቶቻችን በሙሉ የዚህ ባለቤት ነው የሚሆኑት።

ስለዚህ ዋናው መሰረት ይሄ ነው፤ ይህን ካደረግን በኋላ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተለያዩ ምርምሮች ማካሄድ ይገባናል፤ ምርምሮቹ ከማላመድ እስከ ማመንጨት ድረስ ባሉት ተግባሮች ዙሪያ የሚከናወኑ ይሆናሉ። መንግሥታችን ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰጠው ትኩረት በጣም ከፍተኛ ነው። ከ1ኛ ደረጃ ጀምሮ በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ሰፊ ትኩረት በመስጠታችን እነዚህን ወጣቶች በሂደት የቴክኖሎጂ ምንጭ አድርገን ልንወስዳቸው እንችላለን የሚል አስተሳሰብ አለን። በዚህ ደረጃ ቴክኖሎጂ በትምህርት ቤቶች ብቻ አይደለም፣ በዩኒቨርሲቲዎችም ብቻ አይደለም፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማምረቻ ተቋሞችም ጭምር በፈጠራዎች ታግዘው መካሄድ ስላለባቸው የተቀናጀ ሥራ ለመስራት የሚያስችል ፖሊሲ አለን፤ በሂደት በዚህ ዙሪያ እየጎለበትን እንመጣለን የሚል አስተሳሰብ ነው ያለኝ።

አዲስ ዘመን፡- በአንድ በኩል ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራና ውጤት እንዳለ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአገራችንን ገፅታ ለማበላሸት የሚሯሯጡ አክራሪና ፅንፈኛ ዳያስፖራዎች በተለያየ ቦታ የሚሰሯቸው የጥፋት ስራዎች አሉ፡፡ ያለንበት የዲፕሎማሲ ደረጃ ምን ይመስላል? የነዚህ ጥፋት ኃይሎች እንቅስቃሴ አንድምታው ምንድነው? በሌላ በኩል በተለይ በአሁኑ ወቅት ከእርዳታ ይልቅ የልማት አጋር የሚል አገላለፅ ተደጋግሞ ይነሳልና ምን ማለት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- በመጀመሪያ ደረጃ በህገመንግስታችን ውስጥ የተቀመጠው የውጭ ጉዳይ መርሆ እነዚህን በጥያቄው ላይ የተቀመጡ መርሆዎችን የሚዘረዝር ነው። የውጭ ግንኙነት መርሆዎቻችን የሚመሰረቱት በአገራችን ጥቅም ላይ ነው። ማንኛውም አይነት የምናደርገው ግንኙነት የሀገራችንን ጥቅም የሚያስከብር መሆን አለበት።

ሀገራችንን የሚጎዳ ማንኛውም አይነት ግንኙነት መፈጠር የለበትም። ስለዚህ የውጭ ግንኙነታችን በዚህ ደረጃ በጣም መሰረታዊ በሆኑ ህገመንግስቱ ላይ በተቀመጡ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ነው። ዲፕሎማሲያችንም ያተኮረው ድህነትን በመዋጋት ዙሪያ በምናደርገው እንቅስቃሴ ወይም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ብለን የምንወስደው እንቅስቃሴ ላይ ነው።

ሌሎች ቀደም ብለን የተነጋገርንባቸው የሰላም ጉዳዮች፣ የፀጥታ ጉዳዮች የሚመጡት ይሄ ሰላማችን ሳይናጋ ልማታችንን ለማቀላጠፍ ድህነትን ለመዋጋት እንዲያግዘን ነው። ሰላም በራሱ ትልቅ ውጤት ነው። ነገር ግን ብቻውን በቂ አይደለም። ሰላም በመኖሩ ምክንያት ቶሎ ፈጥነን መልማት አለብን። ስለዚህ ከውጭ ሀገሮች እና ድርጅቶች ጋር የምናደርጋቸው ግንኙነቶች በሙሉ ድህነትን ለመዋጋትና ኢኮኖሚያችንን በፍጥነት ለማሳደግ በሚደረግ ግንኙነት መሆን አለበት።

አንዳንድ ጊዜ በእርዳታ ወይም በተለያየ ምክንያት የምናገኛቸው ድጋፎች የየራሳቸው ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተቱ ናቸው። ስለዚህ አገራዊ ነፃነታችንና ፖሊሲያችንን ለማስፈፀም በሚደረገው ሁኔታ የራሳቸውን ተፅዕኖ ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ አገራዊ ነፃነታችን እንዲከበር ካስፈለገ ዋናው ግንኙነታችን መሆን ያለበት በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነው ብለን በሰራነው ሥራ በርካታ ወጤቶችን አግኝተናል።

ስለዚህ አሁን ከእርዳታ ይልቅ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት ድህነትን በመዋጋት ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሚያበረክቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የዲፕሎማሲ ሥራ እንስራ ስንል ይህን ማለታችን ነው። ብድርም የምናገኝ ከሆነ በሀገራችን የምናከናውነውን ልማት የሚደግፍ የራሳችን ጥቅም የሚያሳካ ብድር መሆን አለበት። ከተለያዩ ጥልፍልፍ ነገሮች የፀዳ እና የራሳችንን ልማት የሚያሳካ መሆን አለበት ተብሎ ተወስዶ ነው የሚከናወነው። ስለዚህ እነዚህ በሙሉ ሲታዩ ዋናው ግንኙነታችን መሆን ያለበት በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት ዙሪያ ያተኮረ ዲፕሎማሲ መሆን አለበት የሚለውን መውሰድ ይቻላል።

ከዚያ ባሻገር እርዳታን በተመለከተ ፕሮግራሞቻችንና ፕሮጀክቶቻችንን ለማገዝ የሚያስችል እርዳታ እስከተሰጠን ድረስ እንቀበላለን። ይሄ የራሱን ድርሻና ሚና ይጫወታል። ነገር ግን ዋናው ጉዳይ በዚህ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው በተቻለ መጠን ለልማት የምናወጣቸውን ወጪዎች በሀገራዊ ሀብታችን የምንሸፍንበትን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደግን መሄድ አለብን። ይሄ ማለት በሀገራችን የምንሰበስበው የግብርና ታክስ ገቢ በየጊዜው እያደገ ነው። አሁንም ተጠናክሮ ማደግ አለበት። ይህን ለማድረግ የኢኮኖሚ ነፃነታችንን የበለጠ እናሳድጋለን።

በዚህ 20 ዓመት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ 84 እና 85 አካባቢ መንግሥት ደመወዝ እንኳን መክፈል አይችልም ነበር። ደመወዝ ሳይቀር ከእርዳታ ከሚገኝ የተወሰነ ተለምኖ ይከፍል የነበረ መንግሥት ነው። ዛሬ ላይ ሆነን ስናይ በ20 ዓመት ጉዞአችን 78 በመቶ የሚሆነውን ማንኛውም ወጪያችንን፣ የካፒታል ወጪ ጨምሮ በራሳችን የምንሸፍንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ይሄ ትልቅ እመርታ ነው፤ ግንኙነታችን በእርዳታ ላይ መሆን የለበትም ስንል ይህን ማለታችን ነው፤ አንዳንድ ሀገሮች ያኔ 25 እና 30 ሚሊዮን እርዳታ ሲሰጡን ትልቅ እርዳታ ተደርጎ ነበር የሚታየው። ዛሬ እኛ የደረስንበት ደረጃ ሲታይ ደግሞ የህዳሴ ግድብን የመሰለ ወደ 4ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ግድብ በራሳችን ለመስራት መጀመራችንና እጅግ አብዛኛውንም እያከናወንን መሆናችንን የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የዓለምም ህዝብ በአድናቆት የሚያየው ነው። በዚህ ዙሪያ የኢትዮጵያ ህዝብም ከፍተኛ አሰተዋፅኦ አበርክቷል።

ከዚህም በኋላ 4ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ፕሮጀክት እየቀረፅን መስራት በጀመርንበት በዚህ ጊዜ ግንኙነታችን በኢኮኖሚ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ዙሪያ መሆን አለበት። ይሄ እየሆነ የራሳችንን እቅድ ማሳኪያ ገንዘብ እስከሆነ ድረስ እርዳታውንም እየተቀበልን እንሄዳለን፤ በሂደት ግን ከዚህ ነፃ እየሆንን መሄድ ይገባናል የሚል አቅጣጫ ተይዞ በርካታ ውጤት ተገኝቷል።

ይሄ መልካም ነገር ባለበት ሁኔታ አንዳንድ አክራሪና ፀረ ሰላም ኃይሎች የአገራችንን ሰላም፣ ልማትና እድገት ለማወክ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አለ። የተሳካ እንቅስቃሴ ባይሆንም ሙከራቸው አሁንም አለ። ቅድም እንደገለፅኩት የመከላከያ ኃይላችንና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎቻችን ይህን ነገር በአግባቡ በቁጥጥር ስር የሚያውሉበት ሁኔታ ነው ያለው።

በዋናነት የአክራሪነት ምንጭና መነሻው ሀገራችን አይደለም። አክራሪነት እያየነው እንዳለው ወደ ሽብርተኝነት ተቀይሮ ዓለምን እያናጋ ያለ ጉዳይ ነው። ይህም ሆኖ በሀገራችን በማንኛውም ሁኔታ አክራሪነትንና ፅንፈኝነትን ሊጋብዝ የሚችል ነገር የለም። ህገመንግስቱ ይህን በተገቢው መልሶታል። ከዚህ በፊት ህዝባችን ቅሬታ የሚያቀርብባቸው የሚባሉ ከህገመንግስቱ በፊት የነበሩ የሃይማኖት እኩልነት መታጣት ያለ አንዳች ተፅዕኖ ሃይማኖትን ለማራመድ አለመቻል ችግር አሁን ችግር አይደለም፤ እናም ማንኛውም ሃይማኖት በቡድንም በግልም ለማካሄድ ህገመንግስታዊ መብት በተግባር ተረጋግጧል። ስለዚህ ይሄ መነሻ ሆኖ ለአክራሪነት ወይም ለፅንፈኝነት ሊጋብዝ አይችልም የሚል ፅኑ እምነት አለ።

እንግዲህ ይሄ ካልሆነ ጥያቄው የሃይማኖት ጥያቄ አይደለም ማለት ነው፤ ከሃይማኖት ጥያቄነት አልፎ ወደ ፖለቲካ ጥያቄነት ተቀይሯል ማለት ነው። ስለዚህ የፖለቲካ ጥያቄ ከሆነ ደግሞ የፖለቲካ ምላሽ ያስፈልገዋል። ህብረተሰቡ ደግሞ የፖለቲካ ጥያቄ መሆኑንና ሃይማኖታዊ ጥያቄ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸው ሃይማኖት በግልም በቡድንም ያላቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በዓለም ትልቅ ናቸው የሚባሉ ሃይማኖቶች አሉ። ሰለዚህ የሃይማኖት ብዝሃነት ባለባት ሀገር አንድ ሃይማኖት የበላይነት ሊኖረው አይችልም። የሃይማኖት እኩልነት ህገመንግስቱ ያስቀመጠው አንዱ ጉዳይ ነው። ይህን የሚያናጋ ነገር እንዳይኖር የእምነት ተቋማትና አባቶች መስራት ይኖርባቸዋል። በከፍተኛ ደረጃ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህላችንን እንዲሁም በህገመንግስቱ መግቢያው ላይ ያለንን መልካም ግንኙነት እያጠናከርን እንሄዳለን ብለው ህዝቦች የወሰኑትን ውሳኔ እንደዚሁ የሃይማኖት መቻቻል፣ በጋራ የመኖር ጉዳዮችንም ጨምሮ ማጠናከር ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ለአክራሪነት ምቹ ሁኔታ በሀገራችን ውስጥ የለም። ይህ ማለት ግን አክራሪነትን በሂደት ወደ ሽብርተኝነት ለመቀየር ሙከራዎች የሉም ማለት አይደለም፤ እነዚህ ሙከራዎች በህዝባችን ትግል እንደሚከሽፉ እምነት አለን።

አዲስ ዘመን፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለአገራችንና ለቀጣናው ልዩ ፋይዳ እንዳለው በተለያዩ አካላት ሲገለፅ ይሰማል፤ በእርስዎ እምነት ይህን እንዴት ይገልፁታል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ኢትዮጵያ ሁለት በጣም ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን ሰርታለች። አንደኛው ወራሪ የቅኝ ግዛት ኃይል አንበርክካ የኢትዮጵያ ህዝቦች በሙሉ ኃይማኖትና ብሄር ሳይለያቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከትና መስዋዕትነት በመክፈል ለጥቁር ህዝቦች በሙሉ መኩሪያ የሆኑበት አንድ የታሪክ ምዕራፍ አልፏል። ያ ታሪክ በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻዎቹ አካባቢ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያከናወኑት ታሪክ ነው።

ይህ ታሪክ እስከ ዛሬ በጥቁር ህዝቦችና በአፍሪካውያን እህትና ወንድሞቻችን ዘንድ የነፃነት፣ የመቻልና የአልበገሬ ባይነት እንዲሁም የእኩልነት መንፈስ ፈጥሯል። ለብዙ የነፃነት ታጋዮች መነሻ ሆኖ አገልግሏል። በተመሳሳይ መንገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ታሪክ ነው።

ይህ ሁለተኛ ታሪክ የምልበት ምክንያት እንደተባለው ጥቁር ህዝቦች የሚባሉት በዋናነት ሌሎችንም ታዳጊ ሀገሮች የሚመለከት ቢሆንም የአፍሪካ ሀገሮች ትንሿን ፕሮጀክት እንኳ ለመስራት ከእርዳታና ብድር ውጭ አይቻልም ብለው ሲያስቡት የነበረውን አመለካከት ሰብሮ ብዙዎች ያውም ድሃ፣ ረሃብ ያጠቃትና በጦርነት ስትተራመስ የነበረች አገር ብለው ሲወስዷት የነበረች ሀገር ሁለተኛውን ታሪክ እየሰራች ነው።

ብዙ የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ዙሪያ እንነጋገራለን። እንዲያውም በቅርቡ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት በምንም ተዓምር ይህን ግድብ መጥቼ ማየት አለብኝ፣ ምክንያቱም እኛ ያን የመሰለ ትልቅ የኢንጋ ወንዝ እያለን፣ የኢንጋ ግድብ መስራት አለብን በማለት መግለፅ ከጀመርን 50 ዓመታት ያህል ሆኖታል። አንድም ነገር ሳይሰራ ቆይቷል፤ እናንተ ለእኛም ሞራል ሆናችሁናል፣ ከእናንተ ቀጥሎ እኛም መስራት አለብን ብለው አቋም ይዘው ግድቡን መጎብኘት አለብኝ ብለው በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፣ በቅርቡም መጥተው ያያሉ።

ግድቡ አፍሪካውያንን በይቻላል መንፈስ ምን ያክል እንዳነሳሳ ማየት ይቻላል።የህዳሴ ግድብ የይቻላልን መንፈስ የዘራ ታላቅ ክንዋኔ ነው። ስለዚህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ከማመንጨት በላይ እኛ አፈሪካውያን ከቆረጥንና ከተባበርን፣ ህዝቡ ከተነሳሳ ይቻላል በሚል መንፈስ በሁሉም ዘንድ መስረፅ መቻሉን ያሳያል።

ከሁሉም በላይ ግን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የጋራ የሆነ የህገመንግስታችን ውጤት ሆኖ እና የዚህ 20 ዓመትም ወጤት ሆኖ የተገለፀ ታላቅ ክንዋኔ ነው የሚል እምነት አለኝ። እና እኔ በዚያ አይነት ነው የማየው።

ስለዚህ ሌሎች በርካታ ሀገሮችና ቡድኖች ቢያደንቁት ምንም የሚገርም ነገር አይደለም ማለት ነው። ለእኛ ትልቅ ከድህነት የመውጫ መነሳሻ ነው። ከዚያ አልፎ ግን አሁን ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር እያደረግን ባለንበት ወቅት ደግሞ ኃይል በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ነው። ስለዚህ የኃይል ፍላጎቶቻችንን ይሸፍንልናል። ጎረቤቶቻችንም በዚህ ዙሪያ አብረን እንድናድግ ታላቅ እድል የሚፈጥር ሥራ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡ የህገመንግስቱ 2ዐኛ አመት ሲከበር ሁለት ታላላቅ ፍፃሜዎች ይደረጋሉ፤ የመጀመሪያው ክልላዊና አገራዊ ምርጫ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ የመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተጠናቆ ሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሸን የሚዘጋጅበት ነው። ይህ ከህገመንግስታዊ ሥርአትና ከአገራችን ህዳሴ አንፃር ምን አንድምታ አለው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፡- የህገመንግስታችንን 20ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በተመለከተ በዝርዝር አይተናል፤ ጥቅሞቹና ያገኘናቸው ውጤቶች ምን እንደነበሩም በዝርዝር ገምግመናል። የዚህ20 ዓመታት ክፋይ የሆነው ደግሞ የባለፉት 4 ዓመታት፣ አሁን ደግሞ አንድ ቀሪ ዓመት ያለን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ነው። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችንን በተመለከተም በተደጋጋሚ እንደተገለፀው አገራችን በዚህ ፈጣን የ20 ዓመት የእድገት ጉዞ ውስጥ አንድ ክፋይ ሆኖ ቀጥሏል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በዚህ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወቅት በተለያዩ መስኮች መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ መደላድሎችን የመፍጠር ጉዳይ ነው።

ስለዚህ በግብርና ላይ የተመሰረተው ዋናው የኢኮኖሚያችን ምንጭ ግብርናና ገጠሩ ነው፣ ከዚህ ተነስቶ ግብርናችን ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተቀየረ ነው። አርሶ አደራችን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመቀበል፣ ዘመናዊ የአስተራረስ ሥርዓት ውስጥ በመግባት፣ እንደዚሁም ክህሎቱ በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ ምክንያት የግብርና ትራንስፎርሜሽን በጉልህ መታየት ጀምሯል። ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ የአመራረት ዘይቤ አሁን ለገበያ ማምረት ጀምሯል። አብዛኛው አርሶ አደር ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው አርሶ አደር ትርፍ ስለሚያመርት ወደ ገበያ ያቀርባል። ከፍጆታው አልፏል ማለት ነው፤ ይሄ በጥናት የተረጋገጠ ነው።

ከሁሉ በላይ ደግሞ በዘንድሮ ዓመት በዋና ዋና ሰብሎች የባለፈው ዓመት የዘንድሮን ሳይጨምር 2006 ዓመት ላይ ማለት ነው በዋና ዋና ሰብሎች 250 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል፤ ከዚያ በላይ ደግሞ የስራስር ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የቅመማ ቅመምና ቅባት እህሎች፣ ቡና የመሳሰሉት ሲጨመሩበት ከ300 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማምረት የቻለ አገር ሆኗል። ይሄ በህዝብ ቁጥር በሚከፋፈልበት ጊዜ ሀገሪቱ ራሷን በምግብ እህል መቻሏን ያስረዳል።

ለምሳሌ አሁን በቅርቡ የበቆሎ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መጥቷል፤ እና ወደ 4 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ በቆሎ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ካልተደረገ በስተቀር ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ የሚወድቅ ነው የሚል የባለሙያዎች ጥናት አለ። ስለዚህ ኤክስፖርት ማድረግም ጀምረናል ማለት ነው። ይሄ የሚያሳየው አርሶ አደራችን ለአገር ውስጥም ለዓለም ገበያም ማምረት በመጀመሩ ምክንያት የመጣ ውጤት ነው፤ እናም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ውጤት ነው ብሎ መውሰድ ይገባል።

በተመሳሳይ ኢንዱስትሪው በጣም በፈጣን ሁኔታ እያደገ መጥቷል፤ በዘንድሮው ዓመትም ቢሆን እስከ 22 በመቶ እድገት ያስመዘገበበት ሁኔታ ይታያል። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ውጤቶች የሚያሳዩት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን በ2006 መጨረሻ ላይ የ10 ነጥብ 3 በመቶ እድገት በማስመዝገቡ ፈጣን የእድገት ሁኔታ ውስጥ መኖራችንን ነው። ይሄ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል፤ ቀጣይነት እንዲኖረውም የ2ተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዝግጅት ላይ ነው።

ይሄ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ለምንድንነው የ2ኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የምታዘጋጁት የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፤ ምክንያቱም ምርጫ ከፊት ለፊት አለና ማሸነፋችሁን በምን አውቃችሁ ነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

በምንም መልኩ ይሄ መንግሥት የጀመረውን ሥራ ለማስቀጠል የሚያስችሉ እቅዶችን መቀጠል አለበት። ይሄን ቀጥሎ ደግሞ ህዝባችን በሚሰጠው ውጤት ላይ ተመስርቶ ስራውን የሚሰራ ይሆናል ማለት ነው። ግን ዝግጅት ማድረግ ከወዲሁ መደረግ ያለበት ስለሆነ ከምርጫ በኋላ የሚደረግ ስላይደለ ለመመረጥም ጭምር ምን ይዘህ እንደምትመርጥም ስለሚታወቅ ዝግጅታችንን ማከናወን የግድ ነው የሚሆነው ማለት ነው። ስለዚህ ዝግጅት እያካሄድን ነው ያለነው። ዝግጅቱ ምንድን ነው በ2017 ከዛሬ 10 ዓመት በኋላ መካከለኛ ገቢ ለመድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች የያዙት ራዕይ አለ፤ ይህን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል አንዱ ክፋይ ነው፤ 5 ዓመቱ ደግሞ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ሁለተኛው ክፍል ነው። ስለዚህ ፈጣን እድገት ለማስቀጠል ትራንስፎርሜሽኑን ማረጋገጥ የሚያስችል እቅድ ዝግጅት እያደረግን ያለንበት ሁኔታ አለ። በአጠቃላይ የህገመንግስታችን 20ኛ ዓመት በጣም ታሪካዊ ዓመት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

********

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን፣ ህዳር 28-2007

Curated Content

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago